የአጼ ቴዎድሮስ የቤተ-መንግስት ፈላስፋ እየተጠና ነው

Wednesday, 28 October 2015 13:34

 

በጥበቡ በለጠ


ሰሞኑን የጀርመን ዜግነት ካላቸው ስዎች ጋር ነበርኩ። እነዚህ ጀርመኖች አፍሪካን በተለያየ ሁኔታ ለማጥናትና ስራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ ጥንታዊ የስልጣኔ መሰረቶች ናቸው የሚባሉት ኪነ-ህንጻዎች ታሪካቸውን እንደገና እየበረበሩ ነው። በነገራችን ላይ አክሱም ከተማ ላይ እና በውስጥዋ በያዘቻቸው አስደማሚ ኪነ-ሕንጻዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥናት አድርገው ለአለም ያስተዋወቁት ጀርመኖች ናቸው። በ1906 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱምን አጥንተው ለአለም ያበሰሩት እነዚሁ ጀርመኖች ናቸው። የዚያን ዘመን የቡድን መሪው ፕሮፌሰር ኢኖ ሊትማን ይባላሉ። ከጥናታቸው በኋላ The deutsche- Aksum Expedition የተሰኘ እጅግ ድንቅ መጽሀፍ አሳትመው ሰፊ ተቀባይነትን አግኝተዋል። ዛሬ ይህ ጥናትና ምርምር ከተሰራ 102 አመት አለፈው።


 

አሁን ደግሞ ሌላኛው የጀርመን ትውልድ አፍሪካ ውስጥ የቆዩ ስልጣኔዎችን በዘመናዊ እይታ እየቃኙ ነው። ከእነዚህ ጀርመኖች ጋር ሰሞኑን በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጋር አብሬያቸው ተጉዤ ነበር። ምስራቅ አፍሪካን አካለን ወደ ኢትዮጵያም መጥተን ነበር። ተጠናቀው ያላለቁትን ጅምር ስራዎቻቸውን ይፋ ማድረግ ባልፈልግም ነገር ግን አልቀው ህትመት ላይ ካሉት ውስጥ አንዱ ስለሆነው የአጼ ቴዎድሮስ የቤተ-መንግስት ፈላስፋ ስለነበረው “ዘነብ” ስለተባለው የሀይማኖት ፈላስፋ ጉዳይ አለማቀፋዊ ባለታሪክ ሊሆን ነው። ለአመታት ይህን የዘነብን ታሪክ ሲመረምሩ ከቆዩት ጀርመናዊያን መካከል አንዱ አንድርያስ ብሩክነር ይባላል። ይህ ሰው ዘነብ ማን ነው? የት ተወለደ? የት አደገ? ምን ተማረ? ማን አስተማረው? ስራ የት ተቀጠረ? ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድን ነው? ምን ጻፈ? ምንስ ተፈላሰፈ? ፍልስፍናውስ ምን አዲስ ነገር አለው? እያለ የዘነብን የህይወት ታሪክና የፍልስፍናውን ትንታኔ የያዘ ሰነድ እያዘጋጀ ነው።


ዘነብ ኢትዮጵያዊ እያለ ከ150 አመታት በፊት ስሙን የሚጽፈው ያ ባለታሪክ ዛሬም ዝናው ሊናኝ ነው።

ስለዚሁ ፈላስፋ ጉዳይ እኔም ከዛሬ ሰባት አመታት በፊት በእግዚአብሄር ላይ የተደረገ አመጽ ወይስ ፍልስፍና?በሚል ርእስ የተለያዩ ጉዳዮችን ጽፌ ነበር። የኔ ጽሁፍ ያን ያህል ጥልቅና ጥናት አዘል ባይሆንም የተወሰኑ መረጃዎችን መሰብሰቤም ነው ከጀርመናዊው አንድርያስ ብሩክነር ጋር የበጠ እንድንግባባ ያደረገን። ዘነብ አስገራሚ ሰው ነበር። ከዛሬ ሰባት አመት በፊት ስለዚሁ ሰው የጻፍኩትን በሬዲዮ ሳነበው የተደሰቱ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል በጣም የተቆጡም ነበሩ። ጽሁፉ ምን ነበር ለምትሉ እነሆ ብላችሁስ። ድሮ ያነበባችሁት ወይም የሰማችሁትም የፈላስፋ ጨዋታ ስለማይጠገብ አይሰለችምና በድጋሚ አነሆ ብላችሁስ፡-    


በሀገራችን ኢትዮጵያ ተነስተው ከነበሩት ቀደምት ፈላስፎች መካከል የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘርአ ያዕቆብ በግንባር ቀደምትነት ይነሳል። በተለይም ደግሞ ሃይማኖታዊ እሳቤዎች ላይ ተመርኩዞ ያነሳቸው ጥያቄዎቹ ነበሩ የሰውየውን ጠንካራ ፈላስፋነት ያጐሉት። ለምሳሌ የትኛው ሃይማኖት ነው ትክክል ብሎ የካቶሊኩን፣ የፕሮቴስታንቱን፣ የቅባቱን፣ የየሱሳዊያንን ወዘተ እያነሳ አስተምህሮታቸውንም እየጠቀሰ ይጠይቅ ነበር። ከዚህም ሌላ አያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ በማንሳቱ ከቀደምቶቹ ዘመናዊ ፈላስፎች ጐራ ተመድቧል። ከርሱ ሌላ ደግሞ ብዙም ያልተነገረለትና ሰፊ ጥናትም ያልተደረገበት ሌላ ኢትዮጵያዊም አለ። ይህ ሰው ዘነብ ኢትዮጵያዊ ይባላል። ጉድ የሚያሰኙ የሃይማኖት ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳ ይፈላሰፍ ነበር። ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው?


 

በ1924 ዓ.ም “መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሣዊ” የተሰኘ መጽሐፍ ታተመ። የፀሐፊው ስም “ከዘነብ ኢትዮጵያዊ ተፃፈ” በሚል ተቀምጧል። ነገር ግን በ1951 ዓ.ም ይህንኑ መጽሐፍ ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የቀድሞው ይዘቱንና ሁለመናውን ሳይለቅ እንደገና አሳትመውት ለህዝብ አሰራጩት። ስለዚሁ ጉደኛ መጽሐፍ ተስፋ ገ/ስላሴ የፃፉት መግለጫ እንዲህ ይነበባል።

ይህ “መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሣዊ” በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በ1857 ዓ.ም ዘነብ የተባለ ኢትዮጵያዊ የፃፈው ነው። ይህም መጽሐፍ ከብሉይና ከሐዲስ ተውጣጥቶ የተፃፈ ነው።


 

በስጋዊም ጠቃሚ የሆኑ ፍሬ ነገሮች ስላሉበት መልካም መጽሐፍ ስለሆነ ብዙዎች ሰዎች ከዚያን ዘመን ጀምሮ በብራናና በወረቀት እየፃፉ ራሳቸው እያነበቡ ለልጆቻቸውም እያስተማሩ ሲጠቀሙበት ከኖሩ በኋላ በ1924 ዓ.ም በጐሃ ጽባህ ማተሚያ ቤት ታትሞ ለህዝብ ሳይዳረስ ጠላት ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን ተዘርፎና ተቃጥሎ ባክኖ ጠፋ። ይህን ጠቃሚ ፍሬ ነገር ያለበትን መጽሐፍ የአሁን ወጣቶች አንብበው እንዲጠቀሙበት ታተመ። “አ.አ ሐምሌ 15 ቀን 1951 ዓ.ም” ይላል።


 

እርግጥ ነው መጽሐፉ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገ/ስላሴ እንዳሉት በርካታ ጠቀሜታ ያሉት ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቷል። ቀኝ አዝማች ተስፋም ይህን መጽሐፍ ለማሳተም በመቻላቸውና ኢትዮጵያዊያንን የእውቀት ባለቤት ለማድረግ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ያደረጉት ተጋድሎ በትውልድ ዘንድ ሁሌም ይታወሳል።

ይሄ “መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሣዊ” የተሰኘው መጽሐፍ ብዙ አስተማሪ ሃሳቦች እንዳሉት ሁሉ አስደንጋጭ ፍልስፍናዎችም አሉት። አስደንጋጭ ያልኩበት ምክንያት ሃይማኖታዊ ቀኖና በሚጫናት ሀገር ውስጥ ዘነብ የፃፈው ሃይማኖታዊ ጉዳይ የማይታሰብ ነበር። ይህ መጽሐፍ ገና የመጀመሪያውን ገጽ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡-


 

“እግዚአብሔር እስቲሻር፣ ሚካኤል እስቲሞት ምነው በኖርሁኝ። ገብርኤል ሲያንቀላፋ፣ ሩፋኤል ሲደክም ሐሰተኛ ዲያብሎስ ንስሐ ይገባል” በማለት መጽሐፉ ይጀምራል። ይህ መጽሐፍ እያንዳንዱ ገለፃው ያልተለመደ ሃሳብ በመሆኑ ድንጋጤን መፍጠሩ አይቀርም። ወደ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ያስበረግጋል። ፈጣሪንም እንዲህ እያለ ይናገራል፡-

“አባቶቻችንን ከዚህ ቀደም አታሎ ያወጣው ገንዘብ ይበቃዋል። ባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ መሄድ ይሻላል ይላል። ከእርሱ የበለጠ ባለጠጋ አለን? እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ይኖር የለምን? ይህንን እያመካኘ የሰው ገንዘብ አሻግሮ ማየቱ ምንድን ነው? ከዚህ ቀደም አስሩን ተናግሮ ተናግሮ ከወንጌል አደረሰን፤ አታስቡ እያለ ገንዘባችንን ሲያስበላን ወዲያው ተርቤ አላበላችሁኝም:: ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም። ታርዤ አላለበሳችሁኝም። ታምሜ አላያችሁኝም። እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም። ታስሬ አልጠየቃችሁም ይላል። ይህን ያህል ስድስት ቃል ምን ያናግረዋል። ወዲህ ለነገ አታስቡ ይላል፤ ወዲህ አላበላችሁኝም ይላል። ከኛ ወገን የተራበ፣ የተጠማ፣ የታረዘ የለም መስሎት ይሆን? ተሰማይ ተሰዶ መጥቶ ተርቤአለሁ፣ ተጠምቻለሁ፣ ታርዣለሁ ምንድን ነው? ሰማይን ያህል ሰፊ አገር ይዞ አባቱ ከዚያው አያበላውም? አያጠጣውም? አያለብሰውም? ልጁስ ሲቀላውጥ ነውር አይፈራምን? እኛስ ለሰማይ ንጉስ ልጅ አናበላም፤ አናጠጣም፤ አናለብስም፤ ከዚሁ ካሉት ከድሆች ወንድሞቻችን ጋር ገንዘባችንን ተካፍለን እንበላለን፤ እንጠጣለን፤ እንለብሳለን”


የዘነብ ኢትዮጵያዊ አፃፃፍ በጣም የተለየ ነው። ፈጣሪን ሞጋች ነው። ብዙም ጥያቄ የማይሰነዘርበትን ርዕሰ ጉዳይ ወደ ውስጥ ገብቶ ከመበርበር አልፎ ድምፅ አውጥቶ ይጠይቃል። የሚከተለውም ሀሳብ ከላይኛው ጋር የተያያዘ ነው።

“የሰማይ እሳት ከሰማይ ላይ ወድቆ አለማቃጠሉ ምንድን ነው? ቅዱስ፤ ቅዱስ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ገንዘባችሁን እየሰበሰባችሁ ወደ ሰማይ ላኩ፤ ከዚያ ይቆያችኋልና ይለናል። ለካ የርሱ ገንዘብ አልበቃው ቢል ወደኛ ልጁን የላከ ቀስ ብሎ ገንዘባችንን በብልሃት እንዲያከማች ኖሯል። እንግዲህ አወቅንበት። ገንዘባችንንም አናባክን፤ ከሰማይስ እኛ ምን አለን? ገንዘባችንን ወደዚያ አሸክመን ከምንልክ አንካሶችን፣ እውሮችን፣ ችግረኞችን ወንድሞቻችንን ይዘን እንክት እያደረግን እንበላዋለን፤ እንጠጣዋለን፤ እንለብሰዋለን፤ በገዛ ገንዘባችን ምን ይመጣብናል? አላመጣችሁም ብሎ የሚያደርገውን እስቲ እናያለን።”


ፀሐፊው ዘነብ ኢትዮጵያዊ ከእየሱስ ጋር የቅርብ ትውውቅ ያላቸው እስኪመስል ድረስ ይናገራል። በዚሁ ንግግር ውስጥ ግን ሰፋፊ ሃይማኖታዊ እሳቤዎችን የያዙ ፍልስፍናዎች ይስተዋሉበታል። ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት በነበረው የአስተሳሰብና የሃይማኖት ቀኖና ውስጥ እንዲህ አይነት ደፋር ኢትዮጵያዊ ነበር ማለት ለብዙዎች ከባድ ሊሆን ይችላል። ዘነብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየወሰደ በራሱ የፍልስፍና ሙግት ጋር ያስቀምጣቸዋል። የሚቀጥለው ሃሳብም የዘነብ ነው።

“የክርስቶስ ነገር እጅግ አስቸገረ፤ ልጅ ስለሆነ ይሆን? አንድ ጊዜ ተርቤ አላበላችሁኝም ይላል፤ አንድ ጊዜ አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው አብልቶ አትርፎ ያስነሳል” 22


የዘነብ ብዕር እጅግ ደፋር ነው። በዘመናት ውስጥ ሊነካ ሊደፈር የማይቻለውን ሃይማኖታዊ ጉዳይ እርሱ ግን “መፅሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሣዊ” በሚል ለዛ ባለው ብዕር ይሞግተዋል። ደግሞም እንዲህ ብሏል።


 

“እግዚአብሔር ፈሪ ነው፤ እኛ ብንበድለው ልጁን ልኮ ቀስ ብለህ ተዛምደህ ና ብሎ በልጁ ታረቀን፤ አሁን ምን ያደርጉት መስሎት ነው? ለካ በየቤቱ ፍርሃት አይታጣም፤ እኛ ስለበደልነው የምንክሰውን እርሱ ካሰን። እንግዲህ ወዲህ ስጋችን ከሆነ በሰበብ ባስባብ ብለን እርስቱን እንካፈለዋለን ጥቂት ስጋ እንደ መርፌ ትወጋ እንደሚሉት፤ እንኳን ልጁን ልኮ ተዛመደን።”


የዘነብ አፃፃፍ በአሁኑ ወቅት ላይ እንኳን ሆነን ሽምቅቅ ፈራ ያደርገናል። ግን እሱ መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ እያለ ከሃይማኖቱ ጋር ይጠያየቃል። ለኛም ያወጋናል።

“እግዚአብሔር በደብረ ሲና በእጁ አስር ነገር ዘራ። የሚያጭደውም በታጣ ጊዜ አንድ ልጁን ቢልከው እንግዳ ነውና በዳዊት ቤት አደረ፤ ይህንም አዝመራ 33 ዓመት ሙሉ ብቻውን አጭዶ በጨረሰ ጊዜ አባቴ አባቴ አመስግነኝ አለ፤ ምነው ከእረኛ ቤት ተወለደ ብለን አምተነው ነበረ፤ አሁንስ እርሱ ራሱ እረኝነቱን ገለጠው፤ ለካ የበጐች እረኛ እኔ ነኝ እያለ ከሰማይ ተሰዶ የመጣ በጐችን ሊጠብቅ ነው። ከሠማይ ድረስ መጥቶ በግ መጠበቅ ካልቀረለት ይህችን ታናሽ መንጋ መጠበቁ ለምንድን ነው? ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ ያለውን መንጋ አንድ አድርጐ ጠብቆ ደመወዙን በምስጋና አውጥተን አንሰጠውምን?


በዚህ ከላይ በሰፈረው አባባሉ ዙሪያ ዘነብ የሚያነሳው ጉዳይ ፈጣሪ እኛን ለመጠበቅ ወደ ምድር ከመጣ እንዳንሳሳት፣ አንዱ ሌላውን እንዳይበድለው፣ መከራና እርዛት፣ ችግር፣ ቸነፈር እንዲቀር ለምን ፈጣሪ ራሱ አይከላከልም የሚል መሰረታዊ ሃሳብ የያዘ ይመስለኛል።


 

በዘነብ ጽሁፍ ውስጥ ከፈጣሪ ሌላ መላዕክትም የፍልስፍናው አካላት ናቸው። እነርሱንም በሚከተለው መልኩ ይጠይቃል።

“በ5ሺህ አምስት መቶ ዘመን እግዚአብሔር እጅግ ተዋረደ። አንድ ልጁን ለሰው ባሪያ ሆነህ ስጋ ተሸከም ብሎ ሰደደው። ወዮ፤ ወዮ፤ ወዮ፤ ዋ፤ ዋ፤ ዋ፤ መላዕክትስ ጌታ የሰው ስጋ ሲሸከም እያዩ ቆመው ዝም ብለው ማየታቸው ለምንድን ነው? የስጋ መብል ስለአለበት ሁሉም የምድሪቱን ኑሮ ወደዱ። በሰማይስ ስጋም ጠጅም የለም አሉ። እንደዚህ ያለ ባዶ አገር፤ መላዕክትን እከክ አይቆራርጣቸውም?


በዚሁ በዘነበ ኢትዮጵያዊ ጽሁፍ የሚሞገቱት መላዕክት፣ እየሱስ ያ ሁሉ መከራ፣ ድብደባ፣ ስቅላት .” ሲደርስበት የት ነበሩ እያለ ተፈላስፏል። እንዲህም ብሏል፤


 

“መላእክትስ ጠጅና ስጋ አይወዱም ይሆን? ለሰው ልጆች በስጋ ሲያደላ አይተው ይሆን? ምነው ጌታቸው ሲሰቀል ዝም አሉ? ጌታቸው ሲሰቀል ከቶ ወድየት ሸሹ? ምናልባት እንደርሱ እንሞታለን ብለው ይሆን? መንጋ ፈሪ በሰማይ ተሰብስቦ። ሰይፍን አስረዝሞ ቢቆሙት ካልመቱበት ምን ይሆናል? የፈሪ በትሩ አስር ነው።”


የዘነብ አፃፃፍ ያልተጠየቁ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ዛሬ ላይ ቆመን እንኳን ለመፃፍ፣ ዘነብ የፃፈውን ለማንበብ የምንፈራ ብዙዎች ነን። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረው ይህ ደፋር ፀሐፊ አሁንም መላዕክትን እንዲህ ይሞግታል።

“እንግዲህ መላዕክት ከስጋና ከጠጅ ይከልከሉ። ጌታቸውን ብቻውን አስደብድበውታልና። ይልቁንስ ፀሐይና ጨረቃ ተሸልመው መኖር ይገባቸዋል፤ የጌታቸውን ራቁትነት ቢያዩ ብርሃናቸውን ሰውረዋልና፤ ከዋክብትም ረግፈዋልና ክብር ይገባቸዋል። ሃያ አራቱ ቄሶችስ ወደየት ሄደው ነው? ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የቀበሩት? የጦር ቀን ያልሆነ ሎሌ ለመቼ ነው? መንጋ ቀጥቃጣ ሞት ፈሪ”


የዘነብ ኢትዮጵያዊ ደፋር ብዕር በፈጣሪና በመላዕክት ላይ ጥያቄ ብቻ አያነሳም። ከዚሁ ሌላ ደግሞ ፈጣሪንም ያመሰግናል። ፈጣሪ የዓለም ዋርካ ምሰሶ እንደሆነም ይመሰክራራል።


 

“የፍቅር ምንጭ ማነው? ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ለተራቡ ስጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቷልና” እያለም ፈጣሪን ያሞግሳል።

“እግዚአብሔር ሐኪም ነው፤ ሁሉን በጥበብ አድርጓልና። እግዚአብሔር ምስጉን ነው፤ ፀሐይን ጨረቃን ፈጥሯልና። እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ ሰማይና ምድር የራሱ ናቸውና” እያለም “መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” መጽሐፍ ያወጋናል።


የዘነብ አስተሳሰብ በሁሉም ዘርፍ የተሳለ ፍልስፍና ነው። የፈጣሪን ታላቅነት፣ ሁሉን አድራጊነት ይቀበላል። እንደገና ዛሬ “አፈፃፀም” እንደምንለው ቋንቋ፣ ሕግጋትና ደንቦችን አካሄዶችን ይጠይቃል። እንዲሁም ይፈላሰፍባቸዋል። ሕጉን ተቀብያለሁ፣ አፈፃፀሙ ላይ ግን ጥያቄ አለኝ እንደሚባለው ፈጣሪን ተቀብያለሁ ግን ሕግጋትና ቀኖናዎቹ ላይ የምለው አለኝ አይነት ፍልስፍና ያራመደ ፀሐፊ ነው ዘነብ።


 

ከዚህ ከመንፈሳዊ ፍልስፍናው ሌላ ሕጋዊ በሆኑ አለማዊ ነገሮች ላይም ፀሐፊው አተኩሯል። አንድ የገረመኝን ጽሁፉን ላስነብባችሁ፤

“የውሻ ጅራቱ ወደላይ እንዲቆም፤ የሹመት ፈላጊም ልብ እንደዚያ ነው። መርፌ ሸማን የሚወጋው ምን እጠቅም ብሎ ነው? በኋላው እንጂ ፈትል ተከትሎታል። እነዚያ እንደሚጠቃቀሙ አያውቅምን? እንደዚህ ያለ ሞኝ የፊቱን እንጂ የኋላውን የማያይ፤ ይልቁንስ የርሱን ቀዳዳ በጠቀመ።”


መርፌ የራሱን ቀዳዳ ሳይሸፍን ሌላውን የመድፈኑን ነገር ነው ዘነብ የተመለከተው። እዚህ ላይ “መርፌ” የሚለው ቃል በዘመነ ቴዎድሮስ ነበር። ይሁን እንጂ ይህች ማህበራዊ ፋይዳ ያላት ልብስ መስፊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳትመረት ረጅም ዘመናትን አስቆራራለች።


 

የዘነብ መጽሐፍ 35 ገጽ ያላት ብትሆንም በውስጧ የያዘችው ሀሳብ ቢዘረዘር ግን ከ35 መፃህፍት በላይ ይሆናል። ፀሐፊው የሰውን ልጅ አእምሮ ለማስላት፣ ጥሩ አሳቢና ተመራማሪ ለማድረግ የተጠቀመባቸው ገለፃዎች እጅግ የሚገርሙ ናቸው። ለምሳሌ፡-

“ድንጋይና ጭቃ ቢቀጣጠሉ ታላቅ ቤት ረጅም ቅጥር ይሆናሉ፤ እናንተም መሬታውያን ሰዎች እንደዚህ ብትረዳዱ ጥበባችሁና ኃይላችሁ ከሰማይ በደረሰ። ጣዝማ እጅግ ብልህ ናት፤ መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድኃኒት የሚሆን ማር ትሰራለች። ምነው እናንተ ሰዎች ወይ ከፈጣሪ፣ ወይም ከሰው ብልሃትን አትፈልጉምን? እያለ በዘመኑ ከነበረው ሁኔታ ጋር እያቆራኘ አንባቢዎቹን ያስተምራል። ውብ ቋንቋ ውብ ትምህርት


የዘነብ ጨዋታ የፍልስፍና ቅመም ውስጡ ተደባልቆ ነው የምንጠጣው። ለምሳሌ “እንሰሶች ሁሉ የሚበሉት አንድ ሳር ነው፤ ምነው ፋንድያቸው ተለዋወጠ? ሰዎችም አባታቸው አንድ አዳም ሲሆን ምነው አይነታቸው በዛ?” እያለ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ ምናብ ያሰፋል። ይጠይቃል። ይፈላሰፋል።


 

የዘነብ አስተሳሰብ ሰፊ ነው። ከፈጣሪው ጋር በቅርበት ያወራል፤ ይጠይቃል። እንደገና የራሱን ፍልስፍና ያንፀባርቃል። ግን ፍልስፍናው ከተፃፈው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሳቤ ላይ ተነስቶ ነው። ለምሳሌ ጌታን እንዲህ ይላል፤

“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ አለ። መብራት አብርቶ በእንቅብ ውስጥ የሚኖር የለም ይላል። ዓለምን ያህል እንቅብ ደፍቶብን የለምን? እኛ በወዴት እናብራ?” በማለት ይሞግታል። የስልጣኔን ብርሃን ለማግኘት ፈጣሪውን ይጠይቃል። ልክ በዚህ በዘነብ ዘመን፣ አፄ ቴዎድሮስም ፈጣሪን ሲለምኑ ሃይልና ብርሃን ስጠኝ ይሉ ነበር ይባላል። ምናልባት ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስ መስታወት ይሆን?


በዚሁ “መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ዘነብ ሃይማኖትን ሲያስተምር እንኳን ከብዙ አቅጣጫ አንፃር ነው። ብዙውን ጊዜ ባልተለመደውና ባልታየው ጐኑ ነው የሚያወጋን። እንዲህም አለን፤


 

“ዳዊት ይሁዳን አገሩን ምድረ በዳ ትሁን እያለ ምን ያራግመዋል? እርሱ ካልበላሁለት ብሎ ነውን? እንደ ይሁዳ ያለ መልካም ነጋዴ የለም፤ የዘለአለሙን ምግብ በ30 ብር ሸጠልን” እያለ በጨዋታ መልክ ይሁዳን በስላች አመስግኖ የጌታን ታላቅነት ይነግረናል። ውብ አፃፃፍ።


“አይሁዶች ጅሎች ናቸው፤ ክርስቶስ ከሰማይ ወረድሁ ቢላቸው ከእንጨት ላይ ሰቀሉት፤ ያውም እንጨት ከነአካቴው መሰላል የሰማይ መውጫ ሆነ” እያለ ዘነብ ያጫውተናል።

ዘነብ ኢትዮጵያዊ የፃፋቸው ጥቅሶች ሁሉ የሚነበቡ የሚተረጐሙ ጥልቅ ትንታኔና ማብራሪያ የሚጠይቁ ናቸው። አንዳንዶቹ ሀሳቦቹ ፈገግ ያደርጋሉ። ፈጣሪ አብሮን በአካል ቁጭ ብሎ እያወራ ያለ እስኪመስል ድረስ ዘነብ ይቀርበዋል።


 

“እየሱስ ሠርግ ቢጠሩት በቃና ዘገሊላ ውሃውን ጠጅ አድርጐ አጠጣ፤ በሰው ሠርግ እንዲህ የሆነ በራሱ ሠርግ እንዴት ይሆን? የእግዚአብሔር ልጅ ሠርግ አይቼ ከድግሱም በልቼ ጠጥቼ ከዚያ ወዲያ ምነው በሞትሁ” እያለ ረቂቅ ሃሳቦችን እንደዋዛ ያጫውተናል።


ይሄ እጅግ የሚገርም ፈላስፋ የኖረው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ነው። የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርአ ያዕቆብ የኖረው ደግሞ በአፄ ሱስንዮስና በአፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት ነው። እነዚህ ዘመናት ለፈላስፋ ፀሐፊዎች መምጣት አመቺ ነበሩ? ቢጠኑ ደስ ይለኛል።


 

የዘነብ አፃፃፍን መለየት ይከብዳል። ደጋግመው ከእርሱ ጋር እየተናበቡ ቢቆዩ ደስ ይላል። ግን መለየት ግድ ሆነብኝ። እስኪ ለመጨረሻ እንዲሆነን አንድ ጥቅሱን ላስነብባችሁ፤

“መጽሐፍ አንዳንድ ጊዜስ አያውቅም፤ ሰው ቢሞት ደስ አይበልህ ይላል። ክርስቶስ ባይሞት ለኔ መንግሥትን ማን ሊሰጠኝ ኖሯል? የርሱ ሞት እኔን ጠቀመኝ እሰይ እሰይ እንኳን ሞተልኝ እልል እልል እንግዲህማ ስጋውንስ ብበላው፤ ደሙንም ብጠጣው፤ ምነው? እኔን የመሰላችሁ ሁሉ ደስ ይበላችሁ

በመጨረሻም መግለፅ የምፈልገው፣ ዘነብ ኢትዮጵያዊ ሃይማኖት የለሽ፣ ሃይማኖት ነቃፊ፣ ኢአማኝ እንዳልሆነ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ። ሰውየው በፈጣሪው በደንብ የሚያምን ነው። ግን የእምነት ፍልስፍናቸው ሰፊ ስለሆነ በሁሉም መንገዶች ሃሳብ ሰንዝሯል፤ ተፈላስፏል። ጭራሽ መጽሐፉን ሲያጠናቅቅ በመጨረሻዋ ገጽ ላይ እንዲህ ብሏል።

“ምስጋና ይሁን ለአብ፤ ለወልድ፤ ለመንፈስ ቅዱስ፤ አንድ አምላክ፤ ቀድሞ የነበረ፤ አሁንም ያለ፣ በኋላም የሚኖር አስጀምሮ ላስጨረሰን ክብር ይግባው ለዘላለም አሜን።”

  • ዘነብ፣ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ጽፎ ያስተላለፈልን የመጀመሪያው ሰው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የግል አስተማሪም እንደነበር ይነገራል።

 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
7980 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us