ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/

Wednesday, 26 November 2014 12:59

በጥበቡ በለጠ   

 

ኢትዮጵያ በ1950ዎች ውስጥ ካፈራቻቸው ብርቅዬ ልጆቿ መካከል አንዱ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ ነው። ገሞራው በሐገሪቱ የሥነ-ፅሁፍ ዓለም ውስጥ ሥመ ገናና የሆነ ብዕረኛ ነበር። ከብዕሩ ጫፍ የሚወጣው ነበልባል ነው፤ እሳት ነው፤ መብረቅ ነው። አንዴ የሚፅፈው ነገር አገር ያተራምሳል፤ ያነጋግራል። ገና ከተማሪነት ዘመኑ ጀምሮ መንግሥታት በአይነቁራኛ እየጠበቁት መከራቸውን የሚያዩበት የብዕር ጦረኛ ነበር። እርሱም ቢሆን በብዕሩ ጦስ መከራውን ሲያይ የኖረ- ከሀገሩ ኢትዮጵያ ወጥቶም ለአርባ ዓመታት በስደት ሲንከራተት የኖረ ነው። ገሞራው ከረጅም የስደት ሕይወት በኋላ ሰሞኑን በሚኖርበት ሲውዲን ስቶኮልም ከተማ ውስጥ አርፏል። ባለቅኔው ኢትዮጵያዊ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

አርባ ዓመታት በስደት የተንከራተተው ይህ ብርቅዬ ባለቅኔያችን ሀገሩ ኢትዮጵያን እጅግ የሚወድ ሰው ነበር። በሕይወት እያለ ወደ ሀገሩ መጥቶ መግባት ባይችልም፣ ሲሞት ግን መቀበሪያው ይህችን ከአይነ ህሊናው የማትጠፋው ኢትዮጵያ እንደሆነች ግጥም ፅፏል። መቀበሪያዬ ኢትዮጵያ ናት እያለ። እስኪ የዛሬ ዓመት ከፃፈው ከዚሁ ግጥሙ የሚከተለውን አንብቡለት።

ባያውቁት ነው እንጂ - የእኔን ቋሚ ንግርት፣

በተወለድኩበት ነው - የምቀበርበት፣

ሌላ ቦታ ሳይሆን - በትውልዴ መሬት።

      አስቀድሞም ቢሆን - እትብቴ ተቀብሯል፣

      ቀሪውም አካሌ - በርግጥ በክብር ያርፋል።

ሲንከራተት ኖሮ - አካሌ የትም ምድር፣

በስተመጨረሻ - የሚያርፍበት አፈር፣

ከተወለድኩበት ነው - በክብር የሚቀበር።

      በመቃብሬም ላይ - በስተ ግርጌ በኩል፣

      “እኔም እንደርስዎ - ሕያው ነበርኩ!” የሚል፣

      በትልቅ ቋጥኝ ላይ ተቀርፆ ይፃፋል።

ይሔ ሁሉ ንግርት - ከወዲሁ ታውቋል፣

ከዚያ ርስት ለመንቀስ - ታዲያ እንዴት ይቻላል?!

(ኃይሉ ገ/ዮሐንስ - በግጥም ልተንፍስ ጥር 20/2006 ዓ.ም)

ይህ ባለቅኔ አገሬ ቅበሩኝ እያለ ነው። ኃይሉ በአፀደ ሥጋ ከተለየን ከአስር ቀናት በላይ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ አልተቀበረም። ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ይህን ከላይ የሰፈረውን ግጥሙን ተግባራዊ ለማድረግ አስከሬኑን ወደ ትውልድ ቀዬው ለማምጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። የገሞራው ስርዓተ ቀብርም በአይኑ እንደተንከራተተች በኖረችው በሐገሩ ኢትዮጵያ ይፈፀማልተብሎ ይጠበቃል።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ወጣት በብዙ መልኩ ራቅ ያለ ቢመስልም በየጊዜው የመወያያ አጀንዳ በሚፈጥረው “በረከተ መርገም” በተሰኘው ረጅም ግጥሙ የትውልድ ሰንሰለት እየተቀባበለ ገና አያሌ ትውልዶች ዘንድ ይደርሳል።

የኢ.ሕ.አ.ፓን ታሪክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ “ያ ትውልድ” በሚል ርዕስ ሶስት ተከታታይ መፃህፍትን ያሳተመላቸው ክፍሉ ታደሰ፣ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) በኢትዮጵያ ውስጥ በስነ -ግጥም ትሩፋታቸው አብዮት ካቀጣጠሉ ወጣቶች መካከል ከፊት ያሰልፈዋል። እንደ ክፍሉ ገለፃ፣ በ1959 ዓ.ም ገሞራው “በረከት መርገም” የተሰኘውን ግጥሙን ካቀረበ በኋላ ትውልድ ነቃ፣ ማሰብ ጀመረ፣ ራሱን መጠየቅ፣ ማህበረሰብን መጠየቅ፣ ሀገርን መጠየቅ፣ መንግሥትን መጠየቅ፣ ተፈጥሮን፣ ታሪክን. . . መጠየቅ መጠየቅ. . . ጀመረ። ኃይሉ የለውጥ ክብሪት የጫረ ባለቅኔ እንደነበር ክፍሉ መስክሮለታል።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ስሙ ሲጠራ አብራ ብቅ የምትለው ግጥሙ “በረከተ መርገም” ትሁን እንጂ ሰውየው እጅግ በርካታ ግጥሞችን እና የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ያበረከተ ታታሪ ፀሐፊ ነው። እርግጥ ነው ለበረከተ መርገም የ21 ገፅ ግጥሙ የሀገርን እና የትውልድን አስተሳሰብ ቀያይሮ አብዮት የዘወረ ገጣሚ ነው። በግጥሙ ውስጥ እንደሚያሳየው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትልልቅ ግኝቶችን ያገኙ ሰዎች ይረገማሉ፣ ፈላስፋዎች ይረገማሉ። ፀሐፊዎች ይረገማሉ፣ ተፈጥሮ ሁሉ ሳትቀር ትረገማለች። ታዲያ የኃይሉ እርግማን የሚያሳየው ለሰው ልጅ ያለውን ክብር ነው። የዚህ ሁሉ ሳይንቲስትና ፈላስፋ ስራ ለሰው ልጅ ጉዳት ከሆነ መፈጠርህ መኖርህ እንጦሮጦስ ይውረድ እያለ ይራገማል።

‘በረከተ መርገም’ በሀገራችን የሥነ-ግጥም ታሪክ ውስጥ ረጅም ግጥሞች ከሚባሉት ተርታ ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው። ግጥሙ 21 ገፆች ያሉት ሲሆን፣ ርዕሰ ጉዳዩ የዘመን ኬላን እያሳበረ በመሔድ በሰው ልጆች ዓለም ውስጥ ሁሌም የሚጠቀስ ሆኗል።

በዚህ የርግማን ናዳ ውስጥ ደራሲያን ሁሉ ይረገማሉ።

“ከጥንት ጀምሮ ስናየው የኖርነው፣

ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው።

      ያላንዳች ተውህቦ ያለምንም ጥናት

            ፅሁፍን በማቅረብ፣

      የግልን ቂም ይዞ ለንዋይ አለም በዲቃላ ቋንቋ

            ወሬን ለመተብተብ፣

ጋዜጣ መፅሔት በሚለው ባልትና መርዝን ለመመገብ፣

ማንም ብዕር ጨባጭ እየቦጫጨረ ሀገር ለማሳደብ፣

ደራሲ ነኝ ያልከው ክሽኑ እንቶኔ ድርሰትን ለመፃፍ

            አርአያ ስለሆንህ፣

ያቧሬው ቃልቻ ንፁህ ደም ያስተፋህ!

እንዲህ አይነት ከአፎታቸው ኃይለ ቃል የሚተፉት ግጥሞቹ ኃይሉን ሞገደኛ እንዲባል አድርገውታል። ጠቢባን የተባሉ የአለምሊቃውንቶች እያነሳሳ ይረግማል። እርግማኑ ለሰው ልጅ የተሻለ አለም ካላመጣችሁ ይሔ ይገባችኋል የሚል ነው።

ለምሳሌ ታዋቂዎቹን ፈላስፎችና ሳይንቲስቶችን እንዲህ ይላቸዋል፡-

“ችግርና ደዌ ከቶም ድንቁርና በምድር ሲፈነድቅ፣

የሚሰራው ሞልቶ ስንቱ ተግባር ሳያልቅ፣

የምድሩ ሳይሞላ አዳሜ ሳይረካ የጠፈሩን ማወቅ፣

ሮኬት ሲፒትኒክ ሳተላይት ጋጋሪን እያለ በከንቱ

                           ዝናን ለማዳነቅ፣

ጀማሪያቸው ሆነህ ይህን በማድረግህ የደደቦቹ ሊቅ፣

ጋኔሉ ጋሊሎ፣ በሞው ሥጋህ ላይ ይብረቅበት መብረቅ!”

ያታላይ የዋሾው የሌባው የከጂው የአጉራ ዘለሉ

            የክፉው የጩቁ የቀረውም ቶፋ፣

ጤናው ተጠብቆ ሕይወቱም እረዝሞ አልባሌ ስራው

            እጅግ እንዲስፋፋ፣

አስቦ እንደሆን ያ ንፍጣም ሳይንቲስት ያዋቂ ከርፋፋ፣

ኤክስሬይ የሠራው ዊልያም ወልካፋ፣

በሕይወት እንዳለ ድምጥማጡ ይጥፋ።

የኃይሌ እርግማን በዝቷል፤ ጩኸቱ ፈሩን ለቋል እያሉ በወቅቱ የፃፉበትም ሰዎች አሉ። ብቻ በረከተ መርገም በሀገራችን የስነ-ግጥም ታሪክ ክፍሉ ታደሰ እንዳለው “በትንታግነቷ” ትታወቃለች።

ገሞራው በሠራቸው የሥነ-ግጥም ሥራዎቹ በልዩ ልዩ ጊዜያት ታስሯል፣ ጉሸማና ቡቅሻም ደርሶበታል። የሥነ-ፅሁፍ ሥራዎቹ በመንግሥት ተወርሰውበታል። ይህ ሁሉ ግን ገሞራውን ከመፃፍ አላገደውም።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። 1928 ዓ.ም በልጅነቱ ግዕዝን እና የቤተ-ክህነት ትምህርትን ጠንቅቆ የተማረ እና አእምሮ ክፍት፣ በአንዳንዶች አባባል “የቀለም ቀንድ” ነበር። በዚህም የተነሳ የግዕዝ ቋንቋ የሚቀኝበት፣ የሚፅፍበት የሚናገርበትም አድርጎት ነበር።

ኃይሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (በቀድሞ አጠራሩ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ) ገብቶ ሥነ-ፅሁፍን ተምሯል።

በ1950ዎቹ ውስጥ ብቅ ካሉት የለውጥ አቀንቃኝ ብዕረኞች መካከል ከፊት ተሰላፊ ሆኖ እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ትኩስ ታሪክ የሚነገርለት ስመ ገናና ባለቅኔ ለመሆን የበቃ ነው።

ኃይሉ በ1967 ዓ.ም ወደ ቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርስቲ ለከፍተኛ ትምህርት ተልኮ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይመለስ አርባ ዓመታትን በውጭ ሀገራት ሲኖር ቆይቶ በመጨረሻም በ79 ዓመቱ በህመም ምክንያት በሚኖርበት ሲውዲን ስቶኮልም ውስጥ አርፏል።

ኃይሉ እጅግ በርካታ የግጥም ሥራዎች እንዲሁም የጥናትና የምርምር ውጤቶችንም ያዘጋጀ የድርሰት ገበሬ ነበር። በ1966 ዓ.ም በረከተ መርገም በሚል ርዕስ የግጥም መድብሉን አሳተመ። ከዚያም በ1967 ዓ.ም ፍንዳታ! በሚል ርዕስ ሌላ አነጋጋሪ የግጥም መፅሐፍ አሳትሟል። ኃይሉ በነዚህ መፅሀፎች ውስጥ የደረሰበትን መከራ ከነእሮሮው ጋር አድርጎ ፅፎባቸዋል። ከዚያም በኋላ ወደ ውጭ ሀገር ከሔደ ጀምሮ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ፅሁፎችን አበርክቶልን አልፏል።

በኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ ግጥም ከተለከፉ ሰዎች መካከል ዋነኛው፣ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን የወግ ጸሐፊው መስፍን ኃብተማርያም ይጠቀሳል። መስፍን በረከተ መርገምን በቃሉ ያነበንብ ነበር። ገሞራው ራሱ ስለ መስፍን ኃ/ማርያም የሚከተለውን ፅፏል።

“ብዙዎች ጓዶቼ እንደሚያውቁት ሁሉ መስፍን በረከተ -መርገምን እንደ ውዳሴ ማርያም በቃሉ ይዞ በየደረሰበት የሚያነበንባትና አሁንም እንኳ ከካናዳ የከፍተኛ ትምህርቱ ጉዞ በኋላም አንዲቷን ስንኝ ሳይረሳ የሚያነበንብላት መሆኑ ነው። አይግረማችሁና መምህር መስፍን በረከተ መርገምን ከሥጋውና ከደሙ ጋር ያዋሃደው ከመሆኑ የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ የሚጠራው ወላጆቹ በሰጡት ስሙ ሳይሆን፤ “The Walking BM - ተጓዡ በረከተ መርገም” በመባል ነው።”

መስፍን ኃብተማርያም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የባለ 21 ገጿን በረከተ- መርገም ግጥም እንደ ውዳሴ ማርያም እንዳነበነባት ከ45 ዓመታት በላይ አብሯት ኖሯል። ለመሆኑ መስፍን ኃብተማርያም ስለዚህችው ግጥም ምን አለ? ምንስ ፅፎ ነበር? ሳምንት እመለስበታለሁ። እስከዛው ግን ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ መረጃዎችን በመስጠት በማዋስ ከጎኔ የቆሙትን ሰዓሊ ቱሉ ጉያን እና የመርካቶ አደሬ ሰፈሩን ታሪክ አዋቂውን ኬይድ አህመድን በአንባቢዎቼ ስም አመሰግናቸዋለሁ። 

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
12488 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us