እማማ ኢትዮጵያ. . . አስገራሚው ዶክመንተሪ ፊልም

Wednesday, 28 January 2015 13:05

በጥበቡ በለጠ


ዶ/ር አሸራ ኩዊዚስ እና ሚስ መሪራ፣ አፍሪካን አሜሪካን ባልና ሚስት ናቸው። ሁለቱም የታሪክና የማህበረሰብ ጥናት ምሁራን ናቸው። ከጥናታቸው ዘርፎች ደግሞ ዛሬ በልዩ ልዩ የአሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ያሉ ጥቁሮች የማንነት ችግር እንዳይኖርባቸው የአፍሪካን ታላቅነት እያጠኑ በአያሌ መድረኮች ላይ ያቀርባሉ። በየዓመቱም ጥቁር አሜሪካዊያንን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው እየመጡ ይህች ሀገር የጥቁር ሕዝብ ሁሉ መመኪያ ናት፤ ብዙ ተአምራዊ ስልጣኔዎች የነበሯት እና የጥቁር ህዝብ ማዕከል ናት እያሉ ያስተዋውቃሉ፣ ያስጎበኛሉ።

ዶ/ር አሽራ እና ባለቤቱ መሪራ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረገ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተዋል። የዶክመንተሪው ፊልም ርዕስ `Mama Ethiopia from Ancient Kush to the Black Lions` ይሰኛል። ወደ አማርኛም ስንመልሰው “እማማ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ ኩሽ እስከ ጥቋቁር አናብስት” የሚሰኝ ነው። ፊልሙ ሶስት ሰዓታትን ይፈጃል። በውስጡ የያዘው ደግሞ የኢትዮጵያ ታላቅነት ለዓለም ሁሉ ማስተዋወቅ ነው።

ሁለቱ ባልና ሚስት በቶሮንቶ ካናዳ ውስጥ በኒዮርክ ዩኒቨርስቲ አያሌ ጥቁሮች በተገኙበት መድረክ ላይ ስለ “እማማ ኢትዮጵያ. . .” ፊልማቸው ንግግር አቅርበዋል። በዚህ ሶስት ሰዓታት በፈጀው መድረክ ላይ ከቀረበው ንግግር የመጀመሪያዋን ጥቂት ክፍል ዛሬ አቀርብላችኋለሁ። ታዲያ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን የምፈልጋቸው አካላትም አሉ። ይህን ዶክመንተሪ ፊልም የሰጠኝን እስክንድር ከበደን እና በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ሳቀርበው ውብ የሆነ የሬዲዮ ፕሮዳክሽን የሰሩልኝን ባልደረቦቼን በሙሉ አመሰግናቸዋለሁ።

በዚህ `Mama Ethiopia from Ancient Kush to the Black Lions` ወይም “እማማ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ ኩሽ እስከ ጥቋቁር አናብስት” በተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልም ላይ የመግቢያ ንግግር የምታደርገው የዶ/ር አሸራ ባለቤት ሚስ መሪራ ኩዊዚስ ናት። እንዲህም አለች፡-

“ቶሮንቶ ካናዳ ዮርክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሰላም ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ። የዛሬውን የጥናትና የምርምር ውጤቱን የሚያቀርብልን አሸራ ኩዊዚ ነው። አሸራ የዩኒቨርስቲ አስተማሪና ተመራማሪ ነው። በአፍሪካ የጥንት ታሪኮች ባህሎችና እምነቶች ላይ ያጠና ነው። በአፍሪካ በተለይም በአባይ ሸለቆ ውስጥ ከ26 ዓመታት በላይ ጥናት አድርጓል። የጥናቱ ሽፋንም ግብጽን፣ ኢትዮጵያን፣ ኬኒያን፣ ሱዳንን ሲሆን ዛሬ ግን የሚያተኩረው ኢትዮጵ ላይ ነው። ኢትዮጵያ የጥንታዊያኑ የኩሽ ሀገር መሆኗን እና የሰው ዘር መገኛ ምድር ስለሆነች ዛሬ የዚህን ሁሉ የታሪክ ምርምሩን ያቀርብላችኋል። ጥንታዊዎቹን አፍሪካ አብያተ-ክርስቲያኖችን እንደ ላሊበላ ያሉትን እንዲሁም የዛጉዌ ስርወ መንግስትን በተመለከተ ያቀርብልናል። በክብር እንድትቀበሉልኝ እጠይቃችኋለሁ።” አለች።

ሕዝቡም ከመቀመጫው ተነስቶ ዶ/ር አሸራን የሞቀ አቀባበል አደረገለት። ቀጥሎም ዶ/ር አሸራ የሚከተለውን ውብ ንግግሩን አደረገ፡-

“ዛሬ በአባይ ሸለቆ ውስጥ ነው የምንጓዘው። የአባይ ሸለቆ ውስጥ ስንጓዝ ነው የሰው ዘር መፈጠሪያ ቦታን የምናገኘው። ስለዚህ አሁን የምንነጋገረው ስለ ሰው ዘር መፈጠሪያ ቦታ ላይ ነው። የአርኪዮሎጂ ምርምርና ውጤት የተገኘበት ቦታ ላይ ነው ዛሬ የምንነጋገረው። አውሮፓውያን ከዚህ በፊት አውሮፓ የሰው ዘር መገኛ ነው ይሉ ነበር። ከዛም የሰው ዘር መገኛ ቻይና ነው ይባል ነበር። አፍሪካ የሰው ዘር ምንጭ ናት ተብሎ አይታሰብም ነበር። ወደ አፍሪካም ስመጣ ያገኘሁት የሰው ልጅ መገኛ የሆነውን ስፍረ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር አካባቢ ድንቅነሽ ወይም ሉሲ ተገኝታለች። እነ ፕሮፌሰር ጆሃንሰን በቢትልሶች ሙዚቃ አማካይነት ሉሲ ቢሏትም ኢትዮጵያዊ ስሟ ግን ድንቅነሽ ነው። ትርጉሙም የምታስገርሚ የምታስደንቂ ነሽ ማለት ነው።

“በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ የድንቅነሽ ቅሪተ አካል አምሳያ ቆሞ ይታያል። ያ የሚያሳየው የሰው ዘር እንዴት እንደተፈጠረና እንዴትስ ቆሞ መሐየድ እንደጀመረ ማሳያ ነው።

“ከድንቅነሽ በኋላም ዲቂቃ በተባለ ቦታ ሌላ አለምን ያስደነቀ ግኝት ይፋ ሆኗል። ናሽናል ጆኦግራፊ የተሰኘው መፅሔትም ይህን አስገራሚ ታሪክ ፅፎ ለዓለም አሰራጭቶታል” በምድራችን ላይ በእድሜው የሶስት ዓመት ሕፃን የነበረች እና ዛሬ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዓመት እንደኖረች በሳይንስ ምርምር አርኪዮሎጂስቶች ያረጋገጡላት የሕፃን ቅሪተ አካል የተገኘው እዚህችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

“ዓለማቀፉን የሚዲያ ተቋም CNNን ጨምሮ ሌሎችም ሊዘግቡት የሚገባው ደግሞ አሁን ያለው ዘመናዊ ሰው ቅድመ መገኛው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ነው። በዚሁ በአፋር ክልል ውስጥ የዛሬ 160ሺ ዓመት የነበሩ የዘመናዊ ሰዎች ቅሪተ አካል የተገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የሰው ዘር በኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝቶ ነው ወደ ሌሎች አለማት የተሰራጨው የተጓዘው። (11፡06) ወደ አውሮፓ፣ ኤዥያና ሌሎች ቦታዎች ላይ ጉዞ አድርጓል። ምንጩ ኢትዮጵያ ነች። የሰው ዘር ወልዳ ለዓለም ያበረከተች ሀገር ናት።

“ጀንሲስ /ኦሪት ዘፍጥረት/ የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ ነው። ፍቺውን የመጀመሪያው እንደማለት ነው። በዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል አባይ /ናይል/ግዮን ተጠቅሷል። ይህችው ኢትዮጵያ በሳይንሱም ሆነ በእምነቱ ረገድ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆና እየተጠቀሰች ነው። እንደምናየው ከሆነ ግሪኮች፣ ሮማውያን አልተጠቀሱም የተጠራችው ኢትዮጵያ ናት።

“ኢትዮጵያን በሙሉ ዛሬ አይቻታለሁ። ጊዮን /አባይ/ የሀገሪቱን ሕዝቦች ሁሉ ያስተሳሰረ ነው። ከፍጥረት አለም ጀምሮ የሚፈስ፣ የሚመግብ ወንዝ ነው። በአየር ላይ በአውሮፕላን ሆኜም እየዞርኩ አይቻለሁ። አባይ ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተወጣጥቶ ጉዞ አድርጎ፣ ወደ ጣና ሃይቅ ገብቶ ነው ከዚያም ወጥቶ የሚሔደው።

“ይህች ሀገር ታላላቅ ሚስጢራት ያለባት ሀገር ነች። መንፈሳዊያን እና ታላላቅ ሰዎች የኖሩበት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ የሁሉም እናት ነች። ስልጣም የመነጨው ከአባይ ነው። አባይን ይዞ ነው ወደታች የወረደው።

“J.A ሮጀርስ የፃፈው The Real Facts About Ethiopia (እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ) የሚሰኝ ሲሆን በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የሚጠቀሰው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊያኖች ከሌላው የአፍሪካ አካባቢ ነዋሪዎች የተለዩ መሆናቸውን ጽፏል። ይሄ ልክ አይደለም። ይህ አካሄድ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ ሀገራት ፈልሰው የመጡ ናቸው ለማለት የተሰነዘረ አባባል ነው። ስህተት ነው።

“እኔ ግን ኢትዮጵያን በሙሉ ዛሬ አይቻታለሁ። ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ሔጄ ጂንካ እና አካባቢው ላይ ቆይታ አድርጌያለሁ። አብረውኝም ትምህርታዊ ጉዞ ያደረጉ ተመራማሪዎች አሉ። ሁላችንም ሆቴል ውስጥ አላረፍንም። ገጠር ጫካ ውስጥ ሔደን ነው ከሕዝቡ ጋር የኖርነው። ድንኳን ደኩነን ካምፕ ሰርተን ነው ከህዝቡ ጋር ቆይታ ያደረግነው። በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ነበርን። አንበሳና ከሌሎች እንስሳት ጋር ኖረናል።

“ከተወዳጆቹ ከሙርሲ፣ ከሀመር፣ ከማኑ እና ከሌሎች አስደናቂ የደቡብ ሕዝቦች ጋር ቆይታ አድርገናል። ብዙ ታሪክ ያለበት 15ሺ ዓመታት በላይ አስደማሚ ትንግርቶችን መጥቀስ የሚቻልበት ቦታ ነው። በኩሺያቲክ ማህበረሰብ ስልጣኔ እና ታሪክ ውስጥ ተዘውትረው የሚነሱ ጉዳዮችን ነው በዚህ አካባቢ ያገኘነው። ስለዚህ ይህ ቦታም ቢሆን መንፈሳዊ ቦታ ብሎም የፈጣሪያችን ስፍራ ነው።

በሙርሲዎች በሀመሮች እና በሌሎም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ውስጥ ያየሁት ያገኘሁት ጥናት አስደናቂ ነው።

ይህን በኢትዮጵያ ሀገራችን ላይ ሰፊ ጥናት አድርጎ ለዓለም የምሁራን አደባባይ ላይ የሚያስተዋውቀው ዶ/ር አሸራ ኪዊዚ ብዙ ጥቁሮች በተለይ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከ150 ዓመታት በፊት በባርነት ተግዘው በመሄዳቸው ምክንያት የማንነት እጦት ዋነኛው ችግራቸው መሆኑን ተረድቶ ጥናት አቅርቧል። ጥቁሮች ስልጣኔ የላቸውም፣ ማንነታችሁ አይታወቅም፣ የምዕራባዊያኑ አለም ጥቁር ሊያሰለጥን ነው ወደ አፍሪካ የሄደው የሚሉትን አባባሎች ሁሉ ስህተት መሆናቸውን ለማሳየት ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጎ የቀደምት ስልጣዎች መገኛ መሆኗን ለማስረዳት የቻለ አፍሪካን አሜሪካዊ ነው።

እንደ እርሱ ገለፃ ኢትዮጵያ በደቡብም ሆነ በሰሜን በምስራቅም ሆነ በምዕራብ ያሏት ህዝቦች በቋንቋ ረገድ የኩሽ፣ የሴሜቲክ፣ የኦሞቲክ እና የኒሎ ሳሃራን ተናጋሪዎች መሆናቸውን፣ ባህላቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ፍልስፍናቸው ሁሉ የረቀቀ ገና አጥንተን ያልጨረስናቸው ታሪካዊ ህዝቦች ናቸው በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

(31፡12 -31፡25)

ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶች፣ ቋንቋዎች፣ ህዝቦችና ባህሎች መገኛ ከመሆኗም በላይ የክርስትና፣ የእስልምና እና የጁዳይዝም እምነቶ የረጅም ዘመን ባለቤት ሆና የኖረች ሀገር መሆኗን ተናግሯል።

(35፡26 – 35፡45)

ከዚሁ የኢትዮጰያ ጥንታዊ ታሪክ ተመራማሪው ከዶ/ር አሸራ ንግግር መረዳት እንደሚለው ግሪኮች በጥንት ዘመን በሰሩት የአፍሪካ አህጉር ካርታ ላይ ኢትዮጵያ የሚል ስም አስቀምጠው ነበር ይላል። የአፍሪካ አህጉር በኢትዮጵያ ይጠራ እንደነበር ተመረማሪው ያስረዳል። ሌላ በጣም አስገራሚው ጥናቱ ደግሞ ዛሬ አትላንቲክ ውቅያኖስ ብለን የምንጠራው የውሃ ክፍል በጥንት ዘመን ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይሄው ተማራማሪ ከጥንታዊ ማስረጃዎች ጋር ቶሮንቶ ካናዳ ውስጥ ኒዮርክ ዩኒቨርስቲ ለተሰባሰቡ አፍሪካ አሜሪካዊያን ማህበረሰቦች አቅርቦታል።

ዱሪሴላ ዱንጂ ሀውስቶን የተባለችው ታሪክ ፀሐፊት ቀደም ባለው ዘመን `Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushitic Empire` (የጥንታዊ ኩሽቲክ ስርዓት መንግስት ባለቤት የሆኑት አስደናቂዎቹ ኢትዮጵያዊያን) በተሰኘው መፅሐፏ ውስጥ ኢትዮጵያ ለግብጽ መፈጠር፣ ለሌሎች የአረብ ሀገራና የመካከለኛው ምስራቅ መነሳሳት፣ ብሎም ደግሞ ወደ ሩቅ ምስራቅ ማለትም እስከ ህንድ አገር ድረስ ለጥቁር ህንዶች መፈጠር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ድሩሴላ ፅፋ ነበር። ዶ/ር አሸራም ይህን መጽሐፍ መሠረት በማድረግ ዛሬ ያለችው የተሰራችው ወይም የተፈጠረችው አባይ ይዞት በሔደው አፈር ነው። አባይ ግብጽን ፈጥሯል ባይ ነው።

     በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ሁለት ባልና ሚስት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ እና ታላቅነት ለሶስት ሰዓታት በፈጀው ንግግራቸው በቶሮንቶ ካናዳ ዮርክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አቅርበውታል። የጥናታቸው ውጤትም አያሌ ምሁራንን ያስደሰተ እና ለኢትዮጵያ ሀገራችን ገጽታ ግንባታም በእጅጉ ይጠቅማል። ፊልሙን እንደ ባህልና ቱሪዝም ያሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከባለቤቶቹ ጋር በመነጋገር ለሀገሪቱ ጥቅም በሰፊው ሊያውሉት ይችላሉ።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
17513 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us