የኢሕአፓው ደራሲ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው)

Wednesday, 21 October 2015 15:09

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

የ1960ዎቹ ወጣቶች ውስጥ ስሙና ዝናው በእጅጉ ይታወቃል። የኢሕአፓ ታጋይ የነበረው አስማማው ኃይሉ። ቅፅል ስሙ አያ ሻረው ይሰኛል። ጎንደር ከተማ ላይ ተወልዶ ያደገው አስማማው ኃይሉ የወጣትነት ህይወቱን እስከ መጨረሻው ድረስ ለሚወደው ለኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሰጠ ነበር። አስማማው ኃይሉ ከያ ትውልዶች ውስጥ ምርጥ ብዕር አላቸው ተብለው ከፊት ተሰላፊዎቹ ምድብ ውስጥ ነው። ታሪክን፣ ባህልን፣ ስነ-ልቦናን በሚደነቅ የቋንቋ ችሎታው ሲያስነብበን የከረመው ተወዳጅ ፀሐፊ አስማማው ኃይሉ /አያ ሻረው/ ሰሞኑን በሚኖርበት በሰሜን አሜሪካ ሕይወቱ አልፋለች።

አያ ሻረው /አስማማው ኃይሉ/ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው በልዩ ስብዕናው ነበር። በቅርብ የሚያውቀው ጓደኛው የቴአትር ባለሙያው ዘላለም ብርሃኑ ሲናገር፣ አስማማው እጅግ ቸር የነበረና ያለውን ለማንም እየሰጠ ባዶውን የሚኖር ልዩ ፍጡር ነው ሲለው ገልፆታል። በዚህም የተነሳ ከውብ ብዕሩና ሃሳቡ በስተቀር ገንዘብም ሆነ ቤት የሌለው ግን የትልልቅ ሃሳቦች መናኸሪያ የነበረ ደራሲ እንደሆነ ዘላለም ብርሃኑ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጿል። ኢትዮጵያም ያጣችው ታሪክን፣ ክስተትን በውብ ቋንቋ እየከሸነ የሚያስነብበንን የያን ትውልድ ደራሲ ነው።

አስማማው ኃይሉ በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስነበበን ድርሰቱ “ከደንቢያ -ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” የደራሲው ታሪካዊ ልቦለድ መፅሐፉ ነው። በሀገራችን የልቦለድ መጽሐፍት ውስጥ እንደታተመ ወዲያው ያለቀ እና በእጅጉ የሚወደድ መፅሐፍ ነበር። ከዚያም በዚሁ ርዕስ ቁጥር ሁለቱን አሳተመ።

ሦስተኛውና አራተኛው የአስማማው መፅሐፍ ኢሕአሠ /የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት) ከ1964-1970 ዓ.ም ቅፅ አንድ እና ቅፅ ሁለት መፃሕፍት ናቸው። እነዚህ ሁለቱ መፃሕፍት የኢሕአፓ የጦር ሠራዊትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ እና ደራሲው ራሱ ያለፈባቸውን የሕይወት መንገዶች ያሳየባቸው ናቸው።

አስማማው ኃይሉ ያለፈበትን ታሪክ መፃፍና መተረክ የሚችል ደራሲ ነው። በብዕሩም በአንደበቱም የሚያረካ የዚያ ትውልድ ምስክር ነበር። የኢሕአፓን ታሪክ በጥልቀት እና በስፋት እንደፃፈው የሚታወቀው የፓርቲው መስራችና ከፍተኛ አመራሩ ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ በተሰኙት ሶስት ተከታታይ መጻሕፍቶቹ ውስጥ አስማማው ኃይሉን እየደጋገመ አመስግኗል። ክፍሉ ታደሰ እነዚህን መፃህፍት በሚያዘጋጅበት ወቅት አስማማው ኃይሉ በርካታ ድጋፍ አድርጎለታል። ስለዚህ የኢሕአፓ ታሪክ በተፃፈ ቁጥር ስሙ በአንድም በሌላም የሚጠቀሰው አስማማው ኃይሉ ከታጋይነቱ ባሻገር አይረሴ ማንነቶች እንዳሉት ጓደኞቹ አጫውተውኛል።

1960ዎቹ ውስጥ፣ አስማማው የኢሕአፓ ታጋይ ከመሆኑ በፊት ጎንደር ከተማ አራዳ ልጇን ጥሪ ብትባል የምትጀምረው ከአስማማው ኃይሉ ነው። አስማማው ለስልጣኔ እና ለዘመናዊነት ቅርብ የሆነ፣ በዘመኑ ዘናጭ የነበረ፣ ሽቅርቅር፣ ውበት ከቁመና ጋር የሰጠው ጎምላሌ ተክለ ሰውነት ያለው የጎንደር ልጅ ነበር። ከማንም ጋር በቀላሉ መግባባትና መጫወት ጓደኛ የመሆን ልዩ ተፈጥሮ የተሰጠው የ1960ዎቹ የከተማዋ አራዳ ነበር። እናም የኢሕአፓ መስራቾችና ታጋዮች የጎንደር ወጣቶችን በሙሉ የኢሕአፓ አባል ለማድረግ በሕዝቡ ዘንድ ታዋቂ እና ተወዳጅ የነበረውን ሽቅርቅሩን አስማማው ኃይሉን አሳምነውት የራሳቸው አደረጉት። እናም ኢሕአፓ ጎንደር ውስጥ አስማማው ላይ “መስተፋቅር” አስቀምጣ በወጣቶች ልብና መንፈስ ውስጥ እንደልቧ ዋኘች። የኢሕአፓም ዋነኛ መናኸሪያ የነበረችው ጎንደርና አካባቢዋም እንዲህ አይነት ስመ ገናና ወጣቶች ስለነበሩዋት የፓርቲው ማህፀን ሆነች።

አስማማው ኃይሉ የኢሕአፓ ታጋይ ሆኖ ከደርግ ስርዓት ጋር ሲዋጋ የነበረ ነው። የከተማ ያውም ያራዳ ልጅ ቢሆንም ከፈለገ ድምፁን ቀይሮ ሙልጭ ያለ የጎንደር ገበሬ መሆን ይችላል።

ስለ ሕይወትና ተፈጥሮ የሚፈላሰፍ፣ ነገሮችን እና ከስተቶችን በተለያየ አቅጣጫ ማየት መተንተን የሚችል ደራሲና ታጋይ ነበር። አሁን በቅርቡ እንኳን በካንሰር ሕመም መጠቃቱን የሚያክመው ዶ/ር፣ ሕመምህ ካንሰር ነው ብሎ እንዳይነግረው ሲፈራ ሲቸር አስማማው አስተዋለው። ከዚያም አስማማው ዶክተሩን እንዲህ አለው፡-

ዶክተር አይዞህ አትፍራ። እኔ እንዲሁ ሕይወቴ ሁሉ በብዙ ጭንቅ ውስጥ ስላለፈች አልፈራም። ከችግር ጋር ኖሬያለሁ። ለምን ነገር አልደነቅም፤ በሽታዬን ንገረኝ አለው። ዶክተሩም ነገረው። አስማማው ግን አልደነገጠም። ወዲያው ያደረገው ነገር ቢኖር የጀመረውን መፅሐፉን ጨርሶ ማጠናቀቅ ነበር። በካንሰር ሕመም ውስጥ እያለ መፅሐፍ አዘጋጅቶ ያለፈ ሕያው ደራሲያችን ነው። ይህ መጽሐፍም በቅርቡ ለንባብ ይበቃል።

በስልሳዎቹ የዕድሜ አጋማሽ ላይ የነበረው አስማማው ኃይሉ የዛሬ ስድስት ዓመት እዚህ ሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መጥቶ ዘላለም ብርሃኑ ካስተዋወቀን ጀምሮ የሚደንቀኝ የቋንቋ ብቃት ያለው ደራሲ ነበር። ዛሬ ያ ሁሉ የህይወት ውጣ ውረዱ ተከተተ። የኢሕአፓ ታጋይ ሆኖ፣ ሕይወቱን ለፓርቲው ሰጥቶ፣ ጓደኞቹ በዱር በገደሉ፣ በየከተማው አልቀው፣ የቀሩትም በየፊናው ተበታትነው የታሰበው ሁሉ ሳይሆን ቀርቶ፣ ታሪክ ብቻ (ነበር ብቻ) አስማማው ኃይሉ እጅ ቀረ። ያንን ታሪክ ግን ወርቅ በሆነ ብዕሩ ፅፎታል። ለማስታወሻ ያህል ሰንደቅ ጋዜጣ “ከደንቢያ - ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” የተሰኘው የአስማማው ኃይሉ መፅሐፍ እንደታተመ በጓደኛው በካሊድ የተፃፈውን የሚከተለውን ፅሁፍ አውጥታ ነበር።

አሜሪካን ሒውስተን ቴክሳስ የሚኖረው ፀሐፊ አስማማው ኃይሉን የምናውቀው  (አያ ሻረው) የሚል ቅጽል ስሙ ነው። ይህ ስም እንደፈረስ ስም የተሰጠው ደግሞ በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጐንደር ውስጥ የትጥቅ ትግል አካሂዶ በነበረውና በኋላም በተበታተነው የኢህአፓ ሰራዊት /ኢሕአሠ/ ውስጥ ተሳታፊ የነበረ አንዱ ገበሬ፤ ድርጅቱ ሲበተን ሱዳን ገብቶ ቀጥሎም በአሜሪካ የስደተኞች መልሶ ማቋቋም ኘሮግራም ታቅፎ አሜሪካን ሲኖር ያሳለፈውንና እየኖረበት ያየውን እንግዳና ግራ የተጋባ ሕይወቱን ጐንደር አርማጭሆ ሳለ (አያ ሻረው) ለሚባለው አጐቱ የፃፈውን ደብዳቤ በግጥም መልክ ስለፃፈው ነው።

ደራሲ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው) የሚለውን ግጥሙን የወደድንለት በዛ ጐንደሬ ገበሬ አይን የምእራቡ አለም እንዴት መስሎ እንደሚታይና ብልጭልጭ ወከባ የበዛበት ይሉኝታ የሌለበት' ነውር የማይታወቅበት መቅኖ ቢስ ስልጣኔ ውስጥ ገብቶ እየዳከረ እንደሚገኝ የገለፀበት ረጅም ግጥሙ የገበሬውን ሕይወት ለምናውቅና የውጭውንም አለም ምንነት በተለያየ መንገድ በመጠኑም እንኳ ቢሆን ለመረዳት ለቻልን ሰዎች ሁሉ አዝናኝና አስተማሪ ሆኖልን ደራሲውን እንድናደንቀው አድርጐን ቆይቷል። ደራሲ አስማማው ኃይሉ አሜሪካ ያለውን ጐንደሬ ገበሬ አስተሳሰብ በግጥም ጽፎ እራሱ እያነበበ በካሴት ስላዳመጥነው መቼም ቢሆን (የአያ ሻረው)ን ለዛ እንዳንረሳው አድርጐን ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የታተመውና ገበያ የዋለው ከደንቢያ ጐንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ የተባለው የአስማማው ኃይሉ /አያ ሻረው/ ልብወለድ መጽሀፍ በጉጉት ጀምሬ ያለ ፋታ አንብቤ ስጨርስ ደራሲውን እንደ ግጥም ችሎታው ሁሉ የረጅም ልቦለድ ሥራውም ይበል የሚያሰኝ ሆኖ በማግኘቴ ያላየሁትን ይሁንና በስራው ሳደንቀው የኖርኩትን አስማማውን /አያ ሻረውን/ የበለጠ እንዳመሰግነው አስገድዶኛል።

አዲሱ ልቦለድ መጽሀፍ በጭብጥ ደረጃ ሲታይ አሁንም /የአያ ሻረው /ግጥም ፍሬ  ሀሳብ በዘመናዊና በተማሩ ገፀ ባህርያት ምልከታ ታሽጐ የቀረበበት የባህልና የአስተሳሰብ ተቃርኖ ላይ በስፋት ያተኮረ ነው።

(ከደንቢያ -ጐንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ) በተባለው በዚህ ድርሰት ዋናው ገፀ ባህሪይ ስለሽ ተወልዶ ያደገው ጐንደር ደንቢያ በተባለው አካባቢ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ስለ እውነት፣ ስለ እምነት፣ ስለ ሩህሩህነት፣ ስለ ጀግንነት፣ ስለ ይሉኝታ እየጋተ በሚያሳድገው መደበኛ ባልሆነ ትምህርት ታሽቶ የወጣ ነው። በወላጅ እናቱ ግፊት አስኳላ ትምህርት ገብቶ ጐንደር ከተማ ተምሯል። በእድገት በህብረት ዘመቻን ደቡብ ውስጥ አገልግሏል። ወቅቱ ኢሕአፓ የገነነበት ወጣቱም (በትግል መሞት ሕይወት) ያለበት ሆነና እሱም የኢሕአፓ መንቀሳቀሻ ወደነበረው የትግራዩ አሲንባ አቅንቶ ነበር። እነሱም በዛ በትጥቅ ትግሉም ሆነ በድርጅቱ /ኢሕአፓ/ በቆየባቸው ጊዜያቶች ከጐንደሬነት አስተዳደጉ በላይ የግራ ዘመም ፍልስፍና ጨምሮበት ስብእናው ደንድኖ እያለ በድርጅቱ መፈራረስ ምክንያት ሱዳን የገባና ከሌሎች (ጓዶቹ) ጋር ወደ አሜሪካ ለመሄድ የቻለ ነው።

 ይህ ገፀ ባህርይ /ስለሽ/ በጐንደር ስነልቡና ማደጉና በግራ ፍልስፍና መታሸቱ አዲሱን የአሜሪካ ሕይወት አንዳይላመደው እንቅፋት ፈጥሮበት ይታያል። አገሩን እንዲያላምዱት የተቀበሉት አሜሪካዊያን ቤተሰቦቹ /ሚስስ አና ሚስተር ፓርከር/ የሰጡት ፍቅር ያደረጉለት ውለታ አምኖበት ከቆየው ኢምፒሪያሊዝም ስግብግብ ነው ከሚለው የግራ ዘመም አመለካከት ጋር ተፋልሶበት እራሱን እንዲታዘብ ብቻ ሳይሆን እነኝህን አዲስ ወላጆቹን ሁሌም እንደሚያስታውሳቸው ወላጅ እናቱ ባለ ውለታ መሆናቸውን እንዲያምን አድርጐታል።

ዋናው ገፀ ባህርይ (እግረ ደረቅ) ሆነ መሰለኝ እሱን እንዲያ የተቀበሉትና እንደልጃቸው የሚያዩት (ወላጆቹ) ተደራራቢ ፈተና ሲደርስባቸው እሱም አብሮ እየተፈተነ እናያለን። ያ የሱ ፈተና ግን እራሳቸውም ፈረንጆች የማይረዱትና የማያስጨንቃቸው ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ እየባከነ መኖር ግድና ባህል በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ስለሽ በጐንደሬ ይሉኝታና በኢትዮጵያዊ ትህትና ታንቆ የፈረንጅ ወላጆቹን ጥሎ ላለመሄድ ሲሰቃይ እናያለን።

ከሁለት ዓመት በኋላ ዋሽንግተን ነዋሪ በሆኑ በቀድሞ ጓደኞቹ ግፊትና መከራ ባደከማቸው የፈረንጅ እናቱ ይሁንታ ኒውጀርሲ ትሪንተንን ለቆ በርካታ ሀበሾች በሚገኙበትና የፖለቲካ ክርክርና ወሬ የእህል ውሀ ያህል ከሚናፈቅበት ዋሽንግተን ኑሮውን ሊያደላድል ሲሞክር የገጠመው ፈተናም ይሄው ያደገበት ባህልና ወገንተኛ ያልሆነ የአስተሳሰብ ቅኝቱ ከሌላው ወገኑ ጋር መጣረሱ ነው።

የረባ የፍልስፍና መሠረት ሳይኖራቸው ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚተነትኑና ከራሳቸው አልፈው ሌላውንም የእነሱ ተከታይ ሊያደርጉ የሚሯሯጡት አሜሪካ ነዋሪ ወገኖቹ እንቅስቃሴ እያስጠላው በዘር ሐረጋቸው በአብሮ አደግነታቸውና በቤተሰብ ቅርርባቸው ተሰባስበው ሌላኛውን ወገን የበለጠ ለማራቅ የሚጥሩ ሌሎች ወገኖቹም ቢሆኑ አልጥምህ እያሉት የፖለቲካ ባይተዋር የዋሽንግተን መናኝ ሲሆን እናያለን።

ደራሲ አስማማው ኃይሉ /አያ ሻረው/ የግጭት መነሻ ያደረጋቸው የባህልና የአስተሳሰብ ተቃርኖዎች ኢትዮጵያዊያን ከአሜሪካው አስተሳሰብና ባህል ጋር ምን ያህል እንደምንርቅ ብቻ ሳይሆን በራሳችንም /በኢትዮጵያዊያን/ውስጥ እንዳደግንበትና እንደተወለድንበት ማኅበረሰብ የሚለያይ እሴት እንዳሉንም በሚገባ አስቀምጦታል።

ዋናው ገፀ ባህርይ ስለሺ በኢሕአፓ ውስጥ አብረውት ክፉና በጐውን ካሳለፉት ይሁንና አስተዳደጋቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ማእዘናት ከሆኑት ጓደኞቹ ጋር እጅግ ይዋደዳል፣ ይነፋፈቃል፣ ያግዙታል። ይሁንና ከእነሱም ጋር ቢሆን አብረውት የማያኖሩ የማያስማሙ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል።

በ24ዓመቱ የአሜሪካን ሕይወት መጋፈጥ የጀመረው ስለሺ አግብታ የፈታችና ሴተ ላጤ ከሆነች ወጣት ጋር የጀመረው የፍቅር ግንኘነት ሲደምቅ ሲቀዘቅዝ መልሶ ተጠግኖ ዳግም ሲፈርስ እንደገናም ተጠጋግኖ አብሮ እስከመኖር ከደረሰ በኋላ ጭራሸን ሲፈረካከስ እናያለን።

በተለይ ከመጽሐፉ አጋማሽ ጀምሮ እየጐላ የመጣው የስለሺ እና የፍቅረኛው የመሠረት ግንኘነት ፍቅርና ውጥረት የሞላበት በመሆኑ የአሜሪካን አገር የትዳርና የፍቅር ግንኙነት ሳንካዎችን ከርቀት እንድንገነዘባቸው አድርጐናል።

ከጐንደር ገጠር ተወልዶ ስለ እውነትና ስለ ይሉኝታ አስተምረው ካሳደጉት ከገበሬ ዘመዶቹ በላይ ክብር የሚሰጠው የሌለው ስለሺና አዲስ አበባ ተወልዳ ጥሩ ለብሳ ተሽሞንሙና አድጋ በአጋጣሚና በእድል ሳይሆን በባለስልጣን ዘመድ እገዛ ጀርመን ቀጥላም አሜሪካ የገባችውን ፍቅረኛው ጨዋታቸው መቼ እንደሚደፈርስ ፍቅራቸው መቼ እንደሚቀሰቀስ ስናስተውል የአሜሪካው የኑሮ ዘይቤ ከፈጠረው የግለኝነት ስሜት በላይ በራሳቸውም በኢትዮጵያዊያን የተለያየ አስተዳደግና አስተሳሰብ የልዩነት ስፋት አንዳንድ የባህር ማዶው ትዳር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በሚል መተሳሰብ እንዳልተገነባ ቁልጭ አድርጐ ድርሰቱ ያሳየናል።

የፍቅርና የትዳር ትስስር ምክንያቱ ከእውነተኛ መተሳሰብ ይልቅ ለተለያዩ ጊዜያዊ ግቦች ሊሆን እንደሚችልም ደራሲው እያዋዛ የገለፀበት ስልት አስገራሚ ነው። ለፍቅርና ለፍቅረኛ ባይተዋር የሆነው ስለሺን አክንፋ የነበረችው መሠረት እዩልኝ እንደማለት ወደ ተለያዩ የዋሽንግተን መዝናኛ ሥፍራዎች እንደምታዞረው ሲገልጽ እንዲህ ይላል።

“እንደምገምተው ከሆነ የኔ ውበትና ቁመት እንደምርጥ ኮርማ በየመንደሩ እየጐተቱ በማዞር ለናሙና እታይ ዘንድ የሚያደርስ አይደለም። መሠረት ከኔ ጋር በመታየቷ ከምትኩራራብኝ ይልቅ እኔ እሷን ከመሰለ ውብ ሰንቦዳ ጉብል ጋር በየመንገዱ በመታየቴ ጮቤ ልረግጥ ይገባኝ ነበር። የዚህ ሁሉ ድራማ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ በመላምት ሰካክቸ ራሴው እንደመሰለኝ  መለስኩት። ከሱራፌል /የቀድሞ ባሏ/ ጋር ከተለያየች በኋላ ከብዙ ሰዎች ጋር ተነጣጠለች። ሱራፌልን ለመበቀል ስትል በወሰደችው እርምጃ ተንኮለኛዋና ሰይጣን እየተባለች ትጠራ እንደነበር ታውቅ ስለነበር ሐበሻ ባየች ቁጥር ስትበረግግ ኖራለች።

ስለዚህ ከኔ ጋር መታየቷን የአያሌዎችን አሉታዊ ግምት የምታከሽፍበት ገጠመኝ አድርጋ መጠቀም እየፈለገች ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሱራፌል ሚስት አግብቶና ልጅ ወልዶ እንደሚኖር በማወቋ ያደረባትን ቅናት ተወጥታ እኔንም የሚፈልገኝ ወንድ አለ ያውም በቁመና ካንተ የተሻለ የሚል መልእክት በወሬ ወሬ ይደርሰው ዘንድ ስላሰበች ነው ብዬ አሰብኩ። የሱራፌልን እህቶች ወይም ጓደኛቻቸውን ባየች ቁጥር በጉንጨና በከንፈሬ ድንበር አካባቢ እንደ በኸር ልጇ ትሞጨሙጨኝ እንደነበር ሳስታውስ በሄድንበት ሁሉ የሱራፌል እህቶች ናቸው የሚባሉትን ብናገኝ ምኛቴ ሆነ። ከላይ ከተጠቀሱት የልብ ቁስሎቿ ለመሻር በምታደርጋቸው ጦርነቶች ሁሉ በድል ትወጣ ዘንድ ወደ ውጭ ስትወጣ መሠረት የማትረሳን መሳሪያዎቿ እኔንና ቦርሳዋን ሆነ።

ደራሲ አስማማው ኃይሉ የራሱ ስብእና የተንፀባረቀበትና ማስተላለፍ የፈለገውን መልእክት ለማስተላለፍ የበቃበት ብዬ በገመትኩት በዚህ መጽሐፍ በውጭ የሚኖረው ወገን ካላደገበት እና እንግዳ ከሆነ ዘመናዊ አኗኗርና ባህል ጋር ለመላመድ የሚያደርገው ትግል እጅግ ውስብስብነቱ ጐልቶ ወጥቷል። አገር ከለቀቁ በኋላ እንደ አገር እና እንደወገን የሚናፍቅ ነገር የለምና ለአገር የበልጥ ከመጨነቅ በሚመነጭ ይሆንና ያለ እውቀት በስሜት ከሚገፉ ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ለበለጠ መወናበድ ለበለጠ መራራቅ የተዳረገ ወገን በአሜሪካ እንዳለ አሳይቶናል።

ይህንን እንደጨው ዘር የተበተነ ባይተዋር ስሜታዊ ወገን ወደ አእምሮው ተመልሶ የሚወዳት አገሩን እንደስስት የሚቆጭለት ወገኑን እንደናፈቀ እንዳይቀር አገርህ ዛሬም አገርህ ናት በማለት በትእግስት የሚያግባባ ክፍል እንዳላገኘ ይህ መጽሀፍ እንድንረዳ ያደርገናል።

የደራሲ አስማማው ኃይሉን መጽሐፍ የቋንቋ ፍሰቱን ብቻ ሳይሆን ውበቱም ድንቅ ነው። የዘመናዊነት ውጤት የሆኑትን ሁለንተናዊ እሴቶች የገለፀባቸውን ስልቶችም ሆነ በእነዚህ እውነታዎች ውስጥ የኢትዮጵያዊያንን ፈተና ያስቀመጠባቸውን አገላለፆች እየጣፈጠኝ አጣጥሜዋለሁ። ዋናው ገፀ ባህርይ ስለሽ አሜሪካ ውስጥ ሲከፋም ሆነ ጥቂት ሲደሰት የሚያስታውሳቸውን ሟች እናቱን ‘የትግራይ’ ‘የሱዳንና’ ‘የጐንደር’ ትዝታዎቹን ያቀረበባቸው የምልሰት (Flash Back) አፃፃፍ ስልቱንም አድንቄለታለሁ። ከፖለቲካ ውጭ ሆነው ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ሰዎች አገራቸውን የጠሉና የረሱ ማለት እንዳልሆነ ይልቁንም ከስሜት ነፃ ሆነው ነገሮችን ለመገንዘብ አቅም እንዳላቸው ለማሳየት በገፀ ባህርዮች አማካኝነት የገለፀበትን መንገድ ትምህርት አግኝቸበታለሁ። በአገራችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በባህር ማዶም ጭፍን የጥላቻና የድጋፍ ስሜቶች ምን ያህል እንዳራራቁን ይበልጥ አይቸበታለሁ።

ደራሲው ኢሕአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ በአሜሪካን የነበረውን የሐበሻዎችን ሁኔታ በገፀ ባህርይው ስለሽ አማካኝነት የገለፀው እንዲሀ ነበር።

በዚሁ ሰሞን ነበር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ መቀየርም የጀመረው። የሚፈጠሩት ሁኔታዎችም የቤታችን ችግር ሆነው ቀስ በቀስ ያወዛግበን ጀመር። ደርግ ከስልጣን ወርዶ ኢሕአዴግ ስልጣኑን ይዟል። የኤርትራም ነፃነት እውን እየሆነ በመምጣቱ የሚያነጋግር አጀንዳ ሆነ። በዋሽንግተን አካባቢ የሚገኙት የሬዲዮ ጣቢያዎች በእዚህ አገራዊ አዲስ ክስተት መወያየትንና ማወያየትን እንደዋነኛ ተግባራቸው ተጠምደውበታል። በግንባርም ሆነ በውህደት ኘሮግራማቸውን ያስተዋወቁን የፖለቲካ ድርጅቶች ልክ እንደ ቢራቢሮ ክንፍ አንድ ሰሞን አጊጠውበት ሲረግፉ ማየት የየሳምንቱ ትርኢት ሆኗል።

የኢሕአዴግ መንግሥት በተቃዋሚዎቹ ድክመት ፋፍቶ ያሻውን ቢያደርግ ጠያቂ ስለሌለው አገር ወዳዱ ቆሌ የሚልበት ዛፍ አጣ። ተቃዋሚዎች ሌትና ቀን የሚማፀኑት የምእራቡ አለምም የምትሉትን አልሰማሁም ያያችሁትንም አላየሁም ሲል ትኩረት በመንፈጉ የኢትዮጵያ ነገር ቀመር ያልተገኘለት የሂሳብ ስሎ እየሆነ መጣ። ኢትዮጵያዊያን አገራቸውንም በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ያገባናል ሲሉ ከምር የሚጮሁ መሆናቸውን ቢያስመሰክሩም ቅራኔያቸውን አቻችለው በጋራ መጓዝ የሚያስችል አቅም አጥተው እርስ በርስ እየተነካከሱ የረገፉ ጥርሶቻቸው ለእግዚቢት ቀረበ።

ዘረኛ ነው ተብሎ የተከሰሰውን መንግሥት ለመታገል ዘረኛነት እንደ አማራጭ ተወሰደ። ዛሬ በግንባር ተቃቅፈናል ሲሉ በሬዲዮ ቃለ መጠይቅ ያበሰሩን ዶክተር እገሌና ዶክተር እገሌ ሳምንት ባልሞላው እድሜ ውስጥ አሮ -ፈሶ ሲባባሉ ሰምተን ጆሯችንን ዘገነነው። የራዲዮ የአየር ጊዜን ለመግዛት ነዋይን ብቻ በሚጠይቅ አገር በመኖራችን ድምጽ ማጉያን የደፈረ ሁሉ ጨበጣት። ፖለቲካ ስብሰባ አዋቂዎች በጥንቃቄ የሚገቡበት ጠባብ በር መሆኑ ቀርቶ ደፋር ስሜተኛ ዘሎ የሚደረጐስበት  ሰፊና ትልቅ የኳስ ሜዳ በር ሆነ።

ደራሲ አስማማው ኃይሉ /አያ ሻረው/ የሳለው ዋናው ገፀባህርይ ምርር ያለ መከፋት ሲደርስበት ባገኘው ብጣሸ ወረቀት የሚጽፋቸው ግጥሞቹ ከስድ ንባብ ገለፃዎቹ ባልተናነሱ ቁጥብና የውስጥ ስሜትን ገላጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በአጠቃላይ ከደንቢያ-ጐንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ልቦለድ መጽሀፍ ሊነበብ ብቻ ሳይሆን እውነታም ስላለው ለታሪክም ሊቀመጥ የሚገባው ነው። እንደ ሃያሲ ሳይሆን እንደ አንባቢ መጽሀፉን ያለ ፋታ ለጨረስኩት ለኔ ይህ ልቦለድ ግሩም ነው።

ደራሲ አስማማው ኃይሉ ምርጥ ተራኪ፤ የቋንቋ ቱጃር፤ ሀሳበ ብዙ፤ ያልታየውን ገላልጦ ውበቱን የሚያበራልን የታሪክ ብእረኛ ነበር። ዛሬ አሱም ስሙን ዘላለም የሚያስጠሩለትን መጽሐፎቹን ሰጥቶን ወደማይቀረው ሄዷል። በቅርቡም አምስተኛው መጽሀፉ ለንባብ ይቀርባል።

የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በደራሲ አስማማው ኃይሉ ሞት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለወዳጅ ዘመዶቹ ለአድናቂዎቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።n

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
12366 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us