የ4.4 ሚሊዮን ዓመቱ “ፈረስ” በኢትዮጵያ

Wednesday, 05 February 2014 15:46

በጥበቡ በለጠ

 

ከአንድ ወር በፊት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ግኝት ይፋ ሆኖ ነበር። ይህ ግኝት ደግሞ በእንስሳት ዓለም ውስጥ የሰውን ልጅ ለረጅም ጊዜ መጓጓዣ በመሆን ሲያገለግለው የነበረው ፈረስ ቅድመ ዝርያው ወይም የተፈጥሮ ሐገሩ ኢትዮጵያ መሆኗን አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘግበውት ነበር።

የፈረስን አፅም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ አፋር አካባቢ ያገኙ ተመራማሪ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እኚሁ አርኪዮሎጂስት /የሥነ-ቁፋሮ/ ባለሙያ ግደይ ወልደገብርኤል ይባላሉ። በእርሳቸው ጥናት መሠረት የተገኘው የፈረስ አፅም እድሜው 4.4 ሚሊዮን ዓመት እንደሆነ ተገልጿል።

እንግዲህ ኢትዮጵያ የሰው ልጅም ሆነ እንስሳትም የተፈጠሩባት ምድር እንደሆነች በጥናት እየተገለፀ ነው። ሐገሪቷ የአያሌ አስደናቂ ነገሮች መገኛ ከመሆኗ አንጻር በአለም አቀፍ ደረጃ ጉዳዩን በደንብ የማስተዋወቅ ስራ ከእኛም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት በሰፊው ይጠበቃል።

መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋልና ፈረስ እድሜው 4.4 ሚሊዮን ዓመት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ማስቆጠሩ ከተነገረ፣ የሰው ልጅም እድሜ እንዲሁ ከአራት ሚሊዮን ዓመት በላይ እንደሆነ ከተገለፀ፣ ኢትዮጵያዊያን ፈረሶችን ለመጓጓዣነት መጠቀም ከጀመሩ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል ማለት ነው።

እንግዲህ በአንዳንድ መፅሐፍት ማለትም እንደ ክብረ-ነገስት በመሳሰሉት እጅግ ጥንታዊ መፃህፍት ውስጥ እንደተጠቀሰው ንግስተ ሳባ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት ወደ እየሩሳሌም ስትጓዝ በርካታ እንስሳትን ለመጓጓዣነት ተጠቅማባቸዋለች። ዝሆኖች፣ ግመሎች፣ በቅሎዎችና ፈረሶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በተለይ ደግሞ ፈረስ የኢትዮጵያዊያን ልዩ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል። ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን ከባዕዳን ወረራ የተከላከሉት እና ወደ ጦርነት ሲገሰግሱ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ ሽምጥ እየከነፈ የሚሄደው ፈረስ ነው። ኢትዮጵያን ሊቀራመቱ የመጡ ተስፋፊዎቹ መሐል ዘሎ እየገባ ቅኝ መገዛትን ከሐገራችን ውስጥ ድራሹ እንዲጠፋ ካደረጉት ጀግኖቻችን መካከል አንዱ ፈረስ ነው። የፈረስ ውለታን እንዲህ በቀላሉ አውርተን የምናበቃውም አይደለም።

የኢትዮጵያ ነገስታት ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን ስም ትተው፣ እንዲሁም ሀገር ለመምራት የተሰጣቸውን የንግስና ስም እየተው በፈረስ ስማቸው ይጠሩ ነበር። የአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሪ የሚባሉት አፄ ፋሲል፣ እናታቸው ያወጡላቸው ስም አለምሰገድ ይባል ነበር። የንግስና ስማቸው ደግሞ አፄ ፋሲል ነው። ግን በፈረስ ስማቸው ‘ዞብል’ እየተባሉም ይጠሩ ነበር። አፄ ቴዎድሮስም በስፋት የሚጠሩበት ስማቸው በፈረስ ስማቸው ነበር። ታጠቅ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ጀግናው ቴዎድሮስ በፈረስ ስማቸው እየተጠቀሱ እስከ እየሩሳሌም ገናና ነበሩ።

“ታጠቅ ብሎ ፈረስ - ካሳ ብሎ ስም

አርብ አርብ ይሸበራል እየሩሳሌም”

እየተባሉ በወቅቱ ይዘመርላቸው ነበር። አዝማሪዎቹም ያንጎራጉሩላቸው ነበር። ነገሩ አፄ ቴዎድሮስ እስራኤልን ነፃ አወጣለሁ፣ እንደ ሐገርም እንደገና እመሰርታታለሁ የሚል ሕልም ነበራቸው። እናም ከቀኖች ሁሉ አርብን መርጠው በዚያች ቀን እየሩሳሌም ለመግባት ያስቡ ነበር ይባላል። ከዚህ እስከ እየሩሳሌም የኢትዮጵያ ነው እያሉም ያልሙ ነበር። ብቻ ፈረሳቸው ታጠቅ ዋና መጠሪያቸው ሆኖ ያገለግል ነበር።

አድዋ ላይ ቅኝ መገዛትን፣ ኮሎኒያሊዝምን የደመሰሱት አጤ ምኒልክም መጠሪያቸው ዳኘው በሚለው የፈረስ ስማቸው ነው። እስከ 1966 ዓ.ም የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በፈረስ ስማቸው ጠቅል እየተባሉ ይጠሩ ነበር።

እናም ፈረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የነገስታት ስምና መጠሪያ እየሆነ ያገለገለም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ቅድመ ዝርያው፣ አፅሙ መገኘቱም ምስጢሩ ከኢትዮጵያዊያን ጋር የጠበቀ ቁርኝቱን አያሳይም ትላላችሁ?

ፈረስ ሀገርን ከጠላት ከመከላከል አልፎም በኢትዮጵዊያን የእለት በእለት ሕይወት ውስጥ ሰፊ አስተዋፅኦ ያለው ነው።

በተለይ በገጠር ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችን በመጓጓዣነት፣ እንዲሁም ደግሞ በሬን ሁሉ እየተካ ለእርሻ ስራ ያገለግላል። እንደውም አንዳንድ ጥንታዊ ፀሐፊዎች ፈረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለእርሻ ስራ በእጅጉ አገልጋይ እንደሆነ ፅፈዋል።

ፈረስ መከበሪያም ነው። ፈረስ ያለው ሰው ፈረሱን አስጊጦ እና በቀለማት በተዋቡ አልባሳት አደማምቆት ነው የሚጓዘው። ፈረስ ጋሪም ሆኖ በየከተሞቻችን በሰፊው ሲያገለግል ነው። ባለጋሪው እየተባለም ተዜሞለታል።

ፈረስ በጥንታዊ ኢትዮጵያ ሰረገላ ሆኖ ለታላላቅ ነገስታትና መሪዎች ክብረ-በዓላት ላይ ሲያገለግል ቆይቷል። 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ባለ አራት ጎማ መኪናዎችና ሞተሮች በሚመጡበት ጊዜ የፈረስ ደማቅ ዘመን እየደበዘዘ መጣ። ነገር ግን እንደ እንግሊዝ ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ዛሬም ድረስ ፈረስን የክብር መገለጫ አድርገው በቤተ-መንግስቶቻቸው አካባቢ በሰረገላነት ይጠቀሙበታል።

     ፈረስ ለፀጥታ ሰዎች ማለትም ለፖሊሶች ስራ ቅልጥፍናም አገልጋይ ነው። ፖሊሶች በፈረስ ላይ ሆነው በመጓጓዝ የፀጥታ ስራቸውን ያከናውኑበታል። የፈረስ አገልግሎት ሰፊ ነው። ዛሬ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሁሉ የፈረስ ግልቢያ ይቀርባል። የፈረስ ግልቢያ ውድድርን ማሸነፍ ከፍተኛ ክፍያ አለው። ይሁን እንጂ የዛሬ 4.4 ሚሊዮን ዓመት ጀምሮ ፈረስ የተገኘባት ኢትዮጵያ በፈረስ ግልቢያ ውድድር ውስጥ የለችበትም። ብቻ ፈረስ ሀገሩ ኢትዮጵያ መሆኑ ብዙ እንድናስብ ያደርገናል። ኢትዮጵያ የሰውም የእንሰሳም መፈጠሪያ ሆናለች። የፍጥረት መገኛ ሀገራችንን በሚገባ ልናስተዋውቃት ይገባል ባዮች ነን።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
11479 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us