መምህር ግርማ ወንድሙ እና የሚያባርሯቸው ሰይጣኖች

Wednesday, 11 March 2015 12:47

በጥበቡ በለጠ


በቅርቡ በወጣው የአብነት አጐናፍር የሙዚቃ አልበም ውስጥ አንዲት ዘፈኑ ትገርመኝ ነበር። ይህችም ዘፈኑ “ሲነግሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ” የምትል ተደጋጋሚ ዜማው ናት። እናም ብዙ ታሳስበኝ ነበር። ለምንድንነው እየነገረኝ ውሎ ሳልሰማ የምገባው? እያልኩ አሰብኩ። መስማት ከሌለብኝ ለምንድንነው የነጋሪውንም የራሴንም ጊዜ የማቃጥለው? መስማት ከሌለብኝ ለምን ቁጭ ብዬ አዳምጣለሁ? ወይስ ቁጭ ብዬ እንድሰማ የሚያሳድደኝ ነገር አለ? እያልኩ ስለዘመኔ ሁኔታ አሰላሰልኩ። ሳሰላስል ቆይቼ መምህር ግርማ ወንድሙን አሰብኳቸው። በማዕረግ ስማቸው መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ ነው የሚባሉት። በተለምዶ ግን ሰዎች “መምህር” ይሏቸዋል። የእርሳቸውን ልዩ ልዩ ሲዲዎች በተለያዩ ጊዜያት አይቻለሁ። ሰምቻለሁ። ግን ምንም አላልኩም። አይቼም ሰምቼም ዝም ነው ያልኩት። “ሲነግሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ” ይሆን እንዴ ነገሩ? ብቻ፣ ዛሬ ግን፣ ስለእኚሁ መምህርና ድርጊት ብሎም እየሰሩ ስለሚገኙት “ተአምራዊ ጉዳይ” ጥቂት ነጥቦችን አነሳስቼ ከዚያም ለሁላችንም እንደመወያያ ይሆነን ዘንድ ሀሳቤን ክፍት አድርጌ አልፌዋለሁ።

መምህር ግርማ ወንድሙ በተለያዩ አብያተ-ክርስትያናት ቅፅር ግቢ ውስጥ እየተገኙ ያስተምራሉ፣ በመለጠቅም ሰዎች ከያዛቸው ክፉ መንፈስ ያላቅቃሉ። ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት ባሳተሟቸው ሲዲዎች ውስጥ መመልከት ይቻላል። መቼም የሰው ልጅ በክፉ መንፈስ ተሳስሮ መከራውን ሲያይ ቆይቶ በኋላም ከዚያ እጅና እግሩን ከያዘው እርኩስ መንፈስ፣ ከዚያ ክፉ ከሚያሳስበው እርጉም ቁራኛ ከሆነው መንፈስ፣ በስቃይ ሀበላ ከሚንጠው የመከራ ሸክም ከሆነው መንፈስ ከመገላገል የበለጠ ትልቅ ተግባር የለም። ሰዎች ሲፈወሱ ማየት በራሱ ያስደስታል። የመምህር ግርማ ወንድሙ ድርጊትም በአብዛኛው የፈውስ መርሃ ግብር ስለሆነ ከዚህ አንፃር እወደዋለሁ። ነገሩ እየቆየ ሲመጣ ግን አንዳንድ ጥያቄዎችም በውስጤ ማደግ ጀመሩ።

የመጀመሪያው ጥያቄ መምህር ግርማ ወንድሙ ሰይጣንን እያሰቃዩት፣ እያስፈራሩት፣ በአደባባይ እያወሩት፣ እየጠየቁት፣ በመጨረሻም ሲያባርሩት በተቀረፁት ሲዲዎቻቸው አማካይነት መገንዘብ ይቻላል። ግን መምህር ግርማ ከዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ የኃይማኖት አባቶች መካከል ሰይጣንን እንዲህ አድርጐ የመደብደብ፣ የማዋራት፣ የመመርመር እና በሰይጣን የተለከፉ ሰዎችን የመፈወስ ፀጋ እንዴት ተጐናፀፉ ብዬ እጠይቃለሁ። ጥያቄው ለራሴ ነው። በዚህች ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ብዙ አባቶች መጥተው አልፈዋል። አሁንም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳት፣ ባሕታውያን፣ ሊቀ-ጳጳሳት ወዘተ አሉ። እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ለፈጣሪያቸው ክብር የሚፀልዩ፣ የሚጾሙ ፍፁም ክርስትያን የሆኑ አያሌ ብፁአን አባቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ታዲያ መምህር ግርማ ወንድሙ ለየት ባለ መልኩ ጐላ ብለው ወጥተዋል። የሰው ልጆችን ሁሉ ወደ ሐጢያት መንገድ የሚመራውን ሰይጣን እያሽቀነጠሩ ሲያባርሩ በየአውደ ምህረቱ እናያለን። ይህ መቼም ትልቅ መሰጠት ነው። ይህን ሁሉ ሰይጣን የማተራመስ ኃይሉን እንዴት አገኙት እያልኩ አስባለሁ።

ሁለተኛው ጥያቄዬ፣ መምህር ግርማ ወንድሙ ከልዩ ልዩ ሰዎች ውስጥ የተጠናወታቸውን ሰይጣን ሲያስወጡ እንመለከታለን። ለመሆኑ የወጣው ሰይጣንስ የት ነው የሚሄደው? ከአንድ ወጥቶ ወደየት ይሄዳል?

ሦስተኛው ጥያቄዬ፣ በየአውደ ምህረቱ ሰይጣን አለበት ተብሎ የሚወጣው፣ የሚለፈልፈው፣ በስቃይ ውስጥ ያለው ሕዝብ ብዛቱ የትየለሌ እየሆነ እየመጣ ነው። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ይህ ሁሉ ሰይጣን የሰፈረባቸው ሕዝቦች ናቸው ወይ? ኢትዮጵያዊያን ይህን ሁሉ ሰይጣን የተሸከሙ ሰዎች ከሆኑ ሀገሪቱ ላይ ራሱ ሰይጣን ሰፍሯል ማለት ነው። እናም ሰይጣኑን ከሀገሪቱ ላይ ለመንቀል መፀለይ ይሻላል ወይስ በየአውደ-ምሕረቱ እያንዳንዱን ሰው እየጠሩ ‘ልቀቀው’ ማለት ይሻላል? እያልኩ አስባለሁ።

አራተኛው ጥያቄዬ፣ ሰይጣን ሰፍሮባቸዋል ተብለው ወደመድረክ ወጥተው የሚናዘዙት ሰዎች በአብዛኛው የተማሩ፣ ትንሽ ላቅ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው፣ በማኅበራዊ ኑሯአቸው ቀናዎች፣ የተሻለ ማሰብና መተግበር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አብዛኛዎቹ ሐጢያት ያልሰሩ ናቸው። ሰይጣናዊ ድርጊት ውስጥ ያልገቡ ናቸው። በዚህች ሀገር ውስጥ ታላላቅ ወንጀሎችን የሚሰሩ ሰዎች ሰይጣን ይዞኛል ብለው ሳይለፈልፉ እንዴት እነዚህ የዋህ ኢትዮጵያውያን በሰይጣን ተለከፉ እያልኩ አስባለሁ።

የሰውን ልጅ ያጠፉ፣ የገደሉ፣ ዘር የጨፈጨፉ፣ ያሰደዱ፣ ያሰሩ፣ ያሰቃዩ… ሐጢያተኞች ሳይለፈልፉ እንዴት እነዚህ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ይለፈልፋሉ እያልኩ አስባለሁ። እጠይቃለሁ።

አምስተኛው ጥያቄዬ፣ ክርስትያን መሆን ጥቅሙ ምንድንነው? ሰዎች ክርስትያኖች ሆነው፣ እያመኑ፣ እየፀለዩ፣ እየጾሙ ለሰይጣን ጥቃት የሚጋለጡ ከሆነ መፍትሔው ምንድን ነው? መምህር ግርማ ወንድሙ ባይኖሩ ኖሮ ያ ሁሉ ሰይጣን የተጠናወተው ክርስትያን ምን ይሆን ነበር እያልኩ አስባለሁ፤ እጠይቃለሁ።

ስድስተኛው ጥያቄዬ፣ የመቁጠሪያው ጉዳይ ነው። መምህር ግርማ ወንድሙ ሰዎችን ከሰይጣን ሲያላቅቁ ሁሌም ከእጃቸው ትልቅ መቁጠሪያና አነስተኛ መስቀል አይለይም። መቁጠሪያውንም በታማሚው አንገት ላይ ያንጠለጥላሉ። ለመሆኑ መቁጠሪያ ኃይል አለው ወይ? ሰዎችን ከሰይጣን የመገላገል ልዩ ፀጋ አለው ወይ? እያልኩ እጠይቃለሁ፤ አስባለሁ።

በርግጥ መምህር ግርማ ወንድሙ በ2005 ዓ.ም በሳተሙት “በማለዳ መያዝ የክፉ መንፈሶች ድርጊት” በተሰኘው መፅሐፉቸው ውስጥ በገፅ 155 ላይ ስለ መቁጠሪያ የሚከተለው ተፅፏል፡-

“በቤተ-ክርስትያናችን ካህናትና በንስሐ አባቶቻችንና በተባረከ መቁጠሪያ፤ በእግዚአብሔር አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእመቤታችን ድንግል ማርያምና በቅዱሳን መላእክት ስም፤ ሁለቱ ትከሻዎቻችን መሃል፤ ጀርባችንን እንዲሁም፤ ሕመም የሚሰማን ቦታ ስንቀጠቀጥ፤

  • የማቃጠል ወይም የመለብለብ፤ የመውረር ወይም የመንዘር፤
  • የመብላት ወይም የማሳከክ፤ ከአንዱ ሰውነት ክፍላችን ወደ ሌላው የመዞርና፤ እንደ ድንጋይ በድን መሆን እንዲሁም፤
  • ጭንቅላታችንን ሁለት ከፍሎ፤ የራስ ምታት ዓይነት ስሜት ከተሰማን፤ ሰይጣን በውስጣችን አለ ማለት ነው”

በማለት መምህር ግርማ ወንድሙ ጽፈዋል። አያይዘውም መፍትሔውንም በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውታል።

“የእግዚአብሔርን መንገድ ይዘን፤ እየጾምን እየፀለይን፣ እየተባረክን፣ እየሰገድን እና ሥጋና ደሙን እየወሰድን ከላይ እንደተገለፀው በመቁጠሪያችን እየቀጠቀጥን ክፉ መንፈሶችን በመታገል የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንችላለን።”

ይላሉ። እኔ ግን መምህር ግርማ እርኩስ መንፈሶችን የሚታገሉበት ይህ መቁጠሪያ ከዚህ ከላይ ከገለፁበት በተሻለ ማብራሪያና ትንታኔ ቢያክሉበት የተሻለ ነው እላለሁ።

በርግጥ ጥያቄዎቼ ብዙ ቢሆኑም፣ ሁላችሁንም ላለማሰልቸት ሲባል እዚህ ላይ ልግታቸው። ነገር ግን ጥያቄዎቹ ለመምህር ግርማ ብቻ የቀረቡ አይደሉም። ስለ ሃይማኖት አውቃለሁ፤ ተምሬያለሁ፤ መንፈሶችን መርምሬያለሁ መረጃ መስጠት እችላለሁ የሚል ሁሉ ተጠይቋል፤ እንዲፅፍም ተጋብዟል።

መቼም በዚህች የሦስት ሺ ዓመት ታሪክ አላት እያልን በምናወድሳት ሀገር፣ ክርስትናንም ሆነ እስልምናን በመቀበልና በማስፋፋት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ በምናሰልፋት ኢትዮጵያ ላይ፣ ልዩ ልዩ ድንቅዬ አብያተ-ክርስትያናት፣ ገዳማት፣ አድባራት በሚገኙባት ኢትዮጵያ፣ አያሌ ብፁአንና ቅዱሣን በተፈጠሩባትና ገቢረ-ተአምራት በሰሩባት ኢትዮጵያ፣ ይህ ሁሉ የኃይማኖት ድርሳናት በተፃፉባት ኢትዮጵያ ላይ የሰይጣን ድርጊትና ኃይል ይህን ያህል ሰፍሮ ከተስተዋለ ሀገሪቱ መላዋ ፀሎት ያስፈልጋታል። ከሰይጣን የሚያላቅቃት እምነት ያስፈልጋታል።

እርግጥ ነው ከባሕል ትምህርቶች ዘርፍ ውስጥ አንዱ መንፈሣዊነት ነው። በሃይማኖቱም ረገድ ትልቁ ጉዳይ መንፈሣዊነት ነው። መንፈሣዊነት ደግሞ የበጐና የርኩሰት ተብሎ ቢከፈልም በየትኛውም የባሕልና የእምነት ትምህርቶች በተደጋጋሚ የሚሰበከው በጐ መንፈሳዊነት ነው። ትውልድ የሚታነፅባት፣ ሀገርና ወገን የሚያድግባት፣ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት የሚዳብርበት መንፈስ በዚህች ሀገር ላይ እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል። ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት፣ ከባሕል ተመራማሪዎችና ከሁሉም ዜጋ ብዙ ይጠበቃል።

እንደ መምህር ግርማ ወንድሙ መፅሐፍ ገለፃ ከሆነ ደግሞ እዚህ ኢትዮጵያችን ውስጥ ለአያሌ ክፉ መንፈሶች ተጋልጠናል። ከእነዚህም ውስጥ፡- የዛር መንፈስ፣ የዓይነ-ጥላ መንፈስ፣ የዝሙት መንፈስ፣ የቡዳ መንፈስ፣ የግፍ መስተፋቅር መንፈስ፣ የዓውደ ነገሥት መንፈስ፣ የፃረ-ሞት፣ የሙት ጠሪ መንፈስ (ኤኬራ ዲቢፍቱ)፣ የሥነ-ልቦናና የፍልስፍና መንፈሶች፣ የአንደርቢ መንፈስ፣ በመተት የሚላኩ፣ የተባይና የነፍሳት ወረራ፣ የንቅሳቶች መንፈስ፣ የሰላቢ መንፈስ፣ የቁራኛ መንፈስ፣ የአዚም መንፈስ፣ ሱሉስ የዝውውር መንፈስ፣ ሟርት፣ መተት፣ አስማት፣ ድግምት እና ሌሎችም እርኩስ መንፈሶች በሀገራችን ውስጥ እንዳሉ ፅፈዋል። ከዚህ ሁሉ አደገኛ መንፈሶች ለመዳን ደግሞ ከእምነት ተቋማት ምን ይጠበቅ? ከእያንዳንዱ ግለሰብ ዘንድ ምን ይደረግ? መንግስትስ ምን መስራት አለበት? ማኅበራዊ ተቋሞቻችንን እንዴት እንመስርት ወዘተ የሚሰኙት ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይቻላል።

በአጠቃላይ ግን፤ ድህነት፣ ረሃብ፣ መሃይምነት በእጅጉ ነግሶባት የምትገኘው ሀገራችን ላይ፣ ይህ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ደግሞ ተጠናውቷት ካለ ጉዳዩ አስቸጋሪ ነው። በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ልዩ ልዩ የፀበል ቦታዎች ላይ የማያቸውን የአካላዊ እና የመንፈሣዊ ሕሙማንን ስቃይ ሳስተውል፣ እንደነ መምህር ግርማ ወንድሙ ደግሞ በየአውደ ምህረቱ ሰይጣን የያዛቸውን ሰዎችና ችግራቸውን ስመለከት፣ በየአብያተ-ክርስትያናቱ ጥግ ተኮልኩሎ የማገኛቸውን ነዳያንና ነዳያት (ለማኞች) ለማሰብ ስሞክር፣ በየቀኑ በየአብያተ-ክርስትያናቱ የሚፈፀሙትን የቀብር ስነ-ስርዓቶች ለመቁጠር ሳስብ፣ በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥም የፈውስ መርሃ ግብር ተብሎ ወደ መድረክ እየወጣ ተፈውሰሃል የሚባለውን ወገኔን ሳስበው፣ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ያለውን በየዓረብ ሀገራቱ የሚንገላታውን ዜጋዬን ሳስበው፣ ለመሆኑ በምን ምክንያት ነው የዚህ ሁሉ የመከራ ቀንበር ተሸካሚ የሆነው እላለሁ። ግን የሃይማኖት ተቋሞቻችን አስተምሮት፣ ፍልስፍና፣ ዶግማ፣ ቀኖና ወዘተ የሚባሉት ነገሮች በስርዓት መመርመር ያለባቸው ይመስለኛል። የተሻለ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እንዲመጣ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ምን ይሆን? ልንነጋገርበት ይገባል።

    እነ መምህር ግርማ ወንድሙም ቢሆኑ የድህነትን፣ የአስተሳሰብን፣ የመከራን፣ የእንግልትን…. ክፉ መንፈስ ከኢትዮጵያ ላይ እንዲነቀል ካልፀለዩ፤ በመቁጠሪያ ብቻ የሰውን ጀርባ እየመቱ የተሻለች ኢትዮጵያን ማምጣት አይቻልም።

ይምረጡ
(167 ሰዎች መርጠዋል)
33175 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us