ተዋናይት ሰብለ ተፈራ /እማማ ጨቤ/፣ /ትርፌ/ ከ1968-2008 ዓ.ም

Wednesday, 16 September 2015 13:53

በጥበቡ በለጠ


በትወና ችሎታዋ እና ብቃቷ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅ የነበረችው ሰብለ ተፈራ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም ባለቤቷ በሚያሽከረክራት መኪናቸው ሲጓዙ ከቆመ ሌላ ከባድ መኪና ጋር ንፋስ ስልክ አካባቢ በመጋጨታቸው የእርሷ ሕይወት ሲያልፍ ባለቤቷ የከፋ ጉዳት ሣያጋጥመው ተርፏል። ፖሊሲም ባለቤቷን በማሠር የአደጋውን መንስኤ ምርመራ እያደረገበት ይገኛል።


 

የመኪና አደጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የአያሌዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል። በየቀኑ የዚህች ሀገር ዜጐች በመኪና አደጋ ይሞታሉ። የአብዛኛዎቹ አደጋ መንስኤ በጥንቃቄ ያለማሽከርከር ነው። ለያዙት ሰው እና ንብረት ሐላፊነት ወስዶ መኪናን አለማሽከርከር በተደጋጋሚ የሚነሣ የዚህች ሀገር ችግር ነው። ሌላው አልክሆል   ጠጥቶ ማሽከርከር ነው። መኪናዎች በየመጠጥ ቤቱ ደጃፍ ላይ ቆመው አሽከርካሪዎቹም ሲያሻቸው መኪና ውስጥ አልያም በግሮሰሪው ባንኮኒ ላይ ተገትረው ሲጐነጩ ውለው መኪና ሲያሽከረክሩ የሚከለክል የትራፊክ ፖሊስ የለም። መኪናዎች በየመጠጥ ቤቱ ቆመው ሾፌሮቻቸውን እንደልብ አልኮል የሚያስጐነጩበት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነው። ሀይ የሚል የለም።


 

ተዋናይት ሰብለ ተፈራ ላይ የደረሰውን የመኪና አደጋ መንስኤውን በትክክል ባናውቀውም ከቆመ መኪና ጋር መጋጨታቸው ሲሰማ ደግሞ ብዙዎች ግራ ተጋብተዋል።


 

የመኪና አደጋ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንን በተለያዩ ጊዜያት ከሚወዳቸው ሕዝብ እና ቤተሰብ ለይቷቸዋል። ለምሣሌ በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ ያውም እንደ ዛሬው ብዙ መኪና ሣይኖር ኢትዮጵያዊው የስዕል ሊቀ እና ገጣሚ አገኘው እንግዳ የሞተው መኪና ገጭቶት ነው። አገኘው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዘመናዊ ስዕል ሊቅ ነበር። በጣም የሚያሣዝነው ደግሞ እስክ ዛሬ ድረስ አገኘው እንግዳን በመኪና አደጋ ያደረሰበት አካል ወይም ግለሰብ ማን እንደሆነ አለመታወቁ ነው። ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላም ከሩጫው አለም የተሰናበተው እና በዊልቸር መሔድ የጀመረው የመኪና አደጋ ደርሶበት ነው። ልዑል መኮንን በመኪና አደጋ ነው ሕይወታቸው ያለፈው። ኮሜዲያን አለባቸው ተካም በመኪና አደጋ ነው ያለፈው። የማራቶን ራጩ አትሌት ቱርቦ ቱሞ ወደ አዋሣ ሲጓዝ በመኪና አደጋ ነው የሞተው። ተወዳጁ ድምጻዊና የሚዩዚክ ሜይዴይ አትዮጵያ መስራች ሽመልስ አራርሶም የሞተው በመኪና አደጋ ነው። ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው የሚያሽከረክራት መኪና ባምቢስ ድልድይ አካባቢ አደጋ ስላደረሰ እና አብሮት የነበረው ጉደኛው ሕይወቱ በማለፉ ለአመታት ታስሮ ተፈትቷል። የመኪና አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መጥቷል።


 

የሰብለ ተፈራ ባለቤት መቼም ከፍተኛ የሆነ ሐዘን ውስጥ ነው ። ባለቤቱን ራሱ በሚያሽከረክራት መኪና አደጋ አጥቷታል። ሞታለች። እሱ አካላዊ ጉዳት ሣይደርስበት ተርፏል። ግን ሁሌም የሚፀፅተው ጉዳይ ተከስቶበታል። የመኪና አደጋ በሰከንድ ውስጥ የሚከሰት ሆኖ ግን ፀፀቱ የእድሜ ልክ ነው። የሰብለን ባለቤት አቶ ሞገስ ተስፋዬን ሣስበውም በዚህ ጭንቀት ውስጥ ያለ ይመስለኛል።


 

ሰብለ ተፈራ ድንቅ ተዋናይት ነበረች። ታዲያ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋለች። ሕይወትን ታግላለች። ጉዞው ለሰብለ ቀላል አልነበረም። በችግር አሣልፋለች ግን በመጨረሻም ካሰበችው ደረጃ ደረሣ የልፋቷን ልትመገብ ስትል በድንገት ተቀጨች።


 

ከአንድ አመት በፊት አዲስ ጣዕም በተሰኘው የሬዲዮ ኘሮግራሞች ላይ የቅዳሜ ምሽት እንግዳችን አድርገናት ከምሽቱ 3-6 ሰዓት ድረስ ከኛ ጋር በአየር ላይ ነበረች። በዚህ ጊዜም ሙያዋን ከየት አንስታ የት እንዳደረሰች እና ስለ ልዩ ልዩ ገጠመኞቿ ነበር ያወጋነው። ታዲያ በዚህ ምሽት የደነቀኝ ነገር ነበር። የሬዲዮ ጣቢያው በፅሁፍ መልዕክት መላኪያው በብዙ ሺ በሚቆጠሩ አድማጮች መልዕክት ተጨናነቀ። ከመላው ኢትዮጵያ እና ከተለያዩ የአለም ሀገራት ሰብለ አድናቂሽ ነን፣ እንወድሻለን፣ ጨቤ፣ ትርፌ እያሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አድማጮች የፅሁፍ መልዕክት ላኩላት። እኛም የሚላኩትን መልዕክቶች ተቆጣጥሮ ማንበብ ተሣነን። ሰብለ ተፈራ ምን ያህል በኢትዮጵያዊያን ልብ እና መንፈስ ውስጥ መግባቷን በዚያች ምሽት በሚገባ አረጋገጥኩ። ከትናንት በስቲያ መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን የቀብር ስነ-ስርአቷ ሲከናወን ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ ተገኝቶ ሰብለን ለመጨረሻ ጊዜ እንባ እየተራጨ ተሰናበታት።


 

በዚሁ የሰብለ ተፈራ የቀብር ስነ-ስርአት ላይ የሚከተው የሕይወት ታሪኳ በጓደኞቿ ተፅፎ በቀብር ሥነሥርዓቱ ወቅት ተነቧል።


 

“ተዋናይት ሰብለ ተፈራ ከ1968 እስከ መስከረም አንድ 2008 ዓ.ም። አርቲስት ሰብለ ተፈራ /እማማ ጨቤ/፣ /ትርፌ/ በአዲስ አበባ ከተማ ወሎ ሰፈር አይቤክስ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግንቦት 18 ቀን 1968 ዓ.ም ተወለደች። አርቲስት ሰብለ ተፈራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ት/ቤት የተማረች ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደገሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምራለች።


 

“አርቲስት ሰብለ ተፈራ ለደረሰችበት የኪነ-ጥበብ ሕይወቷ ከ14 አመቷ ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር። 1984 ዓ.ም በክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ የቴአትር ክበብ ስልጠና ወስዳለች። በመጀመሪያም “ጭንቅሎ” የተሰኘውን የቴአትር ስራዋን በማቅረብ ትወናዋን በሚገባ አስመስክራለች።


 

“አርቲስት ሰብለ ተፈራ የትወና ተሰጥዋን የበለጠ ለማሣደግ ባደረገችው ጥረትም የቴአትር ጥበባት ትምህርቷን በወጋገን ኮሌጅ ዲኘሎማዋን ያገኘች ሲሆን፣ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ደግሞ የድግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ነበረች።


 

“አርቲስት ሰብለ ተፈራ ከ30 በላይ ቴአትሮችን፣ የዛሬዋን ኤርትራን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ያቀረበች ሲሆን በሐገራችንም የፊልም ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሣተፍ በተዋናይነት ከሃያ ፊልሞች በላይ በተለየ ብቃት ችሎታዋን አሣይታለች። ከተወነችባቸው ቴአትሮች መካከልም “አምታታው በከተማ”፣” “ወርቃማ ፍሬ”፣ “ሕይወት በየፈርጁ”፣ “የሰርጉ ዋዜማ”፣ “እኩይ ደቀ መዝሙር”፣ “አንድ-ቃል”፣ “የክፉ ቀን ደራሽ”፣ “እንቁላሉ”፣ “አብሮ አደግ”፣ “ሩብ ጉዳይ” እና ሌሎችም ቴአትሮች ይጠቀሣሉ።


 

ከተወነችባቸው ፊልሞች መካከል ደግሞ “ፈንጂ ወረዳ”፣ “ያረፈደ አራዳ”፣ “ማግስት”፣ “ትንቢት” የሚሉት ፊልሞች በአፍቃሪዎቿ ዘንድ ሁሌም ይታወሣሉ።


 

“ከቀን ወደ ቀን ጥረቷ እያደገ የመጣው አርቲስት ሰብለ ተፈራ በከፍተኛ ጥረት ”እርጥባን” የተሰኘውን ቴአትር በኘሮዲዮሰርነት ሰርታ በማጠናቀቅ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ከአራት አመታት በፊት ለእይታ እንዲበቃ ያደረገች ሲሆን፡ በተጨማሪም “አልበም” የተሰኘውን ፊልም በዋና አዘጋጅነት እና በኘሮዲዮሰርነት በማቅረበ ከሁለት አመታት በፊት ለሕዝብ አሣይታለች።


 

“ከቴአትርና ፊልም ስራዋ በተጨማሪ በርካታ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ለዚሁ ሙያዋ ይሆን ዘንድ ከፍታ ታስተዳድረው በነበረው ሰብለ ፊልም ኘሮዳክሽን በመስራት ላይ ነበረች።


 

“አርቲስት ሰብለ ተፈራ በትወና ሙይዋ በአብዛኛው የሀገራችን ክልሎች በመዘዋወር ስራዎቿን ያቀረበች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ውጭም ስራዎቿን በሱዳን አብዬ ለኢ.ፌ.ድ.ሪ የሐገር መከላከያ ሰራዊት የሰላም አስከባሪ ኃይል፣ በእስራኤል “ሴት ወንድሜ” የተሰኘ ቴአትር፣ በሐገረ እንግሊዝ “የኛ እድር” የተሰኘውን ቴአትር፣ በደቡብ አፍሪካ “የዳዊት እንዚራ” የተሰኘውን ቴአትር እንዲሁም በቅርቡ “የኛ እድር” የተሰኘውን ቴአትር በአሜሪካ እና በሌሎች አዋሣኝ ሀገራት ለተከታታይ ስድስት ወራት ይዛ በመጓዝ ከስራ ባልደረቦቿ ጋር ስራዋን አቅርባለች።


 

“በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአምስት አመታት በቀረበው ”ትንንሽ ፀሐዮች” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ከታዳሚው አእምሮ የማይጠፉትን “እማማ ጨቤ” የተሰኙትን ገፀ-ባሕሪ ወክላ በመጫወት ከፍተኛ ዝና እና ፍቅር አፍርታለች። በኢትዮጵያ ብሮድኮስቲንግ ኮርፖሬሽን እየቀረበ በሚኘው “ቤቶች” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የቤት ሰራተኛ የሆነችውን የትርፌን ገፀ-ባሕሪ ወክላ በመተወንም ላይ ነበረች። በነዚህ ስራዎቿ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የትወና ብቋቷን በማስመስከር ልቃ የወጣችበትና በሕዝባችን ዘንድም ከፍተኛ ዝናና ፍቅር ተጐናፅፋበታለች።


 

“አርቲስት ሰብለ ተፈራ ከአቶ ሞገስ ተስፋዬ ጋር ሚያዚያ 27 ቀን 1999 ዓ.ም ትዳር መስርታ በልዩ ፍቅር ይኖሩ ነበር።

“ሰብለ በመንፈሣዊ ሕይወቷ የተለያዩ በአዲስ አበባ እና በመላው ኢትዮጵያ በተጠራችበት ሁሉ ማለትም ከ400 በላይ ቦታዎች ሁሉ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያናትን በማገልገል ትታወቃለች። ከልጅነቷ ጀምሮ በጥበብና በፍቅር ቤተ-ክርስትያን ያሣደጋት አምላኳ ቅዱስ እግዚአብሔርን በምክረ ካህን እና ከተለያዩ መንፈሣዊ ማህበራት ጋር በአንድነት በመሆን ገዳማትን እና ቅዱሣን መካናትን ስታገለግል ኖራለች። በሕይወት ከመለየቷ ከ40 ሰዓታት በፊትም ጳጉሜ አምስት 2007 ዓ.ም በቱሉ ዲምቱ አቃቂ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን በመገኘት የራሷን “የመዳን ቀን ዛሬ ነው” የሚል ግጥምና ሌሎችንም ግጥሞች አቅርባ ነበር።


 

“ለሙያዋ ከፍተኛ ከበሬታ የነበራት አርቲስት ሰብለ ተፈራ፣ ቤተሰቧን አክባሪ፣ በእምነቷ ጠንካራ፣ ሰው አክባሪ፣ ተግባቢ፣ ተጫዋች ፣ፍልቅልቅ እና ሣቅ የማይለያት፣ ሰውን ለማስደሰትና ለመርዳት ሁሌም ጥረት ስታደርግ የኖረች ቅን፣ ባለሙሉ ተስፋ፣ ለሙያዋ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለች ልዩ የጥበብ ሴት ነበረች። ሆኖም መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም ንፋስ ስልክ አባባቢ ከባለቤቷ ከአቶ ሞገስ ተስፋዬ ጋር በግል ተሽከርካሪያቸው በመጓዝ ላይ ሣሉ ቆሞ ከነበረ ከባድ መኪና ጋር በደረሰባቸው አደጋ በተወደለች በ40 አመቷ በዚሁ እለት ከቀኑ 10፡40 ላይ ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች። ለባለቤቷ ለአቶ ሞገስ ተስፋዬ፣ ለቤተሰቦቿ፣ ለአብሮ አደግ እና ለሙያ ጓደኞቿ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ለሚገኙ አድናቂዎቿ ሁሉ እግዚአብሔር መፅናናትን ሁሉ እንዲሰጣቸው እንመኛለን።“


 

በዚሁ በሰብለ ተፈራ የቀብር ሥነ-ሥርአት ላይ ባለቤቷን ጨምሮ ብፁአን አባቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር እና ሌሎችም ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ ስለ ሰብለ ተፈራ ሙያዊ ክህሎት ንግግር አድርገዋል። ሰብለ ተፈራ በቤተሰቦቿና በብዙ ሺ በሚቆጠሩ የሙያ ጓደኞቿ እና አድናቂዎቿ ታጅባ ለመጨረሻ ጊዜ መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም ተሸኝታለች።


 

የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በሰብለ ድንገተኛ ሕልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቿ፣ ለሙያ አጋሮቿ እና ለአድናቂዎቿ መፅናናትን ይመኛል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
17371 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us