የታሪክ ሊቁ - ተክለፃድቅ መኩሪያ

Wednesday, 27 May 2015 17:39

በጥበቡ በለጠ

   

 

    ታላቁ የታሪክ ፀሐፊ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ መስከረም 1 ቀን 1906 በሸዋ (ሰሜን ሸዋ) በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በጊናገር ወረዳ፣ በአሳግርት ልዩ ስሙ አቆዳት በሚባል ስፍራ ተወለዱ። ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በአማርኛና በግዕዝ ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የፈረንሳይኛ ትምህርት ተምረዋል። ለኢጣሊያ የወረራ ዘመን ሶስት ዓመታት በግዞት በሶማሊያ ቆይተዋል። ከዚያም ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በአስተዳደርና በዲፕሎማሲ መስክ አገልግለዋል።

     አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የንባብና የትምህርት ዓለም በስፋት የሚታወቁት ፅፈው ባዘጋጇቸው እጅግ ግዙፍ በሚባሉ መፃሕፍቶቻቸው ነው። በቀደመው ዘመን ላይ ለትምህርት ቤቶች የታሪክ መማሪያ በአምስት ቅፅ የታተሙት መፅሐፍቶቻቸው ነበር የሚያገለግሉት። የኢትዮጵያን ታሪክ ከማንም በበለጠ መልኩ የፃፉ ሰው ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸው የኢትዮጵያን ታሪክ ለባለታሪኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመፃፍ ይታወቃሉ። የእርሳቸው ዘመን ላይ የነበሩ የታሪክ ምሁራንም ሆኑ አሁን ያሉት ምሁራን በአብዛኛው የሚፅፉት በውጭ ሀገር ቋንቋ ነው። እርሳቸው ግን ለኢትዮጵያዊ ወገናቸው ውብ በሆነ የአፃፃፍ ስልታቸው ሲፅፉለት ኖረው የዛሬ 15 ዓመታት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

     ከታሪክ ፀሐፊነታቸው በተጨማሪ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ብዙ አገልግለዋል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1934 ዓ.ም እስከ 1935 ዓ.ም በመዝገብ ቤት ሹምነትና በሚኒስትር ፀሐፊነት ሰርተዋል። ከ1935-1966 ዓ.ም ደግሞ የምድር ባቡር ዋና ተቆጣጣሪ፣ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ፀሐፊ፣ የጡረታ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር፣ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር ዋና ኃላፊ፣ በሚኒስትር ማዕረግ በእየሩሳሌም ቆንስል፣ በቤልግሬድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት በኃይል ከተወገደ በኋላም በዘመነ ደርግ እስከ 1967 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የትምህርትና የባሕል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያወሳል። ከዚያም በጡረታ ተገለሉ።

እኚሁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ለንባብ ያበቋቸውን የኢትዮጵያን የታሪክ መፃሕፍት በአብዛኛው የፃፉት በመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ ነው። ለሕትመት ከበቁላቸው አያሌ ሥራዎቻቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

 1. 1. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣
 2. 2. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ፣
 3. 3. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ልብነድንግል፣
 4. 4. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ፣
 5. 5. የኢትዮጵያ ታሪክና ኑቢያ፣
 6. 6. ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና፣
 7. 7. ጥንታዊት ኢትዮጵያና ግብፅ
 8. 8. የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ፣
 9. 9. የግራኝ አሕመድ ወረራ
 10. 10.አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት
 11. 11.አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣

እና ሌሎችም ያልታተሙ አያሌ ስራዎች አሏቸው።

እነዚህ ከላይ የሰፈሩት የታሪክ መፃሕፍት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ታላላቆቹ ቅርሶች እንደ አክሱም፣ ላሊበላና ጎንደር የሚታዩ እንደሆነ ፀሐፊያን ይናገራሉ። አሁን ያሉ ወጣት ፀሐፊያን የታሪክ መፃህፍት እያሉ የሚያሳትሟቸው ስራዎቻቸው በአብዛኛው ከአቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ስራዎች የተገለበጡ ናቸው። የተኮረጁ ናቸው። የተሰረቁ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ደግሞ የመነሻ ሃሳብ የሚሰጡ ናቸው። ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የታሪክ ፅሁፍ ውስጥ ዘላለማዊ ብርሃን ረጭተው ያለፉ ብርቅዬ ደራሲ ነበሩ። ይህንን ውለታቸውን በመገንዘብ ነው ላዕከ ተክለማርያም ሐምሌ 20 ቀን 1992 ዓ.ም ለተክለፃዲቅ መኩሪያ የሚከተለውን ቅኔ ያቀረቡት።

ተክለፃድቅ መኩሪያ

ያንድ ቤት ያስር ቤት የመቶ ቤት እያልን፣

የታሪኩን ሂሳብ ገና እያሰላሰልን፣

በሺ ቤት መቁጠሩን ሳንማርልዎ፣

አቶ ተክለፃድቅ ምነው መሔድዎ?

      እንግሊዝ ፈረንሳይ ጣሊያኖች እረፉ፤ ሃሳብ አይግባችሁ፣

      አይመጣም እንግዲህ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጠይቃችሁ።

ያፄ ልብነ ድንግል የቦካን ተራራ፣

ያፄ ፋሲል ጎንደር የመቅደላ ጎራ፣

እንደ ተክለፃዲቅ ከሌለህ ወዳጅ፣

ማን ይፅፍልሃል ተረስተህ ቅር እንጂ።

      ተክለፃዲቅ መኩሪያ የበቀለብሺ፣

      ኩሪ አገሬ ቡልጋ ደብረ ፅላልሺ።

የተፈለፈለ የተሰራ ከአለት፣

እንደ ላሊበላ እንደ አክሱም ሐውልት፣

የታሪክ አምድ ነው ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣

መናኸሪያ እሚሆን መነሻ መድረሻ።

      ታሪክ ይመላለስ እንደ ለመደው፣

      የማይመለሰው ተክለፃዲቅ ነው።

ከዚያ ከትልቁ ከሰማይ ቤት፣

የምትፅፈውን ታሪክ ለመስማት፣

ልሂድ ካንተ ጋራ አብሬ ልሙት፣

ተክለፃዲቅ መኩሪያ የታሪክ አባት።

      የተክለፃዲቅ ነፍስ ምን ቸግሯት ቦታ፣

      ቢሻት ከአብርሃም ጎን ከነ ይስሃቅ ተርታ፣

      ቢሻት ከቴዎድሮስ ከዮሐንስ ጋራ፣

      ቢሻት ከምንልክ ከተፈሪ ጋራ፣

      ትኖራለች የትም እንደ ልቧ ሆና፣

      እየፃፈች ታሪክ በጽድቅ ብራና።

ታሪክ አልማርም ባፍንጫዬ ይውጣ፣

ተክለፃድቅ መኩሪያ መምሕሬ ከታጣ።

      ጥያቄ አትጠይቁኝ አታስቸግሩኝ፣

      ተክለፃድቅ መኩሪያ ማነው አትበሉኝ፣

      ጣይ ሞቆት ጣይ ሞቆት አገር ያወቀው፣

      ተረት ተረት ሳይሆን ታሪክ ፃፊ ነው።


 


 

የአራዳዎቹ መፍለቂያ - ድሬዳዋ

     ዛሬ ጉዞ የምናደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ከወደ ምስራቅ በኩል ብዙውን ጊዜ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተደጋግመው ስማቸው ከሚጠራውና የደጋጎች መኖሪያ ናቸው እየተባሉ ዘወትር ከሚጠቀሱት ከድሬዳዋና ከሀረር ከተማ ነው። ድሬዎችና ሐረሮች እንዴት ናችሁ?

    በቅርቡ እጄ ከገቡ መፃህፍት መካከል አንዱ ስለ ድሬዎች የተፃፈ ነው። መፅሐፉ በተለይ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ትኩረት አድርጎ ሰፊውን ትኩረት በዚህችው ከተማ እና በነዋሪዎቿ ላይ አድርጓል።

    በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ድሬዳዋ ተጉዣለሁ። በጉዞዬ ወቅት ታዲያ ሁሌም ተደንቄና ተገርሜ እመለሳለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ህዝቡ ነው። የድሬ ህዝብ በጣም ተግባቢ፣ እንግዳን ሁሉ የራሱ ቤተሰብ አድርጎ የሚቀበል፣ ነገሮችን ሁሉ ቀለል አድርጎ የሚያይ፣ የማያጨናንቅ እና ፈታ ያለ ነዋሪ ይበዛበታል። ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ወደ ድሬዳዋ የመጣ ሰው ካለምንም ችግር ጉዳዩን ፈፅሞ የሚመለስባት ተወዳጅ ከተማ ነች።

    በምስራቅ በኩል የፀሐይ መውጫ ከሆኑት ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ድሬ በበርካታ ከያኒያን ዘንድ ስትወደስ፣ ስሟ ሲጠራ ስትቆለጳጰስ ኖራለች። በመፅሐፍ መልክ ደግሞ ቀደም ባሉት ዘመናት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ባሳተሟቸው መፃህፍት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ከተሞች በሙሉ ታሪካቸውን በተከታታይ መፃህፍት አውጥተዋል። መፅሐፋቸውም History of Ethiopian Cities /towns እያሉ አሳትመዋል።

    ከፕሮፌሰር ሪቻርድ በፊትም ሆነ በኋላ የፃፉ በርካታ ደራሲያን አሉ። ነገር ግን የእርሳቸው ሰፋ እና ዘርዘር ባለ መልኩ ታሪክን የሰነደ ስለሆነ ነው ከፊት አምጥቼ ስሙን የጠራሁት።

     ከሰሞኑ ደግሞ ከዚያው ከድሬዳዋ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አፈንዲ ሙተቂ አንድ ለየት ያለ መፅሐፍ በድሬዎች እና በድሬዳዋ ከተማ ላይ ፅፎ አሳትሟል። አፈንዲ ብዕሩን አንዴ ድሬ፣ አንዴ ሐረር እየወሰደው የሁለቱን ከተሞች መንትያ አስተሳሰቦችን ሲያጫውተን፣ ሲያስቀን ሲያዝናናን ይቆያል በብዕሩ።

    የአፈንዲ መፅሐፍ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽት ድሬዳዋ” ይሰኛል። ርዕሱ በድሬዎች ቋንቋ ትርጉም አለው። ትርጉሙም “አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬዳዋ ሕዝብ” ማለት እንደሆነ ደራሲው አፈንዲ ሙተቂ ይገልፃል። ይህ ደራሲ ድሬንና ሐረርን ለያይቶ ማስቀመጥ ከበድ እንደሚለው ያስታውቃል። እዚያው የመፅሐፉ የፊት ገፅ ላይ “የወግ ሽር ሽር- ከሐረር እስከ ሸገር” ብሎም ጽፏል።

    ለማንኛውም ዛሬ ድሬ ላይ ፍሬኑን ያዝ እናድርግና ጥቂት ስለድሬዳዋ እንጨዋወት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ባለቅኔ እና ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ከዛሬ 40 ዓመት በፊት “እሳት ወይ አበባ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሐፍ ውስጥ ስለ ድሬዳዋም ውብ ግጥም አቅርቦልናል።

ድሬዳዋ ውስጠ ደማቅ

ሽፍንፍን እንደ አባድር ጨርቅ

ብልጭልጭ እንደ ሩቅ ምስራቅ

ያውራ ጎዳናሽ ዛፍ ጥላ

ጋርዶሽ ከንዳድሽ ብራቅ

    እያለ ተቀኝቶላታል። ሞቃቷ ድሬ ከዚያ ሁሉ ሙቀቷ አረፍ የሚያደርገው የከዚራ ጥላዎቿ እና የነዋሪዎቿ ጨዋታ ነው። አፈንዲ ሙተቂም በመፅሐፉ አማካይነት ድሬዳዎችን ወክሎ ያጫውተናል።

    እንደ ደራሲው አባባል፣ ድሬዳዋ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንን የወለደች ብሎም ሌላ ቦታ ተወልደው ድሬዳዋ የመጡትን ደግሞ እንደ የራሷ የአብራክ ክፋይ ከልጆቿ ሳትነጥል ያሳደገች እንደሆነችም ያብራራል። ድሬ ስትጠቀስ ስማቸውም አብሮ ብቅ እንደሚል የሚነገርላቸው ተወዳጅ ድምጻዊ አሊ ቢራ፣ ሐኪሙ ፕ/ር አስራት ወልደየስ፣ ባዮ ኬሚስቱ መምህር ዶ/ር ጌታቸው ቦሎዲያ፣ ዶ/ር አብዱል መጂድ ሁሴን፣ ባሀብቱ ኦክሲዴ፣ ገጣሚው ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ እግር ኳስ ተጫዋቹ ሚግ፣ ተወዳጆቹ ጋዜጤኞች ጳውሎስ ኞኞ እና ደምሴ ዳምጤ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የድሬ ፊት አውራሪዎች እያነሳሳም ያጫውተናል።

    ድሬ በኪነ- ጥበቡ፣ በስፖርቱ፣ በዕውቀቱ፣ በፖለቲካውና በሌሎችም ዘርፎች አያሌ ኢትዮጵያዊያንን ከማፍራቷም በተጨማሪ ውብ እና ፅዱ ከተማ በመሆን ከወደ ምስራቅ የምታበራ ተወዳጅ የከተማ ጀምበር ነች።

    ከተወዳጁ ድምጻዊ ከአሊ ቢራ አፍ ዘወትር የማትጠፋው ድሬ ገና በቀደመው ዘመንም ቢሆን፣ መሐሙድ አሕመድን ማርካ ውብ ዘፈን አዘፍነዋለች።

የድሬ ልጅ ናት የከዚራ

ስለ ውበቷ ስንቱን ላውራ

የሐረር ልጅ ነች አዋሽ ማዶ

ልቤ በረረ እሷን ወዶ

    ይህች ዘፈን ድሬን እና ሐረርን ለማስተዋወቅ በብዙዎችም ዘንድ እንዲወደዱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች።

በሀገራችን የወግ መፃህፍት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የማይታይ አንድ አፃፃፍ አለ። ይህም ከተሞችን እና ህዝቦችን መሠረት አድርጎ የሕዝብ ታሪክ ብዙውን ጊዜ አይቀርብም። አፈንዲ ሙተቂ ግን ድሬዳዋ ላይ ሆኖ ድሬዎች እንዲህ ናቸው እያለ በውስጡ የኮሜዲ ስልት በተሞላበት ብዕር ድሬ ላይ ፍልስስ ያደርገናል።

    ስለ ከዚራ ያጫውተናል። ከዚህ ድሬ ውስጥ ያለ የዛፎች ጥላ ነው። ስለ ድሬዳዋ እና የባቡር ትራንስፖርት ታሪኳ ያወጋናል። ስለ ኮንትሮባንድ ንግዶቿ፣ ስለ ልጅ እያሱ፣ ስለ ተፈሪ መኮንን እና ሌሎችም በርካታ ወጎችን በድሬዎች ቋንቋ ይተርካል።

በሀገራችን ውስጥ በርካታ ከተሞች አሉ። በውስጣቸውም አስገራሚ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ማንነት አለ። እነዚህን የህዝብ ታሪኮችን ፈታ፣ ዘርገፍ እያደረግን በመፃፍ የታሪካችንን ክፍተት መሙላት እንችላለን።

    ድሬን ሳነሳሳ ድምጻዊት ኃይማኖት ግርማ ትዝ አለችኝ። “ከዚራ ነው ቤቴ” የሚሰኝ ውብ ዘፈን አላት። ያንን የመሰለ ስራ አበርክታ ምነው ጠፋችሳ?

ይምረጡ
(15 ሰዎች መርጠዋል)
14506 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us