ዩኔስኮ የጥምቀት በዓልን ዕውቅና ለኤርትራ ሊሰጥ ይችላል

Wednesday, 21 January 2015 15:42

በጥበቡ በለጠ

    

ከዓመታት በፊት በዚሁ በሰንደቅ ጋዜጣችን አንድ አሳሳቢ ነገር ዘግበን ነበር። ይህም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባሕል ድርጅት የሆነው (UNESCO) የመስቀል ክብረ በዓልን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበር የሚታወስ ነው። ጥያቄውም መስቀል በሃገራችን ልዩ በዓል ነው፤ በሌሎች ዓለማት የማይገኝ የአከባበር ታሪክ፣ ባሕል እና ቅርስ አለን የሚል አንደምታ ያለው ነበር። ዩኔስኮም የራሱን ጥናትና መመዘኛ አድርጐ በመጨረሻም መስቀል በዓለም ላይ ልዩ የሆነ አከባበር ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን በማመን ኢትዮጵያን በመዝገቡ ውስጥ አሰፈራት። የዓለም ቱሪስቶችም የመስቀልን በዓል ለማክበር ሲፈልጉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ በድረ-ገፁ ላይ እየፃፈም ይገኛል። አሁን ደግሞ አንድ አሣሣቢ ችግር እየመጣ ይገኛል። የጥምቀት የበዓል አከባበር ጉዳይ!

ኤርትራ የጥምቀት በዓል አከባበር በሀገሬ ልዩ ነው እያለች ነው። በኤርትራ ውስጥ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው፣ ጉዞ አድርገው ውጭ አድረው፣ በምዕመናን አጀብ፣ እልልታ፣ ዝማሬ ብሎም በቀሣውስት ልዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ደምቆ ይከበራል። ኤርትራ በዓለማችን ላይ የጥምቀትን በዓል አከባበር ልዩ በማድረግ ቀዳሚት ሀገር ናት፤ ስለዚህ ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ውስጥ በቅርስነት ይመዝገብላት የሚል አንደምታ ያለው ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረች ሰንበትበት ብሏል።

ኢትዮጵያም በርካታ ቅርሶቿን ለማስመዝገብ ጥረት እያደረገች መሆኑ ይነገራል እንጂ፣ ጥምቀትን በተመለከተ የተለየ እንቅስቃሴ እያደረገች ይሁን ወይስ አይሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር ማግኘት አልተቻለም። እንደ አንዳንድ ምንጮች ገለፃ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ አያሌ ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሌሎችም ብሔረሰቦቿ ቅርሶች እንዲመዘገቡላት ጥረት እያደረገች መሆኗን ነው። አብዛኛዎቹ የተመዘገቡት ቅርሶች ከወደ ሰሜን አካባቢ ብቻ ስለሆነ ይህን ቁጥር ለማመጣጠን በሌሎች ክልሎች ላይም ሰፊ ትኩረት እንዲሰጥ አቅጣጫ መያዙ ይነገራል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ለጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ መመዝገብ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ በስፋት ባይገለፅም የዚህ በዓል አከባበር ታሪክ ግን ለኤርትራ ሊሰጥ እንደሚችል ስጋት አለ። ዩኔስኮ ጥምቀትን ለኤርትራ ሊሰጥ የሚችልባቸው ምክንያቶች አሉ።

አንደኛ ኢትዮጵያ ስለ ጥምቀት በዓል አከባበሯ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ልዩ መስህቦቿን መግለፅ ካልቻለችና በየጊዜው ተፅዕኖ ካላደረገች፣

ሁለተኛኤርትራ የመስቀል በዓልንም ጥያቄ አቅርባ ለኢትዮጵያ ስለተሰጠባት፣ እሱን እንደ መነሻ አድርጋ ጥምቀትም ከእጇ እንዳያመልጥ ሰፊ የመከራከሪያ አጀንዳ ከከፈተች

በእነዚህ ከላይ በሰፈሩት ሁለት ነጥቦች ምክንያት፣ የጥምቀትን በዓል ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ባለቤትነት ከኢትዮጵያ ወጥቶ ወደ ኤርትራ እንዳይሰጥ ስጋት አለ። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የምትጋራቸው በርካታ የታሪክ፣ የባህል፣ የሃይማኖት ጉዳዮች ስላሉ በሁለቱም ሀገሮች እኩል ይወራሉ። በጥንት ጊዜ ወደ እስራኤልም ሆነ ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመጓዝ ኤርትራ መሄድ፣ ኤርትራ ላይ ማረፍ፣ ኤርትራ ላይ ቅርስ ማበጀት የተለመደ በመሆኑ ይህች ሀገር ለመከራከሪያ የምትጠቅሳቸው ብዙ መነሻዎች አሏት። እንደውም አሁን ብቅ እያሉ ያሉ የኤርትራ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ከሆነ የንግሥተ ሣባ መቀመጫ ኤርትራ ነበረች። ኤርትራ ላይ ሆና ነው ስታስተዳድር የነበረችው፤ ቀዳማዊ ምኒልክም የተወለደውና ያደገው፣ አቢሲኒያንም የመራው ከኤርትራ ነው የሚሉ ግራ አጋቢ ታሪኮች እየተነገሩ ነው። በእነዚህ የታሪክ ሂደቶች በሚርመሰመሱ ሃሳቦች መሀል የጥምቀት በዓል አከባበራችን ከኢትዮጵያ ወጥቶ ለኤርትራ እንዳይሰጥ ስጋት አለ።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ስለ ጥምቀት በዓል አከባበር ታሪኳ ምን ልትናገር፣ ምን የታሪክ ሰነዶችን ልታወጣ፣ ምንስ ሃይማኖታዊ መረጃዎቿን ልትሰጥ ትችላለች ብለን መጠየቃችን አይቀርም።

እርግጥ ነው ክርስትና የሚባለው ሃይማኖት ራሱ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚዘክረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ባኮስ) ወደ እስራኤል ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከመጣ በኋላ በ34 ዓ.ም ማለትም የዛሬ 1 ሺህ 973 ዓመት ማለት ነው። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ክርስትናን እንደተቀበለ ከመፅሐፍ ቅዱስ እና ከቤተ-ክርስትያን ልዩ ልዩ ሠነዶች መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ከጥምቀት ጋር የተያያዘው የኢትዮጵያ ታሪክ ከጃንደረባው ጀምሮ መጥቀስ ይቻላል።

ሌላው ግን፣ ብዙ ማስረጃ ያልተገኘለት ጉዳይ፣ አሁን ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ማለትም ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው ሌላ ቦታ አድረው፣ ከዚያም ወደ መንበረ ክብራቸው የሚመለሱበት ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ክዋኔ መቼ ተጀመረ የሚለው ነው። ይሄ ጥያቄ ወሣኝ ነው። ኢትዮጵያንም ከሌሎች ዓለማት ለየት የሚያደርጋት እና ጥምቀትም የራሷ የግሏ ነው እንዲባል የሚያስችላት ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

እርግጥ ነው በቤተ-ክርስትያኒቱ የታሪክ መፃሕፍትም ይህ የጥምቀት በዓል አከባበር እንዲህ በጐዳና ላይ እና በጥምቀተ ባሕር ጉዞ ላይ ሆኖ መከበር የጀመረው በዚህ ዘመን ነው የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ተፅፎ ለማንበብ አልቻልኩም። ግን እኔ በግሌ ላለፉት አስር ዓመታት በቅዱስ ላሊበላ ታሪክ እና በእርሱ ዘመነ መንግሥት ስለነበረው የኢትዮጵያ ሁኔታ በሰበሰብኳቸው መረጃዎች መሠረት አሁን ያለው የጥምቀት በዓል አከባበርን ያስጀመረው ይሄው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ እንደሆነ ሠነዶች ያስረዳሉ።

ታቦታት ከየአብያተ-ክርስትያናቱ ወጥተው በሕዝብ አጀብ፣ እልልታ፣ ዝማሬ፣ ሽብሸባ ታጅበው፣ በቀሣውስት እና በዲያቆናት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክዋኔ ደምቀው በጋራ ተገናኝተው አንድ ቦታ አድረው እንደገና ወደየመጡበት ቦታ የሚመለሱበት እጅግ ውብ ክብረ-በዓልን ያስጀመረው ይሄው ኢትዮጵያን ከ1157 ዓ.ም እስከ 1197 ዓ.ም የመራው ያ ጥበበኛ መሪ ቅዱስ ላሊበላ ነበር።

የላሊበላ ዓላማ እነዚህ ታቦታት አንድነታቸውን የሚያሳዩበት፣ ከየአጥቢያዎቻቸው ያለውም ሕዝብ በጋራ የሚገናኝበት፣ ከአብያተ-ክርስትያናት ውጭም ሀገር፣ ቀዬውን፣ ምድሩን የሚያደማምቁበት፣ ምዕመኑንም በመንፈሣዊ ነፃነት ከታቦታት ጋር ጉዞ የሚያደርግበትና በአጠቃላይ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥ ያሉ አማኒያንን ከእምነታቸው ጋር በጋራ የሚያስተሳስርበት መንገድ እንደሆነ ይታመናል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ይህን የቅዱስ ላሊበላን የጥምቀት በዓል አከባበር ጅማሮ ሃይማኖታዊ ዳራ ይሰጡታል። ቅዱስ ላሊበላ 12 ዓመታት እየሩስአሌም ውስጥ ኖሮ እና ተምሮ የመጣ በመሆኑ ጉዳዩን ከልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ተምሳሌቶች ጋር እያዛመዱ ይናገራሉ። በአጠቃላይ ግን አሁን ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ አማካይነት እንደተጀመረ መናገር ይቻላል።

ከኤርትራ ያሉ ተከራካሪዎች ደግሞ የጥምቀት በዓል አከባበር በዚህ መልኩ የተጀመረው ከእኛ ዘንድ ነው ባይ ናቸው። እነርሱ የሚጠቅሱት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በኤርትራ እንደተጀመረ ነው። ጉዳዩ እውነትነት ሊኖረው ይችላል። ግን እውነታው ደግሞ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ ነው። ምክንያቱም በዚያን ዘመን ወደ ኤርትራ ሄዶ ያስጀመረው የቅዱስ ላሊበላ ብቸኛ ልጅ ይትባረክ ነበር።

ላሊበላ እና ባለቤቱ ልዕልት መስቀል ክብሯ በጋራ የወለዱት ልጅ ይትባረክ ይባላል። ይትባረክ ስልጣን አይረከብም ስለተባለ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኤርትራ ተሰድዶ ነበር። በወቅቱ ባሕረ ነጋሽ የሚባለውን የቀይ ባሕር አካባቢ ያስተዳድር የነበረው ይሄው የቅዱስ ላሊበላ ልጅ ይትባረክ እና የቅዱስ ላሊበላ ቤተሰቦች ነበሩ። ዛሬም ቢሆን ቀይ ባሕር ላይ ባሉት ደሴቶች ላይ ሆነው ያንን የባሕር መስመር የሚኖሩበት የቅዱስ ላሊበላ ቤተሰቦች እንደሆኑ የቅርብ መዛግብት ሳይቀሩ ያስረዳሉ። ስለዚህ ጥምቀት በኤርትራ የተጀመረው ቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጀመረ በኋላ፣ ከዚያም ላሊበላ ይህችን ዓለም በሞት ከተለየ ጊዜ ጀምሮ የእርሱ ልጅ ይትባረክ ወደ ኤርትራ ሄዶ በመጀመሩ ነው። እናም ዛሬ ያለውን የጥምቀት በዓል አከባበር የጀመረችው ኤርትራ ሳትሆን ኢትዮጵያ ናት። ለነገሩ በዚያን ወቅትም ቢሆን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለት ሀገራት አልነበሩም።

ከእነዚህ ምክንያቶች ውጭ ደግሞ የጥምቀት በዓል አከባበርን በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ መሠረት የሚጥልልን ጐንደር ውስጥ የሚካሄደው ልዩ መንፈሣዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ዳራ የያዘው ትርኢት ነው።

ጐንደር ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለሁለት መቶ ዓመታት እጅግ በሚገርምና በሚደንቅ የስልጣኔ ጉዞ ውስጥ ገብታ ነበር። በወቅቱ ኪነ-ሕንፃዎች ተገነቡ፣ የመፃሕፍት ሕትመቶች የትየለሌ ሆኑ፣ መዝገበ ቃላት ሁሉ ተዘጋጁ፣ የጤና ምርምርና ሕክምና በሰፊው ተጀመረ፣ ዘመናዊ ጦር ተቋቋመ፣ የመንግስት አስተዳደር ወደ ዘመናዊነት ተሸጋገረ፣ የኢትዮጵያዊያን ኑሮ በእጅጉ አደገ፣ በተለይ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ጐንደር በስልጣኔ ላይ ከነበሩ የዓለም ሀገራት ተርታ ውስጥ ነበረች። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የአያሌ አድባራት መቀመጫ ሆነች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ አሉ የሚባሉት 44 ታቦታት መኖርያ ናት እየተባለች ይነገርላታል። በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዋነኛዋ መናኸሪያ (መዲና) እንደሆነች ሠነዶች ያረጋግጡላታል። በዚህች የኦርቶዶክስ ማዕከል ውስጥ የጥምቀት በዓል ለየት ባለ መልኩ ይከበራል።

ጥምቀትን ጐንደር ውስጥ ልዩ የሚያደርገው ታሪካዊ እውነት አለ። ይህም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ተነስቶ የነበረው ጦረኛው ግራኝ መሐመድ እርሱ የክርስቲያን መንግስት የሚለውን የወቅቱን ስርዓት ከኢትዮጵያ ምድር እየገረሰሰ ወደ ሰሜን ተጓዘ። ቀሳውስት ግራኝን እየፈሩ ታቦታትን እየተሸከሙ ወደ ጐንደር ማለትም ወደ ጣና ሐይቅ ደሴቶች ላይ ተመሙ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ታቦታት አብዛኛዎቹ በሽሽት ጐንደር ላይ ከተሙ።

በመጨረሻም ጐንደር ከተማ አቅራቢያ ላይ ዘንታራ በር በምትባለው ቦታ ላይ ግራኝ ተገደለ። ለ15 ዓመታት ዝብርቅርቋ የወጣው ኢትዮጵያ ጐንደር ላይ መርጋት መረጋጋት ጀመረች። በሽሽት የሄዱት ታቦታት እና ቀሣውስት አዲስ የሃይማኖት ብልፅግና ጐንደር ላይ ጀመሩ። የሃይማኖት ትምህርት ተስፋፋ፣ ቅኔው አቋቋሙ፣ ፍልስፍናው የትየለሌ ሆነ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩ ውበትን ተጐናጽፎ ጐንደር ላይ አሸበረቀ።

አፄ ፋሲል በ1626 ዓ.ም ባስገነቡት የመዋኛ ገንዳ ላይ ኢትዮጵያን ከ1770-1772 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት የመራው አፄ ሰለሞን ወንዞችን ጠልፎ ጥምቀትን በዚህ ቦታ ላይ ጀመረው። እነሆነ እስከ ዛሬ ድረስ ጥምቀት በዚህ ቦታ ላይ በሚያምር ግርማ ሞገስ ይከበራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ የእምነቱ መገለጫዎች በሙሉ አሉባት የምትባለው ጐንደር ጥምቀትን በልዩ ሁኔታ ታከብራለች። ስለዚህ ይህ በዓል የኢትዮጵያ ሆኖ በዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ እንዲቀመጥ ትልቅ ርብርብ የሚጠይቀን ሰዓት ነው። አለበለዚያ ኮሚሽኑ በቅርቡ ለኤርትራ ሊሰጣት እንደሚችል ማወቅ አለብን። ያ ደግሞ በእጅጉ ያስቆጫል።

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
13145 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us