ሐይማኖት እና ያ ትውልድ

Thursday, 08 January 2015 13:47

በጥበቡ በለጠ 

 

መቼም ቀኑ የገና ዋዜማ ነውና ዛሬ ደግሞ እስኪ ስለ “መንፈሣዊ ፖለቲካ” እናውጋ ብዬ ተነስቻለሁ። “መንፈሣዊ ፖለቲካ” ምን አይነት ፅንሠ ሃሳብ ነው? ብላችሁም መጠየቃችሁ አይቀርም። ለነገሩ “መንፈሣዊ ፖለቲካ” ከተባለ “ስጋዊ ፖለቲካ”ም መኖሩ አይቀርም፤ ብላችሁ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ግድ የለም ሁለቱም ፅንሰ ሃሳቦች ይኑሩ። ዛሬ ግን “መንፈሣዊ ፖለቲካ” የሚለውን ሃሳብ እንጨዋወት። በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ይባል የለ? ተቆጪ ስለሌለን ወደ ወጋችን እንግባ።

ኢትዮጵያ የክርስትናን ሃይማኖት በቀደምትነት ከተቀበሉት ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ነች። ይህች ኢትዮጵያ፣ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተደጋግማ ስሟ በበጐ ጐኑ የተፃፈላት ሀገር ናት። አባቶች “መንፈሣዊት ሀገር” ይሏታል። ጉዳዩን ሲያብራሩም፣ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው ወይም ወደ ሀገሪቱ ምድር ያስገባችው እየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ በአራተኛው ዓመት ነው ይላሉ። ይህ ማለት በ34 ዓ.ም ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ማብራሪያ የሚጠቀሙበት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም የሐዋርያት ሥራ ተብሎ በተጠቀሰው ምዕራፍ ውስጥ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወደ እስራኤል ሔዶ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ ይገለፃል። ይሄ ደግሞ በ30 ዓ.ም ልክ እየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ወቅት ነው። ጃንደረባው በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ የገንዘቧ አዛዥ መሆኑ ተገልጿል። ያ ማለት በአሁኑ አጠራር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትሯ ነበር ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ጃንደረባ (ባኮስ) ትልቅ የመንግሥት መልዕክተኛ ነበር። በመሆኑም ጃንደረባው በእየሱስ ጥምቀት ላይ ተገኝቶ እሱም ተጠምቆ ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለስ ድረስ ወደ አራት ዓመት ፈጅቶበታል። ከዚያም በ34 ዓ.ም ሀገሩ ኢትዮጵያ ገባ። ክርስትናም በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የመንግስት ሃይማኖት ሆነ ብለው መረጃ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ።

ይህን ከላይ የሰፈረውን ሃሳብ በመከራከሪያነት የሚያቀርቡት አካላት በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትና የገባው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉስ ኢዛና ዘመነ-መንግሥት ነው የሚሉትን ምሁራን የመልስ ምት ለመስጠት ነው። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ክርስትና ገባ የሚሉት ምሁራን የእነሱ ማስረጃ አክሱም ከተማ ውስጥ በንጉስ ኢዛና ዘመነ-መንግሥት የተሰሩ የድንጋይ ሐውልቶች ላይ “እኔ ንጉስ ኢዛና ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ሆኛለሁ” የሚለውን ጽሁፍ በመመልከት ነው። በዚህ ጽሁፍ ሀገሪቱን የሚመራው ኢዛና ሙሉ በሙሉ ክርስትያን መሆኑን ስላወጀ፣ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት የሆነው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ባዮች ናቸው ምሁራኑ።

ከቤተ-ክርስቲያን በኩል ሆነው ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም ነው ብለው በሚከራከሩት እና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው ክርስትና የመንግስት ሃይማኖት የሆነው በሚሉት መካከል የ300 ዓመታት ልዩነቶች አሉ። የቤተክርስቲያኖቹ ተከራካሪዎች ማስረጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራኖቹ ማስረጃ ደግሞ አክሱም ውስጥ ያለው የድንጋይ ጽሁፍ ነው።

በነገራችን ላይ ከእነዚህ ከላይ ከሰፈሩት ሁለት ተከራካሪዎች ሌላ አንድ መረጃም አለ። ይህም፣ እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የአክሱም ኢምፓየር ነበር። በዚያን ወቅት ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው ደግሞ ንጉስ ባዜን ይባላል። ንጉስ ባዜን እየሱስ ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያን ለስምንት ዓመታት መርቷታል። ከዚያም የእየሱስ ክርስቶስን መወለድ ሲሰማ ወደ እስራኤል ተጉዞ እንደ ሰብዐ ሰገሎች ሁሉ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እና ሌሎችንም የደስታ ስጦታዎች አበርክቶ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መመለሱ በአፈ-ታሪክ ውስጥ በሰፊው ይነገራል። ከዚያም፣ ማለትም እየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላም ንጉስ ባዜን ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን መርቷታል። ከእየሱስ መወለድ በፊት ስምንት ዓመት፣ ከመወለዱ በኋላ ደግሞ ስምንት ዓመት በአጠቃላይ 16 ዓመታት ኢትዮጵያን መርቷታል። ስለዚህ የክርስትና ጽንሰ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ የገባው እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ በንጉስ ባዜን ዘመነ-መንግስት ነው የሚል ሃሳብ የሚሰነዝሩ የአክሱም መረጃዎችም አሉ።

በአጠቃላይ ግን መናገር የሚቻለው የክርስትና ሃይማኖት የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ኢትዮጵያ ላይ መገናኘት የጀመረው እጅግ ረጅም ዓመታት ወደኋላ ተጉዞ ነው። ኢትዮጵያ ላይ የሚነግሱ ንጉሶች እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ድረስ ያሉት ማለት ይቻላል ሹመታቸው የሚፀድቅላቸው በቤተ-ክርስቲያኒቱ ይሁንታ ነበር። ስለዚህ የሀገር መሪ ሾማ የምትቀባ ሃይማኖት ሆና እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ተጉዛ ነበር።

ወደኋላ ያሉ የታሪክ መዛግብቶችና መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የንጉስን ሹመት ከማፅደቅ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ችግር ሲገጥማት፣ በባዕዳን ስትወረር በመመከትና ነፃ በማውጣት ግንባር ቀደም ሚናም ነበራት። በአድዋ ጦርነት እንኳ የካቲት 1888 ዓ.ም ታቦቶቿን እና ቀሳውስቷን ይዛ የዘመተች በኋላም ከኮሎኒያሊዝም አገዛዝ ኢትዮጵያ ነፃ እንድትወጣ ያደረገች ቤተ-ክርስቲያን እንደሆነች ይገለፃል። ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማቆየቱ ረገድ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሚና በምንም መለኪያ የሚሰፈር እንዳልሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ትምህርትን በማስፋፋት፣ ልዩ ልዩ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን በመገንባት (ዛሬም ድረስ የፕላኔታችን ምስጢራት የሆኑትን እንደ ቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር)ን በማበርከት፣ በመፃህፍት እና በመዛግብት ሕትመት፣ በቋንቋ ልማትና ብልፅግና ብሎም በሌሎችም ኢትዮጵያዊ መሠረቶች ላይ ዘላለማዊ ካስማና ማገር የሆነች የእምነት ተቋም ነበረች። ድንገት ግን 1966 ዓ.ም ላይ ምን እንደነካት ሳይታወቅ አንድ አስደንጋጭ ጉዳይ ገጠማት።

ከ1950ዎቹ እስከ 1966 ዓ.ም ላይ ብቅ ባሉ ወጣት የኢትዮጵያ የለውጥ አቀንቃኞች አዲስ ሃሳብ መጣ። ይህ ሃሳብ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥቶ የሚሰብክ ነው። ያ ትውልድ በነ ማርክስ፣ ኤንግልስና ሌኒን ፍልስፍናዎች የተሞላ ስለነበር ከሀገርኛው መንፈስ፣ እምነት፣ ባሕልና ታሪክ ውጭ የሆኑ አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት አደረገ። ኢትዮጵያን ለማዘመን፣ የተሸለች ሀገር ለማድረግ ከሃይማኖታዊ ተፅዕኖ እና አስተሳሰብ መላቀቅ አለበት ተብሎ ትግል ተጀመረ። የትግሎቹ ሒደት በመጨረሻም በ1966 ዓ.ም ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግን ፈጥሮ ለሦስት ሺ ዓመት የኖረውን የንግሥና ሥርዓት በመጣልና ከ1500 ዓመት በላይ የቆየውን ሃይማኖታዊ መንግሥትን ማውረዱን አወጀ። ከዚያም በየ ጐዳናው ተጨፈረ።

ፋኖ ተሰማራ

ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺ ሚኒ - እንደ ቼኩ ቬራ!

አለ ተቀናቃኙ።

“ተነሣ ተራመድ - ክንድህን አበርታ

ለሀገር ብልፅግና ለወገን መከታ”

እያሉ ሕብረ-ዝማሬ አሰሙ።

“ይህ ነው ምኞቴ

እኔ በሕይወቴ

ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”

እየተባለ ተዘመረ። “ኢትዮጵያ ትቅደም” ብለውም በማታውቀው የሶሻሊዝም የመሮጫ ትራክ ውስጥ ከተዋት ካለ አቅሟ አስሮጧት። አደከሟት።

በኋላም የመፈክር አይነትም ተዥጐደጐዱ።

-          ፊውዳሊዝም ይወድማል!

-          ኢምፔሪያሊዝም ይወድማል!

-          አናርኪስቶች ይወድማሉ!

-          የቢሮ ከበርቴዎች ይወድማሉ!

ብዙ የሚወድሙ ነገሮችም መጡ። ፈተናው እያየለ መጣ።

በወቅቱ በትውልድ ውስጥ ሲብሰለሰል ቆይቶ ድንገት የፈነዳውን ማለትም ሃይማኖትና መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ አንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም በሚሉት አስተሳሰቦች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቃወም ድምፃቸውን ያሰሙት አለቃ አያሌው ታምሩ ናቸው።

አለቃ አያሌው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ውስጥ የሊቆች ሊቅ የሚል መጠሪያ የነበራቸው ናቸው። ታዲያ 1966 ዓ.ም ላይ፣ አለቃን አስቆጥቶ በተቃውሞ ያስነሳቸው ጉዳይ ቢኖር፣ ሃይማኖትና ሀገር /ፖለቲካ/ አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ አይገቡም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ ነው። አለቃ አያሌው ይህን ሃሳብ በመቃወም ያቀረቡት ነገር ቢኖር፣ ይህች ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ከጦርነት ጠብቃ እና ተከላክላ፣ ትውልድን አስተምራና አሳውቃ፣ ነገስታትን እየሾመችና ከጐን ሆና እየመራች፣ እዚህ ያደረሰችው ቤተ-ክርስቲያን ናት። ታዲያ በምን ምክንያት ነው ዛሬ በሀገር አመራር ውስጥ ቤተ-ክርስቲያን ጣልቃ አትገባም የሚባለው? ለመሆኑ ሀገሪቱን ጠብቆ እዚህ ያደረሰው ማን ሆነና ነው። አያገባትም የሚባለው!? በማለት ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው ከአዳዲሶቹ ትውልዶች ጋር ተፋጠው ነበር።

እየዋለ እያደር የጊዜውና የፖለቲካ ትኩሳቱ፣ ግለቱ እየተፋጀ መጥቶ ግድያውም የትየለሌ እየሆነ ሲመጣ፣ ቤተ-ክርስትያን እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፋቱ (ተለያዩ)። የአስተሳሰብ ግድግዳ በትልቁ ተገነባባቸው። እየዋለ እያደር ደግሞ “ሃይማኖት የመጨቆኛ መሣሪያ ነው” የሚሉ ፍልስፍናዎች በስፋት ተቀነቀኑ።

ይህ የመጨቆኛ መሣሪያ ነው ተብሎ የተጠራው ሃይማኖት ደግሞ ክፉኛ ችግር ውስጥ መግባት ጀመረ። ታላቋ ቤተ-ክርስቲያን አሉታዊ ተፅዕኖ እየበረታባት በመሄድ ለሕልውናዋ ሁሉ አስጊ ጉዳዮች መታየት ጀመሩ።

ለዚህች ሀገር ክብር፣ ለዚህች ሀገር ሕዝቦች ልዕልና ሲባል ደረታቸውን ለመትረየስ ጥይት ሰጥተው የሚሞቱ የሃይማኖት አባት ማለትም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ ሰማዕት የሰጠች ቤተ-ክርስቲያን በሀገር ጉዳይ አያገባሽም ተባለች። እሷ ጠብቃ ባኖረቻት ሀገር እነ ማርክስ፣ ኤንግልስ እና ሌኒን የሃሳብ መሪዎች ሆኑ። ለኢትዮጵያ የተሰውት የአቡነ ጴጥሮስ የእምነት ፅናትና ፍልስፍና ኢትዮጵያ ላይ ሳይነገር፣ የባዕዳኖቹ የነ ማርክስ ርዕዮተ ዓለም መመሪያችን ሆኖ ኖረ።

ያ ትውልድ ያቀጣጠለውን አብዮት ከ40 ዓመታት በኋላም ሰከን ብለን ስናስበው ኢትዮጵያዊ መሠረቱ የላላ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። እነ ሆቺ ሜኒ፣ ቼኩ ቬራ፣ ማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ሌኒን… የያ ትውልድ መጠምጠሚያ ሆነው አረፉት። የኢትዮጵያን አብዮት ማቀጣጠያ ችቦ ሆነው አገለገሉ። የመቅደላው ሰማዕት አፄ ቴዎድሮስ ተዘነጉ፤ መተማ ላይ አንገታቸውን ለሀገራቸው ክብር የሰጡት አፄ ዮሐንስ ተረሱ፤ አድዋ ላይ የኮሎኒያሊዝምን ወረራ ድባቅ የመቱት አፄ ምኒሊክ ለምሳሌም መብቃት አቆሙ፤ ኢትዮጵያን ከባዕድ ወረራ አውጥተው ወደ ስልጣኔ መንገድ የቀየሷት አፄ ኃይለስላሴን ስማቸውን የጠራ እንደ እርኩስ ይቆጠር ጀመር። በአጠቃላይ ሀገራዊ ምሳሌና መመሪያ የጠፋበት ዘመን ተፈጠረ - 1966 ዓ.ም

የያ ትውልድ አባላት በአብዛኛው ሃይማኖታቸውን ቀይረው አዲስ ሃይማኖት ጀመሩ። አዲሱ ሃይማኖታቸው ደግሞ “ሶሻሊዝም” ሆነ። ርዕዮተ ዓለሙን እስከ ማምለክ ደረሱ። በየፓርቲዎቻቸው ውስጥ ሆነው አቀነቀኑ። ከየ ካምፓቸው ላይ ሆነው የእኔ ፓርቲ አመለካከት የተሻለ ነው በሚለው ተከራከሩ፣ ተጣሉ፣ ተገዳደሉ፣ በመቶ ሺዎች አለቁ፣ ታሰሩ፣ ተሰደዱ። ያ ጦስ ላለፉት 40 ዓመታት ሰንኮፉ አልወጣም።

“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” ብዬ ሃይማኖትና ያ ትውልድን በጥቂቱ ልዳስሰው ሞከርኩ። መጪው ጊዜም ጥምቀት ነው። ታህሳስ 29 ቀን 2007 ዓ.ም እየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ብለን እናከብራለን። ጥር 11 ደግሞ ጥምቀቱን እናከብራለን። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “እኛ እና እግዚአብሔር” የሚል ግሩም ጽሁፍ አላቸው። ያ ትውልድ እና ሃይማኖት ተራርቀው ኖረው ነበር። ይህ ትውልድ እና ሃይማኖትስ የሚል ጥያቄ ማንሳት ትችላላችሁ። ስለዚህ ወጋችን ሳምንትም ይቀጥላል። ወቅቱ ዓውዳመት ስለሆነ ነው። መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ ብዬ ብሰናበትስ። 


ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
17859 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 79 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us