ልበ ብርሃኑ ሊቅ፡- አለቃ አያሌው ታምሩ ከመጋቢት 23 ቀን 1915 እስከ ነሐሴ 14 ቀን 1999 ዓ.ም

Wednesday, 26 August 2015 13:40

በጥበቡ በለጠ

የታሪክ መሠረት የተዋህዶ ብርሃን

አለኝታ ክንፋችን ለኢትዮጵያዊያን

የታሪክ መዘክር የኢትዮጵያ ብርሃን።

ሁሉ የሚያነበው የተዋህዶ መጽሐፍ

በእርሡ የሚዘጋ የዋልጌዎች አፍ።

አንብቡት ይሰማ ዛሬም እንደ ድሮው

አያሌው ታምሩ የምስጢር መጽሐፍ ነው።

 

ይህ ከላይ ያሰፈርኩት መወድስ ቅኔ “ደም አልባው ሰማዕት” ብለው መምህር ላዕከ ማርያም ከፃፉት ረጅም ግጥም ውስጥ የተወሠነው ክፍል ነው። በዚህ ተቆንፅሎ በወጣው ግጥም ውስጥ እንኳን በርካታ ሃረጐችን እናገኛለን። እነዚህ ሀረጐች አለቃ አያሌው ታምሩን ለመግለፅ የሚሞክሩ ናቸው። ለምሣሌ “የታሪክ መሠረት” የሚለው ሀረግ የአለቃ አያሌውን ማንነት ለመግለፅ የገባ ነው። “የተዋህዶ ብርሃን” የሚለው ሀረግም የእምነታቸውን ውጋግራ እና ጥልቅ አማኒ መሆናቸውን ያሣያል። አለኝታ ክንፋችን የሚለው ሀረግም የእውቀት ሃይላቸውን ሰጥተውን የሚያንቀሣቅሱን ሠው መሆናቸውን ለመግለፅ የገባ ነው። “የታሪክ መዘክር”፣ “የኢትዮጵያ ብርሃን”፣ “ሁሉ የሚያነበው”፣ “የተዋህዶ መጽሐፍ” ወዘተ እያሉ ገጣሚው አለቃ አያሌው ታምሩ ምን አይነት ሰው እንደነበሩ ሊገልፁ ሞክረዋል። ግን አለቃን ዘርዝረው ስለማይጨርሷቸው እንዲህ አሉ:- “አያሌው ታምሩ የምስጢር መፅሐፍ ነው!”

እውነት ነው፤ ሰውየው የምስጢር መፅሃፍ ናቸው፤ ነበሩ!

 

ኢትዮጵያ በታሪኳ ካፈራቻቸው ሀገርኛ አዋቂዎች ውስጥ ገናና ሆነው የሚጠሩት እኝህ የኃይማኖት እና የታሪክ ብሎም የባሕል ሊቅ፣ በዚህች ምድር ላይ ብቅ ብለው አያሌ ጉዳዮችን አበርክተው ያለፉ አባት ናቸው። ባለፈው ሣምንት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ይህችን አለም በሞት ከተሠናበቱ ስምንተኛ አመታቸው ነበር። እናም ትዝ አሉኝ። ብዙ ነገራቸውን ከህሊና ጓዳዬ እያወጣሁ አሰብኳቸው። አንዱ ይመጣል፣ ሌላው ይተካል። እኔም ቅድም ቅኔ እንደተቀኙላቸው ሠው አለቃን መግለፅ ተሣነኝ። የምስጢር መፅሐፍ ናቸውና! ግን ይህች ኢትዮጵያ የምትባልን አገር በጥልቅ በመውደድ እና ለክብሯም ራሣቸውን ከሚሠጡ ሰዎች መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሊቅ እንደነበሩ መናገር እችላለሁ።

 

አለቃ አያሌው ታምሩ ኢትዮጵያን ሲገልጽዋት “ምርጢቱ የእግዚአብሔር የግል ርስቱ” ይሏታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ይህችኑ ኢትዮጵያ እንዲህ ብለው ይገልጿታል፡- “የክርስቶስ ስረ ወጥ ልብሱ” ይሏታል። ሲያሻቸው ደግሞ “እንከን የሌለባት ስንዱ እመቤት” ይሏታል። እንግዲህ ፍቅር ነው! የኢትዮጵያ ፍቅር!

ለበርካታ ጊዜያት እና በበርካታ ጉዳዮች ቃለ-መጠይቅ ካደረኩላቸው ሰዎች መካከል አለቃ አያሌው ግንባር ቀደሙ ናቸው። እውነት ለመናገር የምሔደው ለቃለ-መጠይቅ ብቻ አልነበረም። ስለ ኢትዮጵያዊነት ለመማርም ጭምር ነው።  ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ምን ትምህርት ያስፈልገዋል? ሊባል ይችላል። ለነገሩ ከኢትዮጵያ መወለድ ብቻ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ያደርጋል ወይ?

 

ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል፣ ኃይማኖት አለማወቅ ሙሉ ኢትዮጵያዊ አያደርግም። ኢትዮጵያዊነት ከመወለድ በተጨማሪ ታሪኳን እና ማንነቷን ማወቅ እና መመስከር መቻልንም ይጨምራል። ለምሳሌ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የጀርመንን፣ የፈረንሣይን፣ የእንግሊዝን ወዘተ ዜግነት ለማግኘት ማመልከቻ ቢያስገቡ እና ማመልከቻቸው ተቀባይነት ቢያገኝ ከዚያም ፈተና ይሠጣቸዋል። ፈተናው ስለ ጀርመን ታሪክና ቋንቋ፣ ስለ ፈረንሣይ ቋንቋና ታሪክ፣ ስለ እንግሊዝ ቋንቋ እና ታሪክ ተፈትነው ማለፍ አለባቸው። ስለዚህ ዜግነት ማለት የዚያችን ሀገር ታሪክ፣ ባሕል፣ ማንነትን ማወቅ ጭምር ነው። ለዚህም ነው በውስጤ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከአለቃ አያሌው ዘንድ በተደጋጋሚ የምሔደው። እርሣቸው የታሪክ፣ የባሕልና የሐይማኖት ማሕደር ስለነበሩ ነው።

 

አንድ ቀን አጉል ጥያቄ ያቀረብኩላቸው መሰለኝ። እንዲህ አልኳቸው፡- “ሐይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው፤ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣልቃ አይገባም ይባላል። ሐይማኖት ሐገራዊ ጉዳዮች ላይ አይገባም፤ በእምነቱ ተቋም ብቻ ተወስኖ መንቀሣቀስ አለበት ይባላል፤ እርስዎ በዚህ ላይ የሚሉት ነገር አለ?  አልኳቸው።

 

አለቃ ተቆጡ። “ጥያቄው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መሰለኝ” አሉ። ቀጠሉና እንዲህ አሉ፡- ኢትዮጵያ እንደ ሐገር ፀንታ እንድትኖር ቤተ-ክርስትያን ዋነኛዋ ባልድርሻ ናት። ጠላት ሀገር ቢወር ሕዝቡ ሀገሩን ከጠላት እንዲከላከል ከማነሣሣት ጀምሮ ታቦቶቿን በየጦር ግንባሩ ይዛ በመሔድ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ ስትለምን የኖረች ቤተ-ክርስትያን ናት። ንጉስ ቢሾም ቃለ-መሐላ አስገብታ አጥምቃና ቀብታ የምታነግስ ይህች ቤተ-ክርስቲያን ነበረች። በመንግሥት ውስጥ ችግር ሲኖር መሐል ገብታ የምታረጋጋ እና ሰላም የምታሰፍን ቤተ-ክርስትያን ነበረች። ፊደል ቀርፃ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ብራና ፍቃ፣ ፅፋ የኢትዮጵያን ትውልድ ያስተማረች ይህችው ቤተ-ክርስትያን ነች። ዛሬ እንዴትና በምን ምክንያት ነው ይህችን ቤተ-ክርስትያን ማግለል የሚቻለው? ማን ነው ሐይማኖትና መንግሥት ግኑኙነት የላቸውም ያለው? የእስከ ዛሬ የነበረውን ውህደታቸውን ማን ነው የሚበጥሠው? እያሉ የተናገሩኝ ዛሬም ትዝ ይለኛል። በኋላም የፃፉትን ሣነብ እንዲህ ብለዋል፡-

 

“ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ስትሆን የታሪኳም መሠረት የቆመው፣ ጉልላትዋ የተደመደመው፣ አቃፊው፣ ጣርያው፣ ግድግዳው ሣይቀር በሃይማኖት ላይ ነው። ሃይማኖት በኢትዮጵያ ፊት ከአበው ቃል በቃል በአፍ፣ ኋላም ከካህናት፣ በነቢያት፣ ከሐዋርያት በመፅሐፍ ስለተሰጠ በኢትዮጵያ የጣኦት አምልኮ ስራ ላይ የዋለበት ጊዜ የለም። ስለዚህ ዛሬም ነገም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋች” በማለት አለቃ አያሌው ፅፈዋል።

 

አለቃ አያሌው ታምሩ ከ1983 ዓ.ም በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ አስተሣሰብ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡበትም ዘመን ነበር። ሐይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ከሚለው አስተሣሰብ ሌላ የኦርቶዶክስ ኃይማኖትም ከነፍጠኛው ጋር አብራለች የሚሉ ግለሰቦችም በአደባባይ ድምፃቸው የሚሠማበት ወቅት ነበር። ነፍጠኛው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩን ባንዲራ እያውለበለበ እና በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ድጋፍና አጀብ ነው ሌላውን የወረረው እየተባለ አስተያየት ይሰጥ ነበር። እንደውም ኢትዮጵያ የ100 አመት ታሪክ ነው ያላት የሚሉም እምነቶች ብቅ ብለው ነበር። እናም በሕይወት ካለው ኢትዮጵያዊ የዛሬ ሦስት ሚሊዮን አመት ሞታለች የምትባለው ሉሲ ትሻላለች ብለዋል።

 

ሉሲ ሞታም ቢሆን ኢትዮጵያ እንዲህ ነበረች፤ የሰው ዘር የፈለቀባት፣ ጥንታዊት ምድር፣ ብዙ ታሪክ ያለባት ሀገር ነች ትላለች። አሁን በሕይወት ያለው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ኢትዮጵያ መቶ አመቷ ነው ይላል። ታዲያ የሞተችው ሉሲ አትሻልም ወይ? የሚል አመለካከት ያንፀባረቁበት ወቅት ነበር አለቃ።

 

እኚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን የሊቆች ሊቅ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ የተወለዱት መጋቢት 23 ቀን 1915 ዓ.ም ሲሆን ቦታውም በምስራቅ ጐጃም ዞን፣ እነማይ ወረዳ በታላቁ ደብረ ድማኅ /ዲማ/ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን፣ ልዩ ስሙ ቤተ-ንጉስ በተሰኘ ቦታ ነበር። የአለቃ አባት አቶ ታምሩ የተመኝ  ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ አሞኘሽ አምባዬ ይባላሉ።

 

አለቃ አያሌው ገና የሦስት አመት ተኩል ሕፃን ሣሉ ዲማ አካባቢ የፈንጣጣ በሽታ ገብቶ ስለነበር በዚህም ምክንያት ሁለቱም ዐይኖቻቸው ታወሩ። ቤተሰቦቻቸውም አዘኑ። መልከ መልካሙና ተወዳጁ ልጃቸው ገና የዚህችን አለም ገፅታ ሊመለከት እንቡር እንቡር እያለ በሚነቃቃበት በጮርቃ እድሜው ዐይነ-ስውር ሲሆንባቸው ወላጆች ክፉኛ አዘኑ። ሕፃኑ አያሌው ታምሩ ያንን የዲማ ጊዮርጊስን የቅኔ ዩኒቨርሲቲን ያየው በሦስት አመት ተኩል እድሜው ነው። የዲማን ተራሮች፣ የዲማን ሸለቆዎች በዐይኑ እያየ ባያድግም፣ ነገር ግን በዲማ የትምህርትና የቅኔ መንፈስ ተሞልቶ ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን የዕውቀት ብርሃን አብርቶ ያለፈ ሊቅ ሆኗል።

 

ዲማ ጊዮርጊስ የታላቁ ደራሲ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘው ብርቅዬ መፅሃፋቸው ታሪኩ የሚገኝባት ስፍራ  ነች። የሥነ-ፅሁፍ ሰዎች  “መቼት” ይሉታል ታሪክ የተፈፀመበትን ስፍራ። እናም የፍቅር እሰከ መቃብር መፅሐፍ ዋነኛው መቼት ዲማ ጊዮርጊስ ነው። የፊታውራሪ መሸሻ ቤት፣ የነ ሰብለ ወንጌል መታያ መድመቂያ፣ የበዛብህ መምህርነት፣ የካሣ ዳምጤ /የጉዱ ካሣ/ የለውጥ አቀንቃኝነት እና ፍልስፍና ተምነሽንሾ የታየባት ድንቅ ስፍራ ነች። ጉዱ ካሣ የስርአትን መፍረስና እና መቀየርን በተምሣሌት አድርጐ የተፈላሰፈባት ቦታ ዲማ ጊዮርጊስ ነች። ዲማ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ መቼት ውስጥ ደምቃ መታየቷ ብቻ ሣይሆን እንደ አለቃ አያሌው ታምሩ አይነት የእውነታው አለም ሊቅ የፈጠረች የቅኔ ምድር ነች።

 

ዐይነ ስውሩ /ግን/ “ልበ ብርሃኑ” አለቃ አያሌው፣ በ1920ዎቹ ዓ.ም የኢትዮጵያን የቤተ-ክህነት ትምህርት መማር ጀመሩ። /በነገራችን ላይ አለቃ አያሌውን “ልበ ብርሃን” ያሏቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ናቸው/። ትምህርት ከጀመሩ በኋላ አእምሯቸው ክፍት እና ጠያቂ ተመራማሪ ሆነ። በትምህርታቸውም የሀዲሳትን ጣዕም ትርጓሜ፣ ከብሉያት አራቱን ብሔረነገስት፣ ትርጓሜ ዳዊት ከነቢያት እና ከሰለሞን ጋር የውዳሴ ማርያም እና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ተምረዋል። ከዚያም በ1939 ዓ.ም አጐታቸውን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ መጡ። አጐታቸው ራሳቸው በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ዘመን አይሽሬ የፅሁፍ ቅርሶችን አበርክተው ያለፉ ናቸው።

 

አዲስ አበባም መጥተው በቅድስተ ስላሴ መንፈሣዊ ት/ቤት ገብተው መፅሃፈ ኢሳያስን፣ መጽሐፈ አስራ ሁለቱን፣ ደቂቀ ነብያትን፣ መጽሐፈ አስቴርን፣ መጽሐፈ ዮዲትንና መጽሐፈ ጦቢትን ከነ ሙሉ ትርጓሜያቸው ተምረውም ከመጨረሳቸው በተጨማሪ በዳግማዊ ምኒሊክ መታሠቢያ ት/ቤት ገብተው፣ ስምንቱን ብሔረ ኦሪት እና መጽሐፈ ዳንኤልን ከነ ትርጓሜያቸው ከዚያም የአርባአቱን ወንጌል ትርጓሜ፣ መጽሐፈ ኪዳን እና ትምህርተ ኅቡአትን ተምረዋል። አለቃ አያሌው በቤተ-ክርስትያኒቱ ውስጥ የሚሠጡትን ትምህርቶች አንድ በአንድ ያጠኑ የእውቀት ማሕደር ሆነው በ1940ዎቹ ውስጥ ብቅ አሉ።

 

ከዚያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖት ውስጥ የሚጠየቁ የበዐላት፣ የአጿማት፣ የአምልኮ፣ የፀሎት እና የልዩ ልዩ ጥያቄዎችን መልስ ከነ ማብራሪያው በመስጠት አለቃን የሚተካከላቸው ጠፋ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ገብተው ከመጀመሪያዎቹ የግብረ ገብ መምህራን አንዱ ለመሆን በቅቷል። አለቃ አያሌው ኢትዮጵያን እና እምነቷን፣ ባሕሏን ታሪኳን የተመለከቱ ማናቸውንም ጥያቄዎች ሰፊ ትንታኔ በመስጠት በሬዲዮ፣ በጋዜጣ፣ በልዩ ልዩ ዐውደ ምህረት እና በጉባኤዎች ላይ በማብራራት የዕውቀት ብርሃን ረጩ።

 

አለቃ አያሌው ታምሩ ከሰኔ ወር 1948 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ተመርጠው የስብከተ ወንጌል ክፍል አባል ሆነው አገልግለዋል። በመቀጠልም ከጠቅላይ ቤተ-ክህነት መንበረ ፖትርያርክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን የሊቆች ሊቅ /ሊቀ ሊቃውንት/ተብለው የሊቃውንት ጉባኤው ኘሬዘዳንት ለመሆን በቅተዋል።

 

ከ50 አመታት በላይ በሊቅነታቸው ከማገልገላቸውም በተጨማሪ ከ11 በላይ መፃሕፍትን ደርሰዋል። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

 

1.  የመኮንን ጉዞ /1948 ዓ.ም/

2.  የአንበሳ ዱካ /1953/ ዓ.ም

3.  መቸ ተለመደና ከተኩላ ዝምድና /1953 ዓ.ም/

4.  የኢትዮጵያ እምነት በሶስቱ ሕግጋት /1953 ዓ.ም/

5.  የኑሮ መሰረት ለሕፃናት /1953 ዓ.ም/

6.  ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ /1979 ዓ.ም/

7.  የጽድቅ በር /1979 ዓ.ም/

8.  ምልጃ እርቅና ሰላም /1992 ዓ.ም/

9.  ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ /1993 ዓ.ም/

10. መልዕክተ መንፈስ ቅዱስ /1995 ዓ.ም/

11. ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመአምላክ እና ሌሎችንም ፅፈዋል።

አለቃ አያሌው ታምሩ በ1988 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን አገልግሎታቸው እንዲገለሉ የተደረጉት ዛሬ በሕይወት ከሌሉት የቤተ-ክርስትያኒቱ ፓትሪያክ ከነበሩት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ነው። አቡነ ጳውሎስ  ወደ ሮም ሔደው በቤተ-ክርስትያናችን ለብዙ ዘመናት በውግዝ የኖረን ስርአት አፍርሠዋል በሚል ምክንያት አለቃ ተቃውሟቸውን አሠሙ። በዚህ በተቃውሞ ፅናታቸው ከስራ ገበታቸው ለ11 አመታት ተገልለው በቤታቸው ቁጭ እንዳሉ ግን ሺዎችን እያስተማሩ ነሐሴ 14 ቀን 1999 ዓ.ም በ84 አመታቸው ሕይወታቸው አልፋለች።

አለቃ አያሌው ታምሩ 11 አመታት እቤታቸው ሲውሉ አንዱንም ቀን ካለ ስራ አላረፉም። በርካታ ጋዜጠኞች፣ አጥኚዎች፣ ትምህርት ፈላጊዎች.. ከማይጠገበው ከአለቃ አንደበት በየቀኑ እውቀትና መረጃ ይሰበስቡ ነበር። በአለቃ አያሌው ዘመን የነበረ ጋዜጣ ወይም መፅሄት ከእርሣቸው ጋር ሁሉም ማለት ይቻላል ቃለ-መጠይቅ  አድርጓል።

 

እነዚህን ጋዜጦችና መጽሔቶች መሠረት በማድረግ ሣሙኤል ኃይሉ የተባለ አድናቂያቸውና ወዳጃቸው ትምህርተ ሃይማኖት በሚል ርዕስ መፅሐፍ አሣትሞላቸው በትውልድ ውስጥ ሕያው አድርጓቸዋል። በቅርቡ ደግሞ የመጀመሪያ ልጃቸው የሆኑት ወ/ሮ ስምረት አያሌው አባቴ እና እምነቱ በሚል ርዕስ የአለቃን ስብዕና የበለጠ አግዝፎ  የሚያሣይ ግሩም መፅሐፍ አሳትመዋል። ልጅ መውለድ ትርጉሙ ይሀ ነው። አባት በልጅ ሲዘከር፤ ግሩም ሥነ-ፅሁፍ ነው። አለቃ አያሌው ገና ብዙ የሚፃፍላቸው የኢትዮጵያ ማህደር ናቸው።

 

አንድ ቀን ለረጅም ሰአታት ብዙ ሐይማኖታዊ ባሕላዊ የኢትዮጵያን ጉዳዮችን አጫወቱኝ። በጣም ተመሰጥኩኝ። ገረመኝ። ግን ሣላስበው አንድ አስደንጋጭ ጥያቄ አቀረብኩላቸው። እንዲህ አልኳቸው፡- “እርስዎ  ዐይነ ስውር በመሆንዎ ያጡት ነገር አለ? ዐይነ ስውርነትዎ ይቆጭዎት ይሆን? አልኳቸው። የሚከተለውን መለሡልኝ፡-

$1-          አንድ ቀን የሆነ ጉዳይ አበሳጨኝ። ተነሳሁና ወደ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘንድ ወደ ቤተ-መንግሥት ሔድኩ። ቤተ-መንግሥቱ ለኔ ሁሌም ክፍት ነበር። ገባሁ። ከጃንሆይ  እልፍኝ  ደረስኩ። ጃንሆይም  ቁጭ ብለዋል። ምን እግር ጣለህ አሉኝ። እኔም እጅ ነስቼ፡- “ጃንሆይ የሚሠራው ስራ ሁሉ ልክ  አይደለም  አልኳቸው። ምኑ? አሉኝ። ወጣቱ  ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያን በቅጡ ሳያውቅ ወደ ባሕር ማዶ እየተላከ አንዱ  የአሜሪካንን  ባሕል፣ አንዱ የሞስኮን  ባሕል፣ ሌላው የእንግሊዝን፣ ሌላው  የፈረንሣይን  ወዘተ  እየተማረ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ የተማረበትን  ሀገርና  ባህል አስተሣሰብ  ኢትዮጵያ ላይ ካልጫንኩ ይላል። ይሔ ደግሞ ለኢትዮጵያም ሆነ ለእርስዎ  አደጋ ነው። ጃንሆይ ይህ ጉዳይ መስተካከል አለበት። ነገ አደጋ ይመጣል! አልኳቸው። ጃንሆይ ዝም አሉኝ። መልስ እልሰጥ አሉኝ። ቢቸግረኝ እጅ ነሣው። ከዚያም፡- “እንኳንም አይንህ ጠፋ!”  አሉኝ።

ጃንሆይ  ልክ  ነበሩ።  እኔ  አሁን  የኢትዮጵያን  መቸገር፣  መከራ፣  ስቃይ  ስሰማ  እንኳንም ዐይኔ ጠፋ እላለሁ። ባለማየቴ አይቆጨኝም።

ይምረጡ
(21 ሰዎች መርጠዋል)
13462 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us