ጥያቄ የሚያስነሳው “የዓመቱ የበጐ ሰው ሽልማት”

Wednesday, 19 August 2015 13:10

በድንበሩ ስዩም

 

በኢትዮጵያ ውስጥ ታላላቅ ተግባራትን ለፈፀሙ ሰዎች እና ተቋማት የመሸለም እና የማበረታታት ተግባር እምብዛም አይታይም። በቀደመው ዘመን ብልጭ ብሎ ድርግም ያለው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅትና ተግባሩ በእጅጉ የሚወደስለትን ተግባር ፈፅሞ ቢያልፍም ያንን የመሠለ እንቅስቃሴ እስከ አሁን ድረስ በመንግሥት ደረጃ ማከናወን አልተቻለም:: በደርግ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው በኢትዮጵያ መንግስት ደረጃ የሚዘጋጁት ሽልማቶች ፖለቲካዊ ቅኝት ያላቸው በመሆኑ አላጠግብ ብለው ቆይተዋል። ደርግ በሶሻሊስት እና በኮሚኒስት ፍልስፍና ውስጥ ጐልተው የሚወጡ ወታደራዊ ተግባራትን የፈፀሙ ሰዎችን ሲሸልም ኖሯል። አሁን ባለው መንግሥት ደግሞ ሽልማት ራሱ ምን እንደሆነ ግራ እስከሚያጋባን ድረስ ሲሠራበት ቆይቷል። ብዙ ሺ ገበሬዎችን እየጠሩ መሸለምና ሜዳሊያ ማጥለቅ ራሱ አጠያያቂ ሆኖ ያለፈበት ወቅት ነበር። ምክንያቱም ይህን ሁሉ ገበሬ ለሽልማት የሚያበቃው ተግባር በዚህች ሀገር ላይ ተፈፅሟል ወይ የሚል ጥያቄ ስለሚያስነሣ ነው። ገበሬው ተምሯል? ለሀገርና ለወገን ብሎም ለታሪክ ቀጣይ የሆነ ፈጠራ ፈፅሟል? ከሞፈርና ከቀንበር እርሻ ተላቋል? በምን ምክንያት ተሸለመ? ገበሬው ድህነትን ድርቅን ከኢትዮጵያ ምድር ላይመለስ አባሯል? በየጊዜው ብልጭ ድርግም የሚሉ የሽልማት አይነቶችን በሀገራችን ውስጥ ስንመለከት ቆይተናል።

አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፊት-አውራሪነት የሚመራ የኢትዮጵያ የበጐ ሰው ሽልማት መሰጠት ከጀመረ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል። ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ነሐሴ 30ቀን 2007 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ውስጥ በሚደረግ ዝግጅት የሽልማት ሥነ-ሥርአቱ ይካሔዳል። እጩዎችም ከየዘርፉ ተመርጠዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህን የበጐ ሰው ሽልማትን ሲያዘጋጅ መነሻ ሀሳቡ የሚመስለኝ በልዩ ልዩ ተግባራት ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ለሕዝባቸው ጠቃሚ ጉዳዮችን ያበረከቱ ግለሰቦችን በማመስገን እና እውቅና በመስጠት ለሌላውም ሰው መነቃቂያ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። የዳንኤልን ሃሣብ ከላይ በሠፈረው ፅሁፌ ብቻ ሰብስቦ ማስቀመጥ አይቻልም። ምክንያቱም የበጐ ሰው ሽልማት ብዙ ዝርዝር ጠቀሜታዎች አሉት። እናም ለሀገሪቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ትውልድም ይህን በጐ ሃሣብ እየተቀባበለው እንዲያሣድገው ምኞቴ ነው። ስናሣድገው ታዲያ በየጊዜው የሚታዩትን ሕፀፆች  በጋራ በማረም ነው።

በመጪው ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም በሚካሔደው የበጐ ሰው ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ በእጩነት የቀረቡት ሰዎችና ተቋማት ናቸው። የሰው ልጅ እና ተቋማት ሲወዳደሩ ወይም በእጩነት ቀርበው ማየታችን ግራ ስላጋባኝ ነው ዛሬ ጉዳዩ ላይ መፃፍ የፈለኩት። ለማንኛውም ለዚህ በ2007 ዓ.ም ለዚህ ለበጐ ሰው ሽልማት በእጩነት የቀረቡትን በዝርዝር እንመልከታቸው።

በሳይንስ ምርምር ዘርፍ

1.  ኘ/ር ኢ/ር አበበ ድንቁ/አአዩ/

2.  ኬሚካል መሐንዲስ ጌታሁን ሔራሞ

3.  ዶ/ር አበበ በጅጋ

4.  ኘ/ር አስራት ኃይሉ

5.  ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት/ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል/

በሥነ-ጥበብ ዘርፍ እጩዎች

1.  ሰአሊ አለ ፈለገ ሰላም

2.  እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ

3.  አቶ ተስፋዬ አበበ /የክብር ዶ/ር/

4.  ሰአሊ ታደሰ መስፍን

5.  አቶ አባተ መኩሪያ

በበጐ አድራጐት ዘርፍ እጩዎች

1.  ወ/ሮ አበበች ጐበና

2.  አቶ አስመሮም ተፈራ /ሲኒማ ራስ አካባቢ የተቸገሩትን የሚረዳ/

3.  ስንታየሁ አበጀ /የወደቁትን አንሱ እንጦጦ ማርያም አካባቢ

4.  አቶ አሰፋው የምሩ /የአሠረ ሐዋርያት ት/ቤት መስራች /ዊንጌት አካባቢ

5.  ትርሐስ መዝገበ

በቢዝነስ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ እጩዎች

1.  አባ ሐዊ/አቶ ገብረማካኤል/ በትግራይ ክልል ለአብርሃ ወደአጽብሐ አካባቢ ገበሬዎች ሥራ የፈጠሩ ገበሬ/

2.  ሰላም ባልትና

3.  አዋሽ ባንክ

4.  ካፒቴን ሰለሞን ግዛው

5.  ካልዲስ ቡና

በቅርስና ባሕል ዘርፍ እጩዎች

1.  አቶ ዓለማየሁ ፋንታ

2.  አቶ ኃብተስላሴ ታፈሰ

3.  አቶ ዓለሙ አጋ

4.  EMML/HMML /የኢትዮጵያ የብራና መፃሕፍት ማይክሮ ፊልም ድርጅት/

5.  ማሕበረ ቅዱሳን

በማሕበራዊ ጥራት ዘርፍ እጩዎች

1.  ኘ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት

2.  አቶ ደሳለኝ ራሕመቶ

3.  ዶክተር ፈቃደ አዘዘ

4.  ኘሮፌሰር ሺፈራው በቀለ

5.  ኘሮፌሰር በላይ ካሳ

በጋዜጠኝነት ዘርፍ እጩዎች

1.  አቶ ማዕረጉ በዛብህ

2.  አቶ ያዕቀብ ወልደማርያም

3.  አቶ ነጋሽ ገ/ማርያም

4.  ታምራት ገብረጊዮርጊስ /ፎርቹን/

5.  ቴዎድሮስ ፀጋዬ

በስፖርት ዘርፍ እጩዎች

1.  አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

2.  መምህር ስንታየሁ እሸቱ /ከበቆጅ ብዙ አትሌቶች እንዲወጡ ያደረገ መምህር/

3.  መሠረት ደፋር

4.  ኢነስትራክተር ሺፈራው እሸቱ

5.  ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ

መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ እጩዎች

1.  አቶ ግርማ ዋቄ /የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩ/

2.  አቶ መኰንን ማንያዘዋል

3.  አቶ ሽመልስ አዱኛ

4.  አማኑኤል የአእምሮ ሕክምና ሆስፒታል

5.  ኢንጅነር ስመኘው በቀለ

ከእነዚህ ከላይ የሰፈሩት 45 እጩዎች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የመጨረሻዎቹ ተሸላሚዎች ዘጠኝ ናቸው። እነዚህ ዘጠኙ ተሸላሚዎች ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ይታወቃሉ። ከዚያም ነሐሴ 30 ይሸለማሉ። ዘጠኙን የመጨረሻዎቹን ተሸላሚዎች የሚመርጡ ዳኞችም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና ታማኞች እንደሆኑ ከሰሞኑ የወጡት መግለጫዎች ይጠቁማሉ።

እንግዲህ በነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት እጩዎች ላይ የታዘብኩትን እና ግራ የገባኝን ጉዳይ መጠቃቀስ ፈልጋለሁ።

ሰው እና ተቋማት

የሽልማት መጠሪያው የበጐ ሰው ሽለማት ነው። በጐ የሰሩ ሰዎች መሸለም ነው። ሰው።

 ግን በዚህ በ2007 ዓ.ም የበጐ ሰው ሽልማት ላይ ሰው እና ተቋማት በአንድ ምድብ ውስጥ ገብተው በእጩነት ቀርበዋል። ለምሣሌ በቢዝነስ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ እጩዎች ውስጥ አባ ሐዊ/አቶ ገብረሚካኤል እና ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ከሦስት ተቋማት ጋር ይወዳደራሉ። እነዚህም ሰላም ባልትና፣ አዋሽ ባንክ እና ካልዲስ ቡና ናቸው። የሰውን ልጅ እና ተቋማትን ማወዳደር ይቻላል ወይ? ከካፒቴን ሰለሞን እና ከሰላም ባልትና ማን ይሻላል? ከካፒቴን ሰለሞን እና ከአዋሻ ባንክ ማን ይሻላል? ከካፒቴን ሰለሞን እና ከካልዲስ ቡና ማን ይሻላል? ይሔ ምርጫ ያስኬዳል?

ሁለተኛው ግራ ያጋባኝ የእጩዎች ምርጫ፣ በቅርስና ባሕል ዘርፍ የሚወዳዳሩ ናቸው። በዚህ ዘርፍ ሦስት ሰዎች እና ሁለት ተቋማት ይወዳደራሉ። ሦስቱ ሰዎች አቶ አለማየሁ ፋንታ፣ አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ እና አቶ ዓለሙ አጋ ናቸው። ተወዳዳሪዎችቸው ተቋማት ደግሞ የኢትዮጵያ የብራና መፃህፍት ማይክሮ ፊልም ድርጅት እና ማሕበረ ቅዱሳን ናቸው። በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱን ለመምረጥ የሚያስችለን መስፈርት ምንድን ነው? ለምሳሌ ከአቶ ዓለሙ አጋ እና ከማሕበረ ቅዱሳን መካከል ውድድር ማድረግ ይቻላል ወይ? አቶ ዓለማየሁ ፋንታንና የኢትዮጵያን የብራና መፃሕፍት ማይክሮ ፊልም ድርጅትን ማወዳደር እችላለሁ የሚልስ ሰው ይኖር ይሆን? ምን አይነት ዳኛ ነው ማሕበረ ቅዱሳንን አና እነ አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰን አወዳድሮ እከሌ ይበልጣል የሚለን?

ሌላው አስገራሚ ውድድር የሚደረገው ደግሞ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ ውስጥ የተካተቱት ናቸው። በዚህ ዘርፍ አማኑኤል የአእምሮ ሕክምና ሆስፒታል ከሰዎች ጋር ሊወዳደር ብቅ ብሏል። ከአማኑኤል ሆስፒታል ጋር ሊወዳደሩ የተሰለፉት አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ መኮንን ማንያዘዋል፣ አቶ ሽመልስ አዱኛ እና ኢንጀነር ስመኘው በቀለ ናቸው። ይሔ ውድድር እውነት መሆኑ ራሱ ይገርመኛል። ጉዳዩ የአሽሙር ወግ ይመስላል። ደራሲያን በምናባቸው የቢሆን አለም መስርተው የሚፅፉት የዘመናችን ወግ መሰለኝ። አማኑኤል ሆስፒታልን ከአቶ ግርማ ዋቄ ጋር ሣወዳድር፣ አማኑኤል ሆስፒታልን ከአቶ መኮንን ማንያዘዋል ጋር ሣወደድር፣ አማኑኤል ሆስፒታልን ከአቶ ሽመልስ አዱኛ ጋር ሣወዳድር አማኑኤል ሆስፒታልን ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ ጋር ሣወዳድር ልብ ወለድ ካልሆነ በቀር እንዴት እውነት ይሆናል?

በዚህ ፅሁፌ የሰው ልጅን እና የተቋማትን ልዩነት እና አድነትን በተመለከተ ልገልፀው ሞከርኩና ሠረዝኩት ምክንያቱም ጋዜጣን ማንበብ ለሚችል ሰው የሁለቱን ልዩነቶች ማስረዳት አንባቢን ዝቅ አድርጐ ማየት መሰለኝ ። እናም ተውኩት።

ለውድድር በቀረቡት ሰዎች ላይም ብዙ ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ። ለምሣሌ የስፖርት አሰልጣኞች እና ስፖርተኛ ለውድድር የቀረቡበትም የእጩዎች ዝርዝር አለ። ይሔም እንዴት ማወዳደር የቻላል? መምህርና ተማሪን ማወዳደር ይቻላል?

ባጠቃላይ ሲታይ ውድድር ከባድ ነው። ሁሉንም ሰው በውድድር ማጥገብ አይቻልም። ግን በተቻለ መጠን ውድድሩን ከነቀፌታ እንዲድን ማድረግ በእጅጉ ተገቢ ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩት ውድድሮች ጠንካራ ጐኖችን በመውሰድ፣ ደካማዎቹን በመተው የተሻለ ውድድር አድርጐ ለሽልማት ማብቃት ተገቢ መሆኑን ሁላችንም የምንስማማበት ይመስለኛል። ስለዚህ የዘንድሮው የ2007 ዓ.ም የበጐ ሰው ሽልማት ባለፈው ዓመት ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሊሸልም አስቦ ከተጨናገፈበት የውድድር ልምድ ትምህርት መውሰድ ነበረበት።

ባለፈው ዓመት ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኢትዮጵያዊያኖችን በስዕል ጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በፊልም እና በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ለመሸለም ፈልጐ ሀላፊነቱን ለየማሕበራቱ ይሠጣል። የሰአሊዎች ማሕበር በስዕል ጥበብ ውስጥ ያሉትን አስር እጩዎች እንዲያቀርብ እድል ተሰጠው ። ሙዚቀኞች ማሕበርም እንደዚሁ እጩዎችን እንዲያቀርብ፣ የፊልም ሰሪዎች ማሕበርና ደራስያን ማሕበርም እጩዎቻቸውን አቀረቡ። ከየዘርፉ ከታጩት ውስጥ አንድ ሰው እንዲመረጥ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን በየቀኑ ብዙ ሺ ብር እየወጣበት ማስታወቂያ መነገር ጀመረ። ሕዝቡ ከቀረቡለት እጩዎች ውስጥ ድምፅ እንዲሰጥ ተጋበዘ።

የእነዚህ የሙያ ማሕበራት መሪዎችን የአዲሰ ጣዕም የሬዲዮ ኘሮግራም አዘጋጆች ቃለ-መጠይቅ በማድረግ በአጩዎች ምርጫ ላይ የታዩትን አያሌ ስህተቶች ጠቆሙ። ለምሣሌ ከስዕል ጥበብ ውስጥ ካሉ ተወዳዳራዋች መካከል አቶ አለ ፈለገ ሰላም እና አስኒ ጋለሪ ለውድድር ቀርበዋል። ሰው እና ጋለሪ እንዴት ይወዳደራሉ ተብሎ ጭቅጭቅ አስነሣ። ውድድሩ እንደነዚህ አይነት ችግሮችና ሌሎችም በርካታ ሕፀፆች እንዳሉበት የሬዲዮ ኘሮግራሙ አፅንኦት ሰጥቶ አቀረበ። በእጩዎች ምርጫ ላይ የታዩትን ስህተቶች በመገንዘብ ይመስላል፣ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውድድሩ እንዲቆም አድርጐ ለተወሰነ ጊዜ አራዘመው። የተራዘመው ውድድር እስከ አሁን ድረስ አልተቀሰቀሰም። ሐገሪቷ የታላላቅ ሽልማቶች ሾተላይ ያለባት ትመስላለች። ሽልማቶች አይበረክቱላትም።

ታዲያ የዘንድሮው የበጐ ሰው ሽልማት ከባለፈው የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር “የሰውና የተቋማት” የእጩነት አቀራረብ ችግር፡ ልምድ መቅሠም ነበረበት እላለሁ። ሌላው ችግር ውድድርን በዘመን አለመከፋፈል ነው። ለምሣሌ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሊያካሒደው በሞከረው ውድድር ላይ በእጩነት የቀረቡት ሙያተኞች  አንዳንዶቹ በእድሜ አና በዘመን የማይገናኙ ነበሩ። በሙዚቃ ውስጥ ከቀረቡት እጩዎች እንኳን ብናይ መድረክ ላይ ከ30 ዓመታት በላይ በሙዚቃ አለም ስትምነሽነሽ የኖረችው ደማቋ አስቴር አወቀ፣ ገና ወደ ሙዚቃው አለም ጐራ ብሎ በዳዴ የሚሔድ ከጐሣዬ ቀለሙ/ጃኪ ጐሲ/ ጋር በእጩነት ቀርባለች ይሔን ምን አይነት ውድድር ይሉታል?

ከዚህ ሌላም ለዚሁ ለባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውድድር ደራሲያን ማሕበር ያቀረባቸው እጩዎችም አነጋጋሪ ነበሩ። ለምሣሌ በ1949 ዓም መስከረም በሚል ርዕስ እና በ1952 ዓ.ም ደግሞ ሌላው መንገድ በተሰኘ ርዕስ  ሁለተኛ የአጫጭር ልቦለዶች መድብል ያሣተሙ ደራሲ አሉ። እኚህ ሰው ታደሰ ሊበን ይባላሉ። በኢትዮጵያ የአጫጭር ልቦለዶች አፃፃፍ ታሪክ ውስጥ ከተመስገን ገብሬ ቀጥለው ፈር ቀዳጅ በመሆን ስማቸው ይጠራል። ታዲያ እኚህን ሰው የሚያውቃቸው የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያ እና በ1950ዎቹ ውስጥ የነበረ አንባቢ ብቻ ነው። ታደሰ ሊበን የ1950ዎቹ ደራሲ ናቸው። ከዚያ በኃላ ከእርሣቸው ጋር ለውድድር ከቀረቡት እጩዎች መካከል በዚህ በኛ ዘመን በርካታ መፃሕፍትን የሚያሳትመው ወጣቱ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው። እንዳለጌታ ከበደ እና ታደሰ ሊበን ሰፊ የዘመን ልዩነት በመካከላቸው አለ። ከዚህ ጋር ተያይዘው አያሌ ልዩነቶች አሉ። ታዲያ እነዚህን ሁለቱን ደራሲያን የምናወዳድርበት ምን አይነት መስፈርት ይኖረናል? እንደነዚህ አይነት የእጩዎች መረጣ የባሕል ሚኒስቴርን የሽልማት ሃሣብ እንዲጨናገፍ አድርገውታል። ሌሎችንም ችግሮች መጥቀስ ይቻላል። ግን የተጠቀሰው በቂ ነው።

የዘንድሮው የበጐ ሰው ሽልማት እጩዎችም የዚህ የዘመን ጉዳይ ችግር ሰለባዎች ናቸው። ለምሣሌ በጋዜጠኝነት ዘርፍ ውስጥ ከቀረቡት እጩዎች መካከል ሦስት በእድሜና በሙያቸው ትልቅ  የሆኑ ሰዎች ከሁለት ወጣቶች ጋር ለውድድር ቀርበዋል። በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ሙያውን ወደ ውጭ ሀገር ሔደው ተምረው ከመጡ የመጀሪያዎቹ ኢትዮጵያዊያን መካከል አቶ ነጋሽ ገ/ማርያም  ፊት- አውራሪ  ሆነው ይጠቀሣሉ። እኚህ ሰው የ1950ዎቹ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው ጋር ለውድድር ከታጩት ውስጥ አሁን በEBS  ቴሌቪዥን “የርዕዮት” ኘሮግራም አዘጋጅ የሆነው ወጣቱ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ  ነው። ለመሆኑ ቴዎድሮስ ፀጋዬን እንዴት ከነጋሽ ገ/ማርያም ጋር፣ ከማዕረጉ በዛብህ ጋር፣ ከያቆብ ገ/ማርያም ጋር ማወዳደር ይቻላል? ማነው ለዚህ ዳኝነት ቁጭ ብሎ የሚያወዳድረው? ማን አሸናፊ ሊሆን ነው?

ውድድር አስቸጋሪ ባሕርያት ቢኖሩትም እንደነዚህ አይነት የዘመን ክፍተቶች ግን በቀላሉ የሚስተካከሉ ነበሩ። መቼም ወደፊት ተደግመው እናያቸዋልን ብዬ አላስብም።

ባጠቃላይ ሲታይ  ግን የበጐ ሰው ሽልማት አላማው ትልቅ ነው። ወደፊት አድጐ በሐገር ደረጃ በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ዕውቅና አግኝቶ ልክ ቀድሞ እንደነበረው እንደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት ግርማና ሞገስ እንዲኖረው እመኛለሁ።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ከነዚህ ሁሉ መዓት በጐ ተግባሮቹ መካከል ይህን የሸልማት መርሃ ግብር በሰብሣቢነት እየመራ መጓዙ በራሱ ትልቅ ክብር የሚያሰጠው ነው። ዳንኤል ሩቅ አሣቢ፣ ሀገር ገንቢ፣ ትውልድ አስተማሪ መሆኑን በፅኑ ባምንም ዘንድሮ በቀረቡት የዓመቱ የበጐ ሰው ሽልማት እጩዎች መረጣ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱት እነዚህ ነጥቦች መስተካከል አለባቸው።

በመጨረሻም ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት አና ይህን መርሃ ግብር አብረውት የሚሠሩ ሁሉ በርቱ ጠንክሩ እላለሁ። የኢትዮጵያ የበጐ ሰው ሽልማት እያደገ እየጐመራ እያሸተ በመሔድ ፍሬውን ሁላችንም እንድንቋደሰው እመኛለሁ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
12380 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us