ጥሬ ሥጋን የመብላት ባህል በኢትዮጵያ

Wednesday, 15 April 2015 15:03

በጥበቡ በለጠ  

 

የውጭ ሀገር ሠዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከሚደነቁባቸውና ከሚደነግጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያዊያን ጥሬ ስጋን ጐመድ ጐመድ እያደረጉ (እየመተሩ) ሲመገቡ ማየት ነው። ጥሬ ሥጋ መብላት በኢትዮጵያ በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ በስፋት የሚዘወተር ነው።

በብዙ ሀገሮች ደግሞ ጥሬ ሥጋን መመገብ እምብዛም ስለማይታወቅ የባህር ማዶ ሰዎች ጥሬ ሥጋ የሚበላ ሰው ሲያዩ ይደነግጣሉ፣ ይፈራሉ፣ እንዲሁም ሊቀፋቸውም ይችላል።

አያሌ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ጥሬ ሥጋን መብላት እንደ ሱስ የሆነባቸው ናቸው። ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ጥሬ ሥጋ ካልበላሁ በጣም የተጐዳሁ ያህል ይሰማኛል የሚሉ የጥሬ ሥጋ ሱሰኞች አሉ። ነብሱን ይማረውና ታላቁ ድምፃዊ ታምራት ሞላ በአንድ ወቅት ስለ ጥሬ ሥጋ ፍቅሩ ሲናገር፣ ቁርስም፣ ምሣም፣ ራትም ጥሬ ሥጋ ቢበላ ደስ እንደሚለው ሲያወጋ ነበር።

በኢትዮጵያ ውስጥ ጥሬ ሥጋን መመገብ እንዴት ተጀመረ? መቼ ተጀመረ የሚል ጥያቄ መነሳቱም አይቀርም። የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋት በመፃፍ የሚታወቁት ደራሲ አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ እንደገለፁት ከሆነ፣ ኢትዮጵያዊያን ጥሬ ሥጋን መብላት የጀመሩት ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው ይላሉ። ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ በዘመኑ በሀገሪቱ ውስጥ ከባድ የነበረ የእርስ በርስ ጦርነት ተነስቶ ነበረ። በዚህ ጦርነት ውስጥ የሚሳተፉ ወታደሮች በጦር ሜዳ ውስጥ ምግባቸውን አብስለው ሲመገቡ ጭስ ይታያል። ጭሱ በሚታይበት ጊዜ ለጠላታቸው እይታ በቀላሉ ይጋለጣሉ። ስለዚህ አብስለው የሚመገቡት ምግብ አደጋ እንዳያስከትልባቸው ሳያበስሉት ጥሬ ሥጋን መብላት መጀመራቸው ተጽፏል።

እንግዲህ ጥሬ ሥጋ መመገብ ኢትዮጵያውያንን ከከፋ አደጋ እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል ማለት ነው። የጥሬ ሥጋ የመብላት የታሪክ ዳራ ይሄ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች ጥሬ ሥጋን መመገብ እንደ ባህል ተወስዷል።

የሕክምና ሰዎች ደግሞ ጥሬ ሥጋን መመገብ ለጤና ጠንቅ ነው እያሉ ለረጅም ጊዜ ቢወተውቱም ኢትዮጵያዊያን ግን ጥሬ ሥጋን ከመብላት ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም ይባላል። እንደ ጥሬ ሥጋ አመጋገባቸው የተነሳ ለከፋ የጤና ቀውስ ይዳረጋሉ ተብሎ ቢታሰብም ጉዳዩ ስር የሰደደ ችግር ሳይሆን እስከ አሁን ድረስ አለ።

በመስከረም ወር ላይ ‘ማርቲ ቫን ዴር ዎልፍ’ የምትባል ጋዜጠኛ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ የጥሬ ሥጋ አመጋገባችንን ለዓለም ሚዲያዎች አሰራጭታ ነበር። እንደ ጋዜጠኛዋ ዘገባ ከሆነ ጥሬ ሥጋን መመገብ ለልብ ሕመም፣ ለደም ግፊት፣ ለሪህ በሽታ እንዲሁም ደግሞ ለሆድ ውስጥ ተውሣክ መጋለጥ እንደሚያስከትል እንደ መግቢያ ዘግባለች። ከዚያም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወዳሉት ልኳንዳ ቤቶች በመዘዋወር የልኳንዳ ቤቶቹን ባለቤቶችና ተመጋቢዎችንም አነጋግራለች። ጋዜጠኛዋ ማርቲ ከአብዛኛዎቹ ተጠያቂዎች ያገኘችው መልስ በጣሙን አስገርሟት ነበር።

እንደ ኢትዮጵያውያኑ መልስ ከሆነ ጥሬ ሥጋ መብላታችን ለጤና ችግር አላጋለጠንም። እንደውም ሳንበላ ስንቀር ነው የተጐዳን የሚመስለን እያሉ መልሰዋል። የልኳንዳ ቤቶች ባለቤቶች ደግሞ ሥጋው በቄራ በኩል ተመርምሮ ስለሚመጣ የኮሶ ተውሳክ እና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ጥሬ ሥጋ ላይ የሉም እያሉ መልሰዋል።

አንዳንዶች ሲመልሱ ደግሞ፤ “ጥሬ ሥጋን ሲበሉ የሚያማቸው ፈረንጆች ይሆናሉ፤ አበሾች ግን ጥሬ ሥጋን የሚበሉት በፍቅር ነው” እያሉ ‘ለማርቲ ቫን ዴር ዎልፍ’ መልሰውለታል።

እንደ ዛሬው ሥጋ በኪሎ እየተመዘነ በማይሸጥበት ወቅት ኢትዮጵያውያን አንድ ብልት ለብቻዬ ጨረስኩ፣ አንድ ሽንጥ ለሁለት በላን እያሉ እንደ ተረት የሚያወጉባት ሀገር ነች። እናም ጋዜጠኛዋ መረጃውን ለዓለም ከማሰራጨት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራትም። ይህችው ጋዜጠኛ ማርቲ ቫን ዴር ዎልፍ በመጨረሻም የገለፀችው በአሜሪካ የህክምና ማዕከል ውስጥ ስለ ጥሬ ሥጋ መመገብ የሚያስከትለውን ጉዳት ነው። በዚህም መሠረት ጥሬ ሥጋ ለልብ ሕመም፣ ለስኳር፣ ለስትሮክ፣ ለደም ግፊት፣ ለኰሌስትሮል መጨመር እና ለሆድ ውስጥ ተውሣኮች ያጋልጣል ብላለች። ዘገባዋን ሰትደመድም እንደፃፈችው ደግሞ እንዲህ ብላለች፡- “አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ግን ጥሬ ሥጋን ከመመገብ ወደኋላ አላሉም። ጥሬ ሥጋን ሲመገቡ ምናልባት ኮሶ ይጣባናል ይላሉ። ለእሱ መድሐኒት ደግሞ ካለ ሐኪም ትዕዛዝ ከየፋርማሲው የኮሶ ኪኒን ገዝተን እንጠቀማለን” ይላሉ ስትል ማርቲ ዘግባለች። ይሄ የጥሬ ሥጋ አመጋገባችን ጉዳይ አነጋጋሪነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋል ካልን፤ ምግብን ምግብ ያነሳዋል ብለን ወደ አንድ አስገራሚ ታሪክ ብናመራስ።

በምድር ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ሲያሻችሁ እየቀቀላችሁ፣ ከጣማችሁም እየጠበሳችሁ ቅርጥፍ አድርጋችሁ ብሏቸው ሲል የተባበሩት መንግስታት የምግብና የግብርና ድርጅቱ FAO በቅርቡ ተናግሯል። እነዚህ ነፍሳት ፀረ-ረሀብ ትግልን ይደግፋሉ፣ ያጠናክራሉ ደግሞም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚኖራቸው ሚና ቀላል አይደለም ሲል FAO መግለፁ ይታወቃል።

የጥንዚዛ፣ የአባ ጨጓሬ፣ የንብና የተርብ ዘሮች ነገደ ጉንዳን ሁሉ በገንቢ ምግቦች የከበሩ በቅባት በብረትና በሌሎችም ማዕድናትና ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ናቸው። እናም ብሏቸው ነው የሚለው የተባበሩት መንግስታት የግብርና እና የምግብ ድርጅቱ FAO

ለምን እስከ አሁን እንዳልበሏቸው አውቃለሁ፣ FAOም ያውቃል፤ ‘ኤጭ ቀፋፊ ናቸው ይላሉ፤ ምክንያቱም አባትዎ ወይም እናትዎ ሲበሏቸው አላዩማ! እርስዎ ቁርጥዎንና ጥሬ ሥጋዎን ሲያገላብጡ አጠገብዎ ዓይኑን እያፈጠጠ ‘ኧ!’ የሚል ስንት እንደሆነ ያውቃሉ?’

የአህያ ሥጋስ ቢቀርብልዎ እንዲያ ያገላብጡት ይሆን? አይመስለኝም፤ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድ ግን እንደ ምን ውድ፣ እንደ ምን ጣፋጭ መሰልዎ? እንዲህችም ብለው አይቀላውጡ፤ አይሰጥዎትማ! የተወደዱ እና የተናፈቁ እንግዳ ካልሆኑ በስተቀር።

ለመሆኑ እርስዎ ኤስካርቦ ይመገባሉ? የስሙ ማማር! ፈረንሣዊያኑ እያጣጣሙ የሚመገቡት ቀንድ አውጣ ነው።

አሁን አሁን ታዲያ እንደ FAO ዘገባ ይሄ ቀፋፊ ነው የሚባል አመጋገብ በምዕራቡ ዓለምም እየተቀረፈ ነው ብሏል። በተለይ እነዚያ ባለሙያዎቹ የኒውዮርክ፣ የለንደን፣ የፓሪስ፣ የሳንፍራንሲስኮ፣ ወዘተ ቀቃዮችና ጠባሾች በየሜኑዋቸውና በየምግብ ዝርዝራቸው ቀስ በቀስ ደብለቅ እያደረጉ ሰውን ቢያስተምሩትና ቢያሰለጥኑት ምንኛ በጐ ሥጋ ይሆንላቸዋል? ብሏል FAO

እንደ VOA ዘገባ፤ እንግዲህ ዛሬ በዓለም ዙርያ 2 ቢሊዮን ህዝቦች እነ ጢንዚዛን እና ነገደ ጉንዳንን በየቀኑ እየበሉ ነው። እርስዎም ሰምተዋል። እንግዲህ እንዳሻዎ። እንደ ቀልብዎ እንደ ባህልዎ እና እምነትዎ ያድርጉ። ክፉ ቀን አይምጣ እንጂ ረሃብ ቢከሰት ግን አማራጮች መሆናቸውም ተዘግቧል። 

አዳዲስ ፈጠራ የጠፋባቸው ከያኒያን

በኢትዮጵያ ውስጥ አያሌ ክብረ-በዓላት ይካሄዳሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዘመን መለወጫ፣ ገና፣ ጥምቀቱ፣ ትንሳኤው፣ ሞውሊዱ፣ ሌሎችም በዓላት አሉ። በእነዚህ በዓላት ወቀት ደግሞ የሙዚቃ ዝግጅቶች በስፋት ይካሄድባቸዋል። በእነዚህ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ አንዳቸውም ድምፃዊያን አዲስ የሙዚቃ ሥራ ይዘው አይቀርቡም። ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የዘፈኗቸውን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን አሰልቺ በሆነ መንገድ ባገኙት መድረክ ላይ ሁሉ የሚዘፍኑ ድምፃዊያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ ነው።

ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ ባከበርነው የትንሳኤ በዓል ዝግጅት ላይ በቴሌቪዥን የተመለከትኩት ፕሮግራም ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደተለመደው ሁሉ አንድ ስፖንሰር ፈልጐ የትንሳኤን በዓል ልዩ ዝግጅት ያከብር ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ አንጋፋው ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ የሙዚቃ ስራውን እንደሚያቀርብ ተነገረን። አረጋኸኝ ወራሽ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ለስለስ ባለ ጥሩ ድምፅ ከሚዘፍኑ ከያኒዎቻችን መካከል አንዱ ነው። ድምፁ አሁንም ችግር የሌለበት በደንብ ሊያዜምበት የሚችል ነው። በዚህ በትንሳኤ በዓል ላይ ሙዚቃ ያቀርባል ሲባል ቢያንስ አንድ አዲስ ሙዚቃ ይዞ ይቀርባል የሚል ተስፋ ነበረኝ። አረጋኸኝ ሲመጣ ግን ከ20 ዓመታት በፊት የዘፈነውን፣ በተደጋጋሚ በልዩ ልዩ መድረኮች የሚዘፍነውን ሙዚቃ ይዞ መጣ። “እስኪ ዘለል ዘለል …. እያለ አሁንም ዘፈነ። ምነው? ጥበብ የት ጠፋች? አዲስ ፈጠራ የት ገባች? 20 ዓመት ሙሉ “እስኪ ዘለል….” እየተባለ ጉዞው የት ያደርሳል? ብዬ አሰብኩ።

መነሻዬ አረጋኸኝ ሆነ እንጂ አንጋፋዎቹም ሆኑ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ድምፃውያን በአዳዲስ የሙዚቃ መድረኮች ላይ በአዲስ ፈጠራ መምጣት ካቆሙ ቆይተዋል። ውስጣቸው ጥበብ የነጠፈችባቸው እስኪመስል ድረስ አሰልቺ የሆነውን ድግግሞሽ በየመድረኩ ያበዙታል።

አንድ የሙዚቃ ሰው ቢያንስ በአንድ ዓመት ውስጥ እንዴት አንድ አዲስ ሙዚቃ አይጫወትም? እንዴት አንዲት አዲስ ዘፈን አይፈጥርም? ምኑን ነው ታዲያ የጥበብ ሰው የሚባሉት? ጥበበኛ ፈጣሪ ነው፤ ሁልጊዜም ከአዳዲስ ፈጠራዎች ጋር የሚኖር ነው።

ሌላው መነጋገር ያለብን ደግሞ የሙዚቃን መድረክ ከሚያዘጋጁት አካላት ጋር ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስፖንሰር ፈልጐ እንዲህ አይነት ዝግጅት በሚደግስበት ወቅት ከያኒዎች ከአዳዲስ ስራዎቻቸው ጋር እንዲወጡ ግፊት ማድረግ አለበት። በስብስቴ ዘመን የተዘፈኑ ዘፈኖች ሁሌ በየመድረኩ አድማጭን ማሰልቸት የለባቸውም።

በቀደመው ዘመን በተለይም በንጉሱ ዘመን ብሔራዊ ቴአትር ቤት ውስጥ የአዲስ ዓመት መቀበያ የሙዚቃ ዝግጅቶች ይካሄዱ ነበር። ታዲያ በዚያን ወቅት ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐመድ አሕመድ፣ ሒሩት በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ታምራት ሞላ፣ እና ሌሎችም የዛሬ አንጋፋ ድምፃውያን አዳዲስ ስራዎቻቸውን ነበር ይዘው የሚቀርቡት። አዲስ ዓመቶች ስራዎቻቸውን የሚያስመርቁባቸው መድረኮች ነበሩ በዘመኑ። ዛሬ ደግሞ የተገላቢጦሽ ሆኖ የድሮና የጥንት ዘፈኖችን በየዓመቱ መደጋገም የበዛበት ዘመን ሆኗል።

የዲጄዎች ሥራ ቀደም ተብለው የተዘፈኑ ሙዚቃዎችን እንደየመድረኩ ሁኔታ ማሰማት ማስደመጥ የየዕለት ተግባራቸው ነው። ዘፋኞች ደግሞ አዲስ መድረክ ሲያገኙ ከአዳዲስ ፈጠራዎቻቸው ጋር ብቅ የሚሉበት ነው። ነገር ግን ድምፃውያኖቻችን ሁሌም የዲጄዎችን ሥራ የሚሰሩ ይመስላሉ። ሙዚቃን ከቀድሞው አርካይቭ ውስጥ እየመዘዙ ከመጫወት ውጭ አዲስ ፈጠራ፣ አዲስ ጥበብ የጠፋችባቸው ትመስላለች።

ወደፊት ግን የሙዚቃን መድረክ ብሎም ኮንሰርቶችን የሚያዘጋጁ አካላት ከያኒዎቻችን ከአዳዲስ ሥራዎቻቸው ጋር ወደ መድረክ እንዲመጡ ግፊት ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብዬ አስባለሁ። 

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
17949 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us