የአስናቀች ወርቁ ዶክመንተሪ ፊልም ታየ

Wednesday, 29 July 2015 17:35

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ የክራር ሙዚቃ እና በቴአትር ትወና በእጅጉ የምትታወቀው በአስናቀች ወርቁ ህይወትና ስራ ላይ የሚያተኩረው “አስኒ” የተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልም ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአለ ሲኒማ አዳራሽ ውስጥ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ታይቷል።

ፊልሙን በዳይሬክተርነት የሰራችው ራቼል ስትሆን፣ ኤዲተሩ ደግሞ ኒውዮርክ ውስጥ የፊልም ጥበብ በማስተማር የሚታወቀው የማን ደምሴ ነው። በዚሁ በአስናቀች ወርቁ ፊልም ላይ አያሌ ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል። ለአስናቀች ወርቁ እማኝ ሆነው የቀረቡ ባለሙያዎች ከጥላሁን ገሠሠ ጀምሮ አብረዋት ሲሰሩ የነበሩ ከያኒያን እና ከያኒያት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይታያል። የድምጽ፣ የሙዚቃ፣ የመብራት እና የሌሎችም ሙያዊ ተግባር የፈፀሙ ሰዎችም ፊልሙ ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ በአስናቀች ወርቁ ሕይወትና ሥራዎች ላይ በሚያተኩረው ዶክመንተሪ ፊልም ጎላ ብለው ከታዩኝ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የተወሰኑትን መጠቃቀስ ፈለኩኝ። መጀመሪያ ከጠንካራ ጎኑ ልጀምር።

ፊልሙ በአንዲት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጣት እና አበርክታም ያለፈችው ውለታ ግዙፍ እንደሆነ በሚታወቅላት በአስናቀች ወርቁ ላይ መሠራቱ በራሱ ሊደነቅ የሚገባ ነው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝብና ለሐገሩ ውለታ አበርክተው ለሚያልፉ ሰዎች ምድር ላይ የሚቀመጥላቸው ቅርስ ስለማይሰራላቸው አስኒ ፊልም ትልቅ ምሳሌ ሆኖ ሌሎችንም ያስተምራል። ለምሳሌ ወጋየሁ ንጋቱን የሚያክል ተዋናይ እንኳን ፊልም ሊሰራለት ቀርቶ በአንድ ወቅት ሀውልቱ ሁሉ ፈራርሶ አይቼው ነበር።

ሁለተኛው ጠንካራ ጎን በፊልሙ ውስጥ በርካታ ጥንታዊ ፎቶ ግራፎች እና አልፎ አልፎም ቢሆን የቀድሞ ፊልሞች ከተለያዩ አርካይቮች ተሰባስበው ለፊልሙ ማጠናከሪያ ሆነው ቀርበዋል። ይህም የተለያዩ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የተደረገውን ጥረት ያሳያል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በእማኝነት የአስናቀች ወርቁን የሙያ ጓደኞች ጠይቆ በፊልሙ ውስጥ ማካተት በተወሰነ መልኩ ለፊልሙ ጥንካሬ ሰጥቶታል።

ሶስተኛው ጠንካራ ጎን የፊልሙ የድምፅ እና የብርሃን ጉዳይ ነው። የድምፅ ጥራቱ እና የተጠቀሙበት የብርሃን አሰጣጥ ታስቦበት መሰራቱን ያሳያል። በፊልሙ ውስጥ የሚታየው የአርትአት (editing) ስራም የተዋጣለት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ስለ ጥንካሬው ይህን ያህል ካልኩኝ፣ ፊልሙን በምመለከትበት ወቅት በግሌ የታዩኝን ደካማ ጎኖች ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ።

በዚሁ “አስኒ” በሚለው ዶክመንተሪ ፊልም ውስጥ ካየኋቸው ደካማ ጎኖች እና ምናልባትም መስተካከል የሚችሉ ናቸው የምላቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የፊልሙ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ አስናቀች ወርቁ ሆና ሳለ አንዳንድ ቦታ ፊልሙ ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ጭልጥ ብሎ ይገባል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን የአዝማሪነት ጉዳይ ነው። “በቀደመው ዘመን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች “አዝማሪ” እየተባሉ ክብር አይሰጣቸውም፤ አስናቀች ወርቁ ደግሞ ያንን አባባል ሰባብራ ነው የወጣችው” ለማለት ተፈልጎ ስለ አዝማሪነት የሚተነትነው ነገር አሰልቺ አድርጎታል። ስለ አስናቀች ወርቁ የሚነገረውን ጉዳይ አንዛዝቶታል። አዝማሪነት ራሱን የቻለ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ስለ አዝማሪነት የሚሰጠውም ትንታኔ በራሱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነበር። የአንዳንዱ ሰው ትንታኔም በስህተት የተሞላ ነበር። ስለዚህ ይህ ስለ አዝማሪነት ፊልሙ ውስጥ የገባው ክፍል ማጠር እና መስተካከል የሚችል ሆኖ ታይቶኛል። የአስናቀች ወርቁ ልጅ ት/ቤት ያዝማሪ ልጅ ይሉኛል ትላለች። ስንት ዓመተ-ምህረት? በእሷ ዘመን እንዲህ አይነት ስድብ ነበር?

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሌሎችም መቆረጥ እና መውጣት ያሉባቸው ጉዳዮች ያሉ ይመስለኛል። ለምሳሌ እውቁ የክራር ድምጻዊ ስለሺ ደምሴ /ጋሼ አበራ ሞላ/ ስለ ክራር አመጣጥ የሚተርከው የራሱ ሃሳብ እና እምነት አለ። ክራር ጥንታዊያን ግብፆችና አማልክቶቻቸው ወደ አባይ ሸለቆ መጥተው፣ ጥጥ ዘርተው፣ አብቅለው ከዚያም ጥጡን በደጋን ሲያዳውሩ፣ ከደጋኑ አሰራር ድምፅ ወጣ፣ ያንን ድምፅ ወደ ክራር ለወጡት እያለ የሚተርከው ጉዳይ ከአስናቀች ወርቁ ታሪክ ጋር ግንኙነት የለውም። ይህ ተቆርጦ ቢወጣ ፊልሙን አይጐዳውም።

ይልቅስ በነዚህ ምትክ ፊልሙ ያጎደላቸውን ነገሮች መሙላት የሚገባ ይመስለኛል።ለምሳሌ አስናቀች ወርቁ በአንድ ወቅት በድምፃዊነቷ እና በተዋናይነቷ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ከቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት እጅ ተሸልማለች። ይህ ታሪክ ፊልሙ ውስጥ የለም። ቢኖር የእርሷን ትልቅነት ከፍ ያደርገው ነበር።ከዚህ ሌላም የዛሬ 12 ዓመታት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ የተሰኘው የባህል ማዕከል “የአስናቀች ወርቁ የሙዚቃ ቀን” በማለት ለድምፃዊቷ ስራ እና የጥበብ አበርክቶ እውቅና በመስጠት ትልቅ ክብረ-በዓል አዘጋጅቶላት ነበር። እነዚህ ሁለት ነገሮች በፊልሙ ውስጥ ቢካተቱ የአስናቀችን ፊልም ከፍታውን ይጨምሩት ነበር።

ሌላው የፊልሙ ችግር ለሕዝብ እይታ ለመቅረብ ያለበት ውስብስብ ችግር ነው። ይህ የአስናቀች ወርቁን ህይወትና ታሪክ የያዘው ፊልም በቴሌቭዥንም ሆነ በፊልም ቤት ለመታየት የኮፒ ራይት ጉዳይ አንቆ የያዘው ችግር ሆኗል። የፊልሙ ባለቤት የሆነችው ራቼል አስኒን በፊልም የቀረፀቻት ስለወደደቻት ብቻ ነው። ስታያት ወደደቻት።ከዚያም ፊልም ሰራቻት። ታዲያ ፊልሙ ሲሰራ ለሕዝብ እይታ ይቀርባል፣ በቴሌቭዥን ይታያል፣ ይሸጣል፣ ይለወጣል ተብሎ አልነበረም። ግን ተሰርቶ አለቀ፡፤ ካለቀ በኋላ በቴሌቭዥን ቢታይ ፊልሙ ላይ ብዙ ባለሙያዎች ስለተሳተፉ ክፍያ ይጠይቃሉ። ፊልሙ ቢሸጥም ክፍያ ይጠይቃሉ። ስለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ተብሎ ተጠይቆ ነበር።

የፊልሙ ኤዲተር የማን ደምሴ ሲናገር ገንዘብ ያለው ሰው ወይም ድርጅት ለዳይሬክተሯ ከፍሎ ፊልሙን ማሳየት እንዳለበት ተናግሯል። ካለበለዚያ ሌላ መፍትሔ እንደሌለውም ገልጿል። የአስኒ ፊልም በኮፒ ራይት /በባለቤትነት መብት/ ጉዳዮች ተወሳስቦ እና ተሳስሮ የተቀመጠ ነው። ፊልሙን ለሕዝብ ለማሳየት ገንዘብ መክፈል እንዳለበት ተገልጿል።

ይህ በአስኒ ሕይወትና ሥራ ላይ የሚያተኩረው ፊልም ለሕዝብ በቴሌቭዥን እንዲታይ ፊልሙ ላይ የሰሩ ባለሙያዎች በጎ ፈቃደኛ እንደሆኑ ማግባባት እንደሚገባም አስተያየት የሰጡ ሰዎች አሉ። ምናልባት ገንዘብ የሚከፍል ሰው ወይም ድርጅት ቢጠፋ ፊልሙ ዝም ብሎ ቁጭ ሊል ይችላል። ስለዚህ ፊልሙ ላይ የተሳተፉትን የባለቤትነት መብት ሊያነሱ የሚችሉትን ባለሙያዎች በማግባባትና በማሳመን ለሕዝብ እይታ የሚበቃበት ሁኔታ እንዲመቻች ፊልሙን የተመለከቱ ሰዎች አስተያየት ሰጥተዋል።

አስናቀች ወርቁ ለበርካታ ጋዜጠኞች ቃለ -መጠይቅ በመስጠት የምትታወቅ ሲሆን አያሌ የሬዲዮ፣ የጋዜጣና የመፅሔት አምዶች ላይ ህይወቷና ስራዎቿ ተፅፏል። በቀድሞው የኢትዮያ ቴሌቭዥን MEET ETV ፕሮግራም አዘጋጅ ተፈራ ገዳሙም ሕይወቷን እና ስራዎቿን በጥሩ ሁኔታ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
16555 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us