የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ - ያሳስባል!

Wednesday, 12 February 2014 12:08

ከድንበሩ ስዩም

በሐገራችን ኢትዮጵያ ካሉት የጥናትና የምርምር ተቋማት መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ ብዙ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ነው። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያደረገው ይሔው ተቋም ከአርባ ዓመታት በላይ የሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ነው። ቤተ-መፅሀፍቱ አያሌ መረጃዎች ተሰባስበውበት የሚገኝ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እጅግ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴዎች እየታየበት ነው።

በቀድሞው ዘመን የነበሩ የዚሁ ጥናትና ምርምር ተቋም ሠራተኞችና ኃላፊዎች በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዘንድ በመሄድ በቤት ውስጥ አልያም መስሪያ ቤቶች ውስጥ የተቀመጡ ልዩ ልዩ ሰነዶችን በመለመን፣ በመጠየቅ፣ ካልሆነም ደግሞ በመግዛት ወደዚሁ ቤተ-መፃሕፍ እያመጡ ሲያጠናክሩት ኖረዋል። በዚህ ቤተ-መፅሀፍ ውስጥ ልዩ ልዩ ሠነዶችን ከያሉበት እያመጡ ያከማቹበትና ዛሬ ደግሞ እነዚህ ሠነዶች ለጥናትና ምርምር የሰው ልጆችን ሁሉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ልዩ ልዩ ሠነዶችን እና መረጃዎችን ጠንክሮ የማሰባሰቡ ተግባር አሁን ባሉት የተቋሙ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ዘንድ እጅግ ተቀዘቅዞ እና ደክሞ ይታያል። ተቋሙ ምን ነካው? የሚል ጥያቄ ሁሉ ያስነሳል።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፅሐፍ ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይም እነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሌሎም ሰዎች በቅርበት በሚከታተሉት እና በሚያስተዳድሩበት ወቅት የተሰባሰቡ መዛግብቶች ናቸው? ዛሬም ያሉት። እርግጥ ነው ተቋሙ እየደከመ የመጣው ረዘም ላለ ጊዜ ቢሆንም አሁን ደግሞ በሽታው እየተባባሰበት የመጣ ይመስላል። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ተቋሙ በየእለቱና በየሳምንቱ የሚታተሙትን ጋዜጦችና መፅሔቶች መግዛት ወይም ማስመጣት አቋም ነበር። ይሄ ደግሞ ለወራት የቀጠለ ድርጊቱ ነበር። እናም በነዚህ ጊዜያት የታተሙ የሀገሪቱ ታሪኮች፣ ዜናዎች፣ መረጃዎች ወዘተ በቤተ-መፅሐፍቱ ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል። በዚህም በትውልድ ውስጥ የታሪክ ክፍተት ተከስቷል። ለመሆኑ ለዚህ ክፍተት ተጠያቂው ማን ነው? ማነው ጋዜጦቹ እንዳይገዙ፣ እንዳይሰባሰቡ ያደረገው? ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው?

ይህ በእንዲህ እያለም በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ሌሎችም ችግሮች አሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው አዳዲስ መፅሐፍት ይታተማሉ። በውጭም ሀገራት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ልዩልዩ ሠነዶች ለሕትመት ይበቃሉ። ታዲያ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ማናቸውንም ሠነዶች መሠብሰብ የሚገባው ይህ ተቋም ተግባሩን የዘነጋው ይመስላል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት እየታተሙ ያሉትን የህትመት ውጤቶች በቤተ-መፃህፍቱ ውስጥ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። በዚህ መንግስት ዘመን የተጻፉ ሠነዶች ለታሪክ መቀመጥ ይገባቸዋል። አሁን በስፋት የሚገኙት ቀደም ባሉት ስርአቶች ውስጥ የተፃፉት ናቸው። ለመሆኑ ይሄስ መንግስት ቢሆን ታሪክ አያስፈልገውም? ትውልዱስ ቢሆን በዚህ ዘመን የተሰሩትን ተግባሮች የማወቅ መብት ያለውም? ቤተ-መፃህፉ የአዳዲስ የህትመት ውጤቶች ባለቤት ባለመሆኑ የታሪክ ክፍተት እየፈጠረ ነው። ታዲያ ተጠያቂው ማንነው? ማነው ኃላፊው? ማነው ከልካዩ?

በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መፃሕፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎችና ሌሎችም እንደኔ ተራ የሆነ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ፅፈው ያስቀምጧቸው ፅሁፎች፣ ፎቶ ግራፎች፣ መፅሐፎች፣ ማስታወሻዎች፣ የሠርግ ጥሪ ካርዶች እና ሌሎም ሠነዶች እየተሰባሰቡ የተከማቹበት ነው። ታዲያ እነዚህን ሠነዶች ለማሰባሰብ ነው። ይህን ኃላፊነት ተቀድሞዎቹ ሠራተኞች ተወጥተውታል። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ከቀድሞዎቹ በተሻለ ሁኔታ መተግበር ሲገባው ስራው ግን በእጅጉ ተዳክሞና ተቀዛቅዞ ይታያል። ይህ የሆነው ምናልባት ከላይ እየተሾሙ የሚቀመጡት ሠዎች ስለ ተቋሙ ያላቸው ግንዛቤና ፍቅር የሞቀ ባለመሆኑ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በቅጡ የማያውቁና ከአሜሪካ ድንገት መጥተው ተቋሙን ሲያስተዳድሩት የነበሩት ኃላፊ ይህን ያህል የተሻለ ነገር ያመጣሉ ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ተቋሙን አልለመዱትም። በተቋሙ ውስጥ እያነበቡ እያወቁ አላደጉም። ለተቋሙ ያላቸው ፍቅር አልተለካም። በመሆኑም ተቋሙ የትውልድ ት/ቤት መሆኑን በውስጣቸው አሳድገው ያበለፀጉ ኃላፊዎች ናቸው የሚያስፈልጉት።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ኢትዮጵያን የሚገልፁ ማናቸውንም ነገሮች መሰብሰብ ይገባዋል። ነገር ግን ተቋሙ የአሰራር አድማሱን እንደ ዘመኑ ጥያቄ እያሳደገ ባለመምጣቱ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ውስጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማሰባሰብ አልቻለም። ለምሳሌ በየጊዜው ልዩ ልዩ ፊልሞች ይመረታሉ። እነዚህ ፊልሞች የዚህ ዘመን አሸራዎች ናቸው። ለሚቀጥለውም ትውልድ የታሪክ ሠነዶች ናቸው። ታዲያ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሊያሰባስባቸውና በሠነድነት ሊያስቀምጣቸው በተገባ ነበር። ግን በዚህም ረገድ ድክመቶቹ ይታያሉ። ፊልሞቹ ብቻም አይደለም መሰባሰብ የሚገባቸው፤ የፊልሞቹ ፅሑፎች /Script/፣ በየቴአትር ቤቱ ያሉ የቴአትር ፅሁፎች፣ ሙዚቃዎች። ሲዲ እና ዲቪዲዎች እና ሌሎም የዘመኑ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶችን ሁሉ ተቋሙ ማሰባሰብ ይገባዋል ባይ ነኝ።

ቤተ-መፅሐፉን በተመለከተ በአንድ ወቅት ፐሮፈሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሲናገሩ፣ በውስጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፃህፍትና አርቲክሎች እንዳሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መፅሔቶች መኖራቸውን፣ ከሶስት ሺህ በላይ ጥናታዊ ሚኒስክሪብቶች መኖራቸውን፣ ከአስራ አራት ሺ በላይ በአርካይቭ ውስጥ ያሉ ሠነዶች እና አርባ ሺ ፎቶግራፎች እንዳሉ ገልጸው ነበር። ፕሮፌሰሩ የገለጿቸው እነዚህ ሠነዶች ጥናት የተሰባሰቡ ናቸው። ይሔ የማሰባሰብ ትጋት አሁን ባሉት ኢትዮጵያዊያን ኃላፊዎች ላይ በውስጣቸው አለ ወይ? ስሜቱ፣ ፍቅሩ፣ ሩጫው፣ በየመድረኩ ቤቱመጻሐፉን ማስተዋወቅ፣ ቀጥሏል ወይ?

በዚህ ቤተ-መፅሀፍ ውስጥ ከአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ በሌሎች የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ቋንቋዎች የተፃፉ ሀገራዊ ጉዳዮች ይገኛሉ። በማይክሮ ፊልሞች የተቀረፁ ልዩ ልዩ ሠነዶች እና የመጀመሪያ ድግሪ፣ የማስትሬት ድግሪ፣ የዶክተሬት ድግሪ መመረቂያዎችንም ይገኛሉ። እነዚህን ሰነዶች፣ ለማወቅ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለመስራት አያሌ ተጠቃሚዎች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት ወደ እዚሁ ቤተ-መፅሃፍ በመምጣት ይገለገሉበታል። ቤተ-መፅሃፉ ቀድሞ በነበረው አደረጃጀቱ እስከ አሁን ድረስ ተወዳጅ መሆኑ የሚያስደንቀው ሲሆን፣ ግን አሁን ያሉት ኃላፊዎች ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው እኔ ከመጣሁ በኋላ ከባለፈው የተሻለ ምን አደረኩ? ምን የጨመርኩት ነገር አለ? እያሉ ዘመናቸውን መመርመር ይገባቸዋል።

አሁን በቤተ-መፃሕፍቱ ውስጥ ተመልካች አጥተው የተከማቹ ጋዜጦችና መፅሔቶች የትየለሌ ናቸው። ጠርዞ የሚያስቀምጣቸው ሰው በመጥፋቱ ለአመታት የሠራተኛ ያለህ እያሉ እያለቃቀሱ ናቸው። መቼም ኃላፊ የሚባል አካል ካለ በየቀኑ ሲወጣ ሲገባ ዝም ብሏቸው ማለፍ ያለበት አይመስለኝም። ብዙ ቤተ-መፅሐፍቶች ያሏቸውን ሠነዶች ወደ ዲጂታል አርካይቭ እየቀየሯቸው እና ኮምፒተራይዝድ በሆነ መንገድ በሚያደራጁበት ወቅት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ -መፅሀፍ የመጡለትን ጋዜጦች መጠረዝ አቅቶት ሲከምራቸው ማየት ያሸማቅቃል።

ወደዚህ ቤተ-መፅሀፍ፣ ከተጠቃሚዎች ሌላ ቱሪስቶችም ይመጣሉ። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በውስጡ ሙዚየምም ስላለው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች አብዛኛዎቹ ወደዚህ ሙዚያም መጥተው ይጎበኛሉ። እግረ-መንገዳቸውንም ወደ ቤተ-መፃህፍቱ ጎራ ብለው ያያሉ። አሁን አሁን ደግሞ በተለይ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፉ ሠነዶች ያሉት ቤተ-መፅሐፍ የፅዳት ጉድለትም እየታየበት ነው። የመሬቱ ወለል ላይ የሚታተሙ አቡወሯ ቤተ-መፅሃፉን አይመጥነውም።

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ሌላ ጉዳይ ደግሞ የቤተ-መፅሐፉ ሠራተኞች ትጋት እና ትህትና ነው። የመጣውን እንግዳ በስርዓት የሚያስተናግዱት ሁሉም ሠራተኞች መመስገን አለባቸው። ለማንበብ እና መረጃ ለመጠየቅ የመጣን ሰው ፍፁም ትህትና በተላበሰ ሁኔታ የሚያስተናግዱ ናቸው።

በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚገልጽ መስታወት ነው። አያሌ ቱሪስቶች ወደ ሀገሪቱ መጥተው የሚያዩት ተቋም ነው። በተለይ ሙዚያሙ በተማሩ ሰዎች በቂ መረጃ የሚሰጥ ነው። ነገር ግን መብራት ድንገት ሲጠፋ ጀኔሬተር ባለመኖሩ ባህር አቋርጠው ሊያዩን የመጡት ቱሪስቶች መብራት የለም ተብለው ሲመለሱ ማየት ሌላው አሸማቃቂ ጉዳይ ነው። ለመሆኑ ይሔን የሚያክል ተቋም እንዴት ጄንሬተር የለውም?ተራ የግለሰቦች ቤት መብራት ሲጠፋ በጄኔሬተር ሲጠቀሙ የኢትዮጵያ መስታወት ነው ተብሎ የሚታሰበው ይሄው ሙዚየም ግን መብራት ከጠፋ ዳፍንት ሆኖ አገልግሎት መስጠት ያቆማል። ይሄም በአስቸኳይ መስተካከል የሚገባው ጉዳይ ነው።

በመጨረሻም ማለት የምፈልገው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አያሌ የተማሩ ሠዎችን በውስጡ ያቀፈ ከመሆኑ አንጻር ብዙ አቅም ያለው ነው። ግን ሠርቶ የሚያሰራ ኃላፊ ያስፈልገዋል። ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት ድንገት እየመጡ የሚሾሙ ሰዎች የጎላ ለውጥ ሳያመጡ ተነስተዋል። አሁን ያሉት ኃላፊ ደግሞ የታሪክ ምሁር ከመሆናቸው አንጻር ብዙ ይጠበቅባቸዋል። እስከ አሁን ድረስ ሲንከባለሉ የመጡትን ችግሮች ቀርፈው ከባለፉት የተሻሉ ለመሆን በመጀመሪ ተቋሙን መውደድ፣ ከዚያም የቀድሞውን አይነት ስራ ሰዎችን ማለትም ቤተ-መፅሃፉን ለማደራጀት የሚጥሩትን ሰዎች መደገፍና እርሳቸውም ከፊት ሆነም መምራት በእጅጉ ይጠበቅባቸዋል። “ይህ ቤት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቤት ነው” ብለው የነበሩት ከ10 ዓመት በፊት የተቋሙ ዳይሬክተር የነበሩት ፕ/ር ባዬ ይማም ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቤት የሆነውን ይሄን ተቋም ክብሩን አናጉድልበት። ሞገሱን ከፍ ከፍ እናድርግለት። እንውደደው።

በነገራችን ላይ ይህን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የበለጠ ለማስፋፋትና ለማሳደግ በሚል መርሃ ግብር ሌላ ሕንፃ መታነፅ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ ነበር። የህንጻውና የተቋሙ ስም በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስም የሚጠራ ሲሆን፣ አሁን ግን የመጓተት አባዜ ተጠናውቶት አላልቅ ብሏል። እንደውም ስራው በጣሙን ተቀዛቅዟል።

የዚህ ሕንጻ መታነፅ ሊያመጣ የሚችለው እጅግ ከፍተኛ ነበር። ህንፃው እነዚህን ከላይ የገለፅኳቸውን ችግሮች ይቀርፋል ተብሎ ይታሰብ ነበር። እርግጥ ነው አዲስ ህንጻ ስለተሰራ አዲስ ሃሳብ ወዲያው አይወለድም። አሮጌ ሃሳብ ይዘን አዲስ ህንጻ ውስጥ መግባትም ተገቢ አይደለም። በመጀመሪያ ሁሉንም የቤት ስራዎች በዚህ በቀድሞው ህንጻ ላይ መጨረስ አለብን።

     እ.ኤ.አ. በ1962 ዓ.ም የተቋቋመው ይሔው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሚገኝበት ህንፃ ውበትና ግርማ ሞገሱ አማላይ ነው። ምክንያቱም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቤተ-መንግስት የነበረ ቤት ውስጥ ነው የሚገኘው። ንጉሡ ለትምህርት ባላቸው ቀናኢነት ከአባታቸው የወረሱትን ቤተ-መንግስታቸውን ለተማሪዎችና ለትምህርት ሰጥተዋል። ታዲያ አሁን ከ50 ዓመት ወዲህ ያለው ትውልድ በስጦታ የተረከበውን ቤት የኢትዮጵያን ሕዝቦች የታሪክ እና የማንነት እንዲሁም የፍልስፍና፣ የጥበብ ወዘተ ሠነዶችን ሰብስቦ በማኖር የሐገር መገለጫ ሊያደርገው ይገባል ባይ ነኝ።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
12977 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us