ምስጢረኛዋ መቅደላ

Wednesday, 03 June 2015 14:17

በጥበቡ በለጠ

ከዓመታት በፊት 1999 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የቅዱስ ላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎችና ሥርዓተ-መንግሥቱንም በተመለከተ የ90 ደቂቃ ዶክመንተሪ ፊልም ከጓደኞቼ ጋር ሠርተን ነበር። የፊልሙ ርዕስ Lalibela Wonders and Mystery /ላሊበላ ትንግርትና ምስጢራት/ የሚል ሲሆን፤ በዚሁ ፊልም ምርቃት ላይ ንግግር አድርጌ ነበር። ከንግግሬ መካከል አንደኛው ወደፊት ስለምንሰራቸው ዶክመንተሪ ፊልሞች አይነት ነበር። ታዲያ በወቅቱ ስናገር፣ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን ታሪክ በተመለከተ እንዲሁም የአባቱን የዐፄ ቴዎድሮስንም ታሪክ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናችንን ተናገርኩ። ይህንን በተናገርኩ በማግስቱ አንድ ሰው ስልክ ደወለልኝ።

“ሀሎ፤ ጥበቡ ነህ?”

“አዎ ነኝ፤ ማን ልበል?”

“ታደሰ ተገኝ እባላለሁ። ትናንትና የሠራችሁትን ፊልም አይቻለሁ። በጣም ጥሩ ነው። አንዳንድ አስተያየቶችም አሉኝ። እሱን ሌላ ጊዜ እንነጋገራለን። አሁን የደወልኩልህ ግን አንድ መረጃ ልሰጥህ ፈልጌ ነው” አለኝ ደዋዩ።

“እሺ ይስጡኝ አቶ ታደሰ” አልኩኝ።

“ትናንት መድረክ ላይ ስትናገር ወደፊት የአፄ ቴዎድሮስን እና የልዑል ዓለማየሁን ታሪክ እንሰራለን ብለህ ነበር”

“አዎ ብያለሁ” አልኩኝ።

“መቼም የቴዎድሮስን እና የዓለማየሁን ታሪክ ስትሠራ መቅደላ አምባ መሄድ አለብህ አይደል?” አለኝ።

“ልክ ነው ጌታዬ እዚያም መሄድ አለብኝ” አልኩት።

“መቅደላ ለመሄድ የግድ ከእኔ ጋር መተዋወቅ አለብህ” አለኝ።

“ምነው በሠላም ነው?” አልኩት ንግግሩ እየገረመኝ።

“አዎ በሰላም ነው፤ ግን መቅደላ እንዲሁ በቀላሉ የምትሄድበት አይደለም። መኪናም ሆነ ሌላ መጓጓዣ አታገኝም። ጉዳዩ የሚቃለልልህ ከእኔ ጋር ስንተዋወቅ ነው። የምትሰራውም ሀሳብህ ብዙ ነገር ይቃለልለታል” አለኝ አቶ ታደሰ ተገኝ።

የአቶ ታደሰ ተገኝ ንግግር ቢገርመኝም በአካል ላገኘው ወሰንኩ። “እንገናኝና እንተዋወቅ የት ልምጣልህ?” አልኩት።

“እኔ የምሠራው World Food Program /WFP/ ወይም የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚባለው መስሪያ ቤት ነው። ቢሮዬ ካዛንቺስ ነው። እዚያ ና” አለኝ።

ሔድኩኝ። አስገራሚዬን ሰው አገኘሁት። ታደሰ ተገኝ እድሜው በስልሣዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ፣ ረዘም ዘለግ ያለ፣ የስፖርተኛ ተክለሰውነት ያለው፣ ንግግሩ ግልፅ እና ታታሪ ሠራተኛ መሆኑን አየሁ።

ታደሰ በዓለም የምግብ ድርጅት ውስጥ ትልልቅ ኃላፊነት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በአንድ ወቅት መቅደላ አካባቢ የምግብ እጥረት ተከስቶ አካባቢውን ለማጥናትና ከዚያም የሚያስፈልገውን እርዳታ ለመለገስ በታደሰ ተገኝ የሚመራ የመስሪያ ቤቱ ልዑክ ወደ አካባቢው ይሄዳል።

ታደሰ ተገኝ መቅደላ አካባቢ ሲደርስ በሚያየው ነገር ሊያምን አልቻለም። ያቺ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መናገሻ ቦታ የነበረች፣ ያቺ ኢትዮጵያዊያን ሀገራችንን ለእንግሊዝ መንግሥት አንሰጥም ብለው ጀግኖች የወደቁባት፣ ያቺ ታላቁ መሪ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ክብር ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው የተሰውባት ታሪካዊት ቦታ ተራቁታለች። መቅደላ የመኪና መንገድ የላትም። የመቅደላ ልጆች ት/ቤት የላቸውም ነበር። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍና የጥበብ ማዕከል የነበረችው መቅደላ፣ ታደሰ ተገኝ ሲሄድባት ት/ቤትም የለባትም ነበር። ጭራሽ በምግብ እጥረት ተመታ ነዋሪዎቿ የእርዳታ ያለህ የሚሉበት ወቅት ነበር።

ታደሰ ተገኝ በሚያየው ነገር አዘነ። ግን አዝኖ ብቻ ዝም አላለም። ከንፈሩን መጦ ችላ አላለም። ይልቅስ ራሱን ጠየቀ። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምን ማድረግ እችላለሁ ብሎ አሰበ። ይህን የኢትዮጵያን የታሪክ ማማ አሁን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የራሴን አስተዋፅኦ ላበርክት ብሎ ሃሳብ ነደፈ።

የመቅደላን ታሪካዊ ሕዝቦች ሊያያቸው አቀበቱን ሊወጣ ተራራውን ሊያያዘው ተነሳ። የመቅደላም ነዋሪዎች አዲሱን እንግዳቸውን ሊያስተናግዱት በቅሎ አቀረቡለት። አንዴ በእግሩ፣ አንድ ጊዜ በበቅሎ እያለ መቅደላ አምባ ላይ ከረጅም ሰዓታት ጉዞ በኋላ ወጣ። ታሪካዊው መቅደላ መድሐኒአለም ቤተ-ክርስቲያን አርጅቷል። አንዳንድ ጐኑ ረጋግፏል። የአፄ ቴዎድሮስ ወታደሮች የወደቁበትና የተቀበሩበት ስፍራ ነው። ታሪካዊው ሴፓስቶፖል መድፍም ዝም ብሎ ቁጭ በማለት የታሪክ ሂደትን ይታዘባል። የመቅደላ ልጆችም ተኮልኩለው ወጡ። ታደሰ ተገኝ የተባለውን የመሀል ሀገር ሰው አዩት፣ ተዋወቁት። አባቶች እናቶች ታደሰን አስተናገዱት። ከመሀል ሀገር ሄዶ የሚያያቸው የሚጠይቃቸው ሰው ስለሌለ ታደሰ ተገኝ ብርቅ ሆነባቸው።

ታደሰም የመቅደላን ነዋሪ ደግነት፣ ልበ ቀናነት፣ ታሪካዊነት እና አሁን ያለበትን አስከፊ ድህነት ሲያይ ስሜቱ ተነካ። እስከ እለተ-ሞቴ ድረስ ከናንተ ጋር ነኝ አላቸው።

ታደሰ ተገኝ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ የነበረው የዓለም የምግብ ድርጅትን እና የመቅደላን ነዋሪዎች በማስተባበር “ምግብ ለስራ” በተባለ መርሃ-ግብር ወደ መቅደላ አምባ የሚያስኬድ ጥርጊያ መንገድ አሰራ። በዚህ የመኪና መንገድ ላይ የታደሰ ተገኝ ቶዮታ ላንድክሩዘር መኪና ጥሩንባዋን እያሰማች ለመጀመሪያ ጊዜ መቅደላ አናት ላይ ወጣች። ተአምር ተባለ። መኪና አይተው የማያውቁት የመቅደላ ልጆች ሲደነቁ፣ ሲገረሙ፣ ሲደሰቱ ሰነበቱ።

ታደሰ በዚህ ብቻም አልቆመም። የመቅደላ ልጆች ት/ቤት ሊኖራቸው ይገባል፤ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ተማሪዎች መደበኛ ተማሪ መሆን አለባቸው ብሎ ተነሣ። ፈለገ-ብርሃን የተሰኘ የበጐ አድራጐት ማኅበር መስርቶ ጓደኞቹን እና ወዳጆቹን አስተባብሮ መቅደላ አምባ ላይ ት/ቤት ማሰራት ጀመረ። በመጨረሻም መቅደላ አናት ላይ የት/ቤት ደውል መሰማት ጀመረ። የመቅደላ ልጆች ታደሰ ተገኝ በሚባል ሰው ረዳትነት የት/ቤት ዩኒፎርም ለብሰው፣ ደብተር፣ መፃህፍትና የትምህርት ቁሳቁሶችን ይዘው መደበኛ ተማሪዎች ሆኑ።

እዚህ የመቅደላ አፋፍ ላይ እየወጣች የምትመጣው የታደሰ ተገኝ መኪና ናት። አንድ ቀን እኔን እና በአሜሪካ የሐዋርድ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነውን ጓደኛውን ዶ/ር መንበሩን ይዞን ከሁለት ቀናት ጉዞ በኋላ ከመቅደላ ልጆች ጋር አስተዋወቀን። ያቺ እለት በሕይወት ዘመኔ የተደሰትኩባት ጉዞ ነበረች።

መቅደላን አየሁ። የአጤ ቴዎድሮስን መውጪያ እና መግቢያ፣ መቀመጫ ተመለከትኩ። መቅደላ አምባ ላይ አፄ ቴዎድሮስ ያቀዱትን ትልም አሰብኩ። ታላቁን ቤተ-መዘክር አሰብኩት። አፄ ቴዎድሮስ ከመላው ኢትዮጵያ የሰበሰቧቸው ታላላቅ የብራና ጽሁፎችና ታሪኮች የተቀመጡት መቅደላ ላይ ነበር። ቴዎድሮስ መቅደላን የጥናትና የምርምር ማዕከል ሊያደርጓት አስበው ነበር። እነዚህ የኢትዮጵያ ቅርሶች በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው በበርካታ ዝሆኖች ተጭነው ከሀገር ከወጡ 147 ዓመታት አለፉ።

ምስኪኗን መቅደላ አሁንም አሰብኳት። አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የእንግሊዝ ሀገሩ ገናና ጋዜጣ ‘ፋይናንሻል ታይምስ’። ጋዜጣው በአንድ ወቅት ከመቅደላ አምባ ስለተዘረፉት የብራና ጽሁፎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ነበር። እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ፣ በእንግሊዝ ወታደሮችና በእንግሊዝ መንግስት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ የተዘረፉ የብራና ጽሁፎች ወደ ለንደን መጥተዋል ይላል። እነዚህ የብራና ጽሁፎች በገንዘብ ቢተመኑ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ጋዜጣው ያትታል። ይህን ሁለት ቢሊየን ፓውንድ በአሁኑ ምንዛሬ ወደ ብር ስንቀይረው ከ63 ቢሊየን ብር በላይ ነው። መቅደላ ይህን ያህል ቅርስ ተዘርፋለች። የዛሬዋ መቅደላ ባዶ ነች። ኦና ናት። ድህነትና ጐስቋላነት ክፉኛ ተጫጭኗታል። ከውስጧ ግን 63 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ቅርሶችን ተዘርፋለች።

መቅደላ መድኃኒአለም ቤተክርስትያን አውደ-ምህረት ላይ ቆምኩኝ። ዙሪያ ገባውን በመቃብሮች ታጥራለች። እነዚህ መቃብሮች የመቅደላ ጀግኖች ናቸው። ለኢትዮጵያ ብለው ሕይወታቸውን የሰጡ የቁርጥ ቀን ልጆች። አፅማቸው ያረፈበት ቦታ የታሪክ ማማ ነበር። ግን ዛሬም ርቀት እና ጭርታ ጋርደውት ፍዝዝ ብሏል።

እንደገና ወደ ታሪካዊው መድፍ ሴፓስቶፖል ዘንድ ሄድኩ። አፄ ቴዎድሮስ እንደዳበሱት እኔም ዳበስኩት። እንደሳሙት ሳምኩት። ከሴፓስቶፖል ጐን ቆሜ የመቅደላን ዙሪያ ገባ ቃኘሁ። ገብርዬ የተሰዋበት እሮጌ የምትባለዋን ስፍራም በርቀት ቃኘኋት። ሀሳቦች ተግተልትለው መጡ።

ለመሆኑ መቅደላ ለምን አትካስም? የዘረፉት የእንግሊዝ ወታደሮችና የእንግሊዝ መንግስት መቅደላን ለምን አይገነቧትም ብዬም አሰብኩ። መቼም መካስን እንደ ሽንፈት የሚቆጥር ሕዝብ ያለበት ሀገር ናትና ሀሳቤን በእንጥልጥል ተውኩት። ታደሰ ተገኝ የሚባል ሰው የሚያስተባብረው የመቅደላ ልማት ብቻውንስ ይበቃል? እያልኩ ቆዘምኩኝ።

መቅደላ ከባሕር ጠለል በላይ ከ2 ሺህ 787 ሜትር ከፍታ ያላት እና ከአዲስ አበባ ከተማ በ580 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ፣ በአማራ ክልል ወሎ ውስጥ፣ ከተንታ ከተማ ቀጥሎ እጅግ በሚገርም የተራሮች ጥልፍልፍነት የተከበበች ታሪካዊት ቦታ ነች።

ይህች ቦታ አያሌ የኪነ-ጥበብና የታሪክ ተመራማሪዎችን ቀልብ በመሳብ እስከ ዛሬ ድረስ ወደር አልተገኘላትም። በተለይ ኢትዮጵያዊያን ፀሐፍት ታላላቅ ስራዎቻቸው ከመቅደላ አካባቢ ይመዘዛሉ። ታላቁ ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድሕን “የቴዎድሮስ ስንበት ከመቅደላ” በሚል ርዕስ ዘላለም እንደ አዲስ ግጥም የምትንበለበልና የዘመንን ኬላ ገና እያሳበረች የምትጓዝ ግጥም ጽፏል። ቴዎድሮስን ቴአትር ጽፏል። ብርሃኑ ዘሪሁን ከቴአትር ጀምሮ አያሌ ነገሮችን ጽፎባታል። አቤ ጉበኛ አንድ ለእናቱ ብሎ ግዙፍ መጽሐፉ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ብሎላታል። ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያትም መቅደላ ላይ ቴአትር ጽፈዋል። አያሌዎች ብዙ ብለዋል። እስከ አሁኑ ወቅት እንኳን ብናይ ጌትነት እንየው የቴዎድሮስ ራዕይ በሚል ርዕስ መቅደላን ይዘክራታል።

ከእነዚህ ሁሉ የገረመኝ ናሆም አሰፋ የተባለ የቴአትር ባለሙያ የፃፈው ተውኔት ነው። ናሆም አንድ ቀን ዳጐስ ያለ የቴአትር ጽሁፍ “እስኪ አንብብና አስተያየትህን ስጠኝ” ብሎ እቢሮዬ አስቀምጦልኝ ሄደ። ሳነበው የልዑል ዓለማየሁን ሕይወት በተመለከተ የተፃፈ ተውኔት ነው። ናሆም ግሩም አድርጐት ጽፎት ነበር። ፃፈው እንጂ እስከ አሁን ድረስ ወደ መድረክ አልወጣም። ናሆም እባክህ ይህን ተውኔትህን ለእይታ አብቃው እያልኩኝ በዚህ አጋጣሚ እጠይቀዋለሁ።

የልዑል ዓለማየሁን ጉዳይ ካነሳን ደግሞ ገና ምንም ያልተሰራበት አጓጊ የታሪክ ገጾች ያሉት ልጅ ነው። ልጅ የወለደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለ ልዑል አለማየሁ አንድ ታሪክ ሲነገር ቀልቡ ይሰረቃል። ምክንያቱም ገና በስድስት ዓመቱ አባቱ እናቱ ሞተውበት ምንም የማያውቃቸው የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ ሀገራቸው ወስደውት በባይተዋርነት ኖሮ በ19 ዓመቱ የተቀጨ አሳዛኝ ልጅ ነው። ልዑል ዓለማየሁ እየቦረቀ ያደገባትም የመቅደላ ምድር ከእርሱ ጋር ደብዘዝ ያለች ትመስላለች።

ልዑል ዓለማየሁን በሞግዚትነት ካሳደጉት ውስጥ አማርኛ የሚችለው የእንግሊዝ ወታደሩ ካፒቴን እስፒዲ አንዱ ነው። የዛሬ 11 ዓመት የዚሁ የካፒቴን ስፒዲ አራተኛ ትውልድ የሆነ እንግሊዛዊ እዚህ አዲስ አበባ መጥቶ ነበር። የመጣበት ምክንያት ልዑል ዓለማየሁን ወስደው ያሳደጉት የእርሱ ቤተሰቦች /ዘሮች/ ስለሆኑ አለማየሁንም የራሱ ዘመድ በማድረግ ስለ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ ስብስቦችን ይዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አዳራሽ ውስጥ አቀረበ። በዚያን እለት አዲስ አበባ ውሰጥ ከፍተኛ የሆነ ዶፍ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት በአዳራሹ ብዙ ሰው ባይገኝም 15 የምንሆን ታዳሚያን ነበረን።

ይህ እንግሊዛዊ ስለ ዓለማየሁ ቴዎድሮስና ስለ እሱ ቤተሰቦች ታሪክ አወራልን። የዓለማየሁን የእንግሊዝና የሕንድ ሀገራት ቆይታ ምን እንደሚመስል አወጋን። ከዚያም ፈጽሞ አይተናቸው የማናውቃቸውን የልዑል ዓለማየሁን ፎቶዎች ከመጀመሪያው የእንግሊዝ ሀገር ትውውቁ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ ያለውን አሳየን። ዓለማየሁ ታሞ፣ ዓለማየሁ ይህችን ዓለም በሞት ተለይቶ እና ሲቀበርም ጭምር የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ ስብስብ ለአንድ ሰዓት ተመለከትን። ጉድ ብለን አለቀስን።

ይህን እንግሊዛዊ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት በወቅቱ ጋዜጣ ላይ አውጥቼው ነበር። በጣም የገረመኝ ነገር የዓለማየሁን አንዱንም ፎቶ አልሰጥህም ብሎ ክርር አለብኝ። ብዙ ለመንኩት አልሆነም። እሱ ያቀረበው ምክንያት ኮፒ ራይትን ነው። እንደውም ኮፒ ራይቱ ለእኛ ነው አልኩት። ኢትዮጵያዊውን ልዑል የወሰደችው እናንተ ናችሁ። ዓለማየሁ የእኛ ነው - እያልኩ ክርር አልኩበት። ሰውየው የሚበገር አልነበረምና በአቋሙ ፀና። በጣም የገረመኝ ግን ሀገሩ ከሄደ በኋላ የተወሰኑ የልዑል ዓለማየሁን ፎቶዎች በኢሜይል ላከልኝ። ታዲያ አንድ ነገር አደራ ብሎኛል። ለጥናትና ምርምር ብቻ ተጠቀምባቸው ብሎ የተማፅኖም ጥያቄ አቅርቦልኛል።

በዚሁ በልዑል ዓለማየሁ ታሪክ ላይ ከጠየኳቸው ሰዎች መካከል አቶ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ አንዱ ነው። አቶ ጌትነት ቀደም ሲል በጐንደር ከተማ የሚገኙትን የአፄ ፋሲል ኪነ-ሕንፃዎች ውስጥ ከፍተኛ አስጐብኚ እና ኃላፊም ነበር። አሁን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተዘዋውሮ መጥቷል። ጌትነት በልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ላይ ጥናት ካደረጉ የታሪክና የቱሪዝም ባለሙያዎች አንዱ ነው። ስለ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የሚያውቀውን በርካታ ጉዳዮች ለ40 ደቂቃዎች ያህል እያጫወተኝ በፊልም ቀርጬዋለሁ።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሪታ ፓንክረስትም ልዑል ዓለማየሁን በተመለከተ የሚያውቁትን ሁሉ ሲያጫውቱኝ ቀርጫቸዋለሁ። ከቃለ-ምልልሳችን በኋላ ሪቻርድ ፓንክረስት The Fall of Meqedela የተሰኘ ጥናታቸውን ሰጥተውኛል። በዚህ ጥናታቸው ውስጥ የመቅደላን ውድቀት እና ከልዑል ዓለማየሁ ጀምሮ በርካታ አንጡረ ሀብት በእንግሊዝ ወታደሮች እንዴት እንደተዘረፈች የፃፉበት እጅግ ጠቃሚ ሠነድ ነው።

ከዚህ ሌላም ልዑል ዓለማየሁን በተመለከተ አሜሪካን ሀገር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የምትከታተለው ወጣቷ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሰላም በቀለ አስገራሚ ዶክመንተሪ ፊልም ሠርታለች። ሰላም በቀለ ልክ እንደ ዓለማየሁ ሁሉ ገና በአራት ዓመቷ በማታውቀው ሁኔታ ከሀገሯ ወጥታ አሜካ የምትኖር ናት። ዛሬ የ24 ዓመት ወጣት ናት። የልዑል ዓለማየሁ ታሪክ ከእርሷ ታሪክ ጋር ስለተቀራረበባት ወደ ለንደን አቅንታ ዓለማየሁ የነበረባቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት ቀረፃ አድርጋለች። ቀረፃዋ ከልዑለ ዓለማየሁ ጋር ልክ በሕይወት እንዳለ ሁሉ ምናባዊ ቃል-መጠይቅ እያደረገችለት የሰራችው ዶክመንተሪ ነው። ዓለማየሁና ሰላም በቀለ በምናባቸው ስለባይተዋርነትና ስደት አወጉ። በጣምም የተወደደላት ስራ ነው።

ከዓመታት በፊት ደግሞ በአውሮፓ የምትኖር እህቴ ወደ ለንደን አቅንታ አንድ የጥናትና የምርምር ጽሁፍ አግኝታ ነበር። ጽሁፉ የተፃፈው እዚያው ለንደን ውስጥ በሚኖረው ፈቃድ ሀብቴ በተሰኘ ኢትዮጵያዊ ነው። ዓለማየሁን “ባይተዋሩ መሥፍን” በሚል ርዕስ የፃፈውን ልካልኝ አነበብኩ። በርካታ መረጃዎችን በውስጡ ይዟል።

ልዑል ዓለማየሁ በዚህች ምድር ላይ 19 ዓመታት ሲቆይ፤ የፍቅር ሕይወቱ እንዴት ነበር? ብለው ያጠኑ እና አያሌ መረጃዎችን የያዙ ሰዎችም አጋጥመውኛል። የዓለማየሁ ታሪክ ብዙ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን የሚያሰራ ቢሆንም፤ ገና ምኑንም አልሰራንለትም። ለማንኛውም እኔም ብሆን ጠይቄ ጠይቄ ዝም ከምላችሁ የልዑል ዓለማየሁን ታሪክ ከመቅደላ እስከ የብሪታኒያ ርዕሰ ከተማ ለንደን፣ በተለይ ደግሞ ከከተማዋ ሰላሳ ማይሎች ወጣ ብላ በተቆረቆረች ዊንድሶር እየተባለች በምትጠራ ከተማ በሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ እስካረፈው ዓለማየሁ፣ ሳምንት ባጫውታችሁስ? ግን መቃብሩ ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አለ፡-

“ባይተዋር እንደነበረ ባይተዋር ሆኖ ሞተ።

መስፍኑ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፤ የንጉስ ቴዎድሮስ ልጅ”

ከታች ዝቅ ይልና፡- “ንግሥት ቪክቶሪያ” ይላል። 

ይምረጡ
(12 ሰዎች መርጠዋል)
12858 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us