Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 389

ዓለም አቀፍ ተስፋ የተጣለባቸው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰዎች

Wednesday, 13 November 2013 12:49


 

ሳምንት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች MTV በተባለው አለማቀፉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ምርጫ ውስጥ ገብተዋል። ቴሌቪዥን ጣቢያው ባወጣው መግለጫ እነዚህ ስምንቱ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ወደፊት ምስራቅ አፍሪካን የሚያስጠሩ እንደሆኑ ዘግቧል።

ይኸው MTV የተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቪዥን በዓለም ላይ የሚታወቀው፣ ሙዚቀኞችን እና ሙዚቃዎችን ደረጃ በመስጠት እና በማሸለም ነው። አያሌ አለማቀፍ የሙዚቃ ባለሙያዎች ክብርና ዝና የሚያገኙትም MTV ላይ ከቀረቡ በኋላ ነው።

ታዲያ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ አሁን ደግሞ ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ አድርጎ የኢትዮጵያን ሙዚቃ እየመረመረ ነው። የቴሌቪዥን ጣቢያው መግለጫ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ በአፍሪካ ውስጥ ከሶስት ሺ ዓመታት በላይ በነፃነት የኖረችው የጥቁር ምድር ኢትዮጵያ፣ በሙዚቃው ዘርፍ ስሟ እምብዛም እንደማይነገርላት ያስታውሳል።

ኢትዮጵያ ገና በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ማለትም ከዛሬ 1400 ዓመታት በፊት የሙዚቃ ጥበብ መንፈሳዊ ካባ ደርቦ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ብቅ ያለባት ሀገር መሆኗ ቢታወቅም በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ግን የአለም ትኩርት ሳትሆን ቀርታለች ተብሏል።

 

የአፍሪካን የሙዚቃ እንቅስቃሴን በተመለከተ በአለም አቀፍ መድረኮች ብቅ የሚሉት የሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች መሆናቸውን የሚያስታውሰው የ MTV ዘገባ፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት ግን ከምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ከብዙ ስራዎቻቸው ጋር ብቅ የሚሉት ኢትዮጵያዊያን ናቸው በማለት ስማቸው ሁሉ ይዘረዝራል።

ከነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል ሙዚቀኛው አቀናባሪው ሙላቱ አስታጥቄ እና ስራዎቹ ተገልፀዋል። ሙላቱ አስታጥቄ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮ -ጃዝ ባንዱ አያሌ ሙዚቃዎችን ሲያቀነባብር እና ሲፈጥር የነበረ የምስራቅ አፍሪካ ጎምቱ ሙዚቀኛ እንደሆነ ተወስቷል። የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ረገድ ቀዳሚ ሆኖ እንደሚጠቀስም ተገልጿል።በልዩ ልዩ ሀገሮችም የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች በማቅረብ ታዋቂ ሰው እንደሆነ ተፅፏል።

ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር የተገለፀው ሌላው አቀነባባሪ አበጋዝ ሺዎታ ነው። አበጋዝም እንዲሁ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በልዩ ልዩ አለማቀፋዊ ስልቶች በመስራት ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ የሚመደብ እንደሆነ የ MTV ገለፃ ያስረዳል።

በድምፃዊያን ረገድ ከቀረቡት ውስጥ ደግሞ ቴዲ አፍሮም ተጠቅሷል። ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያዊያን የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ በእጅጉ የሚወደድ እና ከአዳዲስ የሙዚቃ ስራዎቹ ጋር በየጊዜው ብቅ እያለ ስመ-ገናና እንደሆነ ተወስቷል። በተለይ ዘገባው ስለ ቴዲ አፍሮ ሲገልፅ አቦጊዳ እና አሁን በመጨረሻ ላይ የለቀቀው ጥቁር ሰው የተሰኘው አልበሞቹን አፅንኦት ሰጥቶ ዘግቦበታል። ጥቁር ሰው የተሰኘው አልበሙ በ1888 ዓ.ም ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በነጮች ላይ ድል ያገኙበት የጦርነት ገድል እና ቅኝ አገዛዝም በጥንታዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ እንደማይሞከር ያሳዩበት እንደሆነ ይታወቃል። ቴዲ አፍሮም በዘፈኑ ይህንኑ ድል እንደዘከረው የ MTV የቲዩተር ዘገባ ያስረዳል።

ሌላው በዚሁ በ MTV ዘገባ ውስጥ ስሙ የተካተተው የኢትዮጵያ ድምፃዊ ጃሉድ ነው። በወጣቱ ዘንድ በሬጌ ስልቱ ተወዳጅ የሆነው ጃሉድ ወደፊት የምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ ሰብዕና የሚላበስ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። ፅሑፉ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ እና ጃማይካዊያን /ራስተፈሪያዊያን/ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። ራስ ተፈሪያዊያን የተስፋይቱ ምድር የሚሏት ኢትዮጵያን ሲሆን ይህንን እምነታቸውን ደግሞ በሬጌ ሙዚቃዎቻቸው ነው የሚገልፁት። አያሌ ራስ ተፈሪያዊያንም ኑሯቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ አድርገዋል። ታዲያ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ከኢትዮጵያ በኩል ጃሉድ የሬጌ ሙዚቃን በአማርኛ ቋንቋ ይዞ ቀረበ። በሬጌ ስልት በመጪው ጊዜ ምስራቅ አፍሪካን ይወክላል በማት MTV ጃሉድ ላይ ተስፋውን ጥሏል።

በቅርቡ በአሜሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመዘዋወር ሙዚቃቸውን ያቀረቡት የጃኖ ባንድ ሙዚቃ አባላትም የ MTV የትኩረት አቅጣጫ ሆነዋል። የሮክ የሙዚቃ ስልትን በመጫወት የሚታወቁት እነዚህ ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እውቅና ተላብሰው የሀገራቸውን ስም በማስጠራት ላይ ይገኛሉ።

ወጣት ሴቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ድምጻዊያንም እንዲሁ የስም ዝርዝራቸው በጋራ ተገልጿል። የእነዚህ ሴቶች ሙዚቀኞች ተሰብስበው ‘የኛ’ በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን ወደፊትም ተስፋ ተጥሎቸዋል። እነሱም አበባ ደሳለኝ፣ ሄለን በርሔ፣ የትግርኛ ቋንቋ ድምፃዊቷ ኤደን ገብረስላሴ እና ቤዛ መኳንንት ስማቸው ተጠቅሷል። የሙዚቃ ስልታቸውም በR&B ዘርፍ ተቀምጧል።

ሌላው ስሙ የተጠቀሰው ወጣት ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ነው። እርሱም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወጣት ውስጥ ተወዳጅ እንደሆነ በድረ-ገፅ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ተወስቷል። “Sela Bey” የሚለው ዘፈኑም ተወዳጅ እንደሆነለት ተፅፏል።

ቤተ-እስራኤላዊት የሆነችው ከኢትዮጵያ የተወለደችው ትንሳኤ ረዳ (Easter Rada) እንደዚሁ ከአፍሪካ ምድር ከወጡ ድምፃዊያን ተርታ MTV አሰልፏታል። በ R&B የሙዚቃ ስልቷ ተወዳጅ የሆነችው ይህችው ኤስተር ኢትዮጵያን በማስጠራት ላይ ትገኛለች።

MC Mike እና ዮኑ ዮይ በወጣቱ ዘንድ እየፈጠሩ ያሉት የሙዚቃ ስልት በ MTV ቴሌቪዥን የትኩረት አቅጣዎች ሆነዋል። ጎንደርኛ የሚለው ዘፈናቸውም ተጠቃሽ ሆኖላቸዋል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ደቦ ባንድ የ MTV ምርጫ ውስጥ በእጅጉ ተጠቅሷል። በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ስልቱ የሚታወቀው ይህ ባንድ ኢትዮጵያዊያንና አሜሪካዊያንን በህብረት ያቀፈ ሲሆን በልዩ ልዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሙዚቃ ያቀርባል። በሳክስፎኒስት ዳኒ መኮንን አማካይነትም ይመራል።

በአጠቃላይ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ማምጫ ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎቹ ይጠቁማሉ።

 

 

 

አርቲስት አብርሃም አስመላሽን

ስናስታውሰው

 

አርቲስት አብርሃም አስመላሽ በኢትዮጵያ የመነባንብ ኪነ-ጥበብ ውስጥ ግንባር ቀደሙን ተግባር ፈፅሞ ያለፈ የኪነ-ጥበብ ባለሟል ነው። አብርሃም መላው ስብዕናውን ለጥበብ ሰጥቶ የኖረ ታሪካዊ ሰው ነው። ጠዋት ሲነሳ የሚያስበው አንድ ጥበባዊ ሥራ ማበርከት ነው። ይፅፋል፣ ያነባል፣ ይተርካል፣ ይተውናል፣ መጨረሻም መነባንብ አድርጐት ያቀርበዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጰያ ሬዲዮ ላይ የገጠርኛ ዘይቤዎችን መሠረት አድርጐ የባላገሩን ጥያቄ፣ ሀሳብ፣ አስተሳሰብ ሲያስተምርበት፣ ሲያሳውቅበት ኖሮ አልፏል። አብርሃም ገንዘብ ለማግኘት ብሎ የሰራው ኪነ-ጥበባዊ ሥራ የለም። እሱ የሚሰራው ልቡ የፈቀደውን፣ መሠራት አለበት የሚለውን ነው። ለዚህም ነው አብርሃምን ገንዘብ ባለበት ቦታ ላይ እምብዛም የማናገኘው።

አብርሃም አስመላሽ ተወልዶ ያደገው ፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ ነው። ነገር ግን የገጠርኛን ዘዬ እና ቅላፄ በራሱ ጥረት በመማር ይህንንም የተማረውን ኪነ-ጥበባዊ ቀለም እየሰጠው በፍፁም ተመስጦ ሲያቀርበው ኖሯል። አብርሃም ሲናገር ይህን ዘዬ ያገኘው ፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ ወደሚገኘው “ዳንሴ ተራራ” ይመጡ ከነበሩ የመንዝ እና የወሎ የገጠር ነዋሪዎች እንደሆነ ይገልፃል። በተለይ ደግሞ በጐችን ለመሸጥ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች ሸጠው ጨርሰው ወደ መኖሪያቸው ቀዬ እስኪመለሱ ድረስ ለቀናት ስለሚቆዩ የአብርሃም አስመላሽ ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ። አብርሃም እነሱን ከስር ስር ሆኖ እየተከታተላቸው የንግግር እና የአስተሳሰብ መንገዳቸውን ኮፒ እያደረገ ወሰደው።

በመጨረሻም አብርሃም የገጠርኛውን ዘይቤ ኮፒ ከማድረግ ወደ እነሱን ሆኖ መኖር፣ መናገር ጀመረ። የገጠሬውን ዘይቤ የራሱ አደረገውና አረፈው። ዘዬው በአብርሃም የለት ተዕለት ህየወት ውስጥ ተፅዕኖው ትልቅ ነበር።

አብርሃም አስመላሽ “እረኛው”፣ “ጠበል ቅመስ” በተሰኙ ስራዎቹ ሰፊ እውቅና ያገኘ ቢሆንም እቤቱ ውስጥ ግን ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቪሲዲ ስራዎች እንዳሉት ሲናገር ቆይቷል። እነዚህ ስራዎች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሳይታተሙ ቆይተው እሱም እስከወዲያኛው አሸለበ።

የአብርሃም ሕመም የዲስክ መንሸራተት ሲሆን፤ በዚህ ህመም ለአንድ ዓመት ያህል ተሰቃይቷል። ከዚያም በቅርብ ወዳጆች አስተባባሪነት ወደ ጀርመን ሀገር ኑረበርግ ከተማ ሄዶ ሲታከም ቆይቶ ጤንነቱም መለስ ብሎለት ነበር። ነገር ግን ለሞት ያደርሰዋል ተብሎ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ኑረበርግ ከተማ የዚህ የመነባንብ ጀግና ሕልፈተ ሕይወት ሆነ። ከዚያም አስክሬኑ ወደ ሀገሩ መጥቶ ወዳጆቹ፣ የጥበብ አፍቃሪዎቹ በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ተፈፅሟል። አብርሃም አስመላሽ ኑሮውን ያደረገው እጅግ በጣም ከሚወዳቸው መነኩሴ እናቱ ጋር ነበር። በተለይ ለእናቱ ሐዘኑ በእጅጉ መራራ እንደሆነም ይነገራል።

       የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአርቲስት አብርሃም አስመላሽ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ይመኛል።

Last modified on Wednesday, 13 November 2013 16:16
ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
12814 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us