አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ አረፈ ከ1933- 2008 ዓ.ም

Wednesday, 07 October 2015 14:37

 

 

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

ኢትዮጵያ ባለፈው እሁድ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም አንጋፋውን ጋዜጠኛ እና ሃያሲ ሙሉጌታ ሉሌን አጥታለች። ጋሽ ሙሉጌታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

 

ሙሉጌታ ሉሌ በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ በእጅጉ የሚታወቅበት ሙያው ከሥነ-ጽሑፍ ጋር በተያያዘ ነበር። ድንቅ የሥነ-ፅሁፍ ሃያሲ ነበር። የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ምን አይነት እንደነበር የገባው፣ ያስተዋለ እና የሚተነትን ሰው በዚያ ዘመን ላይ ጥሩ ቢባል ሙሉጌታ ሉሌ አንድ ተብሎ ይጀመር ነበር።

 

የሙሉጌታ ሉሌን የሃያሲነት ችሎታ ላስረዳ። ኢትዮጵያ 1962 ዓ.ም ላይ አንድ ጉደኛ መጽሐፍና ደራሲ አገኘች። መጽሐፉ ከአድማስ ባሻገር ይሰኛል። ደራሲው ደግሞ በዓሉ ግርማ ነው። መጽሐፉም ሆነ ደራሲው የዚህች ሀገር አዲስ የሥነ-ፅሁፍ ክስቶች መሆናቸውን መጀመሪያ ያበሰረው ሙሉጌታ ሉሌ ነው።

 

ኢትዮጵያ ከጥንታዊ የሥነ-ፅሁፍ ጉዞዋ ወደ ዘመናዊ አፃፃፍ ተሸጋገረች። አዲስ አተያይ መጣ። አዲስ ጎዳና ተያያዝን። እያለ ሙሉጌታ ሉሌ የበዓሉ ግርማን አፃፃፍ ብርቅዬነት አብስሯል። ከአድማስ ባሻገር የተሰኘው የበዓሉ ግርማ መፅሐፍ የኢትዮጵያን የሥነ-ፅሁፍ የሺ ዓመታት ጉዞ የለወጠ እና ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ሂስ የፃፈው ሙሉጌታ ሉሌ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ላለፉት 45 ዓመታት በበዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር መጽሐፍ ላይ የድግሪ፣ የማስትሬት እና የዶክተሬት ድግሪ መመረቂያ ጥናቶች ይፃፋሉ። በሌሎችም አውደ ውይይቶች ላይ ስለዚሁ መጽሐፍ ጥናቶች ይቀርባሉ። በጣም የሚገርመው ጉዳይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚነሱት ነጥቦች ሙሉጌታ ሉሌ የዛሬ 45 ዓመት የፃፋቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። ለመሆኑ ሙሉጌታ ሉሌ ምን አለ? ምን ፃፈ ሊባል ይችላል።

 

ሙሉጌታ ሉሌ ስለ አድማስ ባሻገር መጽሐፍ የሰጠው ሂስ አንደኛ አፃፃፉ ላይ ነው። ከዚህ ልቦለድ መጽሐፍ በፊት የተፃፉት የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፎች የሚተርኩት ከልደት እስ ሞት ድረስ ነው። ለምሳሌ ወደ ዘመናዊ ሥነ-ፅሁፍ የተደረገውን ጉዞ ይደግፋል የሚባው የሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ትረካው የሚጀምረው ገና በዛብህ ሳይወለድ ነው። የእናትና አባቱን ጋብቻ መጀመሪያ ላይ ይተርካል። ጎጃም ውስጥ ማንኩሳ በምትባለው ቦታ ቦጋለ መብራቱ እና ውድነሽ በጣሙ የሚባሉ ባልና ምሽት እንደነበሩ ይተርካል። በነሱ ጋብቻ ምክንያት በዛብህ መወለዱ፣ ማደጉ፣ መማሩ፣ ስራ መቀጠሩ፣ የፍቅር ሕይወቱ፣ ስደቱ፣ ሞቱ ይተረካል። ከልደት እስከ ሞት ወይም ከአንቀልባ እስከ ቃሬዛ የሚሔድ ትረካ ነበረው የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ። በዓሉ ግርማ የሚባል አብዮተኛ ደራሲ መጥቶ ይህን ሕግ ቀየረው። ከአድማስ ባሻገር በሚባለው መጽሐፉ አዲስ አፃፃፍ ለኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ አበሰረ። የመጽሐፉ ታሪክ ገና ሲጀምር “ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል” በማለት ነው። ታሪክን ከወገቡ  ጀመረው። የቀደመው ሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ከልደት ነበር የሚጀምረው። እናም በዓሉ ግርማ አዲስ አፃፃፍ እንዳመጣ መጀመሪያ የነገረን ሙሉጌታ ሉሌ ነው።

የበዓሉ ግርማ ገፀ - ባህሪዎች እነ አበራ፣ እነ ኃይለማርያም፣ እነ ሉሊት የማንነት ጥያቄ የሚያባዝናቸው የአዲሱ ትውልድ ወኪሎች መሆናቸውን ያብራራልን ሙሉጌታ ሉሌ ነው። በዓሉ ግርማ ስለተረከለት “ጥቁር ጢንዚዛ” ተምሳሌትነት ያብራራን ይኸው ጎምቱ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ነው።

 

ለአንድ ሥነ- ፅሑፍ ተምሳሌት /Symbolism/ አስፈላጊነት እና የበዓሉ ግርማ የተምሳሌት አፃፃፍ እንዴት እንደሆነ ሙሉጌታ ሉሌ ተንትኖልናል። ራሷን “ጠይም ጣኦት” እያች የምትጠራው ሉሊት፣ ወንድን ልጅ የማንበርከክ ችሎታዋ፣ ወንድን በፍቅር ተብትባ እና እጅ እግሩን ይዛ፣ እያነሆለለች የምትጫወትበት ምክንያት ምን እንደሆነ በተባ ብዕሩ ያስነበበን ሙሉጌታ ሉሌ ነው።

 

ሙሉጌታ ሉሌ ለኔ ልዩ ሰው ነው። ምክንያቴ ደግሞ ዛሬም ድረስ ወደር ያልተገኘለትን የበዓሉ ግርማን ከአድማስ ባሻገር ልቦለድ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባውና የተነተነው እሱ ነው። ከአድማስ ባሻገርን ከበዓሉ ግርማ በላይ ያብራራው ሙሉጌታ ሉሌ ነው። ድንቅ ሃያሲ ነበር።

 

 

ሙሉጌታ ሉሌ ከተነተናቸው መጽሐፎች መካከል የሰለሞን ደሬሳን ልጅነት የተሰኘውን የግጥም መድብል ነው። በዘመኑ ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳው የሰለሞን ደሬሳ የአፃፃፍ ቴክኒክ አዲስ ዘዬ /Style/ ነው በማለት የገጣሚውን ሥራ ያስተዋወቀን ሃያሲ ሙሉጌታ ሉሌ ነው። ይህ የሆነው የዛሬ 45 ዓመት ግድም ነው። ሰለሞን ደሬሳ “ጥበብ ለጥበብ” /Art for Art sake/ የሚባል አፃፃፍ ያመጣ ነው። ለሥነ-ፅኁፍ ሕግጋት አይጨነቅም። “ለራሱ ለነብስያው የሚጨነቅ ገጣሚ ነው” እያለ ሰለሞንን ያብራራልን ሙሉጌታ ሉሌ ነው።

የ1960 ዎቹን የኢትዮጵያን የጥበብ ክስቶች ማለትም በዓሉ ግርማን፣ ሰለሞን ደሬሳን፣ ገብረክርስቶስ ደስታን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን ሌሎችንም የተነተነ የሥነ-ፅሁፍ ባለውለታችን ነበር ሙሉጌታ ሉሌ።

 

እሁድ ምሽት ከወደ አሜሪካ አንድ አስደንጋጭ ዜና ብቅ አለ። ሙሉጌታ ሉሌ አረፈ የሚል። የሥነ- ፅሁፍ እና የጥበብ ሃያሲነቱን ላስቀምጠውና በብዙዎች ዘንድ ጎልቶ የሚታይበትን ግርማ ሞገስ ያጎናፀፈውን የጋዜጠኝነት ሕይወቱን ደግሞ በትንሹ ልዳስሰው።

 

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው ሲነሳ ከፊት ከሚሰለፉት መካከል አንዱ ሙሉጌታ ሉሌ ነው።  ምክንያቱም በቀደመው ዘመን ትልልቅ ክብር የነበራቸውን የዛሬይቱ ኢትዮጵያን፣ የመሣሠሉ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ በአመራርነት ያገለገለ፣ የብዙ ጋዜጠኞች ሞዴል በመሆን ወደ ሙያው እንዲገቡ ያገለገለ እና ሙያውን ያስፋፋ ሰው ነበር። በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለው ሰው ነው።

በሄራልድ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በየካቲት መጽሔት፣ በመነን መጽሔት ወዘተ ላይ የፃፋቸው መጣጥፎች ዘመን ተሻጋሪዎች ናቸው። በየትኛውም ወቅት እና ትውልድ ውስጥ የሚነበቡ ናቸው።

 

ሙሉጌታ ሉሌ የቃላት ሀብታም ነው። ቃላት የሚገቡበትን የሚሰኩበትን ቦታ ጠንቅቆ የሚያውቅ የጽሑፍ ሊቅ ነው። ሃሳባቸውን በፅሁፍ በመግለጽ ከሚደነቁ ሰዎች ተርታ ስሙ ወዲያው የሚጠራ የዚህች ሃገር የጋዜጣና የመጽሔት ፊት አውራሪ ባለሙያ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ተለየን።

 

ከ1983 ዓ.ም በኋላ አዲስ ስርዓት ሲመጣ ሙሉጌታ ሉሌ ከቀድሞው የኃላፊነት ቦታውና ስራው ተሰናበተ። ግን ቁጭ አላለም። ወዲያው ደግሞ የነፃው ፕሬስ አዋጅ ወጣ። በግል ጋዜጣና መጽሔት ማሳተም ተፈቀደ። መፃፍ ተፈቀደ። መተቸት ተፈቀደ። እናም ፈጣኑ ሙሉጌታ ሉሌ ከሙያ አጋሮቹ ጋር ሆኖ ጦቢያ መጽሔትን እና ጋዜጣን መሠረተ። ከ1983 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ የነፃው ፕሬስ ምህዋር ውስጥ በእጅጉ ፈንጥቃ ትታይ የነበረችው ጦቢያ የሙሉጌታ ሉሌ የእጅ እና የአእምሮ የሥራ ውጤት ነበረች።

 

 

እስኪ አንድ ጊዜ ወደ አእምሮአችንን ከ1984 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ይታተሙ ስለነበሩ የኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ውጤቶች እንውሰድ። ስንቶቹ መጡባችሁ? ሰንቶቹ ትዝ አሏችሁ? በዚህች ሀገር የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ሁሉም ነገር ደማምቆ የታየበት ወቅት ነበር። ጦቢያ መጽሔትና ጋዜጣ ደግሞ ቀድማ በመምጣት እና ጎልታ በመታየት ትታወሳለች።

ጦቢያ መጽሔት በእጅጉ ከሚሸጡ እና ከሚሰራጩ የህትመት ውጤቶች መካከል ባለ ግርማ ሞገሷ ነበረች። ይህችን መጽሔት የሚገዛ ሰው ደግሞ በዋናነት የሚያነበው “ፀጋዬ ገ/መድህን አርአያ” የተባለ ሰው የሚፅፈውን የፖለቲካ ትንታኔ ጽሁፍ ነው። ይህ ሰው በየወሩ ሰፊ የሆነ ትንታኔ ያቀርባል። ገዢውን መንግሥት ከልዩ ልዩ አንፃሮች እያነሳሳ ሂስ ያቀርብበታል። ማህበረሰብን ይጠይቅበታል። ታሪክን እያነሣሣ የኋላን እንድናይ ያደርገናል። በአፃፃፍ ቴክኒኩ እና ሃሳቡን በመግለፅ ብቃቱ ወደር የማይገኝለት ፀሐፊ ነው። ይህ በፀጋዬ ገ/መድህን አርአያ ስም የሚጠራው ፀሐፊ ሙሉጌታ ሉሌ ነው። ፀጋዬ ገ/መድህን አርአያ የሙሉጌታ ሉሌ የብዕር ስም ነው።

 

ሙሉጌታ ሉሌ በኢትዮጵያ የነፃው ፕሬስ ታሪክ ውስጥም ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠራ ሰው ነው። በሀገሪቱ ውስጥ የነፃ ፕሬስ አዋጅ ከወጣ ማግስት ጀምሮ በተሰጠው መብት እስከ ጥግ ድረስ ለመጠቀም የደፈረ ብዕረኛ ነበር። ሌሎችም እንዲፅፉ፣ እንዲተቻቹ፣ ሃሳብን በፕሬስ እንዲገልፁ፣ መፍራትና መሸማቀቅ እንዲቆም ብርቱ ትግል ያደረገ የነፃው ፕሬስ ተምሳሌት ነበር።

 

ለዘመናት የታፈነው የነፃው ፕሬስ አዋጅ ብቅ ሲል የተረገዘው ብሶት በብዕር መዘርገፍ የጀመረው በዚሁ አንጋፋ ጋዜጠኛ በሙሉጌታ ሉሌ አማካይነት ነው። በፀጋዬ ገ/መድህን አርአያ ስም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን ልምድ ያስተዋወቀ ነው። በእርሱ እግር ተተክተው ብዙ የፕሬስ ሰዎች በዚህች ሀገር መጥተው ነበር። እስከ 1990 ዓ.ም ብቻ ከ300 በላይ የጋዜጣና የመጽሔት ሕትመቶች መጥተው እንደሔዱ በዚያን ወቅት የሰራሁት ጥናት ይነግረኛል። እናም ይህች ሀገር ፕሬስ ዘንቦባት አሁን ደግሞ የፕሬስ ክፉኛ ድርቅ የመታት ሀገርም ለመሆን በቅታለች።

 

የህትመት ውጤቶች ሃሳብን በጋዜጣና በመጽሔት የመግለፅ አብዮቶች ፈክተው በታዩበት ቅድመ 97 ዓ.ም እንደ ሙሉጌታ ሉሌ የመሣሠሉ ፀሐፊዎችን ታሪክ ያስታውሳቸዋል። ለፕሬስ ነፃነት ግንባራቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ነበሩና ነው።

ሙሉጌታ ሉሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደብረብርሃን ከተማ ኃይለማርያም ማሞ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ የዛሬ 50 ዓመት ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ። ሙሉጌታ በጣም አስገራሚ ሰው ነበር። ልክ እንደ ጳውሎስ ኞኞ እጅግ አንባቢና ተመራማሪ ነበር። ሌሎች ቀጣይ የሆኑ የቀለም ትምህርቶችን አልተማረም። የኮሌጅ ዲፕሎማ እንኳን የለውም። ግን በሙያው ወደር የማይገኝለት ሰው ለመሆን የበቃው በንባብ ነው። ፈረንጆች Book Worm እንደሚሉት አይነት ሰው ነው። መጻሕፍትን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን የሚበላም የሚመስል ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፕሬስን እላይ ሆኖ እስከ መምራት የደረሰው። ለዚህ ነው በነፃው ፕሬስ ውስጥም ትልቅ ብዕረኛ ሆኖ ያለፈው።

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ በተወለደ በ75 ዓመቱ በስደት በሚገኝበት በሰሜን አሜሪካ እሁድ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም እቤቱ ውስጥ በድንገት ሕይወቱ አልፋለች። ብዙ የፕሬስ ባለሙያዎች እና አንባቢያን በዜናው ተደናግጠዋል። ሙሉጌታ ሉሌ አልፏል።

የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በአንጋፋው ጋዜጠኛ በሙሉጌታ ሉሌ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ጓደኞቹ መጽናናትን ይመኛል።n     

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
11813 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us