የሐገር ፍቅር ቴአትር መስራች መኮንን ሀብተወልድ

Wednesday, 22 July 2015 13:42

በጥበቡ በለጠ

 

የሐገር ፍቅር ቴአትር ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም 80 ዓመቱን ደፈነ። የ80 ዓመት አዛውንት የሆነው ይህ ቴአትር ቤት እንዴት ተመሠረተ ብለን ስንጠይቅ አንድ ሰው ከፊታችን ብቅ ይላሉ። እኚህ ሰው መኮንን ሀብተወልድ ይባላሉ።

 

መኮንን ሀብተወልድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊ ጉዳዮች ታሪክ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነበር። ኢትዮጵያን ለማዘመን በተደረገው ርብርብ ውስጥ አሻራቸው ደማቅ ሆኖ የሚታይላቸው ሰው ነበሩ። እኚህ ሰው ስማቸው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ጋር ይጠቀስ እንጂ፣ ሰውዬውማ የሀገሪቱን ስልጣኔ እንደ ውጋገን ሆነው ብርሃን ያሳዩ እና ብዙ የደከሙ ናቸው። ዛሬ መኮንን ሀብተወልድን በጨረፍታ ላስታውሳቸው ወደድኩ።

 

የመኮንን አባት ሀብተወልድ ሀብቴነህ ይባላሉ። እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ሲሆኑ ሁለቱም የመንዝ እና ቡልጋ ተወላጆች ናቸው። በጋብቻቸው ወቅትም ስምንት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ መኮንን ሀብተወልድ ሁለተኛ ልጃቸው ናቸው። መኮንን ሀብተወልድ የተወለዱት ጥቅምት 19 ቀን 1886 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በ45 ኪ.ሜ በምትርቀው አድአ ከተማ ነበር። ይህ ማለት የዛሬ 121 ዓመት ነው።

 

የመኮንን አባት ሀብተወልድ የቤተ-ክህነት ሊቅ ነበሩ። በተለይ እንጦጦ ራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን ካገለገሉ እና በቤተ-ክርስትያኒቱም የተሰሩትን ታላላቅ ታሪካዊ ጉዳዮችን ካከናወኑ የድሮ አባቶች መካል አንዱ ነበሩ። ልጃቸው መኮንን ሀብተወልድም የእርሳቸው እግር ተከትሎ ቤተ-ክርስቲያኒቱን እንዲያገለግል ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው። መኮንን እድሜው ለትምህርት ሲደርስ አማርኛን፣ ፅህፈትን፣ ንባብን ተማረ። ከዚያም ዳዊት ደገመ። ለከፍተኛ ትምህርት ተብሎም ወደ ዝቋላ ወንበር ማርያም ተላከ። እዚያም ግዕዝን፣ ዜማን፣ ቅኔን፣ ድጓን፣ ፆመ ድጓን ተምሮ በ15 ዓመት እድሜው አጠናቀቀ።

 

ወዲያውም እንደ አባቱ ፍላጎት የእንጦጦ ራጉኤል ደብር አገልጋይ ዲያቆን ሆነ። በዚህ ወቅት አንድ ቀን አጤ ምኒልክ ይታመሙና ለጠበል ሕክምና ወደ ራጉኤል ይሄዳሉ። እዚያ ራጉኤል ካሉት ዲያቆናት መካከል መኮንን ሀብተወልድ ከአጎቱ ልጅ ጋር ከታከለ ወ/ሃዋርያት ጋር ሆኖ ዜማ ለማሰማት ይመረጣሉ። ምኒልክ በሚጠመቁበት ወቅት እነ መኮንን በሚያሰሙት ዜማ ይመሰጣሉ። ይደነቃሉ። በጣምም ወደዷቸው። ታዲያ በዚያን ወቅት እቴጌ ጣይቴ ለዲያቆናቱ ለመኮንን እና ለታከለ ሽልማት እንዲሰጧቸው ታሪካቸው ያወሳል።

 

ታዲ ምን ያደርጋል ከጊዜ በኋላ መኮንን ሀብተወልድ በፀና ይታመማሉ። በሐገር ባሕል ህክምና በፆም በፀሎቱም ታከሙ። አልሆን አለ። ሰዎች ተሰብስበው መከሩ። ይህ ልጅ አካባቢ ቢቀይር ይሻላል፤ አየሩ ትንሽ ቆላነት ያለው ቦታ ይሂድ ተብሎ ተወሰነ። ከዚያም ወደ አርሲ ቦኩ ተላኩ። እውነትም ተሻላቸው። ታዲያ በአርሲ ቆይታቸውም ከወ/ሮ በላይነሽ ቤዛ ጋር ትዳር መስርተው ሁለት ልጆችን ወለዱ። ልጆቻቸውም ጥላሁን እና ከበደ ይባሉ ነበር። ጥላሁን በዘመኑ ወረርሽኝ በነበረው በፈንጣጣ በሽታ ሞተ።

 

አርሲ ከሶስት ዓመታት በላይ ከቆዩ በኋላ መኮንን ቤተሰቦቹን ሊጠይቅ ወደ አድአ ይመጣል። በወቅቱ ወረርሽኝ ከፍቶ ቤተሰቦቹ እና የአካባቢው ሕዝብ በሽታ ላይ ነበር። እንደውም ከቤተሰቦቹ መካከል ሁለቱ ሞተው አገኛቸው። ስለ እነሱ ህልፈት እያለቀሰ ሳለ ማታ እራሱም በወረርሽኙ ተያዘ። ሕመም ጀመረው።ሊጠይቅ የመጣው መኮንን የአልጋ ቁራኛ ሆነ። በአጋጣሚ አባቱ ስላልታመሙ ጤነኛ ሰዎች ፈላልገው ልጃቸውን መኮንን በቃሬዛ ተሸክመው ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል አመጡት። ሆስፒታል ውስጥም ህክምና እየተከታተለ እያለ በበሽታው እንደማያገግም ታወቀ። ተስፋ ተቆረጠ። አባቱ ሀብተወልድ ልጃቸው ሆስፒታል ውስጥ ሞቶ አስክሬኑን ይዞ ከመሄድ በህይወት ይዘውት ሊሔዱ ሲሰናዱ አንድ መልዕክት ከዘኛቸው ከእማሆይ አጥሩ ዘባ ደረሳቸው።

የእማሆይ አጥሩ ዘባ መልዕክት ምንድንነው?

 

እማሆይ አጥሩ ዘባ ሕልም ታይቷቸዋል። መኮንን ሀብተወልድን በተመለከተ በህልማቸው ያዩትን ነገር ለአባት ለመምሬ ሀብተወልድ እንዲህ በማለት አቀረቡ፡-

“በሕልሜ የታመመውን ልጅህን ማማ ላይ ቆሞ ወፍ ሲያባርር አይቼው ስገረም፣ አንድ መልአክ የመሰለ ሰው በድንገት አጠገቤ መጥቶ፣ ስሚ! ይለኛል። ይህ የምታይው ልጅ ወደፊት የመንግሥት ሹም፣ የንጉስ ባለሟል፣ የንጉሥ ታማኝ ይሆናል። ሰዎች አይበላ፣ አያስበላ የሚል ስም ያወጡለታል። የዕድሜ ፀጋ ያገኛል። ግን ሕመም አይገድለውም. . .” ብሎኝ ከአጠገቤ ተሰወረ። ለሕልሜ ፍቺ አያስፈልገውም ግልጽ ነው። ይልቁንስ እኔ የምመክርህን ስማኝ! መኮንን እዚያው ሀኪሞቹ ዘንድ ይቆይ! ሲሻለው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበል አድርግ! ወደፊት የአሩሲውን ኑሮ ትቶ በዚያው በንጉሡ ከተማ ጎጆ ያብጅ! ለእኔ እንደሚታየኝ መኮንን ትልቅ ሰው ሆኖ ስምህን ያስጠራል።ግን እኔና አንተ እንደርስበትም፤ አናየውም” ብለው ይናገራሉ እማሆይ አጥሩዘባ። (የዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ገፅ 528)

እማሆይ አጥሩዘባ እንዳዩት ህልም ተስፋ የተቆረጠበት መኮንን ተሻለው። ከሞት አፋፍ ወደ ህይወት ተመለሰ።

 

አባቱ መምሬ ሀብተወልድ ልጃቸውን ወደ አርሲ ከመመለስ በእማሆይ አጥሩዘባ ህልም መሠረት እዚሁ አዲስ አበባ እንዲኖር ወሰኑ። በኋላ የጓደኛቸው ልጅ ወደ ሆነው አቶ በቀለ ደስታ ዘንድ ሔዱ። ልጃቸውን ለአቶ በቀለ በአደራ ሰጡት። በቀለም መኮንን የፍል ውሃ መግቢያ ትኬት ሻጭ አድርጎ አስቀጠረው። የመኮንን ስራ እና ህይወት አዲስ አበባ ላይ ተጀመረ።

 

መኮንን ከሌሊቱ አስር ሰዓት እስከ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያለእረፍት ሲሰራ ይቆያል። ከስድስት ሰዓት በኋላ ነፃ ነው። በዚህች በእረፍቱ ሰዓት ፈረንሳይኛ እና የሂሳብ ትምህርት እንዲማር ሰዎች መከሩት። ወደ አሊያንስ ፍራሲስ ሔዶ ተመዘገበ። ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ። ትምህርቱን ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ስራውን መቀየር ፈለገ።

 

የላጋር ጉምሩክ ለመቀጠር አመለከተ። የተማረበትን ሰነድ ለኃላፊው አቀረበ። ኃላፊውም ነገ የሂሳብ ሠራተኛ ሆነህ ስራ ጀምር አሉት። መኮንን ስለተሰጠው እድል አመስግኖ ነገር ግን ችሎታው ሳይመዘን፣ ሳይፈተን እንዴት መቀጠር ይችላል? መጀመሪያ ችሎታዬን ፈትኑኝ፤ ከዚያም ካለፍኩ ቅጠሩኝ ይላቸዋል። ኃላፊውም ጉዳዩ ገረማቸው። ይህ ሰው ነገረኛ ሳይሆን አይቀርም ብለው ጠረጠሩ። እንዴት ሰው ስራ ጠይቆ ግባ ሲባል ካልተፈተንኩ አልገባም ይላል? እያሉ ተደነቁ።

ኃላፊውም እሺ ትፈተናለህ ብለውት አንድ ግብጻዊ ረዳታቸውን ፈትነው ብለው ያዙታል። ግብፃዊውም ለፈተና መኮንን ያስቀምጠዋል። ከዚያም እንዲህ አለው?

 

-    እንግሊዝኛ ትችላለህ?

-    አልችልም። የምችለው ፈረንሳይኛ ነው።

-    እንግሊዝኛ ሳትችል እንዴት ልትቀጠር ትመጣለህ?

-    አንድ ሰው ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ፈረንሳይኛ ከቻለ በቂ ነው። እኔ ደግሞ የመጣሁት የሂሳብ ስራ ላይ ለመቀጠር እንጂ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ አይደለም። ከፈለክ ፈረንሳይኛውንም ልትፈትነኝ ትችላለህ።

-    እኔ እንግሊዝኛ ስለምችል ነው እዚህ የምሰራው ይለዋል ግብፃዊው።

-    መኮንንም ሲመልስ፣ አንተ ግብጻዊ ነህ። እንግሊዝኛ ሀገርህን በቅኝ ግዛት ስለያዙ የግዴታህን እንግሊዝኛ ማወቅ አለብህ። እኔ ነፃ አገር ነኝ። ስለዚህ ግዴታ የለብኝም። ደስ ያለኝን መማር አለብኝ። ይልቅ አንተ ፈረንሳይኛ ስለማታውቅ ፈረንሳይኛ መፈተን አልቻልክም። ስለዚህ ለአለቃህ ሔጄ ጉዳዩን አመለክታለሁ አለ።

 

መኮንን ሀብተወልድ እንዴት አይነት ሞገደኛ ሰው ሆነ። ግብፃዊው ፈርቶት ሂሳብ ፈተነው። መኮንንም ፈተናውን በሚገባ አለፈ። ጉምሩክ ተቀጠረ።

በጥቂት ጊዜ ውስጥ የጉምሩክን አሰራር ለመቀየር የተለያዩ ጥናቶችን እና አማራጮችን ማቅረብ ጀመረ። አስቸጋሪ ሆነው የቆዩ አሰራሮችን ሁሉ ወደ ዘመናዊነት ቀየረ። መኮንን በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በእድገት እድገት እየጨመረ ሄደ። የገቢዎች የሂሳብ ሹም ሆኖ ተሾመ። ታዲያ እርሱ ይህን ሁሉ እድገት እያገኘ ሲሄድ አባቱ መምሬ ሀብተወልድ ይህን ሳያዩ አረፉ። በህልማቸው ያዩት እማሆይ አጥሩ ዘባም አረፉ። ህልሙ እውን ሆነ።

 

በዚህ ወቅት መኮንን ሀብተወልድ የታናናሽ ወንድሞቹ ሕይወት አሳሰበው። እናም ሊያሳድጋቸው ወሰነ። በአባቱ ምትክ ሆኖ ወንድሞቹን ለወግ ለማዕረግ ሊያበቃ ተዘጋጀ። እነዚህ ሶስት ወንድሞቹ ራጉኤል ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የዲቁና ትምህርት ይማሩ ነበር። እነርሱም አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መክብብ ሀብተወልድ እና አካለወርቅ ሀብተወልድ ይባላሉ።

 

እነዚህ ሶስት ወንድሞቹን እቤቱ አመጣቸው። ከዚያም ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አስገባቸው። ከት/ቤት መልስ በአሊያንስ ፍራሴስ ፈረንሳይኛን እንዲማሩ ማድረግ ጀመረ። ማታ ማታ ደግሞ እሱ ለታናናሽ ወንድሞቹ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ምን እንደሆነች፣ ታሪኳ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ፤ ያለባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንደሌሎቹ ሀገራት አላሳድጋት እንዳለ፣ ስለዚህ እናንተ ታናናሽ ወንድሞቼ ተምራችሁ ይህችን አገራችሁን ማገልገል አለባችሁ እያለ ያስተምራቸዋል። ኢትዮጵያ ምን አይነት ለውጥ እና ሽግግር ማምጣት እንዳለባት ማታ ማታ ያስተምራቸዋል።

 

የመኮንን ሀብተወልድ ወንድሞች በትምህርታቸው የቀለም ቀንድ ሆኑ። ሶስቱም እሳት የላሱ ተማሪዎች ሆኑ። በ1911 ዓ.ም አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ (በኋላ አፄ ኃይለሥላሴ) ወደ ውጭ ሀገር ሔደው የሚማሩ ጎበዝ ተማሪዎችን ማሰባሰብ ጀመሩ። በዚያን ጊዜ 33 ተማሪዎች ተመረጡ። ከነዚህ ውስጥ የመኮንን ሶስቱም ወንድሞቹ ማለትም አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መክብብ ሀብተወልድና አካለወርቅ ሀብተወልድ ተመረጡ። ሶስቱ የሀብተወልድ ልጆች እየተባሉም መጠራት ጀመሩ።

እነዚህ ወደ ውጭ ሀገር ሔደው እንዲማሩ የተመረጡት ጎበዝ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው መቃወም ጀመሩ። እንዴት ወደ ውጪ ይሔዳሉ? ከሔዱ የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ይረሳሉ፤ ሌላ ሃይማኖት ይከተላሉ በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ። ራስ ተፈሪ የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ከወላጆች ተቃውሞ የተነሳ ቀኛዝማች ኃይሌ ኪዳነወልድ የተባሉ ወላጅ ሁለት ልጆቼ ሄደው የፈረንጅ ነገር ከሚማሩ ሁሉም ማለትም 33ቱም ተማሪዎች ይለቁ ብለው የሚሔዱብን የባቡር ሐዲድ ሊቆርጡ በሸፈቱ ጊዜ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘዋል። ግን በመጨረሻም እነዚህ 33 ወጣቶች በህዳር ወር 1919 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ውጭ ሀገር ሔዱ።

መኮንን ሀብተወልድ ሶስቱን ወንድሞቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ለትምሀርት ከላኩ በኋላም ሀገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። የሀገር ግዛት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊም ሆኑ። እነዚህ እያለ 1927 ዓ.ም ደረሰ። የጉድ ዘመን ነበር።

 

ፋሺስት ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በአፄ ምኒልክ ጦር ድል የተደረገችበትን የ40 ዓመት ቂም ቋጥራ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ልታዘምት ነው። ከፍተኛ ዝግጅትም እያደረገች ነው። ታዲያ ኢትዮጵያዊያኖች በሙሉ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ፣ ሀገራቸውን ከባዕድ ወረራ እንዲከላከሉ መኮንን ሀብተወልድ አንድ ማህበር አቋቋሙ። ይህ ማበር “የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበር” ይባላል።

 

ማህበሩ ዛሬ የሀገር ፍቅር ቴአትር የሚለውን ወልዷል። መኮንን ሀብተወልድ የሀገር ፍቅር ቴአትር ወላጅ ናቸው። ግንቦት 11 ቀን 1927 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበርን ሲመሰርቱ ዋና አላማቸው ኢትዮጵያን ከጠላት ወረራ መከላከል ነበር። ልዩ ልዩ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ከጠላት ወረራ መከላከል ነበር። ልዩ ልዩ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ማህበር ውስጥ እየተገኙ ለሕዝቡ ስለ ሀገር ምንነት ንግግር ያደርጉ ነበር። ከነዚህ ከተማሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል የመጀመሪያው የአጭር ልቦለድ ድርሰት ደራሲ ተመስገን ገብሬ አንዱ ነበር።

 

እነ መኮንን ሀብተወልድ በዚህ ማህበር አማካይነት ህዝቡ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አሰረፁ። ጦርነቱም አይቀሬ ሆነ። ኢትዮጵያም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በሆነው በፋሽስት ኢጣሊያ ተወረረች። እነ መኮንን ሀብተወልድ የቀሰቀሱትም ሕዝብ ወደ አርበኝነቱ ገባ።  ማዕከላዊ መንግሥቱ ፈረሰ። ጃንሆይም ተሰደዱ።

 

ጦርነቱ ቀጠለ። ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች የተዋረደውን አንድነታቸውን እንደገና አመጡት። ፋሽስቶችን ድል አድርገው መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የቡልጋ አርበኞች አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። በወሩ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በስደት ሲታገሉ የነበሩት አፄ ኃይለሥላሴ፣ መኮን ሀብተወልድ እና እነ ተመስገን ገብሬ፣ ዮፍታሔ ንጉሴ በጣም ብዙ ሆነው አዲስ አበባ ገቡ። አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቀሉ። ታሪካዊ ንግግርም አደረጉ።

 

እንደገና የፈራረሰችውን ኢትዮጵያን ወደ መገንባት ስራ ተገባ። መኮንን ሀብተወልድ ወደ ውጭ ሀገር ልከዋቸው የነበሩት ወንድሞቻቸውም ተምረው መጡ።

ከመኮንን ወንድሞች መካከል አክሊሉ ሀብተወልድ እጅግ የሚደነቅ አዋቂ እና የተግባር ሰው በመሆናቸው በበርካታ የኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጥ የቻሉ ናቸው። በመጨረሻም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስከመሆን ደረሱ። ታዲያ የዚህ ሁሉ ውጤት ጠንሳሹ መኮንን ሀብተወልድ ናቸው። አክሊሉ የሚባል የኢትዮጵያ “ጂኒየስ” ያፈሩ ናቸው።

 

ተበታትኖ የነበረው የሀገር ፍቅር ማህበርም እንደገና ተሰባስቦ ወደ ኪነ-ጥበባት ዘውግ ውስጥ ገባ። ልዩ ልዩ ቴአትሮች እየተሰሩ ስለ አለፈው የጦርነት ዘመን እና ፍዳ፣ ስለ እማማ ኢትዮጵያ ብሎም ስለ ሌሎች ጉዳዮች ጥበባዊ ስራዎችን ማቅረብ ጀመረ። የዛሬው ሀገር ፍቅር ቴአትር ኢትዮጵያዊነት ከውስጣቸው ሲንፎለፎል የነበሩ ሀገር ወዳዶች ያቋቋሙት ቤት ነው። ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም

 

ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የስልጣን ሾተላይ አለባት የሚል አባባል ነበረው። እናም በታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ እና ወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ በጠነሰሱት መፈንቅለ መንግሥት አልተባበር ካሏቸው ሰዎች መካከል መኮንን ሀብተወልድንም ገደሏቸው። ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ሲዋትቱ የነበሩት መኮንን ሀብተወልድ አለፉ።

 

ሌላ አሳዛኝ ነገር ደግሞ መጣ። 1966 ዓ.ም አብዮት ፈነዳ ተብሎ የመኮንን ሀብተወልድ ወንድም ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ 60 ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆችን ደርግ በአንዲት ሌሊት ፈጅቷቸው አደረ። የስልጣኔ እና የዲሞክራሲ ሾተላይ ማለት ይሄ ነው።

 

ያለፈው ብዙ ነገር ያሳዝናል። ግን የ80 ዓመቱ አዛውንት፣ የሀገር ፍቅር ቴአትር ያለፈውን ዘመን ሁሉ እንዴት አድርጎ ያሳየን ይሆን? ለመሆኑ የ80 ዓመት ልደቱንስ ያከብራል ወይ? የመኮንን ሀብተወልድ አስተዋፅኦ እና ግዙፍ ታሪክ በሀገር ፍቅር ውስጥ እንዴት ሊዘከር፣ ሊታሰብ ይችላል? ሀገር ፍቅር የትልቅ ታሪክ ቤት መገለጫ ስለሆነ ትልልቅ ዝግጅቶች ይጠበቁበታል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
11697 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us