በኢትዮጵያ ተራሮች ውስጥ ያለው ምስጢር

Thursday, 05 February 2015 11:53

በጥበቡ በለጠ  

ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔዎቿን አደማምቀው ከሚያሳዩላት አያሌ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የኪነ-ሕንፃ ጥበቦቿ ናቸው። ከዛሬ ሦስት ሺ ዓመታት በፊት የተገነቡት ከተማዎችና ኪነ-ሕንጻዎች በየጊዜው እንደ ብርቅ እየታዩ በመምጣት ላይ ናቸው።

በቅርቡ እንኳ የቢቢሲ ቴሌቭዥን ድረ-ገፅ ባወጣው የፎቶ ዜና በዓለማችን ላይ ሊታዩ የሚገባቸው ብሎ ያተተው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙት ጥንታዊ ኪነ-ህንፃዎችና አብያተ-ክርስቲያናት ነው። እንደ BBC ገለፃ ትግራይ ውስጥ የሚገኘው ገራእልታ ተብሎ የሚታወቀው የተራሮች ጥልፍልፍ ተፈጥሮ ውስጥ ለአያሌ ዘመናት ተገንብተው የሚገኙት አስደማሚዎቹ አብያተ-ክርስትያናትን የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲጎበኛቸው ሲገልፅ ቆይቷል። ለመሆኑ እዚህ ጎራእልታ ተብሎ በሚታወቀው የአያሌ ተራራዎች ሕብረ ውበት ውስጥ ያለው ተአምር ምንድን ነው?

በዚህ ገራዕልታ ተብለው በሚታወቁት ተራሮች ውስጥ አያሌ አብያተ-ክርስትያናት ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩበት ቦታ ነው። ተራሮቹ በውስጣቸው ጥንታዊ ስልጣዎችን፣ ኪነ-ሕንጻዎችን፣ ቅርሶችን ይዘዋል። የሰው ልጅ አለትን እንደ ወረቀት እያጣጠፈ ህንፃ እየገነባ ያሳየባቸው ቦታዎች ናቸው።

በገራዕልታ ተራሮች ውስጥ ቀሳውስት ከሺ ዓመታት በላይ ዘምረውበታል፣ ቀጽለውበታል፣ አስተምረውበታል። የኢትዮጵያ ቅርስ እና ማንነት ጠብቀው አኑረውበታል።

ዛሬ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ቱሪስቶች ሲጓዙ ገራዕልታ ተራሮች ውስጥ ያሉትን እነዚህን ተአምረኛ ኪነ-ህንጻዎች ይጎበኛሉ። ላላየውም እዩ እያሉ ያስተዋውቃል።

ባለፈው ዓመትም አንድ አስገራሚ ዜና ስለነዚሁ ተራሮች ውስጥ ስላለው ምስጢር በዓለም አቀፍ ሚዲያ ተዘግቦ ነበር። ዘጋቢው ደግሞ The Observer የተሰኘው ጋዜጣ ሲሆን በፌብሩዋሪ 2012 ዕትሙ ላይ ከዛሬ ሦስት ሺ ዓመት ቀደም ብሎ ስለተከናወነ አንድ አስገራሚ ጉዳይ ይዞ ወጥቶ ነበር።

የጋዜጣው ዘገባ እንደሚያብራራው ከሆነ አንዲት ሉዊስ ሾፊልድ የተባለች አርኪዮሎጂስት (የስነ-ቁፋሮ ባለሙያ) ከለንደን ተነስታ ወደ ገራዕልታ አካባቢ ለጥናትና ለምርምር ሔዳ ነበር። እዚያም ባካሔደችው ጥናት የገራዕልታ አካባቢ ከሦስት ሺ ዓመታት በፊት ወርቅ እየተቆፈረ የሚወጣበትና ከፍተኛ ሀብትና ንብረት ያለበት ቦታም መሆኑን ጠቁማለች። እንደ ሾ ፊልድ ጥናት በአፈ-ታሪክ ውስጥ ጉልታ የምትታወቀው ንግስተ ሣባ ወደ እየሩሳሌም ከጠቢቡ ሰለሞን ዘንድ ስትሔድ ወርቅ አስወጥታ የሔደችበትን ቦታ ገራእልታ ውስጥ አገኘሁት ብላ በአብዘርቨር ጋዜጣ ላይ ዜናው ወጥቷል።

አብዘርቨር ጋዜጣ የአርኪዮሎጂስቷን የሉዊዝ ሾፊልድን ፎቶ እና ከበስተጀርባዋ ደግሞ የገራእልታን ተራራ ምስሎች ይዞ ወጥቷል። ይህ ዜና ትልቅ ጉዳይ ነበር። ነገር ግን ጉዳዩ ብዙም ሳይወራለት ድብስብስ ብሎ ቀርቷል። ተመራማሪዋ ሉዊስ ሾፊልድ በግኝቷ ላይ የበለጠ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋትና ይህንንም ገንዘብ አርኪዮሎጂን ከሚደግፉ ተቋማት ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ሴትየዋ ውሸቷን ነው፤ ገንዘብ ልትበላበት ነው እያሉ ወሬ በመናፈሱ ምክንያት ሾፊልድም ከጥናቷ ሰብሰብ ብላለች። ይህች ሉዊስ ሾፊልድ ቀድሞ ለንደን ውስጥ በሚገኘው በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ በአስጎብኚነት የምትሰራ ባለሙያ ነበረች።

ጀርመናዊው ኢኖ ሊትማን ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ወደ አክሱም አካባቢ መጥተው በከተማዋ ውስጥ ስለሚገኙት ታላላቅ እና አስደማሚ የድንጋይ ጥበቦችን አጥንተው ለዓለም ሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው። ኢኖ ሊትማን አክሱምን አጥንተው Expedition of Axume የሚለውን መፅሐፋቸውን በተከታታይ አሳትመዋል። የእኚህ ሰው መፃህፍት ዛሬም ድረስ በውድ ዋጋ የሚሸጡና በአክሱማዊያን ጥንታዊ ስልጣኔ ላይ የሚደረገውን ጥናትና ምርምር የሚያግዙ ሆነው እንደቀጠሉ ናቸው። አክሱም በዓለማችን ላይ ከነበሩ አራት ታላላቅ መንግሥታት መካከል አንዱ እንደነበር የኢኖ ሊትማን ጥናት ይገልጻል።

ከኢኖ ሊትማን በኋላም አያሌ ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ጥንታዊ ማንነታችን ሲፈተሹ እና ለዓለምም ሲያስተዋውቁልን ቆይተዋል።

ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት የሆነችው እንግሊዛዊቷ ሲልቪያ ፓንክረስትን የሚያክል የኢትዮጵያ ወዳጅን ማግኘት ይከብዳል። ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ፋሽስቶች በተወረረችበት ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰች ሴት ስትሆን፣ እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎችም ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ትልቅ ውለታ ያበረከተች ነበረች። የኢትዮጵያን አርበኞች እና ታጋዮችን ስትረዳ ቆይታ በኋላም ፋሽስቶች እንዲወድቁ ከፍተኛ የአርበኝነት ሥራ ያከናወነች እንግሊዛዊት ነች። ከፋሽስቶች ውድቀት በኋላም ከነ ቤተሰቦቿ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለዚህች ሀገር መልሶ መገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታ አልፋለች።

ሲልቪያ ከሰራቻቸው ታላላቅ ጉዳዮች መካከል ከ700 ገፆች በላይ የያዘ የኢትዮጵያን ማንነት እና ታሪክ ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቀውን መፅሐፍ አሳትማለች። መፅሐፉ Ethiopia:- A cultural History ይሰኛል። የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ጥንታዊ መሆኑን እና ዓለም ሳይነቃና ሳይሰለጥን ይህች ሀገር ይሔ ሁሉ ተአምር አላት እያለች መላዋን ኢትዮጵያ ያስተዋወቀችበት መፅሐፍ ነው።

ይህ መፅሐፍ ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለይም በአውሮፓውያን እና በአሜሪካዊያን ዘንድ የበለጠ እንድትታወቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበር አያሌ ሰነዶች ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉትን ጥናትና ምርምሮች የበለጠ እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ሰፊ ድርሻ ተወጥቷል። መፅሐፉ ቀደም ሲል ሌሎች የውጭ ሀገር ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ የተዛቡ መረጃዎችን የሰጡባቸውን ገለፃዎች ሁሉ ያረመ እና ትክክለኛ መረጃ ያስቀመጠ ነበር።

ሲልሺያ ፓንክረስት ከዚህ Ethiopia፡- A cultural History ከሚሰኘው መፅሐፏ ሌላ አያሌ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን ለዓለም የሚያስተዋውቁ መፅሐፍትን በማሳተም ፈር ቀዳጅ እንግሊዛዊት ነበረች። ለኢትዮጵያ ሐገራችን ያላት ፍቅር ከምንም በላይ ሲሆን ኑሮዋንም፣ ሞቷንም ሆነ ቀብሯን እዚሁ የኢትዮጵያ አፈር ይብላኝ ብላ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቿ ጋር በቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን ፍትሃት ተደርጎላት ስርዓተ ቀብሯ የተፈፀመላት ሴት ናት።

ሲልቪያ ፓንክረስት ካስተዋወቀቻቸው የኢትዮጵያ ታላላቅ ቅርሶች መካከል የቅዱስ ላሊበላን ትንግርታዊ እና ምስጢራዊ ኪነ-ሕንጻዎችን ነው። Rock Churches of Labibela Grait Wonders of the world ብላ አያሌ ፅሁፎችን ለዓለም ህዝብ አበርክታች። ፅሑፏን ወደ አማርኛ ስንመልሰውም “የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት የዓለማችን ትንግርታዊ ኪነ-ህንጻዎች” እንደ ማለት ነው።

በነዚህ በላሊበላ ኪነ-ህንጻዎች ላይ የሰራችው ጥናት እስከ ዛሬ ድረስ የሚመጡ ተመረማሪዎች ዋነኛው የጥናት ዋቢያቸው አድርገውት የሚጠቀሙበት ታሪካዊ ሰነድ ነው።

በዚህ ፅሁፏ ውስጥ ጥንታዊ የፅሁፍ ሠነዶችን፣ የቤተ-ክርስትያን መረጃዎችን፣ የኪነ-ህንፃ ባለሙያ ጥናቶችን፣ ከዚህ በፊት ስለ ላሊበላ የተፃፉ መፃህፍትን በሙሉ ሰብስባ በማንበብና በመረዳት ከዚያም የራሷን አዳዲስ ግኝቶችን ይዛ ለህትመት አብቅታለች።

ለምሳሌ ከጠቃቀሰቻቸው አዳዲስ ነገሮች ውስጥ አንዱ የላሊበላን ኪነ- ህንጻዎች የሠራቸው ማን ነው የሚል አነጋጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ይገኝበታል።

ሲልሺያ ፓንክረስት ስለ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ከመፃፉ በፊት ይታመን የነበረው እነዚህን ተአምራዊ ኪነ-ህንፃዎችን የሰሯቸው የውጭ ሀገር ሰዎች ናቸው ተብሎ ነበር። በርካታ የውጭ ሀገር ፀሐፊዎችና እንዲሁም በቀደመው ዘመን የነበሩ የሀገር ውስጥ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደገለፁት የላሊበላን አብያተ-ክርስትያናት ያነጿቸው ከውጭ ሀገር በተለይ ከእስራኤልና ከግብፅ ብሎም ከሌሎች ሀገራት የመጡ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች ናቸው ብለው ፅፈው ነበር።

ሲልቪያ ፓንክረስት የነዚህን ፀሐፍት ገለፃዎች አያሌ ማስረጃዎችን በማቅረብ ውድቅ አድርጋቸዋለች። እንደ ሲልቪያ ገለፃ እነዚህን ኪነ-ህንጻዎች የሰሯቸው ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ምክንያቷ ደግሞ ከላሊበላ በፊት ከአንድ ሺ ዓመታት ጀምሮ ከአለት እየፈለፈሉ ቤት መስራት፣ አብያተ-ክርስትያናትን ማነፅ የኢትዮጵያዊያን ልዩ ችሎታ ነው። እንዲህ አይነት ኪነ-ህንጻዎች ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም የአለማችን ክፍል አይገኙም ብላለች። ይህንንም አባባሏን የምታጠናክረው፣ እሷ ራሷ እንደ ላሊበላ አይነት ኪነ-ህንፃዎች ሌሎች ሀገራት ውስጥ መኖርና አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ዓለምን ዞራለች። በመጨረሻም አንድ ድምዳሜ ላይ ደረሰች። የላሊበላ ጥበብ የኢትዮጵያዊያን ብቻ የሆነ ጥበብ ነው። በየትኛውም የዓለም ጥግ ይህ ጥበብ የለም ብላለች ሲልቪያ። 

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
13394 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us