ጋዜጠኛውና ደራሲው አብርሃም ረታ ዓለሙ

Wednesday, 13 May 2015 11:34

በጥበቡ በለጠ

    ሰሞኑን ደራሲ ብርሃኑ ስሙ ከቢሮዬ ድረስ መጣና አንድ መፅሐፍና የጥሪ ካርድ ሰጠኝ። መፅሐፉ “አባቶችና ልጆች እና ሌሎች ታሪኮች” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ደራሲው ደግሞ ዛሬ በአካል ከኛ ጋር የሌለው የቅርቡ ወዳጃችን አብርሃም ረታ ዓለሙ ነው። የጥሪ ካርድ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- “አባቶችና ልጆች በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መፅሐፍ አብረን መርቀን እንድንገልፀው ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ አዳራሽ እንዲገኙልን በማክበር ጠርተነዎታል። በምርቃውም የፀሐፊውን 7ኛ ዓመት መታሰቢያን እንዘክራለን። ከቤተሰቡ” ይላል የጥሪው ካርድ፡

    እነዚህ ቅፅበቶች ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ፣ እንድቆዝም አድርጎኝ ወደኋላ በሃሳብ ተጓዝኩኝ። አብርሃምን አስታወስኩት። ከተለየን 7 ዓመታት ተቆጠሩ። “ወይ አብርሽ. . . .” አልኩኝ።

    ከአብርሃም ጋር ስንገናኝ የሚያወራኝ ጨዋታ የይርጋዓለም ከተማን ልዩ ልዩ ትዝታዎችን ነበር። የዛሬን አያድርገውና ይርጋዓለም ከተማ የደቡብ ኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ የነበረች ወይም የቀድሞው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ ሆና ለረጅም ጊዜ አገልግላለች። ከይርጋለም በፊት ሐገረ-ሰላም የምትባለው ከተማ ነበረች የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ። ሐገረ-ሰላም የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ መቀመጫ ነበረች። በኋላ ደግሞ ታላቅነቷን የራስ ደስታ መቀመጫ ለሆነችው ለይርጋለም ከተማ አስረከበች። ባለቅኔዎችም ይህን የዘመን መቀያየር አጢነው የሚከተለውን ተቀኙ፡-

ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪወስደው፣

ሐገረ-ሰላምን ይርጋለም ወረሰው።

    አሉ። ይርጋዓለም ወርቃማ ዘመን አሳልፋለች። የደቡብ ኢትዮጵያ ምርጥ ልጆች ከያሉበት እየተሰባሰቡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ነበረች። አያሌ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ወልዳና አሳድጋ ለኢትዮጵያ ያበረከተች ብርሃናማ ከተማ ሆና ኢትዮጵያ ላይ ስታንፀባርቅ ቆይታች።

    ይርጋለም ታላቁን ባለቅኔ ፣ ፀሐፊ፣ ተውኔት፣ ሐያሲ እና ተመራማሪውን ደበበ ሰይፉን የሚያክል ሰው ያፈራች ከተማ ነበረች። ዛሬ ስሙንና ስራዎቹን የምናነሳሳለት ወዳጃችን አብርሃም ረታ ዓለሙ ከአራት መቶ በላይ ግጥሞችን የፃፈ ሲሆን፣ ከነዚህ ግጥቹ መሀል ደግሞ እዚያው የአድባር የቄዬው ተወላጁ ስለሆነው ስለ ደበበ ሰይፉ ሰማይ ላይ የሚል ርዕስ ያለው ግጥም ፅፎለታል።

 

“ለምን ሞተ በሉ፣

ከዘመን ተጣልቶ

ከዘመን ተኳርፎ. . .”

በል ብለህ ባዋጅ

ግጥም ፅፈህ ያለፍክ

ቅኔ ነግረህ ያወጅክ. . .

አንተ ብቻም ሳትሆን

ዘመኑ ከዘመን - እርስ በርሱ ተኳርፎ፣

አላየህም እንጂ

እንዲህ ለሚቀረው

ሁሉም ነገር አልፎ፤

የዘመን ኩርፊችን፣ ከስፍር፣ ከልኬት፣

      ከገመታ ተርፎ፤

ዝምታ አደንዝዞት

ተቀምጧል ደምብሾ

      በላዩ ተቆልፎ።

ባጭር ርቀት መካከለኛ

ባካል ሩጫ አንደኛ

      . . . አልወጣህም’ንጂ. . .

በመንፈሱ ግምት - በፀጋ ጥሪቱ

የኮራው የደራው ዓምድህ ባይቀጠፍ፣

የቅኔህ ረመጥ -የግጥምህ እሳት

      ከገበታው ሰማይ ወለል ላይ ቢነጠፍ፣

      ባልማዝ ያጌጠውን የዣንጥላ መርገፍ፣

            እንደ አምድ ወደላይ

            እንደ አድማስ ወደጎን

      ብናቀጣጥለው ኪነትክን እንደጧፍ፣

      ስምህ ርችት ነበር

      ለዓውዳመት እሚተኮስ

            ሰማይ ላይ የሚጣፍ

            ሰማይ ላይ የሚጣፍ

            ሰማይ ላይ የሚጣፍ።

    በማለት አብርሃም ረታ ዓለሙ ለደበበ ሰይፉ ገጥሞለታል። ይህን ግጥም የፃፈው አብርሃም ረታ ዓለሙ ራሱ ስሙ ርችት ነው። ለአውድዓመት እሚተኮስ ነው። ሰማይ ላይ የሚጣፍ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ስነ-ፅሁፍ ሥራዎቹ ዛሬም አብረደነው እንድናወጋው ስለሚያስገድዱን ነው።

    ደበበ ሰይፉ ከዘመን ተኳርፎ አለፈ እንበል። እሱም ብሏልና። የኛው አብርሃምስ ከዘመን አልተኳረፈም?

    አብርሃም ረታ ዓለሙ ግንቦት 11 ቀን 2000 ዓ.ም በድንገተኛ ህመም በግማሽ ቀን ውስጥ ሕይወቱን ከማጣቱ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል እስር ቤት ውስጥ ነበር። ይህ ደግሞ የጋዜጠኝነት ሙያው ያስከፈለው መስዋዕትነት ነበር። ከእስር ቤት እንደወጣም እፎይ ብሎ ሳይረጋጋ ሕይወቱ አለፈች። ይህች በጣም የሚወዳት ኢትዮጵያ ደጋግማ አስረዋለች ወይም አሳስረዋለች። አብረሃምም ሰበበኛ በሚለው ግጥሙ እስራት ያበዛችበትን ኢትዮጵያ እንዲህ ገልጿል፡-

 

አገሬ. . .

ባኮርባጅ በጅራፍ በለበቅ፣

በወህኒ ሰንሰለት ሽብልቅ፣

አሰረችኝ ሶስቴ. . .

በተማሪነቴ በ15 ዓመቴ፣

      ገረፈችኝ አስራ፤

      ‘ለምን?’

ድንጋይ ወረወርክ

      ዐድማ መታህ . . . ብላ።

በ25 ዓመቴ

      በመምህርነቴ

      ድንጋይ አስወረወርክ

            አሳደምክ. . . ብላ።

በ45 ዓመቴ፣

      በጋዜጠኝነት

      ሕዝብን አነሳስህ

            ቀስቀስክ

            አሳመፅክ. . . ብላና አስብላ

ድንገት እድሜ ባገኝ

ተጨማሪ ዘመን

በዓለም ላይ ለመኖር

እኔኑ ለማሰር

ሌላኛው ምክንያቷ

አገሬ ምን ይሆን?

    በማለት አብርሃም ረታ ዓለሙ ኢትዮጵያን ጠይቋት ነበር። ነገር ግን እስራቱ ደከመው መሰለኝ ድንገት አለፈ።

    አብርሃም ረታ ዓለሙ በርካታ የሥነ-ፅሁፍ ስራዎቹን ያበረከተ ታታሪ ባለሙያ ነበር። ከነዚህ ስራዎቹ ውስጥ የተወሰኑት በህይወት እያለ ታትመውለታል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. 1. ቢላዋና ብዕር -የዶ/ር አብርሃም ፈለቀን የሕይወት ታሪክና የግጥም መድብል አዘጋጅቶ በማሳተም (1997 ዓ.ም)
  2. 2. አልን ተባልን አስባልን እና ሌሎችም ወጎች (1998 ዓ.ም)
  3. 3. አባባ ሰው የለም እና አከራይ ተከራይ አካከራይ - ልቦለድና ወግ (1999 ዓ.ም)
  4. 4. እችክችክ - የቃሊቲ እንጉርጉሮዎች - ግጥም (2000 ዓ.ም)

    እነዚህ ስራዎቹ በህይወት በነበረበት ወቅት የታተሙት ናቸው። አሁን ደግሞ፣ ይህችን ዓለም በአፀደ ስጋ ከተሰናበተ ሰባተኛው ዓመቱ ላይ ቀደም ብሎ ሊያሳትመው ያዘጋጀውን “አባቶችና ልጆች” በሚል ርዕስ የፃፋቸው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የፊታችን ቅዳሜ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ አዳራሽ በ10 ሰዓት ላይ ይመረቃል።

    መፅሐፏ 15 አጫጭር ልቦለዶን የያዘች ስትሆን 165 ገጾች አሏት። የታተመችውም በፋር ኢስት ማተሚያ ቤት ሲሆን አሳታሚዎቹ ደግሞ የአብርሃም ቤተሰቦች ናቸው። ከእነርሱ ጎን በመቆም ይህች መፅሐፍ አንባቢን ዘንድ እንድትደርስ ድጋፍ ያደረጉት ደራሲ ብርሃኑ ሰሙ፣ ሰዓሊ ይሔነው ወርቁ እና ወ/ሮ የውብዳር ካሳ ምስጋና ይድረሳቸው። የመፅሐፏ መግቢያ ላይም ደራሲው እና ጋዜጠኛው አብርሃም ረታ ዓለሙ በሚከተለው መልኩ ተገልጿል።

    ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙ ከአባቱ ከአቶ ረታ ዓለሙ ከእናቱ ከወ/ሮ አመተየስ ኃ/ማርያም ነሐሴ 21 ቀን 1950 ዓ.ም በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሐገር በይርጋለም ከተማ ተወለደ። አብርሃም ለትውልድ ስፍራው ለይርጋለም ከተማ እና አካባቢዋ የተለየ ፍቅር አክብሮት ነበረው።

    ከመደበኛ የመንግሥት ትምህርት በፊት በባሕር ዳር ከተማ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን ፊደል ቆጥሯል። ፊደል ከለየ በኋላ ታላቅ ወንድሙ አቶ እጅጉ ረታ መፅሐፍትን እንዲያነብ እና የመፅሐፍት ፍቅር እንዲያድርበት ከፍተኛ ግፊት ያደርጉበት ነበር። ከዚያም ወደ ትውልድ ስፍራው ይርጋለም ተመልሶ እስከ ስምንተኛ ክፍል በራስ ደስታ ዳምጠው ት/ቤት፣ ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልን ደግሞ በሀዋሳ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ1970 ዓ.ም አጠናቋል።

በተማሪነት ጊዜውም ከፍተኛ የንባብ ፍቅር የንባብ ፍቅር ነበረው። በርካታ መፃሕፍትን አንብቧል። ይህም ለጋዜጠኝነትና ለደራሲነት ሙያው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገለት ይገመታል።

    1971 ዓ.ም፤ አብዛኛዎቹ የቀይ ሽብር ሰለባ ከሆኑት ጓደኞቹ ጋር ይርጋለም ወህኒ ቤት ውስጥ ለስምንት ወራት በእስር አሳልፏል። በጊዜው ያጣቸውን እነዚህን ጓደኞቹን በየአጋጣሚው ሁሉ የነበራቸውን የመንፈስ ጥንካሬና ፅናት እያሳ ያስታውሳቸዋል። ይህንንም መፅሐፍ በቀይ ሽብር ሰላባ ለሆኑት ጓደኞቹ በመታሰቢያነት አብርክቶላቸዋል።

    ከሀዋሳ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በ1972 ዓ.ም በመምህርነት ከተመረቀ በኋላ፣ ከ1973-78 ዓ.ም በሀዋሳ ጊኬ ጊና፣ በዳሌ ወረዳ- ጋጃሞ፣ ይርጋለም ከተማ -አብዮት ጮራ ት/ቤት በመቀጠልም እስከ 1980 ዓ.ም በኢሊባቦር፣ በቡኖ እና በበደሌ በመምህርነት አገልግሏል። ከዚህም ሌላ እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕፃናት አምባ፣ በድሬዳዋ አፈተ ኢሣ ት/ቤት እና በሀዋሳ ሐይቅ ት/ቤት አስተምሯል።

     አብርሃም ረታ ዓለሙ ከመምህርነት ስራው በተጨማሪ በሙዚቃ ትልቅ ችሎታ ነበረው። ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ በሲዳማ አውራጃ፣ በሀዋሳ ከተማ እና በሲዳሞ ክፍለ ሐገር የኪነት ቡድኖች እንዲሁም በዝዋይ ሕፃናት አምባ ኦርኬስትራ ውስጥ በድራማ ደራሲነት፣ በመሣሪያ ተጫዋችነት፣ በድምፃዊነት፣ በዜማና ግጥም ደራሲነት፣ ጉልህ ጥበባዊ ስራዎችን አበርክቷል። ለታዋቂ ድምፃዊያንም - ለሂሩት በቀለ፣ ለተሾመ ወልዴ፣ ለበዛወርቅ አስፋው፣ ለአሰፉ ደባልቄ . . . ዜማና ግጥም በመድረስ በሕዝብ ዘንድ እንድደመጥ አድርጓል።

    ከመምህርነት ሙያው ጎን ለጎን የተለያዩ ፅሑፎችን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በመላክም ይሳተፍ ነበር። ከ1987-1992 ዓ.ም ድረስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ በጋዜጠኝነት በመቀጠር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በባህልና ጥበባት አምዶች አዘጋጅነትና በየካቲት መጽሔት በወግ አቅራቢነት አገልግሏል። ከማስ ሚዲያ ማሰልጠኛ ተቋም ለሁለት ዓመት የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቆ በህትመት ሚዲያ ዘርፍ ዲፕሎማ አግኝቷል።

    ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በሩሕ ጋዜጣና መፅሔት፣ በዕለታዊ አዲስ (ዕለታዊ ጋዜጣ)፣ በዜጋ መፅሔት፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በሌሎም በአዘጋጅነት ሰርቷል። እንዲሁም በሪፖርተር ጋዜጣና መፅሔት፣ በጽጌረዳ መፅሔት፣ በቁም ነገር መፅሔትና በሌሎም ላይ በአምደኝነት ፅሁፎቹን አስነብቧል።

    በኤፍ. ኤም ራዲዮ የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ በወግ አቅራቢነት፣ በድራማ ደራሲነትና በሴቶች አምድ አዘጋጅነት ተሳትፎ ነበረው።

    በ1999 ዓ.ም ላይ የሩሕ ጋዜጣ አዘጋጅ በነበረበት ጊዜ በቀረበበት ክስ ምክንያት ለአንድ ኣመት ለእስር ተዳርጓል። ከእስር መልስ ‘እችክችክ -የቃሊቲ እንጉርጉሮዎች’ በሚል ርዕስ የግጥም መፅሐፍ አሳትሟል።

    ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙ ዘርፈ ብዙ በሆኑ የፅሑፍ ዓይነቶች ላይ የሚሰራና የሚተረጉም ማለፊያ ፀሐፊ ነበር። ቁም ነገርን በቀልድና በምፀት እያዋዛ በሚያርባቸው ሥራዎቹም ይታወቃል። በመፃፍ ብቻም ሳይሆን በንግግር ረገድም ጨዋታ አዋቂ፣ አዝናኝ ባሕሪ ነበረው።

    በቀሪ ዘመኑ ሊሰራቸው ያቀዳቸውን በርካታ ሥራዎች ከፊቱ ሳሉ ሩጫው በድንገት ተገታና ግማሽ ቀን በማይሞላ ሕመም ግንቦት 11 ቀን 2000 ዓ.ም ማምሻውን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ተወልዶ ባደገባት ይርጋለም ከተማ በቅዱስ አማኔኤል ቤተ-ክርስቲን ተፈፅሟል።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
17222 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us