በረከተ መርገም

Wednesday, 10 December 2014 13:36

በጥበቡ በለጠ

     

በዚህ ርዕስ የተፃፈችው የኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ ግጥም በኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት የግጥም ሥራዎች በሙሉ ከፊት የምትሰለፍ ናት። ይህች ግጥም ከ1959 ዓ.ም በኋላ የመጣውን ትውልድ በመቀስቀስ እና በማንቃት ሁሌም ትጠቀሳለች። አብዮተኛ ትውልድ ፈልስፋላለች የሚሉም አሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፀሐፊዋን ኃይሉ ገ/ዮሐንስን ለመከራ የዳረገች ነች። ከርሱ በተፃራሪ የቆሙ ወገኖች ሁሉ ኃይሉን የሚያጠቁበት፣ የሚያሳድዱበት ግጥሙ ሆነች። የመከራን፣ የስቃይን፣ የእስራትን፣ የስደትን መስቀል የተሸከመባት ግጥሙ ነች።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የወግ ፀሐፊው መስፍን ኃብተማርያም፣ በ“በረከተ መርገም” ግጥም በከፍተኛ ደረጃ ከተመሰጡ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ባለ 21 ገፅ የበረከተ መርገምን ግም ከ40 ዓመታት በላይ በቃሉ ይዞ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በቃሉ ያነበንብ ነበር። እንደውም “ተጓዡ በረከተ መርገም” The walking B.M ይባል ነበር። ይህ ሰው በዚህች በበረከተ መርገም የግጥም መድብል ውስጥ አስተያየቱን በ1966 ዓ.ም ፅፎ ነበር። እንዲህ ይላል፡-

“ስለ በረከተ መርገም ያለኝን አስተያየት ከመጀመሬ በፊት ለብዙ ዓመታት ሳደንቀው የኖርኩትን ወደፊትም የማደንቀውን ግጥም በገጣሚና በአንባቢ አይን ተመልክቼ ለመተንተን ይህን ዕድል በማግኘቴ ደራሲውን ለማመስገን እወዳለሁ። በ1959 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ በተደረገው የግጥም ውድድር በረከተ መርገም አንደኛ ሆኖ ተመርጦ ነበር።

“በዚያን ጊዜ ደራሲው ሲያነብ ይሰማ የነበረውን የጋራ ጭብጨባ በተለይም አንብቦ ሲጨርስ ውጤቱን ለመስማት ሳይጓጓ “በቃኝ” ብሎ አንገቱን አቀርቅሮ አዳራሹን ባጣበቡት ሰዎች መካከል እየተሹለከለከ ሲወጣ በአዳራሹ የነበረውን አድናቆት የተመላበት ትዕይንት አስታውሳለሁ። በረከተ መርገም በልቤ መስረፅ የጀመረው ያን ጊዜ ነበር። እስከ አሁንም ባነበብኩት ቁጥር ትዝታ ይቀሰቅስብኛል። ጥሩ ግጥምነቱ ካዘላቸው ጠቃሚ ሃሳቦች ጋር እየተጣመረ በረከተ መርገምን አንድ ግዜ በሙሉ በቃል አጥንቼው የነበረው። ለዚህ ይመስለኛል እስከ አሁንም ልረሳው ያልቻልኩት” መስፍን ኃብተማርያም።

የመስፍን ኃብተማርያም አስተያየት ሰፊ ነው። የበረከት መርገምን ግጥም ከልዩ ልዩ ማዕዘናት እየተነተነ የሚሔድ ነው። የገጣሚውንም ፍዳ ያሳያል።

በረከተ መርገም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን መንግሥት ቢፃፍም በእርሳቸውም ዘመን ሆነ ቀጥሎ በመጣው በደርግ ዘመን ተፈላጊ አልነበረም። ምክንያቱም የሰው ልጅ ታላቅነት፣ የተከበረና ሰብዓዊነቱ የተጠበቀ ዜጋ እንዲሆን እሱን የሚጨቁኑትን ሁሉ የሚራገም ግጥም ነው። ስለዚህ ለሰው ቁብ የሌላቸው ስርዓቶች ሁሉ የዚህ ግጥም ተፃራሪዎች ናቸው።

መከራውን አይቶ ከዚህች ዓለም በሞት የተለየው ኃይሉ ገ/ዮሐንስ /ገሞራው/ ከዛሬ 12 ዓመታት በፊት ለኢትዮጵ መፅሔት ቃለመጠይቅ ሰጥቶ ነበር። በዚህ ቃሉ እንዲህ ብሎም ነበር፡-

“ከሀገሬ ከወጣሁ ጀምሮ ለሩብ ምዕተ-ዓመታት እዚህና እዚያ ስንከራተት የኖኩትን ፀሊም ሕይወት በማስመልከት የፃፍኳት “ሞቼም እኖራለሁ” የምትል ትንግርተኛ ግጥም አለችኝ። ግጥሚቱን የፃፍኳት እዚህ ያለሁበት ሀገር ውስጥ፣ ሀገሬንና ወገኔን ለመታደግ የምፅፋቸውን ምግታራዊያን ፅሁፎች መነሻ በማድረግ፣ ባልፈፀምኩት አንዳች ወንጀል፣ ከታላቁ የፍትህ አደባባይ ላይ የፊጢኝ አስረው አቅርበው ‘እብድ ነህ’ የሚል መንግሥታዊ ውሳኔ በተሰጠበት ማግስት ነው። እነሱ በሀገሬ የውስጥ ጉዳይ ባይገቡ ኖሮ ባልተቸነፉ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕይወቴ ቀልቤን እንዳጣ ይገኛል። ሁኔታዎችን ከኔ አንፃር ሳያቸው ‘ደግ አድርገዋል ይበለኝ!’ የምልበት ጊዜ አለ። ወትሮስ ቢሆን እንደኔ ያለ ሰው የመጣው ቢመጣ ከሀገሩ መውጣት አልነበረበትም። ይሔ ኋላ መጥ አስተያየቴ፣ ፍዳዬን እና መከራዬን በጥሞና ሳስታውሰው ነው። ግን እኮ ከገዛ ሀገሬም ውስጥ የነበረኝ እድል ስስ ነበርኮ። እስቲ አንዱን ለምሣሌ ይሆነኝ ዘንድ ልጥቀስ።

“እኔን በቅርብ የሚያውቁኝ ወገኖች ሁሉ እንደሚያስታውሱት በንጉስ ነገስት የዘውድ ግዛት ዘመን፣ ነፍሴ ለጥቂት ዳነች እንጂ (በሆነ ልዩ ተአምር) እንደተንፈራጋጭ እምቦሳ ጥጃ በየወሩ ስታሰር እንደእንቦሳም ስቀጠቀጥ ነበር ለምለሙን የወጣትነት ዘመን ያሳለፍኩት። ከምፅፈው የግል ታሪካዊ ሁኔታ ውስጥ፣ አንድ ታሪከኛ ትንግርት ይኸውላችሁ።

“. . . አንድ ሳምንት ያህል ፔኪንግ እንደቆየሁ፣ ትቼው ከሔድኩት ሀገር አንድ ትንግርተኛ ደብዳቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ደረሰኝ “. . . እግዜር በክንፈ ምህረቱ ከልሎ እንደሚጠብቅህም፣ ዘንድሮ በገቢር አረጋገጥኩ፤ ይኸውም . . .” በሚል መነሻ ርዕስ አለው። ይህንን ያስባለው ምን ነገር ቢገኝ ነው ብዬ ደብዳቤውን በጥሞና ማንበብ ጀመርኩ። እንዲህ ይላል፡- “ አንተ ሀገሩን ለቀህ በሔድክ ማግስት፣ ሁለት ባለቋሚ ተጠሪ ጂፖችና ቁጥራቸው ከአስር በላይ የሆኑ ክላሺንኮቭ ያነገቡ ታጣቂ ወታደሮች፣ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ከቤታችን መጥተው በመውረር ‘ኃይሉን ለመውሰድ ከባለሥልጣን ታዘን ነው የመጣነው፣ እዚህ ከሌለ ያለበትን ንገሩን፣ ኃይሉን ካልወለዳችሁ. . .’ እያሉ፣ ቀኑን ሙሉ ከግቢያችን የገባ እንዳይወጣ፣ የወጣውም እንዳይገባ አግረው፣ አግረው፣ ሲያስቸግሩን ውለው፣ ማምሻው ላይ ተመለሱ” የሚል የትንቅንቅ ሪፖርታዥ ነው. . .

“. . . በዚያን ዕለት አረጋዊ አባቴን እየጨቀጨቁ ‘ልጅዎን ይውለዱ’ ቢሏቸው ‘ትናንት ሔዶ፤ በምድርና በየብስ ሳይሆን፣ በሰማይ ላይ ደመና ሰነጣጥቆ፣ እንደ ቅዱሳኖች እንደነ እዝራና እንደነ ኤልያስ!. . . እናንተው አይደላችሁም እንዴ የፈቀዳችሁለት? እዚህ ያለነው እኛ ነን፤ እኛን እንደብጤታችሁ ማድረግ ትችላላችሁ፤ ሌላም መሔጃ የለንም፤ እሱ ግን ሲሰቃይ ኖሮ ዘንድሮ አዶናይ ረድቶት እጁን አውጥቷል፤ አዶኒስ ይቀደስ!. . .” እያሉ ሲያበግኗቸው ዋሉ አሉ ወታደሮቹን። ድርጊታዊ ትንግርቱ አንድ ቀን ሙሉ ሲያስቀኝ ዋለ። አዎ እያንዳንዱ ሰው በዕለተ ልደቱ ቁጥር መጠን፣ ትንንሽ ሞት አሉበት ይባላል። እኔም በ16ቱ የልደት ቀኔ መጠን፣ የዚያን ቀኑ ትንሽ ሞቴ 7ኛው መሆኑን አስባለሁ። እዚያ ቻይና እያለሁም በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከምኖርበት 4ኛ ፎቅ ስዘል፣ 8ኛ ሞቴ መሆኑን ተረድቻለሁ። እዚሁ ስዊዲን ደግሞ፣ ያለ ወንጀሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤታችው አቅርበው “እብድ ነው” ብለው ሲፈርዱብኝ 9ኛው ትንሹ ሞቴን መሆኑን ቆጥሬያለሁ። የሚቀሩኝን ትንንሽ ሞቴን እናንተው ልታሰሏቸው ትችላላችሁ።

የባለቅኔው የኃይሉ ገ/ዮሐንስ ሕይወትና ሥራ አስደናቂ ነው። አሳዛኝም ነው። 40 ዓመታት በስደት ርቆን ቆይቶ ሞቱ ደግሞ ከፋብን። 

ይምረጡ
(12 ሰዎች መርጠዋል)
17284 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us