የአድዋ ድል እና ይህ ዘመን

Wednesday, 04 March 2015 13:42

በጥበቡ በለጠ  


ከትናንት በስቲያ የአድዋን ድል 119ኛ ዓመት በዓልን አከበርን። በዚህ ወቅት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእግራቸው ለአያሌ ቀናት ሲጓዙ ቆይተው የአድዋ ተራራ ላይ ደርሰው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ተክለው አውለበለቡ። በዓሉን ከአካባቢው ሰዎች ጋር ሆነው አደማመቁት። ይህን የወጣቶቹን ጉዞ ከሚያስተባብሩት መካከል አንዱ የሆነው የኬር አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት መሐመድ ካሣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ‘ሄሎ ሌዲስ’ በተሰኘው ፕሮግራም ከአድዋ ተራራ ላይ ሆኖ ቃለ-መጠይቅ ይደረግለት ነበር። በዚህ ቃለ-መጠይቁ መሐመድ ካሣ ሲናገር፣ በዓሉ በጣም ደማቅ እንደነበርና ብዙ የአክሱምና የአድዋ ብሎም ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት ታድመውበት ስለነበር በእጅጉ እንዳስደሰተው ገለፀ። በመቀጠል ግን የተናገረው ነገር ቆንጠጥ የሚያደርግ ነበር። ይህም ስለ ኢትዮ-ቴሌኮም ጉዳይ ነበር። ኢትዮ-ቴሌኮም በሀገራችን ውስጥ ልዩ ልዩ በዓላት ሲከበሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀድሞ ይልክ ነበር። ነገር ግን በዚህኛው የአድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እስከ አሁን ድረስ አልላከም፤ ግን መላክ ነበረበት የሚል ሃሳብ ያለው መልዕክት መሐመድ ካሣ ከአድዋ ተራራ ላይ አስተላለፈ።

ይህን ጉዳይ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ነበር በመኪና ውስጥ የሰማሁት። ሁሉም ጓደኞቼ ‘ግን እውነት ቴሌ ምን ነካው?’ ማለት ጀመሩ። መሐመድ ቴሌን ሲወቅስ ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ይሆናል። ከዚያም 30 ደቂቃዎች ባልሞሉበት ጊዜ ውስጥ ቴሌ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላከ። ነገሩን በጥሞና አሰብኩት።

እውነት ቴሌ ለምን እስከዚያ ሰዓት ድረስ መልዕክት አልላከም? አድዋ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል ሆኖ ሣለ ጉዳዩ ለምን ተዘነጋ እያልኩ አሰብኩ። ሌላው ጉዳይ ቴሌን የቀሰቀሰው መሐመድ ካሣ ነው ወይ? ብዬም አሰብኩ። ምክንያቱም መሐመድ ከተናገረ በኋላ ቴሌ መልዕክቱን ላከ። አንድ ነገር ደግሞ ደስ አለኝ። ይሄ የመሐመድ ካሣ ቅሬታ ወዲያው መልስ ማግኘቱ።

ከሁሉም ነገር በላይ ግን ትልቁ ጥያቄ አድዋ የሚዘነጋ በዓል ነው ወይ የሚለው ነው። አድዋ ከኢትዮጵያዊያን ሁሉ አልፎ የጥቁር ሕዝብ በሙሉ መኩሪያ መመኪያ ከሆነ ከመቶ ዓመታት በላይ ቆይቷል። ጥቁሮች ለነፃነታቸው ያደርጉ የነበሩት ትግል አድዋን መሠረትና መነሻ በማድረግ ነበር። ጥቁር ከታገለ ማሸነፍ እንደሚችል ፅኑ እምነት የተጣለበት የድል ቀን ነው።

ለዚህ ጉዳይ አንድ ምሣሌ ላስቀምጥ። ወደ ደቡብ አፍሪካ ልውሰዳችሁ። በአንድ ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለትምህርት በተጓዝኩበት ጊዜ አያሌ አብያተ-ክርስትያናት በኢትዮጵያ ስም እንደሚጠሩ ለመገንዘብ ቻልኩ። ጉዳዩን በዝርዝር ለማወቅ ያጓጓል። እንዴት በደቡብ አፍሪካዊያን ሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ተገለፀ? የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ ተመላለሰ። ሌሎችም እጅግ የሚገርሙ ነገሮችን በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል የተገማመዱ የተሳሰሩ ገጠመኞችን አስተዋልኩ። እናም የነዚህን ምክንያት እየመረመርኩ ለበርካታ ጊዜያት ቆይቻለሁ።

የአድዋ ድል በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን ሲበሰር፣ ደቡብ አፍሪካዊያን በነጭ የአፓርታይድ መንግስታት ግፍ እየተፈፀመባቸው ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቆይተዋል። ልክ የአድዋ ድል የዓለም ዜና ሲሆን፤ የደቡብ አፍሪካውያን ትኩረት ኢትዮጵያ ሆነች። ጥቁሯ ኢትዮጵያ የነጭ ወራሪዎች እንዴት አሸነፈች? እንዴት ድል አደረገች? ምስጢሩስ ምንድን ነው? ብለው ደቡብ አፍሪካዊያን ማጥናት ጀመሩ።

ከጥናታቸው ውስጥ ያገኙት አንዱ ውጤት ሃይማኖት ነበር። የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ፅኑ የሃይማኖት ፍቅር ስለነበራቸው በእምነታቸው ውስጥ የነበሩትን ታቦታት ተሸክመው ወደ ጦር ሜዳ ተጉዘው ነበር። ታቦታቱን የያዙበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንደኛውና ዋነኛው ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ከተሸነፈች በተለይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖቷ ይጠፋል። አዲስ የቅኝ ገዢዎች ሃይማኖት ይስፋፋል። ስለዚህ ታቦታቱ ራሳቸው የእምነቱ ፅኑ መገለጫዎች ስለሆኑ ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባለው ምድር የመንፈስ ተራዳኢነታቸውን ከአርበኞቹ ጋር ሆነው እንዲሰጡ ተፈለገ። ስለዚህ ከፀሎት ከምህላ ከቅዳሴ ጋር ታጅቦ የአድዋ ተራሮች ከጦርነቱ በፊት አርበኞች ከፈጣሪያቸው ዘንድ መንፈሣዊ ብርታትን ለማግኘት ፀለዩ። በጦርነቱም ወቅት በግማሽ ቀን ውስጥ ድልን ተጐናፅፈው አስደናቂ ታሪክ ሰሩ።

ይህ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካዊያን ትልቅ ትርጉም ነበረው። እምነት፣ ፅናት፣ መንፈሣዊነት የሚል ፍልስፍና ውስጣቸው ገባ። ስለዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሆኑ። ይህ ሃይማኖት አፍሪካዊ ነው፤ የጥቁር ሃይማኖት ነው የሚል የራሳቸውን ትርጓሜ ሰጡት። በዚህ ምክንያት ነው እስከ አሁን ድረስ ያሉት እነዚህ አብያተ-ክርስትያናት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት። እነርሱም፡-

  1. African United Ethiopian Church
  2. The Ethiopian Mission in South Africa
  3. National Church of Ethiopia in South Africa
  4. St. Philip’s Ethiopian Church of South Africa
  5. Ethiopian Church Lamentation in South Africa
  6. Ethiopian Church of God the Society of Paradise

ታላቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ይህን የደቡብ አፍሪካን እና የኢትዮጵያን ትስስር ሲገልፁ ከአድዋ ድል በኋላ ከፍተኛ ተስፋ እና መነቃቃት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ መታየቱን “Ethiopian Echoes in Early Pan-African Writings” በተሰኘው ጥናታቸው ያወሣሉ። ከአድዋ ድል ማግስት ጀምሮ የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ተረቶች እና ሥነ-ጽሁፎች የታሪክ መዋቅራቸው ሁሉ ተቀይሯል። በነጭ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮችና ደህንነቶች የሚፈለጉ የልቦለድ ገፀ-ባህሪዎቻቸው ሁሉ የሚሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ እንደሆነ መፃፍና መተረክ ጀመሩ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነፃነት ሀገር ስለሆነች፣ ነጮች ጥቁሮችን ሊይዙ ሊያስሩ የማይችሉበት ምድር ስለሆነች - ነፃ መውጫ አገር አድርገው ሳሏት።

በጣም የሚያሳዝነው ነገር፣ ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተከሰተውን ወዳጅነት ትኩረት አለመስጠቷ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች ተደጋጋሚ የሆነ የግንኙነት መረብ ዘርግተው ቢሆን ኖሮ መላው ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የሃይማኖቱ ተከታይ ይሆኑ እንደነበር የሚገልፁ በርካታ ጥናቶች አሉ። አሁን ደግሞ ይህን የደቡብ አፍሪካውያንን ስሜት በመገንዘብ የማኅበረ ቅዱሳን ምሁራን አባላት ወደዚያ በመጓዝ በሚሰጡት ትምህርት ትልልቅ ለውጦች እየመጡ መሆኑን መረዳት ችያለሁ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በሰፊው ያስተዋወቀ የታሪክ ክስተት ነው። ራይሞንድ ጆናስ የፃፈው “The Battle of Adwa African Victory in the Age of Empire” የሚለው መፅሐፍና በሙሉ ቀን ታሪኩ የተተረጐመው አፄ ምኒልክ እና የአድዋ ድል በተሰኘው መፅሐፍ እንደተጠቀሰው፣ ‘አትላንታ ኮንስቲቲዩሽን’ የተሰኘው ጋዜጣ መጋቢት 4 ቀን 1896 እ.ኤ.አ. ‘የጣሊያን ክፉ ዕጣ’ በሚል ርዕስ ከ3ሺ በላይ የኢጣሊያ ወታደሮች በአድዋ ጦርነት ማለቃቸውን ዘግቧል።

ኒውዮርክ ወርልድ እና ቺካጐ ትሪቢውን የሚሰኙት የዘመኑ ዓለም አቀፍ ጋዜጦችም የአድዋን ድል ለዓለም አሰራጭተዋል። መጽሐፉ ሲገልፅ፣ እንደ ዛሬው ‘ታይም መፅሔት ሁሉ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ‘ቫኒቲ ፌይር’ ታዋቂ መፅሔት ነበር። በ1897 እ.ኤ.አ. ቫኒቲ ፌይር የፊት ገፁ ላይ የአፄ ምኒልክን ምስል ይዞ በመውጣት ንጉሡን ለመላው ዓለም አስተዋውቋቸዋል።’ ከቻርልስ ዳርዊን፣ የሩሲያው አሌክሳንደር፣ ናፖሊዮን ሳልሳዊ እኩል የአፄ ምኒልክ ፎቶግራፍ ተከትሎ አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከዓለም ታዋቂ ግለሰቦች ተርታ ተሰለፉ።

ከዚሁ ጋር በመለጠቅ በርካታ አውሮፓውያንም አዳዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ልጆቻቸው “ምኒልክ” የሚል ስም ሰጧቸው ሲል Raymond Jonas በመፅሐፉ ውስጥ የገለፀውን ሙሉቀን ታሪኩ ተርጉሞ አስነብቦናል። ከዚሁ ከአድዋ ድል በኋላ አንዳንድ ደብዳቤዎች ንጉሡን የገንዘብ ውለታ የሚጠይቁም ነበሩ። አንዲት አድናቂያቸው በፃፈችላቸው ደብዳቤ አፄ ምኒልክ ለጅምር መኖርያ ቤቷ ማስጨረሻ የሚሆን 200 ፍራንክ እንዲልኩላት ጠይቃቸውም ነበር።

“የምኒልክ እና የጣይቱ የዓለም አቀፍ ዝና በጨመረ መጠን በርካታ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው መነሳት ጀምረውም ነበር። ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የአፍሪካ ልዕለ-ኃያል እየሆነች ነው? ፖለቲካዊ ድሉ የኢትዮጵያ የንግድ ትንሳኤ መነሻ ይሆን? የይሁዳ አንበሳ ነገድ የሆኑት አፄ ምኒልክ የመላው ጥቁር ሕዝብ መሪ መሆን ይችላሉ?” የሚሉት ጥያቄዎች የልዩ ልዩ ፀሐፊያን የመከራከሪያ አጀንዳዎች ነበሩ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ከቅኝ አገዛዝ በትር የተላቀቀችበት ቀን ነው። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በማንም ነጭ ጦረኛ ያልተገዙበትን ታሪክ እንዲናገሩ ልሣን የሆናቸው ቀን ነው። የአድዋ ድል በብዙ ሺ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት የተገኘ የመስዋዕትነት ነፃነት ነው። ታዋቂዋ ድምፃዊት፣ በአድናቂዎቿ አጠራር “ባለቅኔዋ ድምፃዊት” እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ አድዋ በተሰኘው ድንቅ ሙዚቃዋ ‘ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ’ እያለች እነዚያን የነፃነት ሰማዕቶችን ትዘክራቸዋለች። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ1950ዎቹ አድዋ ምርጥ ግጥም ፅፏል። በመድረክ ባይታይም ቴአትርም ምኒልክ በሚል ርዕስ ፅፏል። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ Adwa:- An African Victory የተሰኘ ፊልም ሰርቷል። ቴዲ አፍሮም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት ብዙ ወጪ በማውጣት የአድዋን ጀግኖች ዘክሯል። በዚህ ረገድ ጳውሎስ ኞኞን ሳልረሳ በርካታ ከያኒያንና ከያኒያትን መጠቃቀስ ይቻላል። እነርሱ አድዋን ለትውልድ አስተላልፈዋል። ዋናው ጥያቄ አሁን ላለው ትውልድ አድዋ ምኑ ነው? የሚለው ነው።

የአድዋ ድል ታስቦ ብቻ የሚውል በዓል ነው። ጉዳዩ ግን ትልቅ ትርጉም አለው። ልክ እንደ ሌሎቹ በዓላት ሕፃናት ተማሪዎቻችን በየትምህርት ቤቶቻቸው ሊያከብሩት የሚገባ ነው። ዩኒቨርሲቲዎችና ትልልቅ የእውቀት ተቋማት ውይይቶችና ጥናቶችን የሚያቀርቡበት ቀን መሆን ይገባዋል። ምክንያቱ ደግሞ ያ የአድዋ ድል የዛሬ ነፃነታችን መገለጫ ቀን በመሆኑ በየዓመቱ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባዋል ብዬ በግሌ አስበዋለሁ። ይህን የምልበት፣ በዚህ የድል ቀን ላይ ተመርኩዘው የፃፉ ታላላቅ የዓለማችን ታሪክ መርማሪዎች ሁሉ እንደሚጠቅሱት ከሆነ ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ግርማ ሞገስ የምታገኝበት የድል ቀኗ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም እንደሆነ በሰፊው ይገልፃሉ። ታዲያ ይህን ቀን ሰፊ ትኩረት ብንሰጠው መላው ጥቁር ሕዝብ በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየጐረፈ የነፃነት ደሴቱ ላይ ፈልሰስ ብሎ እንዲሄድ ማድረግ ይቻል ነበር።

ትልቁ ታሪካችን፣ ትልቁ ማንነታችን እንዳይከሰስ፣ ግርማ ሞገሱ እንዳይከስም ከሁላችንም ብዙ ነገር ይጠበቃል። በተለይ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እና ኮሌጆቻችን፣ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ አድዋ ላይ ልዩ ዝግጅት ቢኖራቸው ጥቅሙ ለሀገርና ለሕዝብ ነው። የሀገራችንንም የታሪክ፣ የባሕል፣ የነፃነት፣ የአርአያነት ተምሳሌት በሰፊው ያሳያል ብዬ አምናለሁ። ምስጋና ለአድዋ ጀግኖች ይሁን! 

Last modified on Wednesday, 04 March 2015 13:47
ይምረጡ
(17 ሰዎች መርጠዋል)
14028 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us