ስፖንሰሮቻችን እና ማሕበራዊ ኃላፊነታቸው

Wednesday, 25 March 2015 11:29

በጥበቡ በለጠ


    በሐገራችን ኢትዮጵያ “ስፖንሰር” የሚለው ቃል በእጅጉ ተደጋግሞ መነገር ከጀመረ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። ይህ ቃል በተለይ አያሌ የመንግሥት እና የግል ኩባንያዎችን በተለይ ደግሞ የሚሸጥና የሚገዛ ቁሳቁስ ያላቸው ድርጅቶች ወደ ገበያው ለመግባት “ይህን ነገር ስፖንሰር ያደረገላችሁ. . .” እየተባሉ መተዋወቅን ስለሚፈልጉ ቃሉ በተደጋጋሚ በሕዝቡ ውስጥ እየሰረፀ መጣ። ከዚህ ሌላም ጥሩ ነገር ሲሰራ ወይም ሲታሰብ አእምሮአቸው ክፍት የሆነ ሰዎች ደግሞ ለዚያ በጎ አስተሳሰብ ድጋፍ ያደርጉና ከዚያም “ስፖንሰራችን እከሌ ነው” እየተባለ ይነገርላቸዋል። ለመሆኑ አሁን አሁን እያየነው የመጣነው የሀገራችን የስፖንሰር ሺፕ እና አንዳንዴ ደግሞ የማስታወቂያ ጉዳይስ እንዴት ነው ብለን ጥቂት ነጥቦችን ለዛሬ እንጨዋወት።

     የስፖንሰር ሺፕ ጥያቄ በአብዛኛው ተደጋግሞ የሚነሳው በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ነው። በተለይ ደግሞ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎች፣ ጥበባዊ ውይይቶች፣ አውደ ጥናቶች፣ ሲምፖዚየምና ወርክሾፖች ብሎም ሌሎችም ጉዳዮች ሲዘጋጁ ስፖንሰር የማፈላለግ ተግባር ይከናወናል። በዚህ ስፖንሰር በማፈላለጉ ስራ ደግሞ እንደ ሙያ የያዙት ሰዎች ተመድበው የኮሚሽን ተከፋይ ሆነው ይሰሩታል።

     እንደ ሙዚቃ ኮንሰርቶች አይነት በራሳቸው ገቢ የሚያስገኙ ዝግጅቶች በመሆናቸው፣ የስፖንሰሮቹ ተሳትፎ ተጨማሪ ገቢ መሰብሰቢያ ሊሆን ይችላል። በዚህም አጋጣሚ የሙዚቃውን ድግስ ድጋፍ ያደረገው አካል “ስፖንሰራችን እከሌ. . .” እየተባለ ይጠራል። ምርትና አገልግሎቱንም ያስተዋውቅበታል። አዲስ ካሴትና ሲዲ የሚያሳትሙ ድምፃዊያንና ድምጻዊያት በየከተማው ላይ ቢልቦርድ ለማሰቀል ስፖንሰር ያስፈልጋቸዋል። የኮሜዲ ሲዲዎችን የሚያወጡ የሚያሳትሙ ከያኒያንም ስፖንሰር እያፈላለጉ ነው የሚሰሩት። አብዛኛዎቹ አርቲስቶች ከፎቶዋቸው ግርጌ ወይም ጎን አንድ የሀገራችን ቢራ ተገማሽሮ ቆሞ እናየዋለን። ቢራ ፋብሪካዎቻችን ውድድር የያዙ የሚመስለውም ዘፈኖችን፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን፣ ካሴቶችን፣ ኮሜዲዎችን ስፖንሰር በማድረግ ነው። እዚህ አካባቢ ብዙ ሃሜታዎች እና ክፍተቶችም እየታዩ ነው። እከሌ ቢራ አንድ ሚሊዮን ብር ስፖንሰር አደረገኝ የሚሉ ከያኒያን እየበዙ መጥተዋል። በቢራዎችና በከያኒዎች መካከል አደገኛ የሆነ የጥቅም ትስስር ማለትም ሙስና እየታየ ነው። በቢራ ፋብሪካዎችና በአንዳንድ የጥበብ ባለሙያዎች መካከል እየተዘረጋ ያለው የሙስና ኔትወርክ ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ቸል እንዲባሉ አድርጓል። በተለይ ይህን የጥቅም ትስስር ወደፊት በዝርዝር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

    ቢራ ፋብሪካዎች ሙዚቃን ብቻ የሙጥኝ ብሎ ስፖንሰር ከማድረግም ወጣ ብለው ታላላቅ ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም መወጣት ይጠበቅባቸዋል። እንደሚታወቀው ኢንዱስትሪ ነክ ድርጅቶች ምርት በሚያመርቱበት ወቅት ተረፈ ምርቶቻቸው ለአካባቢ ብክለት ይዳርጋል። ከፋብሪካ የሚወጡት ጭስ እና ሌሎች ውዳቂ ነገሮች አካባቢ ላይ እና ዜጋ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ማምጣታቸው አይቀርም። ለዚህ ሲባል ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በየአመቱ ለማህበረሰቡ እና ለሀገር የሚበጁ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ። በውጭው አለም እንዲህ አይነት ድጋፎች “Social Responsibility” ወይንም ማኅበራዊ ኃላፊነት በመባል ይጠራሉ። በሀገራችን “ማሕበራዊ ኃላፊነት” እየተባለ ይጠራል። ለመሆኑ ፋብሪካዎቻችን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተን መወያየት እንችላለን።

     ማሕበራዊ ኃላፊነት ስንል በተለይ ለሕዝብ፣ ለሀገር፣ ለትውልድ የሚጠቅሙ እና በሰው ልጅ የአስተሳሰብና የኑሮ ሁኔታ ላይ የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግን ይመለከታል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የጥናትና የምርምር ስራዎችን መጥቀስ ይቻላል። የተለያዩ ምሁራን የሚፅፏቸው፣ የሚያሳትሟቸውና የሚያሰራጯቸው እውቀቶች ድጋፍ አድራጊ አካላት እያጡ እንዲሁ ተልኮስኩሰው የሚቀሩበት ሁኔታ እናያለን። በሀገራችን ውስጥ ያሉትን የጥናትና የምርምር ውጤቶችን የውጭ ሀገራት የተለያዩ ኩባንያዎች ድጋፍ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ኢትዮጵያዊ ኩባንያዎች በእንዲህ አይነት ለትውልድ በሚጠቅሙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን “Social Responsibility” የማይወጡት ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ መወያየት ይቻላል።

     ለዛሬ ግን ቢራ ፋብሪካዎቻችን እየበዙ በመምጣታቸውና ሌሎች ፋብሪካዎችም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ውስጥ ዋነኛዋ የንግድ መናኸሪያቸው እንደሆነች በማመን እየመጡ ስላሉ አንዳንድ ነገሮችን እያስተካከልን እንድንጠብቃቸው ለማሳሰብ ስለፈለኩ ነው። እቤታችንን ስርዓትና ደንቡን፣ አስተሳሰቡን አርቀን አበጅተን እንግዳ ካልጋበዝን፣ በተበላሸ ቤት የገባውም እንግዳ እንደተበላሸው ነዋሪ ይሆንብናል። ስለዚህ እየታዩ ያሉትን ማሕበራዊ ኃላፊነትን ያለመውጣት ክፍተቶችን ማስተካከል ግድ ይለናል።

     ኢትዮጵያ የዘፈን እና የስፖንሰር አገር ብቻ አይደለችም። ትልልቅ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ምሁራን ያሉባት፣ የጥናትና የምርምር ስራዎች የሚዘጋጁባት፣ የተለያዩ አለማቀፍ ጉባኤዎች የሚደረጉባት፣ ወደ ተሻለ ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ የገባች ሀገር ናት። ታዲያ ይህን የማሕበረሰብ ግንባታ የሚደግፉ፣ ከጎን የሚቆሙ፣ የሂደቱም አጋዥ ኃይሎች ያስፈልጋሉ።

አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ፡- ገብረ-ፃድቅ ደገፉ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ከዚህ በፊት አንድ አስደማሚ መፅሐፍ አሳተሙ። መፅሐፉ ከ400 ገፆች በላይ ያለው ነው። ርዕሱ “NILE HISTORICAL LIGAL AND DEVELOPMNTAL PERSPECTIVES” የሚል ርዕስ ያለው ነው። ይህ መፅሐፍ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዟ ላይ ከተዘጋጁ ሰነዶች መካከል ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። የታተመው በ1995 ዓ.ም ነው። መፅሐፉ የኢትዮጵያን ጥቅም በአለም አደባባይ ላይ ቆሞ ለማክበር የሚታገል፣ አባይ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ሕጋዊ የባለቤትነት ድርሻን የሚያስረዳ፣ ገና የህዳሴ ግድቡ ስራ ሳይታሰብ ቀደም ብሎ ብዙ ሃሳቦችን ያጫረ፣ ያበራ እና ያሳየ ድንቅ ሃሳብ ያለው መፅሐፍ ነው። ታዲያ ይህ መፅሐፍ ሲታተም ኢትዮጵያዊያን ኩባንያዎች አንዳቸውም ድጋፍ አላደረጉለትም ነበር።መፅሐፉ በውስጡ የያዘው የነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለችና የጎመራች እንድትሆን የብረት ማዕዘን የሆነ የአባይ ማስረጃ ያቀረበ ነበር። ታዲያ እንዲህ አይነቱን ስራ ካልደገፍን ማህበራዊ ኃላፊነት “Social Responsibility” ማለት ለኛ ሀገር ምን ይሆን? ኢትዮጵያ በዘፈን እና በስፖርት ብቻ የት ትደርሳለች?

     ዛሬም ቢሆን በዚሁ በአባይ ወንዝ ላይ ለሚቀጥለው ትውልድ የተጻፈ፣ የተሰነደ፣ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ የፅሁፍ ዶክመንት ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የሚሉ ምሁራን እና ተቋማት ድጋፍ የሚሰጣቸው ኃይል በመጥፋቱ የእውቀት ስራው እየቀጨጨ በመምጣት ላይ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ግብፆች በአባይ ወንዝ ላይ ለሚፅፍላቸው፣ ለሚያጠናላቸው፣ ትንሽም ቢሆን ድጋፍ ነገር ለሚጭርላቸው አካል የሚያቀርቡለት ልግስና በእጅጉ የገዘፈ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቆም ብለን ስለ ማህበራዊ ኃላፊነት የመነጋገሪያ ጊዜያችን መሆኑን የሚያስረዳ ቀይ መብራት በርቶብናል።

     አሁን አሁን ቢራ ፋብሪካዎችም ሆኑ ሆቴሎቻችን፣ ባንኮቻችን፣ ኢንሹራንሶቻችን፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎቻችን ወዘተ በአብዛኛው ድጋፍ የሚያደርጉት ለመዝናኛው ክፍል ነው። አንዳንዴ ደግሞ በየመንደሩ ላሉ ለአስረሽ ምቺው ዝግጅቶች ሁሉ ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች እየሆኑ ነው። በሬዲዮና በቴሌቭዥን ለሚተላለፉ ዝግጅቶች የሚደረጉ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች አብዛኛዎቹ ማህበራዊ ለውጥ፣ ሀገራዊ ለውጥና እድገት ለሚያመጡ ፕሮግራሞች አይደለም። በየኮሪደሩ ለሚደረጉ የወሬ ሽኩሽኩታዎች ብዙ ብር ሲያወጡ ይስተዋላል። ለማይመለከተን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ስፖንሰር የሚያደርጉ ግዙፍ ተቋማትን ስመለከት “እውነት ያለሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው?” ብዬም የምጠይቅበት ጊዜ አለ።

     በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ሀገር የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በF.M. ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን በኩል የሚወጣውን የስፖንሰሮች ገንዘብ ለሌላ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ፕሮጀክቶችና ስራዎች ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ሀገራችን የት በደረሰች? እያልኩ ቁጭት ይለኛል። እንግሊዞች ሀገራቸው ውስጥ ለተጫወቱት ጨዋታ የኛ ሀገር ስፖንሰሮች ይህን ሁሉ ገንዘብ በማውጣት የሚረባረቡበት ነገር ምንድንነው? ማህበራዊ ኃላፊነታቸው ለማን ነው? ለእንግሊዝ ወይስ ለኢትዮጵያ? እያልኩ አስባሁ። እስኪ ሌሎቻችሁም ይህን ሃሳብ አጠንክራችሁ ተወያዩበት።

     ጠዋት ማታ በድጋፍ አድራጊ ስፖንሰሮች ታጅቦ በጆሯችን የሚጠቀጠቅብን የእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታና ታሪክ ለዚህች ሀገር ወጣቶች የሚያመጣው ባህላዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ታሪካዊ፣ ፍልስፍናዊ ወዘተ አስተሳሰብ ምንድ ነው? በየቀኑ እንግሊዝን አልመን፣ እንግሊዝን ሰምተን፣ እንግሊዝን ተሸክመን እንድንውል እንድናድር የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ፣ በሀገራችን ያሉ ስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ሕጻናት ነገ የተሻሉ አሳቢዎች፣ አላሚዎች እንዲሆኑ ብዙም አይጥሩም። የልጆች አእምሮ ብልፅግና ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች አይደግፉም። እነርሱ ሲመጡ በጀት ጨርሰናል ይላሉ። የነ አርሴና ማንቼ. . . ጨዋታ ላይ ግን ስፖንሰር በማድረግ የልጆቻችንን ጆሮና መንፈስ ሲረብሹት ይውላሉ። አሁን አሁን ደግሞ ትውልዱን የማደንዘዝ ተፅዕኖም እየፈጠሩ መሆኑ ቀስ በቀስ እየታየ ነው። እናም ስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነት Social Responsibility ን እየተወጡ ነው ወይ?

     በስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል በአምቻና በጋብቻ፣ በትውውቅ፣ በጓደኝነት ወዘተ የመጠቃቀም ሁኔታ ነው። በከተማችን ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች የማስታወቂያና የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎች የሚሟሉላቸው ሆነዋል። እነዚህ ግለሰቦች ከመንግስት እስከ ግል ኩባንያዎች ድረስ ያሉ የግንኙነት መረቦቻቸውን ዘርግተው የማህበራዊ ኃላፊነት መወጫ መንገዱን ሁሉ እየዘጋጉት ይገኛሉ። እነዚህ ግለሰቦች የሚሰሩት ፊልም ካለ፣ ቴአትር ካለ፣ እርሱን የሚመሩት መድረክ ካለ ስፖንሰሮቹ ይጎርፋሉ። የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ማህበራዊ ኃለፊነትን መወጫ ከመሆን አልፎ ትውውቅ ሆኗል። መጠቃቀምም በእጅጉ አዘንብሎበታል። የክልልና የወረዳ ዝግጅቶች ሳይቀሩ በጥቂት ግለሰቦች እጅ ወድቀዋል። ለመሆኑ ሀገሪቷ ሌላ ሰው የላትም ወይ? የሚያሰኝ ጥያቄም የሚጠይቁ ሞልተዋል።

     አንዳንድ ኩባንያዎች ደግሞ አሉ። በራቸውን ዘጋግተው ስፖንሰር የማያደርጉ። ስፖንሰር የሚለውን ቃል መስማት የማይፈልጉ ሁሉ አሉ። በራቸው ላይ “የስፖንሰር ሺፕ ጥያቄ አናስተናግድም” ብለው የሚፅፉም አሉ። እነዚህ ኩባንያዎች አትራፊ እስከሆኑ ድረስ ማህበራዊ ሃላፊነት Social Responsibilityን የሚወጡበት ማናቸውም ሀገራዊ ጉዳይ ከመጣባቸው የመደገፍ መብትም ደምብም በሀገራችን አለ። ግን የአስተሳሰብ አድማስን ላቅ አድርጎ ከማስፋት ወደ ማጥበብ ያዘነብሉና ከሀገራዊ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለውና ሰውረው ይኖራሉ።

     በዚሁ በስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የጠያቂው ብዛትም የትየለሌ ሆኖ መገኘቱ ነው። አንዲት ትንሽዬ ግሮሰሪ ለማስመረቅ ከተነሳው ሰው ጀምሮ አያሌ ታላላቅ የሚባሉ ግለሰቦችና ተቋማትም ስፖንሰር ይጠይቃሉ። ከመብዛታቸው የተነሳም ወደ ማሰልቸት ገብተዋል። በነዚህ ስፖንሰር ጠያቂዎች መብዛት የተነሳ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሰነቁ ሃሳቦች ተመልካችና ሰሚ አጥተው መና ሲቀሩ ኖረዋል፤ አሁንም በችግር ውስጥ ናቸው።

     ይህን ስርዓት ያጣውን የስፖንሰር ሺፕ ጉዳይ የሚያቃና አንድ ጠንከር ያለ ደንብና መመሪያ ያስፈልጋል። ማህበራዊ ኃላፊነት መወጫ መንገዶች ናቸው ተብለው፣ ታውቀው፣ ተለይተው የተቀመጡ ግልፅ አቅጣጫዎች መኖር አለባቸው። በዚህች ሀገር ውስጥ የጥናትና የምርምር ማዕከሎች የሚያወጧቸው ህትመቶችና ዝግጅቶች እየቀጨጩ መጥተዋል። በአንጻሩ የእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታዎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የዓመት በአል ዝግጅቶች፣ ቀልዶች፣ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የሸቀጣሸቀጥ ኤግዚቢሽኖች እየገዘፉ መጥተዋል። የእውቀት የፈጠራ፣ የግኝት፣ የሃሳብ፣ የሥነ-ፅሁፍ፣ የባህል፣ የቱሪዝም፣ የህጻናትና የወጣቶች አእምሮ ማበልጸጊያ ላይ ድጋፍ አድራጊ አካል መንምኗል።

     በአጠቃላይ ግን ይህ ፅሁፌ በልዩ ልዩ ጉዞዎቼ የታዘብኩትና በሰነድም ከሰበሰብኳቸው ዶክመንቶች በመነሳት የፃፍኩት ነው። ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ የስፖንሰሮችን እና የሚታዩ የስህተት ድርጊቶችም አጫውታችኋለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ሀገራዊ እና ትውልዳዊ ርዕሰ ጉዳዮች በተነሱ ቁጥር የሚቻላቸውን ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ከፊት የሚሰለፉ ጥቂት ተቋሟትን ሳላመሰግን ፅሁፌን አልደመድምም። እነርሱን በርቱ እላለሁ። እውቀት ላይ፣ ትውልድ ላይ፣ ሀገር ላይ፣ ልማት ላይ፣ ምርምር ላይ፣ ጥናት ላይ፣ ባህል ላይ ወዘተ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ከላይ የሰፈረው ተጓዥ ትዝብቴ እነርሱን አይመለከትም።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
11413 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us