ዓባይ እና ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን

Wednesday, 23 September 2015 13:45

 

 

ከኤሚ እንግዳ (ካምፓላ ዑጋንዳ)

 

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በኢትዮጵያ የሥነ-ግጥም እና የቴአትር ፅሁፍ ውስጥ ወደር የማይገኝለት ብርቅ የጥበብ ሰው ነበር። ፀጋዬ እሳት ወይ አበባ በሚለው እጅግ ድንቅ የስነ-ግጥም መፅሃፉ ውስጥ ብዙ ነገሮች ላይ ተቀኝቷል። በጣም የሚገርመው ነገር ግን ፀጋዬ የኢትዮጵያን ከተሞች በስነ-ግጥሙ ውስጥ በደንብ እያብራራላቸው ቅኔ አዝንቦላቸዋል። የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ሲናገሩ የኢትዮጵያን ከተሞች በግጥም የገለፀ ከያኒ እንደ ፀጋዬ የለም ይላሉ።

ፀጋዬ ስለ ሐረር ከተማ ጥንታዊነት እና የምስራቅ ኢትዮጵያ የብርሃን ጮራ ፈንጣቂ መሆኗን ገጥሞላታል። ስለ ድሬዳዋ ከተማ ውበትና ታሪካዊነት ፅፏል። የተወለደባትን ከተማ አምቦን ምን አይነት ታሪክ እንዳላት ቅኔ ደርድሮላታል። ወለጋን፣ ከፋን፣ መቀሌን፣ አስመራን ወዘተ በተመለከተ ውብ ግጥሞችን አበርክቷል። ሊማሊሞን ተራራ በግጥም ያዋራዋል፤ ይጠይቀዋል። አንዳንዶች ጸጋዬን “ባለቅኔው አርክቴክት” እያሉት ይጠሩታል።


 

በሎሬት ፀጋዬ ስራ ውስጥ ግን ልዕለ ሃያል ነው ተብሎ የሚጠራለት ከዛሬ አርባ አመታት በፊት ስለ ዓባይ የገጠመው ግጥም ነው። የፀጋዬ የቅኔ ሀያልነቱ እጅግ መጥቆ የወጣበት ግጥሙ ዓባይ ዓባይ ወንዝ ቢሆንም፣ ውስጡ ግን ቅኔ ነው። ዓባይ የብዙ ሚሊየን ሕዝቦች ሕልውና ነው። ዓባይ የፈጣሪ ስጦታ ነው።፡ ዓባይ በመፅሃፍ ቅዱሰ ውስጥ ግዮን ነው። ዓባይ የማህበረሰቦችና የባሕሎች ትስስር ነው። ዓባይ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ዓባይ ተምሣሌት ነው። ስልጣኔዎች በአባይ ሸለቆ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ዓባይ የብዙ ባለቅኔዎች፣ ፈላስፋዎች ተመራማሪዎች የትኩረት አቅጣጫ ነው። የሰው ዘር ምንጭ ከአባይ ሸለቆ ጋር ይያያዛል። የጥንቷ ግብፅ፣ ኑቢያ/የአሁና ሱዳን/ የዓባይ ልጆች ናቸው። ዓባይ ከኢትዮጵያ ማህፀን የፈለቀ ነው። ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ወላጅ ናት ባይ ነው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን።


 

ታላቁ የጥበብ ሊቀ ፀጋዬ ገ/መድህን ዓባይ ብሎ የገጠመው ቅኔው ልዕለ-ጥበብ ተብሎ የሚጠራ ነው። ፈረንጆቹ Masterpice ይሉታል። የኢትዮጵያን የሥነ-ግጥም ታሪክ ያጠናው ብርሃኑ ገበየሁ፣ በአንድ ወቅት እንደፃፈው ዓባይ የተሰኘው የፀጋዬ ግጥም ለራሱ ለጸጋዬም ሆነ ለኢትዮጵያ ሥነ-ግጥም በደረጃ ቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጥ ነው ብሏል።

የዓባይ ግጥም ረጅም ነው። ሁሉንም ከማቅረብ የተወሠነችውን በዚህ መልኩ ባቋድሳችሁስ፣


 

ዓባይ የጥቁር ዘር ብስራት፣

የኢትዮጵያ የደም ኩሽ እናት፣

የዓለም ስልጣኔ ምስማክ፣

ከጣና በር እስከ ካርናክ፣

ዓባይ የአቴንስ የጡቶች ግት፣

የዓለም የስልጣኔ እምብርት፣

ጥቁር ዓባይ የጥቁር ዘር ምንጭ፣

የካም ስልጣኔ ምንጭ፣

ዓባይ-ዓባይ ዓባይ-ጊዮን፣

ከምንጯ የጥበብ ሳሎን፣

ግሪክ ፋርስ እና ባቢሎን፣

ጭረው በቀዱት ሰሞን፣

ዓባይ የአማልእክት አንቀልባ፣

የቤተ-ጥበባት አምባ፤

/ከእሳት ወይ አበባ/


 

ፀጋዬ ገ/መድህን በየካቲት 1998 ዓ.ም ኒውዮርክ ውስጥ ሕይወቱ ብታልፍም ገና በትውልዶች ውስጥ ስሙን የሚያስጠሩ የጥበብ ስራዎቹ ዘመናትን ይጓዛሉ። ጸጋዬ ሉሲ (ድንቅነሽ) በ1966 ዓ.ም ከመገኘቷ በፊት እሱ በ1950ዎቹ ውስጥ ኢትየጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት። ሰው የተፈጠረውና ወደ ሌላ አለም የሄደው ከኢትዮጵያ ነው እያለ ይጽፍና ይናገር ነበር። በኋላ እነ ጌታቸው አስፋውና አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ጆሀንሰን በአርኪዮሎጂ ምርምር ሉሲን አገኝዋት። በ1988 ዓ.ም የኖርዌይ መንግሥት ጸጋዬን የክፍለ-ዘመናችን ታላቅ ባለቅኔ ብሎ ሸልሞታል። እንግሊዞች የአፍሪካው ሼክስፒር ይሉታል። አፍሪካዊያን የሎሬትነት አክሊል አጐናፅፈውታል። የአፍሪካን ህዝብ መዝሙር ደርስዋል። የአፍሪካን መሪዎች በጋር አዘምርዋል። አፍሪካዊያን ከቅኝ አገዛዝ እንዲላቀቁ ታግሏል። ኬንያ ነጻ ስትወጣ በክብረ-በአሏ ቀን የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን መርቶ የሄደው እሱ ነው። ኬንያዊያንን እንክዋን ደስ አላችሁ ብሎ ከኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጹን ያሰማቸው እሱ ነው። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በስነ-ፅሁፍ ችሎታው ታላቁን ሽልማታቸውንም አበርክተውለታል።

 

የዓባይ ባለቅኔዋ እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)


ሸማ ነጠላውን ለብሰው

አይበርዳቸው አይሞቃቸው

ሐገሩ ወይናደጋ ነው

አቤት ደም ግባት -ቁንጅና

አፈጣጠር ውብ እናት

ሐገሬ እምዬ ኢትዮጵያ

ቀጭን ፈታይ እመቤት

እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/


 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያን መካከል ከፊት ተሰላፊ ናት። ለምሳሌ በአለም ግዙፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚባለው   CNN በተደጋጋሚ ጂጂን እና የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርቧል። ከአፍሪካ አህጉር የሚደመጥ ጣፋጭ ሙዚቃ እያለ የጂጂን ክህሎትና ተሰጥኦ ሲያወዳድሰው ቆይቷል። ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም በአዘፋፈን ስልቷ፣ በድምጿ፣ በሙዚቃ ቅንብሯ እና በተለያዩ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን እየሰጧት ከመጡ ቆይታለች።

 

 

እጅጋየሁ ሽባባው ባለፉት 16 ዓመታት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም የሙዚቃ፣ የሥነ ግጥም እና የሥነ ፅሁፍ ሃያሲያን ስራዎቿን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲተነትኗቸው ቆይተዋል። በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ላይ በቀረበው ጥናት ጂጂ ከኢትዮጵያ ድምጻዊያን የሚለያት ሙዚቃዎቿ እጅግ የጠለቀ ኢትዮጵያዊነት መንፈስን /ስሜትን/ በውስጣቸው አምቀው የያዙ በመሆናቸው እንደሆነ የተገለፀበትም አጋጣሚ አለ።


 

እጅጋየሁ ሽባባው ሐገርን በየሙዚቃወቿ ውስጥ የምትገልፅባቸው መንግዶችም እየተነሱ ተተንትነዋል። ለጂጂ ሀገር ማለት ቤተሰብ፣ ኑሮ፣ ትዝታ፣ መልክዐ ምድሩ፣ ወንዞች፣ ተራሮች፣ ርቃው የሄደችው ህዝቧ.. ቢሆኑም የአቀራረብ መንገዶቿ ግን ጆሮ ግቡና እጅግ ማራኪ መሆኑም ተወስቷል።


 

ለምሳሌ በአንድ ወቅት ደግሞ አባይ ወንዝ ላይ የተፃፉ ልዩ ልዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ተሰብስበው ሚዛን ላይ ቁጭ ብለው ነበር። ሚዛን ያልኩት ሂሳዊ ምዘናውን ለመግለፅ ፈልጌ ነው። እጅግ በርካታ ገጣሚያን እና ሙዚቀኞች አባይን በየራሳቸው እይታ ሲገልፁት፣ ሲያቆለጳጵሱት ፣ሲሞግቱት፣ ሲወቅሱት፣ ሲቆጩበት.. እንደነበር በጥናት ተዳሷል። በመጨረሻም በግጥም፣ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በሙዚቃ እጅጋየሁን /ጂጂን/የሚያክል የጥበብ ሥራ ግን አልተገኘም ተብሏል። ፀጋዬ የስነ ግጥም ጣሪያ ሲሆን፣ ጂጂ ደግሞ የሙዚቃው ቁንጮ እንደሆነች ስራዎቻቸው እየተተነተኑ ቀርበዋል።

የእጅጋየሁ ሸባባው /ጂጂ/ ዓባይም እንዲሁ ከሙዚቃው ዓለም ከፀጋዬ ገ/መድህን ዓባይ ጋር ተፈርጀል።


 

የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና።

ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት

የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከነገት

ግርማ ሞገስ

የአገር ፀጋ የአገር ልብስ

ግርማ ሞገስ።

ዓባይ…

የበረሐው ሲሳይ……


እያለች ከህሊና በማይጠፋ የሙዚቃ ስልት እያንቆረቆረች የምታወርድ ድምፃዊት እንደሆነች ተነግሮላታል። ለጂጂ አራቱ የመጽሀፍ ቅዱስ ወንዞች ማለትም ግዮን፤ ኤፍራጥስ፤ ኤፌሶንና ጤግሮስ በሙዚቃዋ ቃና ውስጥ አሉ። እነዚህ ወንዞች በገነት ውስጥ ያሉትን እጸዋት ያጠጣሉ ይላል/ዘፍ 2፡10/ ጂጂ የኛን ግዮን/አባይን/ ይዛ ከገነት ፈልቆ ታገኘዋለች። ታጫውተዋለች። ወይ ሙዚቃ……


እነዚሁ ሁለት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ዓባይ ላይ ባቀረቧቸው ጥበባዊ ሥራዎቻቸውም በሚዛን ሲቀመጡ ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል። ዓባይ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው ከመገለፁም በላይ በተለይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተያይዞ መጥቶ ጣና ሐይቅ ውስጥ ገብቶ ግዙፍነቱ ይጨምራል። ጣና ላይ ደግሞ 37 ያህል ደሴቶች አሉ። በነዚህ ደሴቶች ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማት አሉ። አጅግ አስገራሚ የኢትዮጵያ ቅርሶችም በነዚህ ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ ዓባይ ላይ ይፀለያል፣ ይቀደሳል፣ ይዘመራል፣ በብህትውና ይኖራል፣ ይታመንበታል። ዓባይ የኢትዮጵያዊያን መንፈስ ነው። እምነት ነው። ሀብት ነው። ይሄን የጀርባ አንደምታ ይዘው ነው እነ ጂጂ ዓባይ ላይ ፍፁም ተወዳጅ የሆኑ ሰራዎችን ያቀረቡት።


 

የሚገርመው ነገር ዓባይ የሀገርና የህዝብ ትልቅ አጀንዳ ከመሆኑ አስቀድሞ ከ40 አመታት በፊት ሎሬት ጸጋየ ገ/መድህን ዓባይን ሰማየ ሰማያት አድርጎ ተቀኘበት። ጂጂ ደግሞ ከ14 ዓመታት በፊት ውብ አድርጋ ገጠመችለት አዜመችለት። በአሉ ግርማ እውነተኛ ደራሲ ነብይ ነው ይል ነበር።

ይምረጡ
(16 ሰዎች መርጠዋል)
12063 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us