አምባሳደር ዘውዴ ረታ እና የታሪክ መጽሐፍቶቻቸው

Wednesday, 05 August 2015 14:48

በጥበቡ በለጠ

በኢትዮጵያ የታሪክ አፃፃፍ ውስጥ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ሰሞን አንድ አስገራሚ መጽሐፍ ብቅ አለ። ይህ መጽሐፍ የኤርትራ ጉዳይ የሚል ርዕስ አለው። የተፃፈው ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስርዓተ-መንግሥት ውስጥ በአምባሳደርነት እና በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በሰሩት በአምባሳደር ዘውዴ ረታ አማካይነት ነው። ይህ መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በቅርፁ ትልቅ የሚባል ሲሆን ሰፊ ተቀባይነትን አገኘ።

 

ተቀባይነትን ያገኘው በኢትዮጵያዊያን ብቻም አልነበረም። ዛሬ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ራሳቸውን መቻላቸውን በሚናገሩት በኤርትራዊያንም ጭምር ነበር። መጽሐፉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚነበበው ሁሉ ኤርትራ ውስጥም ተነባቢ ሆነ። በርካታ ኤርትራዊያን መጽሐፉን እንደገዙትም ይነገራል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምን ቢጠቀስ ነው የሁለቱም ሀገር ዜጐች የሚያነቡት? የሚል ጥያቄም መነሳቱ አይቀርም።

 

አምባሳደር ዘውዴ ረታ የፃፉት የኤርትራ ጉዳይ መጽሐፍ ትክክለኛ የታሪክ ሠነዶችን በመያዙና እውነተኛ ሃቅ በማንፀባረቁ ነበር። ለምሳሌ ቀደም ባለው ዘመን ኤርትራ በእንግሊዞች የቅኝ አገዛዝ መዳፍ ስር በነበረችበት ወቅት ከዚያ መከራ ወጥታ ከእናት ሀገሯ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ኤርትራዊያን ራሳቸው መሆናቸውን ደራሲው ይገልፃሉ። በወቅቱ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ተዋህደው ለመኖር ካለ ጦርነት እና ተፅዕኖ በሰላምና በፍፁም ደስታ እንደነበር የጽሁፍ ማስረጃዎችን እየጠቃቀሰ መፅሐፉ ይተነትናል። በእነዚህና በሌሎችም የአፃፃፍ ቴክኒኩ መጽሐፉ እስከ አሁን ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ከሚታተሙ እና ከሚሸጡ መፃሕፍት መካከል አንዱ ነው።

 

አምባሳደር ዘውዴ ረታ በዚህ ብቻም አላቆሙም። ሌላ ግዙፍ መጽሐፍ አሳተሙ። ርዕሱ ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የስልጣን ጉዞ የሚል ነበር። ይህን መጽሐፍ የተለያዩ ሰዎች በልዩ ልዩ ዘርፎች ውስጥ እየጠቃቀሱት የብቃት ደረጃውን ሲያደንቁት ቆይተዋል። በ1997 ዓ.ም ይህ ተፈሪ መኮንን የተሰኘው መጽሐፍ ወደ ገበያ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች ሁሉ እንደሚያመለክቱት ውብ የሆነ የትረካ ስልት መያዙን ነው። ደራሲው ዘውዴ ረታ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ታሪክ ገና ከጽንስ እስከ ውልደታቸው፣ ብሎም እስከ ጐልማሳነት ሕይወታቸው ድረስ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ የተረኩበት አፃፃፍ በእጅጉ ተወዶላቸዋል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚጠቀሱት መረጃዎች ደግሞ እውነተኛ በመሆናቸው የተአማኒነት ብቃቱም የዚያኑ ያህል ተወዳጅ እንዲሆን አድርጐታል።

 

ሦስተኛው ግዙፍ መጽሐፋቸው ደግሞ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የሚሰኘው ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምንም እንኳ ርዕሱ ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ቢገናኝም፤ የመጽሐፉ ሰፊ ይዘት ግን ኢትዮጵያ ነች። አብዛኛው ርዕሰ ጉዳይ በንጉሡ ዘመን ስለመበረችው ኢትዮጵያ እና አስተዳደሯ የሚቃኝ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከፍፁም ፊውዳላዊ ሥርዓት ወደ ሕጋዊ አስተዳደር እንዴት እንደተሸጋገረች ልዩ ልዩ ሠነዶችን በመጠቃቀስ መጽሐፉ ያብራራል።

 

ከዚህ ሌላም የትምህርትና የስልጣኔ መንገድ በዚያን ዘመን እንዴት እንደነበር ይተርካሉ። በኋላ ደግሞ ይህች ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ በፋሽስቶች እጅ የወደቀችበትን እና ዜጐቿ ደግሞ በቅኝ ግዛት መዳፍ ሥር ላለመውደቅ የከፈሉትን መስዋዕትነትም አምባሳደር ዘውዴ ረታ ይተርካሉ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራቸውን ጉዳይ ይዘው በመቅረብ በዲፕሎማሲው ረገድ ያበረከቱትን ተግባር በተደራጀ ማስረጃ ዘውዴ ረታ ይተርካሉ። ከኢጣሊያ ወረራ በኋላም እንግሊዝ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነቷን ለማሳየት የፈጠረችውን ደባ ንጉሡ እንዴት አድርገው በዘዴ የሀገራቸውን ሉዐላዊነት እንዳረጋገጡ መጽሐፉ ይተርካል። ይሄው 812 ገጾች ያሉት የዘውዴ ረታ መጽሐፍ ኢትዮጵያ ከ1923 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ ምን እንደነበረች ያሳየናል። ከ1948 እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ያለውን ታሪክ ደግሞ በቅርቡ ያሳትሙታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

እነዚህ ግዙፍ የሆኑ የዘውዴ ረታ መፃሕፍት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ዘመነ መንግሥት ጠንካራ እና ደካማ ጐኖች በማሳየትና በመተንተን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም የውድድር ውጤቶች መሠረት በማድረግ ዘንድሮ በተካሄደው “ንባብ ለሕይወት” በተሰኘው ትልቅ የመፃሕፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ መራጭ ኮሚቴው ለአምባሳደር ዘውዴ ረታ ከፍተኛ ድምፅ ሰጥቶ የዚህ ዓመት የወርቅ ብዕር ተሸላሚ አድርጓቸዋል።

 

ባለፈው እሁድ በኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ ከአንድ ሺ የሚልቅ ታዳሚ በተገኘበት አዳራሽ ለአምባሳደር ዘውዴ ረታ ከንባብ ለሕይወት አዘጋጆች ከነቢኒያም ከበደ የተሰጣቸውን የወርቅ ብዕር ስጦታ በክብር እንግድነት የሰጣቸው የሸገር ሬዲዮ መስራችና ተወዳጅ ጋዜጠኛ የሆነው ተፈሪ ዓለሙ ነበር። ተፈሪ፣ የወርቅ ብዕሩን ሲያበረክት ተንበርክኮ ሰጥቷል። በወቅቱም ለዘውዴ ረታ ክብር ያደረገው በመሆኑ ታዳሚው በከፍተኛ ደረጃ የደስታ ስሜቱን ሲገልፅ አምሽቷል።

 

ለመሆኑ ይህን የወርቅ ብዕር የተሸለሙት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ራሳቸው ከታሪክ መጽሐፍቶቻቸው ሌላ ሰውየውም የትልቅ ታሪክ ባለቤት ናቸው። የሕይወት ታሪካቸውን በመድረኩ ላይ ያነበበው ጋዜጠኛ ደግአረገ ነቅአጥበብ ሲገልጽ፤ ዘውዴ ረታ ለሀገራቸው በሙያቸው ብዙ ተግባራትን ያበረከቱ መሆናቸውን ገልጿል።

 

በመጽሐፋቸው ውስጥ የሚገኘው ፅሁፍ እንደሚያወሳው፣ ዘውዴ ረታ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ መወለዳቸውን ታሪካቸው ያወሳል። ከ1933 ዓ.ም እስከ 1945 ዓ.ም ድረስም ቀድሞ ደጅአዝማች ገብረማርያም ይባል በነበረውና ኋላ “ሊሴ ገብረማርያም” ተብሎ በተሰየመው የፈረንሳይ ት/ቤት የመጀመሪያውንና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አከናውነዋል።

 

ዘውዴ ረታ፣ ከ1945 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት፣ የቤተ-መንግሥት ዜና ጋዜጠኛና በራዲዮ ዜና አቅራቢነት ሠርተዋል። ከዚያም ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ በፓሪስ የጋዜጠኝነት ትምህርት በማጥናት በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ከትምህርታቸው መጠናቀቂያ በኋላ ከ1952 ዓ.ም እስከ 1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣና የመነን መጽሔት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። ቀጥሎም ከ1954 እስከ 1955 ዓ.ም ለአንድ ዓመት የኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። ከ1955 ዓ.ም እስከ 1958 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። ከ1958 ዓ.ም እስከ 1960 ዓ.ም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። በኋላም ከ1960 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል። ከ1956 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም የፓን አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ማኅበር ፕሬዝደንት ሆነው ሰርተዋል። ከ1962 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘዋውረው በሦስት ዘርፎች አገራቸውን አገልግለዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-

 

1ኛ. በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር

2ኛ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር

3ኛ. በሮም እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል።

አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሃያ ሁለት ዓመታት አገልግሎት ካበረከቱ በኋላ፣ በደርግ ዘመን ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ስደተኛ ሆነው በአውሮፓ በቆዩበት ዘመን፣ በሮም የኢንተርናሽናል ድርጅት ውስጥ (IFAD) ለአሥራ ሦስት ዓመታት በፕሮቶኮልና በመንግሥታት ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

 

በ1959 ዓ.ም ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ተጋብተው ሦስት ልጆችንም አፍርተው እንደሚኖሩ የሕይወት ታሪካቸው ያወሳል።

 

አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የምኒልክ የመኮንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኮንን ኒሻን ተሸላሚም ነበሩ። ከዚህ ሌላም ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከአውሮፓ በድምሩ ከሃያ ሁለት አገሮች የታላቅ መኮንን ደረጃ ኒሻኖችን የተሸለሙ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

 

አምባሳደር ዘውዴ ረታ ገና በወጣትነታቸው ዘመን ማለትም ከ1945 ዓ.ም ላይ ሁሉ ወደ አራት የመድረክ ቴአትሮችን ጽፈው ለሕዝብ ያሳዩ የሥነ-ጽሁፍ እና የዲፕሎማሲ ሰው ናቸው። በፀባያቸውም ትሁት፣ ይህን ሠርቻለሁ ብለው ልታይ ልታይ የማይሉ በተፈጥሯቸው ድብቅ ናቸው።

 

አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ የአንድ ስርዓተ-መንግሥትን ማለትም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ዘመን ታሪክ፣ ከውስጥ ሆነው ያዩትን እና የኖሩትን እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ ሰነዶችን በማገላበጥ እና ሰዎችን በመጠየቅ ለትውልድ ታሪክ በማስተላለፋቸው የወርቅ ብዕር ተሸላሚ ሆነዋል። ታዲያ በዚህ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለእኔም አንድ የቤት ስራ አዘጋጆቹ ሰጡኝ። የቤት ስራዬ ደግሞ፣ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን መፃሕፍት ሳነብ የተሰማኝን ስሜት እና ትዝታዬን በተመለከተ በመድረኩ ላይ እንዳቀርብ ተጋበዝኩ። ዘውዴ ረታን ለመግለፅ በጣም ከበደኝ። ምክንያቱም የታሪክ አፃፃፋቸውን እኔ ብቻ ሳልሆን፣ ያነበቡት ሁሉ በእጅጉ ወደውታል። ስለዚህ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ “ወርቃማው ብዕር ወርቅ ተሸለመ” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ፅሁፍ አቀረብኩ።  

 

ወርቃማው ብዕር ወርቅ ተሸለመ

ይህ ፅሁፍ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም አምባሳደር ዘውዴ ረታ የወርቅ ብዕር ሲሸለሙ የቀረበ ነው።

በዚህች በዛሬዋ እለት ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም፣ “ንባብ ለሕይወት” የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ እና የኪነ-ጥበባት ዝግጅት፣ በአይነቱ እና በድምቀቱ በእጅጉ ጎልቶ ትዝታውን እስከ መጪው አውደርዕይ ድረስ አሸጋግሮ ሊሰናበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ታዲያ በዚህ በውቡ የዘንድሮው “ንባብ ለህይወት” የመፃህፍት አውደ-ርዕይ እና የኪነ-ጥበባት ዝግጅት ላይ አንድ ታሪካዊ ሥነ-ሥርዓት ሊካሔድ ነው። በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ግዙፍ የታሪክ ሰነዶችን አደራጅተው፣ በውብ የትረካ ክህሎታቸው ታላላቅ መፃሕፍትን ያዘጋጁልንን አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊያን ለማመስገን እና ለመሸለም እዚህ የተገኘን ታዳሚያን በሙሉ ለዚህች ታሪካዊት ቀን እንዲህ ደማምቀን በመገኘታችን እንኳን ደስ አለን እላለሁ።

ደስ የሚለን ለምን መሰላችሁ? የዛሬው ተሸላሚያችን እርሳቸው የኖሩበትን እና ለሐገራቸውም አያሌ ነገሮችን ያበረከቱበትን ዘመን እና ታሪክ በሚገባ አደራጅተው ለተተኪዎቹ ትውልዶች፣ ማለትም አሁን ላለነው ለኛ እና ለመጪው ትውልድ ፅፈው በማስረከባቸው ብቻም አይደለም። ይልቅስ ጽፈው የሰጡን ታሪክ በራሱ፣ ትውልዳችን በተሳሳተ የታሪክ ትርጓሜ እና በተዛባ መረጃ ባዶ እንዳይሆን፣ ከጥላቻ እና ከባዶ መወቃቀስ እንዲድን የማድረግ ኃይል ስላው ለኢትዮጵያ ሀገራችን እንደ ቤዛ ሆኖ በማገልገሉ ነው።

አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣

እርስዎ ፅፈውና አዘጋጅተው ያስነበቡን መፅሐፍቶችዎ በውስጣቸው ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን እንድመረምር የሚደርጉን አያሌ ጉዳዮችን ይዘዋል። ብዕርም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዘመን ውስጥ የታዩትን ዝርዝር ጉዳዮችን በትክክለኛ ማስረጃ አጠናቅረው ስለሰጡን የታሪክ ክፍተት እንዳያደናብረን ረድተውናል።

ከእርስዎ ብዕር ውስጥ ከወጡት የታሪክ ዘለላዎች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹን እንድጠቃቅስ ይፈቅድልኝ፡-

-    እርስዎ ታሪካቸውን በሚገባ የፃፉላቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሐገርን እና ትውልድን ለማዘመን እንደ ሀገር መሪ ያበረከቷቸውን ውለታዎች ዘርዝሮ መተንተኑ ባይሆንልኝም፣ ግን ሕገ-መንግሥት ቀርፀው፣ ፓርላማ አቋቁመው፣ ፍርድ ቤቶች አስፋፍተው፣ መሠረተ ልማትን በሰው አእምሮ እና በሀገሪቱ ላይ አስፋፍተው ያለፉ ንጉሥ እንደነበሩ ከአፈ-ታሪክነት ወደ ተጨባጭ ማስረጃነት እንዲቀየር አድርገዋል።

-    በዚሁ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መፅሐፍዎ ውስጥ ንጉሡ እንዲህ ብለው መመሪያ ሰጡ፡-

“ልጁን ያላስተማረ እራሱን እንደመግደል የሚያስቆጥር ነው” ብለዋል። ልብ አርጉ ይህን ያሉት ንጉሡ ናቸው።

ከዛሬ 80 ዓመት በፊት ልጁን ያላስተማረ ኢትዮጵያዊ ራሱን እንደመግደል የሚቆጠርበት ሀገር ነበረች። ከ80 ዓመታት በኋላ ደግሞ ልጁን ለማስተማር የትምህርት ቤት ክፍያ ውድነት እራስን የሚያስገድል እየሆነባት ነው።

-    እርስዎ ታሪካቸውን በፃፉላቸው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ተማሪዎች በተማሪ ቤታቸው ውስጥ ምግብ፣ ወተት እና ሳሙና የመሳሰሉት ነገሮች ይቀርቡላቸውም ነበር። እንደውም ምግብ በስርዓት የማይበላ፣ ወተት የማይጠጣ፣ በተሰጠው ሳሙና የማይታጠብ ተማሪ ይቀጣ ነበር። ከጃንሆይ በኋላ የተፈጠርን ተማሪዎች ወተትን የምናውቀው በተረት ነው። “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” እያልን ነው። ላሟም ወተቷም የሉም። እንደውም አንድ ቀን አንዲት በንጉሡ ዘመን የተማሩ ሴት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ እንዲህ አሉ፡- ት/ቤት እየተማርን ሳለ አንድ ጊዜ ሰልፍ አድርገን ነበር። ያ ሰልፍ የተደረገው የሚቀርብልን ዶሮ ወጥ ቀጭን ሆኗል በሚል የቀረበ ተቃውሞ ነው” አሉን። ዶሮ ወጥ ቀጠነ ተብሎ ሰልፍ የተወጣበት ዘመን እዚህ ሀገር ላይ ነበር።

እርስዎ በፃፉለት ዘመን እና ታሪክ ውስጥ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት ተልኮ ሀገሩን የከዳ ተማሪ ወይም ጥገኝነት የጠየቀ ተማሪ አንድም የለም ሲባል ሰምቼ ዘመናችሁን ናፈኩት። ግን ለምን አልተሰደዳችሁም? ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል።

የኤርትራ ጉዳይ ብለው ባዘጋጁት ሌላው ድንቅዬ መፅሐፍዎ ውስጥም፣ አያሌ ተጨባጭ ማስረጃዎችን አደራጅተው ለትውልድ ያወረሱት የፅሁፍ ቅርስ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። ኤርትራን ከቅኝ ገዢዎች ከነእንግሊዝ መንጋጋ ውስጥ አውጥቶ በሰላምና በፍቅር ከእናት ሐገሯ ከኢትዮጵያ ጋር የማዋሃዱ ድንቅዬ ተግባር የእርስዎ ዘመን ታሪክ በመሆኑ እኔና መሰሎቼ እንቀናበታለን። በኛ ዘመን ኤርትራ ቁስል ሆነች።

ሰሞኑን እንኳ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ወደ አፍሪካ በተለይ ኬኒያ እና ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው ሲባል፣ ዓለም ትልቅ ዜና አድርጎት ሲያወራ እኔ የእርስዎን መፅሐፎች እና ሌሎችንም ማገላበጥ ጀመርኩ። በመፅሐፍዎ ውስጥ ስለ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመንና ታሪክ ብዙ የታሪክ ክፍተቶቻችንን ይሞላሉ።

አፄ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ነፃ ለማውጣት፣ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግርና ትንበያ፣ ከዚያም ይህችን ሀገር ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተው፣ የነጮችን የበላይነት አሸንፈው ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የተስፋይቱ ምድር ያደረጉበትን ትግልና ስኬት ሳነብ በኋላም ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህንን ሀቅ ሲመሰክሩ ስሰማ፣ እውነት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ወርቅ ታሪክ ፅፈዋል ብያለሁ።

ታዲያ የገረመኝ ነገር፣ በዚህ ዘመን ፕሬዝዳት ኦባማ ያሰሯት መኪና ምንም አይነት መሣሪያ የማይበሳትና ሙሉ በሙሉ ሽፍን ስትሆን፣ የነጭ ወራሪን ድል አድርገው የጥቁር መንግሥት የመሠረቱት አፄ ኃይለሥላሴ፣ በቅኝ ግዛት መዳፍ ውስጥ የወደቁት የአፍሪካ ሀገራት ከመከራ ተላቀው ነፃ ሀገር እንዲሆኑ ያደረጉት እኚሁ ንጉስ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ሁሉም አፍሪካዊ ኃይልና ጥንካሬ እንዲያገኝ ያደረጉት ንጉስ፣ እንዲሁም ደግሞ የካሪቢያን ሀገራት እነ ጀማይካ እምነታቸውን ሁሉ ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲያደርጉ ግርማ ሞገስ የተሰጣቸው ንጉሥ ኃይለሥላሴ፣ ከ50 ዓመታት በፊት ኪንግ ስተንን፣ ቻይናን፣ ኮሪያን፣ አሜሪካንን ወዘተ . . . ሲጎበኙ በሽፍን መኪና ሳይሆን፣ በክፍት መኪና ለሕዝቡ ሰላምታ እየሰጡ ነበር።

በአጠቃላይ አምባሳደር ዘውዴ ረታ የኖሩበትን ዘመን እና ታሪክ እንዲህ ነበር ብለው በውብ የአፃፃፍ ዘዴዎ ለትውልድ አስተላልፈዋል። በመጪው ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም የ80 ዓመትዎ የልደት ቀን ቢሆንም ዛሬም ልደትዎ ነው! እድሜና ጤና ይስጥዎት እንጂ ገና ብዙ ወርቅ ይጽፋሉ። የእርሰዎንም ታሪክ ትውልዱ ይቀባበለዋል። ለወርቃማው ብዕር ወርቅ የሸለሙትን እነ ቢኒያም ከበደንም በእጅጉ አመሰግናለሁ።

 

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
10039 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us