የገሞራው በሀገሩ መቀበር ለምን ያስቆጣል?

Wednesday, 10 December 2014 13:32

በድንበሩ ስዩም

    ድግሪማ ነበረን

ድግሪማ ነበረን በአይነት በብዛት፣

ከቶ አልተቻለም እንጂ ቁንጫን ማጥፋት

ድግሪማ ነበረን ከእያንዳንዱ ምሁር

አልተቻለም እንጂ ቅማልን ከሀገር።

ድግሪ ተሸክሞ መስራት ካልተቻለ

አሕያስ በአቅሟ ወርቅ ትጫን የለ!!

      ድግሪማ ነበረን - ለወሬ የሚበጅ

      ሞያሌን ከሐገር -አልነቀለም እንጀ።

ድግሪማ ነበረን - በሊቃውንት ተርታ

አልረዳንም እንጂ - ሊሸኝ ድንቁርና።

      አይሸኙበትም እንጂ -  ድግሪማ ነበረን

      አልመከተም እንጂ - ድህነት ሲያጉላላን።

ጥሮ ተጣትሮ ድግሪማ ማግኘት

ለመሆን አልነበር - ለሰው መድሃኒት።

                        ገሞራው /ኃይሉ ገ/ዮሐንስ/

 

ይህን ከላይ የሰፈረውን ግጥም የገሞራው ነው ብላ የሰጠችኝ ኤሚ እንግዳ ነች። ግጥሙ ፊደልን የቆጠረውን ሁሉ የሚያሳስብ ብሎም የሚያስቆጭ ነው። ገሞራው እጅግ አያሌ የሥነ - ግጥም ስራዎቹን ሲፅፍ የኖረ ባለቅኔ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ከሰሞኑ በወጡ መረጃዎች ወደ ዘጠኝ ሺ ግጥሞችን፣ አርቲክሎችን፣ ማስታወሻዎችን የቋንቋና የባሕል ጥናቶችን እንደፃፈ ተነግሮለታል። የሕይወት ዘመኑን በሙሉ ሲፅፍ የኖረ ‘ስደተኛው ሊቅ’ ነበር።

ስለዚሁ የሥነ-ፅሁፍ ምሁር ስርዓተ -ቀብር አስመልክተው የሚፅፉ የተለያዩ ድረ-ገፆችን ለማንበብ ሞክሬ ነበር። አንዳንድ ፀሐፊያን ገሞራው ለምን በሐገሩ ኢትዮጵያ ተቀበረ ብለው ሲወቅሱ ይደመጣሉ። ገሞራው በስደት እንደኖረ በሰደት ይቀበር ይላሉ። ይሔ አስተሳሰባቸው የመነጨው ደግሞ ገሞራው በነበረው የፖለቲካ አቋም ምክንያት ነው። ይህ ሰው በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ተፃራሪ ስለሆነ በኢትዮጵያ መቀበር የለበትም ባይ ናቸው። ግን ይህ አቋማቸው ትክክል ነው ወይ? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አሁን በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር የማይስማማ ነበር። አያሌ የተቃውሞ ግጥሞችን ፅፏል። ግን ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ሕይወቱ ስታልፍ አስክሬኑ ወደ ሐገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ ነው የተቀበረው። ፀጋዬ ከመንግሥት በተፃራሪ ስለቆመ ቀብሩም በውጭ ሀገር ይፈፀም ማለት ይቻላል ወይ?

በዘመነ ደርግ ሰዓሊውና ገጣሚው ገብረክርስቶስ ደስታ ከሀገሩ ተሰዶ ወጣ። በኬንያ አድርጎ፣ ወደ ጀርመን ተጉዞ እዚያም የተወሰነ ጊዜ ቆይቶ፣ በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጓዘ። አሜሪካ ኦክላሆማ ውስጥ በ1974 ዓ.ም ህይወቱ አለፈች። በነበረው የፖለቲካ አቋም በሚል እዚያው ኦክላሆማ ውስጥ ተቀበረ። እስከ ዛሬ ድረስ የዚህ ሰው አፅም ወደ ሀገሩ የሚያመጣው ወዳጅም ሆነ ጓደኛ ብሎም ቤተሰብ የለም። ከሀገሩ እንደወጣ የቀረ ታላቅ የኪነ-ጥበብ ፈርጥ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ከፊታቸው የነበረውን ስሜት ተከትለው ገብረክርስቶስን ኦክላሆማ እንዲቀበር አደረጉት። ዘመን አለፈ። ገብረክርስቶስም እንደወጣ ቀረ።

እኔ በበኩሌ የገሞራው አስክሬን ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ መቀበሩ ትልቅ ደስታ ሰጥቶኛል።  ምክንያቱ ደግሞ ይህ ሰው እንደ ገብረክርስቶስ ደስታ ሆኖ እንዲያልፍ አልፈልግም። የገሞራው አስክሬን ለሀገሩ አፈር እንዲበቃ ያደረጉት አካላትም መወቀስ የለባቸውም። አንዳንድ ፀሐፊያን እነዚህን አካላት ሲወቅሷቸው ስላነበብኩ ነው። የሰዎቹ ጥፋትም አልገባኝም። መልካም ተግባር ፈፅመዋልና ነው።

ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ በጣም ደስ የሚለኝ ‘ይህም ያልፋል. . .’ እያለ የሚፅፋቸው ነገሮች ናቸው። በምድር ላይ የማያልፍ የለም። ፖለቲካውም፣ አስተሳሰባችንም፣ ጦርነቱም፣ ችግሩም፣ ስርዓቶችም ሁሉም ነገሮች ያልፋሉ። ግን ይህች የተወለድንባት፣ እትብታችን የተቀበረባት ሐገራችን የምንላት ኢትዮጵያ ድሮም ነበረች ገናም ትኖራለች። ስለዚህ የገሞራው አስከሬን በኢትዮጵያ ማረፉ በዘላለማዊቷ ሀገሩ ውስጥ እንጂ ነገ በምትፈራርሰው፣ በምትጠፋው ምድር አይደለም። ገሞራው ያረፈው ከወላጆቹ፣ ከዘመዶቹ ጎን ነው። ይህ እንዴትስ ሊያበሳጨን፣ ይችላል? እስኪ ሰከን ብለን እናስበው! 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
11708 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us