ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት “ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሾተላይ ናት”

Wednesday, 19 November 2014 11:32

በጥበቡ በለጠ

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የዛሬ 22 ዓመት ከደራሲ መስፍን ዓለማየሁ እና ከደራሲ ደምሴ ፅጌ ጋር ሆኖ ሲያወጋ ነበር። መስፍንና ደምሴ፣ ፀጋዬን ያዋሩታል። ሎሬቱም ይናገራል።

ሲናገርም፡-

“እኔ የታደለ ብዕር አለኝ። ከልጅነቴ ያካበትኳቸው የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህላዊ ብልፅግናዎች ይመስሉኛል፤ የሕዝቡን ፍቅር ያተረፉልኝ። ከዚህም በመውጣቴ የተሟላሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ አምናለሁ። እኮራበታለሁም። የተለያዩ ባሕሎችን ለማጥናት የገፋፉኝም ይኸው ነው። በቅኔዎቼም ይህንን ሁሉ አንፀባርቃለሁ። ከኢትዮጵያም ውጭ እነ ሴንጎርን ከመሳሰሉ ታላላቅ የአፍሪካ የባሕል አባቶች እኩል አፍሪካዊነትን በቅኔ ለማስረፅ መቻሌ ያኮራኛል” ብሏል። (ለዛ፣ መስከረም፣ 1985)

“ምነው ባንድ የግጥም መፅሐፍ ብቻ ተወሰንክ” ብለው ጠየቁት።

ሎሬቱም ሲመልስ፡-

“ግጥሞቼ ተሰብስበዋል። ማሳተሙ ነው የቀረኝ። አሁን በአንዳንድ መፅሄቶች ላይ ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ትናንት ለማሳተም ችግር ነበር። በጭለማ እፅፋቸዋለሁ። ተደብቀው ቆዩ፤ ለኔም እድሜ ሰጡኝ። ቀምበሬን አስቻሉኝ። አሁንም እየፃፍኩ ነው። የእንግሊዝኛውንም የአማርኛውንም ግጥሞቼን በሌላ ቅፅ አሳትማቸዋለሁ። ተውኔቶቼንና የቅድመ ታሪክ ጥናቶቼን ለማሳተም አቅጃለሁ። ቢሆንም አሁን ቀንበር አለብኝ። በአደባባይ በርታ እያሉ በስውር ያጨልሙብኛል። ማሳተሜና ቴአትሮቼን ማሳየቴ ግን አይቀርም”

በ1985 ዓ.ም ግድም ስላለው የኢትዮጵያ የተውኔትና የግጥም ደረጃ ሎሬቱ ሲናገር፡-

“ስነ-ፅሁፍ ደረጃው ወርዷል። የቅኔና የስነ-ፅሁፍ ወራሽ ሕዝብ ነው ያለን። የሱን የጣዕም ደረጃ የሚመጥን ብዕር ግን የለም። አልተሞከረም ማለት አይደለም። የሚሞክሩ፣ የሚጥሩ አሉ። የሚጮሁም ይበዛሉ። እንዲውም አንጋፋ ነን ብለው የሚጮሁም አሉ። አንጋፋ ነን የሚል ጩኸት በዝቷል። ታዲያ አንጋፋነቱ የሚታየው በብዕሩ ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃን ነው። ብዕር ሳይወልድ አንጋፋ ይሆናል። መፃፍ አባባል ሆነ። ‘ልቦለድ!’ ይላል። ልቦለዱን ግን ከአፍሪካ ደራሲያን ጋር እንኳ ብታወዳድረው በጣም ዝቅ ይላል። ቅኔውም እንዲሁ።

“አንዳንድ ደህና የሞከሩ አሉ። ጥቂት ናቸው። ሁለት ወይም ሶስት። እነሱም ቢሆኑ በርቱ የሚሰኙ እንጂ በአፍሪካ ደረጃ እንኳ የሚያኮሩ አይደሉም።

“ኢትዮጵያ የቃል ሐይልና የልሳን ውበት አገር ነች። የህዝቦች ስነ-ቃል፣ የሕዝቦች ተረት የመጠቀበት አገር ነች። ደራሲ ነን፣ ተርጓሚ ነን ባዮች ግን ቁንፅሎቹ ናቸው። ይህም በዝቶ ደግሞ እርስ በርስ መባላት ሆኗል ወጉ። ድሮ በሣንሡር ነበር የሚሣበብ። አሁን በምን ያሳብቧል?”

-    ለዚህ አይነቱ ሁኔታ መፈጠር ምክንያቱ ምን ይሆን? ተብሎም ተጠየቀ።

“ በጃንሆይ ዘመን፣ በደርግ ዘመን የሳንሡር ጭለማ ብዕርን አፍኖ አቆይቷል። ከዚህ ጨለማ ለመላቀቅ ብዙዎች መስዋዕት ሆነዋል። ከነ ዮፍታሔ ንጉሴ ጀምሮ አቤ ጉበኛ፣ በዓሉ ግርማ ወዘተ. . . ተሰውተዋል። ይሔ የወጣቱን ብዕር ትርጉም ጉያ ስር እንዲሸሸግ አድርጎታል። ግማሹ ወጣት ደግሞ የጫት ዛር ካልሰፈረበት ስነ-ልሳን አይወጣውም።

“ቅኔ፣ ቲያትር፣ የቴሌቭዥን ድራማ ይለዋል። የሚታየው ግን አሳዛኝ ነው። በዲሲፕሊን ታንፆ ያልወጣ አእምሮ፣ የቅኔን ክቡርነት፣ የግስን ውበት ተክኖ ያልወጣ አእምሮ እንዴት የዚህን የረቂቅ ሕዝብ ኪናዊ እሴትና ጥማት ሊያረካ ይቻላል?! እንዴት ብሎ የዚህን ባለቅኔ ሕዝብ ሕይወት ይተረጉማል?!

“ዛሬ ያለው ፈሊጥ ባለቅኔ ነህ በለኝ፤ ፀሐፊ- ተውኔት ነኝ በለኝ። በለኝ! በለኝ! የሚል ብቻ ነው። እስቲ አምጣውና ልይልህ ስትለው የሚሰጥህ ትቢያ ነው።

“ያም ሆኖ ግን ከወደ ጀርባ በኩል ጉድ እየፈላ ይመስለኛል። እገሌ የማይባል አዲስ ሰው በየቦታው ብቅ ብቅ እያለ ነው። ደንግጠው ሊገሉት ቢነሱም አሸንፎ መውጣት የማይቀር ነው። በርግጥ ደህና ብቅ የሚለውን በጠጅ፣ በጫት፣ በገንዘብ፣ በወሲብ ሊገሉት ይራወጣሉ። ጎበዝ ሲያዩ መናኛ ይላሉ፤ ብቅ ሲል አይኑን ይሉታል። ሲበዛ ደፋሮች ናቸው። እኔ በነገስኩበት መድረክ ሌላ ብቅ አይበል ይላሉ። አእምሯቸው የባለቅኔ ሳይሆን የአራጅ ነው።

“ያም ሆኖ የሩቅ እይታችን ጭለማ አይደለም። በተስፋ ብርሃን የተሞላ ነው። ብቅ ብቅ ያሉ ተስፋዎች አሉ”

-    የፀጋዬ ንግግር ፋታ ሲያገኝ፣ መስፍን አለማየሁና ደምሴ ፅጌ የሚከተለውን ተረኩ፡-

ንግግሩን ከፈገግታ ጋር አለበው። እውነትም የከርሞው ባለቅኔ ሰውና የከርሞው ብርሃን በደንብ የታየው ይመስል የዚህ ጊዜ ፈገግታው ከበፊቶቹ ለየት ያለ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ፊቱ እንደገና ቅጭም እያለ አእምሮውን ነገር እንደገባው ግልጽ መሆን ጀመረ። ምናልባት ስለዛሬው ዘመን ወጣት ብዕረኞችና በሱ ዘመን ስለነበረው (ራሱን ጨምሮ) የወጣት ደራሲያን ሁኔታ ይሆን የሚያስበው? እኛም ማሰብ ጀመርን። በፀጋዬ የወጣትነት ዘመን ብዙ ወጣት ደራሲያን አልነበሩም። በአመዛኙ ብዕር የሚጨብጡት በእድሜ የገፉት ነበሩ። ፀጋዬ ግን ቀድሞ ነው የጀመረው። ተሳክቶለታልም። አብረውት የተማሩት ሁሉ ቀንቷቸዋል። ለምሳሌ የቴአትር ጥበብ እንዲያጠና ከፈረንሳይ “የኮሜዲ ፍራንሴ” የሙከራ ቴአትር ሌላ በለንደን ከተማ ወደሚገኘው “ኮርት ሮያል ቴአትር” ተልኮ በነበረ ጊዜ አብረውት ሲማሩ ከነበሩት መካከል ናይጄሪያዊው የኖቤል ተሸላሚ ወሌ- ሾየንካ፣ እንግሊዛዊያኑ ተውኔት ደራሲያን ሃሮልድ ፒንተርና ጆን ኦዝ ቦርን ቢጠቀሱ ይበቃል”

-    የፀጋዬ ትምህርት በአለቃ ማዕምር የቅኔ ት/ቤት፣ በአምቦው ማዕረግ ሕይወትና በጄኔራል ዊንጌት 2ኛ ደራጃ ት/ቤቶች ብቻ የተወሰነ አይደለም። በ1949 ዓ.ም ከአ.አ የንግድ ሥራ ት/ቤት (ኮሜርስ) ተመርቋል። ከዚያም ዩናይትድ ስቴትስ ቺካጎ፣ ኢሊኖይ ውስጥ ከሚገኘው “ብላክስቶን ስኩል ኦቭ- ሎው” በሕግ ሙያ በኤል-ኤል- ቢ ዲግሪ ተመርቋል” ብለው ከተረኩለት በኋላ - አሁን ምን እየሰራህ ነው? አሉት። ሎሬትም ተረከ፡-

“አዲስ ተውኔት እያስጠናሁ ነኝ። “ሀሁ ወይም ፐፑ” ይላል ርዕሱ። ሰላም ወይም ጦርነት ማለት ነው። በቅርቡ ለሕዝብ ይቀርባል ብዬ እገምታለሁ። ወቅታዊ ስለሆነ የባሕል ሚኒስቴርን ድጋፍ አላጣም።”

ከተውኔቱ ሁለቱ ገፀ-ባህሪት ሲያወጉ፡-

ነጋ-

እናታችን ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሾተላይ ናት መሰለኝ። ዲሞክራሲን በስድሳ ስድስት ወልዳ በላች። አስቀድሞም በሃምሳ ሶስት አስጨንግፏታል። ብትወልድም ብትገላገለውም ለዘለቄታ አያደርግላትም። የማሕፀን መርገምት አለባት። የዲሞክራሲ ሾተላይ ናት ኢትዮጵያ። በስድሳ ስድስትማ ወዲያው ማግስቱን መፈክር ተፎከረላት። ‘አብዮት ልጆቿን ትበላለች’ ተባለላት ተሸለለላት። የዲሞክራሲ ሾተላይ እናት፣ በላኤ ሰውነቷን መላው የአለም ሕዝብ አስጠንቅሮ አውቀላት።

ቢ- አራጋው፡-

      ዛሬስ? ዛሬስ?

ነጋ፡-

ዛሬማ አዲሱ ዲሞክራሲ ከተወለደ ገና ዘጠኝ ወሩ ነው። የሾተላይ ጥሪቷ ዳግመኛ እንዳጓጓት፣ በሕፃኑ የልደት ቀን ቤተሰቦቿ ካሉበት ተሰባስበው እንትፍትፍ አሰኝተው በመሃላ ቃል ገዝተዋታል። የሕፃኑ እርግብግቢት ገና በአራሱ፣ በሾተላይ አይኖቿ ተወግቶ እንዳይፈርስ፣ ቃለ-ምህላዋ እንዳይረክስ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዳይነግስ፣ ጨቅላ ዲሞክራሲያዊ አራስ ብሌኑ እንዳይፈስ ቤተሰቦቿ በተሰበሰቡበት እለት በምህላ ቃል ገዝተዋል። እናታችን በግዝት ተይዛለች።. . .

-    ፀጋዬ፤ ለመሆኑ ስንት ልጆች አሉህ? ባንተስ መንገድ የወጣ አለ? ብለው ጠየቁት።

“ሞልተው፤ በተለይ የመንፈስ ልጆች ሞልተውኛል። በብዕር፣ በሥዕል፣ በሙዚቃ ዓለም ብዙ አሉኝ። ከአብራኬ የሚወለዱት ግን ሶስት ናቸው። ሁሉም ሴቶች። የመጀመሪያዋ ዮዲት በአንትሮፖሎጂ ጥናትና በሴቶች መብት ማስከበር ጉዳይ ላይ ነው ትኩረቷ። መካከለኛዋ ማህሌት ወደ ኮምዩኒኬሽን ታደላለች። ትንሿ አደይ ህክምና እያጠናች ነው። ሶስቱም አሜሪካ ነው ያሉት።

“ለ30 ዓመታት አብረን ከኖርነው ባለቤቴ ከወ/ሮ ላቀች ቢተው የሚወለዱት ያሳደግሁዋቸው ሶስት ወንዶች ልጆችም አሉን። ትልቁ ከአጠገቤ የማይለይ አጋዤ ነው። ሁለተኛው አዳኝ ሆኗል። ፕሮፌሽናል አውሬ አዳኝ። ሶስተኛው ለአያትነት አብቆቶኛል”

-    እንዴት ነው፣ አንዳንዴ ወደ አምቦ ብቅ ትላለህ? አሉት።

“እንዴታ! አምቦን ካላየሁማ ያመኛል። አምቦ የዋርካዎች ከተማ፣ የቅዱስ ጠበሎች፣ የወንዞች፣ የሀይቆች ሥፍራ። ጠበሉ ደግሞ መድሃኒት’ኮ ነው። በርግጥ አባቴ ቤት ‘ጉቲ ዳኛ’

ድረስ (12ኪ.ሜ ከአምቦ) ሁል ጊዜ አልሒድ እንጂ አምቦ፣ ‘ሀዳ- ጆሌ’ የሾላ ዋርካ ዘንድ ግን ሳልደርስ ሞቴ ነው።”

ውድ አንባቢያን፡- ባለቅኔውና ሎሬቱ ፀጋዬ ከነ መስፍን አለማየሁና ደምሴ ፅጌ ጋር ያደረገው ውይይት ለሰባት ሰዓታት ነበር። ሁሉንም ማቅረብ ባይቻልም የተወሰነውን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለሳምንት ግን የ1950ዎቹ ነበልባል ብዕረኛውን፣ ባለቅኔውን፣ ሞገደኛውን ኃይሉ ገ/ዮሐንስን (ጎመራውን) ይዤላችሁ ቀርባለሁ።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12786 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us