ግማደ መስቀሉ ኢትዮጵያ ስለመኖሩ ምን ማስረጃ አለን?

Wednesday, 30 September 2015 14:08


በጥበቡ በለጠ

ኢትዮጵያ የብዙ ተአምራት እና ቅርሶች ምድር ናት ብለው የሚያምኑ አያሌ ናቸው። ሀገሪቱ ግን ያላትን ሀብት የሚያስተዋውቅላት ጠንካራ የቱሪዝም መሪ እስካሁን አላገኘችም ብለውም የሚተቹ አሉ። ለምሳሌ ፈጣሪ በራሱ እጅ ጽፎታል ተብሎ የሚታመንበት ጽላተ-ሙሴ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ተመራማሪዎች በተለያየ ጊዜ ከመግለጻቸውም በላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ልዩ ልዩ ትውፊቶችና ስርአቶች ብሎም ታሪኮች መረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያ በዚህ ጽላተ-ሙሴ ታሪክ ብቻ የአለም የቱሪዝም መናኸሪያ ትሆን ነበር። ማን ይናገርላት? ማን ይመስክርላት? ሚዲያዎቻችን ከዚህ ታሪክ ይልቅ እነ ሩኒ ምን በልተው እንዳደሩ በየቀኑ ሲነግሩን ይውላሉ። ከነገ በስቲያ ደግሞ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀሉ ያለበት ቦታ ላይ ማለትም ግሸን ደብረ-ከርቤ ታላቅ በአል ይከበራል። ለመሆኑ ግማደ-መስቀሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ ምንስ ማስረጃ አለን? ግሸን ደብረ-ከርቤን በተመለከተ ከሰራነው ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ለመዳሰስ እወዳለሁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ከሚገኙ ተአምራዊ ከሚባሉ ቅዱስ ቦታዎች መካከል አንዷ የሆነችው ግሸን ናት። በዛሬዋ እለትም ይህች ቦታ እጅግ ድምቅምቅ ብላ የምትውልበት ቀን ነው። እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ያለበት ታሪካዊ ስፍራ ነው። ዛሬ በጥቂቱም ቢሆን በዚህች ቅዱስ ስፍራ ቆየት እንላለን።

ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ፣ አምባሰል ወረዳ ውስጥ፣ በተፈጥሮ የመስቀል ቅርጽን ከያዘው ከግሸን አምባ ላይ የተመሠረተ ገዳም ነው። ይህ ገዳም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ጥንታዊ ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው። ግሸን ደብረ ከርቤን ከሌሎች ገዳማት መካከል ለየት የሚያደርገው ነገር፣የመልክዓ ምድሩ ተፈጥሯዊ ቅርጽ ለየት ያለ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል፣ የቀኝ እጁ ያረፈበት "ግማደ-መስቀል" ከዚህ ገዳም ውስጥ እንደሚገኝ በምእመናን ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚታመንበት ነገር ነው። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሚገኙት መረጃዎች መሠረት፣ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ በ1446 ዓመተ ምሕረት ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ጋር ከስናር (ሱዳን) ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው፣ ግሸን አምባ ላይ፣ ከእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ስር በተዘጋጀ ልዩ ቦታ እንዲቀመጥ በማድረጋቸውና፣ እስከዛሬም ድረስ ከዚህ ልዩ ቦታ እንደሚኖር ስለሚታመንበት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምእመናን በየወቅቱ ወደዚህ ክቡር ቦታ እየተጓዙ ጸሎታቸውን ያደርሳሉ። ግሸን አምባ ከባሕር ጠለል 3ሺህ 019 ሜትር (9 ሺህ 905 ጫማ) ከፍታ ላይ የሚገኝ፣ በአምባው ላይ 37 ነጥብ 74 ሄክተር (93 ነጥብ 27 ኤክረስ) ስፋት ባለው ቦታ ላይ አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም፣ ቅድስትማርያም (ግሸንማርያም)፣ እግዚአብሔርአብ (በመስቀል ቅርጽ የታነጸው)፣ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሚካኤል ይገኛሉ።

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ቤተክርስቲያን መግቢያ አንድ መንገድ ብቻ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይች ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች።

  • ከአጼ ድልናአድ ዘመን (866 ዓ.ም) እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ (ደብረ ከርቤ) ትታወቅ ነበር።
  • በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤተክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዜአብሔር በሚል ስም ትታወቃለች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገስት ተባለች።
  • በ1446 አጼ ዘርአ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገስት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች። በዚህ ጊዜ የነበረው የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መምህረ እስራኤል ዘ ደብረ ከርቤ ይባሉ ነበር።
  • አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ "ገሰ" ወይም በአማርኛው "ገሰገሰ" የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ። አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ ይላሉ አንዳንድ ጽሁፎች።

መስቀልና ግሸን

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የግሸንን ደብር የመሰረታት አንድ ጻድቅ መነኩሴ ነበር። ይኽውም በ514 ዓ.ም፣ ከዘርዓ ያዕቆብ መነሳት 900 አመት በፊት ነበር። የሆኖ ሆኖ አካባቢው በአሁኑ ዘመን የሚታውቀው የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል በማኖሩ ነው። አጼ ዘርአ ያዕቆብ በነገሱ ዘመን ወደ ስናር ሄደው ግማደ መስቀሉንና ሌሎች ብዙ የቤተክርስቲያን ውድ ንዋያትን አምጥተው መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ወደ ደብሩ በመውጣት በዘመኑ የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት እንደገና በማነጽ፤ በኋላም በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ጥግ በጥንቃቄ ጉድጓድ አስቆፍረው መስቀሉን በማስቀበርና ባለቤታቸው ንግስት እሌኒ ደብረ ከርቤ ማርያም ቤተክርስቲያንን እንደገና በማሳነጽ ከፍተኛ ስራ አከናወኑ። ከ5 አመት በኋላ መስከረም 21 ቀን 1449 ጀምሮ የመስቀል በዓል በዚህ ዕለት መከበር ተጀመረ።

እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀሉ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ይነገራል። ቀጥሎም በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ተሸክመውት ዞሯል። በዚያን ወቅት ያዩት ሁሉ አምነውበታል ተፈውሰውበታል፣ በጋራ ተቀብለውታል። መስቀሉ ኢትዮጵያን በመንፈሣዊ ኃይል ያስተሳሰረ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ጥንታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግን መስቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ መጣ? እንዴትስ ተገኘ?

አባ ገብረ መስቀል ተስፋዬ ዘገንተ ማርያም፣ በሐመር መጽሔት 9ኛ ዓመት ቁጥር 4 መስከረም-ጥቅምት 1994 ዓ.ም ላይ ስለዚሁ መስቀል መጣጥፍ አቅርበው ነበር። ርዕሱም “ግማደ መስቀሉ ከሄኖም እስከ ግሸን ማርያም” ይላል። በዚህ ጽሁፋቸው ስለ መስቀሉ ያለውን ታሪክና አጠቃላይ ገፅታውን በሚከተለው መልኩ አቅርበውታል።

“እየሱስ ክርስቶስን ቤተ-እስራኤል በቀራኒዮ ላይ በሰቀሉት ጊዜ ከመከራው ፅናት የተነሳ ደሙ ወርዶ የተሰቀለበትን መስቀል አለበሰው። ከዚያም የማይሞተው አምላክ ሞተ፤ በኋላም ከመስቀሉ አውርደው ቀበሩት። በሦስተኛው ቀንም ተነሳ። ተሰቅሎበት የነበረው የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደ ፀሐይ ሲያበራ፣ በተጨማሪም አጋንንት ሲያባርር፣ ድውይ ሲፈውስ፣ ሙታንን ሲያስነሳ ቤተ-እስራኤል አይሁድ ቀንተው በአዋጅ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ ጠቅላላ ቆሻሻ ማከማቻ እንዲሆን ወሰኑ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ እስከ 300 ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደ ተራራ ሆነ።

“ከዚያ በኋላ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ ንግስት የተባለች ደግ ሴት የክርስቶስን መስቀል በ3 መቶ ዓ.ም መስከረም 17 ቀን በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ-መቅደስ ጐሎጐታ ላይ አሰርታ በክብር አስቀመጠችው። ይህ መስቀልም ከዚያ እለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ፣ አጋንነት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራትን እየሰራ ሙት እያስነሳ ዓይነ ስውራንን እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ በማለት ፀሐፊው ይገልፃሉ።

“ይህንን ታላቅ ዝና የሰማው የፋርስ ንጉስ መስቀሉን ማርኰ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው። በዚህ ጊዜ የእየሩሳሌም ምዕመናን የሮማውን ንጉስ ህርቃልን እርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርገው በኢየሩሳሌም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገስታት ይህን መስቀል እኔ እወስድ እኔ እወስድ እያሉ ጦርነት እንደከፈቱም ይነገራል።

“በዚህ ጊዜ የእየሩሳሌም፣ የቁስጥንጥንያ፣ የአንጾኪያ፣ የኢፌሶን፣ የአርማኒያ፣ የግሪክ፣ የእስክንድርያ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች በመካከል ገብተው ጠቡን አበረዱት። ከዚህም አያይዘው በእየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ከአራት ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት። የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪካ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው።

“ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብፅ የዓረቦች ቁጥር እየበዛ ኃይላቸው እየጠነከረ ከመሄዱም በላይ፤ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች “ለግማደ መስቀሉ አትስገዱ፤ የክርስትያንን ሃይማኖት አጥፉ” እያሉም ስቃይ ያፀኑባቸው ጀመር። ክርስትያኖችም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊው ለዳግማዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ። “ንጉስ ሆይ! በዚህ በግብፅ ያሉ ዓረቦች ለክርስቶስ መስቀል አትስገዱ፤ የክርስትያንንም ሃይማኖት አጥፉ እያሉ መከራ ስላፀኑብን 10 ሺ ወቄት ወርቅ እንሰጥሃለንና ኃይልህን አንስተህ አስታግስልን” ብለው ጠየቁት።

“በዚህ ጊዜ ዳግማዊ አፄ ዳዊት ለመንፈሣዊ ሃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዷቸው፤ 20 ሺ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ። የአባይን ውሃም ለመገደብ ይዘጋጁ ጀመር። በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ሁሉ ደነገጡ፤ ፈሩ፣ ተሸበሩ። ንጉሱ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለዓረቦቹ ላኩ። “በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስትያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ” አሉ።

“የንጉሡ መልዕክትም ለዓረቦቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ ጥንቱ በሃይማኖታቸው ፀንተው በሠላም እንዲኖሩ ከክርስትያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ። ይህንንም ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ። በዚህም ጉዳይ ንጉሱ በጣም ደስ አላቸው። እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። ከግብፅ የሚኖሩ ክርስትያኖችም ከ12 ሺ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን በኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው። ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው። ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ፡-

“በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ። የላካችሁልኝን 12 ሺ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ። የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም። የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ። አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክብሯን እቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው” የሚል ነበር።

አባ ገብረመስቀል ተስፋዬ ጽሑፋቸውን ሲቀጥሉም የሚከተለውን አስቀምጠዋል።

በእስክንድርያ ያሉ ምዕመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቀ-ጳጳሳቱና ከኢጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ “ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስትያን ነው” ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አፅምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው 12ሺ ወቄት ወርቅ፣ የብር፣ የንሐስ፣ የመዳብና የወርቅ ሳጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማሙ።

በክብር በሥነ-ሥርዓት በሰረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው አስረከቧቸው። ያን ጊዜ ንጉሡና ህዝባቸው በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ በእግራቸው እያሸበሸቡ፣ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት። ይህም የሆነው መስከረም 21 ቀን ነው።

“በኢትዮጵያ ታላቅ ብርሃን ሌት ተቀን ሦስት ቀናት ሙሉ ሲያበራ ሰነበተ። (ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “በራ የመስቀል ደመራ” የሚለው ይህን ቀን ነው) ወሬውም ወደ ግብፁ ንጉስ ደርሶ ሰማው። ከዚያም በጣም ተቆጥቶ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልን አሰራቸው። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም የሊቀ ጳጳሱን መታሰር ሰምተው አዘኑ። ለግብፁ ንጉስም ሊቀ ጳጳሱን አባ ሚካኤልን እንዲፈታቸው መልዕክት ላኩ። ንጉሱም መልዕክቱን ተቀብሎ እምቢ አልፈታም የሚል መልዕክት መለሰ። አፄ ዳዊትም የግብፁን ንጉሥ አምቢታ ተመልክተው የአባይ ውሃ ወደ ግብፅ እንዳይወርድ መገደብ ጀመሩ። የግብፁ ንጉሥም ይህንን ጉዳይ ሰምቶ ፈራ፣ ተሸበረ። ጉዳዩ የሊቀ ጳጳሱቱ መታሰር መሆኑን አውቆ ከእስራቸው ፈታቸው። ንጉሱም አፄ ዳዊት ሁለተኛ፣ ጠላታቸውን ድል ስላደረጉ ደስ አላቸው። በዚህ መካከልም ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ አፄ ዳዊት ስናር ላይ በድንገት አረፉ። አሳዛኝ ሞት! ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው ስናር ላይ ቆየ።

ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ አፄ ዘርአያዕቆብ እንደነገሰ ወደ ስናር ሄዶ ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር አምጥቶ በመናገሻ ከተማው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ-መቅደስ ሰርቶ ለማስቀመጥ ሲደክም ቆየ። በኋላም በህልሙ “አንብር መስቀልየ በዲቦ መስቀል” (መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ) የሚል ህልም አየ።

ንጉሱም በኢትዮጵያ ክልሎች ሁሉ መስቀልኛ ቦታ በመፈለግ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች አዙሮት ነበር። በዚህ ዙረት ውስጥ ነው ይህ መስቀል ኢትዮጵያዊያንን በመንፈስ ልዕልና አንድ ያደረጋቸው። ዛሬ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ የመስቀል በዓል በልዩ ሁኔታ የሚከበረው አፄ ዘርአያዕቆብ መስቀሉን በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገሪቱ ውስጥ በሙሉ በማዞሩ እንደሆነ በሰፊው ይነገራል።

ከዚህ ሁሉ ጉዞ በኋላ አፄ ዘርአያዕቆብ ለሰባት ቀናት ያህል ሱባኤ ገባ። በዚህም እግዚአብሔር ተገልጦለት መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ አምደብርሃን ይመጣል አለው። ዘርአያዕቆብም ከዚያ እንደወጣ መስቀልኛውን ቦታ የሚመራው አምደብርሃን ከፊቱ መጥቶ ቆመ። በዚህ ብርሃን መሪነትም ወሎ አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሽን ከመትባል ቦታ መርቶ አደረሰው። በእርግጥም ግሸን የተባለችው አምባ ጥበበኛ በሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሆኖ ስላገኛት የልቡ ደረሰ፤ ሀሴትም አገኘ። በዚህችም አምባ ታላቅ ቤተ-መቅደስ አሰርቶ መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳትን በማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድቦ አስቀመጣቸው። ጊዜው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር።”

በምርምር ጽሁፎቹ የሚታወቀው ኅሩይ ስሜ ደግሞ ከአባ ገብረመስቀል ተስፋዬ የተለየ አመለካከት አለው። ኅሩይ በ2003 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ “የመስቀል ደመራ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በሐመር መጽሔት ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ “በኢትዮጵያ ውስጥ መስቀልን ማክበርና መዘከር የተጀመረው በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን የሚመስላቸው ወገኖች አሉ” በማለት ሌላ አመለካከት ይዞ ብቅ ብሏል። እንደ ኅሩይ ገለፃ በዓለ መስቀል በአፄ ዘርአያዕቆብ ዘመን ጐልቶ ይታይ እንጂ መሠረቱ እጅግ ቀደም ብሎ ነው በማለት ያብራራል።

ኅሩይ ሲፅፍ፣ ይህንን ለማለት ከሚረዱን ዋነኛው አመላካች ማስረጃ፣ ገብረመስቀል የሚባል ስም በነገስታት ታሪክ ውስጥ እንኳን መገኘቱ ነው ይላል። እንደ ፀሐፊው ግመት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መስቀል በቤተ-ክርስትያን አዕማድ ላይ እየተቀረፀ ይከበር ነበር። እንዲሁም ካህናት የሚያሳልሙት መስቀል በከርሰ ምድር ቁፋሮ ተገኝቷል። አፄ ላሊበላም መስቀሉን የቤተ-ክርስትያን መሰረትና ጉልላት አድርገውታል ይላል ፀሐፊው። ሲያክልም፣ በአፄ ያግብአ ጽዮን ዘመንም ለመስቀል አንሰግድም ብለው የተነሱ ጥቂት መናፍቃንን ሰብስበው ንጉሱ ራሳቸው ለመስቀሉ በመስገድ ፈለጋቸውን እንዲከተሉ አሳስበዋል በማለት ይጠቁማል። በመጨረሻም ሲያጠቃልል ይህ ሁሉ የሚያሳየው ለመስቀሉ ክብርን መስጠትም ሆነ በበዓል ማክበር ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ነው።

በዚህ የመስቀል በዓል ላይ በርካታ ፀሐፊዎች ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮችን አካፍለውናል። ከላይ ከጠቀስኳቸው ከአባ ገብረመስቀል ተስፋዬ ዘገነተማርያምና ከኅሩይ ስሜ በተጨማሪ ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ዶ/ር ስርጉው ኃብለስላሴ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ድያቆን ብርሃኑ አድማስ፣ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ እና ሌሎችም ፀሐፊያን በመስቀል በዓል ላይ ያተኰሩ ጽሁፎቻቸው ሰፊ መረጃና እውቀት የሚሰጡ ናቸው።

ለምሳሌ አባ ገብረመስቀል ተስፋዬ ዘገነተ ማርያም፣ “ግማደ መስቀሉ ከሄኖም እስከ ግሸን ማርያም” በሚለው ጽሁፋቸው ስለ ግሸን ማርያም ቅርሶች በተመለከተም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት የግሸን አምባ በዓለማችን ላይ እጅግ ድንቅ የሚባሉ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶችም መኖራቸውን ገልፀዋል።

ከእስክንድሪያ (ግብፅ) ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሳጥን ተቆልፈው የመጡትን ቅርሶች በሚከተለው መልኩ ያቀርቡታል።

ጌታ በእለተ አርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነግ፣ ዮሐንስ የሳለው የኩርአተርእሱ ስዕል፣ ሉቃስ የሳላቸው የእመቤታችን ስዕሎች፣ አስርቱ ቃላት የተፃፈበት የእመቤታችን ጽላት (ታቦት)፣ የሐና አፅምና የራስ ፀጉር የአርሴማ ቅድስት አጽም፣ የያዕቆብ እሁሁ አፅም፣ የበርተሎሜዎስ ሐዋርያ አፅም፣ የቶማስ ሐዋርያ አፅም፣ የቅድስ ጊዮርጊስ ስማዕት አፅም፣ የቅዱስ መርቆርዮስ አፅም፣ የቅዱስ ገላውዲዮስ አፅም፣ ሔሮዱተስ ያስፈጃቸው የቤተልሄም ህፃናት አፅም፣ የቅዱስ ዲዮስቆስ ሊቀ-ጳጳሳት አፅም፣ የኢየሩሳሌም ግብፅ ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር እና የዮርዳኖስ ውሃ ናቸው።

የነዚህን ዝርዝር ለኢትዮጵያ ህዝብና ለግሸን ካህናት በፅሁፍ መስከረም 21 ቀን ላይ ተናገሩ። በመጀመሪያ ይህ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም 21 ቀን ነው። ወደኢትዮጵያም የገባው መስከረም 21 ቀን ሲሆን ቤተ-መቅደስ ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዘርአያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ የመጡትን እቃዎች በጽሁፍ በመዘርዘር የገለፀበትም መስከረም 21 ቀን ነው። ስለዚህ በዚህች በግሸን ደብር የክርስትና እምነት ያላቸው የኢትዮጵያ ምዕመናን ከመስቀሉ እና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማግኘት በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ቦታው ላይ በመገኘት ያከብራሉ በማለት ፀሐፊው ይገልፃሉ።

እነዚህ ከላይ የሰፈሩት ቅርሶችና ታሪኰች በሙሉ “መጽሐፈ ጤፉት” በተሰኘው ጥንታዊ የብራና ጽሁፍ ውስጥ ይገኛሉ። ይህን መጽሐፍ ያፃፈውም አፄ ዘርአያዕቆብ እንደሆነ ይታወቃል። ዘመኑም 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነበር። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን አማንያን ዘንድ እጅግ የተባረከና የተቀደሰ ቦታ የሚባለው ይኸው ግሸን ደብረ ከርቤ ሲሆን፣ በውስጡም ግማደ መስቀሉ እና እጅግ የሚደንቁ የዓለም ቅርሶች ያሉበት ቦታ ነው።

ስፍራውም ጥናትና ምርምር ተደርጐበት ለዓለም ቢተዋወቅ ግሸን ደብረ ከርቤ የምድራችን ትንግርታዊ ቦታ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ለዚህ ሁሉ ታሪክ ምክንያት የሆነችው ቅድስት እሌኒ ማን ናት? ቅድስት እሌኒ /Flavia Iulia Helena Augusta/ የክርስቶስን መስቀል ከቆሻሻ መጣያ አካባቢ ያስወጣች ነች። የኖረችው እ.ኤ.አ በ250 አካባቢ ድራፓኑም (ቅዱስ ቆስጠንጥንዮስ ከነገሰ በኋላ ሔለናፖሊስ ብሎ ይህችኑ ከተማ ለክብሯ ሰይሟታል) በሚባል ከተማ ተወልዳለች። አውራጃውም ቢታኒያ ይባላል።

ለልጇ ለቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለህዝቡ መልካምን እንዲያደርግ እና ለዓለም ህዝብ ሁሉ ሰላም ጤና በረከት እንዲወርድ በመፀለይ በ80 ዓመቷ ግድም የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበትን ቦታ አገኘች።

ቅድስት እሌሊ በጐሎጐታ መስቀሉን ካገኘች በኋላ አብያተ-ክርስትያናትን አሳንፃለች። ለክርስትና እምነትም ሰፊ መሠረት ጥላ አልፋለች። ኢትዮጵያም የመስቀል በዓልን እንዲህ በደመቀ መልኩ ታከብር ዘንድ የቅድስት እሌኒ አስተዋፅኦ ዝንተ ዓለም በኦርቶዶክሳዊያን አውድ ላይ እየተዘከረ ይኖራል። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ሁኔታ ያገኘነውን መስቀል አንሸሽገው።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
17639 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us