እስከ 1966 ዓ.ም ለኢትዮጵያዊያን በውጪ ሀገር ጥገኝነት መጠየቅ አስነዋሪ ድርጊት ነበር

Thursday, 30 April 2015 12:05

በጥበቡ በለጠ

    


     በሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክ የኒቨርሲቲ የፊልም ጥበብን የሚስተምር ኢትዮጵያዊ ወዳጅ አለኝ። ስሙ የማን ደምሴ ይባላል። (የማን ማለት በግዕዝ ቋንቋ ቀኝ እጅ እንደማለት ነው)። ይህ ፊልም ሰሪና ታዋቂ መምህር በአለምአቀፍ ደረጃ የሚታወቅበትን ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቷል። ይህ ዶክመንተሪ ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ- መንግሥት ስልጣንና አስተዳደር እንዲሁም በግል ሰብእናቸው ላይ የሚያተኩር ነው። የማን ደምሴ ይህን የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ታሪክ ዶክመንተሪ ፊልም የሰራው ለደቡብ አፍሪካው ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ቴሌቪዥን ጣቢያውም ለየማን ደምሴ አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖና ተገቢውን ክፍያ ፈጽሞለት ነው የሰራው። የፊልሙ ርእስ፡- TWILIGHT REVELATIONS: Episodes in the Life & Times of Emperor Hale Selassie ይሰኛል።

    ይህ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ዘመን አስተዳደርና ታሪክ የሚቃኘው የየማን ደምሴ ፊልም በኢትዮጵያዊያኖች ከተሰሩ ዶክመንተሪ ፊልሞች መካከል ከፊት የሚሰለፍ ነው። ይህ ዶክመንተሪ ፊልም በውስጡ የያዛቸውን አብይ ጉዳይ በአጭሩ ላስረዳ።

     በዚህ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዶክመንተሪ ፊልም ውስጥ አያሌ ሰዎች ቃለ-መጠይቅ ተደርጎላቸው ይናገራሉ። እነዚህ ተናጋሪ ሰዎች እነማን ናቸው የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ሰዎቹ ታሪክ ጸሐፊዎች፤ ዲፕሎማቶች፤ የጦር መሪዎች፤ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ ሰብእናዎች፤ በንጉሱ ዘመን ፓርላማ አባል የነበሩ እና ቀደም ሲል ንጉሱን ራሳቸውን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች በፊልሙ ውስጥ ተጠይቀው ይናገራሉ።

     እነዚህ ሰዎች በእድሜ የገፉ ናቸው። የህይወትን ውጣ ውረድ ያስተዋሉ ናቸው። የዘመንን መሄድና መምጣት ያዩ ናቸው። በእድሜያቸው የመጨረሻዎቹ ምእራፍ ላይ የሚገኙ ናቸው። እናም በዚህ የህይወት ጫፍ ላይ ሆነው እማኝነታቸውን ሰጡ። ከነዚህ እማኞች መካከል ዛሬ አብዛኛዎቹ በህይወት የሉም። የማን ደምሴ እነዚህን ሰዎች ለማነጋገር የከፈለውን መስዋእትነት በፊልሙ ውስጥ በግልጽ ማየት ይቻላል። ሰዎቹ የተለያዩ የአለማችን ክፍለ-ግዛቶች ስለሚገኙ ፊልም ሰሪው የማን ደምሴ በያሉበት ሀገር እየዞረ ነው ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸው። እናም ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ አስተዳደር የመጨረሻውን ቃላቸውን የተቀበለና ምርጥ ዶክመንተሪ ፊልም የሰራ ሰው ነው።

    በዚህ ፊልም ውስጥ የማን ደምሴ ምንም ነገር አይነግረንም። አይተርክልንም። የሚናገሩትና የሚተርኩት ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው እነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵዊያን ናቸው። ከነርሱ ጋርም ተያይዞ በንጉስ ኃይለስላሴ በስልጣን ዘመናቸው የተቀረጹና ከሰዎቹ ንግግር ጋር የሚገናኙ ምስሎች አብረው ተቀናብረዋል።

    ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ርእሰ ጉዳይ ይህ ፊልም በመሆኑ ነው፤ ስለ ፊልሙ አጭር ማብራሪያ የሰጠሁት። በዚህ በጃንሆይ ዶክመንተሪ ፊልም ውስጥ ከተጠየቁት ሰዎች መካከል በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የቪዛ ክፍል ሀላፊ የነበሩ ወ/ሮ ማርታ ገ/ጻዲቅ የተባሉ ዲፕሎማት ይገኙበታል። እኚህ ዲፕሎማት ሲናገሩ የሚከተለውን ሀሳብ እንደማስታውሰው ሰንዝረዋል።

    “እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ ተማሪ የአሜሪካንን መንግስት ጥገኝነት አልጠየቀም። እደግመዋለሁ! እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ አንድም ኢትየጵያዊ ተማሪ የአሜሪካንን መንግስት ጥገኝነት አልጠየቀም። ይህንን ጉዳይ አሁንም ከስቴት ዲፓርትመንት አጣርቻለሁው“ በማለት ወ/ሮ ማርታ ገ/ጻዲቅ ይናገራሉ።

     የወ/ሮ ማርታ ንግግር ትክክለኛነት ከሌላ ምንጭ ማረጋገጥ ባይቻልም በወቅቱ ከነበራቸው ኃላፊነት አንፃር ሲታይ አስተያየቱ ለእውነት የቀረበ ነው። ሁለተኛው ደግሞ እደግመዋለሁ እያሉ በልበ ሙሉነት ደግመው መናገራቸው ነው። እናም እስኪ እዚህ 1966 ዓ.ም ላይ ቆም ብለን ኢትዮጵያን እናስባት! ስደት የጀመረችው ከዚህ በኋላ ነው? ምነው ኢትዮጵያዬ ምን ሆንሽብን? ምን ገጠመሽ እንበላት።

     የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ረጅሙ የስልጣን ጉዞ 1966 ዓ.ም ማክተሚያው ነበር። ስርአቱ ሲያበቃ አያሌ ጉዶችን መከራዎችን አስከትሎ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ፈነዳ ተባለ። ‘ፈነዳ’ የሚለው ቃል ራሱ ጤነኛ አልነበረም። መፈንዳት ብዙ ፍንጥርጣሪዎች አሉት። እነዚህ ፍንጥርጣሪዎች ደግሞ ብዙ ነገር ይጎዳሉ። እናም አብዮት ፈነዳ!

      ፍንዳታውን ተከትሎ ደርግ ፊት አውራሪ ሆኖ መጣ። በደርግ በተጻራሪ የቆሙ አያሌ የፖለቲካ ቡድኖች መጡ። በተለይ ቀደም ሲል በንጉሱ ዘመን የተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ መሬት ላራሹ ጥያቄ እና አዲስ ሥርአት የመናፈቅ ፍላጎት የጎለበተባቸው ወጣቶች ኢ.ሕ.አ.ፓ ተብሎ በሚጠራው የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ተደራጁ። ሌሎች መ.ኢ.ሶ.ን ተባሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች በስፋት መጡ። ሀገሪቱ በታሪኳም አስተናግዳቸው የማታውቀው የፖለቲካ አስተሳሰቦች ተግተልትለው መጡ። እነዚህን ሁሉ አስተሳሰቦች ማን ያስተናግዳቸው? ዘመኑ ስር-ነቀል ለውጥ የመጣበት ነው ተባለ። ስር ከተነቀለ ደግሞ ማደግ መፋፋት የለም። ያው ሞት ነው።

     እናም የአብዮቱ ፍንዳታ መላው ኢትዮጵያ ላይ አስተጋባ። ጆሮ አደነቆረ። ትውልድ ፈነዳ። ተቀጣጠለ። ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ተባብሎ ቤት ለቤት ጎዳና ለጎዳና መገዳበል መጣ። የኢትዮጵያ አደባባዮች በልጆቿ ደም ጨቀዩ። ሀይ የሚል የለም! እናቶች በልጆቻቸው ሞት አነቡ። የሀዘን ማቅ ለበሱ። ያቺ ገናናይቱ ኢትዮጵያ በሞት መንፈስ ተወረረች።

     ለዚህች ሀገር አዲስ ሀሳብና ዘመናዊ አስተሳሰብ አመጣለሁ ብሎ ያሰበ፤ የጻፈ፤ የዘመረ፤ የታገለ ጭንቅላት ሁሉ መና ቀረ። በህይወት የተረፈው እግሬ አውጭኝ እያለ ኢትዮጵያን ለቆ መብረር መጓዝ ጀመረ። ስደት የኢትየጵያዊያን መገለጫ ሆነ። “ከሀገሩ የወጣ ሀገሩ እስኪመለስ ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ” የሚለው ምሳሌያዊ ንግግርም የስደተኞች አፍ መፍቻ ቋንቋ ሆነ። የአብዮት ፍንዳታው እና ስር-ነቀል ለውጡ የሚያስተናግደው አጥቶ አንድ ትውልድን ሙልጭ አድርጎ በልቷል።

     በዘመነ ደርግ ራስን ከግድያ ለማዳን ዋነኛው አማራጭ ከኢትዮጵያ መውጣት ሆነ። ስደት! እንደውም አንድ ቀልድ ቢጤም ነበር። የስርአቱ መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም በድንገት ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሄዱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ረጅም ሰልፍ ሰርተው ያያሉ።

“ይሄ የምን ሰልፍ ነው?” በማለት ቆጣ ብለው ጠየቁ።

“ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ናቸው“ አለ መላሹ ፈራ ተባ እያለ።

     ኮ/ል መንግስቱም “ሁሉም የሚሄድ ከሆነ እኛ ብቻችንን እዚህ ምን እንሰራለን?” ብለው ለመሄድ ተሰለፉ። በዚህ ጊዜ ሊሰደድ የተዘጋጀው ሰልፈኛ ሰልፉን በትኖ ተመለሰ። አንድ ደንብ አስከባሪ ምነው ምን ሆናችሁ ነው ጉዞዋችሁን የምትሰርዙት?” ቢላቸው እነርሱም እንዲህ አሉ ፡-

     “እኛ የምንሄደው የእሱን ግድያ ሸሽተን ነው። እሱ ከሄደልን በሐገራችን እንኖራለን” አሉ እየተባለ በልጅነታችን የሚነገረን ቀልድ ነበር።

     ከ1966 ዓ.ም በኋላ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተሰብስበው ለዘመናት የኖሩበትን ስርዓተ ማህበር በማፍረሳቸው ሰብሳቢ አጥተው ተበተኑ። አጼ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመናቸውን ክፉኛ ለጥጠውት ለዘመኑ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ባለመስጠታቸው ትውልድ ፈረሰ፤ ሀገር ተጐዳች፤ ለውጥ አቀንቃኙ ወጣት ደግሞ የሐገሩን ባሕል፣ ታሪክ፣ ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ ፍልስፍና በመዋጡ ጥንታዊቷ፤ የእድሜ ባለፀጋዋን ኢትዮጵያን ካለ አቅሟ ወዘወዛት። ኢትዮጵያ ትቅደም እያለ እርስ በርሱ እየተጨፋጨፈ ባልቴቷን ኢትዮጵያ ትንፋሽ አሳጥሮ አስሮጣት። እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ትንፋሽዋን ሰብሰብ አድርጋ ቁጭ ብላ ተረጋግታ ማሰብ አልቻለችም።

     አንድ ጊዜ ማለትም 1995 ዓ.ም ዛሬ በሕይወት የሌሉትን አለቃ አያሌው ታምሩን ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። አለቃ አያሌው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሊቃውንቶች ሊቃውንት /ሊቀ-ሊቃውንት/ የነበሩ ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ግብረ-ገብን እስከ ማስተማር የደረሱ አይነ ስውር ሊቅ ነበሩ። እናም ከእርሳቸው ጋር በነበረኝ ቆይታ አንድ ጥያቄ ጠየኳቸው።

ዓይነ ስውር በመሆንዎ የሚያዝኑበት የሚቆጭዎት ነገር አለ አልኳቸው

የለም አሉኝ

እንዴት የለም?” አልኳቸው

እንደውም የኢትዮጵያን መቸገርና መከራ ሳስተውል እንኳንም አይኔ ጠፋ እላለሁ አሉ። ቀጠሉና ይህን ታሪክ አጫወቱኝ፡-

“አንድ ቀን በጣም ተበሳጨሁና ወደ ቤተ መንግስት ሄድኩ። ቤተ መንግስት ተፈትሸው ከማይገቡ ሰዎች መከከል እኔ አንዱ ነበርኩ። የሄድኩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ለማነጋገር ነበር። እንደተናደድኩ በቤተ መንግስት እልፍኝ ውስጥ ደረስኩ። ቆምኩ። ጃንሆይ ለነገር እንደመጣሁ ገብቷቸዋል።

“ምን ሆነህ መጣህ?” አሉኝ።

    “ጃንሆይ የሚሰራው ነገር ልክ አይደለም እርስዎ የሀገሪቱን ወጣት ሁሉ ለትምህርት ብለው አንዴ አሜሪካን፣ አንዴ መስኮብ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እየላኩ ትውልዱ ሀገሩን እንዳያውቅ እየተደረገ ነው። ተምሮ የሚመጣው የአሜሪካንን፣ የመስኮብን፣ የፈረንሳይን፣ የእንግሊዝን ባሕልና ታሪክ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ ይህ ወጣት ኢትዮጵያን ስለማያውቃት የተማረበትን ሀገር ቅራንቅቦ ነው ይዞ መጥቶ ኢትዮጵያ ላይ ሊጭን የሚፈልገው። ይህ ደግሞ ለእርስዎም ሆነ ለሀገሪቱ ጠንቅ ነው አልኳቸው።

     “ጃንሆይ ዝም አሉኝ። ምንም መልስ አልሰጡኝም። ዝምታው ሲበዛብኝ ደጋግሜ እጅ ነሳሁ። ከዚያም አንድ ነገር ከአፋቸው ወጣ።

እንኳንም አይንህ ጠፋ!” አሉኝ።

     ”ጃንሆይ ልክ ናቸው። አልሳሳቱም። እኔም እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያን መከፋትና ችግር ሳስተውል እንኳንም ዐይኔ ጠፋ እላለሁ” ሲሉ አለቃ አያሌው ታምሩ ከዛሬ 12 አመታት በፊት አጫውተውኝ ጋዜጣ ላይ አትሜዋለሁ።

     ዐጼ ኃይለስላሴ “እንኳንም ዐይንህ ጠፋ“ ያሏቸው፤ እርሳቸው እንደ ሀገር መሪ ሆነው ኢትዮጵያን ሲያስቧት ብዙ የሚያስጨንቃቸው ነገር በመኖሩ እንደሆነ አለቃ በወቅቱ አብራርተውልኛል። የሆኖ ሆኖ ኢትዮጵያ ፊውዳሊዝምን የመሬት ከበርቴን ሶሻሊዝምን አስተናግዳለች። እነ ካፒታሊዝምን ኢምፔሪያሊዝምን ቡርዣውን በመፈክር ስታወድም ኖራለች። አሁን ደግሞ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ውስጥ ነች። በነዚህ ሁሉ አስተሳሰቦች ውስጥ የኢትዮጵያ ባህል ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ እንደምን ተካቷል የሚለው ጥያቄ ዛሬም መነጋገሪያችን ቢሆን ጥሩ ነው።

     የዛሬ 8 አመት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አማካይነት የኢትዮጵያ የልቦለድ ስነ-ጽሁፍን መቶኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ አንድ ዝግጅት በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ዝግጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆነው ቴዎድሮስ ገብሬ አንድ የጥናት ጽሁፍ ያቀርብ ነበር። በዚህ የጥናት ጽሁፍ ውስጥ ኢትዮጵያን ሲጠራት “ወይዘሪት ኢትዮጵያ“ ይላል። “ወይዘሪት ኢትዮጵያ“ የሚለው አባባል ተደጋግሞ በቴዎድሮስ ገብሬ ጥናት ውስጥ ተጠራ። ጥናቱ ቀርቦ ሲጠናቀቅ ለጥያቄና መልስ እንዲሁም ለአስተያየት መድረኩ ክፍት ሆነ።

     በዚያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆነው አቶ ወንደወሰን አዳነ ስለ ወይዘሪት ኢትየጵያ ጉዳይ ጠየቀ።

     “ኢትዮጵያ የሶስት ሺ አመት አሮጊት ሆና ሳለ ለምን ወይዘሪት ኢትዮጵያ እያልክ ትጠራታለህ? “ ተባለ። ጥያቄው ለቴዎድሮስ ገብሬ ከባድ ነው ብለን አስበን ነበር። ግን ቴዎድሮስ በቀላሉ መልሶት አዳራሹ ውስጥ የነበረው ህዝብ በሙሉ አጨበጨበለት። እሱም እንዲህ አለ፡-

“ኢትዮጵያ ሶስት ሺ አመት ቢሆናትም እስከ አሁን ድረስ ባል አላገኘችም። እናም ድንግል ናት። ወይዘሪት ኢትዮጵያ

አለ። ታዳሚው በሳቅና በጭብጨባ አዳራሹ ውስጥ አስተጋባ።

    ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዋን ልጆችዋ በጋራ ተስማምተው ባለመጠቀማቸው ድንግልናዋ እስካሁን አለ። አንዱ የስደት ምንጭ ይህን ጸጋ ተረጋግቶ የለመጠቀም ችግር ነው። ኢትየጵያዊያን ከ1966 ዓ.ም በኋላ እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ስደት ውስጥ ናቸው። ስደት ህጋዊና ህገ-ወጥ እየተባለ እየተጠራም ነው። ምንም ተባለ ምንም ኢትዮጵያዊያን ስደት ውስጥ ናቸው። ስደትን ለመቀነስ ኪነ-ጥበብ፤ ባህል፤ ፖለቲካዊ የአስተሳሰብ መስመር፤ ኢኮኖሚና ሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች ብዙ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር። ግን ዛሬም መንገዱ ክፍት ነው። ጉዞው አላባራም እንደቀጠለ ነው። ምን ይሻላል።

ይምረጡ
(13 ሰዎች መርጠዋል)
10476 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us