የኢትዮጵያ የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ በዮሐንስ አድማሱ

Wednesday, 18 February 2015 13:56

     ዮሐንስ አድማሱ

     ዮሐንስ አድማሱ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ባለቅኔ ነበር። እጅግ ምናባዊ ጥልቀትና የገዘፈ ሀሳብ ያላቸውን ግጥሞችን በመጻፍ ይታወቃል። በአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ ውስጥ ተወዳጅ የስነ-ጽሁፍ መምህርም ነበር። ከነዚህ ሙያና ተሰጥዎቹ በተጨማሪ ጎበዝ ሃያሲ ነበር። በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውሰጥ ካበረከታቸው አያሌ ጉዳዮች መካከልም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

1.  ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ አጭር የህይወትና የጽሁፉ ታሪክ

2.  ጠባሳው (ያልታተመ አጭር ታሪክ)

3.  ጠገራው (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

4.  ውርርዱ (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

5.  ከራኒው (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

6.  የቼሆቭን The Lament የተሰኘ አጭር ልቦለድ በ1962 ዓ.ም ሰቆቃው ብሎ ተርጉሟል

7.  የዶስቶዬቭስኪን The Brothers Karamazove የተሰኘውን ልብ-ወለድ ተርጉሟል።

ሌሎችንም በርካታ ስነ-ጽሁፋዊ ውለታን ለሀገሩ አበርክቶ ያለፈ “ተወርዋሪ ኮከብ” (shooting Star) ነበር።

ከአያሌ ስራዎቹ መካከል በግንቦት ወር 1961 ዓ.ም በመነን መጽሄት ላይ የልቦለድ ሥነ-ጽሁፍ ጉዞ በሚል ርእስ ሂሳዊ ደሰሳ አድርጎ ነበር። ጽሁፉ በርካታ የአትየጵያን ልቦለዶች በተለይ ከ1963 ዓ.ም በፊት የነበሩትን ምሁራዊ ድፍረት በተሞላበት ብእር በሚከተለው መልኩ ጽፎት ነበር።

     ሥነ ጽሁፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኀይል ግዘፍ ነሥቶ፣ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነ ጽሑፍም ምንጩ የሰው ልጅ እውነታ (ሪያሊቲ) ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋ ህላዌ ነው።

     ሥነ ጽሑፍ ጠቅላላ ዓላማው ማስደሰት ነው። ይኸንንም ጉልህ ዓላማ የሚፈጽመው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕይወት ሒስ በማቅረብ ነው። ሥነ ጽሑፍ ጉልህ ዓላማውን ለመፈጸም ጥራትና ወጥነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። “በኖኅ ዘመን በቀን ብዛት፣ የማይነቅዝና የማይሻግት፣” መሆን አለበት። አለዚያ አጉል ጉሕና ወይንም ብስና እንጂ ሥነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም። ሥነ ጽሑፍን ሥነ ጽሑፍ የሚያደርገው የደራሲው የኪነት ኀይሉ፣ የማስተዋልና የማንጠር ስጦታው፣ ያስተዋለውንና ያነጠረውን ከሰው ልጅ እውነታ ጋራ በቋንቋ ኀይል አገናዝቦና አዋሕዶ እነሆኝ ብሎ የሚያቀርብበት ልዩ ችሎታው ነው። ግልብ ደራሲ ግልብ ተመልካች ነው። ጽሑፉም በዚያው ልክ ግልብ የችርቻሮ ጽሑፍ ይሆናል። 

     ይህን አባባል መሠረት በማድረግ ከሰላሳ ሶስት እስከ ሰላሳ አንድ ዓመተ ምሕረት ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነገር ለማውሳት እወዳለሁ።

     በጠቅላላው በነዚህ በሃያ ሰባት አመታት ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነ ጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፣ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት፣ (አስቀያሚነት ውበት ነው ወይንም ውበት አለው ካልተባለ በቀር) ከሥነ ጽሑፋዊ እውነት ይልቅ የአንቀጸ ብጹዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነ ጽሑፍ የሕይወት ሒስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሆኗል። እስከ አሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው። የጎድን ነው። አቅጣጫም ያለው አይመስል። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም፤ እስከ አሁን ድረስ ተመልክተን የተገነዘብነው አካሄዱ አብነት ለመሆን የሚችል አይደለም። በአጭሩ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፤ ቀደም ካለው የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ አዝመራ ጋራ ሲነጻጸር ደረጃው፣ ጥራቱና ወጥነቱ፣ በዚያውም መጠን ውበቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው።

  እያደር ይጫጫል፣ እየሰነበተ ይደገድጋል፣ እየባጀ፣ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ ከቶም ድቀታዋ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ጠቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሞ ጥራት፣ ወጥነት፣ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጽሐፍት መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሁለቱ መጻሕፍት “እንደ ወጣች ቀረች” እና “ፍቅር እስከ መቃብር” ናቸው። (ከነዚህ ከሁለቱ ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች መጻሕፍትም በመጠኑ አሉ።)

     እነዚህ ሁለቱ መጸሕፍት የኪነት ውጤት ናቸው። ጥልቀታቸውም፣ ውበታቸውም፣ ሌላውም መልካም የምንለው ጥራታቸውም ከዚሁ ከኪነት መንፈሳቸው ይሠርጻል። በ“ቴክኒክ” (ቅርጽ) በኩል ከሞላ ጎደል ምሉዕ ናቸው። በትልም፣ በባሕርያት አቀራረጽ፣ በአተራረክ፣ በቋንቋ... ወዘተ። እነዚህ ሁለት የልብ ወለድ መጻሕፍት በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች የሰነዘርኋቸውን ሐሳቦች በሙሉም ባይሆን በከፊል አቀናብረው ይዘዋል። ሁለቱም ሁለት ልዩ እውነታ ያቀርባሉ። በአንድ ነገር ይተባበራሉ፣ ይገናኛሉ። ሁለቱም ያቀረቡልን የሕይወት ሒስ ነው። ሁለቱም በየገጾቻቸው በሚገኙት ቃላት ኀይል እንድናዳምጥ፣ እንዲሰማን፣ በተለይም እንድናይ ለማድረግ ሞክረዋል። ይኸም ሙከራቸው በሙሉም ባይሆን በከፊል ስለተቃናላቸው የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ በዚህም እኛ አንባቢያኑ ሐሴት እናደርጋለን።

     በጠቅላላው ከስልሣ ሶስት ዓመተ ምህረት ወዲህ ጥሩ የምንላቸው የአማርኛ (የኪነት) መጻሕፍት ጥቂት ናቸው። ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ “ብላሽ” ናቸው።

     ለምን?

     ደራሲያኑ በደፈናው ወይንም በጠቅላላው ልዩ ልዩ የኪነት ጽሑፍ ቴክኒክ አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጨነቁም። ጽሑፋቸውን የቴክኒክ ግብዝነት አለልክ ያጠቃዋል። የጽሑፍ ቴክኒክ ለኪነት ጽሑፍ አብይ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። የሀገራችን የኖረ፣ የቆየ የጽሑፉ ቴክኒክ አለ፤ የውጭ ሀገርም የፅሑፍ ቴክኒክ አለ። ደራሲያኑ የውጭውንም ሆነ የሀገራችን የፅሑፍ ቴክኒክ አብስለው እና ጠንቅቀው አያውቁትም።

     በሀገራችን (ለምሳሌ ያህል) የታወቀ፣ የተለመደ፣ ከሙያ የዋለ የገድል አፃፃፍ ቴክኒክ አለ። ገድል የአንድ ሰማዕት ወይም የአንድ ፅድቅ የሕይወት ታሪክ ነው። ገድል በጠቅላላው የሚያወጋው ወይም የሚተርከው የሰማዕቱን ወይም የጻድቁን ተጋድሎ ነው። ስለ ሰማያዊ ልዕልና፣ ለሰማያዊ ክብር መንፈሳዊ የሆነ ምድራዊ ተጋድሎ። አተራረኩ ከመንፈሳዊ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። ትልም እና ባህሪያት የአተራረክ ስልትም አለው። የአተራረክ ፈሊጥም አለው። ብሎም “ገድለ ተክለ ሐይማኖትም” መጥቀስ ይበቃል። አንቱ የሚባል ወይም ለመባል የሚሻ ደራሲ የገድልን አጻጻፍም አጥርቶ ማወቅ ግዴታው ነው። ብዙ ነገር ይማራል፣ አያሌ ጥበብ ይቀስማል። በቴክኒክ ይበለፅጋል።

     የቅኔ ቴክኒክ አለ። ይኽንንም ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፣ በተለይም የገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው። (የቀረውን እንዳለፈው ያነቧል።) ሌሎችም ብዙ የጽሑፍ ቴክኒኮች በሀገራችን በብዛት ይገኛሉ፣- የተረት፣ የሙሾ፣ የእንቆቅልሽ፣ የእንካስላንትያ፣ የቀረርቶ… ወ.ዘተ። እነዚህን ሁሉ አንቱ የሚባል ወይም ለመባል የሚሻ ደራሲ አጠናቆ ማወቅ ግዴታው ነው።

     ከውጭም አለም የተገኙ የጽሁፍ ቴክኒኮች አሉ። የተውኔት የረዥም ልብ ወለድ የአጭር ልብ ወለድ ወዘተ። ደራሲዎቻችን የውጭውንም የጽሑፍ ቴክኒክ አጥርተው አያውቁትም። በአጭሩ የሚጽፉት አገኝ አጣቸውን ነው፤ የሚጽፋት በንዝሕላልነት ብዙ ጊዜም በግዴለሽነት በማን አለብኝ መንፈስ ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙ መጻሕፍት አሉ። ለጊዜው ግን አንዱን መመልከት ይበቃል። “አድልዎን በሰይፍ” መጽሐፋ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ “ብላሽ” ነው” ። ጉድለቱን ጉልህ አድርጎ ማሳየቱ ነው ታሪኩ የሚተረከው በአንደኛ መደብ ነጠላ ቁጥር /እኔ/ ነው። አንድ ታሪክ በአንደኛ መደብ መተረክ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ታላቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አደገኛ ነው። በተለይ ለጀማሪ ደራሲ ክፉ አዚመኛ አንጋዳ ነው። እላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ በአንደኛ መደብ ይተርክና መጽሐፉ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው ”ሞትኩ” ይላል። ይኸን የሚለው የታሪኩ ዋና ባሕርይ ነው። “ሞትኩ” ካለም በኋላ ታሪኩን ይተርካል። ሙቷል በዓፀደ ሥጋ አይገኝም ማለት ነው። ይኸ ንስሐ የሌለው ታላቅ የቴክኒክ በደል ነው። እንደዚህ ያለው በደል የሚፈጸመው ምናልባት ካለማወቅ ይሆናል፣ ምናልባትም ከንዝሕላልነት ወይንም ከንቀት ምክንያቱ የትኛው እንደሆነ አላውቅም። ከደራሲው ጋር መነጋገር ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል። ይኸንና ይኸንን የመሰለ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መጻሕፍት እጅግ ብዙ ናቸው። የሚከተሉትን ይመለክቷል፡- “ውብ ነበረች፤ ሥራ ገንዘቡና ጓደኛው”፤ “የጉድጓዱ ምስጢር”፤ “ንስሐ”፤ “እውነት ስትጠፋ” ፤“የሐሳብ እስረኛ”፤ “ከማን አንሼ”፤ “እኛም ይድረሰን..ወዘተ” እነዚህ ጥቂቱ ናቸው።

     የዘመናችን ደራሲያን በጽሑፍ ቴክኒክ በኩል ከሀገራቸውም አልሆኑ፣ ከውጭውም አልሆኑ። የሀገራችንንና የውጭን አዳቅለውም መጢቃ ቴክኒክ አላቀረቡልንም። ወይንም ከሁለት አንዱን ብቻ ተከትለው ወጥ ጽሑፍ አላበረከቱም። እስከ አሁን ድረስ ቴክኒካቸው ውጥንቅጥ የልብ ትኩሳት የልብ ቃር የሚሆን አጉል ቅይጥ ነው። ከሥርዓት ይልቅ ምስቅልቅል የሰፈነበት ነው።

     ምናልባት ከዚህ ውጥንቅጥ ከዚህ ምስቅል ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ ቴክኒክ እንደ ብሂል እንደ ሠረዝ እንደ ጎዳና ቅኔ ያለ ይፀነስ ይሆናል። ይኸ መቸም ምኞት ነው። ምኞቱ እውት እንዲሆን የኔ ብቻ ሳይሆን ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማደግ መዳበርና ኃይል መሆን የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ነው።

     ሁለተኛው ነቁጥ የሒስ ጥበብ አለመለመድና የሐያሲ አለመኖር ነው። በባህላችን የሒስ ሰዎች አሉ። ከዚህም የተነሣ ደራስያኑ መጻሕፍታቸው በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ሲተቹ /በቀጥተኛ ሒስ/ አንዳንዶቹ ያኩርፋሉ፤ አንዳንዶቹ ይዝታሉ፤ አንዳንዶቹ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ይሳደባሉ፤ ይኸ መንፈስ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ጉዳዩ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ይሁን እንጂ አንድ የማውቀው ነገር አለ። ሒስ በቅኔ ቤት የተለመደ ነው። የቅኔው ተማሪ ከቅኔው ትምህርት ሌላ በጥበቡ የሚጎለምሰው የኪነት ተውህቦውን የሚያተባው የሚያራቅቀውና የሚያደረጀው በሒስ ጥበብ ነው። የተማሪውን ቅኔ የቀለም ጓደኞቹና መምህሩ ይተቻሉ። እሱም እንደዚሁ ያደርጋል። ተማሪዎቹ የመምህራቸውን ቅኔ ይተቻሉ። አንዳንዴም ብትንትኑን ያወጡታል። ኩርፊያና ስድብ ዛቻና ቅያሜ የለም፤ ይህ መልካም ጥበብ እያለ ደራስያናችን ለምን በሒስ /በደንበኛ ሒስ/ ይቆጣሉ።

     ሒስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛና ፍቱን መድኃኒት ነው። ሒስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው። ማስተማሪያም ነው። እንደ ስድብ እንደ ነውር መቆጠር የለበትም። በሒስ መስተዋትነት ስኃውን የማይከላ ሥነ ጽሑፍም ሆነ ደራሲ ከበድን አንድ ነው። ተገቢ ቦታውም ቤተ መዘክር ነው።

     ሶስተኛ ነቁጥ፤ ያለፋት የሃያ ሰባት ዓመታት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሶስተኛ ጉድለቱ የቋንቋ ነው። በጠቅላላው ቋንቋው ውበት ጥራትና ተጠየቅ የተለየው በፀያፍ /ሰዋሰው/ የተበከለ በቃላት እጥረት የተሞሸረ ነው። ይኸን ጉድለት የፈጠሩ ደራስያኑ ናቸው እንጂ ቋንቋው አይደለም። ቋንቋው ማለፊያ ባለሙያ ልባም ደራሲ ካገኘ ብዙ ሰንፍ የሚያስገባ አይመስለኝም። ለዚህም አብነት የሚሆኑ የሚከተሉት ቀደምት ደራስያን ናቸው። አፈወርቅ ገብረእየሱስ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብላቴንጌታ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አለቃ ታዬ፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ወዘተ። በመጻሕፍት በኩል /እላይ የተጠቀሱት ደራስያን ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ/ መጽሐፈ መነኮሳትና አርባዕቱ ወንጌልን መመልከት ይበቃል።

     የአሁኑ ዘመን ደራስያን አማርኛ ለምን ተበላሸ? በዚሁስ የሚቀጥለው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያት መስጠት ይቻላል። አንደኛ ደራስያኑ ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ጥሩ አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም። ሁለተኛ ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም። ጥሩ ጥሩ የሆኑ ተነበው በቋንቋቸው ጥራት በዘይቤያቸው ውበት የሚለዩ መጻሕፍት ጠፍተው አይደለም አሉ። ከፍ ብዬ የጠቀሰኋቸው መጻሕፍት ጥቂቱ ናቸው፤ እነሱን የመሳሰሉ በብዛት አሉ። ፈልጎ ማንበብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መጻሕፍቱን የጠቀስኳቸው ስለ ይዞታቸው ሳይሆን /ይዞታቸውን የማይፈቅዱ ይኖሩ ይሆናል/ በጠቅላላው ስለቋንቋቸው ጥሩነት ነው፤ ስለምናባቸው /ኢማጂኔሽን/ ስፋት ነው፤ ስለ ዘይቤያቸው አስገራሚትና ውበት ነው። ዛሬ ያሉንም ሆኑ ወደፊት የሚነሱት ደራስያን እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት በየጊዜው ቢያነቡ ቋንቋቸው ይዳብራል፤ አስተሳሰባቸው ይተባል፤ ሐሳባቸውን -ጃ ሳይላቸው እንደ ልባቸው መግለጽ ይችላሉ። የማይሰለች ለዛና ወዝ፣ ውበትና ጥራት ያለው “ዞሌ” ጽሑፍ መጻፍ ይችላሉ።

     የጽሑፌ ኃይለ ቃል በድርሞ መልክ የሚከተለው ነው። በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጠቅላላው ጥራቱና ወጥነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። ይኸው የሆነበት ምክንያት

ሀ/ በቴክኒክ ጉድለት

ለ/ በሒስና በሐያሲ እጦት

ሐ/ በደራስያት አማርኛ መበላሸት

      ከነዚህም ምክንያቶች ለሁለቱ  ለ “ሀ” ና ለ “ሐ” ኃላፊዎቹ በከፊል ደራስያኑ ናቸው። አያነቡም፤ የማወቅና የማጥናት ጉጉት የላቸውም። ለሁለተኛው ምክንያት “ለ” ኅላፊነታቸው ኢርቱሀ ነው። ሒስ አለመቀበላቸው ወይንም በሒስ መበርገጋቸው።

     የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተፅእኖው ለመላው ዓለም እንዲተርፍ ከተፈለገ ደራስያናችን /ዛሬ ያሉትም ሆኑ ወደፊት የሚሱት/ ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። የተጋድሎ ጎዳና ረዥም ሁኖ ጎዳጉድ የበዛበት፤ ቅርቅፍት ነው፤ ተስፋ የመቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደጥንታውያኑ ለሀገራቸው ነጻነት ሕይወታቸውን በየጎራው በየሜዳው በየአረሁ እንደሰውት ኢትዮጵያዊን አባቶቻችን ባጭር ታጥቆ የሥነፍሑፍ ዘገር ነቅንቆ፤ የሥነ ጽሑፍ ጋሻ መክቶ ለሥነ ጽሑፍ መጋደል የየአንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው።

      ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሰልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

      (የዚህ ሂስ አቅራቢ ዮሀንስ አድማሱ በአጸደ ስጋ የኖረው ከመስከረም 1929 እስከ ሰኔ 1967 ዓ.ም ነበር።

ይምረጡ
(21 ሰዎች መርጠዋል)
15988 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us