ከዋሽግተን ዲሲ ለአፄ ኃይለ ስላሴ የተጻፈ ደብዳቤ

Wednesday, 09 September 2015 14:00

በ1952 በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ድንቄ በኢትዮጵያ የነበረው ስርዓት ለውጥ መለወጥ እንዳለበት በማመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጻፉትን ደብዳቤ ከተጠቃሹ ቤተሰብ በማግኝታችን ለታሪክ እንደ “ሰነድ” ያገለግል ዘንድ አቅርበነዋል።

ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

አዲሰ አበባ

ግርማዊ ሆይ፡- በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሕይወት የሚታየውን ምሬትና ግፍ፣ በፍትሕም መጓደል ምክንያት የሚደርሰውን የአስተዳደር በደል ስለመለከት ወደ አገሬ ለመግባት ያለኝን አሳብ ማቆየት ግድ እንደሆነብኝ ለግርማዊነትዎ መግለጥ አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል። ይህ ሁኔታ የሚታረምበትን በሕብረት ለመሥራት ባንሞክር ታላቅ ብጥብጥ እንደሚያስከትልብን ከታሪክ መማር ካልቻልን ከተከታዩ መቅሰፍት የምናመልጥበትና የምንከለልበት ሰው ሰራሽ ዘዴ ይገኝለታል ብሎ ራስን መደለል በሕልም ዓለም ውሰጥ ለመኖር እንደመሞከር ይቆጠራል። ከዚህም በቀር ለተተኪው ትውልድ አቋም ይሆናሉ ብለን ተከባክበን ልናሳድጋቸው አላፊነት ያለብንን ሕፃናትና ውለታ ትተው ለማለፍ የተዘጋጁትን ሽማግሌዎቻችንም ደህና ዕረፍት እንዳያገኙ ከአገሪቱ በተፈጥሮ ምክንያት በፈፀምነው ስሕተት ታሪክ ምሕረት ሊያደርግልን በፍፁም አይችልም።

 

ይህን የመሳሰለው ሁኔታ በብርቱ የሚያሳስበን መሆኑን ስንገልጥ ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች “አንተ ምን አገባህ” በማለት በጉዳዩ ባለቤትነት ክፍያ ድርሻችንን ለማሳነስ ቢሞክሩም በኢትዮጵያዊነት ትክክለኛ መብት ላይ አጥብበው ያስመሩትን የወሰን ክልል አሜን ብሎ ለመቀበል ከቶ ስለሚያስቸገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አላፊነቱን የማስወረድ ተግባር እንዳለበት አይካድም። እኔም ይህን ምክንያት አድርጌ በአሁኑ የመንግሥት አስተዳደር የደረሰውን ሕገ ወጥ አፈፃፀም ሁሉ ለማረምና ፍትህን ለማደላደል የሚቻልበትን አሳብ በነፃ ለመግለጥ ስል እውጭ አገር መቆየትን መረጥሁ።

 

በአሁኑ አያያዝ እንዲቀጥል የተተወ እንደሆነ በኢትዮጵያ የወገን መለያየትና የደም መፋሰስ እንደሚያሰጋ የመላው ኢትዮጵያውያን ግምት የወደቀበት ነው። ዋናው አላማ ይህ እልቂት የሚወገድበት መድኃኒቱ ምንድነው? ለተባለው ጥያቄ ለመመለስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። መቸም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚመስለውና በማያምንበት ረገድ መልሱን ለመስጠት ሞክሯል። አሁን የጐደለ መስሎ የሚታየው ከዙፋኑ በኩል የሚጠበቀው ይሁንታ ብቻ ነው። ነገሩን በመጠኑ ለማብራራት ያህል  በሚከተሉት መስመሮች አሰተያተቴን ለመግለጥ እሰነዝራለሁ።

 

የኢትዮጵያ ሕዝበ ለዙፋኑ የሰጠው ልባዊ አክብሮት ዘላቂ ሆኖ በታሪካዊ ቅርስነት እንዲጠበቅ በቤተ መንግሥቱ በኩል አልታሰበበትም ለማለት ያስደፍራል። ባለፈው “መለኮታዊ መብት” የተባለው የዘውድ ቴዎሪ የተሳሳተ መሆኑን ቢረዳውም፣ ሕዝቡ ዘውዱን ታሪካዊ ሲምቦል ወይም ምሳሌ አድርጎ በክብር ሊያኖረው ሲፈቅድ ወደ መለኮታዊ መብት አስተያየት እንደገና እንዲመለስና ጣኦታዊ ስግደት እንዲያደርግ ማስገደድ በእክል ዘውዱን ለማስረገጥ ካልሆነ በቀር ለሌላ አያገለግልም። ጃንሆይ ባለዘውድ፣ አስተዳዳሪ፣ ሕግ አውጭ፣ ዳኛ፣ ምስለኔ፣ ፖሊስ፣ ጭቃ ሹም ሆኜ ልሥራ ሲሉ፣ በሃያኛው ክፍለዘመን የሚገኝ ሕዝብ ይህን መብት አጠቃሎ በፈቃዱ ለዘውዱ ብቻ ይለቃል ማለት የማይታመን ነው። መቸም እየተደጋገመ የሚሰጠው ምክንያት “ሕዝቡ አላፊነትን ለመቀበል አልደረሰም” የሚል መሆኑን በየጊዜው ሰምተናል። በእውነቱ ከአፍሪካና በኤሻ ሕዝብ መካከል አልደረሰም ተብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ  መፍረድ ይገባልን? ደግሞስ ያለ መድረሰ ትርጓሜው ምንድነው? ምናልባት የማሰብ የመምረጥ፣ የማመዛዘን፣ የመፍረድ ሌንሰ አልተፈጠረለትም ማለት ነው? እንደዚህማ ከሆነ በ3000 ዘመን ውስጥ ለዚህ ሕዝብ ጭንቅላት ሆኖ ያሰበለት፣ ዓይን ሆኖ ያየለት፣ ጆሮ ሆኖ የሰማለት የዛሬው ዘውድ ነው ማለት ነዋ! የሚፈተነው ይህን የመሰለ አስተያየት ለማቅረብ እንደሆነ ምሕረት የሌለው በደል ነው።  ይልቁንስ ጃንሆይ የሕግ ጠባቂነትን ልብስ ተጐናፅፈው በዚህ መንፈስ ፍትህን ከሚያጓድሉ ሥልጣኑን ለሕዝብዎ ሰጥተው እርሱ ቢጨነቅበት እንደሚሻል ጥርጥር የለውም። ያለዚያ ከዚህ ማስታወሻዬ ውስጥ ለስማቸው እንኳ ሥፍራ ለመስጠት ዋጋ የሌላቸውና ሕሊና ቢሶች የሚያቀርቡልዎትን “ደህና ታይቷል” እያሉ ፍትሕን ለግል ስሜት መወጫ ማድረግ የቱን ያህል ለትውልድ መተዛዘቢያ ሆኖ እንደሚኖር የተሰወረ ሊሆን አይችልም።

 

ይህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ለማሻሻል የሚቻለው ጃንሆይ ዘውድን ለራስዎ አስቀርተው አስተዳደሩን ለሕዝብ በመስጠትና የዴሞክራሲን መንፈስ በማስገባት ነው። ነገር ግን ይህ አስተያየት ለግርማዊትዎ ሰውነት አለርጂ ሆኖ ቢያስቸግርዎ እንኳ ሌላ ማማረጫ ይኖራል። ይኸውም ዘውዱን ለልዑል አልጋ ወራሽ ማስተላለፍና አብዲኬት ማድረግ ነው። እርሳቸው ሕገ መንግሥትን ጠብቀው ለመኖር ፈቃደኛ እንደሆኑ አያሌ ሰዎች ሲመሰክሩላቸው ሰምቻለሁ። ያለዚያ ተከታዩ ትርምስና ደም መፋሰስ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

 

ይህ አቤቱታ ከኔ ብቻ የቀረበ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርሃት ታፍኖ ነጋም መሸም የሚያጉመተምተው ይህንኑ ነው። ድምፁን ከፍ ለማድረግ ግን አካባቢው አልፈቀደለትም። እኔም ከርሱ የተለየሁ መስዬ ታይቼ እንደሆነ ያጋጣሚ ነገር ብቻ ነው። አዲስ አበባ የታፈንኩትን ያህል እዚህ ከተነፈስሁ በኋላ ወደ አገሬ እንድመለስ ተስፋ አደርጋለሁ። ምናልባት ይህን አቤቱታ በመጻፌ እንደወንጀል ይሆናል። ግድ የለም። የሆነ ሆኖ በትእዛዝ ሳይሆን በነፃ የሚፈርድና በግልጥ የሚያስችል ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ራሴን በሕጋዊ ጠበቃ አማካይነት ለመከላከል ጃንሆይ የሚፈቅዱልኝ ከሆነ በአገሬ ውስጥ ለመተንፈስ ዕድል ተሰጠኝ ማለት ነው።

 

ከዚህም ሁሉ ጋራ ላስተውስ የምፈቅደው ይህን ማስታወሻ በመፃፌ ተቀይመው የኔን ሕይወት ለማስጠፋት በሺ የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም። አዝናለሁ። እኔ ለሞት የተዘጋጀሁ ስለሆነ ገንዘቡ ባይባክና ለነፍስ ገዳይ በመስጠት ፈንታ ለጦም አዳሪ ችግረኛ ቢውል የበለጠ እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም። በበኩሌ በአገራችን ሬቮሉሽን እንዲነሳና የማንም ደም “እንዲፈስ” አልፈቅድም።  በዚህ ባቤቱታዬ የምወተውተውም ሰላማዊ ለውጥ እንዲሆንና የምንፈራው ደም መፋሰስ እንዳይደርስ ስለሆነ ጃንሆይ አንድ ቀን “ለካ ብርሃኑ ውነቱ ኖሯል” ሳይሉ አይቀርም።

 

እንኳን ዘውድ የጫነ ሰውነትንና ማናቸውንም ሰው የማክበር ልምድ ስላለኝ ይህ አቀራረቤ ክብርን ለመድፈር እንደማያስቆጥርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እውነት ሁል ጊዜ መራራ ናት። የመድኃኒት ፈውስ እንጂ ምሬት አይታሰብም እንደተባለው ይህ በቅን ልቡና የቀረበው እውነተኛ አቤቱታዬ የግርማዊነትዎን ልብ አራርቶ ለኢትዮጵያ ማህበራዊ ሕይወት አንድ ፈውስ እንዲመጣለት ተስፋ አደርጋሁ።

 

ጃንሆይ በኢትዮጵያ ወጣቱ፣ ሽማግሌው ሴቱ፣ ወንድ የአኗኗሩ ዘዴ ውሉ ተዘባርቆበታል። አምላካችን፣ ፈጣሪያችን አያለ ቢደልልዎት አይመኑት። ጨንቆት ነው። ከልብ የሚመርቅዎት ግን ራስክን አስተዳድር ብለው አርነት ሲያወጡትና ወደ ዲሞክራሲ ሲመሩት ነው። ይህንንም ስል ሕዝብ በራሱ ሲተዳደር ችግር አይገጠመውም ማለቴ አይደለም። እስከዚህ አልሳሳትም። ነገር ግን ሌላው ገፍቶ ከሚጥለውና ላንሳህ ከሚለው፣ ራሱ ወድቆ በራሱ መነሳትን ይመርጣል። ይኸም ከሥሕተት መማር ይባላል። ስለዚህ ጃንሆይን ተሳሳቱ እያለ ከሚከስዎት እርሱ በስሕተቱ እንዲፀፀትና እንዲማር ቢያደርጉት ከትልቅ ውለታ ይቆጠራል።

 

የዛሬው ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስገባት የሚረዳ ካለመሆኑም በላይ ያንኑም ቅሉ አክብሮ ለመጠበቅ በአንቀጽ 21 እንደተመለከተው ከንጉሠ ነገሥቱ በመሐላ የተሰጠው ቃል ፈርሷል እያሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን እንደሚያማርሩ ግርማዊነትዎ ሳይሰማው አይቀርም። መቸም ሕገ መንግሥቱን ለመጣስ አንድ የጽሕፈት ሚኒስቴር ደብዳቤ ይበቃል። እንግዲህ ሕዝቡ ወይም ሹማምንቱ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ ነኝ እያሉ ቢምሉትም ንጉሠ ነገሥቱ በበኩሉ መሐላውን የሚጠብቅ ካልሆነ በመሐላቸው የደረሰው ሁኔታ ምሳሌ ሲሆን ይችላል ይመስለኛል።

 

ዋሽንግተን ግንቦት 25 ቀን 1952 ዓ.ም

ከታላቅ አክብሮታዊ ፍርሐት ጋር

ብርሃኑ ድንቄ

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
11695 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us