ኢትዮጵያዊው የታሪክ ተመራማሪ አቶ ጊጋር ተስፋዬ አረፉ

Wednesday, 01 April 2015 15:05

በጥበቡ በለጠ  

 

    የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪክ ለተቀረው ዓለም በጥናትና በምርምር ፅሁፎቻቸው ሲያስተዋውቁ የኖሩት የታሪክ ተመራማሪው አቶ ጊጋር ተስፋዬ ባሳለፍነው ሣምንት መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሕይወታቸው አልፎ በማግስቱ መጋቢት 17 ቀን በቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን መላው ቤተሰባቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ተከናውኗል።

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ጠንቅቀው ከተመራመሩ የታሪክ ሰዎቻችን ውስጥ አንዱ ነበሩ። በተለይ ደግሞ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ላስታ ላሊበላ ቡግና ወረዳ ውስጥ ሮሃ ተብላ በምትታወቀው ቦታ ላይ፣ ቅዱስ ላሊበላ ያስገነባቸውን ድንቅዬና ብርቅዬ ኪነ-ሕንፃዎችን በ1970ዎቹ አካባቢ በስፋት ካጠኑ ምሁራን መካከል አቶ ጊጋር ተስፋዬ ከፊት ተሰላፊ ነበሩ። ላሊበላን በጥናትና ምርምር ፅሁፎቻቸው ለዓለም ካስተዋወቁ ምሁራኖቻችን መካከል የሚጠቀሱት አቶ ጊጋር ተስፋዬ እስከ ዕለተ ሞታቸው ቀን ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እየተመራመሩ እያጠኑ፣ እየፃፉ የኖሩ ታላቅ ምሁር ነበሩ። በተለይ ደግሞ በስፋት የሚፅፉት በፈረንሳይኛ ቋንቋ ስለሆነ፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪው የሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያን እንዲያውቅ ማድረጋቸው ይነገራል።

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ ከዚህ በፊት በፈረንሣይኛ ቋንቋ DECOUVERTE d’ INSCRIPTIONS GUEZES á LALIBELA በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ዓመታዊ ታሪክ መጽሔት ላይ በ1980 ዓ.ም ጥናት አቅርበው ነበር። የዚህ ጥናታቸው አብይ ትኩረት በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንጉሥ ላሊበላ ራሱ ባሰራው መንበረ ታቦቶች (የታቦታት መቀመጫ) ላይ ተቀርጸው የተገኙ የፅሁፍ ሰነዶችን የሚመረምር ጥናት ነበር።

     እነኚህ የግዕዝ ፅሁፎች የተገኙት ከ1972 እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ ባከናወኗቸው የጥናትና የምርምር ሥራዎች ሲሆን፣ የተገኙትም ቅዱስ ላሊበላ ባሰራቸው፡-

  1.      ቤተ-ገብርኤል
  2.      ቤተ-ሚካኤል ወጎልጎታ
  3.      ቤተመድሃኒዓለም እና
  4.      ቤተ-ጊዮርጊስ

     ቤተ-መቅደስ ውስጥ ነበር።

     በነዚህ በላሊበላ ውቅር ሕንፃ ቤተ መቅደሶች ውስጥ ተቀርፀው የተገኙት ጥንታዊ የግዕዝ ፅሁፎች ከመሆናቸውም በላይ እነኚህን መንበረ ታቦቶች ያሰራውና ፅሁፎቹንም ያስቀረፀው ንጉስ ላሊበላ ራሱ መሆኑን በሥነ-ፅሑፍ ውስጥ የንጉሡ ስም ተፅፎ እንደሚገኝ የአቶ ጊጋር ጥናት ያሳያል።

     ከዚህ በተጨማሪም ይህ ንጉሣዊ የግዕዝ ድርሰት የዘጠኝ መቶ ሰማንያ /980/ አመት እድሜ ያለው ታሪካዊ መረጃ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በታሪክ ፀሐፊዎች ዘንድ ከዚህ በፊት ያልታወቀና ምንም አይነት ጥናትና ምርምር ያልተደረገበት እንደሆነም በወቅቱ ተገልጿል።

     ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በአክሱም ዘመነ መንግሥት ከአራተኛው እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ክልል ውስጥ በአክሱም ሐውልቶች ላይ ተቀርፀው ከሚገኙት ጥንታዊ የግዕዝ ፅሁፎች በስተቀር እስከ አሁን ድረስ በዛጉዌ ዘመነ-መንግሥት፣ በላሊበላ ጊዜ ተቀርፆ ከተገኘው ሌላ ምንም መረጃ ያለመኖሩ ይገልፃል። ስለዚህ አቶ ጊጋር ያጠኗቸው ፅሁፎች በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት ተቀርፆ የተገኘ የመጀመሪያው የፅሁፍ መረጃ ሲሆን፣ ከዋንዛ እንጨቱ ላይ ተቀርፀው የተገኙ አዲስ አይነት የእንጨት የፅሁፍ ቅርፆች መሆናቸውም ተገልጿል።

     በታቦት መንበር ላይ ከ800 ዓመታት በላይ ተፅፎ የተገኘው ይህ የላሊበላ ፅሁፍ በኢትዮጵያ በሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ አዲስ ሰነድ ያዘለ ፅሁፍ እንደሆነ አቶ ጊጋር ይገልፁ ነበር። የሥነ-ፅሁፍ ብዛትም ሆነ በታሪክ አንፃር ሲገመገም ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ስመ ጥሩ የኢትዮጵያ ንጉሥ ኢዛና በጥንታዊ ኢትዮጵያ መዲና ላይ ካስቀረፀው ከጥንታዊ ግዕዝ ሥነ-ፅሑፍ ቀጥሎ በላስታ መካነ ሮሃ ውቅር ህንፃ ውስጥ ተቀርፆ የተገኘው ፅሑፍ ቀደምትነት ካላቸው የታሪክ መረጃዎች አንዱ ነው ይባላል።

     ከመንበረ ታቦቶቹ ላይ ቅዱስ ላሊበላ በግዕዝ ቋንቋ የፃፈውን አቶ ጊጋር ከነ ትርጓሜው በአማርኛም በፈረንሳይኛም ተርጉመው አቅርበውት ነበር። ለምሳሌ ይኸው ጥበበኛ ንጉሥ የፃፈው በቤተ ጊዮርጊስ የታቦት መንበር ላይ የፃፈው እንዲህ ይላል፡-

     “ማርያም ድንግል ለመስቀል ክብሯ እና ለኔ ለላሊበላ በምህረቱ ብዛት ይቅር እንዲለን ከልጅስ ዘንድ አማልጅን” ይላል። (መስቀል ክብሯ የላሊበላ ባለቤት ነች)

     በሁለተኛ የተፃፈው በቤተ-ሚካኤል ጎልጎታ ውስጥ በአገኘሁት መንበረ ታቦት ላይ የተቀረፀው ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ይላል፡-

     “እኔ ላሊበላ ኃጢያተኛና በደለኛ የሆንኩኝ ይህንን ታቦት ለአንተ ብዬ ያሰራሁት መንበረ ታቦት ነው። ስሟንም የክርስትያን ሰንበት ብዬ የሰየምኩት እኔ ነኝ። አቤቱ ፈጣሪ ለአንተ ብዬ የደከምኩትን የድካሜን ዋጋ ከንቱ አታድርግብኝ”

ብሎ ላሊበላ ራሱ ከ800 ዓመታት በፊት የፃፈውን የአቶ ጊጋር ጥናት ያሳየናል። 


 

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አያሌ የምርምር ጽሁፎችን ከማቅረባቸውም በላይ የቅዱስ ላሊበላ ኮነ-ሕንፃዎች አሰራርን በተመለከተ ዲዛይኑ የተሰራበትን ሰነድ በመመርመር ወደር ያልተገኘለትን ማስረጃ ያቀረቡ ሰው ነበሩ።

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ ከወራት በፊት በሬዲዮ ፋና አዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ላይ ቀርበውም ስለ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሰራር ምስጢር አብራርተው ነበር። ለመሆኑ የአቶ ጊጋር ተስፋዬ የታሪክ ምርምርና ጥናት ከየት መጣ? የት ተወለዱ? የት አደጉ? ምን ተማሩ?

     የሕይወት ታሪካቸው እንደሚወሳው የአቶ ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል እና የወይዘሮ ፍሰሐ ሐውኩ የሥጋ ልጅ የሆኑት አቶ ጊጋር ተስፋዬ፤ ትውልደ ሀገራቸው ትግራይ “ማውርኤ እስጢፋኖስ” በሚባል ቦታ ሲሆን፣ ዘመነ ልደታቸው 1934 ዓ.ም ነው። ፊደል፤ ንባብ፣ ግብረ ዲቁና፣ የቅዳሴ ዜማ፣ የቃል ትምህርት፣ ሰዋሰው እና በመጠኑ ትርጓሜ መፅሐፍትን ለትምህርት በደረሰ አቅማቸው የተማሩት፣ ዲቁና ተቀብለው የቀደሡት ሚስጢር ያገመሩት ከትግራይ ጥንታዊያን ገዳማት አንዱ ሆኖ በሚታወቀው በታላቁ የጉንዳጉንዲ ገዳም ነው። ዕድሜ ልካቸውን ሲመረምሯቸው የቆዩትን ጥንታውያን የግዕዝ ድርሳናት እና የድንጋይ ላይ ፅሑፎችን ለመተንተን የሚያስችላቸውን የግዕዝ እውቀት መሠረት ያገኙትም፤ በዚሁ በጉንዳንጉንዲ ገዳም ነበር።

     ኢትዮጵያዊውን የቤተክርስቲያን ጥንታዊ ትምህርት በእንዲህ ያለ ወግ በሚገባ ከተከታተሉ በኋላ፣ ዣኩሊን ፔሬ በተባሉ ፈረንሳዊት አሳዳጊ እናታቸው አማካኝነት ወደ ፈረንሳይ ሀገር ሄደው፤ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የፈረንሳይኛ ቋንቋን ጨምሮ በሚገባ ተከታትለዋል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1968-1970 በነበሩት ሶስት ዓመታት ውስጥ በፓሪስ ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከዚያም በመቀጠል፣ እ.ኤ.አ. ከ1971-1973 ዓ.ም ደግሞ የኦርየንታል ቋንቋዎችን በከፍተኛ ደረጃ በሚያስተምረው “በፓሪስ ካቶሊክ ኢንስቲትዩት” ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ጥንታውያን የክርስትና ሥነ-ጥበባትን ለማጥናት በነበራቸው ፍላጎትም፣ በፓሪስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የጥንታዊ ሥነ-ጥበባት የጥናት አካዳሚ ገብተው ዲፕሎማ አግኝተዋል። ትምህርታቸውን በተከታተሉባቸው የትምህርት ኢንስቲትዩቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በግዕዝ ድርሳናት ትርጉም፣ በረዳት የቤተመፃሕፍት ባለሙያነት እንዲሁም በኦሪየንታል ጥናት አማካሪነት እና በረዳት የጥናትና ምርምር ባለሙያነት አገልግለዋል።

     ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በመምጣትም፤ በተማሩት ትምህርት ለማገልገል በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ተቀጥረው የአርኪዮሎጂ እና የፓሊዮ አንቶሎጂ የመስክ ጥናት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የትግሪኛ፣ የአማርኛ፣ የኢሮብ፣ የግዕዝ፣ የአፋር፣ የፈረንሳይኛ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸው ለበርካታ የቅርስ እና የታሪክ ምርምር ሥራዎቻቸው የረዳቸው ልዩ ክህሎታቸው እንደሆነ የሚያውቋቸው የሙያ ባልደረቦቻቸው የሚመሰክሩት ነው። በተለይም በፓሊዮ አንቶሎጂ መስክ ጥንታዊ ጽሑፎችን፣ ቅርጻ ቅርጾችን እና የሐረግ ጥበባትን በመመርመር ከሳቢያን እና ከግዕዝ ወደ አማርኛ እና ፈረንሳይኛ በመመለስ ያበረከቷቸው ግኝቶች ወደፊት ለሚነሱ ተመራማሪዎች ትልቅ የምርምር መስክ መፍጠር የሚችሉ ግኝቶች ናቸው።

     በ1972 ዓ.ም ከፈረንሳይ የአርኪዮሎጂ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ጋር በመሆን በደቡብ የመን በሚገኝ ጥንታዊ መካነ መቃብር ውስጥ የመስክ ጥናትና ምርምር በረዳት የጥናትና ምርምር ባለሙያነት አከናውነው የጥናት ውጤታቸውን በፈረንሳይ የጥናት ማዕከል በሚታተም የጥናት መጽሔት ላይ አሳትመዋል። በ1973 ዓ.ም የመስክ ጥናታቸውን ለማድረግ ወደ ትግራይ እና ላስታ አካባቢዎች በመሄድ በዋሊ ኢየሱስ ገዳም፣ በጉንዳጉንዲ የእስጢፋኖስ ገዳም፣ በላሊበላ ውቅር ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት ባደረጉት ምርምር፤ በሳቢያን እና በግዕዝ ቋንቋ በአክሱም እና በዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት ዘመን የተፃፉ የመስቀል ላይ ጽሑፎችን፣ የግድግዳ የሐረግ ቅርጾችን እንዲሁም የመንበረ ታቦታት ቅርጽ ጽሑፎችን በፎቶ ግራፍ በማንሳት የጽሑፍ ዘመናቸውን እንዲሁም የሥልጣኔ ዘመናቱን ሁኔታ የሚያስረዱ የተለያዩ የጥናት ውጤቶቻቸውን በተለያዩ መካነ ጥናቶች በሚዘጋጁ የጥናት መጽሔቶች ላይ ለንባብ እንዳበቁ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

     ከ1975 እስከ 1986 ዓ.ም በኤክስፐርትነት እና የታሪክ ባለሙያነት የሥራ መደብ የግዕዝ ጥንታዊ ጽሑፎችን እና መዛግብትን በማጥናት በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል። ከ1986 እስከ 1987 ዓ.ም የአርኪዮሎጂና ፓሊዮ አንቶሎጂ ዲፓርትመንት የመምሪያ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። ከ1987 በጡረታ እስከተሰናበቱበት 1996 ዓ.ም፣ ድረስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የምርምር፣ የቡድን መሪነት እና የመምሪያ ኃላፊነት ሥራቸውን ሲከውኑ ቆይተዋል።

     በ1996 ዓ.ም በጡረታ እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የመስክ ጥናቶቻቸው ያገኟቸውን አዳዲስ ግኝቶች፤

  •      በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የጥናት መጽሔት “Journal of Ethiopian Studies”፣
  •      በአዲስ ዘመን እና በኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጦች የተለያዩ እትሞች ላይ፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ይታተም በነበረ Annal D’ Ethiopia “የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሔት” በሚሰኝ የፈረንሳይኛ ቋንቋ የጥናት መጽሔቶች ላይ ለንባብ እና ለተጨማሪ ምርምር መነሻ እንዲሆን በማሰብ በተከታታይ ጽፈዋል።

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ ባለፉት አሥር ዓመታት የጡረታ ዘመን ጊዜዎቻቸውም፤ በሥራ ዘመናቸው ያገኟቸውን የታሪክ እና የጥበብ አስረጂ ጥንታዊ ግኝቶቻቸውን በወግ አደራጅተው በመጽሐፍ መልክ ለማሳተም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነበሩ። በሕመም አልጋ ላይ በዋሉባቸው ያለፉት ሦስት ወራት ጊዜዎች ውስጥ እንኳን ያለማሰለስ ይጨነቁ የነበረው፤ ይህንን የመጽሐፍ ማሳተም ውጥናቸውን ከግብ ማድረስ ላይ ነበር። ይህ ምኞታቸው እውን ሊሆን ጥቂት ጊዜያት ሲቀሩ ለወራት አልጋ ላይ ያዋላቸው ሕመም ጠንቶባቸው በሕክምና እርዳታ ቢታገዙም ሕይወታቸውን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቶ በተወለዱ በ73 ዓመት ዕድሜያቸው መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

     አቶ ጊጋር ተስፋዬ በሕይወት ዘመናቸው ፈረንሳይ ሀገር ከጃኒንጋ ጋር ከመሠረቱት ትዳር የተወለዱ ቪንሰንት እና ዤርሚ የተባሉ ወንዶች ልጆቻቸውን ፊልሞን ጊጋርን ከወ/ሮ ዘነበች እንዲሁም ከወ/ሮ መድሕን አርአያ ጋር በትዳር፣ የወለዷቸው ሦስት ወንዶች እና የአራት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ።

     ትሁቱ፣ ቀናው እና ታታሪው የታሪክ ተመራማሪ አቶ ጊጋር ተስፋዬ፤ በበርካታ ወዳጆቻቸው፣ በአብራክ ክፋይ ልጆቻቸው፣ በዘመዶቻቸው እንዲሁም በሙያ ጓደኞቻቸው የመጨረሻ ስንብት፤ የክብር እረፍታቸው መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በአንቀፀ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅመዋል። በሥጋ እረፈታቸው የማይወሰነው የሥራ አበርክቷቸው ግን በታሪክ ሲዘከር ይኖራል። ውጥን ሥራዎቻቸውም በልጆቻቸው ጥረት ለፍሬ ይበቃሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በታሪክ ተመራማሪው በአቶ ጊጋር ተስፋዬ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፀ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለአድናቂዎቻቸው መፅናናትን ይመኛል።

ይምረጡ
(22 ሰዎች መርጠዋል)
13569 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us