የሕክምና ጥበብ በኢትዮጵያ

Wednesday, 20 May 2015 13:17

በጥበቡ በለጠ   

 

ኢትዮጵያ በባሕላዊ ህክምናዎች ታዋቂ ከነበሩ ጥንታዊ ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች። ታላቁ ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ከዚህ ቀደም በሬዲዮ ባቀረበው መጣጥፉ ኢትዮጵያዊያን የሰውን ገላ በባህላዊ መንገድ ኦፕራሲዮን አድርገው ደዌውን አውጥተው ህሙማንን ከበሽታቸው የሚፈውሱ ቀዳማይ ሕዝቦች መሆናቸውን ሰፊ ሽፋን ሰጥቶት ሲተርክ ነበር። የተለያዩ ተጓዥ ፀሐፊዎችም ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ያዩትን የሀገሪቱን የባህላዊ የህክምና ጥበብ ጽፈው ለትውልድ አስተላልፈዋል። ዛሬም በሕይወት ያሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት Medical History of Ethiopia በተሰኘው ግዙፍ መጽሐፋቸው ውስጥ የጥንታዊውን የኢትዮጵያ የባሕላዊ ሕክምና ጥበብን በሚገባ ዘክረውበታል። ዛሬም የምንጨዋወተው ስለዚሁ የህክምና ጥበባችን መፃህፍትና አጥኚዎች ምን አሉ በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ይሆናል።

በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም የኪነ-ጥበብና የዘመናዊ አስተዳደር ላይ ፍልቅልቅ ብላ ወጥታ ትታይ የነበረችው የድሮዋን ጐንደር ከተማን በማጥናት የሚታወቁት አሜሪካዊው ተመራማሪ ዶ/ር ላ ቬርሊ በአንድ ወቅት ቃለ-መጠይቅ ሳደርግላቸው የነገሩኝ ታሪክ ምንግዜም አይረሳኝም።

ዶ/ር ላ ቬርሊ ከሚያጠኗቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምክንያት ወጥተው በውጭ ሀገራት ስለሚገኙት የኢትዮጵያ ቅርሶች ነበር። በ16ኛው ክፍለ ዘመን በጐንደር ደቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንደተፃፈ የሚነገርለትን ቁመቱን ከአንድ አጠር ያለ ሰው የሚስተካከል የብራና ጽሁፍ ወደ አውሮፓ እንደገባ ይናገራሉ ላ ቬርሊ። ይህ የብራና ጽሁፍ በውስጡ የያዘው ጉዳይ ሕክምናን ነው። በሕክምና ጥበብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ይኸው የኢትዮጵያ የብራና ጽሁፍ እንደሆነም ያብራራሉ። ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ የሚከተለውን ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ይህ ከኢትዮጵያ ወጥቶ አውሮፓ የገባው ብራና በውስጡ የያዘው ሃሳብ ሕክምና ቢሆንም፤ አቀራረቡ ለየት ይላል። ብራናው በእያንዳንዱ ገጽ ላይ በሽታውን ይጽፋል። የበሽታውን ስም። በሽታው የሚያስከትላቸውን ልዩ ልዩ ስሜቶች ይፅፋል። ከዚያም ለዚህ በሽታ የሚፈውሱ የመድሐኒት ዘሮችን ይገልፃል። ቀጥሎም የመድሐኒቱን ናሙና በጨርቅ ቋጥሮ እዚያው ገፅ ላይ ያስቀምጣል። እንዲህ እያደረገ ለየበሽታው ዝርዝርና የናሙና መድሐኒት ያቀረበ ብራና ነው። ይህ ብራና በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈ ነው። በርካታ የአውሮፓ የሕክምና ሰዎች ይህን ብራና በማስተርጐም ዛሬ የተገኙትን ዘመናዊ የሕክምና መድሐኒቶችን እንደፈጠሩ ዶ/ር ላ ቬርሊ ግምታቸውን ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ለዓለም የሕክምና ታሪክ ከፍተኛ እገዛ ማድረጓን እኚሁ ምሁር ያወሳሉ።

ወደኋላ ከሄድን አያሌ የህክምና ታሪኮቻችንን እያነሳሳን ሰፊ ወግ መጨዋወት እንችላለን። እሱን ገታ እናድርገውና አሁን በቅርቡ እንኳን በየቤታችን ‘ድንገተኛ’ የሚባል መድሐኒት ነበረን። ዛሬ ደግሞ ድንገተኛን ማግኘት አንችልም። ተመራማሪዎች ደግሞ ይህ ድንገተኛ የተባለው እፅ ከህመም የመፈወስ ትልቅ አቅም እንዳለው እየነገሩን ነው። በነገራችን ላይ ቀበሪቾ የሚባለውን እፅ በዓለም ላይ ጥናት አድርገው የሳይንስ ስም ያሰጡት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር መስፍን ታደስ ናቸው።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኢትዮጵያዊው የሕክምና ሊቅ ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር ደግሞ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ አስገራሚ ነገር ብለዋል። ጋዜጠኛው የጠየቃቸው እንዲህ ብሎ ነበር፡-

“እንደው እርስዎ እንደ ዛሬው ታላቅ የሕክምና ሊቅ ከመሆንዎ በፊት በልጅነትዎ ሐኪም የመሆን ፍላጐት ወይም ዝንባሌ ነበርዎት?” ይላቸዋል።

እርሳቸውም ሲመልሱ፤

“አይ የለም፤ እንዲህ ዘመናዊና የተማረ ሐኪም እሆናለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም። ግን በልጅነቴ ትዝ የሚለኝ ነገር፣ መንደራችን ውስጥ ሰው ሲታመም የምች መድሐኒት እየቆረጥኩ አጠጣ ነበር” ብለዋል ታላቁ ሐኪም ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር።

የፕሮፌሰር ጀማልን ትዝታ እያወጋኋችሁ አንድ ሌላ አስገራሚ የሳይንስ ሰው ትዝ አሉኝ። ዶ/ር ጌታቸው ቦሎዲያ ይባላሉ። ብዙዎቻችሁ ታውቋችኋላችሁ ብዬ አስባለሁ። በ1984 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች Bio-Chemistry የሚባለውን የሳይንስ ትምህርት በማስተማር በእጅጉ ይታወቁ ነበር። ታድያ እርሳቸውንም አንጋፋው የሬዲዮ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፡-

“በልጅነትዎ ሐረር እያሉ፣ እንዲህ አይነት የሳይንስ ምሁር እሆናለሁ ብለው አስበው ያውቃሉ ወይ?” አላቸው።

እርሳቸውም ሲመልሱ፤ “ኧረ በጭራሽ! አንድም ቀን አስቤው አላውቅም። ይልቅ እኔ መሆን የምፈልገው ቄስ ነበር። ምክንያቱም የቄስ አስተማሪያችንን እፈራቸው ነበር። የማውቀው አዋቂ እርሳቸውን ነው። የሚገርፍና የሚቀጣ ሰው የማውቀው እርሳቸውን ነው። ሰው ሁሉ አክብሮ ሰላም ሲላቸው የማውቀው እርሳቸውን ነው። ለእኔ ዓለምን የማይበት መነጽሬ መምህሬ የኔታ ናቸው። እናም እንደ እርሳቸው ቄስ ለመሆን ነበር ፍላጐቴ” ብለዋል ዶ/ር ጌታቸው ቦሎዲያ።

የኢትዮጵያ የሕክምና ሊቆች በልጅነታቸው ወደፊት ሐኪም እንደሚሆኑ አላወቁም ነበር። ወይም ዝንባሌያቸውን የነገራቸው አልነበረም። እናም ክስተት ሆኑ። ሕክምና የሕይወት ጥሪ ነው መሰለኝ።

ዛሬ በዚህ በእኛ ዘመን ሕክምና በቤታችን እያለች ግዙፍ መጽሐፍ ያሳተመችልን በቀለች ቶላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀችው በሶሲዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ነው። የማስትሬት ድግሪዋንም ሠርታለች። አሁን በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ሕክምና በቤታችን የተሰኘ ባለ 400 ገጾች የሆነ መጽሐፍ አሳትማ ሰጥታናለች። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሀገራችን ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ በሽታዎች ከነ መድሐኒታቸው ተካቷል። መድሐኒቱ ደግሞ በቤታችን እና በአቅራቢያችን ያሉ እፅዋት ናቸው። ልዩ ልዩ የአዝእርትና የቅጠላ ቅጠል ዝርያዎችን እያስተዋወቀች ከደዌ እንድንፈወስና ጤነኛ ማኅበረሰብ እንድንሆን የበቀለች ቶላ መጽሐፍ ያስተምረናል።

በቀለች መጽሐፉን ያዘጋጀችበትን ምክንያት ስትገልፅ፤ የሚከተሉትን ነጥቦች አስቀምጣለች፡-

   1. አቅም በፈቀደ መጠን የቤት ውስጥ ህክምና ለቀላል ህመሞች የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለማስገንዘብና በቀላሉ በቤት ውስጥ በሚገኙ ነገሮች በመጠቀም የታመሙ ሰዎችን ማከም እንደሚቻል ለማስረዳት፣ 
   2. ስለ ባሕላዊ መድሐኒት ያለውን ነባር የኅብረተሰብ እውቀት አሰባስቦ በጽሁፍ ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል፣
   3. የባሕል መድሐኒት መገኛ የሆኑ አንዳንድ እፅዋት በአስጊ ሁኔታ እየተመናመኑ እና እየጠፉ ስለሆነ ሰዎች ዕፅዋትን በየጓሯቸው ለማልማት እና በመስክም ለሚገኙት እንክብካቤ ለማድረግ እንዲበረታቱ ለመርዳት
   4. ባሕላዊ መድሐኒቶች ለጤና የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ አጉልቶ ለማሳየት፣
   5. የባሕላዊ መድሐኒት አሰባሰብ፣ አያያዝ፣ አዘገጃጀትና አጠቃቀምን ለማሳወቅና እውቀቱም እንዲሻሻል መነሻ ለመስጠት፣
   6. ስለ ተፈጥሮ የባሕል መድሐኒት እውቀት ለማስጨበጥ
   7. ሰዎች ለተፈጥሮ ባሕላዊ መድሐኒት መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ከፍለው ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ነገር ግን መክፈል ከሚገባቸው ዋጋ በላይ ከፍለው እንዳይታለሉ ለመርዳት፣
   8. በየብሔረሰቡ ያሉ ነገር የሕዝብ እውቀትን መሠረት ያደረጉ

- ስለ እፅዋት ልማት፣ አካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የምግብ ሰብል አመራረትና አያያዝ፣ ስለ ባህላዊ ምግባች አያያዝና ዝግጅት፣ የባሕል መድሐኒት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ስለ ባሕላዊ ህክምና ምንነት አስባና ተጨንቃ ያዘጋጀችው ግዙፍ መጽሐፍ ነው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሕክምና ሳይንስን በስፋት እስከ ከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ፕሮፌሰሮቻችን እና ሐኪሞቻችን ሕዝባቸው ራሱን ከህመምና ከሞት እንዲታደግ በሚገባው ቋንቋ ሲፅፉ አይስተዋሉም። እውቀታቸው ለሕዝብ ሳይሰራጭ ብዙ የኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች አልፈዋል። ያለመፃፋቸው ችግሩ ምንድን ነው ብሎ ያጠና ሰውም ሆነ ተቋም የለም። መጽሐፉም ቄሱም ዝም ሆኗል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ትምህረት ክፍልም፣ ለምንድን ነው ሐኪሞቻችን ለሀገራችን ሕዝብ የማይፅፉት ብሎ አጥንቶ ከዚያም ለችግሩ መፍትሄ ሲሰጥ አይስተዋልም።

ሐኪሞቻችን የተማሩትን የሕክምና ጥበቦች ለሕዝባቸው በልዩ ልዩ መንገድ ግንዛቤ ከመፍጠር ይልቅ ታሞ የመጣውን ሰው ማከሙ ላይ ብቻ የተወጠሩ ሆነዋል። ህዝቡ ከልዩ ልዩ ደዌ አስቀድሞ የሚከላከልበትን መንገድ የሚጠቁሙ የጽሁፍ ሕትመቶችን ሲያሳትሙ አይስተዋልም። ይልቅስ አንዳንዶች በሰፊው የገቡበት ሙያቸውን ገንዘብ መሰብሰቢያ ብቻ ወደ ማድረግ ገብተውበታል። ፕሮፌሽንን እያፈራረሱ ከድሃው ወገናቸው ላይ በህክምና ሰበብ ኪሱን የሚያራግፉት ሐኪሞች እየተበራከቱ የመጡበት ዘመን ነው።

አንዳንድ ሐኪሞች ደግሞ አሉ። ጠዋት ማታ የወገናቸው ስቃይና መከራ የሚያሳስባቸው። ለእሱም ብለው ራሳቸውን መስዋዕት እስከማድረግ የደረሱ አያሌ ሐኪሞችንም እናውቃለን። እንደ እነርሱ አይነቱ እንዲበረክትልንም እንመኛለን።

ከማኅበረሰቡ ውስጥ ተወልደውና አድገው ለዚያው ለተወለዱበት ሀገርና ሕዝብ ታታሪ ሆነው ብዙ የሚሰሩ ሰዎችም አሏት ኢትዮጵያ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ በቀለች ቶላ ተጠቃሽ ናት። በቀለች፣ ሕክምና በቤታችን - የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድሐኒት በሚል ርዕስ አዘጋጅታ ያሳተመችው መጽሐፍ ኢትዮጵያዊ ወዝ እና ለዛ ያለው ነው።

የበቀለች መጽሐፍ በሀገራችን ያሉትን እፅዋት በመጠቀም እንዲሁም ደግሞ ልዩ ልዩ የባሕል ህክምና አባቶች ያዘጋጇቸውን መፅህፍትና ሰነዶችን በዋቢነት በማገላበጥ ለትውልድ የሚተርፍ የባሕላዊ ሕክምና መጽሐፍ አዘጋጅታለች። በዚህ መጽሐፏ ላይ አስተያየት ከሰጡት መካከል ዶክተር መላኩ ወረደ ይገኙበታል። ዶክተር መላኩ የብዝሃ ሕይወት ዓለም አቀፍ አማካሪ ሲሆኑ፤ በጄኔቲክ ሀብት የዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኙ የዘመናችን ሎሬት ናቸው። እርሳቸውም ስለ መጽሐፉ የሚከተለውን ብለዋል፡-

“በዓለማችን ኅብረተሰብ በተለይ በመልማት ላይ ያሉ አገራት ሕዝቦች ሰማንያ በመቶ (80%) ያህሉ ከተፈጥሮ በሚገኘው መድሐኒት ተዋፅኦ እየተገለገሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ሀብቱ እና አብሮት ሲካብት የቆየው ጥምር እውቀት እየሳሳና አቅጣጫውን እየለወጠ በመሄድ ላይ ይገኛል።

“ማንኛውም ዘመናዊ መድሐኒትም ቢሆን መሠረቱ ከተፈጥሮ የሚገኘው የብዝሃ ህይወት ሐብት ነው።

“ይህን ከፍተኛ ሀብት ጠብቆ፣ አልምቶ እንዲሁም ያጠቃቀም ዘዴውን አጐልብቶ የበለጠ ጥቅም ላይ ማዋሉ ለኅብረተሰብ ጤንነት ዋስትና የሆነ አይነተኛ አማራጭ እንደሚሆን አያጠሪጥርም።

“ይህ መጽሐፍ ያለውን በሙሉ ባያካትትም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ባለ ብዙ ጠቀሜታና እምቅ ሀብት ያላቸው ዕፅዋትን እየዳሰሰ ጥቅሙን እና የአጠቃቀሙን ዘዴ እያገናዘበ የተዘጋጀ ነው። ይህ ሥራ ጅምር እንደመሆኑ ሁሉ አዘጋጅዋ ወደፊትም እያስፋፋች የምትሄድ መሆኑን ያመለክታል።” በማለት ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

የመጽሐፉ አርታኢ የሆኑት እሸቱ ደምሴም በሰጡት አስተያየት የበቀለች መጽሐፍ የጊዜውን ሁኔታ በማገናዘብ እና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን መሠረታዊ ተፈጥሮአዊ ህክምና ዘዴን የያዘ ነው ሲሉ ይገልፁታል።

ደራሲዋ በቀለች ቶላ፣ ከዚህ ሌላ አራት መፃህፍትን ለአንባቢያን በማድረስ ትታወቃለች። አንደኛው “ለቤት እንስሳት እንክብካቤ መኖ ልማትና ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድሐኒት” በሚል ርዕስ 224 ገጾች ያሉት መጽሐፍ በ2001 ዓ.ም አሳትማ ለንባብ አብቅታለች።

ሁለተኛው መጽሐፏ “ስለ ዕፅዋት ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች” በሚል ርዕስ ያሳተመችው 80 ገጾች ያሉት መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የታተመው በ2004 ዓ.ም ሲሆን፤ ሕፃናትና ታዳጊዎች ስለ እፅዋት እንዲያውቁና አዕምሯቸው እንዲበለፅግ ኢትዮጵያዊ ውለታዋን ያበረከተች ደራሲት ናት። ለመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን መፃሕፍት በመደገፍና ለተማሪዎች በማድረስ ረገድ የተጫወተው ሚና ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ እምብዛም እንደሆነ እንረዳለን።

ሦስተኛው የበቀለች ቶላ መፅሐፍ “በዐይነት እንጀራ ለምለም እንጀራ ከብዝሃ ሰብሎች” የተሰኘ ነው። ይህ 128 ገጾች ያሉት መፅሐፍ በ2004 ዓ.ም የታተመ ሲሆን፤ የኢትዮጵያውያኖች ልዩ ሙያ የሆነውን የእንጀራን አዘገጃጀት ከጤፍ ውጭ ያሉትን ሰብሎች ሁሉ በመጠቃቀስ ያዘጋጀችው ነው።

በቀለች ቶላ በእንግሊዝኛ ቋንቋ Injera Variety from crop diversity በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 2012 ዓ.ም 144 ገጾች ያሉትን መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች። ይህ መጽሐፏ ቀደም ሲል በአማርኛ የተፃፈ ሲሆን፤ እንግሊዝኛ አንባቢ ለሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያን እና እንጀራዋን የሚያስተዋውቅ ነው።

በአጠቃላይ እንዲህች አይነት ሴት በማኅበረሰባችን ውስጥ መገኘቷ ትልቅ ነገር ነው። ለወገን እና ለሀገር አስበው ከሚሰሩ ሰዎች መካከል አንዷ በመሆኗ ምስጋናና ክብር ይገባታል እላለሁ። 

ይምረጡ
(13 ሰዎች መርጠዋል)
12825 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us