ገሞራውን ቀበርነው

Wednesday, 03 December 2014 13:02

በጥበቡ በለጠ

 

 

 

ዛሬ ይህን ከላይ ያሰፈርኩትን ርዕስ የተጠቀምኩት እንደው ስለዚህ ተአምረኛ ሰው የተሰማኝን ጥልቅ ስሜት ይገልፅልኛል ብዬ በማሰብ ነው። ጽሁፉ ከባለፈው ሳምንት መጣጥፍ ቀጣይም ነው።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ታላቅ ባለቅኔ ነው። ይህ ሰው አሳቢ /thinker/ ነው። አስቦም የሚያሳስብ ነው። ጠይቆም እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው። ያመነበትን ሃሳብም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ አብሮት የሚቆርብ ነው። የስደትን፣ የግዞትን መስቀል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና ብልፅግና ሲል ተሸክሞ የኖረ በመጨረሻም ሕይወቱን የሰጠ ነው። አርባ ዓመታት ሙሉ ሀገሩ ኢትዮጵያ በዓይኑ እንደተንከራተተች ከናፍቆቷና ከትዝታዋ ተቆራኝቶ ስለእሷ እየፃፈና እያወጋ የስደት ዘመኑን በሞት አጠናቀቀው። የገሞራው ይህ ሁሉ ስቃይና መከራ የሚደርስበት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልዕልና ብዕሩን ስላነሳ፣ አንደበቱን ስላሰላ ነው። እዚህጋ ቆም ብለንም የምንጠይቀው አንድ ጉዳይ አለ። ለሀገር ሲባል መሞት፣ ለሕዝብ ሲባል መሞት ዋጋው ስንት ነው? ምን ያህልስ ይከፈልበታል? እንደ ገሞራው ያለ ሰው፣ ለራሱ ሳይኖር፣ ለራሱ ሳያስብ፣ ለራሱ ሳይደላው፣ ከራሱ በፊት ስለ ሀገሩና ሕዝቡ የሚጮህ፣ በመጨረሻም ሕይወቱን ቤዛ አድርጐ የሚያልፍ ሰው ዋጋው ስንት ይሆን? ለመሆኑስ እንዲህ አይነቱን ሰው ቀብረነው ዝም ነው?

እንዲህ አይነቱማ መድሃኒት ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው መንፈሱም ሆነ የአጥንቱ ርግፍጋፊ መልካም ዘር ማፍሪያ ነው። ሰው የሚሆኑ ሰዎችን መፍጠሪያ መንፈሳዊ ዘር ነው። ከዚህ የመንፈስ ዘር ጋር ዛሬ ቆይታ እናደርጋለን።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሕዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም አስከሬኑ በስደት ከሚኖርበት ሀገር ሲውዲን /ስቶኮልም/ ወደ እሚወዳትና የእትብቱ መቀበሪያ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መጥቶ ተወልዶ ባደገበት በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስትያን በስድስት ሰዓት ስርዓተ-ቀብሩ ተፈፀመ።

 
   


ሲንከራተት ኖሮ - አካሌ የትም ምድር፣

በስተመጨረሻ - የሚያርፍበት አፈር፣

ከተወለድኩበት ነው - በክብር የሚቀበር።

 
   


ኃይሉ 40 ዓመታትን በልዩ ልዩ ሀገሮች በስደት ተንከራቶ፣ ተንከራቶ በመጨረሻም በእናት ሀገሩ ምድር በምኞቱ መሠረት ተቀበረ። ቀበርነው!

ኃይሉ ማን ነው?

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ በ1928 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ አጥቢያ አሁን E.C.A. ባረፈበት ስፍራ ከአበ-ብዙሐን መምህር ገብረዮሐንስ ተሰማ እና ከእመ-ብዙሐት ወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተወልድ መወለዱን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል። እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ግራ ጌታ ይትባረክ ሹምዬ ዘንድ ፊደልን፣ ንባብን እና ጽዋተ ዜማን ተምሯል። ኋላም የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሽልማት ድርጅት ቀዳሚ ተሸላሚ ከነበሩት ታዋቂውና ታላቁ የቅኔ መምህር ከየኔታ ጥበቡ ጋሜ ዘንድ ቅኔን ከነ አገባቡ አደላድሏል። በዲቁናም ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስትያን ቀድሷል ይላል በቀብሩ ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪኩ።

የገሞራው አባት ልጃቸው በቤተ-ክርስትያን ትምህርት እንዲገፋበት ብዙ ድጋፍ አድርገውለታል። ወደ ሥነ-ኃይማኖት (ቲዮሎጂ) ት/ቤት ገብቶ ተምሯል። ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሀገሩን ኃይማኖት፣ ባሕል፣ ታሪክ ጠንቅቆ የተማረና የገባው ሰው ነበር። ከዚያም ዘመናዊ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት መከታተል ያዘ። የሚገርመው ደግሞ ዘመናዊ ትምህርቱንም እየተማረ ስርዓተ ቀብሩ በተፈፀመበት በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስትያን በዲያቆንነት ያገለግል ነበር። እነዚህ የእውቀትና የሥራ ገበታዎች ኃይሉን በግዕዝ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ዕውቀት በሁለት በኩል የተሳለ ቢላዋ አድርገው ፈጠሩት። ገና በልጅነቱ ከነበረበት የትውልድና የሀገር አስተሳሰብ አዕምሮው በእጅጉ ተራምዶ አዲስ ዓለም ናፋቂ አደረገው። ያ ዓለም ደግሞ ሰው ሁሉ እኩል የሚሆንበት፣ አንዱ ሌላውን የማይረግጥበት፣ ሰው የተባለ ፍጡር መብቱም፣ ነፃነቱም፣ ብልፅግናውም ሊከበሩበት እንደሚገባ ገሞራው ማቀንቀን ጀመረ።

በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ “ዋንነስ” የምትል አንዲት አነስተኛ ጽሁፍ በእንግሊዝኛ ፅፎ ለእንግዶቹ እንዲከፋፈል ማድረጉን ወዳጆቹ ይገልጻሉ። የአፍሪካ መሪዎች ወደፊት በአንክሮ ሊያስቡበት የሚገባውን ርዕሰ ጉዳይ የመከረበት ፅሁፍ ነው። ታዲያ በዚያን ጊዜ የፀጥታ ኃይሎች ወዲያው ገሞራውን ካለበት ቦታ ይዘውት ወደ እስር ቤት ላኩት።

ከእስር ከወጣ በኋላ ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲም በመግባት በስነ-ልሳን እና በቋንቋ ጥናት መማር ጀመረ። በወቅቱ ደግሞ እርሱ ከትምህርት ጉብዝናው በላይ አብዮት ቀስቃሽ እና ሞጋች፣ ብሎም ትውልድን ሁሉ የሚወዘውዝ ብዕረኛ ሆኖ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ ነበልባል ባለቅኔ ሆኖ መጣ።

በ1959 ዓ.ም በረከተ መርገም የተሰኘ የባለ 21 ገጽ ግጥም ጽፎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ተማሪዎችና መምሕራን ፊት አነበበ። ታዳሚውን በሙሉ አስጮኸ፣ አነቃነቀ። ያ በረከተ መርገም አንደኛ ተብሎ ተሸለመ፣ ተደነቀ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ ገሞራውን ከዩኒቨርሲቲው እንዲባረር አደረገው። አስጐሸመው፣ አሳሰረው። ግን ደግሞ ግጥሙ ሞጋች እና አብዮተኛ ትውልድ የሚፈለፍል አንዳች ልዩ ኃይል ያለው ሆኖ መጣ። የሚያስቆመው ጠፋ። የኢሕአፓን ታሪክ፣ ያ ትውልድ በሚል ርዕስ በሦስት ተከታታይ ትልልቅ ቅጾች መፃሕፍትን ያሳተመው የገሞራው የመንፈስ ወዳጅ የሆነው ክፍሉ ታደሰ፣ በረከተ-መርገም ትውልድን ሁሉ ለለውጥ ያነሳሳ የጥበብ ሥራ መሆኑን ያስታውሳል። እንደ ክፍሉ ታደሰ ገለፃ፤ “ኃይሉና በረከተ መርገም” በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ ዘላለማዊ አሻራ አኑረው ያለፉ መሆናቸውን ጽፎላቸዋል።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት እና ልዕልና ራሱን በድፍረት ከፊት አጋፍጦ ካለምንም ፍርሃት የሚሟገት ስለነበር አያሌ መከራዎችን ሲቀበል ኖሯል። ከዚያም በ1967 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምርት ወደ ቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርስቲ ተጓዘ። እዚያም ለሶስት ዓመታት በትምህርት ሲቆይ በቻይንኛ ቋንቋ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ፅሁፎችን ማዘጋትና ማሰራጨት ጀመረ። የሃሳብ አፈና በተንሠራፋበት ቻይና የገሞራው ብዕር ፍርሃት ለቀቀባቸው። በተለይ ለዶክትሬት ድግሪ ማሟያ የሚያዘጋጀው ፅሁፍ ርዕሱ The Influence of Anarchism on Chinese Literature: with a particular focus put on the case `Ba-Jin` የሚል ስለነበር፣ ገሞራው ቻይናም ሔዶ የደህንነቶች የትኩረት ቀለበት ውስጥ ወደቀ። በመጨረሻም የገሞራው ብዕር ለቻይና መንግሥት አሜኬላ (እሾህ) ነው ተብሎ፣ ሀገራቱንም ሳይበጠብጥ በአጭሩ እንቅጨው ብለው ኃይሉን ከሀገራቸው አባረሩት።

ገሞራው ወደ ሐገሩ እንዳይመለስ ደግሞ፣ እርሱ ወደ ቻይና በሔደበት ወቅት የደርግ የፀጥታ ሐይሎች የእነ ኃይሉ ቤትን ከበው ቤቱ ላይ ከፍተኛ ፍተሻ አድርገው ነበር። ፍተሻቸው ደግሞ ኃይሉን ለመያዝ ነበር። በአጋጣሚ ደግሞ እርሱ ወደ ቻይና ተጉዞ ነበር። ደርጎች ከሚገሏቸው የኢሕአፓ አባላት መካከል የገሞራው ስም ዋነኛው ነበር። ስለዚህ ወደ ሐገሩ ኢትዮጵያ የመመለሱ ነገር የማይቻል ሆነ። ባለቅኔው ሀገር አልባ ሆነ።

ወደ አሜሪካ ለመጓዝም ፈፅሞ አዳጋች ሆነ። ምክንያቱም ድሮ ገሞራው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ አሜሪካዊያኖች ሀገሩ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ይቀሰቅስ ስለነበር የዩናይትድ ስቴትስ የኢምግሬሽን ሰዎች ኃይሉ ገ/ዮሐንስ በጥቁር መዝገባቸው (Black List) ውስጥ ስለፃፉት ወደ አሜሪካ ከማይገቡ ሰዎች መካከል አንዱ እሱ ሆነ። ገሞራው መሰደጃ አጣ።

ቀጥሎም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በዩ.ኤን.ሲ. ኤች. አር ትብብር ወደ ኖርዌይ ሀገር እንዲሔድ መደረጉን የኃይሉ ጓደኞች ይገልፃሉ። በኖርዌይ ውስጥም ሆኖ የሚፅፋቸው ርዕሰ ጉዳዮች ለሀገሪቱ መንግሥት ስላልተስማሙት ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ተገደደ። የብዕሩ ሃይለ-ቃል እና የእምነቱ ጥንካሬ እንደ ጦስ ያዞረው ገባ። በመጨረሻም እስከ እለተ ሞቱ በቆየባት ስዊድን ሀገር ተሰደደ። እዚያም የመከራን ሸክም በጀርባው አዝሎ በብዕሩ ቀስት ግን ከዘጠኝ ሺ በላይ አርቲክሎችን ፅፎ ያለፈ የስደት ባሕታዊ፣ የእምነት ባሕታዊ፣ የመንፈስ ባሕታዊ፣ የብዕር ባሕታዊ ሆኖ ላመነበት ጉዳይ እስከ መጨረሻው ድረስ በፅናት ቆይቶ ለትውልድም አርአያ ሆኖ ያለፈ የዘመኑ ልዕለ ሰብ ሆኖልናል።

ኃይሉ ገ/ዮሐንስ 40 ዓመታት በስደት ሲኖር አንድም ቀን ዜግነቱን ለመቀየር ተደራድሮም ሆነ ፈልጎ አያውቅም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተወልዶ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አለፈ። ስጋው እንኳ እንዳይደላው በመፈለግ ዜግነቱን አልቀየረም። ኃይሉ ትዳር አልመሰረተም። በአንዲት ክፍል ውስጥ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሲፅፍ ኖሮ ያለፈ የብዕር ‘ገሞራ’ነው። በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር ጥበብ አምላኪ ባለቅኔ ነበር። ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለደ በ79 ዓመቱ ሲውዲን ስቶኮልም ውስጥ በህመም ምክንያት ሕይወቱ ብታልፍም ከ40 ዓመታት የአካል ስደት በኋላ ከትናንት በስቲያ አስከሬኑ ለሀገሩ አፈር በቃ።

የገሞራውን አስክሬን ከስዊድን ወደ አዲስ አበባ ያመጣችው ኗሪነቷ በአሜሪካ ሀገር የሆነው የኃይሉ የወንድም ልጅ የሆነችው ወ/ሮ ቆንጂት በትረ ነች። የወንድም ልጅ፣ የእህት ልጅ ባይወልዱትም ልጅ ነው የሚሰኘው አባባል እውነት መሆኑን ያየሁት በወ/ሮ ቆንጂት በትረ አማካይነት ነው። የገሞራውን፡-

ባያቁት ነው እንጂ - የእኔን ቋሚ ንግርት፣

በተወለድኩበት ነው - የምቀበርበት፣

ሌላ ቦታ ሳይሆን - በትውልዴ መሬት።

ብሎ የፃፈውን ንግርት ቆንጂት እውን አደረገችለት። ለካ የገሞራው ንግርት እርሷ ላይ አድሮ ነበር እውን የሚሆነው። “እውነተኛ ባለቅኔ ነብይ ነው” የሚባለው ምሳሌ ማረጋገጫው ገሞራው ሆኖ አረፈው።

    በአጠቃላይ የዚህ ጎምቱ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ የመጨረሻ እረፍት በሚወዳት እናት ሐገሩ፣ ከቤተሰቦቹ የቀብር ቦታ ላይ እንዲያርፍ ለወ/ሮ ቆንጂት፣ ደጀን ሆነው የለፉት አቶ ጥላዬ ይትባረክ፣ አቶ ኃይለማርያም ደንቡ፣ በሲውዲን የሚገኙ የአባ በየነ ሰይፉ ቤተሰቦች፣ የኃይሉ አጎት ኢ/ር ሽመልስ፣ በሲውዲን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፣ ወ/ት ኤሚ እንግዳ፣ ልጅ እንግዳ ገ/ክርስቶስ፣ የአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ክፍል አባላት፣ በሲውዲን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የገሞራው ጓደኞችና ወዳጆች ሁሉ፣ የባለቅኔውን ምኞት እውን ስላደረጋችሁ በሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም ላመሰግናችሁ እውዳለሁ። በኔ በኩል የገሞራውን ጉዳይ ሳምንትም እቀጥልበታለሁ። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
16588 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us