አዲሱ የፖለቲካ ሥነ - ጽሁፍ

Wednesday, 01 July 2015 14:43

በጥበቡ በለጠ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የመፃሕፍት ሕትመትና ስርጭት ከነበረበት አዘቅት ወጣ እያለ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያመለክቱን ጉዳዮች አሉ። ለምሣሌ አያሌ ሰዎች በየመንደሩ እና አደባባዩ መፃሕፍትን ይዘው ሲሸጡ፣ ጎዳና ላይ ዘርግተው ሲሸጡ፣ ሕንፃዎችን ተከራይተው ሲሸጡ፣ አውደ-ርዕይ አዘጋጅተው ሲሸጡ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በመፃሕፍት ኤግዚቢሽን እና ሕትመት ላይ መሣተፉ፣ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ብሎም የጋዜጣና የመፅሔት አምዶች ለመፃሕፍት ሽፋን መስጠታቸውን ስንመለከት ከቀድሞው የተሻሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን እንረዳለን።

 

ከዚህ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የመጡ ክስተቶችም አሉ። በመፅሐፍት ንባብ ላይ አደጋ ውስጥ የገቡ የአፃፃፍ ርዕሰ ጉዳዮች ይታያሉ። ለምሳሌ የልቦለድ ሥነ - ፅሁፍ አሁን ባለው የመፃሕፍት እንቅስቃሴ አንባቢ የማጣት ድርቀት ይታይባቸዋል። እነርሱን ተከትሎም የግጥም መፃሕፍትም ገበያው ላይ ቀዝቀዝ ያሉ ናቸው። ይሔ ለምን ሆነ ብሎም ማጥናት እና ጉዳዩን ለውይይት ብሎም ለመፍትሔ ማብቃት ያስፈልጋል። ለመሆኑ አሁን በመፅሐፍት ስርጭት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እያገኙ ያሉት ርዕሰ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

 

ከመፅሐፍት አከፋፋዮችና ሻጮች አካባቢ ካገኘኋቸው መረጃዎች አንፃር ፖለቲካዊ መፃሕፍት፣ የፖለቲካ ወግ ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች፣ በተለይ ደግሞ የገዢውን መንግስት የሚተቹ ፅሁፎች እና የታሪክ መፃሕፍት በንባቡ ዓለም ቀዳሚ ምዕራፍ እንዳደያዙ ገልፀውልኛል።

 

በርካታ ጋዜጠኞችና አምደኞች ደግሞ ወደ መፃሕፍት ማሳተም ስራ ውስጥ በመግባታቸው የዘርፉን እንቅስቃሴ አሹረውታል። አሹረውታል ያልኩት ጋዜጣ አንባቢ የነበረውን ሰው ወደ መፃሕፍት ንባብ አምጥተውታል። በጋዜጦችና በመፅሔቶች ላይ ይፅፏቸው የነበሩትን መጣጥፎች ወደ መፃሕፍት ሕትመት ስላመጧቸው ፖለቲካዊ ሞቅታ እና ግለት ያላቸው ስነ -ፅሁፎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በእንደዚህ አይነት ጭብጦች ላይ ያተኮሩ መፅሐፍትን በተለይ ከ1960ዎቹ ትግል በኋላ የመጡትን የተወሰኑትን ከዚህ በፊት አጭር ዳሰሳ አድርጌባቸው ነበር። አሁን ደግሞ በዘመነ ኢሕአዴግ ውስጥ የታዩትን ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚያሳዩ ሥነ -ፅሁፎች በርከት ብለዋል።

 

በዚህ ዘመን ውስጥ ያሉትን አፃፃፎች ለመቃኘት ደፋ ቀና በምልበት ወቅት አዳዲስ መፃሕፍትም እየተደመሩብኝ መጡ። በቅርቡ እንኳን ሙሉዓለም ገ/መድሕን የኢሕአዴግ ቁልቁለት የሚል መፅሐፍ ሲያሳትም፣ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ የረከሰ ፍርድ በሚል ርዕስ መፅሐፍ አሳትሟል። ከዚህ በፊት የታተሙትን ፖለቲካዊ ቃናቸው ጎልቶ የሚታዩትን መፃሕፍት የተቀላቀሉት እነዚህ ሁለቱ መፃሕፍት የራሳቸው የሆነ ልዩነትን ይዘው ነው የመጡት።

 

የሙሉዓለም ገ/መድህን የኢሕአዴግ ቁልቁለት የተሰኘው መፅሐፍ 235 ገፆችን የያዘ እና 14 ምዕራፎችን ያካተተ ነው። እነዚህ ምዕራፎች ዝርዝር ገለፃዎችና ትንታኔዎችን በውስጣቸው የያዙ ሲሆን፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥት እንዲሁም ደግሞ በተቃውሞ መስመር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ፓርቲዎችን ድክመትና ጥንካሬያቸውን የሚያሳይ ነው። ከዚህ አልፎ ደግሞ በተለይ በገዢው ፓርቲ ላይ መራር ሂስ በመስጠት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መፅሐፍ ነው።

 

የሙሉዓለም ገ/መድህን፣ የኢሕአዴግ ቁልቁለት መፅሐፍ ውስጥ የተዘረዘሩት ምዕራፎች ፀሐፊው ከዚህ በፊት በፋክት፣ በአዲስ ጉዳይ እና በሎሚ መፅሔቶች ላይ የፃፋቸውን መጣጥፎች ገሚሶቹን አሻሽሏቸውና የተለያዩ መረጃዎችን አክሎባቸው ሰብሰብ አድርጎ ያሳተማቸው ናቸው።

 

ጋዜጠኛ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ የረከሰ ፍርድ በተሰኘው መፅሐፉ 14 ርዕሰ ጉዳዮችን በ189 ገፅ መፅሐፉ እየዘረዘረ ፅፏል። አለማየሁ ገበየሁ አሁን ኑሮውን በውጭ ሀገር ያደረገ ሲሆን በሀገር ውስጥ ሳለ በጋዜጠኝነቱ እየተዘዋወረ ሲሰራ የገጠሙትን ታሪኮች ከማስታወሻ ደብተሩ ላይ እያጣቀሰ ሰፋ ዘርዘር አድርጎ የፃፋቸው ታሪኮች ናቸው። እርሱ እንደሚለው “ትናንሽ ታሪኮች ደንበኛ ታሪክ ከመሆናቸው በፊት ጋዜጣ ላይ ይሰፍራሉ። ጋዜጣ ላይ ከመስፈራቸው በፊት ደግሞ ጋዜጠኛው ማስታወሻው ደብተር ላይ ይሰፍራሉ። የአንድ ጋዜጠኛ ሀብትም ይሄው ነው። እውነት እላችኋለሁ ጋዜጠኛ ሀብት የለውም፤ ከማስታወሻ ደብተሩ በቀር። እድሜ ያጨራመታትን ማስታወሻ ደብተሬን እንደ ቀልድ ማገላበጥ ጀመርኩ። ያልተከተበ ጉዳይ የለም. . .። . . . እናም . . . ይህችን ማስታወሻ ደብተሬን ለናንተ በማጋራቴ ደስ ብሎኛል” ይለናል።

 

ሙሉዓለም ገ/መድህን ቀደም ሲል በልዩ ልዩ መፅሔቶች ላይ የፃፋቸውን፣ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ ከማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያገኛቸውን ትውስታዎች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሥነ- ጽሁፍ በተለይም ፖለቲካዊ ዘውግ ወዳላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ተቀላቅለዋል። እርግጥ ነው አለማየሁ ገበየሁ በመፃህፍት ሕትመት የመጀመሪያው ባይሆንም በአዲሱ መፅሐፉ ግን ለየት ባለ ርዕሰ ጉዳይ ቀርቧል።

 

መፃሕፍቶቹ በውስጣቸው የያዙትን ርዕሰ ጉዳይ በአጭሩ ላስረዳ። የሙሉዓለም ገ/መድህን፣ የኢሕአዴግ ቁልቁለት መራር ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት፣ በተለይ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለሰብዐዊ መብት መከበር ያልቆመ መሆኑን፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሔዱ የመብት ጥሰቶችን እና ድርጊቶችን በትንታግ ቃላትና ገለፃ የሚተነትን ነው። የሙሉዓለም ገ/መድህን የሰላ ሂስ በመንግስት ላይ ብቻ አይደለም። በተቃውሞ መስመር ውስጥ ገብተው የረጅም ዘመን የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉትንም ፓርቲዎች ይተቻል። የውስጥ አሰራራቸውን፣ ራዕያቸውን እና ያስመዘገቡትን ውጤት እያነሳሳ በሚፈጁ የቃላት ውርጅብኞች ይተነትናቸዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ኦነግ /የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ እየተባለ ስለሚጠራው የፖለቲካ ቡድን ከ40 ዓመታት በላይ የተራዘመ ትግል ያደረገው ሀገራዊ አጀንዳ የሌለው በመሆኑ እና ኢትዮጵያንም እንደ ሀገር ለመመልከት ችግር ያለበት በመሆኑ ከስኬቱ ውድቀቱ መብዛቱን ያመለክታል ፀሐፊው። ቀደም ባለው ዘመን ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራደር እንፈልጋለን ይሉ የነበሩት የኦነግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ሌንጮ ለታ፣ ዛሬ ከፓርቲው ራሳቸውን አግልለው ሌላ ፓርቲ መስርተው በተወሰነም ደረጃ ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ ቀርፀው ዳግም ብቅ ማለታቸውም ተአማኒነት የሚያስገኝላቸው እንደማይሆን ሙሉዓለም ገ/መድህን ያስረዳል።

 

ከዚህ በተጨማሪም የቀደመው ትውልድ ማለትም 1960ዎቹ ትውልድ ጥሎት ያለፈው መጥፎ አሻራም በዚህ ዘመን ላይ ላለው ወጣት ትልቅ ሳንካ እንደሆነበትም ይገልጻል። ያለፈው ትውልድ ከውይይትና ከድርድር ውጭ መልስ ይመላለስ የነበረው ከጠመንጃ ላንቃ ከሚንፎለፎሉ አረሮች አማካይነት ስለነበር ዜጎች አለቁ፤ እናቶች አነቡ፤ ትውልድ ተሰደደ፤ ቀሪውም ከፖቲካው መድረክ ራሱን አቀበ። ፍራቻ ነገሰ። አድርባይነት ተስፋፋ። የ40 ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መረጋጋት እንደጠፋበት የሙሉዓለም መፅሐፍ ይገልጻል። ስለ ስደተኛ ፖለቲከኞች፣ ነፍጥ አንስተው ስለሚዋጉ ኃይሎች፣ ከፖለቲካው ዓለም ራሳቸውን ስላገለሉ ሰዎች፣ ስለ ብሔራዊ እርቅ አስፈላጊነት፣ ስለ ነጻው ፕሬስ ሳንካዎችና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዳሷል።

 

ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገበየሁም በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅፏል። የሃሳብ መነሻውን ከጋዜጠኛ ማስታወሻ ደብተሩ ላይ እየወሰደ ሥነ - ፅሁፋዊ ገለፃ እና ትርክቶችን በያዙ ቃላት ፅፏል። በተለይ በምርጫ 97 ወቅት እርሱ የመንግስት ጋዜጠኛ ሆኖ በምርጫ ጣቢያዎች እና በድምፅ ቆጠራ ወቅት ያያቸውን እና በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያሰፈራቸውን ሃሳቦቹን እየዘረዘረ አቅርቧል። በስራ አጋጣሚ በተገኘባቸው ስብሰባዎች ላይ የታዘባቸውን አያሌ አስተዳደራዊ እና ስሜታዊ መልሶችን ሁሉ በመፅሐፉ ውስጥ በወግ የአቀራረብ ስልት ይተርካል።

 

በዓለማየሁ ገበየሁ ብዕር ውስጥ ብዙ የትዝብት ሀቆች እንደተገለፁበት ከሚያሳዩን ቦታዎች አንዱ በስብሰባዎች ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎችና ከሰብሳቢው አካል ደግሞ የሚሰጡ መልሶች ናቸው። ለምሳሌ ጥቂቶቹን እንይ፤

 

“የኢህአዴግ የፍትህ ስርዓት ሽባ ሆኗል። የሆነ ቦታ ያጠፋ ሰው፤ የሆነ ቦታ የሚሾምበት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ዳኞች በነፃነት አይወስኑም፣ ዳኛው ጨክኖ ቢወስንም ወዲያው ፖሊስ ያፈርሰዋል. . .”

 

የሚል ጥያቄ ሲቀርብ የተሰጠው መልስ የሚከተለው እንደነበር መጽሐፉ ይገልፃል፡-

 

“ዳኞችን እያስገደዱና እያስፈራሩ እንዲወስኑ የሚደርግበት አሰራር የለም። ወ/ሮ ብርቱካን ሚድቅሳ ስዬን በነፃ ነው ያሰናበቱት። መንገድ ላይ እንዲያዙ መደረጉ የፍትህ ስርዓቱን የሚቃወም አይደለም። ተፅዕኖ የሚባለው ወ/ሮ ብርቱካን ላይ ተፅዕኖ ተደርጎ በነፃ መልቀቅ የለብሽም ቢባል ነበር” 58

 

 

ሌሎችንም በዚህ አይነት ሁኔታ የተሰጡ ጥያቄና መልሶችን እናነባለን። የጋዜጠኛው የማስታወሻ ደብተሩ ትዝታዎች ናቸው። በርግጥ እንዲህ ባለው መድረክ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶች ሙሉ በሙሉ የመንግሥት አቋም ናቸው ስለማይባል፣ በተለይ ደግሞ መድረኩን እንደሚመራው ሰው አስተሳሰብና ችሎታ የሚወሰን ነው። ግን የሚያሳየው የአስተዳደር ክፍተት ደግሞ ሰፊ ነው።

 

እነዚህ ሁለት መፃሕፍት ዋነኛ ጭብጣቸው መንግሥትና ሕዝብ ነው። ያዩትን የታዘቡትን አንዱ በመራር ፅሁፍ ሌላኛው ደግሞ ሥነ-ፅሁፋዊ ቀለም እየቀባባው ጽፈዋል። ሁለቱም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመፅሐፍት ገበያ ውስጥ ተፈላጊ እየሆኑ ከመጡ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ዘውጋቸውን መሰረት አድርገው ተቀላቅለዋል።

 

አሁን ባለንበት ወቅት የመፅሐፍት ሽያጩ የደራላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ቃና፣ ፖለቲካዊ ሽሙጥ፣ ፖለቲካዊ ወግ፣ የግል የሕይወት ታሪኮች በተለይ በፖለቲካው መድረክ ውስጥ የነበሩ ሰዎች የሚፅፏቸው መፃሕፍት በተደጋጋሚ እየታተሙ ይሸጣሉ። በአዟሪዎች ተደብቀውና ተሸሽገው የሚሸጡ ዋጋቸውም ውድ የሆኑ የእነ ኤርሚያስ ለገሰ እና ነገደ ጎበዜ መፃሕፍትም አሉ።

 

የበርካታ ጋዜጦችና መፅሔቶች ሕልውና እያከተመ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞች ወደ መፅሃፍት ሕትመትና ስርጭት ውስጥ እየገቡ በመሆኑ አዲስ የሥነ-ፅሁፍ ዘውግ ኢትዮጵያ ውስጥ እየጎለመሰ መታየት ጀምሯል። ቀደም ሲል ጋዜጦች እና መፅሔቶች ላይ የምናያቸው ፖለቲካዊ እና በተለይ ያለውን ስርዓት በሰላ ሂስ የሚነቅፉ ፀሐፊያን የኢትዮጵያ የመፅሐፍት ህትመት ሂደት ውስጥ ተቀላቅለዋል።

 

ፖለቲካዊ ሥነ-ፅሁፍ በተለይ በውስጡ ተጨባጭ የሆኑ ነገሮችን ከመያዙ አንፃር እና ልዩ ልዩ ትርጓሜዎች ተሰጥቶት ስለሚፃፍ የአንባቢን ቀልብ የመያዝ ችሎታው ትልቅ ነው። ምንም አይነት የፖለቲካ ፓርቲ ባልነበረበት ዘመን እነ ፍቅር እስከ መቃብር፣ አደፍርስ እና ከአድማስ ባሻገር የመሳሰሉ ረጃጅም ልቦለዶች በመጀመሪያ የተወደዱት በውስጣቸው ፖለቲካዊ ትርጓሜ ያሏቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ስለያዙ ነው በሚል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ስለ አበባ ደማቅነት፣ ፍካት፣ ስለውቢቷ ወጣት ደም ግባት፣ ተክለ ሰውነት፣ ስለ ደኑ፣ ስለመልክአምድሩ ወዘተ ውበት መፃፍ ብዙ አዋጪ እየሆነ እንዳልመጣ የመፅሐፍት ገበያው ያሳያል። ከዚያ ይልቅ የፖለቲካው ትኩሳት ያጋላቸውና ያሞቃቸው መፃሕፍት መድረኩን እየተቆጣጠሩት ነው።

 

ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደ ቀደሙት ዓመታት በሰፊው ገበያ ላይ ባለመኖራቸውና ህልውናቸውም በእጅጉ በመዳከሙ የተነሳ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ሌላ ምዕራፍ እየያዘ በመምጣት ላይ ነው። የተመሰገን ደሳለኝን፣ የአለማየሁ ገላጋይን፣ የሙሉነህ አያሌውን እና የኃይለመስቀል በሸዋም የለህን፣ የአንዷለም አራጌን፣ የርዕዮት ዓለሙን እና የሌሎችንም በርካታ የወቅቱ ፖለቲካዊ መፃህፍትን ስናገላብጥ የምሬት ሥነ-ፅሁፎች በስፋት የታዩበት ዘመነ እየሆነ መጥቷል።

 

በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮቱ በ1966 ዓ.ም ከፈነዳ በኋላ ላለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥነ -ፅሁፍ ምን ይመስላል በሚለው ርዕሰ ጉዳይ መነጋገር ይገባል። ከዘመነ ኢሕአፓ በኋላ በርካታ ፀሐፊያን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ፖለቲካ እና እልቂት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር የፃፉት። በዚህም ሳቢያ መፅሐፍቶቻቸውን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አላነበበም ነበር። አሁን ከቅርብ ጊዜ በኋላ የኢሕአፓን ዘመን ጨምሮ እኛ እስካለንበት ይህ ዘመን ድረስ ስርዓት ተኮር፣ መንግስት ተኮር፣ ፓርቲ ተኮር፣ ትግል ተኮር ወዘተ መፃሕፍት እየመጡ ነው። እስኪ ሳምንትም በአዲሱ የሥነ -ፅሁፍ ዘውጋቸው ላይ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ተቀጣጥረን ብንለያይስ? መልካም ሳምንት!። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11766 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us