ጉራማይሌዋ አዲስ አበባ

Wednesday, 05 February 2014 15:42

በጥበቡ በለጠ

           የከተማ ግንባታ እና ዲዛይን ብዙ ነገሮችን አካቶ ነው የሚሰራው። በውስጡ የአንዲት ሀገር ባሕል አለ። በውስጡ ማንነት አለ። በውስጡ ታሪክ አለ። በውስጡ የሕዝቦች አሻራ አለ። ከተማችንን አዲስ አበባን በምኖርበት ጊዜ ጉራማይሌነቷን እንደያዘች ቀጥላለች።

አዲስ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ሃያ ዓመት አልፎታል። ታዲያ በነዚህ ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ያልተቆፋፈረችበት፣ ያልፈረሰችበት ጊዜ የለም። እንደገና ደግሞ ግንባታዎች ሲካሄዱበት ትታያለች። አዲስ አበባ ቀልብ አጥታለች። ሰከን ብላ ማሰብ አልቻለችም። አቡዋራው፣ ጉድጓዱ፣ የማሽነሪ ጩኸቱ፣ የመንገድ መጨናነቁ፣ የታክሲ ሰልፉ፣ የታሰበበት ቦታ ቶሎ አለመድረሱ፣ የውሃ፣ የስልክ፣ የመብራት አቅርቦቱ ከእለት እለት እየሳሳ መምጣቱ ከተማዋን የቀወሰች እያስመሰላት ነው።

የአፍሪካ መዲና ተብላ የምታታወቀው ይህችው ከተማ አንድም ቀን ተረጋግታ እንግዶቿን ተቀብላ አታውቅም። ለመሆኑ አዲስ አበባ መቼ ነው ተሰርታ የምትጠናቀቀው? መቼ ነው ሙሉ በሙሉ ከተማ የምትሆነው? መንገዱ አለቀ ሲባል ውሃ ልማት ይቆፍራታል። ሌላ ነገሯ አለቀ ሲባል ቴሌ የሆነ ኬብል እቀብራለሁ ይልና ይመነቃቅራታል። መቼ ይሆን አደብ የምትገዛው?

በአሁኑ ወቅት አያሌ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። የሚመጡበት ምክንያት ብዙ ነው። አንዳንዶቹ በአገሪቱ ታሪካዊ ቅርሶችና ማንነት በመደነቅ ሊያዩዋት በመፈለግ ነው። በዓለም ላይ እፁብ ድንቅ የሚባሉት የቅዱስ ላሊበላ 11 ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ተሰርተው የተጠናቀቁት በ23 ዓመታት ነው። 23 ዓመታት የፈጁት እነዚህ ኪነ-ሕንጻዎች ሲሰሩ አንድም ስህተት የለባቸውም። ፍፁም /Perfect/ ስራዎች ናቸው። ከዚያም አልፈው የፕላኔታችን እፁብ ድንቅ /Wonders and Mystery/ የሚባሉ ናቸው።

ታዲያ በዚህችው በኛ ሀገር ከዛሬ 800 ዓመታት በፊት በ23 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ለዘላለም የሚዘከር ኪነ-ሕንፃ እና ከተማ አንጸው በመጨረስ የሚታወቁበት ሐገር ናት። እኛ በዚህ ዘመን አዲስ አበባን መቼ ሰርተናት እንደምንጨርስ አላወቅንም። አዲስ አበባ መቼ ነው የምታልቀው ብለን ቁጭ በማለት አልተነጋገርንም።

ወደ አስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪካችን ስንጓዝም በ1624ዓ.ም የነገሡትን አፄ ፋሲልን እናገኛለን። አፄ ፋሲል ዘመናዊ ከተማ እና ዘመናዊ አስተሳሰብን በመፍጠር የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀዳሚ ተጠቃሽ መሪ ናቸው። ዛሬም ድረስ በበርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙ ኪነ-ሕንጻዎችን እና የጎንደርን ከተማ መስርተዋል። ይህችን ከተማ እና በውስጧ የሚገኙትን ኪነ-ሕንጻዎች፣ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ ከዓለማችን አስደናቂ ነገሮች መዝገብ ውስጥ ካሰፈራቸው ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል። ታዲያ አፄ ፋሲል ከተማዋን ለመመስረት እና አያሌ ኪነ-ሕንፃዎችን ገንብተው ለመጨረስ የፈጀባቸው 15 ዓመታትን ነው።

በ15 ዓመታት ውስጥ የአለማችንን ድንቅዬ ከተማ እና ኪነ-ሕንፃዎችን መገንባት የተቻለባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ታዲያ አዲስ አበባችን እንደው የአለም ድንቅ ከተማ መባሏ ይቅርና ለነዋሪዎቿ ምቹ የምትሆነው መቼ ነው?

በአዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱት የኪነ-ሕንፃ ግንባታዎች ኢትዮጵያዊ አሻራ፣ ወዝና ቀለም ያላቸው ናቸው ወይ? እየተባለ በተደጋጋሚ የሚቀርብና ከሚመለከተው አካል መልስ ያልተገኘለት ሁኔታ አለ። ሕንጻዎቹ ከዱባይ እና ከተለያዩ ኢንተርኔቶች የሚገለበጡ ዲዛይኖች እንጂ ኢትዮጵያዊኛ አስተሳሰብ እና አመለካከት እንዲሁም ፍልስፍና ይዘው የሚታነፁ አይደሉም። አንዱ ኪነ-ሕንፃ ከሌላውጋር አይናበብም። ከየትኛውም አቅጣጫ ሲታዩ የሚነበብ ቅርፅ የላቸውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቦታን /Space/ መሰረት አድርገው የታነፁ ባለመሆናቸው ለህይወት ምቹ የሆነ፣ ሰላም የሚሰጥ ሰፊ ገፅታ የላቸውም። ጭንቅንቅ ናቸው። ፈታ አያደርጉም። ባለ አምስትና አራት ኮከብ ተብለው የሚታነፁት ሆቴሎች ሳይቀሩ መላወሻ የላቸውም። እዚህ ቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ የታነፁትን ሆቴሎች ብቻ ማየት ይበቃል። በትንሽ ቦታ ላይ የታጨቁ ናቸው። ሰፊ ቦታን የመውደድ እና የማሰብ ባሕል ገና ብዙ ይቀረናል።

አውሮፓዊቷ ታላቅ ሀገር ጀርመን የኢትዮጵያን 1/3ኛ ነች። ነገር ግን መዲናይቱ በርሊንን እንኳን ብናይ የሰው ልጅ ለቦታ ወይም /Space/ ያለውን ትልቅ አመለካከት እናይበታለን። በርሊን ውስጥ ሁሉም ነገር ሰፊ ነው። መንገዱ ሰፊ ነው። የመኖሪያ ቤቱ ሰፊ ነው፣ መዝናኛው ሰፊ ነው፣ ነፃነቱ ሰፊ ነው። ሕይወትም ሰፊ ናት። የከተማ አገነባብ ለሰው ልጅ ሕይወት ምቹ እንዲሆን ታስቦ ነው ዲዛይን የሚደረገውም የሚሰራውም። በርሊንን የሰሯት ሰዎች ከመቶ ዓመታት በፊት የነበሩት ጀርመናዊያን ናቸው።

አዲስ አበባን አፍርሶ ከመስራት ለምን ከጎኗ አዲሷን አዲስ አበባን መፍጠር አልተቻለም? ብለው የሚጠይቁ አሉ” አሮጌ ከተማ /Old City/ እና አዲሷ ከተማ /New City/ እየተባሉ በብዙ ሀገሮች ውስጥ የሚታዩ ከተሞች አሉ። አሮጌውን ከተማ በአንድ ጊዜ እያፈራረሱ ነዋሪውም በብዙ መልኩ እየተጉላላ ሕይወትን ከሚገፉ አዳዲስ ኪነ- ሕንፃዎችና ግንባታዎችን በአዲሱ መንደር ከተማ ውስጥ እያደረጉ አሮጌውን ደግሞ እየጠጋገኑ የመሰረታዊ ነገሮች አቅርቦት እንዳይጓደልባቸው እየተደረገ ስራውን መቀጠል ይቻላል የሚል አስተሳሰቦችም ይንጸባረቁ ነበር። ነገር ግን አዲስ አበባ ፈርሳ መስራት አለባት የሚለው የመንግስት አቋም በመኖሩ ከተማዋ ፈርሳም ተሰርታም አላልቅ አለች።

     በአዲስ አበባ ውስጥ የሚታዩት አዳዲሶቹ ኪነ-ሕንፃዎችም ባለሙያዎች አስበውባቸው፣ ተጨንቀውባቸው የተሰሩ አለመሆናቸውም በብዙ የሕንፃ ባለሙዎች ይገለፃል። ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ ምልክቶች፣ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት የአገነባብ ጥበብ የሚያሳዩ ንድፎችና ገጽታዎች የሏቸውም። ኪነ-ሕንፃ የጥንታዊ ኢትዮጵያዊን የረቀቀ ጥበብ ነው። ዛሬ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሐረር የሚመጡ ቱሪስቶች በዋናነት ማየት የሚፈልጉት ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸውን ድንቅ የአገነባብ ጥበብ ለማየት ነው። ኪነ-ሕንጻ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ነው። ይህን የቱሪዝም ሀብታችንን አሁን እየሰራናቸው ባሉት ኪነ-ህንጻዎች ላይ በልዩ ልዩ መልኩ ብናሳርፈው ኢትዮጵያዊኛ ኪነ-ሕንፃዎች ይኖሩን ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል አዲስ አበባ በብዙ ጉራማይሌነቷ ቀጥላለች።

Last modified on Wednesday, 05 February 2014 15:53
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12292 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us