አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ ከ1939-2007 ዓ.ም

Wednesday, 24 June 2015 11:46

በጥበቡ በለጠ


    በኢትዮጵያ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው በእጅጉ ጎልቶ ከሚጠሩት ሰዎች መካከል አንዱ ዳሪዮስ ሞዲ ነው። ዳሪዮስ ሞዲ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በተለይም በዜና እና በልዩ ልዩ ዘገባዎች የአፃፃፍ እና የአቀራረብ ቴክኒክ ውስጥ ሙያዊ አስተዋፅኦ በእጅጉ ሰፊ ነው። አያሌዎች በእርሱ የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ እና ድምፅ ተማርከው ወደ ሙያው ገብተዋል። በሙያ ውስጥም የነበሩት ከእርሱ ተምረው ራሳቸውን አሳድገዋል። ለመሆኑ የዳሪዮስ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ብቃት መለኪያው ምንድን ነው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። በጥቂቱ የተወሰነውን መግለፁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

     በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ውስጥ ድምፅ ትልቁን ቦታ ይወስዳል። ድምፅ ሲባል የፃፍነውን ወይም የተፃፈልንን ነገር የምናቀርብበት ለዛ ነው። ሬዲዮ በባሕሪው በጆሮ የሚደመጥ በመሆኑ የሚቀርበውን /የሚተላፈውን/ ርዕሰ ጉዳይ እንዲደመጥ የማድረግ ችሎታ ከጋዜጠኛው ይጠበቃል። ጋዜጠኛው በተወሰነ ደረጃ የተፈጥሮ የድምፅ ለዛ ሊኖረው ይገባል። ይህን የድምፅ ለዛውን እንደየሚቀርበው ወሬ፣ ዜና፣ ታሪክ፣ ትረካ ወዘተ እያስማማ የአድማጩን ጆሮ መማረክ አለበት። ቃላት በባሪያቸው ይጠብቃሉ፣ ይላላሉ። ግን የሚላሉትና የሚጠብቁት በውስጣቸው ባሉት ፊደላት ላይ አንባቢው /ጋዜጠኛው/ በሚፈጥረው ድምፀት ነው። ይህን ማወቅና ማቅረብ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት የመጀመሪያው ሀሁ ነው። በዚህ ረገድ ደግሞ ዳሪዮስ ሞዲ አፉን የፈታበት ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

     ሌላው ደግሞ ለሬዲዮ ዜናም ሆነ ዘገባ ወይም ታሪክ ሲፃፍ እንደ ጋዜጣ እና መፅሔት ፅሑፎች አለመሆኑን ማወቅ ነው። በጋዜጣና በመፅሔት የሚፃፉ ፅሁፎች አንባቢው በአይኑ እያየ የሚያነባቸውና ካልገባውም ወደ ኋላ ተመልሶ አንብቦ የሚረዳበት፣ የቃሉ ፍቺ ከከበደው መዝገበ ቃላት ሁሉ አምጥቶ የሚረዳበት ነው። ሬዲዮ አድማጭ ግን ካልገባው አልገባውም። ካመለጠው አመለጠው። ወደ ኋላ ተመልሶ የሚረዳበት አጋጣሚ የለም። ስለዚህ ለሬዲዮ አድማጭ የሚፃፉ ስክሪብቶች ቀለል ያሉ ናቸው። ቅለታቸው የሃሳብ ቅለት አይደለም። የአገላለፅ ቅለት ነው። ሁሉም ሰው ሳይቸገር ሊረዳቸው የሚችሉ፣ በሙያ ቃላት ያልታጀቡ፣ እንደ ንግግር፣ እንደ ጨዋታ በጆሮ የሚፈሱ መሆን አለባቸው። የሬዲዮ ጽሁፎች ምንም እንኳን በአይን የማይታዩ ቢሆኑም በጆሮ ሲገቡ ግን ምስል መከሰት እንዳለባቸው የሙያው ጠበብቶች ጽፈውበታል። በዚህ ለሬዲዮ ተብለው በሚፃፉ ጽሑፎች ታሪክ ውስጥም ዳሪዮስ ሞዲ ከፊት ከፊት የሚሰለፍ አንጋፋ ባለሙያ ነበር።

     እኔም ከ15 ዓመታት በፊት የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን በማጠናቀቅበት ወቅት የሰራሁት የመመረቂያ ወረቀት በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በተለይም በዜና አቀራረብና ንባብ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ የጥናት ወረቀት እንደ ማመሳከሪያ አድርጎ ያቀረበው መረጃ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥ በተለይም “ዜና ፋይል” እየተባለ በሚጠራው ፕሮግራም ላይ ነበር። በዚህ በዜና ፋይል ውስጥ የተፃፉ ዜናዎችን በምመረምርበት ወቅት በርካታ ጠንካራ ጎኖችን አግኝቼ ነበር። ለምሳሌ በሌሎች ጋዜጠኞች የተፃፉ ዜናዎችን በብዛት ያርም /የአርትኦት/ ስራ ይሰራ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር። ዜናዎችን ያረመበት እና አስተካክሎ የፃፈበት መንገድም የሬዲዮ ዜና አፃፃፍ ቴክኒኮችን በሚገባ የተከተሉ እንደነበሩ በጊዜው ለማወቅ ችያለሁ። በጥናቴ ውስጥም በዝርዝር ተካቷል። ስለዚህ ዳሪዮስ ሞዲ በኢትዮጵያ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

     ግን ይህን ሁሉ መዘርዘር ሳያስፈልግ የዳሪዮስ ሞዲን አስገምጋሚ የሬዲዮ ድምፅ በመስማት ብቻ ብዙ መናገር ይቻል ነበር። ዳሪዮስ ሞዲ ዜና ሲያነብ አድማጩን ሁሉ ቁጭ አድርጎ፣ የሚጓዘውም ቆሞ እንዲያደምጠው የማድረግ ኃይል አለው።

ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት የመሩት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ባልተጠበቀ እና ባልታሰበ ሁኔታ ከሀገር የመውጣታቸውን ዜና ለሚሊዮኖች ያበሰረው (ያረዳው) ዳሪዮስ ሞዲ ነው። ዜናው የቀረበው ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ነበር። ዳሪዮስ የሚከተለውን አነበበው፡-

“ለረጅም ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሔድ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ለማስቀረት በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሔድ ላይ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆምና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከስልጣቸው ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሔደዋል። “

        ይህን ዜና ያነበበው የአስደማሚ ድምፅና ላዛ ያለው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር። ዜናው በእጅጉ አስደንጋጭ ነበር። “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” እያሉ የፈከሩት መንግሥቱ፣ “አንዲት ጥይት እና ሰው እስከሚቀር እንዋጋለን!” ያሉት መንግሥቱ፣ “ማዕረጋቸውን ቆርጥን፣ ቂጣቸውን በሳንጃ ወጋን!” ያሉት መንግሥቱ፣ “ቀኝህን ለመታህ ግራህን ስጠው የሚለው አባባል የሚያስቃቸው መንግሥቱ፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም እያሉ በወኔ የሚናገሩት መንግሥቱ፣ ከአብዮታዊ መሪያችን ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት የተባለላቸው መንግስቱ፣ አገር ጥለው ሔዱ ሲባል ያስደነግጣል። ለዚያውም የት እንደሔዱ እንኳን አይታወቅም ነበር። የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ በእጅጉ አሳሳቢ ነበር። ጦርነት ከሰሜን ኢትዮጵያ በብርሃን ፍጥነት ወደ ታች እየተጓዘ ነው። እናም ዳሪዮስ ሞዲ በነበልባል ድምፁ ይህን ዜና በማቅረቡ ታሪካዊ ሰው እንዲሆንም አድርጎታል። ለመሆኑ ዳሪዮስ ሞዲ ይህን ዜና እንዴት አነበበው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። በአንድ ወቅት “ኢትዮጵ” በመባል ትታወቅ የነበረችው መፅሔት ግንቦት ወር 1994 ዓ.ም የሚከተለውን ቃለ-ምልልስ ከዳሪዮስ ጋር አድርጋ ነበር።

ኢትዮጵ፡- ዳሪዮስ ያንን ዜና ስታነበው ፍርሃት አልተሰማህም?

ዳሪዮስ፡- ለምን ትንሽ ሰፋ አድርጌ አልገልፅልህም፤ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ አብዱልሐፊዝ ዩሱፍ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያምን ወደ ቢሯቸው ያስጠሩታል። ጌታቸው ያኔ የቅርብ አለቃዬ ነበር። ጌታቸው ከሚኒስትሩ ቢሮ ተመልሶ እንደመጣ “ቆይ ከዚህ እንዳትሄድ” አለኝ። “ለምን” ስለው “የሚነበብ ዜና አለ” አለኝ። “እኔ እኮ ተረኛ አይደለሁም አልኩት። “አይ አንተ ነህ የምታነበው” አለኝ። እና በዚያው አነበብኩት።

ኢትዮጵ፡- ዜናው ምን እንደሆን አስቀድሞ አልተነገረህም?

ዳሪዮስ፡- በፍፁም! እንኳንስ እኔ፣ ጌታቸው ራሱ ያወቀ አልመሰለኝም። ብቻ በቃ “የሚነበብ ዜና አለ” ነው የተባልኩት። ስድስት ሰዓት ሲደርስ ስቱዲዮ ገባሁ። ያኔ ወረቀቱን ሰጠኝ። “ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ይላል።

ኢትዮጵ፡- አልደነገጥክም?

ዳሪዮስ፡- በጭራሽ! እንዲያውም እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። ልክ አንብቤ እንደጨረስኩ “አሁን ወደምትፈልግበት መሔድ ትችላለህ ተባልኩ”።

    ዳሪዮስ ሞዲ ለበርካታ የሬዲዮ ጋዜጠኞች መፈጠር እንደ ማንቂያ እና መቆስቀሻ ሆኖ አገልግሏል። ነጋሽ መሐመድ፣ ዓለምነህ ዋሴ፣ ቢኒያም ከበደ፣ ደረጄ ኃይሌን የመሳሰሉ ጎበዝ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ሞዴላቸው ዳሪዮስ ነበር።

የዳሪዮስ ሞዲ ልዩ መገለጫ ናቸው ከሚባት ውስጥ ለልጆቹ የሚያወጣላቸው ስም ነው። ስማቸው ከወትሮው ስም ለየት ያለ፤ አንዳንዴም ደንገጥ የሚያደርግ ነበር። በዚሁ ዙሪያ የዛሬ 13 ዓመት 1994 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ከወጣው ኢትዮጵ መፅሔት ላይ የሰፈረውን ባወጋችሁስ፡-

ኢትዮጵ፡- ዳሪዮስ ለልጆችህ የምትሰጠው ስም አስገራሚ ነው ይባላል። የሰሙ ሰዎች ለማመን ያቅታል ነው የሚሉት።

ዳሪዮስ፡- ለምን ያቅታቸዋል?

ኢትዮጵ፡- አስገራሚ ስለሆነ ነዋ!

ዳሪዮስ፡- ምን የሚገርም ነገር አለውና?

ኢትዮጵ፡- እስኪ ለምሳሌ ከልጆችህ ስሞች መካል አንዱን ጥቀስልኝ?

ዳሪዮስ፡- ቼ ጉቬራ

ኢትዮጵ፡- እሺ ሌላስ?

ዳሪዮስ፡- ትግል ነው።

ኢትዮጵ፡- የምርህን ነው ዳሪዮስ?

ዳሪዮስ፡- አዎና! ትግል ነው ዳሪዮስ።

ኢትዮጵ፡- ከሴቶቹ መካከል ለምሳሌ?

ዳሪዮስ፡- አምፀሸ ተነሺ!

ኢትዮጵ፡- እየቀለድክብኝ ነው?

ዳሪዮስ፡ ቀልድ አልወድም! “አምፀሸ ተነሺ ዳሪዮስ” ብዬሀለሁ።

ኢትዮጵ፡- እና አሁን ይሄ እውነት የልደት ስማቸው ነው? ትምህርት ቤትም በዚሁ ነው የሚጠሩት?

ዳሪዮስ፡- ስማቸው እኮ ነው!

     ዳሪዮስ ሞዲ ላመነበት ነገር እስከ መጨረሻው ድረስ በአቋሙ ፀንቶ የመቆየት ብቃት ያለው ጋዜጠኛም ነበር። ይህንን ፀባዩን የሚያሳይልን ደግሞ በአንድ ወቅት የተከሰተው ሁኔታ ነው። ጉዳዩ፣ አንድ ሰው የማይወዳቸው ምክትል ምኒስትር ከስራ ቦታቸው በእድገት ይቀየሩና ወደ ሌላ መስሪያ ቤት ይዘዋወራሉ። ታዲያ በዚህ ወቅት ሰራተኛው መዋጮ አድርጎ የአሸኛኘት መርሃ ግብር ያደርጋል። ዳሪዮስ ግን አስገራሚ ነገር ፈፀመ። ታሪኩን ከኢትዮጵ መፅሔት ጋር እንዲህ ተጨዋውቶታል፡-

ኢትዮጵ፡- ለምክትል ሚኒስትሩ መሸኛ ከሰራተኛው ገንዘብ ሲዋጣ አስር ሳንቲም ብለህ ሊስቱ ላይ ሞልተሃል ይባላል።

ዳሪዮስ፡- አይ ተሳስተሃል. . .!! አምስት ሳንቲም ነው ያልኩት። ግን እኮ ታዲያ ለበቀል አይደለም። እንደውም ከኔ በላይ የተጎዱ ሰዎች ነበሩ። እነዚያ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ አዋጥተዋል። ይህንን ሳይ ተናደድኩና አምስት ሳንቲም ብዬ ሞላሁ። “ቦቅቧቆች! ያንን ያደረኩት።

ኢትዮጵ፡- ሚኒስትሩ ተናደው ወደ ቢሮህ ድረስ መጥተው ሳንቲሟን አፍንጫህ ላይ ወርውረው ሔዱ የተባለውስ?

ዳሪዮስ፡- ውሸት ነው። ምክንያቱም እኔ ሳንቲሟን ገቢ አላደረኩም። አምስት ሳንቲም ብዬ ከስሩ ሌላ ነገር ፃፍኩበት።

ኢትዮጵ፡- ምን ብለህ?

ዳሪዮስ፡- ከደሞዜ ላይ የሚቆረጥ!

    እንዲህ አይነት የሚያስቁ የሚያስገርሙ ድርጊቶችና ገጠመኞች ያሉት ዳሪዮስ ሞዲ፣ በሬዲዮ የጋዜጠኝት ታሪክ ውስጥ ሙያውን ጠንቅቆ የሚያውቅና በስራውም እንከን የማይገኝበት ጋዜጠኛ እንደነበር አብረውት የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ።

ዳሪዮስ ሞዲ ገና ስራ በያዘበት ወር 1964 ዓ.ም የመጀመሪያ ደሞዙን እንዳገኘ ውብ ከነበረችው ባለቤቱ ከመሳይ ጋር ጋብቻ ፈፀመ። ላለፉት 43 ዓመታትም ዳሪዮስና መሳይ ፍቅርና ደስታ የተሞላበት ሕይወት ከልጆቻቸው ጋር አሳልፈዋል። ነገር ግን የዛሬ አራት ወር ባለቤቱ መሳይ አረፈች። ከሰሞኑ ደግሞ ይሔው የነጎድጓዳማና የነበልባል ድምፅ ባለፀጋው ዳሪዮስ ሞዲ ተከተለ።

     ብዙዎች የሬዲዮ ጋዜጠኞች በሞት ያጣነው ዳሪዮስ ለሙያው ት/ቤት ሆኖ አገልግሏል ባይ ናቸው። ባለፈው እሁድ የቀብር ስነ-ስርዓቱ ሲከናወን የዳሪዮስን የህይወት ታሪክ የፃፈውና ያነበበው ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ ነበር። በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ውስጥ ዳሪዮስን ተካተዋል ከሚባሉት ውስጥ ቢኒያም ከበደ አንዱ ሲሆን፣ እሱም የዳሪዮስን ታሪክ እንዲህ ፅፎ እየተንሰቀሰቀ አነበበው፡-

የተፃፈለትን ያላነበበ ጋዜጠኛ

     “ጋሽ ዳሪዮስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞች አባትም ነበረ። ይሄ ታሪክ ብቻ ሊሆን ይችላል። ነበር ቅርብ ነው። ነበር እያልን ዳርዮስን ብቻ ሳይሆን ሙያውንም አብረን እንቅበረው።

     በፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፎቶ ቤት ሞሪስ እልቪስን የከፈቱት የሚስተር ሞዲ ጉስታቭ ልጅ ነው፤ ዳሪዮስ ሞዲ። በትውልድ ፐርሺያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ ከሆኑት ከሚስተር ጉስታቭ እና ከወ/ሮ አማረች መኩሪያ ታህሳስ 12 ቀን 1939 ዓ.ም እዚያው ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ተወለደ። የድርሰትና የግጥም ዝንባሌ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ማንበብ፣ ሁኔታዎችን በጥልቀት ማስተዋልና መመርመር የጀመረው ከልጅነቱ ጀምሮ ነው።

     በኢትዮጵያ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ሲታገሉ ከነበሩት ተማሪዎች በተለይም ከጥላሁን ግዛው ጋር ለአንድ አላማ ተሰልፈው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ላይ ቢቆይም የጥላሁን ግዛውን መገደል ተከትሎ ድርጊቱን በፅኑ ካወገዙት አስር ጓደኞቹ ጋር የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ጥሎ ወጥቷል። ዘመኑም 1962 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በነበረው መንግሥት አመለካከቱ ያልተወደደለት ዳሪዮስ፣ ድፍን ሁለት ዓመት ሙሉ ስራ የሚቀጥረው አላገኘም ነበር። ይሁንና በግሉ የትርጉም ስራዎችን ይሰራ ስለነበር በ1964 ዓ.ም በብስራት ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ለመቀጠር ምክንያት ሆነው። ህይወቱ መስመር ያዘ፡-

በመልካም ፀባይ እና ባህሪዋ የቁንጅና ጣሪያ ከሆነችው መሰረት ኃይሌ /መሳይ/ ጋር ትዳር መሰረተ። ትዳሩም ፀንቶ አራት ወንድ ልጆችን እና ሶስት ሴት ልጆችን አፈራ።

     ዳሪዮስ ሞዲ ለሬዲዮ የተፈጠረ ምሉዕ በኩልዔ የሆነ ጋዜጠኛ ነበረ። ተስምቶ የማይጠገብ፣ እያነበበ የሚስረቀረቅ የሬዲዮ ሞገድን የሚገዛ ባለግርማ ድምፅ የታደለው ዳሪዮስ ሞዲ፣ ከዜና ባህሪው ተነስቶ አነባነቡን የሚከተል እንከን አልባም ዜና አንባቢ ነበር። መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የሚሉት ጎልቶ ይደመጥላቸው ዘንድ የሚዲያው ልሳንና የድምፅ ሞገድ ዳሪዮስ ነበር። እንደየጊዜው የአዳዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ ድምፅ ሆኖም አገልግሏል። እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስራ ውስጥ እንደ ዳሪዮስ አይነት የትርጉም ጌታ አልተገኘም። ዳሪዮስ ዘንድ በይመስለኛል እና ይሆናል በሚል አቻ ትርጉም አይገኝም። የቀደምት አባቶቹን መዝገብ እየፈተሸ፣ ለዘመናዊው አለምም እንዲስማማ የራሱንም የትርጉም መንገድ እየፈለገ የሚማስን የቃላት ዲታ እና ታላቅ ሙያተኛ ነበር። የራሱን ትርጉም የሕዝብ ቋንቋ ማድረግ የቻለ፣ የቋንቋ ምሁራንም ደግመው ደጋግመው የሚመሰክሩለት የትርጉም መምህር ነበር። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያኒኛ የመተርጎም ብቃት የመነጨው ካልተቋረጠ የንባብ ብቃቱ ነው።

     ስራው ላይ እንዳቀረቀረ እስከወዲያኛው ያንቀላፋው ይህ ሰው በቁሙ አስታውሶ፣ ሙያዊ ልቀቱን መዝኖ መሸለም ባልተለመደበት ሀገር እንደዋዛ ኖሮ ማለፉን ለምናውቅ ለኛ የእግር እሳት ነው።

     በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የጀመረው የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሕይወቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለ30 ዓመታት ቢቀጥልም ይከፈለው የነበረው ደሞዝ የሰውየውን አስደናቂ ችሎታና የሙያ ልቀት የሚመጥን ቀርቶ ለወር አስቤዛ የማይበቃ ነበር። እንዲህም ሆኖ ህይወት ለዳሪዮስ ሬዲዮ ነው። ጡረታም ወጥቶ የናፈቀውን ሬዲዮ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን በሸገር እና በሬዲዮ ፋና ቀጥሎበት ቆይቷል።

     ዳሪዮስ ሞዲ ወር ጠብቆ ከሚያገኘው ከሶስት አሃዝ ባልበለጠ ደሞዝ ራሱን እና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ቢቸገርም ያን ወርቃማ ድምፁን ግን ለማስታወቂያ ለማዋል፣ ማስታወቂያ ሊሰራበት ግን ፈቃደኛ አልነበረም። ዜና ላይ የሚሰማ ድምፅ እንዴት ሆኖ ሸቀጥ ይተዋወቅበታል ሲል ይሞግታል። ይህ በራሱ የሙያውን ሥነ-ምግባር መጣስ ነው ሲል ለሙያው መርህ እና ልዕልና አጥብቆ ይከራከራል።

     የመጨረሻዎቹ ሶስት ዓመታት ለዳሪዮስ ጥሩ አልነበሩም። ለዘመናት ማልዶ ከስራው ገበታው የማይታጣው ዳሪዮስ ህመም ደጋገመው። እንደ ልብ መተንፈስ ተሳነው። በኦክሲጅን እየተረዳ ቆየ። ዳሪዮስ የልብ ትርታው ቀጥ የምትል የምትመስለው ኦክሲጅን ሲያጣ ብቻ አልነበረም። ካላነበበና ዜና ካልሰማ እስትንፋሱ ያለ አይመስለውም።

ጋሽ ዳሪዮስ ሰውን ቶሎ የማይቀርብና ከቀረበም የእድሜ ልክ እውነተኛ ወዳጅ የሚሆን፣ ትሁት ደግ እና እውቀቱን ያለ ስስት የሚሰጥ ታማኝ ሰው ነበር።

እንደው በቀዝቃዛው በክረምቱ ሰሞን

እንከተላለን አንድ ጎበዝ ቀድሞን

አይ ጉድ መፈጠር ለመሰነባበት

ዳሪዮስን መቼም ማንም አይደርስበት

ሮጥን ሮጥን የትም አልደረስንም

ማን ይከተለዋል ውድ ዳርዮስን

ብለን ለመሰነባበት ከእግዚአብሔር አስገራሚ ስራ አንዱን እንደ ማሳረጊያ እንይ።

     ለ43 ዓመታት ከጎኑ ያልተለየችው፣ ለትዳሯም ለልጆቿም ህልውና የደከመችው፣ ልጆቿ እንኳን አይተዋት ስሟ ሲጠራ የሚንሰፈሰፉላት መሳይ፣ ልክ የዛሬ አራት ወር ከሁለት ቀናት ታማ አርብ እለት ሆስፒታል ገባች። ዳሪዮስም ለመጨረሻ ጊዜ ሆስፒታል የገባው በዕለተ አርብ ነበር። አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 11 ሰዓት በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ባለትዳሮቹ ነፍሳቸው ተለየች። ልክ እንደዛሬው በዚህ ስፍራ መሳይን ሸኘናት። ዳሪዮስ ተከተላት። አርብ፣ ቅዳሜ እሁድ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ይህችን አለም ተለዩ።”

     እኛም የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አባላት በጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ ሞት የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን፣ ለቤተሰቡ፣ ለልጆቹ እና ለመላው አድናቂዎቹ መፅናናትን እንመኛለን።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12442 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us