“ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል”

Wednesday, 04 November 2015 13:50

በጥበቡ በለጠ

 

ከሰሞኑ የሐገራችን አጀንዳ ሆነው የከረሙት መምህር ግርማ ወንድሙ ናቸው። በተለያዩ ድረ-ገፆች እና የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ስለ መታሠራቸውና ስለ መከሠሣቸው ጉዳይ የተለያዩ ፅሁፎች አስተያየቶች አቋሞች ሁሉ ሲንፀባረቁ ቆይተዋል። በርግጥ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ስለሆነ ምንም ማለት ባይቻልም ስለ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሀይማኖት እና የአማኝነት ጉዳይ እስኪ እንጨዋወት።


 

ከወራት ወፊት በዚሁ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ አንድ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር፤ ርዕሱ “መምሕር ግርማ ወንድሙ እና የሚያባርሯቸው ሰይጣኖች” የሚል ነበር። የፅሁፉ መሠረታዊ ጭብጥ መምህር ግርማ በልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ሰፍረዋል የሚሏቸውን ሰይጣኖች እያስለፈለፉ ሲያስወጡና ሰይጣንን ሲባርሩ በሚያሣዩ የተቀረፁ ፊልሞች ላይ መሠረት ያደረገና የራሴን ብዠታዎች የጠየኩበት ነው። ሰይጣን ምን ያህል በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ እንደሰፈረ በመምህር ግርማ ወንድሙ የተቀረፁ ፊልሞች ላይ ይታያል። ታዲያ ይህ ሁሉ ሰይጣን ኢትዮጵያ ላይ ለምን ሰፈረ ሀገሪቱ የሐይማኖት ሀገር ናት እየተባለ ይህ ሁሉ ሰይጣን ሕዝቡ ላይ ምን ይሠራል እያልኩ ያቀረብኩበት ፅሁፍ ነበር።


ይህ ፅሁፍ እንደወጣ ወዳጄ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አወጣው። ብዙ ሕዝብ እየተቀባበለው የመወያያ እና የመከራከሪያ አጀንዳ አደረገው። ከ150ሺ በላይ ሰዎች አስተያየታቸውን በልዩ ልዩ መልኩ ቢገልፁም 99 በመቶው የመምሕር ግርማ ወንድሙ ደጋፊ ነበር። ፅሁፌን ደግፈው አስተያየት የሠጡት አንድ በመቶ ቢሆኑ ነው። በርግጥ አስተያየት ሰጪዎችን ሣስተውላቸው ብዙ የሣቷቸው ነገሮች አሉ። አብዛኛዎቹ የፃፍኩትን ፅሁፍ በስርዓት አንብበው አልጨረሱትም። ርዕሱን አይተው ብቻ መምህር ግርማ እንዴት ተነኩ ብለው የፃፉ ናቸው። ሌላው ደግሞ በጭፍን ካለማገናዘብ ካለመጠየቅ፤ አንዳንዱ ሌላ ሰው ስለደገፈአብሮ የሚደግፍ፤ ሌላው ከጠላ አብሮ የሚጠላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ቀሪው ደግሞ በመምህር ግርማ ድርጊት እና ተአምራት ያመነ ነው። እሱ ደግሞ እምነቴ ተነካ ብሎ ዘራፍ ያለ ነው።


የሆነው ሆኖ እኛ ኢትዮጵያዊያን ራሣችንን መጠየቅ ከራሣችን ጋር መነጋገር የሚገቡን በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምንድን ነው አንድን ጉዳይ በጭፍን የምንወደው ወይም የምንጠላው? ቲፎዞ ወይም ደጋፊ ካለው ነገር ጋር ወዲያው ተለጣፊ የምንሆንበት ክስተቶችን መናገርም ይቻላል። ከዚህ በፊት በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ባሕታዊ ገ/መስቀል የተባሉ ሰው ተነስተው ነበር። እኚህ ሰው አጥማቂ ናቸው። ወንጌል ሰባኪ ናቸው። የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ተንባይ ወይም ነብይ ሁሉ ሆነው ብቅ አሉ። ብዙ ሺ ሕዝብ ተከታያቸው ሆነ። እርሣቸውም አንዴ አሜሪካ፤ አንድ ጊዜ እስራኤል ሌላ ጊዜ አውሮፓ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገዳም ናቸው እየተባለ የሐገሪቱ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኑ።


 

“በዘንግ የሚገዛ መሪ ይመጣል ኢትዮጵያ ማርና ወተት የሚዘንብባት የተባረከች ሀገረ ትሆናለች። ከወደ መስራቅ የተቀባው መሪ ይመጣል፤” ወዘተ የሚሉት - የባሕታዊ ገ/መስቀል ደማቅ ንግግሮች ነበሩ፤ መጨረሻ ላይ ግን በአፀያፊ ድርጊቶች ተከሰው ለእስራት ተዳረጉ። ከዚህ ጦስ ጋር በተያያዘ ብዙዎች ተጐዱ:: በእርሣቸው መልዕክተኝነት እና ተአምር ሰሪነት ያመኑ ሰዎች ተፈውሰናል ያሉ ሰዎች በመንፈስ መጐዳታቸው አይቀርም። አምነውባቸዋልና ነው።


 

በዚሁ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ሌላ ባሕታዊም ዝነኛ ሆነው ብቅ አሉ። አባ አምሃስላሴ ይባላሉ። እርሣቸውም በሺዎች ተከበውና ታጅበው የሚንቀሣቀሱ ነበሩ። የኢትዮጵያን መፃኢ እድልም ይናገሩ ነበር። በኋላ ላይ በእርሣቸው ፊት አውራሪነት በአራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም ቤተ-ክርስትያን ውስጥ እመቤታችን ተገለፀች፤ ታየች፤ ተብሎ የተፈጠረው ሁከት ግርግር ጩኸት ደስታ መከራ ምን ግዜም የማልረሣው ጉዳይ ነበር። እኚሁ አባት በኋላ ወደ ጐንደር አቅንተው ጐንደር ከተማ ላይ የተከሰተው ደም የመፋሰስ ድርጊት ሁሉ ተፈፅሟል።


 

ወደ ኋላ ዞር ብለን እነዚህን ድርጊቶች ክስተቶችን ስናስተውል ጭፍን ተከታይ በመሆናችን የመጡብን ጣጣዎች ናቸው። በርግጥ ለጭፍን ተከታይነታችን የሚያጋልጡን አያሌ ጉዳዮች አሉ። ዋናው ድህነታችን ነው። ድህነት ሰፊ ሀሳብ ነው፤ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ብዙ ትንታኔና ማብራሪያ ያስፈልገዋል። በዓለም አደባባይ ላይ በረሃብ እና በድርቅ የምትጠራ ሐገር ውስጥ ተወልደን ያደግን ዜጐች ነን። መሠረታዊ የሚባሉ የሰው ልጅ ፍላጐቶች ገና ምኑም ያልተሟሉባት ሀገር ልጆች ነን። የአለም ስልጣኔና ግስጋሴ ጥሎን ሔዶ እኛ ገና ከአነስተኛና ጥቃቅን ነገሮች እንጀምር ብለን ልማት ውስጥ የገባን ነን። ግብርናችን ዛሬም፤ የዛሬም ሦስት ሺ አመት ተመሣሣይ ነው። 85 በመቶ ሕዝባችን በገጠር የሚኖር ነው። ገጠር ማለት ደግሞ ከብዙ ነገሮች የታቀበ ነው። መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎቶች ያልተሟሉላት ሐገር ናት። ሕዝቡ ፀበል ፈለቀ የተባለበት ቦታ ሁሉ ለሕክምና የሚጐርፍባት ሐገር ዜጐች ነን። ከበሽታው የሚፈውሰው ሃይል ያጣ ህዝብ ነው። ታዲያ እኛ ውስጥ ትንሽ ተአምራት የሚመስል ነገር ይዞ የሚመጣ ባህታዊም በሉት አዋቂ ልዩ ፍጡራችን ነው። ምክንያቱም እኛ ልንመልሣቸው ያልቻልናቸውን ጥያቄዎች እሱ ያወጋልናል፤ እሱ ይነግረናል፤ እሱ ተአምራት ሲሠራባቸው ያሣየናል። ስለዚህ እንከተለዋለን። ካለሱስ አዋቂ ማን አለ እንለዋለን። የድህነት ትንሹ ዋጋ ይሔ ነው።


 

ኢትዮጵያ ውስጥ የፈረንጅ አጥማቂዎችና ፈዋሾች ሳይቀሩ እየመጡ ነው። እዚሁ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ የፈውስ ኘሮግራም ተብሎ “ፈረንጆች ክራንች እያስጣሉ ነው። ከደዌ ከሰይጣን እያላቀቁ” ነው ተብሎ ትልቅ መርሃ ግብር ተደርጓል። በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ደግሞ የፈረንጅ ፈዋሾች በተደጋጋሚ እየመጡ ብዙ ሺ ተከታይም ሲያገኙ አይተናል። የራሱን ሀገር ያልፈወሰ ኢትዮጵያ ወጥቶ ፈዋሽ ተብሏል። ይህ ሁሉ ጉዳይ ከየት መጣ ስንል የሚጫወትብን አንድ ጉዳይ አለ። ይህም አለማወቃችን ነው። እውቀት ጠፍቶብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ አራት ቁጥር ስድስት እንዲህ ይላል “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል”


አዋቂ ሰው ይጠይቃል። አንባቢ ይጠይቃል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አጥማቂ ነን፤ ፈዋሽ ነን የሚሉ ሰዎች ክብርና ዝናቸው ከፈጣሪ በላይ እየሆነ ነው። ማንበብ ያቆምን ስለሆነ አንጠይቅም:: አንድ ሰው ኢትዮጵያ ላይ እየተነሣ አንድ የሆነ ነገር ሲያሣየን ተነስተን ተከትለነው የምንጠፋው ለምንድን ነው? ምናልባት መጽሐፍ ቅዱሱን ራሱ በስርዓት ባለማንበባችን ባለማወቃችን ነው። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል የተባለውም ለዚህ ነው።


አሁን በቅርቡ እንኳን ኘሮፌሰር ነኝ፤ ዶክተር ነኝ ኢንጂነር ነኝ፤ ፓይለትም ልሆን ነው እያለ ሲያስተምረን የነበረው ሣሙኤል ዘሚካኤልን ማስታወስ ብቻ ይበቃናል። ሣሙኤል ዘሚካኤል የዋሸው ተራውን ሕዝብ አይደለም። ዩኒቨርሲቲዎችን እና ጠቢባን ናቸው ተብለው የተቀመጡትን ኢትዮጵያዊያንን ነው። በ27 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተዘዋወረ የማነቃቂያ ንግግር ያደርጋል። ባራክ ኦባማ የቅርብ አለቃዬ ነው፤ ፑቲን ጓደኛዬ ነው፤ ማንዴላ ቤት በተደጋጋሚ ሔጄ ስለ ኢትዮጵያ ተጨዋውተናል፤ ይላል ሣሙኤል ዘሚካኤል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ያጨበጭቡለታል። ያሞቁለታል። እዚህ ላይ ሌላም ነገር ጨምርላቸዋል። ከአውስትራሊያ ካምቢራ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ማናጅመንት ቴክኖሎጂ የማስተርስ ድግሪውን ሲቀበል ከተማሪዎች ሁሉ የላቀ ውጤት አምጥቶ 500ሺ ዶላር የተሸለመ ኢትዮጵያዊ ሊቅ እንደሆነ በየ ዩኒቨርሲቲው ሲናገር ይጮህለታል። ከታላቁ የኘላኔታችን ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ድግሪውን ሲሠራ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ተብሎ መሸለሙን ለየዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ይናገራል። በቴሌቪዠን የሥራ ፈጠራ ዳኛ ሆኖ አስተያየት እየሰጠ ውጤት እየሰጠ ተወዳዳሪዎችን ሲጥልና ሲያሳልፍ ነበር። ሣሙኤል ዘሚካኤል የኢትዮጵያ ምሁር ላይ ምን ያልሆነው ነገር አለ? ግን አንዱም ተማሪ ወይም መምህር ጥያቄ አልጠየቀም።


ዛሬ በዚህ በሰለጠነው ዘመን መረጃ በየስልካችን ውስጥ ቁጭ ባለበት ዘመን ሣሙኤል ዘሚካኤል ተምሬበታለሁ የሚላቸውን ዩኒቨርሲቲዎች የጠየቀ ያጣራ ሰው አልነበረም። ተማረ አወቀ የምንለው ሕዝባችን እንኳን በቀላሉ እየተሸወደ ነው። ምስጋና ለአዲሰ ጣዕም የሬዲዮ ኘሮግራም ጋዜጠኞች ይሁንና የሣሙኤል ዘሚካኤልን ጉዶች አነፍንፈው ባይከታተሉና ባያጋልጡ ኖሮ ምናልባት ዘንድሮ ተወዳድሮ የፓርላማ አባል ሁሉ ይሆንብን ነበር። የእርሱ ፍላጐትም እንደዚያ ነበር። ያ ደግሞ ያለመከሰስ መብት ሁሉ ስለሚሰጠው ጉዳዩ ሌላ ታሪክ የይዝ ነበር።


 

ባጠቃላይ ሲታይ ባለማንበባችን ባለመመርመራችን የተለየ ነገር ይዘው የመጡ የሚመስሉን ሰዎች ሁለመናችንን ይሠርቁናል፤ ድህነት ሰፊ ነው ብዬ ነበር። አንዱ ድህነት አለማንበብ ነው። ማንበብ የዕውቀት ባለፀጋ ያደርገናል። ጠያቂ ያደርገናል። ስንጠይቅም መልስ ይኖራል። መልስ ውስጥ ደግሞ እውነትና ሀሰቱ ይገለፃል።


 

ኢትዮጵያ ለዘመናት በተደራረበ ድህነት ውስጥ ያለች ሀገር ናት። አንዱ አመት ጥሩ ቢለበስ ቢበላ የሚቀጥለው አመት ላይ ችግር ጓዙን እየጠቀለለ የሚመጣባት ናት። ገበሬው እንኳን ሲናገር

ይኸ ቀን አለፈ ብላችሁ አትኩሩ

ድሕነት ቅርብ ነው ይመጣል ካገሩ

ይላል።


 

በጥጋብ ግዜ እንኳን የሚፈራባት አገር ነች። ምክንያቱም እንደ አዙሪት አልወጣ ያለ ችግር አለ። ድህነት አለ።

አንድ ግዜ 1996 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል አንድ ውይይት ይደረግ ነበር። ውይይቱ ስለ ድህነት ነው። ድህነት ከኢትዮጵያ ያልወጣባቸውን ምክንያቶች አንድ ኢኮኖሚስት ከተለያዩ ነገሮች አንፃር ይተነትናቸው ነበር። እርሱ ካነሣው ሃሣብ በኢትዮጵያ መንፈሣዊ አባቶች ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠቀስ አንድ ጥቅስ እንጥቀስ። ይህም “ሐብታም መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል”የሚል ነው። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሐብታምነት የፅድቅ መንገድ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ የተነገረባት ነው። ስለዚህ ሐብት ጠፋ። ድሃ በዛ። እያለ ኢኮኖሚስቱ ጉዳዩን ተነተነው። በመጨረሻም አንድ ጥያቄ አቀረበ። “ሀጢያት ውስጥ የሚከተው ድህነት ነው ወይም ሀብታምነት? አለ። እውነት ማን ይፀድቃል? ሀብት ወይስ ድህነት?


ኢትዮጵያ የሌላት ሃብት ነው። ሀብት በማጣቷ ነው መከራዋ የበዛው። ተመጽዋች የሆነችው። ስለዚህ ሀብታም መንግስተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል የሚለው ጥቅስ ተደጋግሞ በዚህች ሀገር ላይ ባይነገር የተሻለ ነው እያለ ኢኮኖሚስቱ ሲያብራራ ትዝ ይለኛል።


 

በዚህ ድሃ ሕዝብ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተአምር ይመስላሉ። የፍቼ ከተማውን ታምራት ገለታንም ማስወስ ይበቃል። ከተራ ዜጐች እስከ ታዋቂ አርቲስቶች በታምራት ገለታ የጥንቆላ ድርጊቶች ውስጥ ተመስጠው ገብተው ነበር። በኋላ ሁሉም ነገር አይሆኑ ሆነና ዘብርቅርቁ ወጣ።


 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌል ተሰብኳል ወይ? ብሎ የጠየቀኝ አንድ ጓደኛዬ ነበር። ምን ልበለው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ሚሊየን ነው? ከዚያ ውስጥ ምን ያህሉ ወንጌልን ሲሰበክ ሰምቷል? ግን ግራ ገባኝና ሣልመልስለት ቀረሁ።


 

ዛሬ ካለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ጳጳሳት ይሰደዱባታል። አንዲት ሀገር ጳጳስ ከተሰደደባት ምኑን የወንጌል ሀገር ሆነች? የጳጳሣት ስደት የአሜሪካንን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እያስፋፋ ነው። በውጭ ሀገር ሳይቀር ሌላ ሲኖዶስ ተቋቁሟል። ዲያቆናት እና ቀሣውስትም ስደታቸው በዝቷል። መዘምራን ከበሮ እና ጸናጽል እየያዙ በመውጣት በውጭ ሀገር ጥገኝነት እየጠየቁ ነው። ታዲያ ምኑን የወንጌል ሀገር ሆነች? ዲቪ ሎቶሪ የሚሞሉ የሀይማኖት አባቶች የበዙባት ሀገር ሆናለች።


 

በሀገር ውስጥም ቤተ-ክርስትያን አሠራሯ ለሙስና ተጋልጧል፤ ምዝበራ ዝርፊያ አለ እየተባለ በየጋዜጣው ሲወጣ እናነባለን። የጳጳሳት ፀብ እንሰማለን። አንዳንድ አፀያፊ የሆኑ ሃሜታዎችም አሉ። እነዚህ ነገሮች እየተደራረቡ እየበዙ ሲመጡ ወድየት እንደሚወስዱን አላውቅም። ሀገሪቱ አዲስ የእርቅና የሰላም ጥምቀት ሣያስፈልጋት አይቀርም።


 

በቴሌቨዠን ኘሮግራሞች ላይም የሃይማኖት ዝግጅቶች እየቀረቡ ነው። ኦርቶዶክስ፤ ኘርቴስታንት ሌሎች የሃይማኖት ፍልስፍናዎችም የአየር ሰዓት ወስደው እየሠሩ ነው። ግን ውዝግብና መካሠስም ሌላው የዘመኑ ገፅታ ሆኖ ብቅ ብሏል። አንዱ የኦርቶዶክስ ፍልስፍናን እና አስተምሮትን ነው የምከተለው ሲል፤ ሌላው ደግሞ አንተ ተሃድሶ ነህ እያለ መነታረክ እለት በእለት የምንሠማው ወሬ ነው። በዚህ ንትርክ ውስጥ ዋናው ጉዳይ ፈጣሪ ይረሣል። ሀይማኖት ይረሣል። ጉዳዩ የሠዎች ፀብ ይሆናል። ስለዚህ ምዕምኑ ራሱ ግራ የገባው እየሆነ ነው። በዚህ ግራ በተጋባ ምዕምን ውስጥ ሌሎች ይገቡበትና ይዘውት ይነጉዳሉ።


 

በ1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ፋሽስት ሰራዊት ኢትዮጵያን ሲወር ዝም ብሎ አልነበረም። ብዙ ኢትዮጵያዊያን ያውም የተማሩት ሁሉ ሣይቀሩ ባንዳ ሆነውለት ነው። ባንዳ የሆኑበት ምክንያት ሊለያይ ይችላል። ግን ለጠላት አድረዋል። የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ሣይቀሩ ለኢጣሊያ ፋሽስቶች ሰብከዋል። ቀድሠዋል። ዘምረዋል። እንዲህ አይነት ሕዝብ እና የሀይማኖት ሰው እንዴት ተፈጠረ? ብለን መጠየቅ አለብን። ሐገረ ኢትዮጵያ እንዴት ተከዳች?


 

ይህ ጉዳይ ወደ ኋላ ተኪዶ መልስ የሚሠጥበት ሊሆን ይችላል። ቅድመ 1927 ዓም በተለይ አፄ ምኒልክ አረፉ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ለሃያ አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ነበር ብሎ ማሰብ ይጠይቃል። ሃይማኖቷስ እንዴት ነበር? ይህን ጥያቄ መወያያ ላድርገው። ምክንያቱም መልሱ ሰፊ ሊሆን ስለሚችል ነው። አድዋ ላይ 1888 ዓ.ም ጣሊያንን በአንድ ቀን ጦርነት ድል ያደረገ ሕዝብ ከ40 አመታት በኋላ የተፈጠሩት የእርሱ ልጆች ደግሞ ለኢጣሊያ ባንዳ ሲሆኑ ምክንያቱ ምንድን ነው? ለሚለው መልስ መስጠት ወደፊት ያስፈልጋል። ጉዳዩን እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ክሽፈት ብዬ ብቻ የማልፈው ስላልሆነ ነው።


 

ሕዝባችን አቋም ያለው፤ በራሱ የሚተማመን፤ ለክሩ ለማተቡ ለእምነቱ የፀና፤ እንዲሆን ማንበብ መመርመር አለበት። ኢትዮጵያ 90 ሚሊዮን ሕዝብ እያላት ሦስት ሺ ኮፒ መፃሕፍት የምታሳትም አስገራሚ ምድር ነች። 90 ሚሊየን ሕዝብ እያላት 5 ሺ ኮፒ ጋዜጣ የምታሣትም ናት። ሕዝቡ ምን እያደረገ ነው ቀኑን የሚያሣልፈው? ብሎ የጠየቀኝ ኬኒያዊ ትዝ ይለኛል።


 

መጪው ጊዜ ፈጣን ነው። ሣይንስና ቴክኖሎጂው ላይ በላይ እየተጓዘ ነው። እኛ ገና ነን። ገና በተአምራቶች እየተነጋገርን እየተጨቃጨቅን የምንኖር ሆነናል። ማርሹን የግድ መቀየር አለብን። ከወዲያ በኩል ብርሃን አለ። አለም በስልጣኔ ብርሃን እየደማወቀ ነው። ወደ እሱ የሚያመራንን የንባብ የዕውቀት የመመርመር የመጠየቅ ባሕላችንን እንገንባው።

16 ሚሊየን ሕዝብ ተርቦብን የጥሬ ስጋ ኤግዚቢሽን ላይ አንራኮት። ሕዝባችንን እናስበው። እንርዳው። 16 ሚሊየን ሕዝብ ተርቦብን የማንቸስተር እና የአርሴናል ጨዋታ መንፈሣችንን አያሠቃየው። አንሸወድ።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
9572 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us