ኢትዮጵያ ሐገረ- እግዚአብሔር

Wednesday, 08 April 2015 11:54

በጥበቡ በለጠ

     ኢትዮጵያ በክርስትናው ኃይማኖትም ሆነ በእስልምናው ኃይማኖት በመጀመሪያ ከተቀበሉት ሐገራት መካከል አንዷ ተደርጋ በብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ትጠቀሳለች። ሰሞኑን እንኳን ‘አልጀዚራ ተብሎ የሚጠራው የኳታር ዝነኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ በአባይ ወንዝ ላይ በሰራው ረጅም ዶክመንተሪ ፊልም ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር፣ የጥንታዊ ስልጣኔዎች ባለቤትና ክርስትናን ወደ ሀገሯ ቶሎ አስገብታ ያስፋፋች የአለማችን ቀዳማይ ሀገር ናት ሲል አትቷል። ይህን የተናገረው ዶክመንተሪ ፊልም /Struggle over the Nile/ ይሰኛል። ስለዚሁ ፊልም ጉዳይ ወደፊት እንነጋገርበታለን። አሁን ግን ወቅቱ የአብይ ፆም መጠናቀቂያው ያውም የሕማማት ወቅት ነውና እስኪ በተወሰነ መልኩ እምነታችን ውስጥ ስላሉት ባህላዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች እንጨዋወት።

     “የኢትዮጵያ አምላክ” በሚል በተደጋጋሚ የምንናገረውና የምንሰማው አባባል አለ። ይህ አባባል ብቻም አይደለም፤ እምነት ነው። መቼም እምነት በተጠየቅ /በ Logic/ የሚመራ አይደለም። ካመኑ ማመን ነው። ግን ኢትዮጵያ እንዴት የራሷ አምላክ ኖራት? ሁሉም ሀገራት የየራሳቸው አምላክ አላቸው ወይ? የኢትዮጵያስ አምላክ ከሌላው ይለያል ወይ? እያልን እየተራቀቅን የምንተነትንበት አይደለም። ምናልባት ወደ ኋላ መለስ ብለን የዚህን አባባል ምንጭ፣ ታሪካዊ ዳራዎችና ገጠመኞችን መዳሰስ ያስፈልግ ይሆናል።

     “የኢትዮጵያ አምላክ እስካለ ድረስ ምንም አንሆንም” የሚሉ አባባሎችም አሉ። ይህ የኢትዮጵያ አምላክ ሀገሪቱን ከብዙ መከራና ስቃይ ጠብቆ በሉአላዊነት ያቆማት በመሆኑ በሰፊው የሚታመንበት አባባል እንደሆነም እንገምታለን። እስኪ አእምሯችንን ወደ ኋላ ወሰድ አድርገነው ይህች ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዴት በአንድነቷ ኮርታ፣ አንድነቷን ጠብቃ፣ ለቅኝ ገዢዎችና ተስፋፊዎች ሳትንበረከክ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ተምሳሌት ሆነች? ብለን እንጠይቅ። እርግጥ ነው አማኞች የዚህ ምስጢር መለኮታዊ ፍቺም እንዳለው ያብራራሉ።

     መላዋ አፍሪካ በኮሎኔያሊስቶች መዳፍ ስር በወደቀችበት ወቅት የነፃነት ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ የመውለበለቡ ምስጢር የኢትዮጵያ አምላክ ጠብቋት ነው ወደሚለው አባባል ያመራል። ለምሣሌ አድዋን በማንሳት የምንነጋገርበትን ርዕሰ ጉዳይ ያጠነክረዋል። አድዋ ላይ ጦርነት ለማድረግ አጤ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ የታጠቀ ሠራዊት ብቻ አይደለም ይዘው የዘመቱት። ይልቅስ ታቦታትንም ይዘው ወደ አድዋ ሔዱ። የዚህ ምስጢሩ ወይም ከበስተጀርባው ያለው አስተሳሰብ ምንድን ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

     ከዚህ በፊት በጥቂቱ ለማብራራት እንደሞከርኩት የአድዋ ዘማቾች ታቦታትን ይዘው ወደ ጦር ሜዳ የሔዱት የመጨረሻውን የሞት ሽረት ትግል ለማካሔድ ነው። አድዋ ላይ የሚጠብቃቸው ጠላት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሊይዝ ነው። በዚህም የሀገሪቱ ጥንታዊ እምነት፣ ባህል፣ ማንነትም በሌላ የቅኝ ገዢ እምነት ይተካል ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ታቦታት ሁሉ ፈተና ውስጥ የሚገቡበት ወቅት ነው። የሕልውና ጊዜ ነው። አድዋ ላይ ኢትዮጵያ ከተሸነፈች በየገዳማቱ፣ አድባራቱ፣ በየአብያተ-ክርስትያናቱ ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መገለጫ የሆኑ እነዚህ ታቦታት አይኖሩም። ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ከተሸነፈች ጦሱ መዘዙ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖቷም ጭምር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መገለጫ የሆኑት እነዚህ ታቦታትም ለመጨረሻው ፍልሚያ ወደ አድዋ ጦር ግንባር ዘመቱ። አጤ ምኒልክም እቴጌ ጣይቱም ቤተ-መንግሥታቸውን ትተው አድዋ ላይ የመጨረሻውን ፍልሚያ ሊያደርጉ በተጠንቀቅ ቆመዋል። እናም የአድዋ ጦርነት ተጀመረ።

     በአንድ ቀን ውስጥ ሁሉም ነገር ተጠናቀቀ። ኢትዮጵያ እጅግ ታጥቆ እና ሰልጥኖ የመጣውን የኢጣሊያ ጦር ድል አደረገች። እዚህ ላይ የታቦታቱ ሚና ምን ነበር ብሎ የትንታኔ ሁኔታ ውስጥ መግባት አያስፈልግም። እነዚህ ታቦታት ለአርበኞች ኃይልና ብርታት ከመሆናቸው ባሻገር መለኮታዊ ምስጢራትም ስላሏቸው ለድሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። እናም ሀገሪቱን የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቃታል የሚለው አባባል ተደጋግሞ ሲነገር የሚያስገርም አይደለም።

     እዚህ ላይ አንድ የጳውሎስ ኞኞ ጽሁፍ ትዝ አለኝ። ጳውሎስ የኢጣሊያ የታሪክ ፀሐፊዎችን ጠቅሶ የፃፈው መጣጥፍ አለ። በዚህ መጣጥፉ ውስጥ እንደሚገልፀው፣ በአድዋ ጦርነት ወቅት ኢጣሊያኖች ያልቻሉት ፈረስ ላይ ቁጭ ብሎ ጎራዴ ይዞ እየበረረ ወደ ጣሊያኖች ምሽግ እየመጣ የሚጨፈጭፋቸውን ፈረሰኛ ነበር። በጳውሎ ኞኞ አገላለፅ ይህ ፈረሰኛ ጊዮርጊስ ነበር።

      የኢትዮጵያ አምላክ የሚባለው በነዚህ መገለጫዎች ብቻም አይደለም። በአንዳንድ አባቶች የፅላቱ ዘላለማዊ መቀመጫ አድርጎም መርጧታል ይላሉ። ስለዚህ ሀገሪቱ የእርሱ ናት፤ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አምላክ የሚባለው እያሉ ያስረዱናል። ፅላተ - ሙሴ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ይተረካል፤ ብዙም ተጨባጭ የሆኑ ማስረጃዎችም ኢትዮጵያ ውስጥ ፅላቱ መኖሩን ይናገራሉ። ይህን ፅላት የዛሬ ሁለት ዓመት መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ አለ ተብሎ በርካታ አርኪዮሎጂስቶች ሔደው ቢቆፍሩም ሊያገኙት አልቻሉም። በወቅቱ በተሰጠው መላ ምት በዓለም ላይ ተፈልጎ ያልተገኘው ይህ ፅላት መኖሪያው ኢትዮጵያ እንደሆነ ተነግሯል። ኢትዮጵያ ሐገረ-እግዚአብሔር ናት የሚባለው ለዚህ ነው ያሉኝ አባቶች አሉ።

     ከሁሉም በላይ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ከአንቀፅ አንቀፅ እያነበቡ ትንታኔ የሚሰጡ ሰዎችም አሉ። ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በፈጣሪ የተወደደች ናት፤ ስሟም ተደጋግሞ በበጎ የተጠራላት ናት። “ኢትዮጵያ ታበፅዕ እዴዊሃ ኀበ እግዚሐብሔር” (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች) ተብሎ ተነግሯል። እናም ሀገረ እግዝአብሔር ናት ብለው የሚያስረዱን አሉ። ሌሎችንም በርካታ ጉዳዮች እያወሱ ኢትዮጵያን ከፈጣሪ ዘንድ የተወደደች መሆኗን የሚያስረዱን በርካታ ምሳሌዎችና ተምሳሌቶችን እየጠቃቀሱ የሚያወጉን መንፈሣዊያን ሞልተዋል።

     መቼም ጥያቄው የሚነሳው እግዚአብሔርና ኢትዮጵያ ይህን ያህል ከተዋደዱ ከተቀራረቡ፣ ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ነክቷት ነው በአለም አደባባይ ላይ ለዘመናት በድህነት፣ በኋላቀርነት፣ በጦርነት፣ በስደት፣ በሞት፣ በበሽታ ወዘተ ስሟ ተጠቃሽ የሚሆነው? እኛ ኢትዮጵያዊያን እና ፈጣሪ ምን ያህል እንቀራረባለን?

     እርግጥ ነው በዚህች ሐገር ስር የሰደደ ሃይማት አለ። በርካታ አማንያንን በየዕለቱ በየአብያተ-ክርስትያናቱ ማየትም የተለመደ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለፈጣሪያቸው በየበዓላቱ ምስጋና ያቀርባሉ። ይዘምራሉ፤ ያወድሳሉ፤ በእልልታና በአጀብ ሃይማኖታዊ ክብረ በአላቸውን ያከብራ። ግን ወደ ስጋዊ ኑሯቸው ስንመጣ የፕላኔቷ ድሃ ከሚባሉ ሕዝቦች መካከል አንዱ ናቸው። ይህ ለምን ሆነ?

     እዚህ ላይ ልብ ሊባልልኝ የምፈልገው የድህነትን መንስኤ ለመፈተሸ የሃይማኖት መነጽር በማድረግ ለመመርመር መፈለጌ አይደለም። እኔ የፈለኩት አንዳድ ሰዎች እንደሚሉት ጠንካራ እምነት ያለው ሰው ድሃ አይሆንም የሚለውን አባባል እንዴትስ ታዩታላችሁ? ብዬ ለመጠየቅም ነው?

     በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሥነ-ፅሁፍን ላለፉት 40 ዓመታት ሲያስተምሩ፣ ሲፅፉ፣ ሲመራመሩ የኖሩት አንጋፋው ምሁር ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ያልተሰሙ ድምፆች /Unheard Voices/ የተሰኘ መፅሐፍ አላቸው። በዚህ መፅሐፋቸው የኢትዮጵያ ገበሬ በልዩ ልዩ ወቅት የሚከሰትበትን ድርቅ አስምልክቶ የሚገጥማቸውን ስነ-ቃሎች ሰብስበው የተነተኑበት ነው። ገበሬው ድርቁ አይኑን አፋጥጦ ሲመጣበት ለፈጣሪው የሚናገረውን፣ ከፈጣሪው ጋር ሁሉ የሚያወጋበትን አፍአዊ ኪነ ቃል አደራጅተው ትውልድን አስተምረውበታል። ታዲያ በእርሳቸው መፅሐፍ ውስጥ ድርቅን፣ ጠኔን እና ፈጣሪን እናገኛቸዋለን። ይህን ሁሉ አበሳ የሚሸከመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፈጣሪው የሚያቀርበውን ጥያቄ እናነባለን። ግሩም የሆነ የጥትና የምርምር ስራቸው ነው ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ። ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለን ስሜትና ቁስል ሰብስበው አስነብበውናል።

     ለመሆኑ የኢትዮጵያ ደራሲያን ድህነትን እንዴት ገለፁት? ተብሎ ቢጠየቅስ? መቼም መልሱ አያልቅም። በጀርመን ሀገር የዶክተሬት ድግሪውን እየተከታተለ ያለው ወዳጄ የሆነው ኤፍሬም ዳንኤል የጥናትና የምርምር ስራው ድሕነት በኢትዮጵያ ረጃጅም ልቦለዶች ውስጥ የሚል ነው። በልቦለድ ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት የኢትዮጵያ ደራሲያን የኢትዮጵያንን ድህነትን እንዴት ገለፁት ብሎ ትንታኔ ውስጥ የሚገኝ ጥናት ነው። በአሉ ግርማ ሀዲስ በተሰኘው ረጅም ልቦለዱ ውስጥ የሀዲስ ሰኃሌን እናት እና የሀዲስን የድህነት ሰንሰለት የገለፀበትን፣ ብርሃኑ ዘሪሁን ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮቱ መባቻ፣ ማዕበል የአብዮቱ ማግስት በተሰኙት ረጃጅም ልቦለዶቹ አማካይነት ድርቅን ድህነትን እንዴት እንደገለፀው የኤፍሬም ጥናት ይዳስሳል። ሐዲስ ዓለማየሁም በፍቅር እስከመቃብርበወንጀለኛው ዳኛበእልም እዣት መፃሕፍቶቻቸው ድህነትን የገለፁባቸውን ሀሳቦች ይዞ ያጠነጥናል። የሌሎችንም ደራሲያን ስራዎችን በድህነት ዙሪያ እየሰራባቸው ነው። የጥናቱ ውጤት ምን እንደሚሆን ባይታወቅም የመረጠው ሃሳብ ጥሩ ይመስለኛል። ብዙ ያሰራል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሚከተለው ገጠመኝ ነው።

     ከዚህ በፊት ሐይማኖተኝነት በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ ምን እንደሚመስል የተሰራ ጥናት ስላለ ወደፊት የኤፍሬም ጥናት ሲጠቃለል ሁለቱን ጥናቶች በማየት ሃይማተኝነት እና ድህነት ላይ ሰፊ የመወያያ አጀንዳ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።

     መቼም ያለንበት ሳምንት የሕማማት በመሆኑ፣ እየሱስ ክርስቶስም የተገረፈው፣ የተሰቃየው፣ የተሰቀለው ለኛ ለሰው ልጆች ድህነት በመሆኑ፣ የእርሱም ስቃይና መከራ በምናስብበት በዚህ ወቅት እኛም ኢትዮጵያዊያን ይታሰብልን በሚል ዘዬ ይህችን መጣጥፍ ማስነበቤ የሚያስከፋ አይመስለኝም። እየሱስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀሉም በዚህችው በሀገራችን ኢትዮጵያ ግሸን ደብረ-ከርቤ በመኖሩ ቀደም ሲል የገለፅኩት “ሀገረ-እግዚአብሔር” የሚለው አባባል አሁንም መሬት የያዙልን ይመስለኛል።

     በአጠቃላይ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም ሆናችሁ ለመላው አንባቢዎቼ መልካም የትንሳኤ በዓል እመኝላችኋለሁ።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
11507 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us