እናት ለምን ትሙት ትሒድ አጎንብሳ ታበላ የለም ወይ በጨለማ ዳብሳ

Thursday, 07 May 2015 17:41

በጥበቡ በለጠ 

 

     የዛሬ ጽሑፌ የተፀነሰው የእናትነትን ርዕሰ ነገር ከወጣቱ ጓደኛዬ ከእሱእንዳለ በቀለ ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ነው። እሱእንዳለ በቀለ በተለይ የሚታወቅበት ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን እናቶችን በየዓመቱ ሲያሰባስብ፣ ሲያስደስት እና ሲዘክር በመቆየቱ ነው። ከዚህ በፊት በሂልተን ሆቴል፣ በኢምፔሪያል ሆቴል፣ በጣይቱ ጃዝ አምባ፣ በጋንዲና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች፣ በካፒታል ሆቴል ውስጥ የእናቶችን ቀን እያከበረ በጣም ጥሩ የሆነ ማህበራዊና ባሕላዊ ዕሴት እየገነባ የሚገኝ ወጣት ነው። እናም የፊታችን ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ውስጥ ከ9-12 ድረስ በሚቆይ ዝግጅት ለሰባተኛ ጊዜ የእናቶቻችንን በዓል ሊያከብር መዘጋጀቱን ሲነግረኝ ቀልቤ ተሰረቀ። ከእርሱ ጋርም ቁጭ ብለን ረጅም ሰዓት ወስደን እናትነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ ምንድን ነው? ብለን አወራን። የዛሬ ፅሁፌ የዚሁ ወጋችን ውጤት ነው።

     በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ እናትነት ልዩ ስፍራ ሲሰጠው ኖሯል። ኢትዮጵያ እናትነት በሁለት መንገዶች ትገልፃለች። አንደኛዋ እናት እንደ ሰው አርግዛ፣ አምጣ፣ ወልዳና አሳድጋ ለቁም ነገር የምታበቃው እናት ነች። ሁለተኛዋ እናት ሀገር ነች። እናትነትን በሀገር መመሰል፣ መግለፅ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ በሰፊው ጎልቶ የምናገኘው ነው።

    ጥላሁን ገሠሠ መድረክ ላይ ሆኖ በዓይኑ እንባ እየፈሠሠ እንዲህ ነበር ያዜመው፡-

“ክብሬ እናቴ ሀገሬ የኔ መመኪያዬ፣

አንቺው ነሽ ኢትዮጵያ መከታ ጋሻዬ፣

ጥቃትሽን ከማይ በሕይወት ቆሜ፣

ስለ ክብርሽ እኔ ልሙት ይፍሰስ ደሜ።

     የእናትነት መገለጫ ቃሉ፣ ዜማው፣ ቋንቋው ጥልቅ ነው። ኪነ-ጥበባችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ እናገኘዋለን። ዛሬ በሕይወት የሌሉት ድምጻዊያኑ ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ እና ብዙነሽ በቀለ ሙዚቃ ውስጥ ካገነኗቸው ስራዎቻቸው መካከል ስለ እናት ያዜሟቸው ሙዚቃዎች ናቸው። የናትነትን ርዕሰ ጉዳይ ይዘው ብቅ የሚሉ የጥበብ ውጤቶች የታዳሚን መንፈስና ቀልብ በቀላሉ የመቆጣጠር አቅማቸው ትልቅ ነው።

     የአፄ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል /Chronicle/ ፀሐፊ የነበረውና የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የቤት ውስጥ አስጠኚ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ደብተራ ዘነብ፣ ከመቶ አርባ ዓመት በፊት በፃፈው የፍልስፍና ፅሁፉ እናትነትን ሀይማኖታዊ ዳራ ሰጥቶት ገልፆታል። ደብተራ ዘነብ “መፅሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወ መንፈሳዊ” በተሰኘው መፅሐፉ የእየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ያስታውሰናል። እየሱስ በቀራኒዮ ሲሰቀል ወዳጆቹ መላዕክትና ቅዱሳኑ ራሳቸው አብረውት አልነበሩም። ይህን ሁኔታ ነው ደብተራ ዘነብ በፍልስፍና ጽሁፉ ውስጥ የሚተቸው። ከእናቱ ከማርያምና ከሌሎቹ ሴቶች በስተቀር አጠገቡ ማን አለ? እያለ በሰላ አፃፃፉ ያስታውሰናል። እናት በልጇ ነገር ሁሉ ከፊት እንደምትሰለፍ ዘነብ ኢትዮጵያዊ ውብ በሆነው መፅሐፉ ዘላለማዊ ትርክትን አስቀምጦልን አልፏል።

     እናትነት በኪነ-ጥበባችን ውስጥ ምን እንደሚመስል ለመግለፅ ሰፊ የሆነ ፅሑፍ ያስፈልገናል። ስለዚህ በቀላሉ ገብተንበት በቀላሉ የምንወጣበት አይደለም። እናት የአለሙን ፈጣሪ እየሱስ ክርስቶስን ወልዳለች፣ አጥብታለች፣ አሳድጋለች። እናት በሰው ልጆች ውስጥ ወደር ያልተገኘለትን የሳይንስ ምርምርና ግኝት ያደረገውን አልበርት አንስታይንን ያክል ፍጡር አርግዛ፣ ወልዳ፣ አጥብታና አሳድጋ ለዓለም አበርክታለች። እናት ሰር አይሳክ ኒውተንን የሚያክል የምርምር ሰው ለዚህች ምድር አበርክታለች።

     እናትነትን ለመግለፅ ቅኔ ቢደረድሩ፣ ቋንቋ ላይ ቢራቀቁ፣ ዜማ ላይ ቢፈላሰፉ. . . ተገልፃ አታልቅም። እናትነት ጥልቅ ነው። ውስብስብ ነው። ምስጢር ነው። ዲስኩረኛው ባለ ወግ፣ በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ስለ እናትነት ሲያወጋ፣ እናት ልጇ አድጎ ትልቅ ሰውም ቢሆን ራሱን ቻለ አትልም። ለእሷ አሁንም ልጅ ነው። እንደ ልጅነቱ ሁሉ በጉልምስናው ጊዜም ትጨነቅለታለች ብሏል።

     ልጅ መጀመሪያ የሚያውቀው ፈጣሪ እናቱን ነው። ከናቱ ጡት ይጠባል። ይመገባል። ይፀዳዳል፣ ለእሱ እናቱ ናት ፈጣሪው። ከዚህ በፊት አንድ ፅሑፍ አንብቤ ነበር። ፀሐፊው መምህር ሰለሞን ፋንቱ ይባላሉ። እርሳቸው በፃፉት ፅሑፍ “እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ ስለማይገኝ እናቶችን ፈጠረ” የሚል ሃሳብ ያለው ነው።

     ይህችው ፈጣሪ ነች የምትባለው እናት ኢትዮጵያ ውስጥ ለየት ያለ ትርጓሜ አላት። ለምሳሌ አውሮፓውያን እናቶች ልጆቻቸውን እስከ 18 ዓመት ድረስ ካሳደጉ በኋላ ለመተያየት እንኳን አይችሉም። ልጆች ራሳቸውን ከቻሉ ወደ ወላጆቻቸው ዘነድ እምብዛም አይመጡም። ለአብነት ያህል ኖርዌጂያን /የኖርዌይ/ እናቶች እና የጀርመን የሌሎችም እናቶች በልጆቻቸው ናፍቆት እንደሚሰቃዩ ጥናቶች ያሳያሉ።፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ እናትና ልጅን የሚለያያቸው ሞት ብቻ ነው። ፍቅራቸው እስከ መቃብር ይወርዳል።

    ኢትዮጵያዊት እናት ሁሌም ቅኔ ሲደረደርለት ቢኖርም ጥልቅ እና ውስብስብ የአንጀት የደም ምስጢሯ ገና ተገልፆ አላለቀም።

     “ቢርቁት የማይርቅ የናት ሆድ ብቻ ነው” ተብሎ ቢዜምላትም፣ ወይም ደግሞ ፋጡማ የተባለች ወጣት እንደገጠመችው፤

“ሆድሽ ቤቴ ልብሽ የኔ፣

ደምሽ ደሜ ፍቅርሽ ለኔ፣

ያነቺ ሁሉ ሆኖ ለኔ፣

ልጄ አትበይ፣ በይኝ እኔ።

     ብትልም እናት ገና አልተገለፀችም። አንድ ገጣሚ ደግሞ አየ አየና ቢቸግረው እንዲህ አለ፡-

ቢሰፈር ቢለካ፣

እናትን የመሰለ

አይገኝም ለካ!

     ስለ እናት የተገጠሙ ስንኞች አያሌ ናቸው። ስፍር ቁጥር የላቸውም። ሁሉም ታዲያ ፍቅሩን ነው የሚገልፅላት። ሌላ ገጣሚ ደግሞ እንዲህ አለ፡-

የሕይወቴ መብራት የኑሮዬ ፋና

የመኖሬ ምስጢር እናቴ ናትና

አደራ አምላኬ አኑራት በጤና

     ይህ ገጣሚ እናቱ በጤና እንድትኖርለት የሚመኝ ነው። ሁሉም የናቱን ዘላለማዊነት ይመኛል። እናቴ ኑሪልኝ ይላል። እሌኒ በየነ የምትባል ሴት ደግሞ ከዚሁ ጋር ተመሳሳሰይነት ያለው ግጥም ስለ እናቷ አቅርባለች።

እማ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ፣

ዘመድና ወገን የለኝ ከጎኔ፣

የለኝም ጓደኛ የኔነው የምለው፣

ያላንቺ እናቴ ሕይወቴ ባዶ ነው።

ባክሽ አትሙችብኝ ኑሪልኝ ዘላለም፣

አመሌን የሚችል ካንቺ ሌላ የለም።

     እናት ገመና ሸሻጊ ናት። እናት ቤት ናት፣ መጠለያ ናት። ብዙ ዘመድ ናት፣ ጓደኛ ናት። ለዚህም ነው ገጣሚዋ ከላይ የሰፈሩትን ስንኞቿን የደረደረችው። አንዳንዶች “እውነተኛ ፍቅር የማየው ከናቴ አይን ነው” በማለት ይናገራሉ።

እናት እናት አሏት ስሟን አሳንሰው፣

አለምን ሁሉ የምትበልጠዋን ሰው።

     በማለት ትልቅነቷን ለመግለፅ ሁሉ ተሞክሯል። ዓለምን ሁሉ የምትበልጥ ግዙፍ ስብዕና ያላት ናት እያሉ ገጣሚያን ይደረድሩላታል። ይህን ከላይ የፃፍኩትን ግጥም የጎጃም ሰዎች ደግሞ እንዲህ ይሉታል።

እናት እናት አሏት ስሟን አሳንሰው፣

አባይና ጣናን የምትበልጠዋን ሰው።

     ጎጃም ውስጥ ላሉ የገጠር ሰዎች የትልቅነት ማሳያቸው አባይና ጣና ነው። እርግጥ ነው፤ አባይ ገና ከፍጥረት አለም ጽንሰት በፊት ጀምሮ ሲፈስ የኖረ ትልቁ ወንዝ ነው።

     በኢትዮጵያ የግጥም /የአገጣጠም/ ስልት ውስጥ መንቶ /Couplet/ የሚባል አፃፃፍ አለ። ይህም ሁለት ስንኞችን በመደርደር የሚገጠም ነው። በሁለት ስንኞች የዓለምን ውጣ ውረድ ሁሉ የሚገልፁ ገጣሚያን ያሉባት ሀገር ነች። ሁለት ስንኞች በዚህች ሀገር ውስጥ ብዙ የሆድ ሆድ ጨዋታዎችን ሲያቀባብሉ የኖሩ ናቸው።

እናቴን አሰብኳት በሶስት አማርኛ፣

ሲርበኝ ሲጠማኝ ታምሜ ስተኛ።

     እነዚህ በሁለት መስመር የሚገጠሙ ስንኞች የውስጥ ራሮትን የመግለፅ ከፍተኛ አቅም አላቸው። ከላይ የተገጠሙትን እንኳ ብናያቸው ብንመረምራቸው ሰፊ ትንታኔ የሚያሰጡ ናቸው። ግን ዝርዝሩን በሁላችንም ልቦና ውስጥ አስቀምጠነው ወደ ሌሎቹ ሃሳብ እናምራ።

     ብዙ ሰዎች በቤታቸው ግድግዳ ላይ ጥቅስ ሲያስቀምጡ የእናት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ “ያለ እናት አለም ጨለማ ናት” የሚል ጥቅስ አንብቤያለሁ። ይህ ማለት እናት ብርሃን ናት የሚለውን አባባል አንድን ወሰድ ያደርጋል። ለዚህም ነው ቀጣዩ ግጥም እናቴን አደራ የሚለው።

ከማር ጭማቂ ላይ አይወጣም መራራ፣

እባክህ አምላኬ እናቴን አደራ።

     በዓለም ላይ ከሚደርሱ ክፉ ነገሮች መካከል የእናት እና የልጅ በሞት መለያየት ነው። ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ደግሞ ይከፋል። ምክንያቱም የናትና የልጅ ቅርብርብ የማያረጅ የማይጠወልግ፣ የማይደበዝዝ በመሆኑ ነው። ሁሌም አዲስ ነው። ለዚህም ነው ቀጣዩ ግጥም ከባለብዕረኞች ብቅ ያለው፡-

እናቴ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ፣

ከጎኔ ሳጣሽ ይባክናል አይኔ።

     እዚህ ላይ አንድ ነገር ማንሳት ይቻላል። በተለይ እኔና እሱእንዳለው በቀለ ስለዚሁ በኢትዮጵያ ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ስለሚከበረው የናቶች ቀን ስንጨዋወት አንድ ነገር ተነሳ። ነገሩ ቀፋፊ ቢሆንም ብዙ ሃሳቦች በውስጡ አሉት። ይህም “እናት መቼ ትሙት?” የሚል ጥያቄ ነው። ሞት አይቀርምና እናት መች ትሙት?

     የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የሆነው ፍፁም አስፋው /የማለዳ ኮከቦች የተሰጥኦ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅ/ ስለ እናቱ አንድ አስገራሚ ግጥም አቅርቧል። የግጥሙ ሃሳብ የናትን ሞት በውስጡ የያዘ ነው። ፍፁም ሲገልፅ “እናቴ ሞትሽን ከኔ በፊት ያድርገው” እያለ ነው። “ራስ ወዳድ ሆኜ አይደለም፤ አንቺ ለኔ ያለሽን ፍቅር ስለማውቀው እኔ ሞቼ ብታይ እጅግ ትጎጅብኛለሽ ብዬ ነው” እያለ ግጥሙ ትረካ ያቀርባል። ብዙ ጊዜ በባህላችን “ካንቺ/ካንተ በፊት ሞቴን ያድርገው” ነበር የምንለው። ግን በፍፁም አስፋው ግጥም ውስጥ “ሞትሽን ከኔ በፊት ያድረገው” የሚል ሃሳብ የሚያፀባርቅ ነው።

     እናት በዚህ ጊዜ ትሙት የሚል ሃሳብ የሚናገር ሰው ማግኘት ከባድ ነው። ግን እናት በአፀደ ስጋም ብትለይ በልጆቿ ነብስ ውስጥ ህያው ናት።

እናት ለምን ትት ትሒድ አጎንብሳ

ታበላ የለም ወይ በጨለማ ዳብሳ

     የእናትነትን ርዕሰ ጉዳይ አንስተን መቋጫ የለውም። የእናት ርዕስ አያልቅም። ትውልዶች እየመጡ ሲፅፉት ይኖሩታል እንጂ አያልቅም። ታዲያ ይህን የማያልቅ ርዕሰ ጉዳይ ቢያንስ በዓመት አንዴ እየተሰበሰብን እናቶቻችንን እናመስግን፣ እናስደስት፣ ያጣናቸውንም እናቶች በፍቅራቸው ገፀ-በረከት እንዘክራቸው ብሎ ወጣቱ እሱእንዳለ በቀለ ለሰባተኛ ጊዜ በካፒታል ሆቴል ውስጥ ግንቦት ሁለት ቀን ከ8-12 ሰዓት ክብረ-በዓል አዘጋጅቷል። ሁላችንም እናቶቻችንን ይዘን እንድንመጣ እና የተለዩንንም እናቶች እንድንዘክራቸው ጋብዞናል።

ይምረጡ
(144 ሰዎች መርጠዋል)
38757 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 927 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us