ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የተሰራው ትራጄዲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

Wednesday, 11 November 2015 13:32

 

 

በድንበሩ ስዩም

ከወራት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሁሴን ባራክ ኦባማ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱም ሰፊ የሆነ የሚዲያ ሽፋን ጉብኝታቸው አግኝቷል። ዛሬ የምንጨዋወተው ስለ ጉብኝታቸው አይደለም። በጉብኝታቸው ሰበብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ስለተሰራው ትራጄዲ ነው።

‘ትራጄዲ’ የሚለውን ቃል ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ወደ አማርኛ ሲመልሰው ‘መሪር’ ይለዋል። አሳዛኝ፣ አስከፊ፣ የጠለሸ፣ መራር ወዘተ እንደማለት ነው። ‘ትራጄዲ’ የሚለው ቃል ከጥንታዊ ግሪኮች የቴአትር ዓይነት ወይም ዘውግ የተወሰደ ነው። ከሁለት ሺ አመታት በፊት ግሪካዊው ተውኔት ፀሐፊ ሶፎክለስ ‘Oedipus the King’ ወይም ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ወደ አማርኛ ሲተረጉሙት ‘ኤዲፐስ ንጉስ’ ያሉት ቴአትር፣ የትራጄዲን አጠቃላይ ገፅታ የሚያሳይ ነበር። ጥንታዊ ግሪኮች ከክርስቶስ ልደት በፊት (500 ዓ.ዓ) ፍየሎችን እያረዱ መስዋዕት እያደረጉ የሚያከብሩት በዓል ነው-ቀስ በቀስ ወደ ትራጄዲ የተቀየረው። በዚያ የፍየሎች መስዋዕትነት በሚደረግበት በዓል ላይ ትራጄዲ /መሪር/ ታሪክ ተፈጠረ። የዚህ ትራጄዲ ጀማሪ ተዋናይ የሚባለውም Thespis /ቴስፒስ/ የተባለው ግሪካዊ ነው። በዚህ በእኛ ሀገር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እውነተኛውን ትራጄዲ በማከናወን ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና ተባባሪዎቻቸው የመጀመሪያዎቹ ይመስሉኛል።

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡-

ፕሬዝደንት ኦባማ ኢትዮጵያን በሚጐበኙበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጐራ ብለው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምንም ይጐበኛሉ የሚል ፕሮግራም ተያዘ፣ ወሬ ተናፈሰ። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው የራሱን መሰናዶ ማድረግ ጀመረ። ከእነዚህ መሰናዶዎች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ሰነዶች እና መፃሕፍት በሙሉ በማውጣት ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ማከማቸት ነበር። መፃሕፍቶቹ የሚወጡት ወይም የሚባረሩት ለኦባማ ምቾት እና ደህንነት ሲባል ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። እነዚህ ታላላቅ የኢትዮጵያ ሰነዶች እንደ አልባሌ እቃ እየተነሱ ወደ ሌላ ቦታ ተጓጓዙ። ቤተ-መፃሕፍቱ ራቁቱን ቀረ። እርቃኑን ሆነ። ታረዘ።

እኔም የዚያን ሰሞን ወደዚሁ ተቋም መፃሕፍት ለማንበብ ሄጄ ነበር። ነገር ግን አገልግሎት እንደማይሰጥ ተነገረኝ። ለምን? ስል፣ መፃሕፍቶቹ ወጥተው ወደ ሌላ ቦታ ሄደዋል አሉኝ። አሁንም ለምን? አልኩ። ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ሲባል ነው አሉኝ። ኦባማ እነዚህን መፃሕፍት ይዘርፋሉ ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? ስል፣ አይ ለኦባማ ደህንነት ሲባል ነው አሉኝ። እንዴት ነው ነገሩ? እነዚህ መፃሕፍት ኦባማን ምን ያደርጓቸዋል? እያልኩ ጠየኩ። መልስ የለም። የቤተ-መፃሕፍቱ ሰራተኞች በሙሉ ማለት ይቻላል ሐዘን ላይ ነበሩ። መፃሐፍቶች ለምን ወጡ? ለምን ተባረሩ? እያሉ ይቆዝማሉ። እኔም ግራ ገባኝ። ሐዘን መታኝ።

ለመሆኑ የእነዚህን መፃሕፍት መባረር ሲሰሙ ኦባማ ምን አሉ? አልኳቸው። ሰራተኞቹ ሲነግሩኝ ኦባማ ከነጭራሹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ብቅ አላሉም፤ አልመጡም። ሲሉ ነገሩኝ። ታዲያ ኦባማ ከሄዱስ በኋላ ለምን መፃሕፍቶቹ አይመለሱም? ብዬ ጠየኩኝ። ሁሉም አንገቱን ደፋ። ማን ይመልስ?

እኔም እጅግ በጣም የምወደውን እና የማፈቅረውን ይህንኑ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መፃሕፍት አዳራሹን አሻቅቤ ተመለከትኩኝ። የዚያ ቤት ግርማ ሞገስ የሆኑት እነዚያ ታላላቅ ሰነዶች ከሆዱ ውስጥ ወጥተዋል። መፃሕፍቶቹ የዚያ ቤት እስትንፋስ ነበሩ። መፃሕፍቶቹ የዚያ ቤት ልሣን ነበሩ። መፃህፍቶቹ የዘጠና ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን የማንነት ማሳያ ነበሩ። መፃሕፍቶቹ በአፍሪካ ምድር ላይ በጥቁሮች ዓለም ውስጥ የተካሄዱ የስልጣኔና የማንነት ማሣያ አርማዎች ነበሩ። መፃሕፍቶቹ የአፍሪካዊያን ብሎም የዓለም ሕዝቦችን የነፃነትና የሕይወት ጉዞ የሚያሳዩ ብርቅዬ ሠነዶች ነበሩ። እናም ከእነዚህ ሠነዶች ውጭ ይህ ቤት ምንድን ነው? ሕይወት አለው? ይተነፍሳል? ይናገራል?

እኔም ሳላውቀው እንባዬ ፈሰሰ። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እስትንፋሶቹ ተነቅለውበት ሳይ ሕይወቱ መቋረጡ ተሰማኝ። በእውቀት ያበለፀገኝ፣ ብዙ እንዳነብ እንዳውቅ ያደረገኝ ይህ ተቋም፣ ደሙ፣ አጥንቱ፣ እስትንፋሱ የነበሩት ውድ እና ብርቅ መፃሕፍቶቹ እንደ አልባሌ ነገር ተጐልጉለው ወጥተዋል ስባል መራር እንባ አነባሁ።

ይህን የደረሰብንን ሐዘን ለመፃፍ ብዙ ጊዜ ሞከርኩ፤ አልችል አልኩ። ከባድ ሐዘን ስለሆነ መግለፅ አቃተኝ። መፃሕፍቶቹን ራሳቸውን አፈርኩ። ይህን ሁሉ የሐገሪቱን ምሁራን ያፈሩ ባለውለታዎች ተሽቀንጥረው ወጥተዋል ስባል ውለታ የበላው ባለዕዳ ሆንኩኝ። አልመልሳቸው ነገር አቅም የለኝ። እናም ለወራት ያህል በአካባቢያቸው ዝር ሳልል ጠፋሁኝ። ናፍቆታቸው ደግሞ አላስቀምጥህ አለኝ። እንዴት ባለውለተኛ ይረሳል? እንደ ወላጅ ሆነው በመንፈስ ያሳደጉኝ ወላጆቼን ጥያቸው መጥፋት አቃተኝ። እኔም ውስጤ ባዶ ሆነ። ካለ እነሱ መናገር አልችልም፤ መፃፍ አልችልም። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም መፃሕፍቶችን ሳላነብ ከሳምንት በላይ መቀመጥ አልችልም። ግን ደግሞ እነዚህ መፃሕፍት የሉም ስባል የማደርገው ጠፋኝ።

ከሰሞኑ አንጀቴ ይሁን ልቤ ወይም ሆዴ አልችል ብሎ ብቻ ቁጭ ማለት ስላልቻልኩ ወደ ዩኒቨርሲቲው ስፈራ ስቸር ተጓዝኩኝ። ባለግርማ ሞገሱ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፃሕፍት ከያዘው ደዌ የተላቀቀ ይመስላል። የውስጥ መብራቶቹ በርተውለት መተንፈስ ጀምሬያለሁ ያለኝ መሰለኝ። አላመንኩም። ጠጋ አልኩት። ሰዎች መፃሕፍት ይዘው ሲያነቡ አየሁ። ትንፋሹ ተመልሶ ተገጥሞለታል። ደስታ መታኝ። የደስታ እንባዎች ከዓይኖቼ ውስጥ ተጐልጉለው ወጡ። ከሞት ወደ ሕይወት መጣ የመንፈስ ወላጄ።

ግን ማነው የዚህን ቤተ-መፃሕፍት ሕይወት የሚነቅል እና የሚሰካ? ማነው ደፋሩ?

ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የተዘጋጀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ትራጄዲ ተጠናቀቀ። የትራጄዲ ፀባይ ማስጨነቅ፣ ልብ መስቀል፣ የደም መፋሰስ፣ የታላላቅ ስህተቶች መታየት እና እነዚያ ስህተቶች የሚያስከትሉት ነቀርሳ ብዙዎችን ሲጐዳ ማሳየት ነው። ትራጄዲ በስህተት የሚመጣ መሪር ሐዘን ነው። ያ ሐዘን ያስለቅሳል። ያ ሐዘን መንፈስ ይጐዳል። ሀገር ይጐዳል። ትውልድ ይጐዳል። እናም ከዚሁ ቤተ-መፃህፍት ጋር ተያይዞ የተከሰተው ትራጄዲ ብዙ ትርጓሜ እየተሰጠው የሚተነትን ቢሆንም እኔ ግን ሰሞኑን ቤተ-መፃሕፍቱ ውስጥ ከወራት በኋላ ስገባ የተሰማኝን ግላዊ ስሜት ላጫውታችሁ።

እዚህ ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ገብቼ ቁጭ አልኩ። ብዙ ነገሮች እፊቴ ተደቀኑ። ለመሆኑ ከባራክ ኦባማ እና ከእነዚህ መፃሕፍት ማን ይበልጥብናል የሚል ቀሽም ጥያቄ መጣብኝ። መቼም ለጥያቄዬ መልስ መኖር አለበትና መልሱን ሌላኛው መንፈሴ ያወራኛል።

“ምን ማለትህ ነው? እዚህ ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ሠነዶች የተፃፉት ኦባማ ከመወለዱ በፊት ነው። እነዚህ ሰነዶች ከሦስት ሺ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊያን በዚህች ፕላኔት ላይ ምን እንዳከናወኑ ዘርዝረው የሚያስረዱ ናቸው። አክሱማዊያን ለዓለም ስልጣኔና ብልፅግና ያቆሟቸው ታላላቅ ኪነ-ሕንፃዎች በመፃሕፍቶቹ ውስጥ ይናገራሉ። እዚህ የጥቁር ዓለም ውስጥ የተከናወኑትን ጥንታዊ ስልጣኔዎች ይመሰክራሉ። ለኦባማ ብርታትና ጥንካሬ የሚሆኑ የጥቁር ሕዝብ አሻራዎች ናቸው። እናም ኦባማ ሲመጣ እነርሱ መውጣታቸው ልክ አይደለም” የሚል መልስ ሕሊናዬ ሰጠኝ።

አርኪዮሎጂስቱ አለማየሁ አስፋውና አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰንም ትዝ አሉኝ። ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት ሉሲን /ድንቅነሽን/ በአፋር ምድር ላይ ቆፍረው አገኙ። ሉሲ ከሦስት ሚሊዮን ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳላት ለአለም አበሰሩ። የሰው ልጅ የተፈጠረባት የመጀመሪያዋ ምድር ነች ተብላም ኢትዮጵያ ተጠራች። በዚህ ዙሪያ የተፃፉ አያሌ መፃሕፍትና መጣጥፎች ጥናቶች በዚህ ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ነበሩ። ለምሳሌ ‘Lucy - The Beginnings of Human Kind’ የሚሉት መፃሕፍት እነዚህን ግዙፍ ሠነዶች ከክብር ቦታቸው እንዲነሱ ያደረገው ማን ነው? መፃህፍቶቹ የእኛ ኩራቶችስ አይደሉም ወይ?

አዕምሮዬ ሌሎቹንም ሠነዶች አስታወሰ። ፖርቹጋላዊው ቄስ እና መልዕክተኛ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እ.ኤ.አ. በ1520 ዓ.ም የፃፈው ግዙፍ ሠነድ በዚህ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ አያሌ እውነታዎችን ይዞ ቁጭ ብሎ ነበር። መፅሐፉ The Portugize Embassy in Abbyssinia ይሰኛል። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ስለነበረችው ኢትዮጵያ በዓይኑ ያየውን ምስክርነት የፃፈው ነው። አልቫሬዝ በዚህ መፅሐፉ ውስጥ የቅዱስ ላሊበላን ድንቅዬ ኪነ-ሕንፃዎችን አይቶ የመሠከረው ቃል ይገኛል። አልቫሬዝ ሲፅፍ እንዲህ ይላል፡-

“ስለ ቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስትያናት ላላያቸው ሰው ይህን ይመስላሉ ብዬ ብናገር የሚያምነኝ የለም። ነገር ግን የምፅፈው ሁሉ እውነት መሆኑን በኃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ….”

እያለ ከዛሬ 488 ዓመታት በፊት ስለ ኢትዮጵያ እየማለ የመሰከረበት ጽሁፍ እዚህ ቤት ውስጥ አለ። ለመሆኑ ማን ነው ይህን ሠነድ ለኦባማ ሲባል እንዲወጣ ያደረገው? ይህ ሠነድ ኦባማን ምን ያደርጋቸዋል? ያስፈራራቸዋል?

እዚህ ቤት ውስጥ የጥቁር ሕዝቦች በሙሉ መኩሪያ የሆኑ ሌሎች ታላላቅ ሠነዶች አሉ። እነዚህ ሠነዶች በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን የአልገዛም የጀግንነት አቋማቸውን ያሳዩባቸው ናቸው። መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት በወደቀችበት ወቅት በነጮች የበላይነት ያልተያዘችው ኢትዮጵያ ነበረች። እናም የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ይህችን ብቸኛ ሀገር ለመውረር ከፍተኛ ጦርና ሠራዊት ይዞ አድዋ ላይ ገጠመ። ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በቅኝ ግዛት አንገዛም አሻፈረኝ ብለው፣ ሆ ብለው አንዱ ባንዱ ላይ ወድቆ ጦርነቱን በአንድ ቀን ድል አደረጉ። የነጭ ሠራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር ተሸነፈ ተብሎ ተነገረ፤ ተፃፈ። በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ላይ የተፃፉ አያሌ ሠነዶች በዚህ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ ነበሩ። እነዚህ መፃህፍት የጀግኖች ታሪኮች ናቸው። የጀግኖቻችን ሕያው ድምጾች ልሳኖች ናቸው። ለመሆኑ ኦባማ ሲመጡ እነዚህ ሠነዶች ለምን ይወጣሉ? ማን ነው እንዲወጡ ያዘዘው? የሕልውናችን መሠረቶች መሆናቸውን ማን ነው የዘነጋው? በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ጥቁሮች በባርነት ሕይወት ውስጥ ሲዳክሩ የተሰማው የነፃነት ወሬ የአድዋ ድል ነው። አድዋ ጥቁሮችን ከባርነት ሕይወት ማውጫ የነፃነት ደወል ነው። የነፃነት ተስፋ ነው። ለዚህም ጥቁር ማሸነፍ እንደሚችል ያበሰረ የነፃነት ጐዳና ነው የሚባለው። ይህ ታሪክ ለኦባማ ኩራት እንጂ የሚያስፈራ አይደለም። ግን ስህተት ተሰራ። ትራጄዲ ተፈጠረ። የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የነፃነት አንደበት የሆኑት እነዚህ መፅሐፍት ከክብር ቦታቸው ለምን እንዲወጡ ተደረገ? ማን ነው ፈቃጁ?

ትራጂዲው አያልቅም። ደግሞ ስልጣኔዎች ትዝ አሉኝ። አሜሪካ የምትባል ምድር ከመገኘቷ በፊት ላስታ ላሊበላ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ምስጢራቸው ያልታወቁ ብርቅዬ ኪነ-ሕንፃዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ታንፀዋል። የሰው ልጅ አለት እየፈለፈለ ፎቅ ቤቶችን ወደ ላይ ሳይሆን ወደ ታች (ወደ መሬት ውስጥ) የሰራው ላስታ ላሊበላ ውስጥ ነው። ታዋቂዋ የታሪክ ፀሐፊት እና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቿ ሲልቪያ ፓንክረስት የዛሬ 60 ዓመት ‘Churches of Lalibela:- The Greet Wonders of the World.’ ብላ አያሌ ታሪኮችን ጽፋለች። የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት የምድራችን ታላላቅ ትንግርቶች መሆናቸውን ሲልቪያ ፓንክረስት እና ሌሎች አያሌ ፀሐፍት መስክረዋል። ታዲያ የዛሬ 900 ዓመታት እነዚህ ኪነ-ሕንፃዎች በዚህች የጥቁር ሕዝቦች ምድር ላይ ሲታነፁ፣ ዛሬ ኦባማ የሚመሯት አሜሪካ አልተገኘችም ነበር። አትታወቅም ነበር። ታዲያ አሁን ኦባማ መጡ ሲባል እነዚህ የጥቁር ሕዝቦች የስልጣኔ ቀንዲሎች የሆኑ የታሪክ መፃሕፍት ለምን ከክብር ቦታቸው እንዲወጡ ተደረገ? ምናቸው ያስፈራል?

በዚህ በኢትዮጵያ የጥናትና የምርምር ተቋም ውስጥ የታላላቅ እምነቶችና ፍልስፍናዎችም አሉ። ገና የክርስትና ሃይማኖት በዓለም ላይ ከመስፋፋቱ በፊት ኢትዮጵያዊያን ፅላተ-ሙሴን ወደ ሀገራቸው አምጥተው ዘመነ ኦሪትን እምነታቸውን ጠብቀው የኖሩባቸው ሙክራቦች እና ታላላቅ ኪነ-ሕንፃዎች ዛሬም ድረስ የጥቁር ሕዝብን ጥንታዊ ማንነት የሚመሰክሩባቸው ሥፍራዎች አሉ። ከኦሪት በኋላም የክርስትና ሃይማኖት በሰፊው የበለፀገባት፣ አፍሪካዊ ለዛ እና ማንነትን ይዞ የተገለፀባት ጥንታዊት ሀገር ናት። መፅሐፍ ቅዱስን እና ኢትዮጵያን የሚተነትኑ Ethiopia in the Bible የሚሉ አያሌ ፅሑፎች ያሉበት ቤተ-መፃህፍት ነው።

በእስልምናውም ሃይማኖት ቢሆን የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ታሪክ፣ ነብዩ መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩባቸው ሠነዶች ታሪኮች እዚህ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ አሉ። ኢትዮጵያን በሁለቱም ሃይማኖቶች የሚገልፁ፣ የሚተነትኑ የሚያስረዱ ታላላቅ ቅዱሳት መፃህፍት ሁሉ እዚህ ቤት ውስጥ ነበሩ። ማነው ውጡ ያላቸው? ማነው ከክብር ቦታቸው ያነሳቸው? እነዚህ መፃሕፍት የማንነታችን የኩራታችን የነፃነታችን መግለጫዎች ናቸው። ማነው እንዲወጡ ያደረገው?

ኢትዮጵያ የትግል እና የነፃነት ምድር እንደሆነች የሚተነትኑ አያሌ መፃሕፍት የተከማቹበት ቦታ ቢኖር ይኸው የጥናትና የምርምር ተቋም ነው። ኢትዮጵያ የነጭ ወራሪ ሲቆጣጠራት በሕይወት እያለሁ ማየት አልፈልግም በማለት ሽጉጡን ጠጥቶ የተሰዋላት አጤ ቴዎድሮስና ታሪኮቹ በዚህ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ አሉ። አጤ ዮሐንስ ኢትዮጵያን አላስደፍርም ብለው ከደርቡሾች ጋር እየተዋጉ አንገታቸውን የሰጡላት ሀገር መሆኗን የሚተነትኑ መፃሕፍትና ሠነዶች ያለፈው ታሪክ ይኸውና እያሉ የሚያወጉን ቦታ ነው። ታዲያ ለምን እንዲወጡ ተደረጉ? የማንነት ማሳያ ሠነዶችን ማን ነው የደፈራቸው? እነ ቴዎድሮስ እነ ዮሐንስ ምን ይሉናል?

እዚያው ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ቁጭ ብዬ መዓት ትዝብቶች ይመጡብኛል። ለዚህች ሀገርና ሕዝብ መስዋዕት የሆኑ የአያሌ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ተሰብስቦ የተቀመጠበት ድንቅ ቦታ ነው። በፋሽት ኢጣሊያ የመርዝ ጋዝ እና ጭስ ያለቁ ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪኮች የተሰነዱበት መዘክር ነው። እነዚህን ያለፈውን ታሪክ የሚያወጉንን ሠነዶች ለምንድን ነው አውጥተን ሌላ ቦታ ያከማቸናቸው። ቢናገሩ ቢመሰክሩ ምን ችግር አለው?

በዚህ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መፃህፍት ውስጥ የሀገሪቱ ሕዝቦች ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ታሪክ የሚገልፁ አያሌ ሠነዶች ተቀምጠውበታል። የብሔረሰቦቿ ቋንቋዎች የተሠነዱበት፣ ባሕሎች ተሰብስበው ተፅፈው የተቀመጡበት፣ አያሌ የሀገሪቱ እና የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች የፃፏቸው የጥናት ወረቀቶች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ልሳን ነው። ይህን የዘጠና ሚሊየን ሕዝብ ታሪክ ማነው እንደፈለገ አንስቶ የፈለገበት ቦታ የሚያስቀምጠው? ማነው ይህን ኃላፊነትና መብት የሰጠው? ማነው ይህን ድርጊት የፈፀመው?

በዚህ ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ካሉት መጣጥፎች አንዳንዶቹ ደግሞ ትዝ አሉኝ። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የፃፏቸው መጡብኝ። ‘How to Destroy Your History the Temple of Yeha, and its Killer Trees የሚለው ጽሁፋቸው How to Lose Your History, How to preserve your culture, How to Remember Your History’ ወዘተ የሚሉት መጣጥፎች ያሉበት ቤት ነው። ታሪክን ባሕልን እንዴት እንደምናጠፋና እንደምናለማ ተፅፏል። ዛሬ ታሪካችንን የምናለማበት ወቅት ነው። ታሪካችንን የምንደብቅበት ጊዜ አይደለም።

በአጠቃላይ ሲታይ በዚህ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የሀገሪቱ ታሪክ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ቀመር፣ የጊዜና የዘመን አቆጣጠር፣ ያሳለፍናቸው ውጣ ውረዶች፣ ስኬቶች፣ ውድቀቶች ሁሉ የተመዘገቡበት እንደ መቅደስ የምንቆጥረው ቤት ነው። ይህንን መቅደሳችንን ማንም ሰው ሊዘጋው ወይም ሊከፍተው አይችልም። ይህን ተቋም ለመምራት የሚመረጥ ወይም የሚሾም ባለስልጣንም ስሜቱ ለነዚህ ታላላቅ ቅርሶች ስሱ /Sensitive/ መሆን አለበት። በአልባሌ ስብሰባዎችና ውይይቶች ተቋሙ መዘጋት የለበትም። ቤቱ ሲዘጋ፣ የሚዘጋው የኢትዮጵያ ልሣን ነው። ኢትዮጵያ እንዳትናገር እንዳትተነፍስ እንደማድረግ ነው። ኦባም ሆኑ ማንም ቢመጣ የኢትዮጵያ ጌጦች ከቦታቸው መነቀል የለባቸውም።

የኢትዮጵያ ምሁራን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። የሀገራቸውን ታሪክና ማንነት የያዙ ሠነዶች እንደ አልባሌ ነገር ከቦታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ ሲጓጓዙ መጠየቅ አለባቸው? ማነው ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ብለው በመጠየቅ የቅርሶቹን ታላቅነት መመስከር አለባቸው። እነሱ ያልመሰከሩ ማን ይመስክርላቸው። ይህ ትራጄዲ እንዳይደገም መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። አሁንም ቢሆን የተሰራው ስራ መጣራት መመርመር አለበት። የወጡት መፃሕፍት ስንት ናቸው? ርዕሳቸው ምንድንነው? መለያቸው ምንድን ነው? ሲመለሱስ የጐደለ የለም ወይ? ኃላፊነቱን የወሰደው ማን ነው? ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው።¾       

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
15784 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us