ንባብ ለሕይወት

Wednesday, 15 July 2015 13:31

 

 

በጥበቡ በለጠ

ሕይወትን በሁለት ነገሮች ማቆየት እንችላለን። አንድም በስጋዊ ለሆዳችን ጥያቄ መልስ እየሰጠነው። ሁለትም ለመንፈሣችን ለህሊናችን ረቂቅ ነገር እየሰጠነው። የሰው ልጅ ሰው መሆኑም የሚለየው ስጋዊ እና መንፈሳዊ ነገሮች ውስጡ ስላሉ ነው። እንስሳት መንፈሳዊ ነገር የላቸውም። ሰውና እንስሳት በስጋ ሲገናኙ በህሊና ግን ይለያያሉ። ሰው ህሊና አለው። ዛሬ የምናወጋውም ይህን ሰው የመሆኑን ምስጢር የሚያበለፅጉትን የሚያሳድጉትን ረቂቃን ጉዳዮችን ነው። እነርሱም መፃሕፍት ናቸው። ሰው የመባልን፣ ሰው የመሆንን ልዩ ፀጋ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን የህሊና ምግቦችን ትንሽ እስኪ ቀመስመስ እያደረግናቸው ብንቆይስ።

ከፊታችን ሐምሌ 23 እስከ 26 2007 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኤግዝቢሽን ማዕከል “ንባብ ለሕይወት” በሚል ታላቅ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ይካሔዳል። በዚህ ዝግጅት ላይ ከ100 በላይ በሀገሪቱ ያሉ የመፃህፍትን አከፋፋዮችና አሣታሚዎች ይሣተፋሉ። ከዘጠና ሺ በላይ በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ መፃሕፍት ለእይታና ለሽያጭ ይቀርባሉ። የመፃሕፍት ምረቃ እና ውይይቶችም ይደረጋሉ። የዓመቱ የንባብ አምባሳደሮችም ይፋ ይደረጋሉ። ሌሎችም በርካታ ዝግጅቶች በኤግዚቢሽኑ ላይ መካተታቸውን የፕሮጀክቱ ኃላፊ የሆነው ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያው ቢንያም ከበደ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጿል። አዘጋጁ ደግሞ ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ ነው።

 

ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ እመርታ ላይ ለሚገኘው የፊልም እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ምክንያቱም ላለፉት 15 ዓመታት ብቻ እጅግ በርካታ የፊልም ኤዲተሮችን፣ የካሜራ ባለሙያዎችን፣ ዳይሬክተሮችን፣ የድምጽና የመብራት ባለሙያዎችን እና ከፊልም ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሙያዎችን እያስተማረ በማስመረቁ የተመረቁትም ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን የፊልም ስራ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረሣቸውን በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው። በኢትዮጵያ ፊልም ስራ ውስጥ ውጤታማ የሆነው ማስተር፣ አሁን ደግሞ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ አዘጋጅቶ አንባቢ ትውልድ እንዲስፋፋ ለማድረግ “ንባብ ለሕይወት” ብሎ ቆርጦ ተነስቷል። በነገራችን ላይ፣ ማስተር ፊልምና ከሚኒኬሽንስ ዛሬ በሀገራችን በስፋት የምናየውን የኤግዚቢሽን ሥራ ፈር በመቅደድ እና በማስተዋወቅም ረገድ ድርሻው ግዙፍ ነው። ማስተር ወደ መፃህፍት አውደ-ርዕይ እና ወደ ንባብ ጉዳዮች ከገባ እንደ ቀደሙት ስራዎቹና ተግባሮቹ ይህንንም ጉዳይ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

 

በሐገራችን ኢትዮጵያ የንባብ ጉዳይ ተደጋግሞ እየተወተወተ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ንባብ የሰውን ልጅ ከእንስሳ ባህሪ ለየት አድርጎት ስብእናው የላቀ እንዲሆን የማድረግ ኃይል ስላለው ነው። ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ “ንባብ ለሕይወት” ሲልም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። ቀደም ሲል እንደገለፅኩት መብላትና መጠጣትን ሰውም ሆነ ሌሎች እንስሳትም ለመኖር ሲሉ ይጠቀሙበታል። ንባብ ደግሞ የሰውነትን ልዕልና፣ የአስተሳሰብን ከፍታ፣ የማስተዋልን ረቂቅ ኃይል፣ የትህትናን ገፀ-በረከት፣ የፍቅን ችሮታ፣ የአስተዳደርን ብልሃት ወዘተ ስለሚያጎናፅፍ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠው ብቸኛው ሀብት ነው። ይህ ሃብት ተከማችቶ የሚገኘው መፃህፍት ውስጥ ነው።

 

መፃሕፍት ዝም ብለው ጠንካራ ልባድ እና የውስጥ ገፆች ብቻ ያላቸው አይደሉም። ውስጣቸው ሰው አለ፤ ሕዝብ አለ፤ ታሪክ አለ፤ የሰው ልጅ ውጣ ውረድ አለ፤ አለምን የገዙ፣ በአስተሳሰብ ሊቅነታቸው አርአያነታቸውን የምንከተላቸው ፈላስፎች፣ ተመራማሪዎች፣ የህይወት መንገድ እያመቻቹልን እነሆ በዚህ ተጓዙ፣ ያኛው ብዙ አሜኬላና እንቅፋት አለው እያሉ የዚህችን ዓለም ምስጢራት ይገላልፁልናል። መፃሕፍት ውስጥ ዋዛ እና ለዛ አለ። በዋዛና በለዛ ቋንቋ ተቀነባብሮ የሕይወትን አቅጣጫ እንድንፈትሽ እንድናውቅ፣ እንድንመራመር፣ እንድንጠይቅ፣ እንድንመልስ፣ እንድናብራራ ያደርጉናል። ለሰውልጅ በተሰጠው መንበር ላይ ቁጭ ብለን ሰው የመሆናችንን፣ ሰው የመባላችንን ልዩ ገፀ-በረከት የሚያጎናፅፉን ሀብቶቻችን ናቸው።

 

መፃሕፍት ሲከፋን የሚያፅናኑን፣ ስንሳሳት የሚያርሙን፣ ትዕቢትን፣ ጉራን፣ ጀብደኝነትን ከውስጣችን አስወግደው የመልካምነትን ስብዕና የሚገነቡልን የሊቃውንቶች ስጦታ ናቸው። መፃህፍት በመደርደሪያ ላይ ቆመው ስናያቸው ነብስ የሌላቸው የሚመስሉን የዋሃን እንኖራለን። ይልቅስ የሕይወት ምስጢራት፣ ያልተፈቱ የሚመስሉንን የሕይወት ጉዞዎች፣ አቅጣጫቸው የማይታወቅ የሚመስሉን የሕይወት ጎዳናዎች በሙሉ በመፃህፍት ውስጥ ከነ መፍትሔያቸው ቁጭ ብለዋል። ስለ መፃሕፍት ርዕሰ ጉዳይ ከፃፉልን የሀገራችን ደራሲያን መካከል አንዱ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ናቸው። ሻምበል አፈወርቅ ዛሬ በአፀደ ስጋ በዚህች ምድር ባይኖሩም በመፅሐፍቶቻቸው ግን ሕያው ናቸው። በሰው ልጅ ዘር ሁሉ ስማቸውን የሚያስጠሩላቸውን ከ17 በላይ መፃሕፍት አበርክተውልን ያለፉ ናቸው። እኚህ ሰው በ1972 ዓ.ም “የእውቀት አውራ ጎዳና” በሚል ርዕስ ስለ መፃሕፍት ጉዳይ ውብ የሆነ ፅሁፍ አበርክተውልናል። እንዲህ ይላሉ፡-

 

“ በመፃሕፍት ቤታችን ላይ ተደርድረው ለሰው ልጅ ዘር ውለታ የዋሉ. . . ትዝታቸው እንኳ እንደ በረከት የሚቆጠር ታላላቅ ሃሳቦችን ያመነጩና ዓላማዎችን የቀየሱ ታላላቅ ሰዎች ይጠብቁናል። . . . እነዚህ ሰዎች እውነትን ውበትን ፍቅርን ብርሃንን ነፃነትን እና ሥልጣንን ፈር ያስያዙ የሁሉም አገርና የሁሉም ዘመን መምህራን ናቸው። የነሱ ብርሃን ባይኖር ዓለም በጨለማነት ይገኝ ነበር. . . በአሁኑ ዘመን በየአገሩ በአስተዋይነት እና በአዋቂነት ላቅ ብለው በመታየታቸው ምሳሌነታቸው ይረዳል እየተባሉ የተደነቁ ሰዎች ሁሉ ለዚህ የበቁት እነዚህን ታላላቅ መፃሕፍት ደጋግመው ያነበቡ በመሆናቸው ብቻ ነው። እኛም ለነዚህ መፃሕፍት ማንበቢያ በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ብንሰዋ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምን ያህል ከፍተኛ ለውጥ እንደሚገጥመን መረዳት እንችላለን”

በማለት ወርቃማው ብዕረኛ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በ1972 ዓ.ም ፅፈዋል።

 

አለማንበብ በጨለማ ውስጥ እንደመጓዝ ይቆጠራል። ጨለማው የማየት፣ የመለየት፣ የመወሰን. . . ብቃታችንን ይገድብብናል። በራሳችን ምሉዕ እንዳንሆን ያደርገናል። ንባብ ግን ጨለማውን በረጋግዶ ወደ ኋላ እና ወደፊት ብዙ ሺ ዓመታት እንድናይ እና እንድንኖርበት ያደርጋል።

 

ዛሬ በሕይወት የሌሉትን አለቃ አያሌው ታምሩን ከአስር ዓመታት በፊት በተደጋጋሚ ቃለ-መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። አለቃ ገና የአራት ዓመት ህፃን እያሉ ሁለቱም ዓይኖቻቸው ታወሩባቸው። ለብዙዎቻችን ይህ አጋጣሚ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ በሕይወት ጎዳና ላይ ውጤታማ ሆነን እንዳንጓዝ ሳንካ ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን ትንሹ አለቃ አያሌው ምንም እንኳ የዓይን ብርሃኑን ቢያጣም በማንበቡ ብቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የዘላለም ብርሃን አብርቶ ያለፈ የስኬት ተምሳሌት ነው።

 

አለቃ አያሌው ታምሩ አይኖቻቸው ባያዩም በጣቶቻቸው ፊደልን ለይተው፣ ፊደል አውቀው፣ አንብበው፣ ተምረው በእውቀት አውራ ጎዳና ላይ መንሸረሸር ጀመሩ። መዝሙረ ዳዊትን፣ ዜማን፣ ፆመ ድጓን፣ ምዕራፍን፣ ድጓን፣ ቅኔን፣ አቋቋምን እየተማሩ የየትኛውም ዘመን ሰው ሆኑ። አለቃ መች በዚህ ብቻ አቆሙ፡ የአለምን ምስጢራት ሁሉ ከልዩ ልዩ መፃህፍትና ደራሲዎች የተጠራቀመ እውቀት ገበዩ። በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የሊቃውንቶች ሊቅ ተብለው “ሊቀ-ሊቃውንት” የተባለውን ማዕረግ አግኝተዋል። የቤተ-ክርስትያኒቱም የሊቃውንት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በርካታ መፃህፍትንም አሳተሙ። በዘመነ አፄ ኃይለስላሴም የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የግብረ-ገብ እና የሃይማኖት መምህርም ነበሩ። ታዲያ እኚህን ሰው ከታላላቅ ሰዎች መንበር ላይ ያስቀመጧቸው ንባብ እና መፃሕፍት ናቸው።

 

በማንበባቸው ብቻ የስኬት ሰገነት ላይ የደረሱት የየትኛውም ዘመን ሰዎችን ከሀገራችንም ሆነ ከባህር ማዶ እየጠቃቀስን ማውጋት እንችላለን። ግን ማንን አንስተን ማንን እንተዋለን? ብዙ ናቸው። የብዙዎች ማሳያ ይሆነን ዘንድ ግን በ1985 ዓ.ም በአፀደ ስጋ የተለየንን ጳውሎስ ኞኞን እናስታውስ። የቀለም ትምህርቱን በችግር ምክንያት አራተኛ ክፍል ላይ አቋረጠ። ግን ማንበቡን አላቋረጠም። በማንበቡ ብቻ የአራተኛ ክፍሉ ጳውሎስ ኞኞ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የስኬት ተምሳሌት ሆኖ ዝንት ዓለም የሚጠራ ሰው ሆኖ አልፏል። ምርጥ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ጥሩ ብንባል ጳውሎስ ኞኞ፣ መርጥ ታሪክ አዋቂ እና ፀሐፊ ጥሩ ብንባል ጳውሎስ ኞኞ፤ ትጉህ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ . . . እያልን ዘላለም እንድንጠራው ያደረገን የመፃህፍት ንባቡ ያጎናፀፈው ፀጋ ነው።

 

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ፣ እንደ ግለሰብ ራሳችንን እስኪ ዞር ብለን እንየው? በቤታችን ምን ያህል መፃሕፍቶች አሉን? እኛስ በቀን ምን ያህል እናነባለን? ለወለድናቸው የአብራካችን ክፋዮችስ ንባብን አውርሰናል ወይ? እነዚህን ጥያቄዎች በእዝነ ልቦናችን እንደያዝን እስኪ ወደ ሌላም ምዕራፍ እንጓዝ።

 

ኢትዮጵያ የተሳፈረችበት የታሪክ መርከብ ጉዞው ላይ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ። መርከቧ ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊነት አሉ። እነዚህ ሕዝቦች በጉዟቸው ወቅት የሚወሱላቸው አያሌ ታሪኮች አሉ። እርስ በርሳቸው በተከባበሩ እና በተዋደዱ ጊዜ እንደ አክሱም ዘመን ስልጣኔ፣ ለአለም አሳይተዋል። እንደ ትንግርትና እንደ ብርቅዬነት እስከ አሁን ድረስ ምስጢራቸው ያልታወቁትን የቅዱስ ላሊበላን 11 ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናትም አንፀዋል። በጎንደር ዘመን ላይ በኪነ-ሕንፃውም ሆነ በሥነ-ጽሁፍ እጅግ ዘምነው እንደ ብርቅም ታይተዋል። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የተሳፈሩበት የታሪክ መርከብ ወጀብ ተነስቶ ከወዲያ ወዲህ ሲያጋጫት ደግሞ፣ እንኩትኩት ብለው በድህነቱም በስልጣኔውም የአለም ጭራ ሆነው ይታያሉ። የመርክቢቱ ጉዞ እንዳይደናቀፍ እውቀትና ንባብ የግድ መምጣት አለባቸው። የኢትዮጵያን የታሪክ መርከብ ወደ ኋላ የሚያስቀረው ተሳፋሪዎቿ አለማንበባቸው ነው። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን በሌላ የመርከብ ተጓዦች የተበለጡትም ባለማንበባቸው ነው። እናም የኢትዮጵያ መርከብ ለሕይወቷ ለሕልውናዋ ንባብ ያስፈልጋታል ብዬ በፅኑ አምናለሁ። ጋዜጠኛውና የማስታወቂያ ባለሙያው ታታሪው ቢንያም ከበደም የዚህችን መርከብ ጉዞ መንገራገጭ እንዳያሰናክለው “ንባብ ለሕይወት” ብሎ ትልቅ አላማ ሰንቆ መነሳቱም ለዚሁ ነው።

 

ኢትዮጵያ የተጓዘችበትን የታሪክ ጉዞ መለስ ብለን ስንመለከተው 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የስልጣኔ ሾተላይ እንዳጋጠማት እናስባለን። በዚህ ወቅት “ዘመነ መሳፍንት” የተሰኘ አገዛዝ ብቅ አለ። ትንንሽ ንጉሶች በየአካባቢው ነገሱ። ኢትዮጵያ ተከፋፈለች። ማዕከላዊ መንግስት ጠፋ። ይህ ዘመን የኢትዮጵያ ጨለማው ወቅት ነበር። የተፃፉ መፃህፍትን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የእልቂትና የጦርነት የግድያ ታሪኮች ነበሩ። በወቅቱ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ልክ በዚያን ወቅት አውሮፓ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን /ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን/ ተሸጋገረች። ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ከፋፍህ ግዛ የዘመነ አፄዎች ታሪክ ውስጥ ታጎረች። ይህ የጨለማ ወቅት ከ80 ዓመታት በላይ ቆየ። ከዚያም ካሳ ኃይሉ /አፄ ቴዎድሮስ/ ተነስቶ ጠራርጎ እስከሚያጠፋቸው ድረስ አያሌ ጥፋቶችን ፈፅመዋል።

 

አፄ ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንትን አስተዳደር አስወግደው አንዲት ኢትዮጵያን መሠረቱ። ከዚያም በተለይ መቅደላ አምባ ላይ ትልቅ የቤተ-መዛግብትና የመፃህፍት የቅርሶች ማኖርያ መዘክር ሰሩ። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ታላላቅ የፅሁፍ ቅርሶችን ሰብስበው በዚህ ቤተ-መዘክር ውስጥ ማኖር ጀመሩ። ይሁን እንጂ የቴዎድሮስ ጉዞም እንቅፋት በዛበት። የብሪታኒያ ወታደሮች ብዙ ሺ የህንድ ወታደሮችን አስከትለው ወደ መቅደላ አምባ ዘመቱ። ቴዎድሮስም ራሳቸውን ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ሰው። ነገር ግን እንግሊዞች በመቅደላ አምባ ላይ ተከማችተው ያገኟቸውን የኢትዮጵያ ብርቅዬና ድንቅዬ የፅሁፍ ሀብቶች በብዙ ዝሆኖችና ፈረሶች ጭነው ወደ ለንደን አቀኑ። ዛሬ የለንደን ሙዚየምን እና የአውሮፓ ሙዚየሞችን ያጨናነቁት የብራና ፅሁፎች ከመቅደላ የተዘረፉ ናቸው። እንግሊዝ ሀገር የሚገኘው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ለንደን ሙዚየም ውስጥ የሚገኙት ብራናዎች በገንዘብ ሲተመኑ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ ያወጣሉ ሲል ጽፏል።

 

ኢትዮጵያ የፅሁፍና የታሪክ ሀብታም ነች። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ሀብቷ ታሪኳ ነው። ይህን ታሪኳን በአግባቡ የምንሰበስበው ቅርሶቿን፣ መፃህፍቶቿን ስናውቅ እና ስንመረምር ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /UNESCO/ ከኢትዮጵያ ምድር ብቻ 12 የሥነ- ፅሁፍ ሀብቶችን የዓለም ታላላቅ ቅርሶች ብሎ መዝግቧቸዋል። ይህ ቁጥር በጣም ብዙ ነው። የሚሳየንም ነገር ቢኖር ሀገሪቱ የሥነ-ፅሁፍ ምድር እነደሆነች ነው። ለምሳሌ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው “መፅሐፈ ሔኖክ” በዓለም ላይ የጠፋ ምዕራፍ ነበር። ይህ መፅሐፈ ሔኖክ በውስጡ ሄኖክ የአዳም የልጅ ልጅ ከሆኑት የመፅሐፍ ቅዱስ አበው አንዱ ሲሆን፣ መፅሐፉም ከተፃፈ ዘመን ጀምሮ እስከ አለም ፍፃሜ በዚህ ዓለም ላይ ስለሚሆነው ማናቸውም ነገር የሚናገር የትንቢት መፅሐፍ ነው። ምድር ላይ ጠፋ ተባለ። ግን ኢትዮጵያዊያን አባቶች በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ ተርጉመውት አስቀምጠውታል። ጀምስ ብሩስ የተባለ የስኮትላንድ አገር አሳሽ እ.ኤ.አ. የካቲት 14 ቀን 1770 ዓ.ም ወደ ጎንደር መጥቶ ከእቴጌ ምንትዋብ ጋር ተዋውቆ፣ በቤተ-መንግስታቸው ተቀምጦ ልጃቸውንም አግብቶ ሲኖር ቆይቶ ወደ ሀገሩ ሲሄድ መፅሐፈ ሔኖክን ሰርቆ አመለጠ። ዛሬ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው መፅሐፈ ሔኖክ ከኢትዮጵያ የተገኘ ነው። ጀምስ ብሩስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከሔደ በኋላ እ.ኤ.አ በ1790 ዓ.ም Travels to Discover the Source of the Nile በሚል ርዕስ ግዙፍ መፅሐፍ አሳትሟል።

 

የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ ብሎም እስራኤል የግዕዝን ቋንቋ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ውስጥ ያስተምራሉ። ካስተማሩም በኋላ ጥንታዊ የኢትዮጵያን ብራናዎች ከግዕዝ ወደ አማርኛ እያስተረጎሙ ታላቅ ጉዳዮችን ይቀስማሉ። እኛ ዘንድ ግን ብራናዎቻችንን የመተርጎም ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ቋንቋችን ራሱ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው። የእውቀት የሥነ-ፅሁፍ ሀብታሞች ሆነን ግን ገና አልነቃንም። ብልጦቹ አውሮፓውያን ከኛ ብዙ ነገር ቃርመዋል። ብራናዎቻችን ውስጥ የህክምና ጥበብ አለ፤ አስትሮሎጂ አለ፤ ስነ-ፅሁፍ አለ፤ ጂኦግራፊ አለ፤ የሂሳብ ቀመር አለ፤ ፍልስፍና አለ። የሌለ ነገር የለም። የፅሑፍ መሠረታችን ጥልቅ ነው። ጠንካራ ነው። እላዩ ላይ ትንሽ መገንባት ብንችል የት በደረስን!

 

ከሐምሌ 23 -26 ቀን 2007 ዓ.ም በኤግዚቪሽን ማዕከል የሚካሔደው የኢትዮጵያ የመፃሕፍትና የትምህርት ተቋማት አውደ-ርዕይ ስንቆጭበት የኖርንበትን የሥነ-ፅሁፍ ታሪካችንን ከሚያድሱልን ተግባራት መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ አሳታሚዎች፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ መፃህፍት አከፋፋዮች፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጀርመን የባህል ተቋም፣ የኢትዮጵያ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር፣ የብሪትሽ ካውንስል ሌሎችም የመንግስት አካላት ሁሉ ለዝግጅቱ ርብርብ እያደረጉ ነው። ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ብለው እነ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ኤቢ ሀም ኢንተር ፕራይዝም የመፃሕፍትን እና የንባብን ጉዳይ በመደገፍ ላይ ናቸው። ልዩ ልዩ የብዙሃን መገናኛዎችም የጉዳዩን ትልቅነት ተረድተው ሽፋን እየሰጡት ነው።

 

በዚሁ አውደ ርዕይ ላይ ለልጆችም ትልቅ ቦታ ተሰጥቷል። የንባብ ባህላቸው የሚገነባው ከዚሁ ከልጅነት እድሜ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ውይይቶችና አውደ ጥናቶችም ይቀርባሉ። ጋዜጠኛውና የማስታወቂያ ባለሙያው ቢኒያም ከበደ ይህን ትልቅ ጉዳይ በኃላፊነት ወስዶ አንባቢ ትውልድን ለማስፋፋትና ለመገንባት የሚደረገውን ትግል እዳር ለማድረስ መነሳቱ በበኩሌ አድናቆት አለኝ።

 

በመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ላይ መገኘት መሳተፍ መወያየት ከትልቁ የሕይወት ዘመን ስራዎቻችን መካከል አንዱ መሆን አለበት። ጉዳዩ መፃሕፍት ናቸውና። ውስጣቸው ብዙ ነገር አለ። ትውልድ፣ ሀገር፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ሀዘን፣ ደስታ፣ ስንቱ ተገልፆ ያልቃል? ተመግበን ከማንጨርሰው የዕውቀት ማዕድ መካከል መፃህፍት ዋናዎቹ ናቸው። ከማያልቀው የሰው ልጅ ስጦታ ጋር አብረን እንኑር።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12232 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us