ውለታ የረሱት ደቡብ አፍሪካውያን

Friday, 24 April 2015 12:34

በጥበቡ በለጠ


     ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ ልዩ ልዩ ከተሞች ውስጥ ከአያሌ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ዜጐች ይውጡልን በሚል መሪር የሆነ ጭካኔ በጥቁሮች ላይ ሲወርድባቸው ቆይቷል። ችግሩ አሁንም አልበረደም። ደቡብ አፍሪካውያን በእነዚህ የአህጉሪቱ ወንድምና እህቶቻቸው ላይ ይህን የመሰለ ጥላቻ ከየት አመጡት? ለደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስ እና የደቡብ አፍሪካን ጥቁሮች ከመከራ ቀንበር ለማላቀቅ በተከፈለው መስዋዕትነት ውስጥ የኢትዮጵያ እና የሌሎች ሀገሮች አስተዋፅኦ እንደምን ነው በሚሉትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እስኪ እናውጋ።

     ደቡብ አፍሪካውያን ከ300 ዓመታት በላይ በነጮች የበላይነት በተለይም በአፓርታይድ /በቀለም ልዩነት/ መከራዋን ስታይ የኖረች ሀገር ናት። የደች እና የእንግሊዝ ተወላጆች የሆኑት ነጮች እንዲሁም ደግሞ የእነርሱ ጀሌ የነበሩ ሌሎችም ተባባሪዎቻቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው፣ ይህችን በተፈጥሮ ፀጋ በእጅጉ የበለፀገችን ሀገር ጠቅልለው ወሰዷት። ደቡብ አፍሪካውያን ከአንድ ባርያ ያነሰ ኑሮ መግፋት ጀመሩ። ፕሪቶሪያ፣ ደርባን፣ ጆሃንስበርግ፣ ኬፕታውን፣ ፖርት ኤልዛቤት እና ሌሎችም ከተሞች ውስጥ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ ነበር በባርነት እንዲያገለግሉ የሚፈቀድላቸው። 12 ሰዓት ሲሆን፤ ከተሞቹን ለነጮች ለቀው መውጣት አለባቸው። ከ12 ሰዓት በኋላ የተገኘ ጥቁር ይታሰራል፣ ይደበደባል ሊገደልም ይችላል።

      ከዚህ ግፍ ውጪ ደግሞ ነጮችና ጥቁሮች አንድ አውቶብስ ውስጥ፣ ባቡር ውስጥ በሌሎችም የትራንስፖርት መገልገያዎች አብረው መጓዝ አይችሉም። ጥቁርና ነጭ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ አብሮ ተቀምጦ መማር አይችልም። ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የተፈጠሩት ነጮችን ለማገልገል ብቻ ሆኖ ከ300 ዓመት በላይ በስቃይ የኖሩ ሕዝቦች ናቸው።

     ከዚህ ስቃያቸው የሚገላግላቸው ተአምር ይጠብቁ ነበር። የጭቆናው ዘመን ስለረዘመባቸው ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አይመስላቸውም ነበር። በነጮች የሚደርስባቸው መከራና እንግልት ተነግሮ አያልቅም። ታዲያ በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ እያሉ በ1888 ዓ.ም በአፄ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር ከአፍ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር አድዋ ላይ ድባቅ መታው። ዜናው የዓለም ሆነ። ጥቁሮች ነጮችን በአንድ ቀን ጦርነት ፈጇቸው እየተባለ ተፃፈ። በወቅቱ ከ200 ዓመታት በላይ በነጮች የአፓርታይድ ሥርዓት መከራ ያዩ የነበሩት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ዜናውን ሲሰሙ ተነቃቁ። ጥቁር ማሸነፍ እንደሚችል ከአድዋ ጀግኖች ተማሩ።

     ከዚያም ታላላቅ የደቡብ አፍሪካ ታጋዮች የሚባሉት ኢትዮጵያን ማጥናት መመርመር ጀመሩ። እንዴት ነጮችን አሸነፈች? እንዴትስ አንድም ጊዜ በነጮች ሳትያዝ ኖረች እያሉ ጠልቀው አጠኗት።

     በተለይ አድዋ ላይ በእነ አጤ ምኒሊክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ ሲመረመር ፀሎተኛ ሆኖ ተገኘ። ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት ንጉሱ አጤ ምኒልክና ሌሎችም ባለሟሎቻቸው ይፀልያሉ። የፈጣሪን ስም ደጋግመው ያነሳሉ። ይህ አልበቃ ብሎ ታቦታትን ሁሉ ይዘው ነበር ወደ አድዋ የዘመቱት። ቀሳውስትም አብረዋቸው ነበሩ። በእነዚህ ሁሉ የተደገፈው የኢትዮጵያ ጦር አድዋ ላይ ነጮችን ድል አደረገ ብለው የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች አመኑ።

     ከዚያም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ሃይማኖት እንከተላለን ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞች መሆን ጀመሩ። ምክንያታቸው ደግሞ አድዋ ላይ የተገኘው የጥቁሮች የበላይነት እምነቱም የፈጠረው ጀግንነት እንደሆነ አመኑ። ከዚያም የተለያዩ አብያተ-ክርስትያናትን በኢትዮጵያ ስም ማነጽ ጀመሩ።

     ታላቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሃምሳኛውን ዓመት የአፍሪካ ኅብረት ክብረ በዓልን በተመለከተ በተዘጋጀው JUBILEE በተሰኘው ግዙፍ መጽሔት ውስጥ Ethiopian Echoes in Early Pan-African Writings በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል። በዚህ ጽሁፋቸው ፕሮፌሰሩ እንደሚገልፁት ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በነጮች ላይ በጦርነት የምታሳየው የበላይነት የደቡብ አፍሪካውያንን ቀልብ ሰርቋል። ደቡብ አፍሪካውያን ለነፃነታቸው ለሚያደርጉት ትግል ኢትዮጵያ አርማቸው ሆና ብቅ ማለቷን ጽሁፉ ይገልፃል። በዚህም የተነሳ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩ አያሌ አብያተ-ክርስትያናት መመስረታቸውን ዘርዝረው ጽፈዋል። እነዚህም አብያተ-ክርስትያናት ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. African United Ethiopian Church
 2. Ethiopian Mission in South Africa
 3. The National Church of Ethiopia in South Africa.
 4. St.Philip’s Ethiopian Church of South Arica
 5. Ethiopian Church Lamentation in South Africa
 6. The Ethiopian Church of God the Society of Paradise.

     የተሰኙት አብያተ-ክርስትያናት ጥቂቶቹ ናቸው። የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትስስር በዚህ ቀጠለ።

     በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በዓለም አቀፉ መድረክ ወረራውን ሲቃወሙ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር መላኩ በያን (ከ1892 - 1932) በአያሌ ንግግሮቻቸው ደቡብ አፍሪካ ከአፋቸውም ከብዕራቸው አትጠፋም ነበር። ጥቁሮች ሁሉ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት፣ ጥቁሮችን ከባርነት ለመገላገል በሕብረት መነሳት እንዳለባቸው ይወተውቱ ነበር። ኢትዮጵያ በሕዝቦቿና በደጋፊዎቿ ተጋድሎ ከፋሽስቶች ወረራ በቅርቡ ትላቀቃለች። ይልቅስ ጥቁሮች ሁሉ በመተባበር ደቡብ አፍሪካን እና ሌሎች የአፍሪካን ሕዝቦች ከከፋ ባርነት እናውጣቸው እያሉ ይናገሩ ነበር። ከእርሳቸው ጋርም ጀማይካዊው ማርክስ ጋርቬይ (ከ1880 - 1932) እና አሜሪካዊው W.E.B Du Bois (ከ1860 - 1955) ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ደቡብ አፍሪካውያን ፈጽሞ መርሳት የለባቸውም።

     ከኢጣሊያ ወረራ በኋላም ኢትዮጵያ ነፃ ላልወጡ የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች። ድጋፍ ካደረገችላቸው ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ትይዛለች። ANC /African National Congress/ ፓርቲ መሪ የሆኑት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ የወታደራዊ ትምህርት የወሰዱት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። አስገራሚው ነገር ደግሞ የማንዴላ የዜግነት ሁኔታ ነው። የኔልሰን ማንዴላ ፓስፖርት ላይ የተፃፈው ዜግነታቸው “ኢትዮጵያዊ” የሚል ነው። ማንዴላ እንዴት ኢትዮጵያዊ ሆኑ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

     ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ የነጮች አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ሊታሰሩና ሊገደሉ ከሚፈለጉ ሠዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ነጮች በሙሉ የሚጠሏቸው ሰው ነበሩ። የዴሞክራሲ ሀገር የምትባለው አሜሪካ ሳትቀር ኔልሰን ማንዴላን በአሸባሪዎች መዝገብ ውስጥ አስቀምጣቸው ነበር። ስለዚህ አሜሪካ ማንዴላን ብታገኝ እስር ጥፍር አድርጋ በሽብር ወንጀል የምትቀጣ ነበረች። አሜሪካ ማንዴላን ከሽብር መዝገቧ ውስጥ የሰረዘችው እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ነበር። ሌሎችም በነጮች የበላይነት የሚመሩ ፓርቲዎች ለመግደል ከሚፈልጓቸው ሠዎች መካከል ዋነኛው ዒላማቸው ማንዴላ ነበሩ። ታዲያ ከእነዚህ ሁሉ አደጋዎች ማንዴላን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ የራሷ ዜጋ አድርጋቸው በ1954 ዓ.ም ለኔልሰን ማንዴላ ፓስፖርት ሰጠቻቸው። በዚህም ፓስፖርት ማንዴላ በየሀገሩ ድንበር ይሸጋገሩበት ነበር።


    

በዘመነ ደርግ እንኳ በኢትዮጵያውያኖች የሚሰጠው ፓስፖርት ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር የትኛውም ሀገር መጓዝ እንደሚችሉ የሚያሳስብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግስት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ጥላ ስለነበር ዜጎቿ ደቡብ አፍሪካ እንዳይሄዱ በይፋ እገዳ ጥላ ነበር፡፡

 

    ኢትዮጵያ ለማንዴላ የሰጠችው ስም ዴቪድ ማታሳዊ የሚል ሲሆን፣ ሥራው ደግሞ ጋዜጠኛ ነበር። ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ። እኚህን ብርቅ የደቡብ አፍሪካ መሪ ከሞትና ከአደጋ ጠብቃ ለጥቁሮች ነፃነት ድል፣ ብርሃን ሆና ደቡብ አፍሪካ ላይ ያበራች ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያ ዛሬ በስልጣን ላይ ያለው የደቡብ አፍሪካ የጥቁሮች መንግስት እንዲመሠረት ትልቅ የመዐዘን ድንጋይ ሆና ያገለገለች አርማቸው ናት። ይህን ውለታ ደግሞ ኔልሰን ማንዴላም ደጋግመው የተናገሩት ጉዳይ ነው። አፄ ኃይለሥላሴ በግላቸውና በመንግስታቸው ባለሟሎች በኩል ለማንዴላና ለደቡብ አፍሪካ የዋለችው በጐ ነገሮች አያሌ ናቸው።

በቀዳማዊ ኃይለስላሴ አሳሳቢነት ማንዴላ ሽጉጥ ተሰጥቷቸው ምክር ተለግሷቸው፣ መንቀሳቀሻ ፍራንክ ተደጉሟቸው ነው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዙት። ኢትዮጵያ ለማንዴላ ልዩ ሀገር ነበረች። እርሳቸው ራሳቸው በፃፉት Long Walk To Freedom በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ብለዋል፡-

     “ከአክራ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረን ኮንፍረንሱን ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ በረርን። ወደ አውሮፕላኑ ስገባ የአውሮፕላኑ አብራሪ ጥቁር መሆኑን ለማስተዋል ቻልኩ። ብርክ ያዘኝ። አንድ ጥቁር እንዴት አውሮፕላን ሊያበር ይችላል? ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን በራሴ አስተሳሰብ ተናደድኩ። ጥቁሮች የነጮችን ያክል አሪፎች አይደሉም ለሚለው የአፓርታይድ ወጥመድ ውስጥ ተተብትቤ ነበር” (ትርጉም ከረጅም የነፃነት ጉዞ መጽሐፍ)

     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥቁር ፓይለት መብረሩ፣ ሆስተሶቹ በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው፣ ማንዴላን አነቃቅቷቸዋል። ጥቁር ታላላቅ ነገር መስራት እንደሚችል ከአየር መንገዳችን ተምረዋል። የማንዴላን የሕይወት ታሪክ የሚሰሩ የሆሊውድና የደቡብ አፍሪካ ፊልም ሠሪዎች ሁሌም የሚመጡት ወደ ኢትዮጵያ ነው። ማንዴላና ኢትዮጵያ የተሳሰሩ ነበሩ።

     በዘመነ ደርግ እንኳን ለኢትዮጵያውያኖች የሚሰጠው ፓስፖርት ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር የትኛውም ሀገር መጓዝ እንደሚችሉ የሚያሳስብ ነበር። ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግስት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ጥላ ስለነበር ዜጐቿ ደቡብ አፍሪካ እንዳይሄዱ በይፋ እገዳ ጥላ ነበር። ይኸው የደቡብ አፍሪካ የነጮች አገዛዝ እንዲፈርስ ኢትዮጵያ ብዙ ታግላለች። ከአፍሪካ የእግር ኳስ ማኅበር ውስጥ የአፓርታይዱ ሥርዓት እንዲታገድ አድርጋለች። የአፓርታይድ ሥርዓት ከFIFA እንዲሰረዝ ኢትዮጵያ ታግላለች። ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያምም ማንዴላ ከእስር ሲፈቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ሰጥተዋቸዋል።

     ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ አያሌ ድጋፎችን ባታገኝ ኖሮ ዛሬ የምናየው የጥቁሮች መንግስት ወደ ሥልጣን ለመምጣት ረጅም ጊዜ ይወስድበት ነበር። እኔ ራሴ የዛሬ 11 ዓመት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለትምህርት ሄጄ ሳለ የታዘብኩት ነገር ቢኖር፤ በርካታ ድርጅቶች ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ስም ይጠሩ ነበር። ለምሳሌ ከሀብታሞቹ ከተማ ከፖርት ኤልዛቤት ወደ ሮድስ ዩኒቨርሲቲ (ግራሃምስታውን) ከተማ በሚያስኬደው መንገድ ላይ ላሊበላ የሚል ትልቅ ጽሁፍ እናገኛለን። ላሊበላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የበርካታ የንግድ ማዕከላት መጠሪያ ነበር። ሌሎችንም መጠቃቀስ ይቻላል። ግን ዛሬ በዚህ ይብቃ።

     ጉዳያችን የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ መገደልና መዘረፍ ነው። ይህን ሁሉ ውለታ ለደቡብ አፍሪካ የዋለ ሕዝብ እንዲህ መደብደብ፣ መዘረፍና መገደል ይድረስበት? ደቡብ አፍሪካውያን የተደረገላቸውን ውለታ የት ቀቅለው በሉት? የነጮች አገዛዝ በአፓርታይዱ ዘመን ያላደረሰውን ግፍ ዛሬ ያሉት ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች በወንድምና በእህቶቻቸው የአፍሪካ ተወላጆች ላይ ፈፀሙት። ታላቅ ስህተት! ታሪካዊ ሰህተት!

     የደቡብ አፍሪካ መንግሥትም በአግባቡ መጠየቅ አለበት። ለነፃነት ያበቁት ውድ የአፍሪካ ልጆች ከነፃነት በኋላ መዘረፍ፣ መቀጥቀጥ፣ መገዳል አለባቸው ወይ? የአፍሪካ ኅብረት አንድ ውሣኔ ላይ ካልደረሰ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ነገሮች ይፈጠራሉ። አፍሪካውያን አፍሪካውያንን የሚገድሉበት ዘመን መምጣት የለበትም። ዘመኑ የሕብረት ነው! የአንድነት ነው። የሞቱ ወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም። ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን። ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይስጥልን!

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
18937 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 993 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us