ቅዱስ ያሬድ

Wednesday, 08 April 2015 11:57

    

በጥበቡ በለጠ

 

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እጅግ ስመገናና የሆነው ቅዱስ ያሬድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ቤተ-ክርስቲያኒቱ የምትታወቅበትን የዜማ፣ የዝማሬና የሽብሸባ፣ የቅዳሴ ስርዓቶችን የፈጠረ የፕላኔታችን ሃያል ሊቅ ስለነበር ነው።

     ቅዱስ ያሬድ የተወለደው አክሱም ሲሆን ቀኑም ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም ነው። የዛሬ 1502 ዓመት ማለት ነው። ከዛሬ 1ሺ አምስት መቶ አመት ገደማ ይህ ሰው ዜማ በመድረስ በማስፋፋት በሙዚቃው አለም እንኳ ብናየው የዓለም መስታወት የሆነ ብርሃን ፈንጣቂ ሊቅ ነበር።

     ቅዱስ ያሬድ ከተወለደበት ከአክሱም ወደ ጎንደርና ጣና ቂርቆስ በመሔድ አያሌ ስራዎችን አበርክቶ ያለፈ ሰው ነው። በቤተ-ክርስቲያኒቱ የሚታወቁትን ድጓ፣ ፆመ-ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሲት የሚባሉት የዜማ አይነቶች የደረሰ ሊቅ ነው። እነዚህንም በሶስት የዜማ አዚያዜም ከፍሎ አስቀምጧቸዋል። 1ኛ/ ግዕዝ፣ 2ኛ/ እዝል 3ኛ/ አራራይ በመባል ይታወቃሉ።

     ይህንንም ዜማ በትውልዶች ዘንድ ዘላለማዊ ሆኖ እንዲኖር ስምንት አይነት የዜማ ምልክቶችን የፈጠረ ነው። እነዚህም፡-

  1. 1. ይዘት
  2. 2. ጭረት
  3. 3. ድፋት
  4. 4. ቅናት
  5. 5. ሂደት
  6. 6. ድረት
  7. 7. ቁርጥ
  8. 8. ርክርክ ናቸው።

     ቅዱስ ያሬድ በጣና ቂርቆስ ገዳም ቀለም የበጠበጠበት ድንጋይ፣ የፃፈው ድጓ፣ መቋሚያው እና ፀናፅሉ እስከ ዛሬ ድረስ አሉ። በጎንደር ልዩ ልዩ ቦታዎች በመዘዋወር የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያንን የዜማ፣ የሽብሸባ፣ የዝማሬን ስልት በመንደፍ እስከ ዛሬ ድረስ ወደር ያልተገኘለት ቅዱስ ሰው ሆኖ አልፏል።

    ቅዱስ ያሬድ ግንቦት 11 ቀን 571 ዓ.ም በ66ኛ ዓመቱ ላይ በብህትውና እዚያው ጎንደር ጠለምት በረሃ በሚገኝ ገዳም ሕይወቱ አልፋለች። ይህ ሰው ዛሬ በየአብያተ ክርስትያናቱ ያሉትን ዝማሬዎች የፈጠረ ሊቅነው። የሚያዚያ ወርም ቅዱስ ያሬድ ከ1ሺ 500 ዓመታት በፊት ወደዚህች ምድር የመጣበት ወቅት በመሆኗ ልንዘክረው ወደድን።

     በዚህ በሕማማት ሳምንትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን አማንያን ስርዓተ ቅዳሴ የሚያካሒዱበት ስልት፣ ወረብና ዜማ በሙሉ ቅዱስ ያሬድ የፈጠራቸው ናቸው።

ይምረጡ
(38 ሰዎች መርጠዋል)
18787 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us