ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ በታሪክ ውስጥ

Wednesday, 31 December 2014 12:42

በጥበቡ በለጠ


በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በ1960ዎቹ መጨረሻ እና በ1970 መጀመሪያ አካባቢ አንድ ትውልድ ተቋርጧል ወይም አልቋል። በተለይ ደግሞ ተምሯል፣ አውቋል ነቅቷል ተብሎ የሚታሰበው ሃይል ነው የሞት ሐበላ እላዩ ላይ የወረደበት። ታዲያ ያንን ዘመን፣ ያንን የሞትና የስቃይ ወቅት ከፊት ሆነው የመሩት ዛሬ በስደት የሚገኙት የቀድሞው የሐገሪቱ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ የኢሕአፓ /የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ አባላት ተሰልፈዋል። የዚህ የሞት ዘመንን ማጥፊያ ማቆሚያ ደግሞ ራሳቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሊገደሉ ነው ተብሎ በኢሕአፓዎች ታመነ። እናም ኢሕአፓዎቹ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል ዝግጅት ጀመሩ።

የ1960ዎቹን እና 70 ዎቹን ታሪክ የሚዘክሩ ልዩ ልዩ መፃሕፍት እንደሚያወጉት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን የመግደል ሙከራ የማድረጉን ሚና የወሰዱት ኢሕአፓዎች መሆናቸውን ነው እንጂ ዝግጅታቸው፣ ሃሳባቸው ግን ምን እንደነበር መፃሕፍቶች እምብዛም አይናገሩም። ኮሎኔሉ ራሳቸው ኢሕአፓዎች የመግደል ሙከራ አድርገውባቸው ባላቸው ችሎታ የመትረፋቸውን ብቃት ከመግለፃቸው ውጭ ዝርዝር ታሪኩን እምብዛም አያውቁትም።

ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም በጣም ከሚጠሉት እና በጥብቅ ከሚፈልጓቸው የኢሕአፓ አመራሮች ውስጥ ዋነኛው ክፍሉ ታደሰ ነው። የከተማውን የኢሕአፓ ትግል እየመራ እርሳቸውንም ከምድረ-ገፅ የማስወገዱን ሚና ከበላይ ሆኖ የሚያስፈፅመው እሱ መሆኑን አምነዋል። እርግጥ ነው ክፍሉና ጓደኞቹ ደግሞ ይሔ ሁሉ የከተማ ግድያ የሚፈፀመው በመንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ምክንያት ስለሆነ የእርሳቸው መወገድ ሠላም ያመጣል፣ ግድያውንም ያቀዘቅዘዋል ብለው አመኑ። እናም አይበገሬውን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል ቆርጠው ተነሱ።

የኢሕአፓን የከተማ ትግል እንደመራው የሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ፣ በፃፋቸው ሶስት ተከታታይ ግዙፍ መፅሐፍቶቹ ውስጥ እነዚህን ጉዳዮችና ሌሎችንም የዘመኑን ምስጢራት ለታሪክ አስቀምጧቸዋል። ያ ትውልድ በሚሰኙት በነዚህ ሰሞኑን በድጋሚ ለንባብ በበቁት መፃህፍቶች ውስጥ በተለይ በቅፅ ሁለት እትሙ የኮ/ል መንግሥቱን የግድያ ሙከራ አስምልክቶ ፅፏል። የታሪኩ ተሳታፊ ስለነበር የወሬውን ትክከለኛ ምንጭነት እንዳንጠራጠር የሚያደርገን ፅሁፍ ነው። እንዲህ ይላል፡-

“ሌላው በዚህ ወቅት ከተወሰዱት እርምጃዎች መሀል ደግሞ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል የተደረገው ሙከራን ይመለከታል። የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሞት ቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈው በሶስት የደርግ አባላት ላይ ብቻ ነበር። እነሱም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ በጂማ ከተማ ጭፍፋ የፈፀሙት ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ እና ኮ/ል ተካ ቱሉ ነበሩ። ከሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት አባላት መካከል ደግሞ የማጥፋት ጦርነቱን አዋጅ በረቀቁና በአዘጋጁ ላይ ብቻ ውሳኔው ተላልፏል።”

ከነሐሴ 1968 ዓ.ም ጀምሮ የኢሕአፓ ታጣቂ ክንፍ የኮሎኔል መንግሥቱን እንቅስቃሴ መከታተል ይዟል። በዚያን ወቅት ኮሎኔሉ መኖሪያቸውን አራተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ አድርገው ጽ/ቤታቸው በታላቁ ቤተ-መንግሥት ነበር። ኮ/ል መንግሥቱ፣ መኖሪያቸውንም ሆነ ጽ/ቤታቸውን በታላቁ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ስለታወቀ፣ ይህንን እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት እሳቸውን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እቅዱ ተነደፈ። ኮሎኔል መንግሥቱ ከአራተኛ ክፍለ ጦር ወደ ታላቁ ቤተ-መንግሥት ሲሔዱ ወይም ከዚያ ሲመለሱ ተመሳሳይ መንገድና መስመር ፈፅሞ አይጠቀሙም። ታጣቂ ክንፍ የኮሎኔል መንግቱን መኪና በአራተኛ ክፍለ ጦር ደጃፍ ላይ ወይም ደርግ ጽ/ቤት፣ ማለትም ታላቁ ቤተ-መንግሥት መግቢያ ላይ አድፍጦ ሊያጠቃ አሰበ። ይሁንና፣ ይህ እቅድ በአንዳንድ የደህንነት ችግሮች ምክንያት ውድቅ ሆነ።

የኮሎኔል መንግሥቱ ከደርግ ጽ/ቤት ወደ መኖርያቸውም ሆነ ከቤታቸው ወደ ደርግ ጽ/ቤት የሚሔዱበት ቋሚነት የሌለው የእንቅስቃሴ የጊዜ ሰሌዳን አስቀድሞ ለመገመት የሚያስቸግር፣ ንቅናቄያቸው የማይፈታ ቋጠሮ ሆነ። አንዳንድ ግዜ፣ከሚጠበቀው ጊዜ በአንድ ሰዓት ያህል ይዘገዩና ለአጥማጆቻቸው የደህንነት እንቅፋት ይፈጥራሉ። ከስድስት ወይም ከሰባት ጊዜ ተከታታይ ሙከራዎች በኋላ ኮሎኔል መንግሥቱን አድፍጦ የማጥመድ ስልት ተቀየረና በምትኩ “ተንቀሳቃሽ ኢላማን መከተል” የተሰኘ የጥቃት ስልት ተነደፈ። በአዲሱ ዘዴ መሠረት፣ አጥቂ አሃዶቹ የኮሎኔል መንግቱን መኪና መከተል የሚጀምሩት ከአራተኛ ክፍለ ጦር ወይም ከደርግ ጽ/ቤት ተነስታ መሸመቂያ ሥፍራ እስክትደርስ ይሆናል። የተዘጋጀው ስፍራ ላይ ሲደርሱ የኮ/ል መንግሥቱን መኪና የሚከተሉት መኪኖችም ሆኑ ሸምቀው የሚጠባበቁት ኃይሎች ተኩስ ይከፍታሉ።

ይህን እርምጃ ለማሳካት እንደ መገናኛ ዘዴዎች የሚያገለግሉ አያሌ የመልዕክት ምልክቶች ተሰናዱ። ደርግ ጽ/ቤት ደጃፍ ላይ አንድ ግለሰብ ተመድቦ ከእሱ ቀጥሎ ለሚገኘው ሰው የኢላማውን መቃረብ በምልክት ያስተላልፋል። ይሄ መልዕክት በዚህ ሁኔታ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሰናሰለ፣ በመስመሩ መጨረሻ ላይ፣ በተለያዩ ማዕዘናት ላይ ሸምቀው ለሚገኙ ሰዎች ይደርሳል። የመኪና መብራቶች፣ የእጅ ባትሪ ብርሃንን፣ የእጆች እንቅስቃሴና የመሳሰሉት የምልክት ማስተላለፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለኢላማነት የተመረጠውን መኪና እንዲሁም ኮሎኔል መንግሥቱ በመኪናው በየትኛው በኩል እንደተቀመጡ ለማሳየት ይችላል። ከኢሕአፓ መኪናዎች መካከል እንኳ የመኪናዋን መብራት እንደ ምልክት ማስተላለፊያ በመጠቀም ከኮሎኔል መንግሥቱ መኪና ፊት በመቅደም ትበራለች። ሌሎች አባላትንም ኢላማው እየደረሱ መሆናቸውን ታሳውቃለች።

መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡30 ላይ ሊፈፀም የታቀደው እርምጃ የመሸመቂያ ስፍራው አዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም አጠገብ እንዲሆን ተወሰነ። ኮሎኔል መንግሥቱ ደርግ ጽ/ቤትን እንደለቀቁ የመድረሳቸውን ምልክት የምታስተላልፈው መኪና መንቀሳቀስ ጀመረች። ነገር ግን፣ ይህች መልዕክት አስተላላፊ መኪናን ቀድመው ሌሎች መኪኖች በመሃል ስለገቡ፣ በመጨረሻ ሸምቀው ለሚጠብቁት ጥቃት ፈፃሚ አባላት መልዕክት ሊደርስ አልቻለም። ስለሆነም፣ ኮሎኔል መንግሥቱ አካባቢያቸው መድረሳቸውን ሳያውቁ ቀሩ። የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መኪና ከኋላ ሲከተል የነበረው የኢሕአፓ መኪና በመሸመቂያ ስፍራው እንደደረሰ ተኩስ ከፈተና የኮሎኔል መንግሥቱን አጃቢዎች ከጥቅም ውጭ አደረጋቸው። ሸምቀው የነበሩት አባላት ግን ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ።

የኮሎኔል መንግሥቱን መኪና ይከተሉ የነበሩት አባላት ከመኪናቸው ደርሰው ተኩስ መክፈት እንደጀመሩ፣ ኮሎኔሉን የያዘችው መኪና አራተኛ ክፍለ ጦር በራፍ ላይ ተጠግታለች። የኮሎኔሉ ሹፌር እንደምንም ብለው መኪናዋን ወደ ግቢው ሲያስገቧት ኮሎኔል መንግሥቱ ወንበር ስር እጥፍጥፍ ብለው ተገኙ። የበረደች ጥይቅ ሙሃሂታቸው ላይ አግኝታቸው ተረፉ። በሻምበል ሞገስ መረጃ መሠረት፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ከመኪናዋ ውስጥ ሲወጡ በጣም በሚያሳፍር መልክ ተደናግጠው ነበር። በመኪናቸው ወንበር ሥር ሲሸሸጉ ሽጉጣቸውን እንኳን መያዝ ተስኗቸው እንደ አልባሌ እቃ ከመኪናው ወለል ላይ ወድቆ ተገኘ።

ይህ ጥቃት ከመከናወኑ በፊት የታጣቂው ክንፍ አሃዶች አባላት በኢላማቸው ላይ ለመፈፀም የታቀዱትን እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ባለመቻላቸው ተወቅሰዋል ይላል ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ በተሰኘው መፅሐፉ። ገለፃውንም ሲያክልበት፡- ይህ የመጨረሻም ሙከራቸውም ተስፋ የመቁረጥ መንፈስ የታከለበት እርምጃ መስሏል በማለትም ያብራራል።

እርግጥ ነው በወቅቱ የነበረውን የከተማ ውስጥ ግድያ /ቀይ ሽብርን/ ለማክሰም ኢሕአፓዎች ከላይ ባነበብነው ታሪካቸው ውስጥ ኮ/ል መንግሥቱን ለመግደል ሙከራ አድርገው አልተሳካም። ባለመሳካቱ ደግሞ እጅግ የበዙ ወጣቶች በየጎዳናው ላይ ደማቸው ፈሰሰ። ታጣቂዎች ቤት ለቤት ሁሉ እየዞሩ ትውድን ጨረሱ።

እዚህ ላይ አንድ የታሪክ አጋጣሚን ወደ ኋላ ሔጄ ልጥቀስ። በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የአጭር ልቦለድ መፅሐፍ ደራሲ የሚባለው አስገራሚ ሰው ነበር። ስሙ ተመስገን ገብሬ ይባላል። ይህ ሰው በዘመኑ ማለትም በ1920ዎቹ ውስጥ ተምረዋል ከሚባሉት የነቁ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነበር። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር ስትሰናዳ ሁሉንም መረጃ ስላገኘ “ጣሊያኖች ሊወሩን ነው፤ እንዘጋጅ! እንታጠቅ! እንዋጋ!” እያለ ህዝብ ሲቀሰቅስ የነበረ ነው። በኋላም ጣሊያኖች ወረሩን። ታዲ ይህ ተመስገን ገብሬ በድብቅ ከነ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ጋር እየሆነ እየመከራቸው፣ አያሌ ነገሮችንም አመቻችቶላቸው ግራዚያኒ ላይ ግድያ እንዲፈፅሙ አደራጃቸው። ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭም ቦንቡን ወርውረው ግራዚያንን አቆሰሉት። ከዚያም ከ30ሺ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ተገደለ ተጨፈጨፈ። እነ ሞገስና አብርሃ በመጨረሻ ተገደሉ። ተመስገን ገብሬ ደግሞ በተአምር አምልጦ ወደ ሱዳን ተሰደደ። ክፍሉ ታደሰም ተመስገንን ገብሬን ይመስለኛል። ምክንያቱም ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም እሳት ጎርሰው፣ እሳት ለብሰው ሁል ጊዜ ታድኖ እንዲያዝ ትዕዛዝ ያስተላለፉበት ነበር። አልያዙትም፤ አልተያዘላቸውም። ተመስገን ገብሬም በግራዚያኒ እና በወታደሮቹ በእጅጉ የሚፈለግ ሰው ነበር፤ አልተያዘም አምልጧል።

    በአጠቃላይ ይህን ርዕሰ ጉዳይ ወደ ኋላ ሔጄ ያነሳሁበት አብይ ምክንያት፣ እነዚህ ወራቶች ላይ ልክ የዛሬ 40 ዓመት ኢትዮጵያ ልጆቿ የተጨራረሱበት፣ ያለቁበት ዘመን በመሆኑ፣ መፃህፍትና የታሪክ ሰነዶች ምን ይላሉ እያልኩ ወቅቱን ላስታውስ ፈልጌ ነው። የ40 ዓመቱ የኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ ምን ይመስላል በሚሉትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ምን ተፅፏል ብዬ ሳምንትም ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ይምረጡ
(17 ሰዎች መርጠዋል)
12106 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us