ንባብ እና ህልውና

Wednesday, 02 September 2015 12:58

በጥበቡ በለጠ

ንባብ የሰውን ልጅ ከሌሎች እንስሳት የሚለየው ጉዳይ እንደሆነ በዘርፉ ላይ የጻፉ ሰዎች ሲያወሱት ይደመጣል። እኔም ደግሞ(የ2007 እና 2008 ዓ.ም) የንባብ አምባሳር ተብዬ በመሾሜ ስለ ንባብ ዝም ብል እወቀስበታለሁ። የንባብ አምባሳደሮች ተብለን የተሾምን ቀን በእውቀቱ ስዩም እንዲህ አለ፡- እኔ በልጅነቴ ሳድግ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር እሆናለው ብዬ ነበር፤ ይሔው ሳድግ የንባብ አምባሳደር ሆንኩ። ሩቅ አሳቢ…… እያለ አስቆናል።

ለካ መሾም ታላቅ ኃላፊነት ነው። በዚህች ሹመቴ ምን ሰራሁ እያልኩ አስባለው፤ አበዛኸው ካላላችሁኝ ደግሞ እጨነቃለሁ። ግን የመንግስት ሹመኞችም እነደዚህ ይጨነቁ ይሆን?

 

እኔ ግን ለሹመቴ መልስ ትሆን ዘንድ አብነት ስሜ ንባብን አስመልክቶ ንባብ ለህይወት የመጻህፍት አውደ-ርእይ ላይ ያቀረበውን ንግግሩን ባካፍላችሁስ፤ አብነት ማን ነው ብላችሁ ለምትጠይቁኝ ደግሞ ወዳጄ ነው፤ በስራው በጣም አድናቂው ነኝ፤ አብነትም ይህ ነው ልበላችሁ፡-

 

 • በ1989 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ የባችለር ኦቭ ኦርትስ ዲግሪውን በማዕረግ አግኝቷል።
 • - በ2002 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ Historical and Comparative Linguistics (በታሪካዊ እና ንጽጽራዊ ሥነልሳን) የማስተርስ ዲግሪውን ተቀብሏል።
 • - በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በGeneral Linguistics and Comparative Linguistics (አጠቃላይ ሥነልሳን) መርሐግብር በታሪካዊና ንጽጽራዊ ሥነልሳን   (Historical and Comparative Linguistics) የዶክትሬት ዲግሪውን አየሠራ ይገኛል።
 • - በዩነኒቨርሲቲ ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ላለፉት 15 ዓመታት በአስትሮኖሚ፣ በአስትሮሎጂ፣ በቋንቋ እና በሥነጽሑፍ ጥናት እና ምርምሮችን ሲያደርግ ቆይቷል።
 • - ለማስተርስ ዲግሪው”ጌ” በተሰኘው የሴማዊ ቋንቋዎች ምእላድ ላይ ያደረገው ጥናት ቪዲኤም በተባለ የጀርመን አሳታሚ በ2002 ዓ.ም ላይ ታትሞለታል።
 • - ብሪል የተባለ የላይደን አሳታሚ ‘The Body in Language’ የተባለ መጽሐፍ በ2007 ዓ.ም አሳትሟል። በዚህ መፍሐፍ ውስጥ የተካተተው ሁለተኛው ምእራፍ የአብነት ስሜ ጥናት ነው።
 • - ለቢአ ዲግሪ ማሟያው ያደገው ጥናት የአማርኛ የመዚያ ግጥሞች ቅርጻዊ ትንተና ነው። የዚህን አጠር ያለ ዘገባ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1989 በሚያዚያ 5 እና 9 እትም ላይ አቅርቦታል።
 • - በ1991 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተካሔደው የቋንቋዎች ጥናት ኮንፍረንስ ላይ “በአማርኛ ግጥሞች ውስጥ በአናባቢ ቤት የመምታት ስልት” በሚል ርእስ ጥናት አቅርቧል።
 • - በ2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተካሔደው የቋንቋዎች ጥናት ኮንፍረንስ “የጉዱ ካሳ ኮበብ” በሚል ርእስ አንድ ጥናት አቅርቧል።
 • - በ2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ኮንፍረንስ ላይ Grammaticalizing Words and Dying Stars: A Sketch of Analogy የተባለ ጥናት አቅርቧል።
 • - በ1999 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሦስት ተከታታይ መድረኮች “የኢትዮጵያ ኮከብና ሦስተኛው ሚሌኒየም” የተሰኘ ጥናት አቅርቧል።
 • - ለብዙኃን አንባቢያን ያቀረባቸው መጻሕፍት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ- የኢትዮጵያ ኮከብ /ጥቅምት 2006/ በዚህ መጽሐፍ በአስትሮኖሚና በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በ21ኛው ምእተ ዓመት የኢትዮጵያ መጻኢ እድል ተተንብዮአል።

 

2ኛ- ፍካሬ ኢትዮጵያ /ጥቅምት 2007/፡- የዚህ መጽሐፍ መሠረቱ አስትሮሎጂ ቢሆንም አካሄዱ ግን ኤትኖግራፊያዊ፣ ሥነሰብአዊ፣ ሥነልሳናዊ እና ሥነጽሑፋዊ ነው። በአገራዊ ምሳሌዎች ከተብራሩ ከ12 የሰው ልጆች ባሕርያት በተጨማሪ የፍቅር እስከመቃብር ገፀባህርያት ውክልና እና ኮከብ ተተንትኖበታል።

 

3ኛ- የቋንቋ መሰረታዊን /ሰኔ 2007/፡- ይህ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማስተማርያነት ሲያገለግል የቆየ መጽሐፍ ነው። ከቋንቋ ጥንተ አመጣጥ እስከ ሥርዓተ ጽሕፈት ያሉ እሳቤዎች ተብራርተውበታል።

 

4ኛ- ሳይኪ እና ኪዩፒድ/ሐምሌ 2007/ ፡-ይህ መጽሐፍ ከ7-17 የእድሜ ክልል ላሉ ሕጻናት እና ወጣቶች የተዘጋጀ የ10 ተረቶች የ500 አንቆቅልሾች እና የአንድ የእንግሊዝኛ ልቦለድ መድብል ነው።

 

5ኛ- ጠቢባን ምን አሉ / በነሐሴ 2007 የሚወጣ/፡- ይህ መጽሐፍ ፍቅር እና ትዳርን በመሳሰሉ 44 ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የዓለም ጠቢባን የተናገሯቸው እና የጻፏቸው ናሙና ጥቅሶች ጥንቅር ነው።

 

አብነት የዶክትሬት ዲግሪውን በመጪው ዓመት ያጠናቅቃል።  

አብነት ስሜ ንባብና ህልውና ብሎ የቀረበውን ንግግሩን እነሆ እላለሁ፡-

 

ዕውቀት ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው ደመነስፍሳዊ፣ ሁለተኛው ኢ-ደመነፍሳዊ ነው። ደመ-ነፍሳዊ ዕውቀት በዘር ወይም በደም የሚወረስ ነው። ይህን ዕውቀት እንስሳትም አራዊትም፣ ሰዎችም ከወላጆቻቸው ይወርሱታል። ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት አይመረጥም፣ አይሻሻልም። ይሻሻል ቢባልም ተፈጥሮ ብዙ ሺህ ዓመታትን መውሰድ አለባት።

 

ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት በዘር ወይም በደም አይወረስም። ይህን ዕውቀት የምናገኘው በትምህርት ነው። ትምህርት ደግሞ በመስማት፣ በማየት እና በማንበብ ነው የሚገኘው። እንስሳትና አራዊት ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀትን ሊያገኙም ሆነ ሊኖራቸው አይችልም። ቢያገኙና ቢኖራቸውም በጣም የተወሰነና እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም።

 

የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለየው ከተወለደ በኋላ በሚያዳብረው ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት ነው። የሰው ልጅ ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት ለብዙ ዘመናት ሲጠራቀም ቆይቷል። ከትውልድ ወደ ትውልድም በቃል እና በጽሑፍ ሲተላለፍ ቆይቷል። የሰው ልጅ አሁን የደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ የዚህ ውጤት ነው። ይህን ዕውቀቱን በአንዳች ሰበብ ቢያጣ ከዛሬ 10 እና 20 ዘመን ወደ ነበረበት የዋሻ ውስጥ ኋላ ቀር ኑሮ ይመለሳል።

 

ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት ሰዎችን ከእንስሳት እንደሚለየው ሁሉ፣ ሰዎችንም ከሰዎች ይለያል። የምእራቡ ዓለም ሰዎች ከእኛ ከአፍሪካዊያን የሚለዩት ባጠራቀሙት ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት ነው። ስለዚህ ሰው ከእንስሳ የሚበልጠውን ያህል ምእራባዊያን ደግሞ አፍሪካዊያንን ይበልጣሉ።

 

አሁን የበላይ የሚሆን ሁሉ የበለጠ ዕውቀትና ጥበብ ያለው ነው።

ፍጥረትና ጀግንነት የበላይ ቢያደርጉ ኖሮ አንበሳና ነብር ከምድረ ገፅ ላይ እየጠፉ ያሉ አራዊት አይሆኑም ነበር። ጉልበትና የዋህነትም የበላይ እንደማያደርጉ አህያ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች።

 

ስለዚህም ጀግና እና ጉልበተኛ ከመሆን ይልቅ ጥበበኛ መሆን ነው የሚያዛልቀው። ጥበበኛ ለመሆን ደግሞ ዕውቀትን እየተንገበገብን እና እየተስገበገብን መብላት ነው። መጻሕፍትም የዕውቀት ማህደር እና አገልግል ናቸው።

 

የምዕራባዊያንን እና የአፍሪካዊያንን ልዩት ባነበብነው የመጻሕፍት ቁጥር ማስቀመጥ ይቻላል። በህይወት ዘመኑ ሁሉ ምንም ያላነበበ ፈረንጅ አፍሪካዊ ይሆናል።

 

አህያን እና አህያን እንደመሰሉት እንስሳት በፈረንጅ እንዳንገዛ ማንበብ እና መላቅ አለብን። ነብርን እና እሱን እንደመሰሉት አራዊት ከመድረ ገጽ እንዳንጠፋ ማንበብና ጥበበኛ መሆን አለብን።

 

ንባብ፣ ዕውቀት እና ጥበብ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን የህልውና ጉዳይ ነው። ካላነበብን እንጠፋለን። ማንበብ፣ ማወቅና መሰልጠን የፋሽን ጉዳይ አይደለም። የሞትና የህይወት ጉዳይ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው።

 

አንድ ትርኳት (anecdote) ላካፍላችሁ።

ሰውየው ነጋዴ ነው። ከሩቅ ሀገር ቆይቶ ሲመለስ የሆነ ነው። አጋሰሱን ይዞ ወንዝ ሊሻገር ባለበት አንድ ባህታዊ ከአሸዋ ውስጥ ተቀብሮ ሲፀልይ ያገኘውና በብዙ ይደበድበዋል። የልቡን ካደረሰ በኋላ፣ ባህታዊው “የሆነስ ሆነና ምን አድርጌህ ነው እንዲህ የደበደብከኝ? ይለዋል። ነጋዴውም፣ “እናንተ እያላችሁ በዬት በኩል እንፀድቃለን?” ይለዋል።

 

ባህታዊው ለፅድቅ የተንገበገበ ነውና ቀንና ለሊት በጋና ክረምት ይፀልያል። ነጋዴው ግን ለዚህ ጊዜ የለውም። ባመት ወይ አንዴ ወይ ሁለቴ ፈጣሪውን ቢያስብ ነው።

 

የነጋዴውና የባህታዊው ልዩነት በፈረንጅና በኢትዮጵያዊ መካከል ካለው ልዩነት ጋር ይመሳሰላል። ፈረንጅ ቀንና ለሊት፣ በጋና ክረምት ሳይል እየተንገበገበ ያነባል፣ ዕውቀትን ያግበሰብሳል፤ ይሠራል፤ ይጠባበል፤ እናም ይበልጠናል። እኛ ለዚህ ጊዜ የለንም። ስለዚህ ፈረንጅ እያለ ማደግ አንችልም ማለት ይሆናል። ያ ግን ምርጫችን ነው። ፈረንጅን ማጥፋት አንችልም። መብለጥ ግን እንችላለን። በጉልበትና በድፍረት የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ነው። ልዩነት የሚመጣው በዕውቀትና በብልጠት ነው። በድፍረቱም ሆነ በጉልበቱ የሚመካ ይጠፋል። ዕውቀትን የሙጥኝ ያለ ግን ይኖራል። ባለ ዕውቀት የሆነው የሰው ልጅ እንስሳትን ገዝቶ፣ አራዊትን አጥፍቶ ወይም አሸንፎ ይኖራል።

 

ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀት አይወረስም። በደም ወይም በዘር አይተላለፍም። የዚህ ጥሩ ማስተላለፊያው መጽሐፍ ነው። የአንድ ሳይንቲስት ልጅ ሲወለድ ያባቱን አንድም ዕውቀት ይዞ አይወለድም። የሳይንቲስቱ ልጅ እና የአንድ ማይም ልጅ እኩል አላዋቂ ሆነው ነው የሚወለዱት። አንዱ ካንዱ የሚበልጠው በንባብና በትምህርት ብቻ ነው። የማያነብ ሀገር ህልውናው አደጋ ላይ እንደሆነ መታወቅ አለበት ባይ ነኝ።

 

ኢ-ደመነፍሳዊ ዕውቀትን ደግሞ የምናስተላልፈው መጻሕፍትን በመጻፍ ነው። ልጅ በመውለድና መጽሐፍ የምናስተላልፈው ያው ዕውቀትን ነው።n

ይምረጡ
(13 ሰዎች መርጠዋል)
18249 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us