ደማቸው የትም ፈሶ ያለፉት የኢትዮጵያ ዶክተሮች

Wednesday, 17 December 2014 11:42

በጥበቡ በለጠ

     

                  ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ      ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ          ዶ/ር ሠናይ ልኬ

 

ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ መጨረሻ እና በ1970ዎቹ መግቢያ ላይ ልጆቿ ተጣልተው፣ ተቧጭቀው፣ ተገዳድለው አንድ ትውልድ እምሽክ ብሎ አልቋል። በዚያ ትውልድ ውስጥ የነበሩ እናቶች አባቶች እህትና ወንድሞች አንብተዋል። ከዚያ በኋላም የትውልድ ክፍተት ታይቷል። ከመሀል የወጣና ያለቀ ትውልድ በመኖሩ ማሕበራዊ ልልነት፣ ቆራጥነት፣ በራስ የመተማመን፣ ላለሙት ነገር በጽናት ያለመቆም የመሣሠሉት ነገሮች መከሰታቸውን ልዩ ልዩ ፀሐፊያን ገልጸዋል።

በያ ትውልድ ውስጥም ቢሆን የቆራጥነት የአይበገሬነት መንፈስ ቢኖርም በዚያው መጠንም ቢሆን አድርባዩ እና ህሊና የለሹም የፈላበት ወቅት ነበር። በሐገራችን የኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ በደንብ ያልዳሰስነው፣ ፊልም ያልሠራንለት፣ ያልዘፈንለት፣ ቴአትር ያልጻፍንለት. . . ዘመን ቢኖር የያ ትውልድን ነው።

በሶስት ተከታታይና ግዙፍ መፅሐፎች ያ ትውልድ እያለ፣ በሚገባ የዘከረው ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ን ከመሠረቱት ጥቂት ምሁራን መካከል አንዱ ነው። የኢሕአፓ አመራሮች አብዛኛዎቹ አልቀው ለወሬ ነጋሪ የቀረው ይሔው ክፍሉ ታደሰ ነው። ዛሬም ቢሆን ስለነዚያ ጓደኞቹ፣ ህልም አልመው ስለጨነገፈባቸው ወጣቶች ታሪካቸውን ይዘክራል። እነዚህ መፅሐፍቶች ደግሞ የሕትመት ብርሃን አግኝተው አሁን በገበያ ላይ ይገኛሉ። እንደው የሱን መጽሐፍት መሠረት አድርጌ የሦስት ምርጥ የኢትዮጵያ ዶክተሮችን ሞት ላውራ። ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ያለፉት እነዚህ ዶክተሮች ሁሌም ያሳዝኑኛል። በፖለቲካ አቋማቸው የተጨራረሱ ያለቁ ታላላቅ ሠዎች ስለሆኑ ዛሬ እነሱን በጥቂቱ ላስታውስና ስለ ያ ትውልድ አስገራሚ ታሪኮች ወደፊት እቀጥልበታለሁ።

ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ

ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ብሎ የፃፈውን ታሪክ ማስታወሻነቱን ለዶ/ር ተስፋዬ ደባሣይ ነው የሠጠው። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነው። አንደኛው የትግል አጋሩ ስለነበርና የቅርብ ምስጢረኞችና ወዳጆች ስለነበሩ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ተስፋዬ ደበሣይ የኢሕአፓ ቆራጥ መሪ በመሆኑና ሕይወቱንም አሳልፎ በመስጠቱ ምክንያት ዘላለማዊ ዝክር ሰጥቶታል። ክፍሉ ሲገልፅ፡-

“ተስፋዬ ደበሣይ፣ ታጋይ የኢሕአፓ ግንባር ቀደም መሪ፣ አርቆ አሳቢና ትሁት ቢሆንም፣ ይህን (ያ ትውልድ)ን መፅሐፍ ለእሱ መዘከሩ በፖለቲካ ትግሉ ካበረከተው ድርሻ በመነሳት አይደለም። በቀይ ሽብር ሊመተሩ ተደግሶላቸው የነበሩ ቁጥራቸው በርካታ የወቅቱ ታጋዮችን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ እሱ ራሱ በመውደቁ ነው። መጋቢት 14 ቀን 1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ አሠሣ ሊደረግ እንደታቀደ ኢሕአፓ ተረዳ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ታጋዮች ከአዲስ አበባ መውጣት እንዳለባቸው ታመነበት። ከጊዜ አንጻር፣ ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት በኢሕአፓ ድርጅታዊ መዋቅር አማካይነት ማካሔድ እንደማይቻል ደግሞ ግልጽ ሆነ። ተስፋዬ፣ ማንንም ሳያማክር ኃላፊነቱን ለራሱ ሰጠ። አሰሳው ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው፣ ቀኑን ሙሉ አዲስ አበባ አውቶቡስ ጣቢያ በመዋል ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ታጋዮችን በመገናኘት፣ የሚሸሸጉበትን የሸዋ ከተማ ስምና እዚያም ሲደርሱ ከአካባቢው የኢሕአፓ መዋቅር አባላት ጋር የሚገናኙበትን ምስጢራዊ ቃል ሲሰጥ ዋለ። እሱ ግን፣ በርካታ የድርጅት አባላትን በመከራ ጊዜ ትቶ መሔድ አልሆንልህ አለው። አዲስ አበባ ቀረ። የመከራ ፅዋውንም እዚያ ከቀሩት ጋር አብሮ ሊጎነጭ ወሰነ። በዚያን ጊዜ ተስፋዬ ወደ ሸዋ የገጠር ከተሞች ከሸኛቸው ከብዙዎች ታጋዮች መሀል በርከት ያሉት አሁንም በህይወት አሉ። ተስፋዬ ደበሣይ ግን. . . ተስፋዬ የቀይ ሽብር ሰለባ ብቻ አይደለም። ከቀይ ሽብር መዓት ሌሎችን ለማዳን ራሱን አሳልፎ የሰጠ ታላቅ መሪ ነው” ይለዋል ክፍሉ ታደሰ።

ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ ከአባቱ ከአቶ ደበሣይ ካህሳይ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ምሕረታ ዳዶ- ዑማር በ1933 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ በምትገኘው አሊቴና በመባል የምትጠራው የገጠር ከተማ ተወለደ። ተስፋዬ ደበሣይ ትምህርቱን በአዲግራት እና በመቀሌ ከተሞች ከተማረ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኢጣሊያ ኡርባኒአና ዩኒቨርስቲ ተልኮ በፍልስፍና የዶክተሬት ድግሪውን ተቀብሎ የመጣ ፈላስፋ ነበር።

ከትምህርቱ በኋላ በማስታወቂያ ሚኒስቴርና በተለያዩ ቦታዎች ሲሰራ የቆየው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ጊዜውን ለኢሕአፓ አመራርነት ሰጥቶ በመጨረሻም በቀይ ሽብር ዘመቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ከፎቅ ላይ ተከስክሶ ሕይወቱ አልፋለች። የተከሰከሰበት ህንፃ አምባሳደር ፊልም ቤት ፊት ለፊት ካለው ኪዳኔ በየነ ከሚባለው ህንፃ ላይ ነው። እጅ ከመስጠት ተከስክሶ መሞትን የመረጠ የፍልስፍና ሊቅ ነበር።

ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ

ይህ ሰው መኢሶን /የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ/ ፓርቲ መሪ ነበር። በርካቶች እንደሚመሰክሩለት የሊቆች ሊቅ ነው ይሉታል። በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ከተነሱ የለውጥ አቀንቃኞች መካከል አንዱ እሱ ነበር።

የገነት አየለ የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥ አምባገነኑ የቀድሞው ወታደራዊ መሪ የዶ/ር ኃይሌ ፊዳን ሞት እንኳን በቅጡ እንደማያውቁ ይናገራሉ። ሞተ እንዴ? ማን ገደለው እያሉ እንደ አዲስ አስገዳዩ ራሳቸው ጠያቂ ሆነው ቀርበዋል። ደሙ ደመ ከልብ የሆነ ምሁር ነው ኃይሌ ፊዳ!

ታስሮ እና ማቆ ከዚያም የተረሸነ ኢትዮጵያዊ! የተገደለው ሐምሌ 1971 ዓ.ም ነው። አፈሩን ገለባ ያድርግለት። ወደፊት ስለዚሁ የፖለቲካ መሪ እና ምሁር ግለ-ታሪክ አጫውታችኋለሁ።

ዶ/ር ሠናይ ልኬ

በደርግ ውስጥ ይሰራ የነበረ ወጣት ምሁር ነበር ሠናይ ልኬ። በተለይ ደግሞ የሕዝብ ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ይሰራ ነበር።

ደርግ እንደሚገልፀው ዶ/ር ሠናይ ልኬ በ1969 ዓ.ም የተገደለው በፀረ ሕዝብ ሴረኞች በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ከቆሰለ በኋላ በሆስፒታል ውስጥ ነው። ዕድሜው ደግሞ 33 ነበር።

ዶ/ር ሠናይ ልኬ የተወለደው በወለጋ ክፍለ ሐገር በዮብዶ ከተማ ውስጥ በ1936 ዓ.ም ነበር። የልጅነት ጊዜውን በጎሬ ከተማ ነው ያሳለፈው። በ1934 ዓ.ም ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ጎሬ ከተማ በሚገኘው በጎሬ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ገብቶ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ት/ቤት ቆይቶ አስረኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርት አጠናቀቀ። ከዚያም በ1954 ዓ.ም ደብረዘይት በሚገኘው የስዊድን ኤቫንጀሊካል ገብቶ 11ኛን እና 12ኛን ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ጨረሰ።

ከዚያም ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገብቶ የመጀመሪያውን ዓመት በከፍተኛ ማዕረግ አለፈ። ቀጥሎም የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ ሔደ። እዚያም ላፋዩት ከሚባል ኮሌጅ ለሶስት ዓመታት ተምሮ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ በድግሪ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ።

ከዚያም በ1958 ዓ.ም የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በበርክሊ ከፍተኛ ትምህርቱን እንዲቀጥል ስኮላርሺፕ ሰጥቶት በ1964 ዓ.ም በ28 ዓመቱ የዶክትሬት ድግሪውን አግኝቷል። ከዚያም ወደ ሀገሩ መጥቶ የፖለቲካ አቀንቃኝነቱን ቀጠለበት።

ደርግ ውስጥ ከገቡት የፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ነው የሚባለው ዶ/ር ሰናይ ልኬ በጥይት ተመትቶ ነው የሞተው። በወቅቱ ፀረ-አብዮተኛ ይባል የነበረው ደግሞ ኢሕአፓ ነበር። እውን ዶ/ር ሠናይን የገደለው ማን ነው? ገና ያልተነገረ፣ ይፋ ያልሆነ ወሬ ነው። እነዚህ ዶክተሮች ትንታግ የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ። ሁሉም ብቅ አሉ፤ ተማሩ፣ ፍክትክት ብለው ወጡ።ሀገርና ወገን ብዙ ሲጠብቅባቸው ጭልምልም ብለው ጠፉ!

    በሚቀጥለው ተከታታይ ፅሁፎቼም የዚያን ትውልድ አሳዛኝም አስገራሚም ታሪክ በተቻለኝ መጠን ላጫውታችሁ እሞክራለሁ። ለዚህ ፅሁፌ የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ የተሰኘው መፅሐፍ ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገልኝ በዚህ አጋጣሚም እገልጻለሁ። ቸር እንሰንብት

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
13388 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us