በርካታ መጽሐፍት ሊመረቁ ነው

Wednesday, 29 July 2015 17:34

በጥበቡ በለጠ

 

 

ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደውና መጠሪያውን “ንባብ ለሕይወት” ያለው የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ላይ በበርካታ ደራሲያን የተደረሱ መጽሐፍት ለምርቃት እንደሚበቁ ተገለፀ።

ከእነዚህ መጽሐፍት መካከልም አብዛኛዎቹ ገና ለገበያ ያልቀረቡና አዳዲስ ናቸው። በደራሲና በተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ ከልሌ የተተረጐመው የታዋቂው ደራሲ የጀምስ ሬድ ፊልድ መጽሐፍም ከሚመረቁት ውስጥ አንዱ ነው። ጀምስ ሬድ ፊልድ The Celectine Prophecy (An Adventure) በማለት የደረሰውን አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ (የሰማየ-ሰማያት ትንቢት) ጀብዱ” በማለት ተርጉሞታል።

ይኸው መጽሐፍ በሰላሳ ሀገሮች ውስጥ፣ ከስምንት ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የተሸጠ ሲሆን፣ በዓለም ውስጥ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት፣ በወቅቱ በአሜሪካ ውስጥ፣ ጠንካራ የማስታወቂያ ሽፋን ከነበራቸው መጽሐፍት ሁሉ የበለጠ መሸጡም ይነገርለታል።

ይህን በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ የተዘጋጀውን መጽሐፍ የአርትኦት ስራውን የሰራው ደራሲ አበረ አዳሙ መሆኑም ታውቋል። መጽሐፉ 284 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ አፈወርቅ የጤናው ሁኔታ እንደ ቀድሞው ጤነኛ ባልሆነበት እና ከህመምና ከህክምና ጋር እየታገለ ጽፎ የጨረሰው የትግል ውጤቱ ነው። ይህን መጽሐፍ ወደ አማርኛ እንዲተረጉመው የሰጠውም ገጣሚና ደራሲ ስንቅነህ እሸቱ መሆኑንም አፈወርቅ ገልጿል። አፈወርቅ በቀለ ከዚህ በፊት “የደም ጐርፍ”፣ “የአሁንነት ኃይል”፣ “የአምላክ ፈዋሽነት ኃይል” እና ሌሎችንም መፃሕፍትን እና መጣጥፎችን ከ1950ዎቹ ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ ያለ አንጋፋ ደራሲ ነው።

ሌላው በዚሁ የመጽሐፍት አውደ-ርዕይ ላይ ለምረቃ ከሚበቁት መጽሐፍት ውስጥ በደራሲ አብነት ስሜ የተዘጋጁት ሁለት መፃሕፍት ይገኙበታል። መጽሐፍቶቹ አንደኛው “የቋንቋ መሰረታዊያን” የተሰኘ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “ሳይኪ እና ኪዩፒድ” ይሰኛል።

በደራሲ አብነት ስሜ የተዘጋጀው “የቋንቋ መሰረታዊያን” የተሰኘው መጽሐፍ በውስጡም የቋንቋን ልዩ ልዩ ብያኔዎች፣ የተግባቦት መዋቅርን፣ የእንስሳት ተግባቦትን፣ የቋንቋን ንድፋዊ ገፅታዎችን፣ የቋንቋ ጥንተ አመጣጥ መላምቶችን፣ ስለ አፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ሁለተኛ ቋንቋን መማርና መልመድን በተመለከተ፣ የቋንቋን ተግባራት፣ ቋንቋና ማኅበረሰብ እና ሥርዓት ጽሕፈትን እንዲሁም በሌሎችም ሰፋፊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር አድርጐ ያዘጋጀው መጽሐፉ ነው። ይህ የአብነት ስሜ መጽሐፍ በቋንቋ እና በባሕል ላይ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንደ መምሪያ የሚያገለግል መሆኑንም ለማየት ችለናል።

በቀደመው ዘመን የቋንቋ ትምህርት በቤተ-ክህነት ውስጥ ብቻ ተገድቦ ለብዙ ዘመናት ከቆየ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት ወደ ሀገራችን ሲገባ ከዓለም ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ጋር ተቀናጅቶ መሰጠት ከጀመረ ብዙ እድሜ ባያስቆጥርም በአሁኑ ወቅት ግን ትምህርቱ በመስፋፋት ላይ ይገኛል።

በ1944 ዓ.ም ተክለማርያም ፋንታዬ፣ ሆህተ ጥበብ ዘስነ ጽሁፍ፣ በሚል ርዕስ የቋንቋ መማርያ አሳትሟል። በ1947 ዓ.ም ታዋቂው ደራሲ በእምነት ገብረ አምላክ፣ “የአንድ ቋንቋ እድገት - አማርኛ እንዴት እንደተስፋፋ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሟል። ከእርሱ በፊትም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ቋንቋን በተመለከተ ጽፈዋል። በ1948 ደግሞ ብላታ መርስኤ ሐዘን ወልደቂርቆስ የአማርኛ ስዋሰው በሚል ርዕስ አሳትመዋል።

ከዚያም በኋላ ዘመናዮቹ የቋንቋ ምሁራን እንደ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም፣ ዶ/ር ጌታሁን አማረ እና ዶ/ር ግርማ አውግቸውን የመሳሰሉ አያሌ ጠቢባን ቋንቋ ላይ እየፃፉ እየተመራመሩ ይገኛሉ። የአብነት ስሜ የቋንቋ መሰረታዊያን መጽሐፍም በሀገሪቱ ውስጥ በእውቀት ላይ በተመሠረተ መልኩ የሚካሄዱትን የቋንቋ ጥናትና ምርምሮች የበለጠ ከፍ እንደሚያደርገው ይታወቃል። ኢትዮጵያ የአያሌ ቋንቋዎች መገኛ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ጥናቶች ስሜታዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ሳያድርባቸው በእውቀት ላይ ተመስርቶ ብቻ እንዲተነተኑ እንደ አብነት ስሜ አይነት የቋንቋ ጥናት መጽሐፍት በጣም አስፈላጊ መሆናቸው ይነገራል። ይህ መጽሐፍም በዚሁ ከሐምሌ 23 እስከ 26 በሚካሄድው የመፃሕፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ ሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓ.ም በ11 ሰዓት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይመረቃል።

ሁለተኛ የአብነት ስሜ መጽሐፍ ለልጆች ያዘጋጀው ዳጐስ ያለው የተረቶችና የእንቆቅልሾች መጽሐፍ ነው። ርዕሱ ሳይኪ እና ኪዩፒድ ይሰኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተረቶች ደራሲው አብነት ስሜ Most Beloved Stories ከተሰኘ መጽሐፍ የተረጐማቸው ሲሆን፤ የመጽሐፉ ተረቶችም የተሰበሰቡት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ወላጆች በ“ተረት ምሽት” ላይ ከተረኳቸው ውስጥ በጣም ተወዳጅ የሆኑትን መርጧቸው ነው። “ሳይኪ እና ኪዩፒድ” የተሰኘው ተረትም የግሪክ አፈ-ታሪክ መሆኑንም አብነት ስሜ ገልጿል። ይህ የአብነት መጽሐፍ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ 411 ገጾች ያሉት ነው። ለልጆች የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍም ሐምሌ 24 በ11 ሠዓት ይመረቃል። አብነት ስሜ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኮከብ እና ፍካሬ ኢትዮጵያ የተሰኙ ሁለት ተወዳጅ መጽሐፍትን ያሳተመ ደራሲ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በቋንቋ የዶክትሬት ድግሪውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ዕጩ ተመራቂ ነው።

ከዚሁ ከልጆች መጽሐፍት ጋር ተያይዞ ሌሎች ሁለት መጽሐፍትም በዚሁ ኤግዚቢሽን ላይ ይመረቃሉ። እነዚህ ሁለት መጽሐፍትን ያዘጋጁት ሩሲያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ንጉሴ ካሳዬ ናቸው። እርሳቸውም የቋንቋ እና የሥነ-ጽሁፍ ምሁር ሲሆኑ፤ ለኢትዮጵያ ልጆች ያዘጋጇቸውን ሁለት መጽሐፍት ከሩሲያ ድረስ ይዘው በመምጣት ለልጆች በነፃ እንደሚሰጡ ታውቋል። የፕሮፌሰሩ መጽሐፍትም የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በአራት ሰዓት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይመረቃሉ። በዚሁ በመጽሐፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ ሌሎችም በርካታ መፃህፍት ከመመረቃቸውም በላይ የመፃሕፍት ገበያውም በእጅጉ እንደሚደራ ይጠበቃል። ገበያ ላይ የሌሉ፣ የጠፉ እና አዳዲስ መጽሐፍት በዝቅተኛ ዋጋ ለአንባቢያን እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።

በዚሁ ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን በኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደው ታላቅ የመጽሐፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ የዓመቱ ምርጥ የንባብ አምባሳደሮች እና በኢትዮጵያ የታሪክ ጽሁፍ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ አንድ ታላቅ ሰውም ይሸለማሉ። ከአንድ መቶ አስር በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበትን ይህን የመጽሐፍ ኤግዚቢሽን ያዘጋጀው ታዋቂው ጋዜጠኛ እና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነው ቢኒያም ከበደ ነው።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
9872 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us