የክቡር ዶክትሬት ድግሪ የተነፈገው መሐሙድ አሕመድ ክብር አገኘ

Wednesday, 17 June 2015 16:34

በጥበቡ በለጠ

     በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዓለም ውስጥ በተለይ በድምፃዊያን ተርታ ስናስቀምጥ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐሙድ አሕመድ. . . እያልን መዘርዘራችን የተለመደ ነው። በተለይ መሐሙድ ደግሞ የጓደኞቹ የጥላሁን ገሠሠ፣ የብዙነሽ በቀለ አድናቂ እና ወዳጅ በመሆኑ ለራሱ ዝናና ክብር ብዙም ሳይጨነቅ ረጅም ጊዜ አሳልፏል። መሐሙድ የጥላሁን ገሠሠ ስም ሲጠራ ቀድሞ የሚገኘው እሱ ነው። ለጥላሁን ግንባሩን የሚሰጥ የምን ግዜም ወዳጁ ነው።

     በ1995 ዓ.ም በኢግዚቢሽን መአከል 50ኛ ዓመት የመድረክ ዘመን ለጥላሁን ገሠሠ ሲከበር ዋነኛው ተደሳች መሐሙድ ነበር። በእያንዳንዱ የፕሮግራም እንቅስቃሴ ውስጥ መሐሙድ ነበር። ስለ ጥላሁን ገሠሠ መሐሙድን ጥያቄዎች እቅርቤለት ነበር። ስለ ጥላሁን ገሠሠ ካጫወተኝ ውስጥ የማልረሳው ጉዳይ አለ።

     “ጥላሁን ገሠሠ የአደራ ጓደኞዬና ወንድሜ ነው” ሲል ገልፆልኛል መሐሙድ። ጉዳዩ እንዲህ ነው፡-

     ጥላሁን እና መሐሙድ አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ይሄዳሉ። ወሊሶ ውስጥ የጥላሁን አያት ይኖራሉ። ከአያቱ ጋር ሲጫወቱ ውለው ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ ሆነ። በዚህ ግዜ ጥላሁን ከሰዎች ጋር ሲያወራ፣ አያቱ መሐሙድን ወደ ጓሮ ወስደውት ከመሬት ላይ ሳር ነጭተው በእጁ አሲዘውት እንዲህ አሉት፡-

“ጥላሁን ገሠሠ ወንድምና እህት የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። አደራ ሰጥቼሃለሁ። በምድር የሰጠውክን በሰማይ እጠይቅሃለሁ” ብለውት አደራ ለመሐሙድ ሰጡት።

     ጥላሁን ገሠሠ ይህን አደራ አያውቅም። መሐሙድም ነግሮት አያውቅም። ግን ሁል ጊዜ ጥላሁን ባለበት ቦታ ሁሉ መሐሙድ አለ። የአደራ ወንድሙ፣ የአደራ ጓደኛው ነበር።

     መሐሙድ አሕመድ ጥላሁን ገሠሠን እያነገሰ በመኖሩ እርሱን የሚያየው ጠፍቶ ነበር። የዛሬ ዓመት ግድም በሬዲዮ ፋና በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ይህን ድምፃዊውን በተመለከተ ሰፊ ፕሮግራም ተሰርቶ ነበር። በተለይ የሐገራችን ዩኒቨርስቲዎች ለበርካታ ታዋቂ ሰዎች የክቡር ዶክትሬት ድግሪ ሲሰጡ መሐሙድ አሕመድ እንዴት ይዘነጋል በሚል ርዕስ የከያኒውን ፕሮፋይል ጥልቀት ባለው መልኩ ሰርቶ አየር ላይ አውሎት ነበር።

      ልክ በዓመቱ ደግሞ ከሰሞኑ የክቡር ዶ/ር ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ይህን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሌጀንድ አክብረው የሚገባውን ማዕረግ አሳይተውታል። በኢትዮጵያ ታሪክ ላበረከተው የኪነ- ጥበብ ስራ በአደባባይ አምስት ሚሊዮን ብር የተሸለመ ከያኒ የለም። መሐሙድ የልፋቱን ዋጋ ተክሷል።

     ይህን መርሃ ግብር እውን እንዲሆን ላመቻቹ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። በርግጥ በዚህ በሸራተን ሆቴል በተካሔደው መርሃ ግብር በአዘጋጆቹ ስለ መሐሙድ አሕሙድ የጥበብ አበርክቶ አጭር ዶክመንተሪ ቢቀርብ እና ስራዎቹና ማንነቱም በዝርዝር ቢነገር ጥሩ ነበር። ወደፊትም በሕይወት እያለ የሕይወት ታሪኩ በመፅሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ቢቀርብ በ70ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለውን መሐሙድን ይበልጥ ህያው ያደርገዋል።

      የመሐሙድ ስም ሲጠራ አብረው ብቅ የሚሉት ዘፈኖቹ አያሌ ናቸው።

“ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም

ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሽልኝም”

ብሎ የዘፈነልን መሐሙድ ኢትዮጵያንም እየዞረ ስለ ከተሞችና ነዋሪዎቻቸው አዚሟል።

“የድሬ ልጅ ናት የከዚራ

ስለ ውበቷ ስንቱን ላውራ

የሀረር ልጅ ናት የአዋሽ ማዶ

ልቤ ተጨንቋል እሷን ወዶ”

ሲል፤ አይደለም የሐረርና የድሬ ልጅ፣ መላው ኢትዮጵያ ከርሱ ጋር ያውረገርጋል።

“የዘገየሽበት ምን ይሆን ምክንያቱ

አይኖቼ ተራቡ ደረሰ ሰዓቱ”

ሲለንማ የፍቅር ሐድራዎች በሙሉ ጓዛቸውን ሰብስበው ይሰፍሩብናል።

     ሐገሩን ለቆ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በያለበት እየዞረ መሐሙድ እንዲህ ይለዋል።

“መቼ ነው?

ዛሬ ነው?

ሀገሬን የማየው?

ኢትዮጵያን የማየው?”

እያለ ያዜማል። አብሮ ያለቅሳል።

     አጉል ነገር ጀመርኩ። የመሐሙድን ሙዚቃዎች ተንትኜ መጨረስ አልችልም። ግን ለአሁን የዛሬ ዓመት በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ላይ ከቀረበው የመሐሙድ ፕሮፋይል ጥቂቱን ባቋድሳችሁስ?

     ታላቁ የሙዚቃ ሰው መሐሙድ አሕመድ ኒውዮርክ አሜሪካ ውስጥ ልኬ የዛሬ ዓመት ኮንሰርት እንዲያቀርብ ፕሮግራም ተይዞለት ነበር። ኮንሰርቱን ያዘጋጁለትም አካላት በወቅቱ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን በየከተሞች እና በድረ-ገፆች ጭምር ይሰሩለት ነበር። ማስታወቂያዎቹ እንደሚገልጹት ከሆነ ደግሞ ታላቁ የአፍሪካ አንጋፋ ድምፃዊ ሙዚቃዎቹን ሊያቀርብ ነው፤ በማለት ደረጃውን ከኢትዮጵያ አውጥተው በአፍሪካ ደረጃ አስቀምጠውት ነበር። በዚሁ በኒውዮርክ ሬድ ሁክ፣ ቦርክሌይ ውስጥ በሚቀርበው የመሐሙድ አሕመድ ኮንሰርት ቀደም ብለው አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሐሙድ ከአፍሪካ ምድር ከተገኙ ምርጥ ድምፃዊያን መካከል አንዱ መሆኑን ዋቢ እየጠቃቀሱ ይናገሩ ነበር። ይህን ኮንሰርት ያዘጋጁለት ድርጅቶችም መቀመጫቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያደረጉት “ዘ ኢሹ ፕሮጀክት ሩም” እና “ፓዮኒየር ዎርክስ ፎር አርትስ” የተባሉ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ አለማቀፍ ድርጅቶች ልክ የዛሬ ዓመት ባወጡት መግለጫ፣ መሐሙድ አሕመድ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ “ወርቃማ ዘመን” እየተባለ በሚጠራው ከ1950 ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ስልሳዎቹ አጋማሽ ድረስ በታየው ድንቅዬ ዘመን ላይ፣ እንደ ከዋክብት ሲያበሩ ከነበሩ የሙዚቃ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ገልጸውለታል።

     ከሀምሳ ዓመታት በላይ ከመድረክ ላይ ሳይወርድ፣ መድረክን ለረጅም ሰዓታት እየተቆጣጠረ ጡዑመ ዜማዎችን ሲያንቆረቁር የኖረው መሐሙድ አሕመድ፣ በአፍሪካ የጥበብ መድረክ ላይ በሕይወት ያለ ባለታሪክ /A Living Legend/ በማለት አዘጋጆቹ ጠርተውታል።

     ስለ መሐሙድ አሕመድ የሙዚቃ ክህሎት፣ ተሰጥኦ እና አቀራረብ እየዘገቡ ያሉት የሙዚቃ ልሂቃን እንደሚናገሩት ከሆነ፣ መሐሙድ የሀገሩን የኢትዮጵያ ሙዚቃ በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በማቅረብና እናት ሀገሩን ኢትዮጵያን በጥበቡ ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ወደር የማይገኝለትን አስተዋፅኦ ማድረጉን ይናገራሉ። አሁንም እንኳን በ70ዎቹ የእድሜ አጋማሽ ላይ ሆኖ ካለምንም የትንፋሽ መቆራረጥ መድረክ ላይ ሆኖ እየዘፈነ፣ እየተውረገረገ፣ እየጨፈረ፣ እየተረከ . . . የጥበብ መንፈስን የሚያረካ ተአምረኛ ከያኒ እንደሆነም አስመስክሯል።

      መሐሙድ አሕመድ የሚዘፍናቸው ጥዑመ ዜማዎች ከኢትዮጵያ አፈርና ነብስ ያልተወለዱትን አውሮፓውያንን ሳይቀር የሚማርኩ እንደሆኑም እማኝ እየጠቀሱ መናገር ይቻላል። ድምፁ እና የአቀራረብ ቃናው ለአውሮፓ የሙዚቃ አፍቃሪዎችም ጆሮ ግቡ ሆኖ እንደሚያስደስታቸው ይወሳል። በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም የዓለም አቀፉን የቢቢሲ ሬዲዮ ጣቢያን ሽልማት፣ በምርጥ ድምጻዊነት ተመርጦ የሽልማት አክሊል የደፋ ከያኒ ነው። በዚህም ሽልማት የተነሳ መሐሙድ ዓለማቀፋዊ እውቅናው እየገዘፈ መጣ። በልዩ ልዩ ሀገራት ውስጥ መሐሙድ ሙዚቃ ያቀርባል ከተባለ ጥቁሩም ነጩም እኩል ተጋፍቶ በመግባት በዝግጅቱ ላይ ይታደማል። በቢቢሲ ሬዲዮ ጣቢያ ምርጥ ድምጻዊና ከያኒ ተብሎ የተመረጠ ስለሆነ ዝናው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

     ወደዚህች ዓለም በ1934 ዓ.ም የመጣው መሐሙድ አሕመድ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሙዚቃ ምትሃት እንደተለከፈ ይናገራል። በትምህርት ቤት ውስጥ ሆኖ ያዜማል። ትምህርቱንም አቋርጦ በሊስትሮ ስራ በተሰማራበትም ወቅት ያዜማል። ሙዚቃ ከደሙና ካጥንቱ ብሎም ከመንፈሱ ጋር የተዋሃደችው ገና በጨቅላ እድሜው ጀምሮ እንደሆነ መሐሙድ ይናገራል።

     ቀጥሎም አሪዞና ተብሎ በድሮ አራዶች ዘንድ ይጠራ በነበረው ጭፈራ ቤት /ናይት ክለብ/ ውስጥ በአስተናጋጅነት ይቀጠራል። ይህ አሪዞና ተብሎ የሚጠራው ክለብ ከ1955 ዓ.ም በፊት ታዋቂ ቤት ነበር። የሚገኘውም መድሐኒአለም ት/ቤት ፊት ለፊት ሲሆን፣ ቤቱም የራስ ኃይሉ ቤት እንደሆነም ይወሳል። እዚያ ቤት በአስተናጋጅነት የተቀጠረው መሐሙድ፣ አንድ ቀን የክለቡን ኃላፊ ይለምነዋል።

     “እባክህ ከነዚህ ድምጻዊያን ጋር አንድ ዘፈን ልዝፈን? እባክህ ፍቀድልኝ” እያለ ይማፀነዋል።

     ታዲያ አንድ ቀን ኃላፊው ፈቀደለት። መሐሙድም አዜመ። በተፈጥሮ የተሰጠውን የሙዚቃ ፀጋ አሳየ። ሁሉም ታዳሚ አድናቆቱን ገለፀለት። ደጋግሞም ማዜም ጀመረ። ታዲያ አንድ ቀን፣ የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ኃላፊዎች አሪዞና ክለብ ሊዝናኑ ይመጣሉ። መሐሙድ አሕመድ የተባለ ድምፃዊ የነ ጥላሁን ገሠሠን ዘፈኖች ልዩ በሆነው የድምፅ ለዛው ያቀነቅናቸዋል። የክለቡንም ታዳሚ ቁጭ ብድግ ያደርግበታል። በድምፁና በአቀራረብ ችሎታው የተማርኩት ክቡር ዘበኞች በታህሳስ ወር 1955 ዓ.ም መሐሙድን ከአሪዞና ክለብ ማርከው ወደ እነርሱ የሙዚቃ ካምፕ አስገቡት። ከዚያች ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያም በሙዚቃው ዓለም የሚያስከብራትን የወርቃማ ድምፅ ባለፀጋውን መሐሙድ አሕመድን አገኘች።

      ወደ ክቡር ዘበኛ ሙዚቃ የተቀላቀለው መሐሙድ አሕመድ፣ እዚያም ጥላሁን ገሠሠንና ብዙነሽ በቀለን የመሳሰሉ ተአምረኛ ድምፃዊያንን አገኘ። እንደ ኮ/ል ሳህሌ ደጋጎ እና ተዘራ ኃይለሚካኤልን የመሳሰሉ የሙዚቃ ሊቆች ጋርም ተዋሃደ። ከዚያም የራሱን ለዛ እና ማንነትን ይዞ ተወዳጅነትን ደርቦ እና ደራርቦ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ላይ ይዞት ወጣ።

      መሐሙድ አሕመድ በ1955 ዓ.ም ክቡር ዘበኛን ሲቀላቀል የተጫወታት የመጀመሪያ ዘፈኑ እስከ አሁን ድረስ ተወዳጅነቷ እያየለ እስከዚህ ዘመን ደርሳለች። ገናም በትውልዶች ውስጥ ታልፋለች።

ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም

ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሽልኝም

ሰላምን ለማግኘት አጥብቄ ብመኝም

ታበሳጪኛለሽ ግን አላወቅሽልኝም

ከሕይወቴ ይልቅ አስባለሁ ላንቺ

ግን ድካሜ ሁሉ አልገባሽም አንቺ

     “ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም” ብሎ ሙዚቃ የጀመረው መሐሙድ አሕመድ ተአምረኛ የሚባሉ ሙዚቃዎችን መጫወት ጀመረ።

“እንቺ ልቤ እኮ ነው ስንቅሽ ይሁን ያዢው

አንጀትሽ ሲታጠፍ ምሳ ብለሽ ጋብዢው

ስፍራው ጉራንጉር ነው ያለሽበት ሰፈር

አይሻልሽም ወይ የልቤ ላይ መንደር”

     የግጥሟ ሃሳብ ጥልቀትና ምጥቀት እንዲሁም የዜማዋ ልኬት፣ ከዚያም የሙሐመድ የአዘፋፈን የድምፅ ለዛ ታክሎበት፣ እንቺ ልቤ እኮ ነው ስንቅሽ ይሁን ያዢው፣ አንጀትሽ ሲታጠፍ ምሳ ብለሽ ጋብዢው የምትሰኘዋ ሙዚቃ ከሰው ልጅ የጥበብ መንፈስ ጋር ዘላለም ትኖራለች።

     የመሐሙድ ዘፈኖች አንዴ ተሰርተው ከወጡ በኋላ በአድማጮች ዘንድ ዘላለማዊ ተወዳጅነትን ይዘው የመቆየት ብቃት አላቸው። ምክንያቱ ደግሞ ርዕሰ ጉዳያቸው የሰው ልጅ የጋራ ጉዳይ መሆናቸውም ጭምር ነው። የሺ ሐረጊቱን የመሳሰሉ ዘፈኖቹ ታሞ የተኛን ሁሉ ቀና አድርገው የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው ገጠመኞቻቸውን የገለፁልኝ ሰዎችም አሉ።

     በነዚህና በሌሎቹም ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሙዚቃዎቹ የተወደደው ሙሐሙድ፣ የራሱን ማንነት እና ቀለም ወደሚያሰጠው ማዕረግ ተሸጋገረ። የሙዚቃ ሰዎች ሙሐመድን “የትዝታው ንጉስ” እያሉ ይጠሩት ጀመር። የትዝታን ሙዚቃ በመጫወት ወደር የማይገኝለት ከያኒም እየሆነ መጣ። እሱ ራሱ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ካሊፎርኒያ ውስጥ የሙዚቃ ኮንሰርቱን ካቀረበ በኋላ ስለ ትዝታ ሙዚቃ የሚከተለውን ሃሳብ ተናግሮ ነበር።

“ትዝታ ዘፈኖች ከእኔ የትዝታ ትዝታዎች ናቸው። ትዝታን እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም ሰው ሲጫወተው ሰውነቴን ይወረኛል። በተለይ ክራር የሚጫወት ሰው የክራር ቅኝቱን ሲጀምር ሰውነቴን ያሳክከኛል። ያቁነጠንጠኛል። አልዋሽም! ትዝታን ስጫወት ሰውነቴን ራሴን እረሳዋለሁ”

ብሏል።

     ይህ ድምፃዊ ሐገሩ ኢትዮጵያን በተለያዩ ሐገሮች ውስጥ በችሎታው በማስተዋወቅ ግዙፍ ውለታ የዋለና እየዋለም ያለ ትልቅ የጥበብ አምባሳደር ነው። ከዓመታት በፊትም ወደ እስራኤል ሀገር ሄዶም የሙዚቃ ኮንሰርቱን ሲያቀርብ በሺ የሚቆጠሩ ታዳሚያን ተገኝተው ተደስተው ወጥተዋል። በወቅቱም የእስራኤል ልዩ ልዩ ቴሌቪዥኖች 50 ዓመታት መድረክ ላይ ከተአምረኛ ሙዚቃዎቹ ጋር ስለሚውረገረገው ድምጻዊ ሰፊ ሽፋን ሰጥተውት ነበር። በወቅቱም በዚህችው የኢትዮጵያ የመንፈስ ወዳጅ በሆነችው በእስራኤል ውስጥ የሚገኘው በአማርኛ የሚተላፈው ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመሐሙድ አጠር ያለች ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው አሰራጭተዋል።

     በዚህ ዶክመንተሪ ላይ መሐሙድ ሲናገር፣ ብዙውን ጊዜ የዘፈኖቹን ሃሳብ ለገጣሚያን እየነገረ፣ በዚህ ሃሳብ ላይ ግጥም ፃፉልኝ እያለ እንደሚያፅፍ እና እንደሚያቀነቅንም አውስቷል።

     ለምሳሌ በያዘው ሃሳብ እና በአገጣጠም ስልቱ ብሎም በዜማው በእጅጉ የተወደደለትን “ተው ልመድ ገላዬ” የተሰኘውን ዘፈን የመጀመሪያው የሃሳቡ ጠንሳሽ መሐሙድ ራሱ ነው።

ተው ልመድ ገላዬ

ተው ልመድ ገላዬ

ትቶ የሔደን ሰው አትበል ከለላዬ

ተው ልመድ ገላዬ

     ይህን የመሳሰሉ የሙዚቃ ሃሳቦችን የፈጠረ ነው። ከዚህ ሌላም የጉራግኛ ብሔረሰብን ዘፈን ወደ አደባባይ አምጥቶ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረውና ተወዳጅ ሆኖ እንዲመጣ ከፍተኛ ውለታ ያበረከተ ከያኒ ነው።

     መሐሙድ አሕመድ ለ50 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ በጦር ሜዳዎችና በዱር በገደሉ እየተጓጓዘ አዚሟል። ወገኑን አዝናንቷል። በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስለ ፍቅር ሲያቀነቅን ኖሯል። ከዛሬ 16 ዓመታት ጀምሮ ከፈረንሳዊው የሙዚቃ ፕሮሞተር ከፍራሲስ ፋልሴቶ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን አልፎ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮች ላይ እየሰራ ነው። በሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች ሰፊ ተቀባይነት ካገኘ ውሎ አድሯል። መሐሙድ እረፍት የሌለው ተጓዥ ድምፃዊ! አይታክቴ ከያኒ ነው!

     መሐሙድ ዛሬም በሕይወት በመኖሩ ምክንያት ልንሳሳት ልንጨነቅለት፣ ልናስደስተው የሚገባ ሰው ነው። ዛሬ በሕይወት የሌሉት ምርጥ ጓደኞቹ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ታምራት ሞላ፣ ተፈራ ካሳ፣ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ ኮ/ል ሳህሌ ደጋጎ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ምርጥ ከያኒያንና ከያኒያት በሙሐሙድ ልቦና ውስጥ ሕያው ናቸው። ዛሬም ስለ እነሱ አውርቶ አቀንቅኖ አይጠግብም። ወዲያውም እንባውን መቆጣጠር አይችልም።

“ስንቱን አስታወስኩት

ስንቱን አሰብኩት

ልቤን በትዝታ ወዲያ እየላኩት

አንዴ በመከራው አንዴ በደስታዬ

ስንቱን ያሳየኛል ይሄ ትዝታዬ”

እያለ ያቀነቅንላቸዋል። መሐሙድ የፍቅር ሰው ነው።

     ከዚህ ሁሉ የ50 ዓመታት የሙዚቃ ጉዞ በኋላ አንድ ቀን ወጣቱ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ መሐሙድ ዘንድ መጣ። ጥሩ የሃሳብና የዜማ ስልት ያለውን ሸግዬ ሙዚቃ በጋራ አቀነቀኑ።

“በድንገት ያለፈውን ጊዜ በትዝታ

ባሰበው ተጉዤ ወደ ኃላ

እኔስ አጣሁ መላ”

            መሐሙድ

“ይቅርና ማሰብ በትካዜ

አጫውተኝ ስላለፈው ጊዜ”

ጎሳዬ

     በዚህ ዘፈን ውስጥ ተግተልትለው የሚመጡት ሀሳቦች በሙሉ የመሐሙድ ትዝታዎች ናቸው። በእጅጉ የሚወዳቸው ጓደኞቹ ትዝ ይሉታል። ያለፈው ሕይወታቸውና ፍቅራቸው ፊቱ ላይ ግጥም ይላል። መሐሙድ ያለፉ ጓደኞቹን ማሳያ ቋሚ ምስክር ነው። ቋሚ ባለታሪክ። ፈረንጆቹ /A Living Legend/ የሚሉት የኪነት ሰው ነው። መሐሙድ የሚሣሣለት አርቲስቶችን ነው። በሀገራችን ውስጥ ያሉ አያሌ ዩኒቨርስቲዎች አንዳቸውም ለመሐሙድ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አልሰጡትም። ቢሰጡት ለእነርሱም ክብር ነበር። ሕዝብና ዓለም የሰጠው ክብር ግን ትልቅ ነው። የክቡር ዶ/ር ሼህ መሐሙድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ደግሞ የሚገባውን አደረጉለት።

     የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በታደሙበት ደማቅ መድረክ ላይ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ የአምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክተውለታል። ምስጋና ይገባቸዋል!

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
12197 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us